መልካም የጋብቻ አጋር መምረጥ- ልጆች አስተዳደግ- ክፍል 1

1
6372

በእስልምና አንድን ሰው ማነፅ የሚጀምረው ከቤተሰብ ነው። የሀገር መሠረቱ ቤተሰብ ነውና። ጋብቻ ለተፈጥሮአዊ ጥሪ ምላሽ መስጫ መንገድ ከመሆኑም በላይ የሰውን ልጅ የህይወት ፍላጎት ማስኬጃ፣ ልጆችን ከወላጆች ማገናኛ፣ ማህበረሰቡን ከአደገኛ በሽታዎች መጠበቂያ፣ ከሥነምግባር ውድቀት መታደጊያ መድረክ ነውና እስልምና ትልቅ እውቅና ሰጥቶታል።

አንድ ሙስሊም ኢስላማዊ ቤተሰብ መመሥረት፣ መልካም ዝርያ መተካት፣ አማኝ አላህን ፈሪ ትውልድ ማፍራት ከየት እንደሚጀምር በትክክል ካወቀ ወደፊት የሚጠብቁት የህይወት ሀላፊነቶችም ከወዲሁ ይቃለሉለታል።

ኢስላም የልጆችን አስተዳደግ አስመልክቶ ያስቀመጣቸውን መርሆች በዝርዝር ከማየታችን በፊት ስለ ትዳር በከፊሉ እንመልከት።

ስለ ትዳር /ጋብቻ/ በአጭሩ ሦስት ነገሮች ማለት ይቻላል።

1. ጋብቻ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው።

2. ጋብቻ ማህበራዊ ፋይዳው የላቀ ነው።

3. ጋብቻ መፅዳት እና መጥራት ነው።

ዝርዝሩን በከፊል እንመልከት

1. ጋብቻ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው

አላህ (ሱ.ወ) የሰው ልጆችን የፈጠረው ለአምልኮው ነው። ይህ ሲባል ግን ሰዎች በአምልኮ ሥራዎች ብቻ ተጠምደው ዓለማዊ ህይወታቸውን እንዲዘነጉ አይደለም። እስልምና የሰው ልጆች ለሁለቱም ዓለም ህይወታቸው ዋጋ እንዲሠጡ አስተምሯል አሣስቧልም። የሰው ልጅ በዚህች ዓለም ላይ የተገኘው ምድርን እንዲያለማትና እንዲበዛባትም ጭምር ነው። ስለሆነም የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ ለምንኩስናና ባህታዊነት ቦታ የለውም። ይበልጥ ወደ አላህ ለመቃረብ ታስቦ በአምልኮ ተግባራት ለመነጠል የዚችን ዓለም ጣጣ ሁሉ ርቆ ገዳም መግባትን ዲናችን አጥብቆ ይቃወማል። ምክኒያቱም ይህ ድርጊት ከሥጋና መንፈስ ከተሠራው የሰው ልጅ የተፈጥሮ ባህሪ ጋር የሚሄድ አይደለም። ከስሜቱ ከዝንባሌውና ከውስጣዊ ስሪቱ ጋር በእጅጉ ይጋጫል። በዚህ በኩል እስልምና ከሌሎች ሃይማኖት በተሻለ መልኩ አሣማኝ የሆነ ሚዛናዊ እይታ አለው። ኢማም በይሀቂ ሰዕድ ኢብኑ አቢ ወቃስን በመጥቀስ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

إن الله أبدلنا بالرهبانية الحنيفيّة السمحة

“አላህ ምንኩስናን ገር በሆነችው ቀጥተኛ መንገድ ቀይሮልናል።”

ጦበራኒ እና በይሀቂ ባስተላለፉት ሌላ ዘገባ ደግሞ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ)

من كان موسراً لأن ينكح ثم لم ينكح فليس مني

“ለማግባት ነገሮች ሁሉ ተግራርተውለት ሣለ ያላገባ ሰው ከኔ አይደለም።” ብለዋል።

ከሁለቱ ነቢያዊ ሀዲሦች የምንረዳው የእስልምና ሃይማኖት ከጋብቻ መታቀብን የሚከለክል መሆኑን ነው። በተለይ አንድ ሙስሊም የማግባት አቅሙ እያለው የትዳርንም ጣጣ መወጣት እየቻለ የማያገባ ከሆነ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) “የኔ ወገን የኔ መንገድ ተከታይ አይደለም።” ብለውታል።

የያንዳንዱን የሰው ልጅ ደህንነት ከመጠበቅና ነፍሱንም በተሟላ መልኩ ከማከም አንፃር የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ምርጥ አቋም አላቸው። የአቋማቸውን መነሻ ያስተዋልን እንደሆነ የሰውን ልጅ ማንነትና ምንነት በጥልቀት ከመረዳትና ፍላጎቱንና ዝንባሌውን ጠንቅቆ ከማወቅ የመነጨ መሆኑን እንገነዘባለን። ምልከታቸውም እያንዳንዱ የማህበረሰብ አባል የተፈጠረበትን ወሠን እንዳያልፍና ከአቅሙ በላይ የሆነንና የማይችለውን ነገር ለመሥራት እንዳይነሣሣ የሚያግዘው መሆኑን እንረዳለን። ነቢያዊ አስተምህሮ የሰው ልጅ ያለአንዳች እክል በትክክለኛው መንገድ ላይ አዋጭ እና ቀጥ ያለ ጉዞ ይሄድ ዘንድ ያስችለዋል። መንገዳቸውን አጥብቆ የያዘ አማኝ ሰው ሁሉ ወደፊት በቀደመበት ዘመን ወደኋላ የሚቀርበት ምክኒያት አይኖርም። የሰው ልጆች ጥንካሬን ባገኙበት ጊዜም እሱ የሚደክም አይሆንም። ይህ ነው አላህ (ሱ.ወ) የሰው ልጆችን የፈጠረበት ሁኔታ። ሱረቱ ሩም ቁ- 30 እንመልከት።

فَأَقِمْ وَجْهَكَ لِلدِّينِ حَنِيفًا فِطْرَتَ اللَّهِ الَّتِي فَطَرَ النَّاسَ عَلَيْهَا لَا تَبْدِيلَ لِخَلْقِ اللَّهِ ذَٰلِكَ الدِّينُ الْقَيِّمُ وَلَٰكِنَّ أَكْثَرَ النَّاسِ لَا يَعْلَمُونَ

“ወደ እውነት ተዘንባይ ኾነህም ፊትህን ለሃይማኖት ቀጥ አድርግ። የአላህን ፍጥረት ያችን አላህ ሰዎችን በእርስዋ ላይ የፈጠረባትን (ሃይማኖት ያዟት)። የአላህን ፍጥረት መለወጥ የለም። ይህ ቀጥተኛ ሃይማኖት ነው። ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም።” (አር-ሩም 30፤ 30)

የሰውን ልጅ አፈጣጠር በትክክል አውቆ ፍቱን መድሃኒት ከመጠቆም አንፃር እስቲ የህይወት ሞዴላችን ከሆኑት ከነቢዩ አስተምህሮ የተወሰኑ ምሣሌዎችን እንመልከት..

ኢማም ቡኻሪና ሙስሊም ከአነስ ኢብኑ ማሊክ (ረ.ዐ) እንደዘገቡት፡-

جاء ثلاثة رهط إلى بيوت أزواج النبي صلى الله عليه وسلم يسألون عن عبادته، فلما أخبروا كأنهم تقالوها (وجدوها قليلة) فقالوا: وأين نحن من النبي صلى الله عليه وسلم، قد غفر له ما تقدم من ذنبه وما تأخر، قال أحدهم: أما أنا فإني أصلي الليل أبداً، وقال آخر: أنا أصوم الدهر ولا أفطر، وقال آخر: أنا أعتزل النساء فلا أتزوج أبداً. فجاء رسول الله صلى الله عليه وسلم فقال: أنتم الذين قلتم كذا وكذا؟ أما والله إني أخشاكم لله، وأتقاكم له، لكني أصوم وأفطر، وأصلي وأرقد، وأتزوج النساء، فمن رغب عن سنتي فليس مني.

ሦስት ሰዎች ወደ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሚስቶች ቤቶች መጡና ስለ አምልኮአቸው ሁኔታ ጠየቁ። በተነገራቸውም ጊዜ ሁኔታውን ለማሣነስ ሞከሩ። እንዲህም አሉ። ‘ታዲያ እኛ ከነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) አንፃር የት ነን። በርግጥ እርሣቸው የቀደመውም ሆነ የቀረው ሀጢዓታቸው ሁሉ ተምሮላቸዋል።’ ካሉ በኋላ አንደኛቸው ‘እኔ እድሜዬን በሙሉ ለሊቱን እሰግዳለሁ።’ አለ። ሁለተኛው ሰው ‘እድሜ ልኬን እፆማለሁ። ፈፅሞ አላፈጥርም።’ አለ። ሦስተኛው ደግሞ ‘እኔ ከሴቶች እርቃለሁ። ፈፅሞ አላገባም።’ አለ። በዚህ ሁኔታ ላይ ሳሉ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) መጡ። ‘እናንተ ናችሁ ወይ እንዲህ እንዲያ ያላችሁት?’ በማለት ጠየቋቸው። በማስከተልም ‘ወላሂ እኔ ከናንተ ይበልጥ አላህን ፈሪ እና ጠንቃቃ ነኝ። ነገርግን እፆማለሁ አፈጥራለሁ፤ እሰግዳለሁ እተኛለሁ፤ ሴቶችንም አገባለሁ። ከኔ መንገድ ያፈነገጠ ከኔ አይደለም።’ አሏቸው።”

ከሀዲሦቹ መረዳት የምንችለው ነገር ጋብቻ በኢስላም ውስጥ የሰው ልጅ የተፈጠረለት ክቡር ማረፊያ መሆኑን ነው። አንድ ሙስሊም ለዚህ ተፈጥሮአዊ ጥያቄ ምላሽ የሠጠ እንደሆነ መንከባከብና ማነፅ ከሚገባው ቤተሰብ አንፃር ትልቅ የአደራ ሀላፊነት ላይ ይወድቃል።

2. ጋብቻ ማህበራዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው

ጋብቻ ሁለገብ የሆነ ጥቅም እና ማህበራዊ ፋይዳ አለው። ዋንኞቹን እንመልከት..

1ኛ.  የሰው ልጅን መጠበቅ

ጋብቻ የሰው ልጅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከምድር ላይ እንዳይጠፋ አላህ (ሱ.ወ) በምድር ላይ ያኖረው መጠበቂያ ፕሮጀክት ነው። በጋብቻ የሰው ልጅ ዝርያ ወደፊት ይቀጥላል። የትውልድ ሠንሰለቱም ይበዛል ይቀጣጠላል። የሰው ልጅም ሆነ የፍጥረት ሁሉ የፍፃሜ ቀን እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ። ያለ ጋብቻ ትውልድ ማፍራትም ሆነ መብዛት አይታሰብም። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

وَاللَّهُ جَعَلَ لَكُم مِّنْ أَنفُسِكُمْ أَزْوَاجًا وَجَعَلَ لَكُم مِّنْ أَزْوَاجِكُم بَنِينَ وَحَفَدَةً

“አላህም ከነፍሶቻችሁ (ከጎሶቻችሁ) ለእናንተ ሚስቶችን አደረገ። ለእናንተም ከሚስቶቻችሁ ወንዶች ልጆችን፣ የልጅ ልጆችንም አደረገላችሁ።” (አን-ነህል 16፤ 72)

يَا أَيُّهَا النَّاسُ اتَّقُوا رَبَّكُمُ الَّذِي خَلَقَكُم مِّن نَّفْسٍ وَاحِدَةٍ وَخَلَقَ مِنْهَا زَوْجَهَا وَبَثَّ مِنْهُمَا رِجَالًا كَثِيرًا وَنِسَاءً وَاتَّقُوا اللَّهَ الَّذِي تَسَاءَلُونَ بِهِ وَالْأَرْحَامَ إِنَّ اللَّهَ كَانَ عَلَيْكُمْ رَقِيبًا

“እናንተ ሰዎች ሆይ! ያንን ከአንዲት ነፍስ (ከአዳም) የፈጠራችሁን ከእርስዋም መቀናጆዋን (ሔዋንን) የፈጠረውን ከእነርሱም ብዙ ወንዶችንና ሴቶች የበተነውን ጌታችሁን ፍሩ። ያንንም በርሱ የምትጠያየቁበትን አላህንና ዝምድናዎችንም (ከመቁረጥ) ተጠንቀቁ። አላህ በእናንተ ላይ ተጠባባቂ ነውና።” (ኒሣእ 1፤ 1)

2ኛ. ዝምድናን መጠበቅ ፤ ዝርያን ማገናኘት

በዛሬዋ በዓለማችን ላይ አባት አልባ ልጆች ተበራክተዋል። ይህም የሆነው ከህጋዊ ጋብቻ ውጭ የሚወለዱ ልጆች በመብዛታቸው ነው። በርግጥም ይህ ሁኔታ በግለሰብ ስነልቦና ላይ የሚያሣድረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። የማህበረሰቡን ማህበራዊ ህይወት መስተጋብር ቀውስ ውስጥ ይከታል። ለልጆች ባህሪ መበላሸትም ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። የሰው ልጆች አላህ (ሱ.ወ) ባስቀመጠው የጋብቻ መንገድ ቢጓዙ የሚወለዱ ልጆች በአባታቸው ይኩራራሉ። እናት አባትም ሆነ ዘመድ ስላላቸው ተረጋግተው ይኖራሉ። ክብርና ሞገስም ያገኛሉ።

3ኛ. ማህበረሰቡን ከመጥፎ ባህሪዎች መጠበቅ

በጋብቻ ምክኒያት ማህበረሰቡ ከእኩይ ባህሪዎች ይጠበቃል። የሰዎች የርስበርስ ግንኙነትም የተሻለ ዋስትና ያገኛል። ሀላል ነገርን መሠረት ያደረገ የሰዎች ለሰዎች ግንኙነት ለማህበረሰቡ ሞገስን ያጎናፅፋል፤ ውበትን ይጨምራል፤ በረከትና ረድኤትን ያመጣል፤ ደህንነትና ሰላምን ያስገኛል። በግለሰብም ሆነ በቡድን ደረጃ ኢስላማዊ መልእክትን ማድረስና አላህ (ሱ.ወ) ባዘዘው መልኩ ሀላፊነትን መሸከም የሚችል ሥርዓት ያለው የምርጥ ሥነምግባር ባለቤት የሆነ ማህበረሰብ መፍጠር የሚቻለውም በጥሩ ጋብቻ ነው። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የትዳርን ጥበብና ሚስጢር ባማረ መልኩ እንዲህ በማለት ተናግረውታል።

يا معشر الشباب: من استطاع منكم الباءة  فليتزوج، فإنه أغض للبصر، وأحصن للفرج، فمن لم يستطع فعليه بالصوم فإنه له وجاء

“እናንተ ወጣቶች ሆይ! ከናንተ መካከል የትዳርን ጣጣ የቻለ ሰው ያግባ። ጋብቻ ዐይንን ለመስበር ብልትንም ለመጠበቅ ይረዳልና። ያልቻለ ደግሞ ይፁም። ፆም ለሱ ጋሻ ነውና።”

4ኛ. ማህበረሰቡን ከአደገኛ በሽታዎች መታደግ

ጋብቻ በሀራም ግንኙነት በተለይም በዝሙት አማካይነት ከሚመጡ አደገኛ በሽታዎች ማህበረሰቡን ይጠብቃል። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ኤድስን የመሣሰሉ ከግለሰብ አልፈው ለልጅ ልጅ የሚተላለፉ በሽታዎች የዓለምን ማህበረሰብ በእጅጉ እየተፋታተኑት ነው። በኢኮኖሚውም ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያስከተሉ ነው። ንፁህ ጋብቻ ማህበረሰቡን ከነኚህ አደገኛ መቅሠፍቶች ለመጠበቅ ዓይነተኛ ዋስትና ነው።

5ኛ. ጋብቻ የነፍስም ሆነ የመንፈስ መርጊያ ነው

ጋብቻ በተጋቢዎች መካከል የመዋደድ እና የመተዛዘን መንፈስን ከፍ ማድረጉ ሌላው ጥቅሙ ነው። ባል ከሥራ መልስ ደክሞ ወደቤቱ ሲመለስ ከሚስቱና ልጆቹ ጋር ሲሰበሰብ ቀን ሲያጨናንቀው የዋለበትን ነገር ሁሉ ይረሣል። ሚስትም ቀኑን ሙሉ ጠፍቶባት የዋለውን የህይወት አጋሯን ባሏን ስታገኝ መንፈሷ ይታደሣል። በዚህ መልኩ አንዱ በሌላኛው ይጠለላል.. ይጠነክራል። አንዱ ወደሌላኛው ይጠጋል። ደስታንም ያገኛል። ይህንን ሁኔታ አላህ (ሱ.ወ) በሚያስደንቅ መልኩ እንዲህ በማለት ገልፆታል።

وَمِنْ آيَاتِهِ أَنْ خَلَقَ لَكُم مِّنْ أَنفُسِكُمْ أَزْوَاجًا لِّتَسْكُنُوا إِلَيْهَا وَجَعَلَ بَيْنَكُم مَّوَدَّةً وَرَحْمَةً إِنَّ فِي ذَٰلِكَ لَآيَاتٍ لِّقَوْمٍ يَتَفَكَّرُونَ

“ለእናንተም ከነፍሶቻችሁ (ከጎሶቻችሁ) ሚስቶችን ወደእነርሱ ትረኩ ዘንድ መፍጠሩ፣ በመካከላችሁም ፍቅርንና እዝነትን ማድረጉ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው። በዚህ ውስጥ ለሚያስተውሉ ሕዝቦች ተዓምራቶች አልሉ።” (አር-ሩም 30፤ 31)

6ኛ. ቤተሰብን በመገንባትና ልጆችን በማሣደጉ ረገድ የባልና ሚስት መተጋገዝ

በጋብቻ አማካይነት ባልና ሚስት ቤተሰብን በመገንባቱና ሀላፊነትን በመሸከም የመተጋገዝ እድል ያገኛሉ። ሰው ሆኖ በምሉእነት የተፈጠረ የለምና አንዱ የሌላኛውን ድካም ለመጠገን ክፍተቱንም ለመሙላት ምክኒያት ይሆናሉ። ሴት ልጅ አላህ ያገራላትንና ከሷ ባህሪ ጋር የሚሄዱትን የቤት ውስጥ ሥራዎች ልጆች ማሣደግንና የመሣሰሉትን ትሠራለች። በዚህም ትላልቅ አባቶችንና እናቶችን በማብቃቱ ረገድ ሚናዋን ትወጣለች።

ባልም የተፈጠረለትንና ከርሱ ጋር የሚሄዱትን የጉልበት ሥራዎች ቀኑን ሙሉ በመሮጥና በመድከም ሁለገብ በሆነ መልኩ የቤተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅ ሲል ከባባድ ፈተናዎችን ጭምር ይጋፈጣል። በዚህ መልኩ በመተጋገዝ ባልና ሚስት የዚህችን ዓለም ፈተናዎች በማለፍ ወደ ከፍተኛ ውጤት ለመድረስ ይታትራሉ። መላውን ቤተሰባቸውንም በመልካም ነገራት ብቻ የተሞላውን የእስልምናን መንፈስ ያላብሳሉ።

7ኛ. የአባትነት እና የእናትነት እዝነት መጨመር

በጋብቻ አማካይነት እናት አባት መተሣሰባቸውና መተዛዘናቸው ከፍ ይላል። በመካከላቸው በተገኙ ልጆች አማካይነት ከቀልባቸው ጥሩ ስሜትና አመለካከት ይፈልቃል። ይህም ስሜት ለልጆቻቸው ይበልጥ እንዲያዝኑና እንዲንከባከቡ ለጥሩ እድገታቸው ዘወትር በተሻለ ሁኔታ እንዲለፉ ያደርጋቸዋል። እነኚህ ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ከጋብቻ የመነጩ የተወሰኑ ትሩፋቶች ናቸው። ጋብቻ ለማህበረሰቡ ያለው ፋይዳ በርግጥ ከዚህም በላይ ነው።

የእስልምና ሃይማኖት በጋብቻ ያዛል። ወጣቶች እንዲያገቡም ያነሣሣል፤ ይገፋፋል። የአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

ما استفاد المؤمن بعد تقوى الله عز وجل خيراً له من زوجة صالحة، إن أمرها أطاعته، وإن نظر إليها سرته، وإن أقسم عليها أبرّته، وإن غاب عنها حفظته في نفسها وماله

“አንድ አማኝ ከአላህ ፍራቻ ቀጥሎ ከመልካም ሚስት የሚጠቀመውን ያህል ከሌላ አይጠቀምም። ሲያዛት ትታዘዘዋለች፤ ወደርሷ ሲመለከት ደስ ትለዋለች፣ እንደማታሣፍረው አውቆ በርሷ ቢምል አታሣፍረውም መሃላውን ታፀናለታለች፤ ከርሷ ቢርቅ ነፍሷንና ገንዘቡን ትጠብቅለታለች።” (ኢብኑ ማጀህ ዘግበውታል)

በሌላም ሀዲሣቸው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል

الدنيا متاع وخير متاعها المرأة الصالحة

“ይህች የቅርቢቱ ዓለም መጣቀሚያ ናት። ከመጣቀሚያዎቿ ሁሉ በላጩ መልካም ሚስት ናት።” (ሙስሊም ዘግበውታል)

3. ጋብቻ መፅዳትና መጥራት ነው

ሀላል ነገር ንፁህ ነው። ጣእሙም ለየት ያለ ነው። እርካታውም የትየሌሌ ነው። ኢስላም ሀላል ነገርን ንፁህ እና ፅዱ ሀራምን ደግሞ መጥፎና ቆሻሻ አድርጎ ነው የሚመለከተው። ጋብቻ መፅዳት ሲሆን ዝሙት ደግሞ መቆሸሽ ነው። ዲናችን ላቅ ባለው መንገዱና ህግጋቱ ለጋብቻ በሚጠይቀው ወንድና በምትገባው ሴት መካከል ምርጥ የሆነ መመሪያና መስፈርት አስቀምጧል። ሰዎች በዚህ መመሪያ ቢመሩና በመንገዱ ቢጓዙ ትዳርም እጅግ የመግባባትና የስኬት መድረክ በሆነ ነበር። ከወንድና ሴት ልጅ የተገነቡ ቤተሰቦችም እጅግ በተመቻቸ እምነት ሰላማዊ በሆነ አካልና አዕምሮ አንዲሁም ነፍሦች በተረጋጉና በፀዱ ነበር።

1 COMMENT

  1. ማአህ ተባረከሏህ አሏህ ከይርስራችሁን ይክፈላችሁ
    በዱኒካ ስኬትን በአኺራ ጀነትን ይወፍቃችሁ ኢንሸአላህ በጣም ምርጥ ትምህርት ነው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here