የወሰጢያ መንገድ መገለጫ ቦታዎች
1. ተፈጥሯዊውን መንገድ መሰረት ያደረገ ዐቂዳ፦
ይህ ነጥብ ቁርአንን ሱናን እንዲሁም የሰለፎችን መንገድ መሰረት ያደረገ የዐቂዳ አስተምህሮት ነው። በተቃራኒውም ቴክኒካዊ ከሆኑ ሙያዊ የቋንቋ ብያኔዎች ምጉትና ክርክር በመራቅ ዐቂዳ በነፍስ ላይ ያለውን ጉልህ ሚና በተገቢው መንገድ ተጽዕኖ እንዲኖረው ትኩረት ማድረግ። ከአላህ ጋር ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር ዐቂዳዊ መረጃዎችን በቀጥታ ከምንጫቸው መውሰድ እንዳለብን ሁሉ አዕምሯዊ ጥረትን መጠቀም የሚፈቅድ መንገድ ነው።
2. በሀይማኖት ስርዓታዊ ክንውኖችና በዱንያዊ የልማት እንቅስቃሴ መካከል ሚዛናዊ መሆን፦
ይህ የዱንያ ህይወትን /ኑሮን/ ለማሸነፍና ያማረ ህይወትንም ለመኖር ብሎም መሬትን ለማበልጸግ የሚደረገው ጥረት ሀይማኖታዊ ስርዓቶችንና ክንውኖችን (ሸዓኢረዲን) የሚቃረን አይደለም። እንዲያውም ኢስላማዊ የሀይማኖት ስርዓቶች ለስራና ለምርታማነት ምቹና ገር ከመሆናቸውም ባሻገር አበራታች ናቸው።
3. በተሃድሶና በኢጅቲሃድ ሚዛናዊ መሆን፦
ይህ የሚሆነው ጥንታዊውን አተያየት (አል-አስል) ከዘመናዊ (አል-ዐስር) ጋር አጣምሮ በማስኬድ ነው ።
4. በጽንፈኛ የመዝሀብ አራማጆችና ካለዕውቀት ዑለሞችን የሙጢኝ በሚከተሉ ወገኖች መካከል ባለው አካሄድ ሚዛናዊውን መንገድ መከተል፦
መካከለኛው መንገድ ጽንፈኛ የመዝሀብ አካሄድን (ተዐሱብ መዝሃብ) እና ካለዕውቀት ዑለሞችን ያለአግባብ የሙጥኝ ማለትን (ተቅሊድ አዕማ) አይቀበልም። በዚህ ላይ ኢማሙ ኢብኑ አል-ቀይም እንዲህ ብለዋል፦ መከተል (ኢትባዕ) በሌላ አዋቂ ማስረጃ መሰረት የሆነን ተግባር መፈፀም ሲሆን፣ ያለዕውቀት መከተል (ተቅሊድ) ደግሞ ያለማስረጃ የሆነን ተግባር መፈፀም ነው። ወሰጢያ ኢጅቲሃድን፣ ኢትባዕንና ተቅሊድን ሚዛናዊና ተደጋጋፊ በሆኑ መልክ የሚራምድ የአስተሳሰብ ዘይቤ ነው።
5. በፈትዋ ሚዛናዊ መሆን፦
መካከለኛው መንገድ መሰረታዊና ጥቅል (ኩልይ) እና ዝርዝር (ጁዝኢይ)፣ የሸሪዓውን ዓላማ (መቃሲድ)ና ቅርንጫፍ (ፍሩዕ) ጉዳዬችን፣ የሸሪዓውን ቀዳሚ ማስረጃዎች (ቁርአንና ሱና)ና ፋይዳን መሰረት ያደረጉ ግለሳባዊ አስተያየቶችን (ረዒ) ሁሉ የሚያቀናጅና እነዚህን ነገሮችም ግምት ውስጥ አስገብቶ ፈትዋ የሚሰጥ ነው። በፈትዋ ጽንፈኝነትንና የወረደ አቋምን ማንጸባረቅ የዚህ መንገድ አቋሙ አይደለም። በአጠቃላይ ሽይኸ ዐብደሏህ ኢብኑ በያህ እንደሚሉት፣ ፈትዋ አራት ነገሮችን መሰረት አድርጎ ይከናወናል። እነሡም፦
- የጊዜና የቦታ ለውጥን
- የልምድና የባህል ሁኔታን
- የፈትዋ ማስፈፀሚያ ስልቶችን እና
- ግለሰቦችንና የነገሮችን አይነት መሰረት ያደርጋል።
6. በልዩነት (ኺላፍ) ሚዛናዊነትን መጠበቅ፦
ልዩነት ሁለት አይነት ሲሆን፣ የመጀመሪያው መሰረታዊና አጠቃላይ (ኡሱል ወል ኩሊያት) በሆኑ ዐቂዳዊና ሸሪዓዊ ጉዳዬች ላይ ሲሆን ይህ አይነቱ ኺላፍ በኢስላም የተወገዘ ነው። ሌላው ኺላፍ ደግሞ መሰረታዊ ባልሆነው (ፉሩዕ) የሸሪዓው ማስረጃ የሚኖረው ልዩነት ነው። ይህን መሰረት አድርገው የሚከሰቱ ልዩነቶች ተቀባይነት ያላቸው ናቸው። በዚህ አይነቱ ሁኔታ የውይይት ተገቢ ስልቶችን በመጠቀም ልዩነትን ማስወገድ ወይም ማጥበብ ይቻላል።
7. ሙስሊም ካልሆኑ ወገኖች ጋር በሚኖር መስተጋብር መካከለኛ መሆን፦
ይህ መንገድ ሙስሊም ካልሆኑ ወገኖች ጋር በሚኖር መስተጋብር ውይይትን መሰረታዊ ድልድይ ያደርጋል። ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖች ሀይማኖታዊ ስርዓታቸውን የመከወን ነጻነትን አይነፍግም። ስለሆነም በጋራ ተባብሮ መኖርን እንጂ ሀይማኖታዊ ልዩነትን የጥላቻ መሳሪያ ማድረግን አይቀበልም። ከዚህ ይልቅ በአንድ ሀገር ላይ አብሮ መኖር መቀራረብንና የጋራ ሀገራዊ ጥቅምን ለማሳካት ባንድነት መስራት ትልቅ መንገድ ነው ብሎ ያምናል ።
8. በሸሪዓዊ ጉዳይ ላይ መካከለኛ መሆን፦
ይህ መሰረታዊ ህጎችን (ኡሱል) ከፍተኛ ቦታ መስጠትና ቅርንጫፎችን (ፉሩእ) ደግሞ ማግራራትን (ተይሲር) የሚመለከት ነው። የመካከለኛው መንገድ መሰረቱ፣ ይኸው መሰረታዊ የሸሪዓው ህጎች ናቸው። ቀደም ባሉት ሀይማኖቶች ላይ የተከሰተው እንዳይከሰት፣ መሰረታዊ የሸሪዓውን ህጎች ሰርጎ-ገብ አጥፊ እጆች እንደፈለጉ እንዳይጠመዙዟቸው ይህ መንገድ ከፍተኛ ጥበቃ ያደርጋል። በሌላም መልኩ የነኚህን መሰረታዊ ሸሪዓ ህጎች መሰረታዊ ትርጓሜያቸውና የሚያስተላልፉት መልዕክት ለማዛባት የሚደረግ ሙከራንም ይከላከላል። መካከለኛው መንገድ ለመሰረታዊ የሸሪዓ ህጎች ጥበቃ እንደሚያደርግ ሁሉ፣ ለቅርንጫፍ ሸሪዓዊ ጉዳዮችም የተግራራ መንገድን ይከተላል። ይህን የሚያደርገው ችግርን ለመከላከል፣ ጭንቅና መከራን ለማስወገድ ነው። ይህ ደግሞ የየአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የማይቀየር መሰረታዊ አቋም ነው:: የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም
ما خُير بين أمرين إلا اختار أيسرهما، ما لم يكن إثمًا
“ከሁለት ነገሮች አንዱን እንዲመርጡ ሲጠየቁ፣ ወንጀል እስካልሆነ ድረስ ቀለል /ገር የሆነውን/ ያለውን ይመርጡ ነበር”
9. መካከለኛው መንገድ ለዘመናዊ ጉዳዮች በጎ እይታ አለው፦
ለዘመናዊ ግኝቶች ወይም ስልጣኔዎች ጨለምተኝነትን መሰረት ያደረገ ሳይሆን አዎንታዊ እይታ ይኖረዋል። ይህ ሲሆን ግን ራስን ለባዕድ የሃሳብ “ምርኮኛ” ባደረገ መልኩ አይደለም። ከማንኛውም ወገን “መልካም”ን ነገር ሲቀበል፣ የራስን ክብር በጠበቀ፣ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት በሌለበት፣ መቻቻልን መሰረት ባደረገና ውርደትን በማይፈቅድ ሁኔታ ነው። ሙስሊሞች ራሳቸውን ችለው የሚቆሙና የራሳቸው መለያ ባህሪይ ያላቸው ኡማ ናቸው። የአላህ መልእክተኛም እንዲህ ገልፀዋቸዋል፦
المؤمنون تتكافأ دماؤهم، ويسعى بذمتهم أدناهم، وهم يد على من سواهم…
“ሙእሚኖች ህይወታቸው አንዱ ለአንዱ ዋቢ ሲሆን፣ በእነሡ የበላይነት ሌላው በስራቸው የሚያድርና ከነሱ ውጪ ለሆነው ደግሞ ሀይል (እጅ) ናቸው” (ነሳኢ)።
ማጠቃለያ
መካከለኛው አቋም (አል-ወሰጢያ) አስተሳሰቡ ካልጠራና ከእንቶ-ፈንቶ እሳቤ በእጅጉ የራቀ ነው። ለሁለገብ ዕውቀት (ሠቃፋ) ብቻ የሚውል፣ ወይም አዕምሮን ለማርካት የሚደረግ ፍልሰፋዊ ትረካም አይደለም። መካከለኛው አቋም (አል-ወሰጢያ) ሁለገብ የሆነ የአስተሳሰብና የህይወት መንገድ ነው። ግለሰብንና ማህበረሰብን እንደሚመለከት ሁሉ ሀገራዊ ጉዳዮችንም ጉዳዩ ያደርጋል። ይህ መንገድ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ሙስሊሞች በተለያዩ የህይወት ዘርፎች ሊከውኑትና ሊያራምዱት የሚገባውን ኢስላማዊ አስተምህሮት የሚያመላክትና የሚመራ ዕሳቤም ነው። መካከለኛው አቋም ሙስሊሞች በዳዕዋና በእንቅስቃሴ፣ በሁለገብ ዕውቀት፣ በባህል፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በማምረት፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ ወዘተ… ሁለገብ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው የሚያስችል መንገድ ነው።