በራስ መተማመንን በልጆቻችን ላይ ማስረጽ

1
8092

ወላጆች ለልጆቻቸው ሊያደርጉት ከሚገባቸው ነገር ውስጥ አንዱና ዋነኛው ልጆች በራሳቸው ላይ እምነት እንዲያሳድሩና ስለራሳቸው አዎንታዊ እይታ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው።

በራስ ላይ እምነት መጣል (በራስ መተማመን) አዎንታዊ የሆነ ማህበራዊና ውስጣዊ መስተጋብር በመፍጠር ረገድ ቁልፍ ቦታ አለው። ከፍተኛ የራስ መተማመን ያላቸው ልጆች በራሳቸው ጥሩ ውሳኔ ይወስናሉ፣ በሥራቸውም ኩሩዎች ናቸው። ኃላፊነትን ለመቀበል ፍቃደኞችና በከባድ (አስፈሪ) ሁኔታዎችም ውስጥ ለማለፍ ዝግጁዎች ናቸው። በማህበራዊ ህይወታቸው ውጤታማ፤ በትምህርት ቤትም ውስጥ ተፎካካሪዎች፤ ህይወታቸውን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ እንደ ትምህርት “መፎረፍና” ዕፅ መጠቀምን የሚያስወግዱ ናቸው።

ወላጆችና አካባቢ በልጆች ላይ ከፍተኛ የሆነ በራስ መተማመንን በመገንባት ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ልጆች እንደሚደመጡ ማሰብ ሲጀምሩና ሠዎች ከእነሡ ቁምነገር እንደሚጠብቁ ሲያውቁ ከልባቸውም እንደሚንከባከቧቸው ሲያስቡ በራሳቸው ላይ ያላቸው እምነት ከፍተኛ ይሆናል። ከዚህ በታች የልጆቻችንን በራስ መተማመን የሚያዳብሩ ነጥቦች ተጠቅሠዋል።

1. ተሰጥኦዎቻቸውን ተንከባክቦ ማሣደግ

ማንኛውም ልጅ አፈጣጠሩ ለአላህ እጅ የሠጠ (ፊጥራ) ሆኖና አንድ ልዩ ተሰጥዖ ይዞ ነው። ከዚያ በኋላ ግን ከእድገት ጋር ተያይዞ አዳዲስ ባህሪያት (ማንነቶች) ይመጣሉ። እነዚህ ተሰጥዖዎች ልዩ ለሆነ ዓላማ ነው የተፈጠሩት። እናም ልንከባከባቸውና በሙሉ አቅማቸው እንዲያድጉ ልናደርግ ይገባል። በዚህ ረገድ ታዲያ ወላጆች ከፍተኛውን ሚና ይጫወታሉ። በመጀመሪያ እነዚህን ተሰጥዖዎች ለይቶ በማውጣቱ ረገድ ከዚያም እነዚህ ተሰጥዖዎች በማሣደግ ረገድ መንገዶችን በሚፈላለጉ በኩል። በርግጥ ይህ ሥራ ልጆች እያደጉ በመጡ ቁጥር ቀላል ይሆናል። ነገር ግን፤ አንዳንድ ተሰጥዖዎች በጣም በትንሽ ዕድሜ ውስጥም የሚታዩ (የሚኖሩ) ናቸው። ትምህርት፣ ዝንባሌዎች፣ ስብስቦች፣ ስፖርቶችና ሌሎችም ፍላጎቶች እነዚህን ልዩ ተሠጥዖዎች የምንከባከብባቸው አጋጣሚዎች ናቸው። ይህ ነጥብ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ብዙ ጊዜ የሚረሡ የሆኑትን ሴት ህፃናትም ያጠቃልላል። የልጆች ተፈጥሮአዊ ችሎታዎችን እድገት መቅጨት በልጆች የራስ መተማመን ላይ ግልፅ የሆነ ተጽዕኖ ያሳድራል። አንደ ልጅ ከችሎታውና ከፍላጎቱ ጋር የማይሄድ ዘርፍ ውስጥ እንዲገባ ከተገደደ በራሡ ላይ የሚኖረው እምነት አነስተኛ ይሆናል። ወላጆቹም የሚጠብቁበትን ነገር አያገኙም።

2. ከልጆች ጋር መወያየት

በኢትዮጵያውያን ላይ የተሠራ ጥናት ባይኖርም፤ አስገራሚው የቁጥር መረጃ እንደሚሳየን አንድ አሜሪካዊ ልጅ በሳምንት በአማካይ 1680 ደቂቃዎችን በቴሌቪዢን ላይ በማፍጠጥ ሊያሳልፍ 38.5 ደቂቃውን ብቻ ነው ከቤተሠቦቹ ጋር ትርጉም ያለው ውይይት በማድረግ የሚያሳልፈው። በእንደዚህ አይነት ማህበረሰብ ውስጥ ታዲያ የልጆች ማህበራዊ ጉድለት ማነስና የቤተሠብ በብዙ ችግሮች ውስጥ መዘፈቅ ምንም አያስገርም። ለልጆች በራስ መተማመን ማደግ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ብዙ ምክንያቶች ሲባል ወላጆች በየቀኑ ከልጆቻቸው ጋር መነጋገራቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ጥሩ መስተጋብር ለመፈጠር ዋነኛ መንገድ መደማመጥ ነው (በደንብ መደማመጥ)። ማለትም የልጃችንን ሃሳብና ስሜት ለመረዳት እንሞከር። ሀሳቡ ስሜቱና ፍላጎቱ ባጠቃላይ ትኩረት ሊሠጣቸው ይገባል። ወላጅ ልጁ የሚሠራው ሥራ ጠቃሚና አስፈላጊ መሆኑን ሊያሣየውና ስለአስፈላጊነቱ ሊያወራው ይገባል። በርግጥ የኛን አመለካከትና እምነት ማብራራት ይኖርብናል። ነገር ግን፤ ይህ መሆን ያለበት በተለያየ መንፈስና ምክንያታዊነት ሊሆን ይገባዋል።

ችግሮች የልጆችን ማንነትና ባህሪ በማያቃውስ መልኩ ሊመሩ ይገባል። ልጆች ችግር እያለባቸው በችግራቸው ግን አለመቀወሳቸውን ሲረዱ ለችግራቸው ከምንጊዜውም በተሻለ መልኩ መፍትሄ ይፈልጉለታል።

3. ኃላፊነትንና ራስን መቻል ማስተማር (መገንባት)

በመጨረሻም ልጆቻችን ፈሪሀ-አላህ ያላቸውና በራሳቸው ውሳኔ መወሠን እንዲችሉ ማድረግ እንፈልጋለን። የዚህ ጤናማ የሆነ በራስ መተማመንና ውሳኔ የመስጠት አንዱ ክፍል ደግሞ እነዚህን ክህሎቶች ለመማርና ለማሳደግ ዕድል ማግኘት ነው። ወላጆችም ልጆቻቸው የውሳኔ ሰጪነትና የችግር አፈታት ክህሎትን እንዲማሩና በዕለት ተዕለት ህይወታቸው ውስጥ እንዲተገብሩት ሊያበረታቷቸው ይገባል። እነዚህ ክህሎቶች ለልጆቻችን ኃላፊነትን በመስጠትና ቀስ በቀስ የራሳቸውን ህይወት እንዲመሩ ነፃነት በመስጠት እውን ሊሆን ይችላል።

በተለይም ልጆች እያደጉ ሲመጡ የምንሠጣቸው ኃላፊነት ዕድሜያቸውን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባና ምክንያታዊ ሊሆን ይገባዋል። ወላጆችም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሁሉ ሊረዷቸው ግድ ነው። ይህ ዕድል ያላቸው ልጆች ራሳቸውን ጠቃሚ፣ ገንቢ ዋጋ ያላቸውና ተፎካካሪ እንደሆኑ ያስባሉ። ታዲያ ይህ በራሡ በወላጆችና በልጆች መሀል ያለውን መተሣሠብ (እምነት) ይጨምራል።

4. ከምንም ነገር በላይ ልጅህን ውደድ

ይህ ማለት ልጅህን ምን ያህል እንደምትሳሳለት/ላት ማሣየትና እንደምትወደው/ዳት ሁሌም ቢሆን መንገር ነው። ከልጅህ ጋር ጊዜ ሠጥተህ ማሣለፍ፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መጫወት፣ ማውራት ምርጥ የሚባሉ ክስተቶችን አብሮ ማሣለፍ የእግር መንገዶችን አብሮ መሄድ፣ መፅሀፍ እንዲሁም ቁርኣን መቅራትና ሌሎች ብዙ ብዙ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ወላጆች ከልጆች ጋር በሚያወሩበት ወቅት የልጆችን በራስ መተማመን የሚገነቡ ቃላት መጠቀም አለባቸው። ለምሳሌ “አመሠግናለሁ”፤ “በጣም ጥሩ ሃሳብ”፣ “የምትገርም ልጅ ነህ”፣ “በሥራህ ኮራሁ”፣ “ማሻአላህ” እና ሌሎችም። ልክ እንደ ዱአ እና ሌሎች ልዩ አድናቆቶች ሁሌም በምስጋና ጀርባቸውን መታ እያደረጉ እያቀፉ በመሣም በሌሎችም የተለያዩ መንገዶች ለልጆቻችን ያለንን ቀረቤታና ፍቅር ማሣየት ያስፈልጋል። ከምንም በላይ ደግሞ ውዱ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) ለልጆች በጣም ቅርብ አዛኝና ተንከባካቢ እንደነበሩ ማስታወስ ተገቢ ነው።

ባጠቃላይ ከላይ የጠቀስናቸው የልጆችን በራስ መተማመንና በራስ ላይ እምነት መጣል ለማሣደግ ከምንጠቀማቸው መንገዶች ውስጥ የተወሠኑት ብቻ ናቸው። ልጆች አንዴ ስለራሳቸው አዎንታዊ የሆነ አመለካከት መገንባት ከቻሉ በህይወታቸው ውስጥ ሊገጥማቸው የሚችሉ ሌሎች ችግሮችን መጋፈጥ ይችላሉ። በዚህም ስኬታማ፣ ተፎካካሪ እና በራሳቸው እምነት ያላቸው ይሆናሉ። ከፍተኛ የሆነ በራስ መተማመን ማሣደግ ጥቅሙ ለልጆች ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ ለቤተሰቡ ነው። ይህ ነገር የልጆችና የቤተሠብን መስተጋብር በማጠናከር የልጆችና የወላጆች ግንኙነት እንዲያምር በማድረግ አላህ የሚፈልገው አይነት ቤተሠብ እንዲፈጠር ያደርጋል።

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here