“ተጅዊድ” የሚለው ቃል ጥሬ ትርጉም ማሻሻልና ትክክለኝነት እንደ ማለት ነው። አንድን ነግር በ“ተጅዊድ” ሰራኸው ማለት የመጨረሻ ውብና በጣም ትክክል አድርገህ ሰራኸው ማለት ነው። ይህ በቋንቋ ደረጃ ያለው ትርጉም ሲሆን በቁርኣን ንባብ ህግ ሳይንስ መሰረት ተጅዊድ ማለት የቁርኣን አነባብ ሳይንስን የሚመለከት ሆኖ ትክክለኛ አነባበብና የቁርኣን ፊደላትን፣ ቃላትን፣ አንቀፆችን ትክክለኛ ድምፀታቸውንና አነባበባቸውን ጠብቆ ማንበብ ነው። ቃሉ በቋንቋ ደረጃ እና በቴክኒክ ደረጃ ያለው ትርጓሜ ያላቸው ግንኙነት ግልፅ ነው። በቋንቋ ደረጃ ያለው ትርጓሜ ተግባራትን በትክክል መስራትን የሚመለከት ሲሆን በቴክኒካል ትርጓሜው (ኢስጢላህ) ቁርኣንን በአግባቡ መቅራት (ማንበብ) ማለት ነው።
በመጀመሪያዎቹ የኢስላም ዘመናት ከኢስላም ፈጣን መስፋፋት በኋላ- በተለይም አረብ ያልሆኑ ሙስሊሞች መሀል- ለቁርኣን ተማሪዎች ማጣቀሻ የሚሆን የተጅዊድ ህግጋት መጽሐፍት ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ። ስለዚህም ቁርኣንን በተጅዊድ ማንበብ ለሚፈልጉ ሁሉ መነሻ (ማጣቀሻ) የተጂዊድ መጽሐፍት ማየቱ ተገቢ ሆነ። ይህ ማለት ግን ያለ አስተማሪ እገዛ ቁርኣንን በተጅዊድ መጽሐፍ እገዛ ብቻ ማንበብ ይቻላል ማለት አይደለም። ብቸኛና ልዩ የሆነ ሰነድን መሰረት ያደረገና የተቀናጀ የተጅዊድና የቁርኣን ንባብ አስተምህሮት ታሪካዊ ሂደቱን እንደጠበቀ ለተማሪዎች እየተሰጠ ይገኛል። በዚህም ሰነድን መሰረት ባደረገው አስተምህሮት መሰረት ተማሪዎች ሙሉ ቁርአኑን በልባቸው (በቃላቸው) ሙሉ የተጅዊድ ህጎቹን ጠብቀው ከመነሻው እስከ መድረሻው ቁርኣን የማስቀራት ፍቃድ ባለው ብቁ የቁርኣን አስተማሪ ላይ ቁርኣንን በማንበብ ቁርኣን የማንበብ የማስተማር ፍቃድ ይሰጣሉ። ይህ ፍቃድ “ኢጃዛ” ተብሎ ይታወቃል። ትክክለኛ የሆነ ኢጃዛ ከነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጀምሮ እስከ ግለሰቡ ድረስ የነበሩ ፍቃዱ የተሰጣቸውንና የሚሰጡ ግለሰቦችን ስም ዝርዝር የያዘ ነው።
በሙሁራን ትርጓሜ መሰረት ተጀዊድ ማለት፣ ሁሉንም የቁርኣን ፊደሎች ከትክክለኛ ቋሚ መውጫ ቦታዎች ማውጣት እንደዚሁም ተለዋዋጭ የሆኑትን ፊደላትም እንደየሁኔታዎች አስገዳጅነት ከትክክለኛ ቦታቸው ማውጣት ነው። ቋሚ ቦታዎች በሚለው ማመላከት የተፈለገው ፊደላት ከዚህ ቦታቸው ካልወጡ በስተቀር በትክክለኛ ድምፀት ሊቀሩ እንደማይችሉ ለማሳየት ነው። ተለዋዋጭ ባህሪ ያላቸው ፊደላት የተባሉት ፊደላቱ በሚያርፋባቸው ሀረካ፣ ከተቀመጡበት ቦታ፣ ከሌሎች የድምፀት ባህሪያቸውን ሊቀያይሩ ከሚችሉ ፊደላት ጋር ያላቸው አቀማመጥ ቅደም ተከተል ጋር ተያይዞ ድምፀታቸው የሚቀያየሩ ናቸው።
ዋና ዋና ተጠቃሽ የተጅዊድ መጽሐፎች የቁርኣን ማንበብን አስፈላጊነት እና አነባብ ስርዓት በማስተዋወቅ የትክክለኛ አነባበብ ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎች፣ ቁርኣንን በተጅዊድ መቅራት ከኢስላማዊ ህግጋት አንፃር እንዴት እንደሚታይና የቁርኣን አነባበብ ዓይነቶች ከአነባበብ ፍጥነት አንፃር በስንት እነደሚከፈሉ በማስተማር ትምህርታቸውን ይጀምራሉ። ከላይ የተገለፁት ትርጓሚዎች በግልፅ እንደሚያስቀምጡት የተጅዊድ ዋናው አካል ቁርኣንን በአግባቡ ማንበብ ነው። ይህም በሚከተሉት መሰረታዊ ነጥቦች በጥልቀት ይዘረዘራል።
- የፊደላት መውጫ ቦታ (መኻሪጀል ሁሩፍ)
- የፊደላት ባህሪያት (ሲፈቱል ሁሩፍ)
- ሌሎች የተጅዊድ ህጎች፡- ለምሳሌ የተወሰኑ ፊደሎች በቃል ውስጥ ያረፉበት ቦታና በዙሪያቸው ካሉ ቃላቶች አንፃር የድምፀት ለውጥ መቀየር ይከሰትባቸዋል። ሳድስ የሆኑ “ሚም” እና “ኑን” ፊደሎችን ህግ እዚህ ላይ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል (አህካሙ ኑን ወልሚም አስ-ሳኪናህ)።
የሥነ-ድምፅ (Phonetics) ተማሪዎች እነዚህ ርዕሰ አንቀፆች የተለመዱና ከትምህርታቸው ጋርም ተመሳሳይ ሆነው ያገኟቸዋል። ለምሳሌ የ “ኢድጋም” ጭብጥ ሀሳብ ውህደት (Assimilation) ከሚለው የሥነ-ድምፅ ጭብጥ ሃሳብ ጋር ይመሳሰላል።
ቁርኣን በሚነበብበት ጊዜ የተጅዊድን ህጎች ጠንቅቆ ማየቱ ግዴታ መሆኑን የተጅዊድ ሙሁራን ይገልፃሉ። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-
“ቁርኣንንም በዝግታ ማንበብን አንብብ።” (አል-ሙዘሚል 73፤ 4)
አንቀፁ ቁርኣንን በዝግታና አላህን በመፍራት ማንበብንና የሚሳበውን በመሳብ (መድ አል-ሙዱድ) የሚያጥረውን በማሳጠር (ቀስር አል-ቁሱር) መቅራትን ይገልፃል። ከላይ የተጠቀሰው አንቀፅ በትዕዛዝ መልክ (ዐምር) የተነገረ በመሆኑ የተጅዊድን ግዴታነት (ዋጂብ) ያመለክታል። ከዚህ ውጭም አንቀፁ ሊያመላክት ያለመው ሌላ ሀሳብ የለም። (አል-መርሳፊ፣ ሂዳየቱል ቃሪእ ኢላ ተጅዊድ ፊ ከላም አል-ባሪ)
ከጥንታዊያን የተጅዊድ ሙሁራኖች መካከል አንዱ የሆኑት ኢማም ኢብኑል ጀዘሪ “ቱህፈቱል አጥፋል” በሚለው ታዋቂ የጀማሪዎች ተጅዊድ መፅሐፋቸው እንደገለፁት “የተጅዊድን ህግ ማጥናቱ ግዴታ ነው። እነዚያ ይህን ህግ ሳያዩ ቁርኣንን አላግባብ የሚያነቡ ሰዎች ወንጀል እየፈጸሙ ነው። ቁርኣንን ያወረደልን አላህ (ሱ.ወ) ነው። የተተላለፈልን ደግሞ በተጅዊድ ህግ መሰረት ነው። ስለሆነም ተጅዊድን ማጥናት ግዴታ (ዋጅብ) ነው።” ይላሉ።
ይሁንና ሌሎች ሙሁራኖች የቁርኣን ቃላቶች በትክክል እስከተነበቡ ድረስ፣ ስህተት እስካልሆኑ ድረስ፣ የተጅዊድን ህግ መከተሉ ይወደዳል (ሙስተሃብ) እንጂ ግዴታ (ዋጂብ) አይደለም ይላሉ። የሆነ ሆኖ ቁርኣንን በተቻለ አቅም በአግባቡ ለማንበብ መሞከር በሁሉም ሙስሊም ላይ ተገቢ የሆነ ነገር ነው። ዓኢሻ (ረ.ዐ) ከነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) ይዘው እንደዘገቡት፡-
“ቁርኣንን ፍፁም ቆንጆ አድርጎ የሚቀራ ከተከበሩ ታማኝ መላኢካዎች ጋር ነው። ቁርኣንን እየከበደውና እየተንገታገተ የሚቀራ ሰው እጥፍ ምንዳ ይመነዳል።” (ቡኻሪና ሙስሊም)
ተጅዊድ አላህ (ሱ.ወ) ቁርኣንን ከየትኛውም ብረዛ የተከላከለበት አንዱ መገለጫ ነው። የተጅዊድ መጽሐፎች በምንቃኝበት ጊዜ ለጥቃቅንና ዝርዝር የቁርኣን የአነባበብ ስልቶች የተደረገውን ትልቅ ጥንቃቄ እናያለን። ይሄ ሁሉ የሚያመላክተው ከዛሬ 14 ክፍል ዘመናት በፊት በነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጊዜ ቁርኣን ይነበብበት በነበረው መልኩ ዛሬም ምንም ሳይቀየር እንደሚነበብ ነው። የሰነድ ሰንሰለትን መሰረት ካደረገው የቁርኣን አነባበብ ያለመበረዝ ዋስትና በተጨማሪም ከፍተኛ ጥራትንና ትክክለኝነትን ባረጋገጠ መልኩ የተጅዊድ ህጎች ከአንድ ተውልድ ወደ ሌላ ትውልድ በተግባራዊ አነባበብ ስልት ቃል በቃል ይተላለፋሉ።
በአጠቃላይ ተጅዊድ ከመነሻው ቁርኣንን ለማገልገልና ከብረዛ ለመጠበቅ ከተቋቋሙት ሳይንሶች አንዱ ነው። ሌሎች በዚህ መስክ እንደ ቂራኣት (የአነባብ አይነቶች) እና አር-ረስም ወድ-ዶብጥ (የቁርኣን አጻጻፍ) ተጠቃሽ የቁርኣን ሳይንሶች ናቸው።
*****