ቁርአንን የመቅራት ትሩፋት (ክፍል 1)

0
9685

ቁርአንን ማንበብ የትክክለኛና እውነተኛ ሙእሚኖች መገለጫ መሆኑ ጥርጥር የለውም። የአላህንም እዝነት ተላብሰው የሚገኙት እነዚሁ ሰዎች ናቸው። በዚህ ፅሁፍ ቁርአን የመቅራትን ትሩፋት የሚዘረዝሩ ማስረጃዎቸችን ለማየት እንሞክራለን።

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ መልእክተኛውን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ቁርአንን ያነቡ ዘንድ እንዲህ በማለት ያዛቸዋል፦

وَرَتِّلِ الْقُرْآنَ تَرْتِيلًا
  

“ቁርኣንንም በዝግታ ማንበብን አንብብ፡፡” (ሙዘሚል 4)

ሀሰን ይህን ሲፈስሩት ግልፅ የሆነን (የተብራራን) ማንበብ አንብብ ማለት ነው ይላሉ። (ተፍሲር ጠበሪ 23/680)

አላህ (ሱ.ወ) ቁርአንን በመቅራት ተግባር ላይ የታተሩ ሰዎችን ሲያወድስ እንዲህ ይላል።

إِنَّ الَّذِينَ يَتْلُونَ كِتَابَ اللَّهِ وَأَقَامُوا الصَّلَاةَ وَأَنفَقُوا مِمَّا رَزَقْنَاهُمْ سِرًّا وَعَلَانِيَةً يَرْجُونَ تِجَارَةً لَّن تَبُورَ لِيُوَفِّيَهُمْ أُجُورَهُمْ وَيَزِيدَهُم مِّن فَضْلِهِ ۚ إِنَّهُ غَفُورٌ شَكُورٌ

“እነዚያ የአላህን መጽሐፍ የሚያነቡ፣ ሶላትንም አስተካክለው ያደረሱ፣ ከሰጠናቸውም ሲሳይ በምስጢርም ኾነ በግልጽ የለገሱ፣ በፍጹም የማትከስርን ንግድ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ምንዳዎቻቸውን ሊሞላላቸው፣ ከችሮታውም ሊጨምርላቸው (ተስፋ ያደርጋሉ)፡፡ እርሱ በጣም መሓሪ አመስጋኝ ነውና፡፡ (ፋጢር 19-30)

በሀዲስም በተመሳሳይ መልኩ ቁርአንን በማንበብ የሚገኘውን ክብርና ጥቅም በተመለከተ በርከት ባሉ አጋጣሚዎች ተውስተዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከሁሉም በፊት ሊታወቅ የሚገባ አንድ ትልቅ ቁም ነገር አለ። እሱም ይህን ድንቅ መፅሀፍ ማንበብ ጥቅሙ የሚጎላው ውስጡ ባዘለው መልእክትና አስተምህሮ የሰራንበት እንደሆነ ነው፡፡

ቁርአንን የማንበብ ፍሬዎች

1-    የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በመጥፎ ተምሳሌትነት ከገለጽዋቸው ሰዎች ከመሆን ያድናል

ኢብን አባስ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-

‹‹ ያ በውስጡ ከቁርአን አንዳች ነገር የሌለው (ምሳሌው) እንደ ወና ቤት ነው፡፡›› ቲርሚዚ

አቢ ሙሳ አል አሽዓሪይ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ባስተላለፉልን ዘገባ ተወዳጁ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለምእንዲህ ብለዋል፡-

‹‹ቁርአንን የሚቀራ አማኝ ምሳሌው ልክ እንደ ትርንጎ ነው፡፡ ትርንጎ መዓዛውም መልካም ጣዕሙም መልካም ነው፡፡ ቁርአንን የማይቀራ አማኝ ምሳሌው እንደ ቴምር ነው፡፡ ቴምር መዓዛ ባይኖረውም ጥፍጥናው ግን ልዩ ነው፡፡ ሙናፊቅ ሆኖ ቁርአንን የሚቀራ ሰው ምሳሌው እንደ አሪቲ ነው፡፡ አሪቲ መዓዛው መልካም ቢመስልም ጣዕሙ ግን መራራ ነው፡፡ እንዲሁም ሙናፊቅ ሆኖ ቁርአንን የማይቀራ ሰው ምሳሌው እንደ የቅል ፍሬ ነው፡፡ የቅል ፍሬ መዓዛም የለውም ጣዕሙም መራራ ነው፡፡›› ቡኻሪና ሙስሊም

2-   ቁርአንን በመቅራት ላይ የዘወተረ ሰው ደጋግ ሰዎች ከሚቀኑባቸው ተርታ ይሰላፋል

ከኢብን ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-

‹‹በሁለት ነገሮች ካልሆነ በስተቀር ቅናት የለም (አይፈቀድም)፡፡ (እነሱም) አላህ የቁርአን እውቀትን ሰጥቶት ቀን ከሌት በሱ የቆመበት (ሰላት የሰገደበት) ግለሰብ እንዲሁም አላህ ገንዘብ ሰጥቶት ቀን ከሌት ከሚመፀውት›› ቡኻሪና ሙስሊም

እዚህ ቦታ ላይ የተጠቀሰው ‹‹ቅናት›› ወንድምህ ዘንድ ያለውን መልካም ነገር ከሱ አንዳች ሳይቀነስ አልያም እንዲወገድበት ሳትከጅል ላንተም እንዲኖርህ መመኘት ማለት ነው፡፡

3-   ቁርአንን መቅራት በዚህኛውም ሆነ በቀጣዩ ዓለም ልቅናን የመጎናፀፊያ ምክንያት ነው፡፡

ዑመር ኢብኑል ኸጣብ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል በማለት ዘግበዋል፡-

‹‹አላህ በዚህ መፅሀፍ ህዝቦችን ከፍ ያደርግበታል ሌሎቹን ደግሞ ያዋርድበታል፡፡›› ሙስሊም

4-   ቁርአንን መቅራት መጀመርያውም መጨረሻውም በረከት ነው

አቡዘር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዲህ ይለናል፡-

‹‹አንቱ የአላህ መልእክተኛ ሆይ ምከሩኝ አልኳቸው፡፡ እንዲህም አሉኝ ‹አላህን በመፍራት ላይ አደራ እልሃለሁ ምክንየቱም አላህን መፍራት የነገሮች ሁሉ ቁንጮ ነውና፡፡› እኔም አንቱ የአላህ መልእክተኛ ሆይ ይጨምሩልኝ አልኳቸው፡፡ ‹ቁርአንን በመቅራት አደራ፤ እሱ በምድር ላይ ብርሀን በሰማይ ላይም መታወሻ ይሆንልሃልና፡፡› አሉኝ፡፡›› ኢብኑ ሂባን

‹‹በምድር ላይ ብርሀን ይሆንልሃል›› የሚለው ሀረግ ሁለት ትርጓሜዎች አሉት። አንደኛው ቁርአንን የሚያነብና በተግባር የሚያውል ሰው ከእንስሳዊ ማንነት ይላቀቃል ማለት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “መቀናት” ማለትም ወደቀጥተኛው መንገድ መመራት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አላህም እንዲህ ሲል ይህንን ሀሳብ ያፀናዋል፡-

قَدْ جَاءَكُم مِّنَ اللَّهِ نُورٌ وَكِتَابٌ مُّبِينٌ
 

“ከአላህ ዘንድ ብርሃንና ገላጭ መጽሐፍ በእርግጥ መጣላችሁ፡፡ (አል ማዒዳ 15)

ኢብን ዓባስ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዲህ ይላሉ፡- ‹‹የቁርአንን ቅን መስመር የተከተለ ሰው በዚህ ዓለም እንደማይጠምና በመጪውም ዓለም እድለ ቢስ እንደማይሆን አላህ ቃል ገብቷል፡፡›› በማስከተልም ተከታዩን የቁርአን አንቀፅ አነበቡ፡-

فَمَنِ اتَّبَعَ هُدَايَ فَلَا يَضِلُّ وَلَا يَشْقَىٰ
 

 “መሪየን የተከተለ አይሳሳትም አይቸገርምም፡፡ (ጣሃ 123)

ኢብኑ አቢ ሸይባ ዘግበውታል፡፡

‹‹በሰማይ ላይ መታወሻ ይሆንሀል›› የሚለው ሀረግ ሀሳቡ በመጪው ዓለም የጌታችን እዝነት፣ ምልጃና ጀነትን መገጠም ሊሆን ይችላል። በሌላ መልኩ ደግሞ አል መናዊ አላህ ይዘንላቸውና እንዳሉት ‹‹የሰማይ ባልደረቦች መላእክት ናቸው፡፡ እነሱም እያነበብከው ባለኸው ቁርአን ላይ ፅናትንና ዘውታሪነትን ላንተ ይለግስህ ዘንድ እርስ በርስ አላህን ይለምናሉ፡፡›› የአላህ መልእክተኛም ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በግልፅ እንደነገሩን አላህ ያስታውሳሀል።

5-   ቁርአንን ማንበብ ከዝህች ዓለምና በውስጧ ከያዘችው ነገር ሁሉ ይበልጣል፡፡

ዑቅባ ቢን ዐሚር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዲህ ይላሉ፡-

‹‹የአላህ መልእክተኛሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለምከእለታት በአንዱ ቀን ተሰብስበን ወደ ተቀመጥንበት መጡና እንዲህ አሉን፡- ‹ከናንተ ውስጥ ወደ ሜዳ ወጥቶ አልያም ወደ ኮረብታዎች ሄዶ በየእለቱ ባለሻኛ ግመል ቢሰጠውና ያለ አንዳች ወንጀልና ዝምድናን መቁረጥ ቢመለስ የሚወድ አለን;› ብለው ጠየቁ። እኛም ፡፡ ብለን መለስን፡፡ እሳቸውም ‹እንግዲያውስ አንዳችሁ ወደ መስጂድ ማልዶ በመሄድ ከአላህ ቃል ሁለት አንቀፆችን ቢያስተምር አልያም ቢቀራ ለሱ ከሁለት ግመሎች የበለጠ ነው፡፡ ሶስት አንቀፆችንም ቢያስተምር ከሶስት ይበልጥለታል፡፡ አራትም አንቀፅ ቢሆን እንደዛው፡፡ ባጠቃላይ ባስተማረውና በቀራው አንቀፅ ልክ ከግመሎቹ ይበልጣል፡፡› አሉን፡፡››ሙስሊም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here