ትዳር የተፈጥሮ ፀጋ ነውና አንዳቸው ላንዳቸው ሠላምን ፀጥታን ይፈጥራሉ። ትዳር በፍቅርና በእዝነት ላይ ይመሠረታል።
“ለእናንተም ከነፍሶቻችሁ (ከጎሶቻችሁ) ሚስቶችን ወደእነርሱ ትረኩ ዘንድ መፍጠሩ፣ በመካከላችሁም ፍቅርንና እዝነትን ማድረጉ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ለሚያስተውሉ ሕዝቦች ተዓምራቶች አልሉ፡፡” (አል-አሩም 30፡21)
ብጥብጥ በትዕግስትና ውይይት ይፈታል። ችግሩ ከአቅም በላይ ሲሆንም ከቤተሠቦቻቸው ከሽማግሌዎችና አማካሪዎች እርዳታን ይጠይቃሉ። ብጥብጥ መራራቅና ትልቅ ችግርን እንጂ መፍትሔን አያመጣም። መጥፎው እድል በዘመናችን አለመግባባት እየጨመረ ሲሆን በትዳር ላይ ደግሞ እየተባባሠ ነው።
ሠዎች በተማሩ ቁጥር ባህላቸውን እንደሚያበልፅጉ ቢታሠብም ዘመናዊው ባህል ግን የሠዎችን ትዕግስት፣ አዛኝነትና ተንባካቢነት አስወግዷል። አለመግባባት የአንዳንዴ ክስተት መሆኑ ቀርቶ ባህል ሆኗል።
በአሜሪካ የፍትህ ክፍል እንደገለጸው ከ 1- 3 ሚሊዮን ሴቶች አሜሪካ ውስጥ ከባሎቻቸው ወይንም በወንድ ጓደኞቻቸው አካላዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል። በየቀኑ 3 ሴቶችና አንድ ወንድ በተጓዳኞቻቸው ይገደላሉ። 2000 ዓ.ል 1247 ሴቶች በተጓዳኞቻቸው ተገድለው ነበር። በተመሳሳይ ዓመት 440 ወንዶች ከተጓዳኞቻቸው ተጋድለዋል። የባለትዳሮችና የ “ፍቅረኞች” መገዳደል ውስጥ 30 ሴቶችና 5 ወንዶች ይገዳላሉ። (የፍትህን የወንጀለኛ መረጃ ቢሮ የተጓዳኞች ብጥብጥ 1993 – 2001 ፌብርዋሪ 2003ና 1993 – 2004፣ 2006)
በአገራችን ያለው ሁኔታም አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ግልጽ ነው። ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በባሎቻቸውና “በፍቅረኞቻቸው” የተገደሉ፣ አሲድ የተደፋባቸው፣ ዘግናኝ አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው፣ ወዘተ ሴቶች ተበራክተዋል።
ሁላችንም በማህረሠቡም ሆነ በቤታችን ስለሚከናወኑ ሠይጣናዊ ድርጊቶች በጥልቅ ማሠብ አለብን።
1. ማንም ሠው ቤተሠባዊ አለመግባባት በኢስላም ተቀባይነት እንዳለው ማሠብ አይርኖበትም። ኢስላም ሁሉንም አለመግባባቶች ያስወግዳል – በተለይ በቤተሠብ መሀከል ሲሆን። ቤተሠብ የፍቅርና የእዝነት ተቋም እንጂ የጥላቻና የጭካኔ አይደለም። ባልና ሚስት በአላህ ስም ሊጠባበቁና በጥሩ ጥንቃቄ፣ በእዝነት ሊተያዩ ከቤተሠብም ሆነ እርስ በርሳቸው ያላቸው ግንኙነት በመተማመን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) “ከእናንተ ምርጡ ለቤተሠቡ ምርጥ የሆነው ነው እኔ ከናንተ ለቤተሠቤ ምርጥ ነኝ” ብለዋል። (ቲርሚዚ 4062)
ጥንዶች፣ ወላጆች ወይንም ልጆች እርስ በርስ መጣላት ከጀመሩ የግድ ምክር፣ እርዳታና ተገቢው እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል። ጥላቻና መደባበር (መከፋፋት) ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ መፍቀድ አይገባም። ምክንያቱም፤ መራራቅና ብጥብጥን ነውና የሚያመጡት። ማንም ወንድ ሆነ ሴት የራሳቸውን አስከፊ ባህሪይ ኃይማኖታዊም ሆነ ባህላዊ ምክንያትና ሽፋን መስጠት የለባቸውም።
2. ማንኛውም አይነት አለመግባባቶች በቤተሠብ መሀከል ከተፈጠረ የቤተሠቡ ታላላቅ ሠዎች፣ ዓሊሞችና የማህበራዊ ጉዳዮች ሠራተኞች ትኩረት ሠጥተው ሊሠሩባቸው ይገባል። አለመግባባትን ለመገሰፅም ሆነ ለማሳወቅ እፍረትና ኃይማኖታዊ ገደብ ሊይዘን አይገባም። አሳፋሪው ነገር ብጥብጥ እንጂ ብጥብጥን ማሳወቅ አይደለም። ብጥብጥን ልንቃወምና ልናስተካክለው ይገባል። የቤተሠብ ግጭት በሽታ ስለሆነ በቶሎ መታከም ይኖርበታል።
3. የቤት ውስጥ አለመግባባት አቤቱታዎች ችላ ሊባሉ አይባም። ምንም እንኳን ያልተግባቡት ወጣቶች፣ ድሀዎች ወይም ያልተማሩ ሠዎች ሊሆኑ ቢችሉም የሚያውቁ ሠዎች ይህን ወንጀል ችላ ለማለትና ለማድበስበስ አይፈልጉም (ሊያደርጉትም አይገባም)። ሠውየው ሀብታም ወይ ድሀ፣ መሪ ወይ ተራ ግለሠብ፣ ወዳጅ ወይ ወዳጅ ያልሆነ፣ ተጣማሪ ወይ ተጣማሪ ያልሆነ ሊሆን ቢችልም እንኳን። በማንኛውም ሁኔታ ከዚህ ችግር ልንማርና በቁም ነገር ልንይዘው ይገባናል። አንድ ግለሠብ የመጣበት ክስ እውነት ከሆነ በሥልጣኑ፣ ከሱ ጋር ባለን ግንኙነት ወይም በዝምድናችን ምክንያት በቸልታ ማለፍ የለብንም። ፍትህ ማለት ያንድ ሠው አለማዳላት ነውና። ይህን ሠው ልንረዳው የምንችለው ይህን ተግባር ደግሞ እንዳይፈጽመው ማስቆም ስንችል ነው።
4. እነዚያ በቤተሰብ ግጭት ምክንያት የተጎዱት በፍጥነት እርዳታ ማግኘት አለባቸው። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በቤት ውስጥ አለመግባባት ሴቶች ይበልጥ ተጠቂዎች ናቸው። ስለዚህም፤ ለዚህ ጉዳይ የተለየ ትኩረት መስጠት አለብን። ማህበረሠቡ በዚህ ጉዳይ ላይ ማምረር አለበት። ሴቶች ቤተሠባቸውን እንዳያጡ ከመፍራትና ብዙውን ጊዜ መሄጃ ስለማይኖራቸው በዚህ ጉዳይ ሲጎዱና ሲማረሩ ይታያል። በርግጥ ሁሉም ሠው እንዴትና ምን መወሠን እንዳለበት ያውቃል። ሆኖም፤ አንዱ በሌላው ላይ አይወስንም። ሁሌም የዚህ ጉዳት ሠለባዎች እርዳታ በሚፈልጉበት ጊዜ መርዳት ሞራላዊም ኃይማኖታዊም ግዴታ ነው።
5. ቤተሠባዊ መተሳሰብን የምናሳድግባቸው ቋሚ ስርዓቶች ቢኖሩንም መልካም ነው። ራሳችንንና ሌሎችን እንዴት መንከባከብ እንደሚቻልና በአክብሮት ችግሮችን መፍታት እንዴት እንደሚቻል ማስተማር አለብን። ቁጣን መቆጣጠርና ሠላማዊ ፀባይ ማዳበርን ከቁርኣን ሱናና ዘመናዊ የሥነምግባር ሳይንስ ልንማር ግድ ነው። በሐገራችን እንደዚህ አይነት የቤተሰብ አለመግባባት ህይወታቸውን ላጡና ጉዳት ለደረሰባቸው እህቶቻችን ቤተሠቦችና ለጓደኞቿ መፅናናትን ይሰጣቸው። እኛንም በቀጥተኛው መንገድ ላይ እንዲያፀናን ለቤተሠቦቻችን፣ ለጎረቤቶቻችንና ለአላህ ፍጥረታት ሁሉ ጥሩ እንዲያደርገን እንለምነዋለን። አሚን