የኢስላም ድል አድራጊነት – በነቢያዊ ሐዲስ (ክፍል 1)

0
6680

ከነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሐዲስና ታሪክ የኢስላምን ድል አድራጊነት የሚያበስሩ በርካታ መልዕክቶችንና ክስተቶችን እናገኛለን። እነዚህን ነቢያዊ ብስራቶች በሐዲስ መድብሎቻችን ውስጥ በብዛት ይገኛሉ። ግና ሙስሊሞች ለኋላ ቀርነት በተዳረጉባቸው ዘመናት እነዚህን ሐዲሳዊ መልዕክቶች ዘነጓቸው። የሁከት (ፊትና) እና የቂያማ ምልክቶችን (አሽራጡ ሳዓህ) የሚመለከቱ ሐዲሶችን ብቻ እንጂ አያወሱም።

እነርሱንም ቢሆን ከየትኛውም ኡማውን ካለበት ተጨባጭ ከሚያወጣና ከሚቀይር በጎ ተግባር ሁሉ ተስፋ በሚያስቆርጥ መልኩ ነው የተረዷቸው። የቅን ጎዳና መሪ ከሆኑት ነቢይ ተከታዮቻቸውን ከበጎ ነገር ተስፋ የሚያስቆርጡ መልዕክቶች ይነገራሉ ተብሎ ፈጽሞ ሊታሰብ አይችልም።

የሐዲስ ሃብታችንን ስንፈትሽ መጭው ጊዜ የኢስላም እንደሚሆን፣ ነገ የሙስሊሞች እንደሆነ ከልብ ወለዳቸው የማይናገሩት ታላቅ ነቢይ ሙሐመድ ኢብን ዐብዱሏህ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በግልጽ ተናግረዋል። ይህ የሙስሊሞች ድል ለዓለም ሰላም ፍቅርና ደህንነት ታላቅ ተስፋ ነው።

ነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በራሳቸው ነገ የሚመጣውን ነገር (ገይብ) እንደማያውቁ እናምናለን። በራሱ የነገውን የሚያውቀው አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ብቻ ነው። በሱራ አን-ነምል፤65 አላህ እንዲህ ብሎናል፡-

قُل لَّا يَعْلَمُ مَن فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ الْغَيْبَ إِلَّا اللَّهُ

“በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ ሩቅን ምስጢር አያውቅም። ግን አላህ (ያውቀዋል)።”(አን-ነምል 27፤ 65)

ነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ስለነገ የሚያውቁት ነገር ቢኖር አላህ ያሳወቃቸውንና መረጃ የሰጣቸውን ያህል ብቻ ይሆናል። ነጋሪው አላህ ነው። ለወደደው ከሰፊ ዕውቀቱ ይለግስና ስለ መጪው ዘመን እንዲናገር ያስችላል።

عَالِمُ الْغَيْبِ فَلَا يُظْهِرُ عَلَىٰ غَيْبِهِ أَحَدًا إِلَّا مَنِ ارْتَضَىٰ مِن رَّسُولٍ

“(እርሱ) ሩቁን ምስጢር ዐዋቂ ነው። በምስጢሩም ላይ አንድንም አያሳውቅም። ከመልክተኛ ለወደደው ቢኾን እንጅ (ለሌላ አይገልጽም)።”(አል-ጂን 72፤ 26-27)

ነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በአላህ እገዛ ዘመናትን አቋርጠው ከተናገሯቸው ትንቢቶች መካከል የኢስላምንና የሙስሊምን ድል አድራጊነት የሚያበስሩትን እንደሚከተለው አቅርበናል።

1. ኢስላም በመላው ዓለም መስፋፋቱ

ተሚሙ ዳሪ እንዳወሱት የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-

ليبلغن هذا الأمر (يعني أمر الاسلام) ما بلغ الليل والنهار، ولا يترك الله بيت مدر ولا وبر، إلا أدخله الله هذا الدين، بعز عزيز، أو بذل ذليل، عزا يعز الله به الاسلام، وذلاً يذل الله به الكفر

“ይህ ጉዳይ (ኢስላም) ሌሊትና ቀን የደረሰበት ቦታ ሁሉ ይደርሳል። የአፈርም ሆነ የፀጉር ቤቶች (ድንኳኖች) ውስጥ ይህን ዲን አላህ ሳያስገባው አይቀርም…”

“ሌሊትና ቀን የደረሰበት ቦታ ሁሉ” የሚለው አገላለጽ ኢስላም እንደሚስፋፋ ያመለክታል። “የአፈርም ሆነ የፀጉር ቤቶች” የሚለው ደግሞ በከተማም በገጠርም ኢስላም እንደሚስፋፋ ያበስራል። የአላህ ቃል ይፈጸማል። አላህ የገባውን ቃል የሚያጥፍ ጌታ አይደለም።

“ከሁሉም ኃይማኖቶች በላይ ይፋ ይሆናል” የሚለው የቁርአን መልዕክት በምድር ላይ ካሉ እምነቶች ሁሉ ኢስላም ይበልጥ ተሰሚነትና ተደማጭነት የሚያገኝ መሆኑን በግልጽ ይናገራል። ይህ ቁርአናዊ ብስራት በአት-ተውባህ 33፣ በአል-ፈትሕ 28 እና በአስ-ሶፍ 9 ተደጋግሞ ተነግሯል። በመጀመሪያዎቹ የቁርአን ዘመናት ኢስላም የአይሁድንና የክርስትና እምነቶችን፣ የዐረቦችን የጣዖት አምልኮ እምነትንና የፋርሳዊያን የእሳት አምልኮ ሥርዓት አሸንፎ ወጥቷል። የተወሰኑ የእስያና የአፍሪካ ባሕላዊ ኃይማኖቶችንም አሸንፏል። ቢሆንም በመላው ዓለም በሚገኙ ኃይማኖቶች ላይ ግን ድል አልተቀዳጀም። እናም አላህ ተናግሯልና ኢስላም ከሁሉም ኃይማኖት በላይ ሆኖና ደምቆ የሚታይበትን ዘመን ገና እንጠብቃለን። ይህን ብስራት (ቢሻራ) ሚቅዳድ ኢብን አስወድ ያወሱት ሐዲስም ያጠናክረዋል። የአላህ መልዕክተኛ እንዳህ ብለዋል፡-

لا يبقى على ظهر الأرض بيت مدر ولا بر إلا أدخله الله كلمة الإسلام، بعز عزيز، أو بذل ذليل…

“በምድር ላይ ያለ የአፈርም ሆነ የፀጉር ቤት (ድንኳን) ውስጥ አላህ የኢስላምን መልዕክት ማስገባቱ አይቀርም…”(አሕመድ፣ ጦበራኒና ኢብን ሒባን)

2. ኢስላም ወደ አውሮፓ መመለሱና የሮም ሽንፈት

ኢማም አሕመድ በዘገቡት ሐዲስ አቢ ቁበይል እንዲህ ብለዋል፡-

ከዐብደላህ ኢብን ዓምር ኢብነል ዓስ ጋር ነበርን። “(ከታላላቅ) ከተማዎች (በሙስሊሞች እጅ) ለመጀመሪያ ጊዜ የምትገባው ማን ነች? ቆስጠንጢኒያ ወይስ የሮም ከተማ?” ተብሎ ተጠየቀ። ዐብደሏህ ጡሩራ ያለበት ሳጥኑ እንዲቀርብለት ጠየቀ። ከውጡ መጽሐፍ አወጣ። እንዲህ አለ፡- “ከአላህ መልዕክተኛ ዙሪያ ሆነን (የሚናገሩትን) ስንጽፍ[1]፡- “የትኛዋ ከተማ ነች ቀድማ የምትቀናው (ነፃ የምትወጣው)?” የሚል ጥያቄ ቀረበላቸው።“ቆስጠንጢኒያ (ኮኒስታንቲኖፕል/ቱርክ) ወይስ ሮም?” ተብለውም ተጠየቁ። (ነቢዩም) “የሂረቅል ከተማ በመጀመሪያ ትቀናለች (በኢስላም እጅ ትገባለች)” በማለት መለሱ።

ከሶሐባዎች ጥያቄ የምንረዳው ኢስላም ሁለቱን ከተሞች በቁጥጥሩ ሥር እንደሚያውል እርግጠኞች ነበሩ። ነዋሪዎቹም ኢስላምን እንደሚበቀሉ ተገንዝበዋል። ለማወቅ የፈለጉት ቅደም ተከተሉን ነው። ነቢዩም የሂረቅል ከተማ፣ ማለትም ቆስጠንጢኒያ በቅድሚያ በኢስላም እጅ እንደምትገባ ነገሯቸው[2]።በዚህ የነቢዩ ትንቢት መሠረት ቆስጠንጢኒያ (ኮኒስታንቲኖፕል) ከሮማውያን እጅ የምትወጣበት ዘመን መምጣቱ አልቀረም። አንድ የሃያ ሦስት ዓመት ወጣት ለዚህ ታላቅ ትንቢት መፈጸም ሰበብ ሆኗል። ሙሐመድ ኢብኑ ሙራድ ይባላል። በታሪክ ሙሐመድ ፋቲሕ (ድል አድራጊው ሙሐመድ) በመባል ይታወቃል። የሂረቅል ከተማ በዘጠነኛው የሂጅራ ዘመን (በ15ኛው ክፍለ ዘመን) በሙስሊሞች እጅ ገባች። ማክሰኞ ጀማደል አወል 857 ዓመተ ሂጅራ። ሜይ 19፣ 1453 (እ.ኤ.አ) መሆኑ ነው። ቆስጠንጢኒያ ከዚህ ወቅት ጀምሮ የሙስሊም ዓለም ዋነኛ አካል ሆናለች። ሕዝቡም ኢስላምን ተቀብሏል። የነቢዩ ሙሐመድ ትንቢት በዚህ ረገድ ተፈጻሚ ሆኗል። የሂረቅልን ከተማ ኢስላም ይዟል። የትንቢታቸው ሁለተኛ ክፍል ማለትም የሮም ዕጣ ፈንታ ወደ ፊት እውን እንደሚሆን ይጠበቃል። በዚህ ትንቢት እውን መሆንም ኢስላም ዳግም ወደ አውሮፓ ይገባል። ኢስላም ከአውሮፓ ሁለት ጊዜ እንዲወጣ መደረጉ ይታወሳል። የመጀመሪያው ለ800 ዓመታት ስፔንን ካስተዳደረ በኋላ በ1492 እንዲወጣ ተደርጓል። ሁለተኛው ክስተት ደግሞ የባልካን (ምስራቅ አውሮፓ) ክልል አገራትን ለ500 ዓመታት ከገዛ በኋላ ከቅርብ ምዕተ ዓመታት በፊት እንዲወጣ ተደርጓል።

ምናልባት ኢስላም ዳግም ወደ አውሮፓ በመመለስ ሮማን የሚያቀናው በትጥቅ ትግልና በአፈሙዝ ፍልሚያ ሳይሆን በብዕርና በደዕዋ (ጥሪ) እንደሚሆን እንገምታለን። በሐዲሱ “ቱፍተሑ” የሚለው ቃል የግድ ድሉ በትጥቅ ትግል መሆን እንዳለበት ያመለክታል የሚል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ አንገደድም። “ፈትሑል ሲልሚይ” ሰላማዊ ድል – ዲፕሎማሲያዊ የበላይነትም “ፈትሕ” ነው። የማቅናት ዘመቻ ነው። አላህ (ሱ.ወ) የሁደይቢያ ስምምነትን “ፈትሕ” (ድል) ብሎ ጠርቶታል። ያውም የድል ድል። “ፈትሐን ሙቢና” (ግልጽ ድልን አጎናጽፈንሃል) (አል-ፈትሕ፤9)። በወቅቱ የሁደይቢያን ዲፕሎማሲያዊ ስምምነት ውጫዊ ገጽታ በመመልከት በርካታ ሶሐባዎች እንደ ሽንፈት ቆጥረውት ነበር። አላህ ስለ “ፈትሕ” የሚገልጽ አንቀጽ ሲያወርድ “ለመሆኑ ድል የተባለው ይህ ስምምነት ነውን?” የሚል የግርምት ጥያቄ አቅርበዋል። ነቢዩም “አዎ ይህ (ስምምነት) ድል ነው” ብለዋል።

3. የኢስላም ግዛት በምስራቁም በምዕራቡም ስለመስፋፋቱ

ከሐዲሳዊ ብስራቶች ውስጥ ኢማም ሙስሊምና ሌሎች የሐዲስ አውታሮች ሠውባንን ዋቢ በማድረግ ያስተላለፉት ዘገባ ይገኝበታል።

ሠውባን የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል ይሉናል፡-

إنَّ اللهَ زَوى لِي الأرضَ، فرأيت مشارقَها ومغارِبها، وإن أمتي سيبلغ ملكها ما زوى لى منها، وأعطيت الكنزين: الأحمر والأبيض…

“አላህ መሬትን ሰብስቦ አሳይቶኛል። ምስራቁንም ምዕራቡንም። የተከታዮቼ ግዛት (አላህ) ሰብስቦ ያሳየኝን ያህል ይደርሳል። ሁለት ሃብትም ተሰጥቻለሁ። ቀይና ነጭ (ወርቅና ብር)…”

ይህ ሐዲስ የኢስላማዊው አስተሳሰብ ምስራቆችንና ምዕራቦችን (ማለትም ምድርን ባጠቃላይ) እስኪያጠቃልል እንደሚሰፋ ያበስራል። ከላይ የተወሱት የተሚምና የሚቅዳድ ሐዲሶች ኢስላማዊው መልዕክት እንደሚስፋፋና ቃሉ የበላይ እንደሚሆን የሚያበስሩ ሲሆኑ፣ ይህ ሐዲስ ደግሞ የኢስላማዊውን መንግስት ጥንካሬና የግዛቱን መስፋት፣ ማለትም ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የተመለከቱትን የምስራቅም ሆነ የምዕራብ ክፍል እንደሚያጠቃልል ይገልጻል። እናም ኢስላም የደዕዋ ብቻ ሳይሆን መንግሥታዊ ጥንካሬና ጉልበትም ይኖረዋል። በሌላ አገላለጽ የቁርአንና የኃይል ብርታት ያገኛል። ይህ ደግሞ ለበጎ ነገሮችን በር ከፋች ይሆናል።

4. ድሎትና ሰላም እንዲሁም የገንዘብ መትረፍረፍ

በዚህ ረገድም ሌላ ብስራት አለ። አቡ ሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ባወሱት ሐዲስ የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-

لا تقوم الساعة حتى تعود أرض العرب مروجًا وأنهارًا

“የዐረብ መሬቶች ወንዞች ሳይፈሱባቸው ዕለተ ትንሳኤ አይከሰትም።”(ሙስሊም)

ኢማም አህመድ በዘገቡት ሐዲስ ደግሞ ይህን እናገኛለን፡-

وحتى يسير الراكب بين العراق ومكة لا يخاف إلا ضلال الطريق

“ዕለተ ትንሳኤ እውን አይሆንም፤ አንድ መንገደኛ (ፈረሰኛ) ከዒራቅ እስከ መካ ሲጓዝ የመንገዱን አቅጣጫ መሳት እንጂ ሌላ የሚያሰጋው ነገር የማይኖርበት ዘመን ይመጣል።”

በተመሳሳይ ቡኻሪና ሙስሊም በዘገቡት ሐዲስ አቡ ሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ማለታቸውን ሰምተዋል።

لا تقوم الساعة حتى يكثر فيكم المال فيفيض، حتى يُهم ربَّ المال من يقبل منه صدقته، وحتى يعرضه فيقول الذى يعرضه عليه: لا أرب لى

“ገንዘብ በዝቶ እስኪትረፈረፍ ድረስ ዕለተ-ቂያማ አይመጣም። ባለገንዘብ ሶደቃውን የሚቀበልለት እስኪያሳስበው ድረስ። (ገንዘቡን) ማቅረብ ችሎም የቀረበለት ሰው ዛሬ ገንዘብ አያስፈልገኝም (ብሎ) ይመልስበታል።”

ይህን ሐዲስ በአቡ ሙሳ በኩል የተገኘው ሐዲስም ያጠናክረዋል፡-

ليأتين على الناس زمان يطوف الرجل فيه بالصدقة من الذهب! ثم لا يجد أحدًا يأخذها منه

“አንድ ሰው የወርቅ ዘካውን ይዞ የሚንከራተትበት ዘመን ይመጣል! የሚቀበለው ሰው ግን አያገኝም።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

ሐሪሰት ቢንት ወህብ ያስተላለፉት ዘገባም ይህንኑ ያመለክታል፡-

تصدقوا، فإنه يأتي عليكم زمان يمشي الرجل بصدقته فلا يجد من يقبلها، يقول الرجل: لو جئت بها بالأمس لقبلتها، فأما اليوم فلا حاجة لى بها

“ምጽዋት ለግሱ። ከመካከላችሁ አንዱ ዘካውን (ምጽዋቱን) ይዞ የሚንከራተትበትና ተቀባዩ ሰውም “ትናንት መጥተህ ቢሆን ኖሮ እቀበልህ ነበር። ዛሬ ግን አልፈልገውም” የሚልበት ዘመን ይመጣል።”(ቡኻሪና ሙስሊም)

ይህ ሁሉ ተድላና ብልጽግና እውን እንደሚሆን፣ ኑሮ እንደሚሻሻል ድህነት ከኀብረተሰቡ እንደሚወገድ፣ ዘካ የሚገባው ወይም ሊቀበል ፈቃደኛ የሚሆን ሰው እስከማይገኝበት ደረጃ እንደሚደርስ ያመለክተናል። ይህ የኢስላም ፍትሕ በረከት ነው። በሰዎች ሕይወት ኢማንና ተቅዋ የሚኖራቸው ፍሬ ነው። ይህንንም አላህ ( በቁርአን አረጋግጦልናል)።

وَلَوْ أَنَّ أَهْلَ الْقُرَىٰ آمَنُوا وَاتَّقَوْا لَفَتَحْنَا عَلَيْهِم بَرَكَاتٍ مِّنَ السَّمَاءِ وَالْأَرْضِ وَلَٰكِن كَذَّبُوا فَأَخَذْنَاهُم بِمَا كَانُوا يَكْسِبُونَ

“የከተማዋም ሰዎች ባመኑና በተጠነቀቁ ኖሮ በእነሱ ላይ ከሰማይም ከምድርም በረከቶችን በከፈትንላቸው ነበር። ግን አስተባበሉ። ይሠሩት በነበሩትም ኃጢኣት ያዝናቸው።”(አል-አዕራፍ 7፤ 96)[1] ይህ አባባል የሐዲስ መድብል ማዘጋጀትና መጻፍ በነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ዘመን እንደተጀመረ ያመለክታል። በዚህ ረገድ በርካታ መረጃዎች አሉ። ዐብደላህ ኢብኑ ዓምር የሐዲስ መልዕክቶችን የሚጽፉባት አስ-ሷዲቃሀ የተባለች መጽሐፍ እንደነበረቻቸው ተዘግቧል። በዚህ ሐዲስ ከሳጥን ውስጥ እንዳወጡት የተጠቀሰችው ኪታብ ይህች ልትሆን ትችላለች።

[2] ሂረቅል በነቢዩ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ዘመን የሮም አስተዳደር አንድ ክፍል የነበረው የቤዛንታንያ ኢምፓየር ያስተዳድር ነበር። እርሱንም ሆነ ሕዝቦቹን ወደ ኢስላም እንዲመራ ነቢዩ ጥሪ አድርገውለታል። ስለነቢዩና ይዘውት ስለመጡ ዓላማ በሚገባ ከተረዳ በኋላ የኢስላምን እውነታ መገንዘብ ችሏል። ይሁንና አማካሪዎቹና በዙሪያው የነበሩ ባለስልጣናት ኢስላምን ሊቀበሉ ባለመፈለጋቸው በውሳኔው ሊገፋበት አልፈለገም። አዱንያ አሸነፈችው። ሥልጣን አታለለው። በዑመር (ረ.ዐ) ዘመን ሶሪያ በሙስሊሞች እጅ እስከወደቀችበት ድረስ በሶሪያ ኖሯል። “ሶሪያ ሰላም ለአንች ይሁን፤ ከእንግዲህ አንገናኝም” በማለት ከተማዋን ለቆ አፈግፍጓል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here