“ይህን ነፍሳችንን (እራሳችንን) ብንመግብ ኖሮማ፤ አሳዋም ባልወጣች ነበር።”

3
8136

የታሪኩ ባለቤት፦ “አቡ ናስር አስ-ሰያድ”

በጣም አስተማሪ ታሪክ ነው። ይህን ታሪካዊ ክስተትም የሚተርኩልን  “አህመድ ኢብኑ ሚስኪን” ይባላሉ። ታቢኢይ ሲሆኑ በዘመኑ ከነበሩ ዛሂዶች መካከል ይገኙበታል። እርሳቸውም የታሪኩ አካል ነበሩና ታሪኩን እንዲነግሩን ለርሳቸው እንተውላቸው። . . .

እንዲህ ይላሉ . . .

“በአንድ ከተማ ውስጥ ‘አቡ ናስር አስ-ሰያድ’ የሚባል ሰው ከሚስቱ እና ከልጁ ጋር ይኖር ነበር። ታዲያ ከእለታት አንድ ቀን በጣም ተጨንቆና ሀሳብ ገብቶት ከቤቱ ወጥቶ መንገድ ይጀምራል። ባለቤቱና ልጁ በረሀብ አለንጋ እየተሰቃዩ መሆኑን ያስተዋለው ይህ ሰው፤ አላህን ከዚህ ጭንቅ እንዲያወጣውና ሀላል የሆነ ርዝቅ (ሲሳይ) እንዲለግሰው ይጠይቃል። በዚህ ሁኔታ ሳለ ‘አህመድ ኢብኑ ሚስኪን’ ከተባሉ አዋቂ (ሼኽ) ዘንድ ሲደርስ እንዲህ አላቸው።

“አለቃዬ! እጅግ በጣም ተቸግሪያለው፤ . . . ” (ምን ይሻለኛል ለማለት የፈለገ ይመስላል)

የአቡ ናስር አስ-ሰያድን ችግር የተረዱት እኚህ ሼኽ አህመድ ኢብኑ ሚስኪን ነበሩና ከተቀመጡበት ተነስተው ወደ ባህር ዳርቻ ተከተለኝ ብለው ይዘውት ሄዱ። ቦታው ላይ ሲደርሱም የዚህን ወጣት ክጃሎት ከአላህ ብቻ እንዲሆን በማሰብ እንዲህ አሉት።

“(አሳ የማጥመድ) ሂደቱ ገር እንዲሆንልህ አስበህ ሁለት ረከዓ ሰላት ስገድ፤ አላህንም ጥሩና ሀላል የሆነውን ሲሳይ እንዲቸርህ ጠይቀው።” አቡ ናስርም ያዘዙትን እንዳሉት ፈጸመ። በመቀጠልም . . .

“የአላህን ስም አውሳ፤ ሁሉ ነገር በአላህ ይሁንታ ነው” በል። አሉት። እሱም ያሉትን ሁሉ ካደረገ በኃላ የአሳ ማስገሪያ መረቡን ወደ ባህሩ ላይ ወረወረ።

ይህ አጋጣሚ ለአቡ ናስር አስ-ሰያድ መልካም ነበር። የወረወረው መረብ ትልቅ አሳ ይዞ ወጣ። ሼኹም . . .

“በል አሳውን ሽጠውና ለቤተሰብህ የሚሆን ቀለብ ግዛበት” ብለው ሸኙት።

የሼኽ አህመድ እብኑ ሚስኪንን ምክር በመስማት ወደ ገበያ ቦታ አሳውን ይዞ ሄደ። ሸጠውም። በምትኩም በስጋና በሀላዋ የተሰሩ ሁለት ፈጢራዎችን ገዛ። ከገዛ በኃላ ግን አንድ ነገር ወሰነ። እሱም ሼኹ ላደረጉለት መልካም ውለታ ምስጋና ይሆንለት ዘንድ አንዱን ፈጢራ ሊሰጣቸው በማሰብ እርሳቸው ዘንድ ሄደ። ግና ሼኹ . . .

“ይህማ ላንተና ለቤተሰብህ ነው።” በማለት እንደማይቀበሉት ነገሩት። በተጨማሪም እንዲህ አሉት፦ “ይህን ነፍሳችንን (እራሳችንን) ብንመግብ ኖሮማ አሳዋም ባልወጣች ነበር።”

አቡ ናስር አስ-ሰያድ ሼኽ አህመድ ኢብኑ ሚስኪን እንደማይቀበሉት ሲነግሩት የገዛቸውን ሁለት ፈጢራዎች ይዞ ወደ ቤቱ ሲያቀና መንገድ ላይ ሌላ ነገር ተከሰተ። አንዲት እናት እና ልጇ በረሀብ የተነሳ ተጎሳቁለው ሲያለቅሱ ያገኛቸዋል። ይህን የተመለከተው አቡ ናስር እጆቹ ላይ ወዳሉት ፈጢራዎች ተመለከተ። በውስጡም እንዲህ አለ፦ . . .

“ይህች ሴትና ልጇ ማለት ልክ እንደኔ ሚስትና ልጅ ናቸው። . . . በረሀብ እየታረዙ ነው። . . . ታዲያ ምን ባደርግ ይሻለኛል?” ይህን በአይነ ህሊናው እያብሰለሰለ ሳለ ከእናትየው ዓይን የሚወርደውን እንባ ሲያይ ልቡ አላስችል አለው። እናም በእጁ የያዛቸውን ፈጢራዎች “እነዚህ ፈጢራዎች ለእናንተ ናቸው።” በማለት ሰጣቸው። ይህን እንዳደረገ የእናትየው ደስታ ከፊቷ ላይ ይነበብ ነበር። ልጇም ከደስታ ብዛት ሲቦርቅ ተመለከተ።

አቡ ናስር ምንም እንኳ ደስታቸውን ማስገኘት መቻሉን ቢመለከትም ቅሉ የሚስቱንና የልጁን ሁኔታ ዳግም እያሰበ ጭንቅ ይዞት መንገዱን ቀጠለ። በዚሁ አጋጣሚ ታዲያ አንድ አስገራሚ ሁኔታ ተፈጠረ። እሱም አንድሰው “አቡ ናስር አስ-ሰያድን እምታውቁ አመላክቱኝ፤ የቱ ነው?” እያለ ሲጣራ ሰማ። ሰዎችም ወደ አቡ ናስር አስ-ሰያድ ጠቆሙትና አገኘው። ሰውዬውም አቡ ናስር ዘንድ ሲደርስ እንዲህ አለው፦ . . .

“ከ20 ዓመታት በፊት አባትህ ገንዘብ አበድሮኝ ነበር። ሆኖም ብድሩን ሳልመልስለት ሞተ። . . . እንካ . . . ይሄ ሰላሳ ሺህ ዲርሀም የአባትህ ገንዘብ ነው። ተቀበለኝ።” አቡ ናስር አስ-ሰያድም በክስተቱ እየተገረመ ገንዘቡን ተቀበለ።

አቡ ናስር አስ-ሰያድ ከዚህ ክስተት በኃላ ያጋጠመውን ነገር እንዲህ ይተርክልናል፦ . . .

“ከዛች ቀን በኃላ ሀብታም ሆንኩኝ። በአላህ ፍቃድም ሀብቴ ይበልጥ በረከተ። የራሴ ቤት ኖረኝ፣ ንግዴም ተትረፈረፈ። ብሎም ለአላህ ምስጋና ይሆንልኝ ዘንድ በአንድ አጋጣሚ ብቻ እስከ አንድ ሺህ ዲርሀም ሰደቃ ማውጣት ጀመርኩ። ይህንን እያደረኩም በራሴ እስክገረምና እስክደነቅ ድረስ ሰደቃ እየሰጠሁ ብዙ ጊዜያት ነጎዱ።”

“በእንዲህ ሁኔታ ላይ ሳለሁ ከእለታት አንድ ቀን ሌሊት ላይ ህልም አየሁ። እሱም ሚዛን ቀርቦ አንድ  ተጣሪ ‘አቡ ናስር አስ-ሰያድ’ የመልካም እና መጥፎ ስራህ ይመዘን ዘንድ ወደዚህ ና ተባልኩኝ። በማስከተልም መልካም ስራዬ ቀርቦ በአንድ በኩል መጥፎ ተግባሬም እንዲሁ በሌላኛው የሚዛኑ ክፍል ተቀመጡ። . . . ወይ ጥፋቴ . . . መጥፎ ስራዬ ሚዛን ደፋ።

ይህን ስመለከት ‘ያ . . . ሰደቃ እሰጥ የነበረው ገንዘቤስ . . . የታለ።’ አልኩኝ።. . .

‘አምጡት እና አስቀምጡለት ተባለ’ . . . ግና ከእያንዳንዱ አንድ ሺህ ዲርሀም ስር ምንም ክብደት ያለው እማይመስል ነገር ግን (ሸህዋ) ስሜትና በራስ መገረም ተመለከትኩ። በዚህም ምክንያት የመጥፎ ስራ ሚዛኔ አደፋ። አለቀስኩ፤ . . . እራሴን እማጣ እስኪመስል ድረስ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ።

‘ከዚህ ማጥ መዳኛው ምንደን ነው? . . . ‘እንዴት ነው እምድነው?’ ብዬ ማልቀሴን ቀጠልኩ።

እንዴት የሰው ልጅ ብዙ ገንዘቡን፣ ጊዜውንና ሀይሉን አውጥቶ በከንቱ ስሜት ምክንያት አኼራውን ይከስራል! እንዴትስ የአዛኞችን ሁሉ አዛኝ የሆነውን የአላህን ውዴታ እንዲነፈግ ሰበብ ይሆናል!

በመሀል አንድ ተጣሪ . . .

“ከዚህ ውጪ ሌላ የሚቀረው ነገር አለ?” ብሎ ሲናገር ሰማሁት። ሌላ መላእክ . . .

“አዎ! ሁለት ፈጢራዎች ይቀሩታል።” ብሎ መለሰ። ከመልካም ስራ ሚዛኔ ላይ ተደረጉ። በዚህም ምክንያት ቀሎ የነበረው ሚዛኔ ከመጥፎው ስራዬ ጋር እኩኩል ሆነ። ቢሆንም . . .  አሁንም በፍራቻ እንደተዋጥኩኝ ነኝ። . . . በድጋሚ ተጣሪው “ከዚህ ውጪ ሌላ የሚቀረው ነገር አለ . . . ?” በማለት አስተጋባ። መላእኩም . . .

“አዎ!  . . . አለ!” በማለት መለሰ። እኔም “ምን ይሆን . . . ?” ብዬ አስብ ጀመር።

“ሁለቱን ፈጢራዎች ለዛች እናት በሰጠሀት ቅጽበት ከዓይኖቿ ይወርድ የነበረው እንባ ነው።” ተባልኩ። . . . ከመልካም ስራ ሚዛኔ ላይም ሲቀመጥ እንደ አንድ ግዙፍ አለት ከበደ። የመልካም ስራ ሚዛኔ ይበልጥ ጨመረ። ይህን ስመለከት እጅግ በጣም ተደሰትኩ።

አሁንም በድጋሚ ያ . . . ጥሪ ተስተጋባ። “ከዚህ ውጪ ሌላ የሚቀረው ነገር አለ?” . . . ምላሹም “አዎ . . . !” ነበር። እሱም ያቺ እናት ለልጇ ፈጢራውን ስትሰጠው ፊቱ ላይ ይታይ የነበረው ፈገግታ ነው።” ተባለ። አሁንም ይኸው የመልካም ስራ ሚዛኔ ላይ ተጨመረ። ይበልጥ ወደታች . . . ወደታች . . . ወደታች ማመዘኑን ሳያቆም መውረድ ጀመረ። የመልካም ስራ ሚዛኔ እጅጉን አመዘነ።

የተጣሪው ድምጽ ይህን ማለት ጀመረ፦

“በርግጥ ድኗል! . . . ስኬታማ ሆኗል . . . !”

በዚህ የደስታ ሰመመን ውስጥ ሳለሁ  እኚያ ሼኽ አህመድ ኢብኑ ሚስኪን ፈጢራውን አልቀበልም ያሉኝ ጊዜ የተናገሩትን ቃል እየደጋገምኩ ድንገት ከእንቅልፌ ብንን አልኩኛ።

 “ይህን ነፍሳችንን (እራሳችንን) ብንመግብ ኖሮማ፤ አሳዋም ባልወጣች ነበር።”

. . . . ተፈጸመ . . . .

አዎ. . . ትክክል ብለዋል . . . !

የሼኹን አባባል ምን ለማለት ፈልገው እንደሆነ ወድ አንባቢው ለመገንዘብ እንዲሞክር እየጠቆምኩ፤ ግና አንድ መሰረታዊ አስተምህሮ ለማንሳት ልሞክር።

አንድ ሰው በሚሰራቸው ስራዎች ትልቀትና ስፋት ተታሎ የሚሰራበትን አላማ ፍጹም መዘንጋት  የለበትም። ከታሪኩ እንዳየነው በመጠን ትንሽ ቢሆንም እንኳ በኢኽላስ ያሸበረቀ ተግባር ምንም ያህል ግዙፍ ቢሆንም ቅንጣት ያህል የነፍስያ ብጥስጣሽ ከተቀላቀለበት ተግባር በጣም ብልጫ አለው። ብሎም የመጀመሪያው የጭንቅና የፈተና ሰዓት ጋሻ ሲሆን ሁለተኛው ዓይነት ተግባር ግና ለጥፋትና ለክስረት ሰበብ መሆኑ አይቀሬ ነው። እናም ታብዒዩ ሼኽ አህመድ ኢብኑ ሚስኪን የተናገሩትም ነገር ከዚህ ብዙ የራቀ  አይደለም። ለአላህ ብለን የሰራነውን ተግባር በቅጽበታዊ ደሞዝ ወይም ከፍጡራን በሚገኝ ተራ ስጦታ አልያም ክፍያ የምንለውጥ ከሆነ ታላቁን ውዴታና የፍጡራን ባለቤት ከሆነው አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ የሚያርቅ ተግባር መሆኑ አይቀሬ ነው። ታዲያ ጥፋት ማለት ይሄ አይደል . . . ? ክስረት ማለት ይህ አይደለምን  . . .? እንዴት የሰው ልጅ ብዙ ገንዘቡን፣ ጊዜውንና ሀይሉን አውጥቶ በከንቱ ስሜት ምክንያት አኼራውን ይከስራል! እንዴትስ የአዛኞችን ሁሉ አዛኝ የሆነውን የአላህን ውዴታ እንዲነፈግ ሰበብ ይሆናል!

አላህ ይጠብቀን! አላህ ስራችንንም መጨረሻችንንም ያሳምርልን። አሚን!

3 COMMENTS

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here