መልካም የጋብቻ አጋር መምረጥ – ልጆች አስተዳደግ- ክፍል 2

17
10594

የትዳር አጋርን ለመምረጥ መስፈርቶቹንና መመሪያዎቹን እንመልከት

1. ሃይማኖትን መሠረት ባደረገ መልኩ መምረጥ

ሃይማኖት ስንል ለስም ብቻ ሙስሊም መሆንን ሣይሆን እውነተኛ በሆነ መልኩ የእስልምና ሃይማኖትን መረዳት፤ ምርጥ አስተምህሮዎቹንና የመጠቁ ሥርዓቶቹን ወደ ተግባር መተርጎም ማለት ነው። ከዚህም በተጨማሪ በእስልምና አስተምህሮዎችና መመሪያዎች ላይ መዘውተርን ዘላለማዊ የሆኑና ጊዜና ዘመን የማይሽራቸውን መርሆዎቹን መከተልን ያጠቃልላል። ለጋብቻ የሚፈላለጉ ወንድና ሴት በዚህ የግንዛቤ፣ የተግባርና በሃይማኖት የመፅናት ደረጃ ላይ የደረሱ እንደሆነ የባህሪ መንሸራተትና የሥነምግባር መበላሸት አያጋጥማቸውም። ከእስልምና የመራቁ ጉዳይም የማይታሰብ ነው የሚሆነው።

ሰዎችን ለማወቅ በተለይ ለጋብቻ ጠያቂ የሆኑ ወንዶችን ማንነት ለመረዳት ፍትሃዊው ኸሊፋ ዑመር ኢብኑ አልኸጧብ የተጠቀሙትን ይህን ቃለምልልስ እንመልከት።

አንድ ሰው ለሌላኛው ለመመስከር ወደርሳቸው ዘንድ መጣ።

እርሣቸውም “ይህን ሰው ታውቀዋለህን?” አሉት።

ሰውየውም “አዎን” አለ።

ዑመርም “ጎረቤቱ ሆነህ መግቢያና መውጫውን ታውቃለህን?” አሉት።

“አይ አይደለም” አላቸው።

“የሰው ልጅ ይፈተንበታልና መንገድ አብረሀው ወጥተህ ምርጥ ሥነምግባር አስተውለህበታልን?” አሉት።

“የለም አልሄድኩም።” አላቸው።

“አንድ ሰው ለአላህ ላይ ያለው ፍራቻ ሊገመገም የሚችለው በገንዘብ ነውና በገንዘብ ጉዳይ ላይ እንዴት ነው ታውቀዋለህን?”

“አላውቀውም።” አላቸው።

ዑመርም ጮሁበትና “እንግዲያውስ አንተ የምታውቀው በመስጊድ ውስጥ ቆሞ አሊያም ተቀምጦ ሲሰግድ ጭንቅላቱን አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ ሲያደርግ አይተሀው ነው።” አሉት።

ሰውዬውም “አዎን” አለ።

ዑመርም “እንግዲያውስ አንተ አታውቀውምና በል ሂድ።” ወደ ባለጉዳዩ ሰውዬ በመዞርም “አንተን የሚያውቅ ሰው ይዘህልኝ ና።” አሉት።

ዑመር በርግጥም የሰውየው ውጫዊ ገፅታ በማየት ብቻ ታላቁን ሀላፊነት ጋብቻን ሊያፀድቁለት አልፈለጉም። የአንድ ሰው እውነተኛ ማንነት የሚለካው ሃይማኖቱና በባህሪው ነውና ያን የሚያስረዳቸውን ሰው ነበር የፈለጉት።

ይህም አጋጣሚ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም

إن الله لا ينظر إلى صورآم وأموالكم وإنما ينظر إلى قلوبكم وأعمالكم..

“አላህ ወደናንተ ቅርፅም ሆነ ሀብት ንብረት አይመለከትም። ነገርግን ወደ ቀልቦቻችሁ እና ሥራዎቻችሁ ነው የሚመለከተው።”የሚለውን ሀዲሣቸውን ትርጉም የያዘ ነው።

የአላህ ነቢይ (ሰ.ዐ.ወ) ለትዳር ፈላጊዎች ሃይማኖትን ዋና መስፈርት ያደረጉት ሃይማኖተኛ የሆኑ ባልና ሚስት አንዳቸው የሌላኛውን መብትና ግዴታ በማወቁና በመወጣቱ ረገድ የቀረቡ በመሆናቸው ነው። ይህም ቤተሰባቸውን ኢስላም ባለው መልኩ ለመምራትና ለማስተዳደር ያግዛቸዋል።

ቡኻሪ እና ሙስሊም አንዲሁም ሌሎችም አቡ ሁረይራን በመጠቀስ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል

تنكح المرأة لأربع: لمالها ولحسبها ولجمالها ولدينها، فاظفر بذات الدين تربت يداك.

“ሴት ልጅ ለአራት ነገሮች ትገባለች። ለሀብት ንብረቷ፣ ለክብሯ፣ ለቁንጅናዋ እና ለሃይማኖቷ። አመድ አፋሽ ሁንና ያችን ሃይማኖት ያላትን ምረጥ።”

ጦበራኒም አነስ ኢብኑ ማሊክን በመጥቀስ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል

من تزوج امرأة لعزها لم يزده الله إلا ذُلاًّ، ومن تزوجها لمالها لم يزده الله إلا فقراً، ومن تزوجها لحسبها لم يزده الله إلا دناءة، ومن تزوج امرأة لم يرد بها إلا أن يغضَّ بصره، ويحصِّن فرجه، أو يصل رحمه، بارك الله له فيها، وبارك لها فيه

“ለታላቅነቷ ብቻ ብሎ አንዲትን ሴት ያገባ አላህ ውርደትን እንጂ ሌላን አይጨምርለትም። ገንዘቧን ብሎ ያገባት አላህ ድህነትን እንጂ አይጨምርለትም። ለክብሯ ብሎ ያገባት አላህ ቅሌትን እንጂ አይጨምርለትም። ነገርግን ዐይኑን ለመስበር፣ ብልቱን ለመጠበቅና ዝምድናን ለመጠበቅ ብሎ አንዲትን ሴት ያገባ አላህ እሷን ለሱ እሱንም ለሷ ይባርካል።”

በሌላ በኩል ደግሞ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) የምትገባዋ ሴት ወኪሎች ለልጃቸው የሃይማኖት እና የሥነምግባር ባላቤት የሆነውን ሰው እንዲመርጡላት አመላክተዋል። ይህም የወደፊቱን የሙስሊም ቤተሰብ ጤነኛና ጠንካራ በሆነ መልኩ ለመገንባት ያታለመ ነው።

ቱርሙዚ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ

إذا جاءكم من ترضون دينه وخلقه فزوّجوه، إلا تفعلوا تكن فتنة في الأرض، وفساد عريض

“ሃይማኖቱን እና ሥነምግባሩን የወደዳችሁት ሰው ወደናንተ ከመጣ (ልጃችሁን ለትዳር ከጠየቀ) ዳሩት። ይህ ካልሆነ በምድር ላይ ፈተና እና ሰፊ ጥፋት ይከሠታል።”

በርግጥም አንዲት ሴት ልጅ ስለ እምነቱ ሆነ ስለ ልጆቹ አስተዳደግም ግድ ለሌለው ስለኢስላማዊ ህይወትም ለማይጨነቅ ሰው መዳርን የመሠለ ትልቅ ፈተና የለም። ውጤቱም አደገኛ ስለመሆኑ ሣይታለም የተፈታ ነው። ዛሬ በየአካባቢው በርካታ ነገሮችን መታዘብ እንችላለን። ዲን በሌለው ቤት ውስጥ የሚያድጉ ልጆች ተዓምር ካልተፈጠረ በቀር በጥሩ ስነምግባርና የአላህ ፍራቻ ላይ ያድጋሉ ተብሎ አይታሰብም። የባልም ሆነ የሚስት ምርጫችን መስፈርቱ ሃይማኖትና ጥሩ ሥነምግባር የሆነ እንደሆነ ባልና ሚስት በእስልምና ጥላ ሥር የተሟላ ደስታን ያገኛሉ። ይህም ሁኔታ ለቤተሰብ ክብርን፣ ለማህበረሰብ የተሟላ ደህንነትን ለሀገር ደግሞ እድገትና ብልፅግናን ያስገኛል።

2. ክብርን መስፈርት አድርጎ መምረጥ

ኢስላም ካስቀመጣቸው ሌሎች መስፈርቶች መካከል ሌላኛው ባል አሊያም ሚስት ከተከበረና በሃይማኖተኝነቱ እንዲሁም በግብረገብነቱ ከሚታወቅ ቤተሰብ ቢሆኑ የተሻለ መሆኑን ነው። በስብእና፣ በሃይማኖትም ሆነ በመልካም ባህሪ “ትልቅና የተከበረ” ተብሎ ከሚታወቅ ቤተሰብ ማግባት በዲንም ሆነ በዱኒያ ጥቅሙ የጎላ ነው። ከመልካም ቤተሰብ መጥፎ ነገር ሊወጣ አይችልም ተብሎ ይታሰባልና። ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ) ይህንኑ ተናግረዋል

الناس معادن في الخير والشر، خيارهم في الجاهلية خيارهم في الإسلام، إذا فقهوا

“ሰዎች በመልካምና መጥፎ ይበላለጣሉ። በጃሂሊያ /መሃይምነት ዘመን/ በላጭ የሆኑት እስልምና ውስጥ ገብተው እውቀትን ያገኙ እንደሆነም በላጭ ናቸው።”

በሌላ ደከም ባለ ዘገባ ደግሞ ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ፊት በማየት እንዳንታለል አሣስበዋል።

إياكم وخضراء الدِّمَن، قالوا: وما خضراء. الدمن يا رسول الله؟ قال: المرأة الحسناء في المنبت السوء

“አደራችሁን ኸድራእ አድ ደምን /ደመ ግቡ የሆነችዋን/ ተጠንቀቁ።” አሉ። ሰዎች “ምንድነው እሱ የአላህ መልእክተኛ ሆይ!” በማለት ጠየቋቸው። እርሣቸውም “በመጥፎ ቦታ ላይ የበቀለች ቆንጆ ሴት ናት።” አሏቸው።” (ዳረልቁጥኒ ዘግበውታል )

ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) በዚህ መልኩ ነበር ከልጅ በፊት እናት መረጣ ላይ እንድንጨነቅና እንድንጠበብ የመከሩን። ልጅ ዘር ነውና ከመዝራታችን በፊት የዘር መዝሪያችንን በጥንቃቄ እንድንመርጥ አሣስበውናል። በዚሁ መነሻነትም ይመስላል ዑስማን ኢብኑ አልዓሲ አስ-ሰቀፊ እንዲህ በማለት ለልጆቹ ምክር ሲሠጥ የተደመጠው

يا بنيّ ! الناكح مغترس، فلينظر امرؤ حيث يضع غرسه، والعِرْق السوء قَلَّمَا يُنجب، فتخيروا ولو بعد حين

“ልጆቼ ሆይ! ጋብቻ አዝመራ ነው። አንድ ሰው ተክሉን የት እንደሚተክል ያስተውል። መጥፎ ዘር ፍሬ አያፈራም። ጊዜ የሚወስድባችሁም ቢሆን ጥሩ ነገር ምረጡ።”

ታላቁ ኸሊፋ ዑመር ኢብኑ አልኸጧብ የሆኑ ልጆች አንድ ልጅ በአባቱ ላይ ያለውን መብት በጠየቁት ጊዜ

“እናቱን መምረጥ፣ መልካም ሥም ማውጣት፣ ቁርዓንን ማስተማር” በማለት መልሰውላዋቸል።

የዘመኑ ተመራማሪዎች ህፃን ልጅ ከውልደቱ ጊዜ ጀምሮ የወላጆቹን አካላዊ እና አዕምሮአዊ ባህሪ እንደሚወርስ አረጋግጠዋል። አንድ ልጅ ከወላጆቹ በመውረስም ሆነ በሃይማኖቱ አስተምህሮ ምርጥ እሴቶችን ሰብስቦ የሚያድግ ከሆነ በሥነምግባርም ሆነ በሃይማኖቱ እውቀት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል። በአላህ ፍራቻ የታነፀ፤ ተግባቢና ሰውን አክባሪ ከመሆኑም በላይ ለሌሎችም መልካም አርዓያ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ትዳር ፈላጊዎች ለራሣቸው ጊዜያዊ ስሜት ሣያደሉ ለኢስላም በማሰብ በዚህም ሆነ በዚያኛው ዓለም የምታዋጣቸውን ተጣማሪ ከመምረጥ አንፃር በእጅጉ ማሰብ ይኖርባቸዋል።

3. በጋብቻ መራቅ

ሌላው እስልምና ከሚያመለክትባቸው ነገሮች መካከል የስጋ ዘመድ ከሆነችው ይልቅ እራቅ ያለችውን መምረጡ ላይ ነው። ይህም አካሄድ ለሚወለደው ልጅ በማሰብ በደም ሊወራረሱ ከሚችሉ በሽታዎችም ሆነ ሌሎች ነገሮች ቀጣዩን ትውልድ ለመጠበቅ ያስችላል። ከዚህም በተጨማሪ ባዳ የሆነችን ሴት ማግባት በሙስሊሞች መካከል ለመተዋወቅና ማህበራዊ ትስስርን ለማምጣት የጎላ ፋይዳ አለው። አንድነታቸውንም ያጠናክራል። ባህሪም ሆነ አካላዊ ገፅታ ተወራራሽ ነውና በዚህኛው ቤተዘመድ ውስጥ የሚታየው ድክመትም ሆነ ጉድለት ባዕድ የሆኑትን በማግባት የሚሸፈንበት ሁኔታ ይኖራል። ልጅ ደካማ ሆኖ እንዳይወለድ፣ የወላጆች ድክመትም ሆነ በሽታዎች ለሚወለደው ልጅ እንዳይተርፍ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከሥጋ ዘመድ ጋር የሚደረግ ጋብቻን እንድንጠነቀቅ መክረዋል ።

በዚህ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶችም ቢሆኑ የሥጋ ዘመድ ጋብቻ በአካላዊም ሆነ አዕምሮአዊ ሁኔታ ላይ ድክመት እንደሚያመጣና ለልጅም መጥፎ ባህሪን ሊያወርስ እንደሚችል ያረጋግጣሉ። ይህንን እውነታ ከ14 ምእተ አመታት በፊት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) አረጋግጠውታል። ይህም አላህ (ሱ.ወ) ከሠጣቸው ተዓምራት መካከል የሚመደብ ነው።

لا تنكحوا القرابة فإن الولد يخلق ضاوياً

“የቅርብ ዘመድ አታግቡ- ደካማ ልጅ ይፈጠራልና።”

4. ልጃገረዶችን ማስበለጥ

ሌላውና ኢስላም ከሚያመለክትባቸው ነገሮች ነጥቦች ተጠቃሽ የሚሆነው ጋብቻ ሲታሰብ ልጃገረድ የሆነችውን ካልሆነችው ማስቀደም ነው። ይህም የሆነበት ምክኒያትና ጥቅም ስላለው ነው። ልጃገረድን ማግባት የቤተሰብን ጤናማ ግንኙነት ከሚያደፈርሱ ነገሮች ይጠብቃል። አላስፈላጊ አተካራዎችና ግጭቶችን ለማስወገድ ጥላቻን ለመቀነስ ጥቅም አለው። ሰው ሁሌም ቢሆን የመጀመሪያውን ይወዳል። የመጀመሪያው ካልሆነች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ቀልቧ ሊሸፍት ይችላል ብሎ ሊያስብና ሊጠራጠር እንዲሁም በሷም በኩል በአንዳንድ ነገሮች ላይ ከቀደመው ህይወቷ ጋር የማመዛዘን አጋጣሚ ሊኖር ስለሚችል ትዳሩ ነፋስ ይገባዋል ተብሎ ይፈራል።

እናታችን ዓኢሻ የምታወራልን ይህ ጣፋጭ ቡኻሪ የዘገቡት ሀዲስ ደግሞ ነገሮችን ይበልጥ ይገልፅልናል። ስለዚህ ጉዳይ ለነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ስታወጋ እንዲህ በማለት ጠየቀቻቸው

“ወደ አንድ ሸለቆ ወረድክ እንበል። አንድ ከላይዋ ላይ የተበላና ሌላ ምንም ያልተበላባት የፍሬ ዛፍ ቢያጋጥምህ በየትኛው ዛፍ ሥር ነው ግመልህን ማሣረፍ የምትወደው” አለቻቸው።

የአላህ መልእክተኛም (ሰ.ዐ.ወ) “ምንም ካልተበላባት” አሏት።

እርሷም “እሷ ማለት እኔ ነኝ።” አለቻቸው።

ዓኢሻ (ረ.ዐ) ይህን ያለችው ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከሚስቶቻቸው መካከል ያገቡት ብቸኛዋ ልጃገረድ እርሷ ብቻ በመሆኗ ከሌሎቹ የምትበልጥ መሆኑን ለማስረዳት ነው። ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ) በዚሁ አመላክተዋል። እንዲህ በማለት

عليكم بالأبكار فإنهن أعذب أفواهاً، وأنتق أرحاماً، وأقل خِبّاً، وأرضى باليسير

“አደራችሁን ልጃገረድ አግቡ። እነርሱ አንደበታቸው ጣፋጭ፣ ማህፀናቸው ንፁህ፣ ቶሎ የማያረጁ፣ በትንሽ ነገርም የሚወዱ ናቸውና።”(ኢብኑ ማጃህ እና በይሀቂ ዘግበውታል)

በአንድ ወቅት የአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ከዛት አር ሪቃዕ ዘመቻ በመመለስ ላይ ሣሉ ከጃቢር ጋር እያወጉ መጡ።

“ጃቢር ሆይ! አግብተሃልን?” አሉት።

እርሱም “አዎን።” አላቸው።

“ልጃገረድ ወይንስ ሴት ነው ያገባሀው?” አሉት።

“ሴት ነው ያገባሁት።” አላቸው።

“እንድታጫውትህና እንድታጫውታት ለምን ልጃገረድ አላገባህም?” አሉት።

ጃቢርም “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! አባቴ በኡሁድ ዘመቻ ቀን ሲሞት ሰባት ሴት ልጆችን ነው ትቶ ያለፈው። ለዚህም ነው ሁሉ ነገር የምትሰበስብልኝ ሴት ያገባሁት። ትሰበስብልኛለች ትንከባከባቸዋለችም።” አላቸው። ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ) “ኢንሻአላህ ጥሩ አድርገሃል።” አሉት። (ቡኻሪ፣ ሙስሊምና ሌሎችም ዘግበውታል)

ከዚህ ሀዲስ የምንረዳው ሌላው አንዳንድ ጊዜ ከልጃገረድ ይልቅ ሴት ልጅ የምትመረጥበት ጊዜ መኖሩን ነው። ከህይወት ልምዷ ብዙ ነገር ይገኛልና።

5. የምትወልደዋን መምረጥ

ሌላው ኢስላም ለትዳር ከሚያመላክትባቸው ነገሮች መካከል ደግሞ ወላድ የሆነችውን ሴት ማግባት ነው። ስናገባ አንዲት ሴት ከእርግዝናና ከወሊድ ከሚከለክሉ በሽታዎችና ነገሮች ነፃ መሆኗን በማስመርመርም ሆነ በሌላ ማለትም የእናቷን የዘመዶቿን የኋላ ታሪክ በማወቅ ያገቡ እህቶችም ካሏት ወላድ ስለመሆናቸው በማጥናት ሊሆን ይችላል። ወላጆቿም ሆነ እህቶቿና የቅርብ ዘመዶቿ ወላድ ከሆኑ እሷም ትሆነለች ወደሚለው ድምዳሜ ሊደረስ ይቻላል።

ወላድ ሴትን የማግባቱ ሚስጢር የነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) ኡመት ከማብዛት ጋር የተያያዘ ነው። ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ህዝባቸው በዝቶ በእለተ ትንሣኤ ከሌሎች ነቢያት ጋር ለመፎካከር ያልማሉ። በመሆኑም የርሣቸውን ምኞት ለማሳካት ወላድ የሆነችን ሴት ማግባት አስፈላጊ ነው።

በአንድ ወቅት አንድ ሰው ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ መጣና

يا رسول الله إني أحببت امرأة ذات حسب ومنصب ومال إلا أنها لا تلد، أفأتزوجها؟ فنهاه، ثم أتاه الثانية فقال له مثل ذلك، ثم أتاه الثالثة فقال له عليه الصلاة والسلام: ” تزوجوا الولود الودود فإني مكاثر بكم الأمم”

“የአላህ መልእክተኛ ሆይ! እኔ ከተከበረ ቤተሰብ የሆነች ሴት ወደድኩኝ። ነገር ግን መውለድ አትችልም። ላግባት ወይ? አላቸው። ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዳያገባ ከለከሉት። ሰውየው ሌላ ጊዜ በመምጣት ደግሞ ጠየቃቸው። አሁንም ከለከሉት። ለሦስተኛ ጊዜ መጥቶ በጠየቃቸው ጊዜ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ “ወላድ እና ተወዳጅ የሆኑ ሴቶችን አግቡ። እኔ በናንተ አማካይነት ህዝቤን አበዛለሁና”(አቡ ዳውድ ነሣኢ እና ሃኪም ዘግበውታል።)

ይህ የኢስላማዊ የጋብቻ መርሆ ነው። በእስልምና አንድን ሰው ማነፅ የሚጀምረው ከቤተሰብ ነው። የሀገር መሠረቱ ቤተሰብ ነውና። ጋብቻ ለተፈጥሮአዊ ጥሪ ምላሽ መስጫ መንገድ ከመሆኑም በላይ የሰውን ልጅ የህይወት ፍላጎት ማስኬጃ፣ ልጆችን ከወላጆች ማገናኛ፣ ማህበረሰቡን ከአደገኛ በሽታዎች መጠበቂያ፣ ከሥነምግባር ውድቀት መታደጊያ መድረክ ነውና እስልምና ትልቅ እውቅና ሰጥቶታል።

አንድ ሙስሊም ኢስላማዊ ቤተሰብ መመሥረት፣ መልካም ዝርያ መተካት፣ አማኝ አላህን ፈሪ ትውልድ ማፍራት ከየት እንደሚጀምር በትክክል ካወቀ ወደፊት የሚጠብቁት የህይወት ሀላፊነቶችም ከወዲሁ ይቃለሉለታል። ምክኒያቱም ማህበራዊ መስተጋብሮቹን የሚያሻሽልበትንና በላጭ የሆነ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችል የትክክለኛ አስተዳደግ መሠረት የሆነችዋን መልካም ሴት የመሠረት ድንጋዩ አድርጎ በቤቱ አስቀምጧልና።

በእስልምና የልጅ አስተዳደግ መጀመር ካለበት ቦታ ማለትም ከሚስት አሊያም ከእናት ምርጫ ይጀምራል። ይህም መልካም አስተዳደግ ላይ ተፅእኖ የምታሣርፈውንና ገንቢ የሆነ ቀጣይ ትውልድ ለማዘጋጀት ብቃት ያላት አርዓያ መሆን የምትችል ሴት በማግባት ነው። ልብ ያለው ልብ ይበል።

17 COMMENTS

  1. በጣም ምርጥ የሙሥሊሙን ቀልብ የሚሥቡ ትምህርቶች ናቸው በርቱ አላህ ያግዛችሁ

  2. በጣም አሥፈላጊ የሆነና ግልፅ በሆነ ትርጓሜ ነዉ ያቀረባችሁት።ጀዛኩምአላህ ኸይረን።ለመማር ዝግጁነንቀጥሉበት።

  3. ወላሂ በጣም ደስ የሚሉ ትምህርቶችን ነው የምትሰጡን ነገር ግን ብዙ ሙስሊም ይህን ድረ ገፅ የሚያውቀው አይመስለኝም እናም የማስተዋወቅ ስራ ብትሰሩ እላለው አላህ ይጨምርላቹ ብያንስ ላለማወቃችን ምክንያት አሳጥታችሁናል በዚህ ዘመን ስለ ኢስላም አለማቅ አይቻልም

  4. ወላሂ ምን እደምላቹህ አላውቅም
    አላህ ሱበሀነ ወተአላ አጅራችሁን ከፍ ያድርግላቹህ
    ሱበበሀን አላህ እዚህ ደህረ ገፅ ገብቼ የምወጣበት ሰአት ይናፍቀኛል በጣም ነው የምደሰተው ትምህርቶቹ ልቤ ውስጥ ገብተው ስምጥ ነው የሚሉት አላህ ኽይር ጀዛችሁን ይክፈላቹህ አላህ ይጠብቃቹህ በናተ ፒጅ ብዙ በቃላት የማልገልፅው ትምህርት አግቼበታለሁ አላህ እጥፍ ድርብ አድርጎ ኽይር ጀዛችሁን ይክፈላቹህ በርቱልኝ ጠንክሩልኝ እ…..ወ…..ዳ….ች…..ኃ……ለ…..ሁ ለ አላህ ብዬ የናተው እህት ረምላ ነኝ በዱአችሁም አትርሱኝ አብበው ከሚተገብሩበት ባሮቹ ያድርገን

  5. masha allah ewnet ehenin website bemekfetachu des blonal muslimu mahbereseb beteleyayu mengedoch ewketun liyasadg ygebal lezihm social media lewetatu hunegna amarach new enam yeteleyayu ye da’awa srawochn wede tshuf bemekeyer le nibab btakerbu sl asteyayet bemestet hasaben ekuachalehu

  6. mashaALLAH ወላሂ ደስ የሚል ት/ት በዚሁ ቀጥሉ ኡማውን ይጠቅማል እናንተንም አላህ ኽይር ጀዛዕ ይክፈላችሁ

Leave a Reply to Abdu Cancel reply

Please enter your comment!
Please enter your name here