ከሀርቫርድ ዶክትሬት የተሻለ

0
2135

አንድ “ሻይ” እየጠጣ ያለ ሠው ብትመለከትና ምን እየጠጣህ ነው ብለህ ብትጠይቀው ሻይ እየጠጣሁ ነው የሚል መልስ ይሰጥሀል። በርግጥ ሻዩ ውስጥ ስኳር አለ። ነገር ግን፤ ስለ ስኳሩ አያነሳም ማንም ቢሆን ሻይ እና ስኳር እየጠጣሁ ነው አይልህም። የቱንም ያህል የስኳሩ ጥፍጥና ሻዩን ቢሞላውም ስለ ስኳሩ ምንም አያነሳም።

ለረጅም ጊዜ የቆየው ቁርአንን በቃል የማጥናት (የማሃፈዝ) ባህልም እንደዚሁ ነው። ውጤቱ (የሚያስገኘው ለውጥ) ሚስጥራዊ ነውና።

አንድ ቁርአንን በቃል በማጥናት ላይ ያለ ልጅን ብንመለከት እጆቹ፣ አፍንጫው፣ ጆሮውና አይኖቹ እንዲሁም ምላሡ ያላቸውን ሚና መለየት እንችላለን። ግልፅ ነው ምላሶቹ የሚያወሩ ይመስላሉ። የቱንም ያህል ለኛ እውነታው ይህ ቢመስለንም የሚያወሩት ምላሶቹ የሚሠጡት ጆሮዎቹ ብቻም አይደሉም። የሚናገረውና የሚያዳምጠው ሰዋሰውኛ ያለው ድብቅ አካል ነው።

ቁርአንንም በቃል መያዝ የሚፈጥረውም ለውጥ እንደዚሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። እንግዲህ አንድ ቁርአንን በቃሉ በማጥናት ላይ ያለ ልጅ ላይ የሚከሠተው ለውጥ ይህን ይመስላል። እኛ ቃላትን እየሸመደዱ ብቻ እንዳሉ አድርገን እናስብ ይሆናል እውነታው ግን እያንዳንዱ የሚተነፍሷት ፊደል የሚፈጥሩት ድምፅ በልባቸውና በአይምሮአቸው ላይ የራሡን አሻራ በማሣረፍ እያንዳንዷን የቁርአን ቃላት ወደ ተግባር ለመለወጥ ይረዳቸዋል።

“ሠዎች በአላህ ቤት ውስጥ ቁርአንን ለመቅራትና ለማጥናት አይሠባሠቡም የአላህ እዝነት በነሡ ላይ ቢወርድ፤ መላኢካዎች ቢከቧቸው እንጂ” (ሙስሊም)

ለመጀመሪያ ጊዜ በሂፍዝ መርሀ-ግብር ያስተማርኳቸው በ9 አመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆችን እ.ኤ.አ በ1998 ነበር። በዛ ወቅት እኔ እንግሊዝኛ መምህራቸው ነበርኩ። ልጆቹ ከቀን ወደ ቀን ንቃተ ህሊናቸው ሲጨምር ልመለከት ችያለሁ። በወቅቱ ብዙም ጠቃሚ የማይመስሉ ግንኙነቶቻቸውና መስተጋብሮች ወደ ወንድማማችነት ለመቀየራቸው እኔው ምስክር ነኝ። የአንዱ ሞገስ የሁሉም ሲሆንና የሌላኛውን ችግር ደግሞ የሁላችንም ነው በሚል ሁኔታ ውስጥ ሆነው አይቻቸዋለሁ። ልጆቹ የትምህርት አመቱን በሁሉም የትምህርት አይነቶች 98 በማምጣት አጠናቀዋል። ከዚያም በኋላ ቢሆን በትምህርታቸው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል። እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች አልፎ አልፎ ብቻ ነው የሚገኘው። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ምንም ተዐምር የለም። ልጆቹ ራሳቸውን በሚገርም ሁኔታ ሊቀይሩ የቻሉት የአላህ (ሱ.ወ) ቃል የሆነውን ቁርአን በቃላቸው ለማጥናትና ለመረዳት በመስጠታቸው ነው።

ኢስላምን ጠብቀን ልናቆይበት የምንችለው ከረጢት ያለው በልጆቻችን ልቦና ውስጥ ነው።

‹‹አይደለም እርሡ (ቁርአን) በነዚያ ዕውቀትን በተሠጡት ሠዎች ልቦች ውስጥ (የጠለቀ) ግልጾች አንቀጾች ነው፤ በአንቀጾቻችንም በዳዮች እንጂ ሌላው አይክድም›› (ቁርአን 29፡49)

ይህን ምርጥ ዘር በልጆቻችን ልብ ውስጥ መዝራት የኛ ግዴታ ነው። ከፊታቸው ለተጋረጠባቸው ችግር በአግባቡ ልናዘጋጃቸውና ልናስታጥቃቸው ይገባል። አዎ ማንነታችንንና ቅርሳችንን ጠብቀን ለማቆየት ከዛሬ የተሻለ ቀን የለም። ዛሬ ወሳኝ ቀን ነው።

ሙሉ ቀን የሚያስተምሩ ብዙ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም እኛ ግን እንደ ወላጅ የልጆቻችንን ጊዜ የአላህ (ሡ.ወ) ቃልን በቃል እንዲያጠኑ በመሠዋት ልጆቻችን የአላህ ደስታ ከሚከጅሉ ሺዎች ተርታ እናሠልፍ። ለኢስላማዊ ማንነታችንም ቢሆን መሠረት እንጣል። አዎ! ይህ በእውነትም ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ዶክትሬት የተሻለ ነው።

ቡረይዳህ (ረ.ዐ) እንደሚናገረው ‹‹ከአላህ መልዕክተኛው ጋር ተቀምጬ ነበር›› ይላል። ‹‹እንዲህ ሲሉም ሠማኋቸው የመጨረሻው (የቂያም) ቀን ቁርአን ወዳጁን ይገናኛል። ሠውየው ቀብሩ ሲከፈትለት ‹እኔ ማን እንደሆንኩ አስታወስከኝ?› ይለዋል ሠውየውም ‹‹አላስታወስኩም›› ይለዋል። ደግሞም ይጠይቀዋል ሠውየውም በድጋሚ እንዳላወቀው ሲነግረው ‹‹እኔ ወዳጅህ ቁርአን ነኝ። በሞቃት ጊዜ ያስጠማሁህ፤ በሌሊት ከእንቅልፍ ያስነሳሁ። ማንኛውም ነጋዴ ሲነግድ የሚያተርፍበት ቀን አለ እናም ዛሬ አንተ ለንግድህ ታተርፋለህ›› ይለዋል። ከዚያም በግራ እጁ ሀይል በቀኝ እጁ ዘላለማዊነት (ህያዊነት) ይሠጠዋል። በጭንቅላቱም የክብር ዘውድ ይደፋለታል። ለወላጆቹም በዚህ ዓለም ሠዎች ሊሠራ የማይችል ሁለት ልዩ ካባ ይሠጣቸዋል። ‹‹ይህን እንዴት አገኘን?›› ብለው ይጠይቃሉ። ‹‹ልጃችሁ ቁርአንን በመማሩ›› ይባላሉ። ለሱም ቁርአንን እየቀራህ ደረጃውን ውጣ በጀነት ውስጥም እለፍ ይባላል። ባነበበ (በቀራ) ቁጥርም ደረጃው ይጨምርለታል።›› (አህመድ)

በቅድሚያ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባን እውነታ በአንድ ወቅት ላይ ከፍተኛ የሆነ የስልጣኔ እርከን ላይ ደርሶ የነበረ ትውልድ ዛሬም አዲስ ስልጣኔ መፍጠር መቻሉን ነው። የምዕራቡን ዓለም ሣይንሳዊ አመርታ ጥሩ ጎን በመጠቀምና ከሰብአዊና መንፈሳዊ አስፈልጎቶች እንዲሁም አምላካዊ ህግጋት ጋር እንዲጣጣሙ በማድረግ የምዕራባውያን ስልጣኔ ነውር ሊቀለበስ ይችላል። በርግጥ ይህ ዓለምን በሙሉ ያስደመመው ምዕራባዊ ቴክኖሎጂ እድገት ህይወትን ቀላል ያደረጋት ይመስላል። የምንፈልገውን ነገር ሁሉ ቁጥሮችን ብቻ በመንካት ማግኘት የምንችልበት ደረጃ ደርሠናል። ከዚህም አልፎ የሠው ልጅ ወደ አድማስ በመዝለቅ በጨረቃ ላይ በመመራመርና ከዚያም ያገኘውን ቁስ ወደ ቤተ-ሙከራ ይዞ ሊመጣ ችሏል። እንደዚህ አይነቱ ሳይንሳዊ እመርታ ከዚህ በፊት ሊታሠብ የማይችል አይነት ነበር። በርግጥ እንደነዚህ አይነት ክስተቶች በሚከተለው የቁርአን አንቀጽ ይጠቃለላሉ።

“የማታውቁትንም ድንቅ ነገር ይፈጥራል።” (አል-ነህል፤ 8)

አሁን ዋነኛ ጥያቄ የሚሆነው ‹‹ይህ የሠውን ልጅ ወደ ጨረቃ ለማምጠቅ የበቃ ሳይንሣዊ እምርታ ደስታን አጎናፅፎታልን?›› የሚለው ነው። መራሩ እውነት ግን በተቃራኒ ነው። ይህ ሙሉ ለሙሉ ቁሣዊ ፅንሰ ሀሳብ ያዘለው ምዕራባዊ ዕውቀት የሠጠው አካላዊ ምቾት እንጂ ውስጣዊና መንፈሳዊ አይደለም። የሠው ልጅ ብዙ አንጻባራቂ ሊባሉ የሚችሉ ቴክኖሎጂያዊ እመርታ ሊያስገኝ ችሏል ነገር ግን የአእምሮ ሠላም ሊያስገኝለት አልቻለም።

ጭንቀት፣ ፍርሃት፣ ኃዘን፣ ተስፋ መቁረጥ ‹‹አደጉ›› በሚባሉት ሀገራት አካባቢ መስማት የተለመደ ክስተት ነው። በዚህ ሁሉ ምቾት ውስጥ እያሉ ግን የመንፈስ መረጋጋት ይጎድላቸዋል።

በእነዚህ ሀገራት ውስጥ ታዲያ የአይምሮ ሀኪሞች በጣም የተጨናነቀ ፕሮግራም ቢኖራቸው የሚያስገርም አይነሆንም። ብዙ ደንበኞቻቸውም የሞራል ውድቀት፣ ጭንቀት፣ የቤተሠብ መብትን የማህበራዊ ህይወት አለመረጋጋትና ብቸኝነት ያጠቃቸው ናቸው። እነዚህ ነገሮች በሙሉ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ላለው የወንጀል መጠን ፍርሀትና አስፈሪ ሁኔታ በህዝቡ መሀከል ሊፈጥር ችሏል። የዚሁ ሁሉ ምክንያት ደግሞ በስልጣኔ ስም የተሰጠው ገደብ የለሽ ነፃነት ነው። በመሆኑም፤ ይህ የሠው ልጆችን ተፈጥሮ ከመበዝበዝ ባለፈ ያልተሟላለትን መንፈሳዊ ፍላጎት ሊያሟሉለት አልቻሉም። አንዱን ፍላጎቱ ባሟላ ቁጥር ለሌሎች ተጨማሪ (ቅንጦቶች) የሚሠጠውም ቦታ አብሮ ይጨምራል።

ምዕራቡ ዓለም ያላስተዋለው ነገር በዚች ዓለም ላይ ‹‹ፍፁም›› የሚባል ነጻነት አለመኖሩን ነው። ጀርመናዊው ገጣሚ ባሮቸርት የዚህ ትውልድ ችግሮች ሁሉ እየመጡ ያሉት በዚህ ስልጣኔ ጥላ ስር መሆኑን ይገልጻል። ትውልዳችን ውስጡ እሾኽማ ነው። በእውነቱ እኛ ሀይማኖት፣ ምቾትና ንፅህና ይጎድለናል፤ ፍቅራችን ውጫዊ ነው፤ ወጣቱ በእኛ ላይ ያለው ተስፋ ተሟጧል። ትውልዳችን ምንም አይነት ገደብ አያውቅም፤ ምንም ድንበርና ጥበቃም የለውም። ከፖለቲከኞችም ውስጥ ይህ ጉዳይ ያሳሰባቸው አልጠፉም። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የነበረው ጆንርስተር ነው። ጆንርስተር ‹‹ሠላም ወይስ ጦርነት›› በሚለው መጽሃፉ ተመሳሳይ ነገር ገልጿል። ችግሩ ቁሳዊ ነገሮች ላይ አይደለም። ምክንያቱም፤ ሁሉም ጊዜ አመጣሽ (የወቅቱ ምርጥ) ነገሮች አሉን። ችግራችን ጠንካራ እምነት (ኢማ) ነው። ያለሱ ያሉን ቁሳዊ ሐብቶች ሁሉ ባዶ ናቸው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here