ሕይወት እንደ መስጊድ
ወደዚህች ዓለም የመጣው አላህን ለማምለክ ተግባር እንደሆነ ሙእሚን ያምናል።
“ጋኔንንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም።” (አዝዛሪያት፤ 56)
አምልኮ (ዒባዳ) በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ብቻ ሳይወሰን ምድርን ለማነጽ፣ የአላህን ቃል በምድር ላይ የበላይ ለማድረግ፣ ትእዛዙን ለመፈጸም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ሁሉ ያካትታል።
ኢባዳ በሙእሚን ልቦና ውስጥ የጸና በሁሉም ጉዳዮች አላህን የማምለክ ስሜት ነው። እናም በሁሉም ስራዎቹ የአላህን ውዴታ ይሻል። ሁሉም እንቅስቃሴዎች ልክ እንደመንፈሳዊ ክንውኖች አምልኮ ይሆኑለታል። ዓላማው (ኒያው) በአላህ መንገድ እስከሆነ ድረስ።
ሙስሊም ከሚሰራቸው የኢባዳ ተግባራት መካከል ትልቁ የአላህን ዲንና ሸሪዓ ለመተግበር የሚያደርገው ጥረት ነው። ይህውም እርሱ በዘረጋው የሕይወት ስርዓት ግለሰባዊ፣ ቤተሰባዊና ማሕበራዊ ሕይወቱን እንዲመራ ለማስቻል የሚደረግ ትግልና ጥረት ነው።
ሙእሚን፣ አላህ የሰውን ልጅ እና አጋንንትን ለፈጠረበት ዋነኛ ዓላማ የማይንቀሳቀስ ከሆነ ኢባዳው ጎደሎ እንደሆነ ይሰማዋል። ይህም ዓላማ የአላህን ቃል የበላይ ማድረግ ነው። ይህ ሲሆን ነው የተከታዩ የአላህ ቃል መልእክት በተግባር የሚረጋገጠው፦
“ጋኔንንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም።” (አዝ ዛሪያት፤ 56)
ከአላህ ሌላ አምላክ እንደሌለና ሐመድም መልእክተኛው መሆናቸውን የመመስከር ትርጉምና ፋይዳ በተጨባጭ ሕይወት ውስጥ የሚረጋገጠውም እንዲህ ሲሆን ነው። ሙስሊም ከዚህ ሁለንተናዊ የኢባዳ ትርጓሜው በመነሳት በሕይወት ውስጥ ምንጊዜም የላቀ ዓላማ ያለው መሆኑን አይዘነጋም። ይህም ዓላማው የአላህ መመሪያ በሁ ም የሕይወት መስኮች ተፈጻሚ ይሆኑ ዘንድ መስራት ነው። ለዚህ ዓላማ የማይንቀሳቀስ ከሆነ እስልምናው ጎደሎ ነው። ይህን ዓላማ በተግባር እውን እንዲሆን ለማድረግ ልሰራ ለአላህ ታዛዣነቱ አይሟላም። ሙስሊም የዚህ ዲን አባል ለመሆኑ የምስክርነት ወረቀቱ ይህ ዓላማ ነው። ከእውነተኛና ታጋይ ስሊሞች ጎራ የሚያሰልፈውም ይህው ዓላማ ነው። በምድር ላይ የአላህ ወኪል ለሆነውና ከሌሎች ፍ ራን ይበልጥ ልቅና ለተሰጠው የሰው ልጅ ሕይወት ተገቢና ትርጉም እንዲኖራት የሚያደርገውም ይህው ተልእኮ ነው።
“የአደምንም ልጆች በእርግጥ (ከሌላው ፍጡር) አከበርናቸው። በየብስና በባህርም አሳፈርናቸው። ከመልካሞችም (ሲሳዮች) ሰጠናቸው። ከፈጠርናቸውም ፍጡሮች በብዙዎቹ ላይ ማብለጥን አበለጥናቸው።” (አል ኢስራእ፤ 70)
ሙስሊም ለዚህ ግላማ ተግቶ ይሰራል። ያለውን ሁሉ ሳይሰስት ለርሱ ያውላል። ጊዜውን፣ ገንዘቡን፣ ጉልበቱን ሁሉ ይሰጣል። የሕይወቱ ዋነኛ ክፍል፣ የመኖሩ ትርጉም ነውና። ወደ አላህ የሚቃረብበት ትልቁ ነገርም እርሱው ነው። ይህ ተልእኮ ከሌለ ሕይወት ለዛ አይኖራትም። ሕልውናውም ትርጉም የለውም። የአላህን ፍቅር ለማግኘትም ለአላህ ዲን እድገት አስተዋጽኦ ማድረግ ግድ ነው።
ዳእዋ ሙእሚን ወደ አላህ ከሚቃረብባቸው ኢባዳዎች ሁሉ በእርግጥም ትልቁ ነው። ወደ አላህ የሚያቃርበው ትልቁ ስራው ነው። እናም ለዚህ ትልቅ ዓላማ ራሱን አሰልፏል። ለርሱ ይሰራል። የርሱን አርማ ብቻ ያነሳል። ከርሱ ጎን ብቻ ይቆማል።
ቁርአንን በብዛት ያነባል
ሙስሊም ከዚህ የመጠቀ ደረጃ ላይ ለመድረስ በማራኪው የቁርአን ጥላ ስር ይጠለላል። ከቁርአን አንቀጾች ከሚፈልቀው ጣፋጭ ምንጭ ይጎነጫል። የበጎ ነገርን አድማስ ይመለከታል። ቁርአንን በተመስጦና በማስተንተን አዘውትሮ ይቀራል። ቁርአን የሚቀራባት የተለየች ወቅት አለችው። ያችን ወቅት በምንም ሁኔታ አያሳልፋትም። በዚህች ወቅት በቁርአን አማካይነት ከጌታው ጋር ይገናኛል። ቃሉን ይሰማል። ንግግሩን ያደምጣል። መልእክቱን ወደ ውስጥ በማስረጽ ነፍሱን ያጸዳዋል። አእምሮውን ያጎለብተዋል። ከቀልቡ ጋር በመቀላቀልም እምነቱን ይጨምርለታል።
“(እነሱም) እነዚያ ያመኑ ልቦቻቸውም አላህን በማውሳት የሚረኩ ናቸው። ንቁ! አላህን በማውሳት ልቦች ይረካሉ።” (አር ረእድ፤ 28)
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እጅግ ማራኪ በሆነ የገለጻ ስልታቸው ቁርአን የሚለግሰውን ውበትና ድምቀት ገልጸዋል። ቀኑንም ሌቱንም በቁርአን ንባብ ለማድመቅ፣ በጥልቅ እና ብሩህ መልእክቱ ለማዜም ይህ የነቢዩ ቃል ብቻ በቂ ነው። እንዲህ ብለዋል፦
“ቁርአን የሚቀራ ሙእሚን ምሳሌ ልክ እንደ ትርንጎ ነው። ሽታው ጥሩ ነው። ጣእሙም ጥሩ ነው። ቁርአን የማይቀራሙእሚን ደግሞ ልክ እንደ ተምር ነው። ሽታ የለውም። ጣእም ግን አለው። ቁርአንን የሚቀራ ሙናፊቅ አምሳያ ልክ እንደ አሪቴ ነው። ሽታው ያውዳል። ጣእሙ ግን ይመራል።፡ ቁርአንን የማይቀራ ሙናፊቅ ደግሞ ልክ እንደ እንቧይ ነው። ሽታ የለውም። ጣእሙም መራራ ነው።” (ቡኻሪና ሙስሊም)
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህም ብለዋል፦
“ቁርአንን ቅሩ። እርሱ በእለተ ቂያማ ለባለቤቶቹ አማላጅ ሆኖ ይመጣል።” (ሙስሊም)
እንዲህም ብለዋል፦
“ቁርአንን አሳምሮ የሚቀራ ከተከበሩ የአላህ ባሮች ዘንድ ይሆናል። አስቸግሮት እየተንተባተበ የሚቀራው ደግሞ እጥፍ ምንዳ ያገኛል።” (ቡኻሪና ሙስሊም)
ታዲያ እውነተኛ ሙስሊም- ይህ ሁሉ ደረጃና ምንዳ እያለ- ቁርአን ከመቅራትና መልእክቱንም ከማስተንተን ይዘናጋልን?
በመጨረሻም እስካሁን ያየነው፣ ሙስሊም ከአምላኩ ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ነው። እውነተኛና ጥልቅ እምነት፣ ቀጣይነት ያለው በጎ ስራ፣ ምንጊዜም የአላህን ውዴታ ለማግኘት መጣር። ለአላህ ለርሱ ተገዥነቱን በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ ያጸናል። አላህ እንዲህ በማለት የገለጸውን የሕይወት አላማውን በተግባር ይተረጉማል፦
“ጋኔንንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም።” (አዝ ዛሪያት፤ 56)