ቁርአንን የመቅራት ትሩፋት (ክፍል 2)

0
6857

6-    ቁርአን በመቅራትህ አላህ ከ 4 ነገሮች አንዱን እውን ያደርግልሀል፡፡ ከነሱ ውስጥ አንዱ ፀሀይ ከወጣችበት ነገር ሁሉ ይበልጣል፡፡

አቡ ሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ባስተላለፉልን ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ፡-

‹‹ሰዎች በአላህ ቤት ተሰባስበው የአላህን መፅሀፍ እያነበቡና በመሀከላቸውም እየተማማሩ አይቀመጡም፤ በነሱ ላይ እርጋታ የወረደችባቸው፣ እዝነትም ያካበባቸው፣ መላእክት በዙሪያቸው የሸፈኗቸው፣ አላህም እሱ ዘንድ ካሉት ጋር ያወሳቸው ቢሆን እንጂ፡፡›› ሙስሊም

የልቅና ባለቤት የሆነው አላህ ደካማ ባርያውን ማውሳቱ ለባርያው ምንኛ ታላቅ ክብር ነው!

በሌላም  ዘገባ  

‹‹የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ለኡበይ እንዲህ አሉት ‹አላህ ባንተ ላይ ቁርአንን እንድቀራ አዞኛል፡፡› ኡበይም ‹ አላህ በስሜ ጠርቶ ነው ያዘዞዎት› አላቸው፡፡ ‹አዎ›  አሉት  ‹በአለማት ጌታ ዘንድ ተወሳሁ ማለት ነው?!›አላቸው፡፡ ነቢዩም ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም  ‹አዎ›  አሉት። ኡበይ እንባውን መቆጣጠር አልቻለም፡፡

በራእ ኢብኑ ዓዚብ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንደሚተርኩልን

‹‹ አንድ ቀን አንድ ሰው የካህፍን ምእራፍ ያነባል፡፡ ፈረሱን ደግሞ ከአጠገቡ በሁለት ገመዶች አስሮት ነበር፡፡ ወዲያው ደመና አካባቢውን ጋረደው፤ ወደ ስውየውም እየቀረበ መጣ፡፡ ይህን ጊዜ ፈረሱ ለማምለጥ ይታገል ገባ፡፡ በነገታውም የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ዘንድ በመምጣት ስለ ተከሰተው ነገር አጫወታቸው፡፡ እሳቸውም ‹ይችማ ለቁርአን ስትል የወረደች ሰኪና (እርጋታ) ነች፡፡› አሉት፡፡›› ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል፡፡

7-   ቁርአንነበ ንዱ ፊደል በአስር ሀሰናት (መልካም ስራ) ተባዝቶ ይታሰባል

ኢብን መስኡድ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ባወሩት ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ማለታቸው ተዘግቧል፡-

‹‹አንድን የቁርአን ቃል ያነበበ ሰው ለሱ ሀሰና (ምንዳ) አለው፡፡ ይህም በአስር አምሳያው ይባዛለታል፡፡ (አሊፍ ላም ሚም) አንድ ፊደል ነው አልላችሁም፡፡ ነገር ግን አሊፍም ፊደል ነው፤ ላምም ፊደል ነው፤ ሚምም ፊደል ነው፡፡›› ቲርሚዚ

8-   ቁርአንን የሚያነቡ ሰዎች የአላህ ቤተሰቦች ናቸው፡፡

ከአነስ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡

‹‹ለአላህ ከሰዎች የሆኑ ቤተሰቦች አሉት፡፡›› ሰሃቦችም ‹አንቱ የአላህ መልእክተኛ ሆይ እነሱ እነማን ናቸው;› ሲሉ ጠየቋቸው፡፡ እነሱ የቁርአን ቤተሰቦች ናቸው፡፡ የአላህ የተለዩ ቤተሰቦች፡፡›› ነሳኢና ኢብኑ ሂባን

9-   የሰው ልጅ ቁአንን በማ በዱንያ ላይ ይጠበቃል፡፡

ኢብን አባስ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ሲናገሩ እንዲህ አሉ፡-

‹‹ቁርአንን የሚቀራ ሰው ከወራዳው እድሜ ላይ አይደርስም፡፡ ይህንንም የአላህ ቃል ብግልፅ ይነግረናል፡፡ (ከዚምከፊሉን ከዝቅተኞች ሁሉ በታች አድርገን መለስነው፡፡ እነዚያ ያመኑት ሲቀሩ…) እነዚህም ቁርአንን የሚቀሩ ናቸው፡፡ ሀኪም

10-   አንድ ባርያ ቁርአንን በመቅራቱ ብቻ ሌሊቱን ቆመው ከሚያሳልፉ ባሮች ተርታ ይመደባል፡፡

አቡ ሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-

‹‹በተደነገጉት ሰላቶች ላይ የተጠባበቀ ሰው ከዘንጊዎች አይሆንም፤ በሌሊቱ ክፍል መቶ አንቀፆችን ያነበበ ሰው ቆመው ካደሩት ሰዎች ይመደባል፡፡›› ኢብኑ ኹዘይማ በሰሂሃቸው ዘግበውታል፡፡

11-   ቁርአን ለባለቤቶቹ አማላጅ ይሆናል

ከአቢ ኡማማ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በተወራ ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-

‹‹ቁርአንን አንብቡ እሱ እኮ (ቁርአን) በትንሳኤ እለት ለባለቤቱ አማላጅ ሆኖ ይቀርባል፡፡›› ሙስሊም

ቁርአን በምስክርነትም እንዲሁ ይቀርባል፡-

ከነዋስ ኢብኑ ሰምዓን አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንደተገኘው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ሲሉ ሰምቻለሁ አለ፡-

‹‹በትንሳኤ ዕለት ቁርአንና በምድራዊ ዓለም በሱ ይሰሩበት የነበሩ ባለቤቶቹ ይቀርቡና በየተራ የበቀራ ምእራፍና የአል ዒምራን ምእራፍ እየመጡ ለባለቤቶቻቸው (ለሚቀሯቸውና ለሚሰሩባቸው) ምስክርነታቸውን ይሰጡላቸዋል፡፡›› ሙስሊም  

በተጨማሪም አቡ ሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ቀጣዩን ሀዲስ ይነግሩናል፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-

‹‹በእለተ ትንሳኤ ቁርአን ይመጣና፡- ጌታዬ ሆይ (ቁርአን የሚቀራውን ሰው) አስውበው ይላል። ሰውየውም የክብር ዘውድ ይደረግለታል፡፡ ጌታይ ሆይ ጨምርለት ይላል፡፡ የክብር ጌጥ ይለብሳል፡፡ ከዚያም ጌታዬ ሆይ ከሱ የሆነን ውደድ ይላል፡፡ ጌታውም ከሱ የሆነን ይወዳል፡፡ከዚያም እንዲህ ይባላል፡- አንብብ፣ ከፍ በል፣ በያንዳንዱ አንቀፅ ደረጃህ ከፍ ይደረግልሃል፡፡›› ቲርሚዚ  

12-   ቁርአንን መቅራት በጀነት ውስጥ የከፍተኛ ክብርና ደረጃ ባለቤትነትን ያወርሳል፡፡

ዓብደላህ ኢብን ዐምር ኢብኑል ዓስ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ከነብዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ይዘው እንዳወሩት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ፡-

‹‹ለቁርአን ባለቤት እንዲህ ይባላል፡- አንብብ፣ ከፍ በል፣ በዱንያም ላይ ታነበንብ እንደነበረው አንብብ፣ ማረፊያህ(ደረጃህ) የሚሆነው ታነባት በነበረችው በመጨረሻይቱ አንቀፅ ላይ ይሆናል (በንባብህ ልክ)፡፡›› አቡዳውድና ቲርሚዚ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here