ህይወት ከቁርኣን ጋር

3
7136

ነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ከመላካቸው በፊት በመካና በዙሪያዋ የሚኖሩ የዐረብ ምድር ህዝቦች በመሃይምነት ጨለማ ውስጥ የሚደናበሩ ሆነው እናገኛለን።

መለኮታዊው ራእይ ቁርኣን ደረሠና ከድቅድቁ ጨለማ ውስጥ አወጣቸው፤ ወደ መጠቁ ዘመናዊና ንቁ ህዝቦች አሸጋገራቸው።

ቁርአን ምንጊዜም ህያውና ዘላለማዊ የሆነ የአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ቃል ነው። የአላህ ጥበቃ ስላልተለየው በርካታ ዘመናትን ተሻግሮ ሣይከለስ ሣይበረዝ ዛሬም ድረስ በመካከላችን ይገኛል። ቁርኣን ላወቀው፣ ላስተነተነውና ለሚሠራበት ሁሉ በማንኛውም ዘመንና ቦታ ጥቅሙ ከፍተኛ ነው። በሱ የፈረደ በፍትህ ፈረደ። በሱ የተናገረ እውነት ተናገረ። በሱ የታከመ አስተማማኝ ጤናን አገኘ። በቁርኣን ውስጥ የቀደሙን ህዝቦች ታሪክ አለ። ወደፊት ስለሚሆኑ ክስተቶችም ትንበያ አለ። ከፊት ለፊታችን ስለሚጠብቀን ስለ ታላቁ የትንሣኤ ቀን ምልክቶችና በውስጡ ስለሚከሰቱት አስፈሪና አስደንጋጭ ሁኔታዎችንም ይዟል።

ቁርኣን ውሽትና እውነትን መለያ ነው። ስህተትንና ትክክሉን ማሣወቂያም ነው። ቁምነገር ነው ቀልድ አይደለም። ቁርኣን የማይበጠስ የሆነ የአላህ ገመድ ነው። አላህንም ለማወቅ የሚረዳ ትክክለኛው መንገድ ነው። የሰው ልጅ ስሜቶችና ፍላጎቶች አያሸንፉትም። የብልሃትና የደመ ነፍስ ሰዎች እሱን ለመቀየር አይቻላቸውም። ፍጥረታት ሁሉ ተሠባስበው አምሣያውን እናምጣ ቢሉ ፈፅሞ አይችሉም። ዑለማኦች ከሱ አይጠግቡም። ተማሪዎች ከእውቀቱ ጨልፈው አይጨርሱም። ደጋግመው ቢያነቡት አይሠለችም። በጊዜ ብዛት አያረጅም። ትንግርቱ በዘመን ብዛት ተነግሮ አያልቅም። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

سَنُرِيهِمْ آيَاتِنَا فِي الْآفَاقِ وَفِي أَنفُسِهِمْ حَتَّىٰ يَتَبَيَّنَ لَهُمْ أَنَّهُ الْحَقُّ أَوَلَمْ يَكْفِ بِرَبِّكَ أَنَّهُ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ شَهِيدٌ

“እርሱም (ቁርኣን) እውነት መሆኑ ለነርሱ እስከሚገለፅላቸው ድረስ በአፅናፎቹ ውስጥና በነፍሦቻቸውም ውስጥ ያሉትን ታምራቶቻችንን በርግጥ እናሣያቸዋለን። ጌታህም እርሱ በነገሩ ላይ ሁሉ አዋቂ መሆኑ አይበቃቸውምን!” (ፉሲለት 41፤ 53)

በሌላ የቁርኣን አንቀፅም እንዲህ ይላል

وَقُلِ الْحَمْدُ لِلَّهِ سَيُرِيكُمْ آيَاتِهِ فَتَعْرِفُونَهَا
 

“ምስጋናም ለአላህ ነው። ተዓምራቶቹን ወደፊት ያሳያችኋል። ‘ታውቋትምአላችሁ’ በላቸው።” (ነምል 27፤ 93)

ይህም ማለት ምልክቶቹንና ሀያል ችሎታውን ታውቃላችሁ ማለት ነው። አስከትሎም

وَمَا رَبُّكَ بِغَافِلٍ عَمَّا تَعْمَلُونَ

“ጌታህም ከምትሠሩት ሁሉ ዘንጊ አይደለም።” (ነምል 27፤ 93) ይላል።

በዚህም ንግግር ውስጥ አላህ ተቆጣጣሪያችን እንደሆነና ከእይታው ያልራቅን ስለመሆኑ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ አዘል መልእክትና ማስፈራሪያ አለበት።

ቁርኣን ቀልብን ህያው ያደርጋል

ቁርኣን የሞተን ቀልብ ህያው ያደርጋል። ውሃ መሬት ከሞተች በኋለ ነፍስ እንደሚዘራባትና አዝመራን እንደሚያበቅል ሁሉ ህይወት የሌላትንም ሰውነት ሩህ ይመልስባታል። ቁርኣን የወረደው ከሰማይ ነው። ይህ ከሰማይ የወረደ የአላህ ራህመት ልብን ባገኘ ጊዜ ልብ ትፍታታለች፣ ዘና ትላለች፣ ትደሠታለች፣ ነፍስ በመዝራትም መንቀሣቀስ ትጀምራለች። በተቃራኒው ደረቅ ቀልብ ግን እንደ አለት ናት አንዳችም ህይወት የላትም። ቁርኣን አያለዝባትም።

أُوْلَئِكَ فِي ضَلالٍ مُبِين  
“እነሱም ግልፅ በሆነ ጥመት ውስጥ ናቸው።” ይላል አላህ። ህይወት ያላትና የሌላት ቀልብ በምንም መልኩ ፈፅሞ ሊወዳደሩ አይችሉም። በመካከላቸው ያለው ልዩነት እጅግ ሰፊ ነው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ፡-

أَوَمَن كَانَ مَيْتًا فَأَحْيَيْنَاهُ وَجَعَلْنَا لَهُ نُورًا يَمْشِي بِهِ فِي النَّاسِ كَمَن مَّثَلُهُ فِي الظُّلُمَاتِ لَيْسَ بِخَارِجٍ مِّنْهَا كَذَٰلِكَ زُيِّنَ لِلْكَافِرِينَ مَا كَانُوا يَعْمَلُونَ

“ሙት የነበረና ህያው ያደረግነው ለርሱም በሰዎች መካከል በርሱ የሚሄድበትን ብርሃን ያደረግንለት ሰው በጨለማዎች ውስጥ ከርሷ የማይወጣ ሆኖ እንደለ ሰው ቢጤ ነውን? እንደዚሁ ለከሀዲዎች ይሠሩት የነበረ ነገር ተጌጠላቸው።” (አል አንዓም 6፤122)

በሌላ አንቀፅም ቁርኣን የያዙ ሰዎች ትልቅ ብርሃንና መመሪያ እንደያዙ ሲገልፅ እንዲህ ይለናል፡-

وَكَذَٰلِكَ أَوْحَيْنَا إِلَيْكَ رُوحًا مِّنْ أَمْرِنَا مَا كُنتَ تَدْرِي مَا الْكِتَابُ وَلَا الْإِيمَانُ وَلَٰكِن جَعَلْنَاهُ نُورًا نَّهْدِي بِهِ مَن نَّشَاءُ مِنْ عِبَادِنَا وَإِنَّكَ لَتَهْدِي إِلَىٰ صِرَاطٍ مُّسْتَقِيمٍ

“እንደዚሁ ከትእዛዛችን ሲሆን መንፈስን ወዳንተ አወረድን፤ መፅሃፍም እምነትም ምን እንደሆነ የምታውቅ አልነበርክም፤ ግን (መንፈሱን) ከባሮቻችን የምንሻውን ሰው በርሱ የምንመራበት ብርሃን አደረግነው። አንተም ወደ ቀጥተኛው መንገድ በርግጥ ትመራለህ።” (ሹራ 42፤ 52)

የህይወት መሠረቱ ሩህ ነው። ሩህ ከሌለች ህይወት የለም። ብርሃን ጨለማን ይገፋል። በሱም አንፀባራቂ የሆነ ወገግታ ይገኛል። ህያው ሊባሉ የሚችሉትም ሰዎች ቁርኣንን በመተግበር ዘውታሪ የሆኑት ናቸው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

لِّيُنذِرَ مَن كَانَ حَيًّا وَيَحِقَّ الْقَوْلُ عَلَى الْكَافِرِينَ

“እሱ መገሰጫና ግልፅ የሆነ ቁርኣን እንጂ ሌላ አይደለም። ሕያው የሆነነን ሰው ሊገስፅበት።” (ያሲን 36፤70)

ከሃዲያን ግን ሙታኖች ናቸውና አይሰሙም። ይህ ማስጠንቀቅያም ጠቃሚነቱ ለህያውያን እንጂ ለነሱ አይደለም። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا اسْتَجِيبُوا لِلَّهِ وَلِلرَّسُولِ إِذَا دَعَاكُمْ لِمَا يُحْيِيكُمْ

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! መልእክተኛው ህያው ወደሚያደርጋችሁ ነገር በጠራችሁ ጊዜ ለአላህና ለመልእክተኛው ጥሪ ምላሽ ስጡ።” (አል አንፋል 8፤ 24)

ትክክለኛ ህይወት የሚገኘው ለአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላና ለመልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም በመታዘዝ ነው። ከቁርኣን ጋር የሚኖር ቀልብ እሱ ምንጊዜም ህያው የሆነ ቀልብ ነው። በውስጡ ቁርኣን የማይቀራበት ቤትና ኦና/ባዶ ቤት ሁለቱም ባዶ በመሆናቸው ተመሣሣይ ናቸው። በሀዲስ እንዲህ የሚል ዘገባ ተላልፏል።

إن الرجل الذي ليس في جوفه شيء من القرآن كالبيت الخرب. الترمذي

“በሆዱ ውስጥ ከቁርኣን አንዳችም ነገር የሌለው ሰው እንደ ባዶ ቤት ነው።” (ቲርሚዚ)

በሌላም ሀዲስ ነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም እንዲህ ብለዋል

وإن القلب الذي ليس فيه من كتاب الله شيء، خرب كخراب البيت الذي لا ساكن له. الدارمي

“ከአላህ ኪታብ አንድም ነገር ውስጡ የሌለ ሰው ነዋሪ እንደሌለው ቤት ባዶ ነው።” (ዳሪሚ)

ቁርኣን አላህ እኛን ሥርኣት የሚያስይዝበት መመሪያ ነው። በሀዲስ

ليس من مؤدب إلا وهو يحب أن يؤتى أدبه وإن أدب الله القرآن. الدارمي

“አንድም ሥርኣት የሚያስተምር አካል የለም ያስተማረው ሥርኣት ተግባር ላይ እንዲውልለት የሚወድ ቢሆን እንጂ። የአላህ ሥርኣት ማስያዣ ቁርኣን ነው።” (ዳሪሚ) ተብሏል። በመሆኑም አላህ እንዲወደን የምንሻ ከሆነ በአላህ ቁርኣን መኖርና መመራት ይኖርብናል። የአላህ መልእክተኛ ሰላሁ ዐለይህ ወሠለም ባህሪያቸው ቁርኣን ነው።

ቁርኣን መቅራት (ማንበብ)

የሰው ልጆች ቁርኣን በሚቀሩበት ወቅት ድምፃቸውን ለማሣመር፣ የአቀራር ሥልታቸውን ጥሩ ለማድረግና ለፊደል አወጣጥም ጭምር እጅግ ሲጨናነቁ እለንያሉ። ይህ በርግጥም ማለፊያና ወሣኝ ነገር ቢሆንም ከዚህ በበለጠ ሊያሣስብ የሚገባው ነገር ቁርኣንን በጥልቀት ማወቅ፣ ማስተንተንና በመመሪያዎቹ መሥራቱ ነው። አብዛኛው የዛሬ ሰው በቁርኣን ከመሥራት ይልቅ በማንበቡ ላይ ብቻ ተወስኗል። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ለሰዎች የቁርኣንን መልእክት ለሌሎች ማድረስ የፈለጉ እንደሆነ ሰዎች በትክክል ይገባቸው ዘንድ እየቆራረጡና እየቆሙ ያነቡላቸው ነበር። ግልጽ ባለና ፊደል በፊደል በሚለይ መልኩም ያነቡላቸዋል። ይህም ሰዎች እንዲመከሩበትና ያስተነትኑት ዘንድ ያግዛቸዋል። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

وَقُرْآنًا فَرَقْنَاهُ لِتَقْرَأَهُ عَلَى النَّاسِ عَلَىٰ مُكْثٍ وَنَزَّلْنَاهُ تَنزِيلًا

“ቁርኣንን በሰዎች ላይ በዝግታ ላይ ሆነህ ታነበው ዘንድ ከፋፈልነው። ቀስ በቀስ ማውረድንም አወረድነው።” (አል-ኢስራእ፤ 106)

ይህም ማለት ቁርኣን በረጅም ጊዜ ውስጥ አንቀፅ በአንቀፅ፤ በምእራፍ በመከፋፈልና ለንባብ እንዲቀል በቀስታና ጊዜ በመውሰድ የወረደ መሆኑን የሚገልፅ ሲሆን ይህም በቀላሉ ለመገንዘብና በጥንቃቄ በቃል ለማስቀመጥ ይረዳል። ቁርኣን ሙሉ በሙሉ በአንድ ጊዜ ሣይሆን እየተቆራረጠና በክፍፍል የወረደ መሆኑን ያሣየናል። ሁሉንም ግዴታዎች ለማሣወቅ በአንድ ጊዜ የወረደ ቢሆን ኖሮ ሰዎች ከትግበራው በሸሹ ነበር፣ መተግበሩም ይከብዳቸው ነበር። እዚህ ላይ ቂርኣት /ማንበብ/ ሲባል ዝም ብሎ ሽምደዳና ሩጫ ብቻ ሣይሆን በማስተንተን በመገንዘብ መሆን ይኖርበታል። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

كِتَابٌ أَنزَلْنَاهُ إِلَيْكَ مُبَارَكٌ لِّيَدَّبَّرُوا آيَاتِهِ وَلِيَتَذَكَّرَ أُولُو الْأَلْبَابِ

“ይህ ወዳንት ያወረድነው ብሩከ መፅሃፍ ነው። አንቀፆቹን እንዲያስተነትኑና የአእምሮዎች ባለቤቶችም ይገሠፁ ዘንድ” (ሷድ፤ 29)

ይህም ማለት ብዙ መልካም ነገርና በረከት እንዲሁም የቅርቢቱ ዓለምና የመጭውን ዓለም ጥቅም የያዘ ሲሆን ማለት ነው። ከዚህም አልፎ ሰዎች የቁርኣን አንቀፆችን መልእክት እንዲያጤኑ በሷ ውስጥ ያሉትንም ድንቅ ተዓምራትና ምርጥ ጥበባት እንዲያስተነትኑ፤ የትክክለኛ አዕምሮ ባለቤት የሆኑ ሰዎች እንዲመከሩበት ነው። ሀሠን አልበስሪ እንዲህ ይላሉ

والله ما تدبّـُره بحفظ حروفه وإضاعة حدوده حتى إن أحدهم ليقول: والله لقد قرأت القرآن فما أسقط منه حرفًا، وقد أسقطه والله كله، ما يُرى للقرآن عليه أثر في خلق ولا عمل..”

“ወላሂ ማስተንተን ሲባል ማለት ፊደላቱን መሸምደድና ድንበሩን መጣስ አይደለም። በዚህም የተነሣ አንዲህ የሚሉ አሉ ‘ወላሂ ቁርኣን ቀርቻለሁ አንድንም ፊደል ሣልጥል።’ እኔም እላለሁ ‘ወላሂ በርግጥ ሁሉንም ጥለውታል፤ በሥራም ይሁን በሥነምግባር በነሱ ላይ አንድም የቁርኣን ምልክት ለማየት እስኪቸግር ድረስ’።”

በሰፍወት አተፋሲር ከሙጃሂድ እንደተዘገበው

يُؤْتِي الْحِكْمَةَ مَن يَشَاءُ وَمَن يُؤْتَ الْحِكْمَةَ فَقَدْ أُوتِيَ خَيْرًا كَثِيرًا

“ጥበብንም ለሚሻው ሰው ይሠጣል፤ ጥበብን የተሠጠ ሰው ብዙን መልካም ነገርን ተሠጠ።” የሚለው አንቀፅ “ቁርኣንን በትክክል ማወቅ ነው” ተብሎ ተተረጉሟል።

ቁርኣን በሚቀራበት ወቅት ከሚያስፈልጉ ነገሮች መካከል አንዱ አላህን ከእዝነቱ መጠየቅን ከቅጣቱ በመጠበቅ መጠየቅ ነው። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ቁርኣን በሚቀሩበት ወቅት በአንድም የእዝነት አንቀፅ አያልፉም ቆም ብለው ከአላህ ረህመት የለመኑ ቢሆን እንጂ። በአንድም የቅጣት አንቀፅም አያልፉም ከሷ በአላህ የተጠበቁ ቢሆን እንጂ።

ይህም በርግጥም በለሊት ሰላት ነው ተብሏል። በአጠቃላይ መልኩ ግን ቁርኣንን ስናነብ በጥልቅ ማስተንተንና ግንዛቤ መሆን ይኖርበታል። በሀዲስ

أعطوا أعينكم حظها من العبادة: النظر في المصحف والتفكر فيه، والاعتبار عند عجائبه (الجامع الصغير: 1161، ضعيف)

“ከዐይናችሁ ከኢባዳ የድርሻዋን ስጡ። ይህም ሊሆን የሚችለው ቁርኣንን በማስተንተን መመልከት፤ ትንግርታዊ መልእክቱንም ጠልቆ በማየት ነው።” የሚል ተዘግቧል።

ቁርኣን መስማትን በተመለከተ ደግሞ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ነው ቁርኣን በሚቀራበት ወቅት ዝም እንድንልና በፀጥታ እንድናዳምጥ ያዘዘን።

وَإِذَا قُرِئَ الْقُرْآنُ فَاسْتَمِعُوا لَهُ وَأَنصِتُوا لَعَلَّكُمْ تُرْحَمُونَ

“ቁርአን በተነበበበት ጊዜ እርሱን አዳምጡ፤ ፀጥ በሉ ይታዘንላችሁ ዘንድ” (አል አዕራፍ 7፤ 204)።

በዚሁ ምእራፍ ዝቅ ብሎም وَلا تَكُنْ مِنْ الْغَافِلِينَ “ከዝንጉዎች አትሁን” ይላል። ይህም ቁርኣንን ማስተንተን ያለብን ህያው በሆነ ቀልብና በነቃ ሰውነት መሆን እንዳለበት ነው። ለምን ቢባል አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የሚናገረው በትክክል ለሚያዳምጡት ነውና። አላህ እንዲህ አለ፡-

إِنَّمَا يَسْتَجِيبُ الَّذِينَ يَسْمَعُونَ

“ጥሪህን የሚቀበሉት እነዚያ የሚሠሙት ብቻ ናቸው።” (አል-አንዓም 6፤ 36)

የማያዳምጡ ሰዎች፣ መሃይሞችና አስተባባዮች ሆን ብለው ነውና የቁርኣንን መልእክት አይሠሙም፤ አይገነዘቡምም። ስለሆነም ለዚሁ ጉዳይ የሚጠቀሙባቸው የሰውነት ክፍሎቻቸውና የስሜት ህዋሣቶቻቸው ትርጉም አልባ ይሆናሉ። አላዋቂ የሆነውን ሰው ግን እውነት ይገለፅለት ዘንድ ማስታወሱ ግድ ይላል። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዳለው

وَالَّذِينَ كَذَّبُوا بِآيَاتِنَا صُمٌّ وَبُكْمٌ فِي الظُّلُمَاتِ

“እነዚያ በአንቀፆቻችን ያስተባበሉ ደንቆሮዎች፣ ዲዳዎችም በጨለማዎች ውስጥም ያሉ ናቸው።” (አል-አንዓም 6፤ 39)

እነኚህ ዓይነቶቹ ሰዎች በቁጥር ብዙ ሆነው እናገኛቸዋለን። አላህ ሱብህነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

أَمْ تَحْسَبُ أَنَّ أَكْثَرَهُمْ يَسْمَعُونَ أَوْ يَعْقِلُونَ إِنْ هُمْ إِلَّا كَالْأَنْعَامِ بَلْ هُمْ أَضَلُّ سَبِيلًا

“ይልቁንም አብዛኛዎቻቸው የሚሠሙ ወይንም የሚያውቁ መሆናቸውን ታስባለህን! እነርሱ እንሠሣዎች እንጂ ሌላ አይደሉም ከቶውንም ከነሱ በበለጠ መንገድን የሣቱ ናቸው።” (አል ፉርቃን 25፤ 44)

በሌላም አንቀፅ ቁርኣን ጠቃሚነቱ ለማን እንደሆነ ሲናገር

إِنَّ فِي ذَٰلِكَ لَذِكْرَىٰ لِمَن كَانَ لَهُ قَلْبٌ أَوْ أَلْقَى السَّمْعَ وَهُوَ شَهِيدٌ

“በዚህ ውስጥ ለርሱ ልብ ላለው ወይንም እርሱ (በልቡ) የተጣደ ሆኖ ጆሮውን ለጣለ ሰው ግሣፄ አለበት።” (ቃፍ 50፤ 37)

ቀልብ ንጹህ የሆነ እንደሆነ እውነታን ያገኛል፤ ማስተንተን በሚገባው ነገርም ያስተነትናል። ቀልብ ህያው ነው ሊባል የሚችለውም ነገሮችን ሲያውቅና ሲገነዘብ ነው። ግንዛቤ የሌለው ሰው ደግሞ ህይወት አለው ለማለት ይቸግራል። በአካል ቢኖርም እንኳ በውስጡ ነገሮችን መረዳት ተስኖታልና። ቁርኣን ትርጉሙን ሣይረዱና ሣያውቁ፣ ከሱ ጋርም ሣይኖሩ፣ የአላህን ጠላቶች ሣይታገሉና በመንገዱም መከራና ችግር ሣያዩ በማንበብ ብቻ ወደ ቀልብ ሊደርስ አይችልም። ቀደምት ሙስሊሞች በብዙ ጦርነቶችና ታላቅ መከራዎች ውስጥ አልፈዋል። ቁርኣንም ሁኔታቸውን በመግለፅ ይወርድ አላህ በዋለላቸው ፀጋና በድሉም ያስታውሣቸው ነበር። የያኔዎቹ ደጋግ ሰዎች ከቁርኣን ጋር በተሀጁድ /በለሊት ሰላት/ ኖረዋል። በቀንም ቁርኣን ህይወታቸው ነበር።

ቁርኣንን ማወቅና በሱም መሥራት ያስፈልጋል። ማወቅ ሲባል ደግሞ ዝም ብሎ እላይ ላዩን ማወቅ ብቻ አይደለም። እሱን ማወቅ ሰውን ለሥራ የሚያነሣሣ መሆን አለበት። ሙስሊሞች ገና ከህፃንነታቸው ጀምሮ በቁርአን አስተምህሮ ተኮትኩተው የሚያድጉት በእውቀቱ ሊሠሩበት ነው። የሚያነቡትም ለዛውን ለማጣጣም ብቻ ሣይሆን የአላህን ትእዛዛት ለመተግበርና በግልም ሆነ በጋራ ጉዳዮቻቸው ውስጥ ለሚኖሩበት ህይወት ሊጠቀሙበት ነው። በመሆኑም ትእዛዙን ተቀብለው ወዲያው እንደሰሙ ሊተገብሩት ይጣደፋሉ። ማንኛውም በግንባር ያለ ወታደር የእለት ትእዛዙን እየተቀበለ እንደሚሠራበት ሁሉ። ከበርካታ ሰሃቦች እንደተዘገበው ነቢዩ ሰላሁ ዐለይህ ወሠለም ሰሃቦችን አሥር አንቀፆችን ያቀሯቸው /ያስተምሯቸው/ ነበር፤ ወደ ሌሎቹ አሥር አንቀፆችም አያልፉም በተማሯት ውስጥ ያለውን መልእክት ተግባር ላይ ማዋላቸውን እስካላረጋገጡ ድረስ። ነቢያችን “ቁርአንንም ተግባሩንም አንድ ላይ ያስተምሩን ነበር” ይላሉ። እንዲህም ብለዋል – ሰሃቦች “አሥር አንቀፅ የተማርን እንደሆነ ሌላ አሥር አንማርም። የተማርነውን አንቀፅ ሀላል ሀራም፤ ትእዛዝና ክልከላ የተማርን ካልሆነ በቀር።”

ቁርኣንን ተግባር ላይ በማዋሉ ረገድ የአላህን መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የሚስተካከል ማንም አልነበረም። እርሣቸው በምድር ላይ የሚሄዱ ተንቀሣቃሽ ቁርኣን ነበሩ። ባህሪያቸውም ሆነ አጠቃላይ ሥነምግባራቸው ቁርኣን ነበር። የርሣቸውም ሰሃቦች ፈለጋቸውን በመከተል አንዲት የቁርኣን አንቀፅ በወረደች ቁጥር በሷ ለመሥራት ይሽቀዳደሙ ነበር። ቁርኣን ለሁሉም አማኝ ከአላህ የወረደ መልእክት ነው። ከወዳጃችን የሆነ መልእክት ሲደርሰን እያንዳንዱን መስመር በጥንቃቄ እንደምናነብ እናውቃለን። ከሀያሉ ጌታችን የሆነውን መልእክትስ ምነዋ ችላ አልን!

ሀሠን አልበስሪ አንዲህ ይላሉ፡-

من كان قبلكم رأوا القرآن رسائل من ربهم، فكانوا يتدبرونها بالليل وينفذونها بالنهار.. ومن الأدب مع القرآن أن تعتبر نفسك المقصود بكل خطاب في القرآن..

“ከናንተ በፊት የነበሩ ህዝቦች ቁርኣንን ከጌታቸው እንደሆነ መልእክት አድርገው ይመለከቱ ነበር። በለሊት ጊዜያቸው ያስተነትኑታል። በቀኑ ደግሞ መልእክቱን ተግባር ላይ ያውሉታል። ከቁርኣን ጋር ሥርኣት ማድረግ ሊባሉ ከሚችሉ ነገሮች መካከል – አላህ በሚናገረው በያንዳንዱ የቁርኣን አንቀፅ “እኔን ነው እያናገረኝ ያለው” ብሎ ማሰብ አንዱ ነው።”

አንድ ዓሊም “ቁርኣን የደረሠው ሰው አላህ እንዳናገረው ነው።” ብለዋል። ቁርኣን እምነት፣ መንገድና ህግጋት ሲሆን ሰዎችም በመልካም ሁኔታ እንዲኗኗሩ ያግዛል። በሀዲስ

(طوبى لمن عمل بعلمه.. (الترمذي

“..በእውቀቱ የሠራ ሰው ምንኛ ታደለ..” (ቲርሚዚ) የሚል መጥቷል። ሥራ የእውቀት ፍሬ ነው። እውቀት ያለውና የተማረ ሰው በተማረው ነገር መሥራት ይኖርበታል። ካልሆነ እውቀት በሱ ላይ ማስረጃ ነውና ይጠየቃል። በሀዲስ፡-

لا تزول قدم ابن آدم يوم القيامة حتى يسأل عن عمره فيم أفناه وعن شبابه فيم أبلاه وماله من أين اكتسبه وفيم أنفقه، وماذا عمل فيما علم (الترمذي)

“በትንሣኤ ቀን የአደም ልጅ እግሮች አይንቀሣቀሱም እድሜውን በምን እንደጨረሠ፤ ወጣትነቱን በምን እንዳባከነ፤ ገንዘቡን ከየት እንዳገኘና በምን ላይ እንዳዋለ፤ በእውቀቱ ምን እንደሠራ እስኪጠየቅ ድረስ” (ቲርሚዚ) ብለዋል ነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም።

የቂያማ ቀን፡-

يؤتى برجل تعلم العلم وعلمه، وقرأ القرآن فأتى به فعرفعه الله نعمه فعرفها، فقال: ماذا عملت فيها؟ قال: تعلمت العلم وعلمته، وقرأت القرآن فيك، قال: كذبت، ولكنك تعلمت العلم ليقال عالم، وقرأت القرآن ليقال قارئ، فقد قيل، ثم أمر به فسحب على وجهه حتى ألقي في النار (جزء من حديث مسلم والنسائي وأحمد).

“በአንድ እውቀትን የተማረና ያስተማረ እንዲሁም ቁርኣንን በቀራና አላህም ፀጋውን ባሣወቀው ሰው ይመጣል። እሱም ‘(ባወቅከው /በተማርከው/) ምን ሠራህበት?’ ተብሎ ይጠየቃል። ሰውዬውም ‘እውቀትን ተማርኩ አስተማርኩ። ላንተም ብዬ ቁርኣንን ቀራሁ’ በማለት ይመልሣል። ‘የለም ዋሽተሃል ነገር ግን የተማርከዉ ዓሊም /አዋቂ/ እንድትባል ነው። የቀራሀውም ቃሪእ /ቁርኣንን ያውቃል/ እንድትባል ነው። ያ ተብሎልሃል።’ ይባላል። ከዚያም እንዲያዝ ይታዘዝና ተወስዶ በፊቱ እሣት ውስጥ እንዲወረወር ይደረጋል።” (ሙስሊም፣ ነሳኢና አህመድ)

በአንድ ወቅት ታላቁ ዓሊም ኢብራሂም አብኑ አድሀም ተጠየቁ “ለምንድነው ዱዓእ እያደረግን ምላሽ የማናገኘው” እርሣቸውም “በአምስት ምክኒያት ነው” በማለት ከነዚያ ውስጥ “ቁርኣንን ትቀራላችሁ ነገር ግን በውስጡ በያዘው ነገር አትሠሩም” የሚለው ተጠቅሷል።

ቁርኣን መስማት የሚያሣድረው ተፅእኖ

ሙእሚኖች የታላቁን ጌታ ንግግር በሰሙ ጊዜ በሱ ውስጥ ባለው የቃል ኪዳን፣ የዛቻ፣ የማስፈራሪያና የማስጠንቀቂያ መልእክቶች ይነካሉ። በቁርኣን በሚያሣድረው ተፅእኖ ከሚታዩ ምልክቶች መካከል እነኚህ ይጠቀሣሉ

 

إِنَّمَا الْمُؤْمِنُونَ الَّذِينَ إِذَا ذُكِرَ اللَّهُ وَجِلَتْ قُلُوبُهُمْ وَإِذَا تُلِيَتْ عَلَيْهِمْ آيَاتُهُ زَادَتْهُمْ إِيمَانًا وَعَلَىٰ رَبِّهِمْ يَتَوَكَّلُونَ

“ፍፁም ምእመናን አነዚያ የአላህ በተወሣ ጊዜ ልቦቻቸው የሚፈሩት በነሱም ላይ አንቀፆቻችን በተነበቡ ጊዜ እምነትን የሚጨምሩላቸው በጌታቸውም ላይ ብቻ የሚመኩት ናቸው።” (አል-አንፋል 8፤ 2) ይህም ማለት ቁርኣንን በሚያነቡበት ወቅት ማለትም ልባቸው ትፈራለች ትደነግጣለች ማለት ነው።

تَقْشَعِرُّ مِنْهُ جُلُودُ الَّذِينَ يَخْشَوْنَ رَبَّهُمْ ثُمَّ تَلِينُ جُلُودُهُمْ وَقُلُوبُهُمْ إِلَىٰ ذِكْرِ اللَّهِ

“ከርሱ (ግሣፄ ) ጌታቸውን የሚፈሩ ሰዎች ቆዳዎቻቸው ይኮማተራሉ ፤ ከዚያም ቆዳዎቻቸውና ልቦቻቸው ወደ አላህ በማስታወስ ይለዝባሉ።” (ዙመር፤ 23) ማለትም ቆዳቸው ከፍራቻ የተነሣ ኩምትር ይላል። ኋላም እዝነቱንና ርህራሄውን ስታስብ ተመልሣ ትለሠልሣለች። የቅጣት አንቀፅ ሲወሣ ትሸማቀቃለች፤ የእዝነቱ አንቀፅ ሲነሣ ደግሞ ቀልብም ሆነ የሰውነት ቆዳቸው ይፍታታል ማለት ነው።

إِذَا تُتْلَىٰ عَلَيْهِمْ آيَاتُ الرَّحْمَٰنِ خَرُّوا سُجَّدًا وَبُكِيًّا

“የአልረሕማን አንቀጾች በነሱ ላይ በተነበቡ ጊዜ ሰጋጆችና አልቃሾች ኾነው ይወድቃሉ” (መርየም 19፤58) ይህ ስለ ነቢያት የተገለፀው ሲሆን ከነዚያ ምርጥ ምሣሌዎችና መሪዎች ጋር ለመሆን መጣጣር ያስፈልጋል። የአላህ አናቅፆች በሚነበቡበት ጊዜ ከሚያለቅሱትና ሲጁድ ከሚወርዱት ለመሆን መትጋት ይኖርብናል። በአንድ ወቅት ዐብዱላህ ለነቢዩ ቁርኣን ቀራላቸው ሱረቱ ኒሣእ

فَكَيْفَ إِذَا جِئْنَا مِن كُلِّ أُمَّةٍ بِشَهِيدٍ وَجِئْنَا بِكَ عَلَىٰ هَٰؤُلَاءِ شَهِيدًا

“ከሕዝቦችም ሁሉ መስካሪን ባመጣን ጊዜ አንተንም በእነዚህ ላይ መስካሪ አድርገን በምናመጣህ ጊዜ (የከሓዲዎች ኹኔታ) እንዴት ይኾን?” (አኒሳእ 4፤41) የሚለው አንቀፅ እስኪደርስ ድረስ። በዚህን ጊዜም ነቢዩ “አቁም” አሉት። ዐብዱላህ ቀና ብሎ ወደ አላህ መልእክተኛ ሲመለከት ሁለቱ ዐይናቸው በእንባ ታጥበው አገኛቸው።

ኢማም ነወዊ ረሂመሁሏህ:-

“ቁርኣን በሚቀራበት ጊዜ ማልቀስ የአዋቂዎች ምልክት የደጋግ ሰዎችም መለያ ነው” ብለዋል።

ኢማም አልገዛሊም:-

“ቁርኣንን በሚያነቡበት ጊዜ ማልቀሱ የተወደደ ነው። ይህንንም ማግኘት የሚቻለው ቀልብን በሀዘንና በፍራቻ ስሜት ውስጥ በማስገባት የቁርኣንን ማስጠንቀቂያዎቹን፣ ቅጣቶችንና ያለፉትን ታሪኮች በማስታወስና በማስተንተን ነው። ወደራስ በመመለስም ያሉበትን ከአላህ የመራቅና የመዘናጋት ሁኔታ በማስታወስ ቀልብን በሀዘን መሙላት ያስፈልጋል። ይህ ሁሉ ለቀልብ ፍራቻንና ለቅሦን የማያመጣላት ከሆነ ባለቤቱ ትልቅ አደጋ ውስጥ እንዳለ ሊያውቅ ይገባል። አላህ ይጠብቀን።”

በሀዲስ:-

لا يلج النار رجل بكى من خشية الله (الترمذي)

“ከአላህ ፍራቻ ያለቀሠች ዐይን እሣት አይነካትም” (ቲርሚዚ) የሚል ተዘግቧል።

ቁርኣን በሚቀራበት ጊዜ ሌላው ተወዳጅ ነገር ዱዓእ ነው። ኡሙ ደርዳእ እንዲህ ብላለች፡-“የቆዳ መኮማተር የሚሠማህ ከሆነ በዚያን ጊዜ ዱዓእ አድርግ ምላሽ አታጣምና”።

ዓኢሻም ረዲየሏሁ ዐንሃ “ቆዳ ሲሸማቀቅ፣ ቀልብ ሲፈራ፣ ዐይን ስታለቅስ ዱዓእ ምላሽ የሚያገኝበት ጊዝ ነው” ብላለች።

ማንኛውም የደዕዋን አደራ መሸከም የሚፈልግ ወጣት ሁሉ ይህንኑ የቁርኣንና የዲን እንቅስቃሴ መንገድ ይዞ መጓዝ አለበት። በመልእክቶቹም ስሜቱ መነካት ይኖርበታል። በርግጥ መንገዱ ከባድ ነው። ቢሆንም ግን ቁርኣን ትክክለኛውን መንገድ ያሣያል። ወደ አላህ መንገድ የሚጠሩ የተለያዩ ሰዎች ሌሎችን ወደ ትክክለኛው መንገድና ወደ ጌታቸው ለመመለስና የአላህን ቃል ከፍ ለማድረግ ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት ከሰዎች ጋር መጋፈጥና የሚያደርሱባቸውንም መቻል ግድ ይላቸዋል። ያኔ ቀደምቶቻቸው የቁርኣንን ጥፍጥና እንዳጣጣሙ ሁሉ እነሱም ያጣጥማሉ። ይህም የአላህ ችሮታ ነው። እሱ የታላቅ ችሮታ ባለቤት ነው። ይህንኑ ችሮታውንም ለሚሻው ሰው ይሠጣል።

ጌታችን ሆይ! ቁርኣንን ለቀልባችን ማረፊ፣ ለልባችን ብርሃን፣ ለሀሣባችን ማስኬጃ፣ ለጭንቀታችን ማስወገጃ አድርግልን። ምስጋና የዓለማት ጌታ ሁሉ ለሆነው ለአላህ ይሁን።

3 COMMENTS

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here