የኢስላም ድል አድራጊነት – በነቢያዊ ሐዲስ (ክፍል 2)

1
4932

5. የነቢያዊ ሥርዓት ወራሽ የሆነው ኸሊፋዊ አስተዳደር መመለስ

ሑዘይፋህ ቢን አልየማኒ ያስተላለፉትና ኢማም አህመድ የዘገቡት ሐዲስ በዚህ ርዕስ ሥር ተጠቃሽ ነው፡-

تكون النبوة فيكم ما شاء الله أن تكون، ثم يرفعها إذا شاء أن يرفعها، ثم تكون خلافة على منهاج النبوة، فتكون ما شاء الله أن تكون، ثم يرفعها إذا شاء أن يرفعها، ثم تكون ملكًا عاضًا، فتكون ما شاء الله أن تكون، ثم يرفعها إذا شاء أن يرفعها، ثم تكون ملكًا جبريا، فتكون ما شاء الله أن تكون، ثم يرفعها إذا شاء أن يرفعها، ثم تكون خلافة على منهاج النبوة

“የነቢይነት ሥርዓት አላህ እስከፈቀደ ጊዜ ድረስ በናንተ ውስጥ ትቆያለች። አላህ ሊያነሳት ሲፈልግም ያነሳታል። ከዚያም የኸሊፋ ሥርዓት በነቢያዊ ጎዳና መሠረት ይተካል። አላህ እስከ ፈቀደ ጊዜ ድረስም (ይህች ሥርዓት) ትቆያለች። ከዚያም ሊያነሳት ሲፈልግ ያነሳታል። ከዚያም ቧጣጭ ንጉስ ይይዛታል። አላህ እስከሻ ወቅት ድረስም ትቆያለች። ከዚያም ሊያነሳት ሲፈልግ ያነሳታል። ከዚያ አምባገነን መሪዎች ይመጣሉ። እሷም አላህ እስከሻው ወቅት ድረስ ትቆያለች። ከዚያም ሊያነሳት ሲሻ ያነሳታል። ከዚያም በነቢያዊ ጎዳና (የምትመራ) ኸሊፋዊ ሥርዓት ትነግሳለች” ከዚህ በኋላ ዝም አሉ።

“ቧጣጭ ንጉስ” ማለት ሕዝቦቹን በግፍ ጥፍሩ እየቧጠጠ የሚበድል፣ የሚያሰቃይ ማለት ሲሆን፣ አምባገነን ሥርዓቶች ደግሞ ልክ እንደ ዘመናችን ወታደራዊ መስተዳድሮች በአምባገነንነትና በወሰን አላፊነት ላይ የተመሠረተ ማለት ነው።

ይህ ሐዲስ በግልጽ እንደተተነበየው ከነቢዩ ሙሐመድ መለኮታዊ አስተዳደር በኋላ የርሳቸውን ቅን መንገድ የተከተሉ ሶሐባዎች የሚመሩት የኸሊፋዊ አስተዳደሮች ይመጣሉ። ከዚያም ሰዎች የሚያዝኑበትና የሚጨቆኑበት የንጉሳዊ አስተዳደር ይተካል። ቀጥሎም በዘመናችን እንደሚታየው ዓይነት ወታደራዊ አምባገነን ሥርዓት ይተካል። ይህም ፈርሶ ሕዝበ ሙስሊሙ ዳግም ወደ ኸሊፋዊ ሥርዓት ይመለሳል። በደል፣ ጭቆና፣ ጥመትና አምባገነንነት ተወግደው በምትኩ ፍትህና ምክክራዊ ሥርዓት ይሰፍናል። የአላህ ወሰንና መብት ይጠበቃል። የሰው ልጆች መብትና ፍላጎትም በሚገባ ይከበራል።

6. ኢስላም በአይሁድ ላይ ድል ይቀዳጃል

ከነቢዩ ሐዲሳዊ ብስራቶች መካከል ሙስሊሞች አይሁዶችን ድል እንደሚያደርጉ የሚገልጹ ሐዲሶች ይገኙበታል። የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ሲሉ ሰምቻለሁ በማለት ኢብኑ ዑመር አስተላልፈዋል፡-

تقاتلكم اليهود، فتسلطون عليهم، ثم يقول الحجر: يا مسلم، هذا يهودى ورائى، فاقتله

“ከአይሁዳዊያን ጋር ትፋለማላችሁ። በነርሱ ላይም የበላይነት ትቀዳጃላችሁ። ድንጋዩም እንዲህ ይላል፡- አንተ ሙስሊም ሆይ፣ ከኔ ጀርባ አይሁድ አለ፣ ግደለው”  (ቡኻሪና ሙስሊም የዘገቡት)

አቡ ሁረይራ ያወሱት ሐዲስም ተመሳሳይ መልዕክት አለው። እንዲህ ይነበባል፡-

لا تقوم الساعة حتى يقاتل المسلمون اليهود، فيقتلهم المسلمون، حتى يختبىء اليهودى من وراء الحجر والشجر، فيقول الحجر أو الشجر: يا مسلم؛ يا عبد الله؛ هذا يهودى خلفى، فتعال فاقتله

“ሙስሊሞች ከአይሁዳዊያን ጋር ሳይፋለሙ ዕለተ ትንሳኤ አይቆምም። ሙስሊሞች (አይሁዶችን) ይገድላሉ። አይሁዱም ከድንጋይና ከዛፍ ጀርባ ይደበቃል። ድንጋይና ዛፉም፡- አንተ ሙስሊም ሆይ፣ አንተ የአላህ ባሪያ ሆይ፣ ከጀርባዬ የተደበቀ አይሁድ አለልህና ግደለው” ይላሉ።” (ሙስሊም የዘገቡት)

ድንጋይና ዛፍ ይናገራሉ ሲባል ምን ማለት ነው? አዎ፣ እኛን እንድንናገር ያስቻለን ጌታ እነርሱንም እንዲናገሩ ያደርጋል። ይህ ለአላህ የሚከብድ አይደለም። አልያም ተምሳሌታዊ ንግግር ሊሆን ይችላል። ሁሉም ነገር “ዛፍ ቅጠሉ” የአይሁዳዊያንን ዘር ያጋልጣል፣ ማለት ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ሐዲሱ የሙስሊሞች ድምፅ የሚሰማበትና የአይሁድ ሴራ የሚከሽፍበት ጊዜ እንደሚመጣ ያስገነዝባል።“የማይሸነፈው ኃይል” እያለ የሚመጻደቁበት ጊዜ ያከትማል። በኃይል የቀሙት የፍልስጥኤም ምድር ወደ ባለቤቶቹ ይመለሳል። በዳዮችን የሚቀጣው አላህ አይቀጡ ቅጣት ይቀጣቸዋል። የታጠቁትና የሚመኩበት የኒኩሊየር ኃይል አያድናቸውም። አባቶቻቸውም እንዲህ ጠንካራ ምሽጋቸው የሚያድናቸው መስሏቸው ነበር። የአላህ ቅጣት በመጣባቸው ጊዜ በነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የተመራው የአማኝ ሠራዊት ዶግ አመድ አድርጓቸዋል። አሁንም ነቢዩ ሙሐመድን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለምበተከተለው የአማኝ ሠራዊት ታሪኩ ይደገማል። ቁርአን በኒ ነድር ተብለው የሚታወቁ የአይሁድ ማኀበረሰብ አባላት የደረሰባቸውን ሽንፈት እንዲህ ዘክሮታል፡-

هُوَ الَّذِي أَخْرَجَ الَّذِينَ كَفَرُوا مِنْ أَهْلِ الْكِتَابِ مِن دِيَارِهِمْ لِأَوَّلِ الْحَشْرِ مَا ظَنَنتُمْ أَن يَخْرُجُوا وَظَنُّوا أَنَّهُم مَّانِعَتُهُمْ حُصُونُهُم مِّنَ اللَّهِ فَأَتَاهُمُ اللَّهُ مِنْ حَيْثُ لَمْ يَحْتَسِبُوا وَقَذَفَ فِي قُلُوبِهِمُ الرُّعْبَ يُخْرِبُونَ بُيُوتَهُم بِأَيْدِيهِمْ وَأَيْدِي الْمُؤْمِنِينَ فَاعْتَبِرُوا يَا أُولِي الْأَبْصَارِ

“እርሱ ያ ከመጽሐፉ ሰዎች እነዚያን የካዱትን ከቤቶቻቸው ለመጀመሪያው ማውጣት ያወጣቸው ነው። መውጣታቸውን አላሰባችሁም። እነርሱም ምሽጎቻቸው ከአላህ (ኃይል) የሚከላከሉላቸው መኾናቸውን አሰቡ። አላህም ካላሰቡት ስፍራ መጣባቸው። በልቦቻቸውም ውስጥ መርበድበድን ጣለባቸው። ቤቶቻቸውን በእጆቻቸውና በምእምናኖቹ እጆች ያፈርሳሉ። አስተውሉም የአእምሮ ባለቤቶች ሆይ!” (አል-ሐሽር 59፤ 2)

7. ምን ጊዜም አላህ የሚወደው- የኢስላም ተቆርቋሪ ኃይል- አይጠፋም

ከሐዲስ ብስራቶች መካከል በሙዓዊያና በሌሎች በርካታ ሶሐባዎች የተወሳው ተከታዩ ሐዲስ ይገኝበታል፡-

لا تزال طائفة من أمتى قائمة بأمر الله، لا يضرهم من خذلهم ولا من خالفهم، حتى يأتى أمر الله، وهم ظاهرون على الناس

“ከሕዝቦቼ የተወሰኑ ወገኖች (ቡድኖች) በአላህ ትእዛዝ ፀንተው ይቆያሉ። ሊያዋርዳቸው የሚሞክርም ሆነ የሚፃረራቸው አይጎዳቸውም። የአላህ ትእዛዝ (ውሳኔ) እስኪመጣና ከሰዎች በላይ እስኪሆኑ ድረስ (ትግላቸውን ይቀጥላሉ)።” (ቡኻሪ፣ ሙስሊምና አህመድ)

አቡ ኡማማ ባስተላለፉት ሐዲስም የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-

لا تزال طائفة من أمتى على الدين ظاهرين، لعدوهم قاهرين، لا يضرهم من خالفهم، إلا ما أصابهم من لأواء حتى يأتى أمر الله، وهم كذلك. قالوا: يا رسول الله، وأين هم؟ قال: ببيت المقدس وأكناف بيت المقدس

“ከሕዝቦቼ የተወሰኑ ወገኖች (ቡድኖች) በኃይማኖታቸው ጸንተው ይቆያሉ። ጠላቶቻቸውንም ያሸንፋሉ። የተቃወማቸው አይጎዳቸውም። በርግጥ መከራና ችግር ያገኛቸዋል። በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ የአላህ ውሳኔ (እርዳታ) ይፈጸማል” አሉ። (ሶሐቦችም)፡- “የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እነኝህ ኃይላት የት ይገኛሉ?” የሚል ጥያቄ አቀረቡላቸው። እርሳቸውም፡- “በበይተል መቅዲስ (ቁድስ) እና በቁድስ (እየሩሳሌም) ዙሪያ” የሚል ምላሽ ሰጡ።” (አልሙስነድ፣ ሐይሠሚ ዘግበውታል)

እነኝህ ሐዲሶች እንደሚጠቁሙት ይህ ኡምማ በጎ ነገር የሚሠሩ ወገኖች ምን ጊዜም አይጠፉበትም። የአላህ ጠበቆች፣ የእውነት ረዳቶች፣ የፍትሕ ወገኖች ምንጊዜም ይኖራሉ። እስከ ዕለተ ትንሳኤ ሕዝበ ሙስሊሙ እንዲህ ዓይነት ወገኖችን ከውስጡ አያጣም። በርግጥ እንግልት፣ እስር፣ ግርፋት፣ ግድያ ሊፈጸምባቸው ይችላል። ቢሆንም እጅ አይሰጡም። ለሐሰት አይንበረከኩም።

8. በየክፍለ ዘመኑ “ሙጀዲዲን” ይመጣሉ

የኢስላምን ድል አድራጊነት ከሚጠቁሙ ነቢያዊ ሐዲሶች አንዱ በየክፍለ ዘመኑ ኡማው ሲወድቅ፤ ለጥቃት ሲዳረግ፣ በኢስላም ላይ ያለው እምነት ሲላላ፣ አመለካከቱም ሲዘበራረቅ፣ በጠላቶቹ ክፉኛ ሲንገላታ አላህ አዲስ ነቢይ አይልክለትም። ግና “ሙጀዲድ” – የለውጥ ሃዋርያ፣ ኢስላምን በወጉ የሚያስረዳና ለተፈጻሚነቱም ትግል የሚያደርግ ስብእና ወይም ቡድን ይልክለታል።

አቡ ሁረይራ ባስተላለፉትና አቡ ዳውድና ሐኪም ባቀረቡት ዘገባ የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-

إن الله يبعث لهذه الأمة على رأس كل مائة سنة، من يجدد لها دينها

“አላህ ለዚህ ኡምማ በየመቶ ዓመቱ ዲናቸውን የሚያቀናላቸው ሰው ይልካል።”

ይህን የለውጥ ኃላፊነት የሚወጣው አካል-ዑመር ኢብን ዐብዱል ዐዚዝ፣ ሻፊዒይና አልገዛሊ እንዳሉት- ግለሰብ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ሌሎች የሐዲስ ተንታኞች እንዳሉት ቡድን (ጀማዓ) ሊሆን ይችላል። የኋለኛውን እይታ ይበልጥ ገዢ ይመስላል። ይህ የለውጥ አራማጅ (ሙጀዲድ) አካል የደዕዋ፣ የእነጻ፣ ወይም የትግል (ጂሃድ) ቡድን ሊሆን ይችላል። እያንዳንዱ ሙስሊም ይህ የተጠቀሰው የለውጥ ሰው (አካል) እስኪመጣ እጁን አጣጥፎ መቀመጥን መምረጥ አለበት ማለት እንዳልሆነ ግን ልብ ይሏል። ይልቁንም እያንዳንዱ ሙስሊም የሚገባው በዚህ የ “ተጅዲድ” (ተሃድሶ) እንቅስቃሴ የኔ ሚና ምንድነው? በሚል ራሱን መጠየቅና ለሂደቱ አጋዥ ሆኖ መገኘት ነው[1]

9. የነቢዩ ዒሳ መምጣት

በሐዲስ ከተነገሩ ብስራቶች መካከል የመርየም ልጅ ዒሳ ዓለይሂ ሰላም በመጨረሻው ዘመን በኢስላማዊው ሸሪዓ ሊያስተዳድር የነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ወራሽ ሆኖ እንደሚመጣ የሚገልጹ ሐዲሶች ይገኙበታል።

የሐዲስ ጠበብት እንደሚሉት የዒሳን መምጣት የሚያበስሩ ሐዲሶች “ሙተዋቲር” ከሚሰኘው ትክክለኛነቱ ፍጹም ከተረጋገጠ የሐዲስ ደረጃ የደረሱ ናቸው። መውላና አንዋር አልከሽሚሪ የተባሉ የሐዲስ ጠቢብ “ተስሪሕ ቢማ ተዋተረ ፊ ኑዙሊ ዒሳ” በተሰኘ መጽሐፋቸው በዚህ አጀንዳ ዙሪያ አርባ ትክክለኛ (ሶሒሕና ሐሰን) ሐዲሶችን ዘክረዋል። ይህን መጽሐፍ ሸይኸ ዐብዱልፈታሕ አቡጉዳህ አዳብረውታል።

በሰማያትም ሆነ በምድር አንዳች በማይሣነው የአላህ ችሎታ ያመነ፣ አላህ በፍጥረተ ዓለሙ ውስጥ የረጫቸውንና መልዕክተኞቹን ያወረደበትን ተዓምራት ያጸደቀ ዒሳ ዓለይሂ ሰላም ከሰማይ እንደሚወርዱ ማመን አይከብደውም። በአን-ኒሳእ፤185 እንደተገለጸው ጠላቶቻቸው ሊገድሏቸው ካሴሩ በኋላ ወደ ላይ በመውሰድ ያነሳቸው አላህ ወደ ምድር እንደሚያወርዳቸው ማመን አይከብደውም።

10. የመህዲ ይፋ መሆን

መህዲ የሚባል መሪ መምጣቱ በሐዲስ መገለጹ ከነቢያዊ ብስራቶች ውስጥ ነው። በዚህ ረገድ የተለያዩ ሐሳቦች የቀረቡ ቢሆንም ዋናው ነጥብ ግን ኢስላምን በሚገባ የሚጠብቅ ሙስሊም መሪ መምጣቱ ነው። ምድር በጭቆናና በኢ-ፍትሃዊነት ስታቃስት አላህ ደግ መሪ ይልክላታል። ይህ መሪ የአላህን ዲን ሕያው ያደርጋል። ፍትህንም ያሰፍናል። ይህ ሐሳብ ሙሉ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን የሐሳብ ልዩነት ያለው የዚህን መሪ ስሙን፣ መልኩንና ቅርጹን እንዲሁም የሚመጣበትን ወቅት በሚመለከት ነው። ይህ ሊያሳስበን አይገባም። ዋናው ነገር መሠረታዊ ሐሳቡ ነው። እርሱን በሚመለከት በሁሉም ዘንድ ስምምነት አለ። እናም ከነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ብስራቶች መካከል እንደ አንዱ ይወሰዳል። በዚህ ረገድ ከተወሱ ሐዲሶች ውስጥ የሚከተለውን እንጠቅሳለን። አቡ ዳዉድ ዐሊይን አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ዋቢ አድርገው እንደዘገቡት ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ሲሉ ተንብየዋል፡-

لو لم يبق من الدنيا إلا يوم، لبعث الله رجلا منا، يملؤها عدلاً، كما ملئت جورًا

“ከዚች ዓለም (ዕድሜ) አንድ ቀን እንኳ ቢቀር አላህ ከኛ የሆነን ሰው ይልካል። ይህም ሰው ምድር በጭቆና እንደታመሰች ሁሉ በፍትሕ ይሞላታል።”

ሐኪምም አቡ ሰዒድን ዋቢ አድርገው የሚከተለውን ሐዲስ ዘግበዋል፡-

لا تقوم الساعة حتى تملأ الأرض ظلمًا وجورًا وعدوانًا، ثم يخرج رجل من أهل بيتى يملؤها قسطًا وعدلاً، كما ملئت ظلمًا وجورًا وعدوانًا

“ምድር በግፍና በጥላቻ ከተሞላች በኋላ ከኔ ዝርያ የሆነ ሰው ተነስቶ በግፍና በጭቆና እንደታመሰችው በፍትሕ ሳይሞላት በፊት ትንሳኤ አይከሰትም።”

ኋላ ላይ የመጡ አንዳንድ ጸሐፍት በመህዲ መምጣት ማመንን ከዐቂዳ (እምነት) ክፍል ውስጥ በማካተት በርሱ ማመን ግድ እንደ ሆነ አድርገው አቅርበዋል። ነገር ግን ይህን የአስተሳሰብ መስመር ሕዝበ-ሙስሊሙ ክስተቱን ከማመን በዘለለ እንደ አንድ የእምነት መሰረቱ አድርጎ መያዙ ተገቢ አይደለም። ቁርአን የነገረን በአላህ፣ በመላኢኮች፣ በመጻሕፍት፣ በመልዕክተኞችና በመጭው ዓለም መኖር ማመን በቂያችን ነው። በሐዲስ “በቀዷ ቀደር ማመን” የሚል ጽንሰ-ሐሳብ ቢታከልም በአላህ የማመን አካል በመሆኑ ቁርአን ለብቻው አላወሳውም።

በጥቅሉ የኢስላም ድል አድራጊነት ቁርአናዊና ሐዲሳዊ መሠረት ያለው እውነት ነው። ኢስላም-ዕድል ከተሰጠው- የሰዎችን ሕሊናና ቀልብ አስማምቶ መግዛት የሚችል ነው። ሙስሊሞች ኢማንና ተቅዋ እስካላቸው ድረስም እርዳታው አይለያቸውም። መጪው ጊዜ የኢስላም ነውና በጥሩ ተስፋ ለለውጥ እንነሳ። የአላህ ቃልኪዳን አይታጠፍም። የነቢዩ ሙሐመድ ትንቢትም እውነት ነው።

____________________

ምንጭ፡- “የኢስላም ድል አድራጊነት”-(አል-ሙበሺራት ቢል ኢንቲሳሪል ኢስላም)– በ ዶ/ር ዩሱፍ አልቀረዳዊ፤ ትርጉም ሀሰን ታጁ፤ ነጃሺ አሳታሚ።

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here