የትውልድ ክፍተትን መሙላት

0
4980

وَالَّذِينَ يَقُولُونَ رَبَّنَا هَبْ لَنَا مِنْ أَزْوَاجِنَا وَذُرِّيَّاتِنَا قُرَّةَ أَعْيُنٍ وَاجْعَلْنَا لِلْمُتَّقِينَ إِمَامًا أُولَٰئِكَ يُجْزَوْنَ الْغُرْفَةَ بِمَا صَبَرُوا وَيُلَقَّوْنَ فِيهَا تَحِيَّةً وَسَلَامًا خَالِدِينَ فِيهَا حَسُنَتْ مُسْتَقَرًّا وَمُقَامًا

“እነዚያም ‘ጌታችን ሆይ! ከሚስቶቻችንና ከዘሮቻችን ለዓይኖች መርጊያን ለእኛ ስጠን። አላህን ለሚፈሩትም መሪ አድርገን’ የሚሉት ናቸው። እነዚያ በመታገሳቸው የገነትን ሰገነቶች ይምመነዳሉ። በእርሷም ውስጥ ውዳሴንና ሰላምታን ይስሰጣሉ። በእርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች ኾነው (ይስሰጣሉ)። መርጊያና መኖሪያይቱ አማረች።”(ሱረቱል ፉርቃን .25 ÷74-76)

وَالَّذِينَ آمَنُوا وَاتَّبَعَتْهُمْ ذُرِّيَّتُهُم بِإِيمَانٍ أَلْحَقْنَا بِهِمْ ذُرِّيَّتَهُمْ وَمَا أَلَتْنَاهُم مِّنْ عَمَلِهِم مِّن شَيْءٍ كُلُّ امْرِئٍ بِمَا كَسَبَ رَهِينٌ

“እነዚያም ያመኑትና ዝርያቸውም በእምነት የተከተለቻቸው ዝርያቸውን በእነርሱ እናስጠጋለን። ከሥራቸውም ምንም አናጎድልባቸውም። ሰው ሁሉ በሠራው ሥራ ተያዢ ነው።” (ሱረቱ አጥ-ጡር 52 ÷21)

ብዙ ሠዎች ስለ ትውልድ ክፍተት (generation gap) በተደጋጋሚ እያወሩ መፍትሄ ያሉትን ሃሳብ ይሠነዝራሉ። ኢስላም የትውልድ ክፍተትን በሁለት መልኩ ያየዋል። አዎንታዊና አሉታዊ፤ አሉታዊ ክፍተት የሚባለው፡- አለመከባበር፣ አለመግባባት፣ ሲኾን አዎንታዊ የሚባለው ደግሞ በራስ መተማመን፣ ከጥገኝነት መራቅ፣ አዲስ ነገር ለመቀበል መዘጋጀት፣ ትኩስ ሃሳብ አዲስ ነገር መፍጠር ነው። እንዲህ አይነቱ የትውልድ ክፍተት ለእድገትና ለልማት ወሳኝ በመሆኑ ኢስላም ያበረታታዋል። ቁርአን የትውልድ ክፍተቱን በሁለት ያየዋል። በአንድ በኩል ምንም ማሠሪያ የሌለውንና ትርጉም አልባውን “የአባቶቻችን መንገድ” የተባለ ነገር ሲወቅስ በሌላ በኩል “የቀጥተኛው አባታችን የአብርሃም መንገድ” ያደንቀዋል።

አሉታዊ የትውልድ ክፍተት የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው። መንስኤውም ብዙ የልጅ ልጅ ያራቡት ቤተሰብ መጥፋት፣ ህፃናት በመኝታዎቻቸው ላይ ተጋድመው ከአያቶቻቸው ተረት መስማት እየቀረ፣ ከወንድ አያታቸው ጋር አብሮ መጓዝ ሲጠፋ የመጣ ሊሆን ይችላል። ሌላው የአሉታዊ የትውልድ ክፍተት መንስኤ ግለኝነት /individualism/ ነው። ግለኝነት “ነፃነት እና እኔ ብቻ” የሚባል ፍልስፍና ነው። በልጆችና በወላጆች መካከልም ያለው የመነጋገሪያ ርዕስ እጥረት (የጋራ አጀንዳ ማጣት) የዚህ መንስኤ ነው። በኢኮኖሚ ጫና ምክንያት እናትም አባትም ሥራ ይሠራሉ። በተሠራ ጥናት መሠረት (በምዕራቡ ዓለም) ወላጆች በሣምንት ከልጆቻቸው ጋር የሚነጋገሩት ለ 15 ደቂቃ ብቻ ነው። የአቻ ላቻ ክለቦችም ሁሉም በየእድሜ እርከኑ ላይ ብቻ እንዲንጠላጠል የሚያደርጉ ሌላኞቹ የትውልድ ክፍተት መገለጫዎች ናቸው።

አሉታዊ የትውልድ ክፍተት ኢ-ተፈጥሮአዊ ነው። መግባባትና መነጋገር ለሠው ልጅ ባህልና ሥርዓት መዳበር ወሣኝ ሚና አለው። አላህ አንድ ትውልድ ከሌላኛው ጋር እንዲዋደድ አድርጎ ፈጥሮታል። አረጋውያን ወጣቶችን እንደሚወዱት ወጣቶች ህፃናትና አረጋውያን ይወዳሉ። የሠው ልጅ በመማር ያድጋል። መማር ደግሞ ዘርፈ ብዙ ነው። አንድ ትውልድ ለሌላኛው እውቀት ያሻግራል። የተቀበለውም ትምህርቱን ይበልጥ አዳብሮ ለሚቀጥለው ይሠጣል። ለመማማር ደግሞ መተባበርና መረዳዳት እንዲሁም ሠላምን ይፈጥራል። ኢስላም ታላቅ ለታናሽ እንዲያዝን፣ ታናሽም ታላቅን እንዲያከብር ያሣሥራል። ምዕመናን ማለት ደግሞ ልክ እንደ ጀሃነም ሠዎች ትውልድን የሚወቅሱ ሣይሆኑ ከነሱ የቀደሙትን በዱዐ የሚያስታውሱ ናቸው።

وَالَّذِينَ جَاءُوا مِن بَعْدِهِمْ يَقُولُونَ رَبَّنَا اغْفِرْ لَنَا وَلِإِخْوَانِنَا الَّذِينَ سَبَقُونَا بِالْإِيمَانِ وَلَا تَجْعَلْ فِي قُلُوبِنَا غِلًّا لِّلَّذِينَ آمَنُوا رَبَّنَا إِنَّكَ رَءُوفٌ رَّحِيمٌ
 

“እነዚያም ከበኋላቸው የመጡት ‘ጌታችን ሆይ! ለእኛም ለእነዚያም በእምነት ለቀደሙን ወንድሞቻችን ምሕረት አድርግ። በልቦቻችንም ውስጥ ለእነዚያ ለአመኑት (ሰዎች) ጥላቻን አታድርግ። ጌታችን ሆይ! አንተ ርኅሩህ አዛኝ ነህና’ ይላሉ።” (አል-ሃሽር 59፤10)

قَالَ ادْخُلُوا فِي أُمَمٍ قَدْ خَلَتْ مِن قَبْلِكُم مِّنَ الْجِنِّ وَالْإِنسِ فِي النَّارِ كُلَّمَا دَخَلَتْ أُمَّةٌ لَّعَنَتْ أُخْتَهَا حَتَّىٰ إِذَا ادَّارَكُوا فِيهَا جَمِيعًا قَالَتْ أُخْرَاهُمْ لِأُولَاهُمْ رَبَّنَا هَٰؤُلَاءِ أَضَلُّونَا فَآتِهِمْ عَذَابًا ضِعْفًا مِّنَ النَّارِ قَالَ لِكُلٍّ ضِعْفٌ وَلَٰكِن لَّا تَعْلَمُونَ

“ ‘ከጋኔንም ከሰውም ከእናንተ በፊት በእርግጥ ካለፉት ሕዝቦች ጋር ኾናችሁ እሳት ውስጥ ግቡ’ ይላቸዋል። አንዲቱ ሕዝብ ወደ እሳት በገባች ቁጥር (ያሳሳተቻትን) ብጤዋን ትረግማለች። መላውም በውስጧ ተሰብስበው በተገናኙም ጊዜ የኋለኛይቱ ለመጀመሪያይቱ (ተከታዮች ለአስከታዮች) ‘ጌታችን ሆይ! እነዚህ አሳሳቱን። ከእሳትም ስቃይ እጥፍን ስጣቸው’ ትላለች። (አላህም)፡- ለሁሉም እጥፍ አለው ግን አታውቁም ይላቸዋል።” (አል-አዕራፍ 7፤ 38)

አሉታዊ የትውልድ ክፍተትን ለመሙላት ሠላም፣ ፍቅር፣ ርህራሄ እና ህብረትን ለመፍጠር የተጠና ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። በተቻለ መጠን ሙስሊም ቤተሠቡን ሊያሠፋ፣ ወላጆችንና አያቶችን በየጊዜው መጎብኘት ያስፈልጋል። በተለይም ወላጆችን ከልጆች ጋር በመሆን መጠየቅ ያስፈልጋል። ወላጆች ለልጆቻቸው ሠፊ ጊዜና ትኩረት መሥጠትና እንዲጠይቁ ማበረታታት አለባቸው። የፈለጉትን ቢጠይቁም ሊቀለድባቸው አይገባም። ልጆች ምንም ቢሣሣቱ በራሳቸው እንዲያፍሩ ማድረግ የተሳሳተ ነው። ኢስላማዊ አስተዳደግ ሲባል ተገቢውን እውቀት መስጠት (ተዐሊም) እና ጥልቅ የሞራልና የሥነ-ምግባር (ተዝኪያ) ትምህርትን ያጠቃልላል። ለኢስላማዊ ቤተሠብ ሹራ (ምክክር) ከፍተኛ ቦታ አለው። ሹራ በኢስላማዊ ክብር (ከራማህ)፣ ፍትህ (ዐድል) እና እኩልነት ላይ የተመሠረተ ነው። በዚህ መሠረት ሹራ (ምክክር) ለቤተሠብም ያስፈልጋል። ከነቢያችን /ሠ.ዐ.ወ/ ውጭ ማንም እንከን አልባ ባለመኖሩ እንከን አልባነትን ከማንም አንጠብቅም። ቢሆንም፤ እርስ በርስ መተጋገዝና መተሳሰብ ይጠበቅብናል። ሌላው መርሣት የሌለብን ጉዳይ ቢኖር የባህልና የሃይማኖት ልዩነትን መዘንጋት የለብንም። የባህላችን አካል ሁሉ የተከለከለ አይደለም። እንዲሁም፤ አባቶቻችን የሰሩት ሁሉም ኃይማኖት አይደለም።

አንዳንድ ጊዜ የትውልድ ክፍተት መኖሩ ጥሩ ወይም አስፈላጊ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ። ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ጋር ተያይዞ የሚመጡ ለውጦች የትውልድ ክፍተት ይፈጥራሉ። ዑመር ኢብኑል ኸጣብ እንዳለው፡-

“ልጆቻችሁን አክብሩ። ጥሩ ስነ-ምግባር አስተምሩ። እነሱ የተፈጠሩት ከናንተ ዘመን በተለየ ጊዜ መሆኑንም አጢኑ”

ልጆቻችንን የኛ ኮፒ ማድረግ ተገቢ አይደለም። ነፃነት ያስፈልጋቸዋል። አንዳንዴ ስንሣሣት በአክብሮት እንዲገስፁን መፍቀድ አለብን። አንዳንዴ እነሱ ከኛ የተሻለ ሃሣብ ያመነጫሉ። መቶ በመቶ በኛ ላይ የተጣበቁ እንዲሆኑ ማድረግ የለብንም። በቤታችን፣ በንግዳችንና ለሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮቻችን ላይ እንዲሳተፉ በር እንክፈትላቸው። ምክንያቱም፤ ነገ የመሪነት ሚና መጫወቱ አይከብዳቸውም። በዚህ መልኩ ልጆቻችን ጥሩ ሙስሊም ኢትዮጵያዊ እና ጥሩ የዓለም ዜጋ እናደርጋቸዋለን።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here