ሙስሊም መሆን፡ ሙስሊም ከአምላኩ ጋር (ክፍል 1)

0
5892

ንቁና ጥንቁቅ

ኢስላም ከአንድ አማኝ ከምንም ነገር በፊት የሚፈልገው በአላህ እዉነተኛ እምነት እንዲኖረዉ፤ ከርሱ ጋር ያለዉ ትስስር ጠንካራ እና ጽኑ እንዲሆን ነዉ። አምላኩን ዘወትር እንዲያስታዉስ፣ በርሱ እንዲመካ ይፈልጋል። የሚፈለግበትን ሁሉ ጥረት ካደረገ በኋላ የአላህን እገዛ እንዲሻ፣ ምንጊዜም የአላህ ሐይል፤ ብልሐት፤ እገዛና ድጋፍ እንደሚያስፈልገዉ በጥልቅ እንዲሰማዉ ኢስላም ይፈልጋል።

የሰዉ ልጅ የቱን ያህል ቢለፋም፣ የቱን ያህል ማድረግ ያለበትን ቢያደርግም ከአላህ እገዛና ድጋፍ ሊብቃቃ አይችልም።

እዉነተኛ መስሊም ንቁና ጥንቁቅ ሕሊና፣ አስተዋይ አእምሮ አለዉ። የሰማያትና የምድርን ድንቅ አፈጣጠር ጥበብ ያስተዉላል። የዚህን ዩኒቨርስና የሰዎችን ጉዳይ የሚያስኬድ፣ ነገሮችን የሚያንቀሳቅስ ሐይል መኖሩን አይዘነጋም። እናም ይህን ሐይል ዘወትር ያስታዉሰዋል። በእያንዳንዱ የሕይወት እስትንፋስ፣ በእያንዳንዱ የዓለም ክስተት ወስጥ የሐያልነቱንና የጥበቡን አሻራ ይመለከታል። እናም በርሱ ላይ ያለዉ እምነት ዘወትር ይጨምራል። ማስታወሱና መመካቱ ይበረታል።

إِنَّ فِي خَلْقِ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَاخْتِلَافِ اللَّيْلِ وَالنَّهَارِ لَآيَاتٍ لِّأُولِي الْأَلْبَابِ

“ሰማያትንና ምድርን በመፍጠር ሌሊትና ቀንንም በመተካካት ለባለ አእምሮዎች በእርግጥ ምልክቶች አሉ።”(አሊዒምራ፤ 190)

ለአምላኩ ታዛዥ

ስለዚህም እውነተኛ ሙስሊም ለአላህ ታዛዥና ተገዥ፣ ወሰኖችን የማይዳፈር፣ ስሜቶቹን የሚቃረን ትእዛዙን እንኳ ያለማመንታት የሚፈጽም መሆኑ ጥርጥር የለውም። የሙስሊም እምነት መለኪያ መስፈርት በትንሽም በትልቁም ጉዳይ ለአላህና ለመልእክተኛው ያለ ማንገራገር መታዘዝ ነው። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦

“ከናንተ አንዳችሁ ስሜቱ እኔ ያመጣሁትን መልእክት እስ ልተከተለ ድረስ አላመነም።” (አል ነወዊ)

አላህ እንዲህ ብሏል፦

فَلَا وَرَبِّكَ لَا يُؤْمِنُونَ حَتَّىٰ يُحَكِّمُوكَ فِيمَا شَجَرَ بَيْنَهُمْ ثُمَّ لَا يَجِدُوا فِي أَنفُسِهِمْ حَرَجًا مِّمَّا قَضَيْتَ وَيُسَلِّمُوا تَسْلِيمًا

“በጌታህም እምላለሁ በመካከላቸው በተከራከሩበት ፍርድ እስከሚያስፈርዱህ ከዚያም ከፈረድከው ነገር በነፍሶቻቸው ውስጥ ጭንቀትን እስከማያገኙና ፍጹም መታዘዝንም እስከሚታዘዙ ድረስ አያምኑም፤ (ምእመን አይኾኑም)።”  (አል ኒሣእ፤ 65)

አዎ፣ ለአላህ እና ለመልእክተኛው ትእዛዞች ሙሉ በሙሉ እጅ መስጠት፣ ሙሉ በሙሉም መታዘዝ። ያለዚህ እምነት የለም። ይህ ሳይሆን ሙስሊምነትም አይረጋገጥም።

ይህም በመሆኑ ከሙስሊም ሕይወት ውስጥ ከአላህ መመሪያና ከመልእክተኛው ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ትእዛዝ የማፈንገጥ ባህሪ አይታይም። ይህ ሁኔታ በራሱና፣ በቤተሰቡ፣ በስሩ ባሉት ሁሉ ላይ ይንጸባረቃል።

ከቤተሰቡ ጋር የተያያዙ ሐላፊነቶቹን ይወጣል

እነሆ በቤተሰቡ ጉዳይ ላይ የሚያሳየው ቸልተኝነት እንደሚያስጠይቀው ያውቃል። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦

“ሁላችሁም ኃላፊዎች ናችሁ። በሐላፊነታችሁም ትጠየቁበታላችሁ።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

እውነተኛ ሙስሊም ይህ ሐላፊነት ይሰማዋል። እናም በቤተሰቡ አባላት ውስጥ የሚታይ ግድፈት ያመዋል። አይታገሰውም። በፍጥነት ሊያስወግደው ይሞክራል። ውጤቱ ምንም ይሁን ምን በዝምታ አያልፈውም። ሐጢአትን በቤቱ ውስጥ የሚታገስ፣ እምነቱ የደከመ፣ ሐይማኖቱ የሳሳ፣ ወንዳወንድነቱ የሟሸሸ ሰው ብቻ ነው።

የአላህን ውሳኔዎች በጸጋ ይቀበላል

እውነተኛ ሙስሊም የአላህን ውሳኔዎች ምንጊዜም በጸጋ ይቀበላል። የሚከተለውን የአላህ መልእክተኛ ንግግር ምንጊዜም አይዘነጋም፦

“የሙእሚን ጉዳይ ይገርመኛል። ሁሉም ነገር ለርሱ በጎ ነው። መልካም ነገር ሲያገኘው አላህን ያመሰግናል። እናም በጎ ይሆንለታል። ክፉ ነገር ሲያገኘውም ይታገሳል። እናም በጎ ይሆንለታል።” (ቡኻሪ)

ምክንያቱም በቀዷቀደር ማመን የእምነት ዋነኛ መሠረት መሆኑን ከልብ ይረዳልና። ያገኘው ነገር ሊስተው፣ የሳተውም ሊያገኘው እንደማይችል በጥልቅ ያምናል። በአላህ የተወሰነ፣ በመለኮታዊው ብእር የተፃፈ፣ መዝገብ ውስጥ የሰፈረ ነገር አይቀርም።

የአላህን ውሳኔ በጸጋ መቀበል ከአላህ ዘንድ የበረከተ ምንዳ ያስገኛል። ከደጋግ እና ታዛዥ ስኬታማ የአላህ ባሮች ጋርም ያስመዘግባል።

ይህም በመሆኑ ሁሉም ነገር ለርሱ በጎ ነው። መጥፎ የሚባል ነገር የለም። ደግ ነገር ካገኘ አላህን ያመሰግናል። ለችሮታው ያወድሰዋል። መጥፎ የሚባል ነገር ካገኘውም የአላህን ውሳኔ በጸጋ በመቀበል ይታገሳል። እናም በሁለቱም ሁኔታዎች ምንዳ ያፍሳል። አጅር ያገኛል።

ወደ አምላኩ ተመላሽ

የሙእሚን ነፍስ ዘወትር ንቁና ጥንቁቅ እንደሆነ ይቆያል ማለት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ መዘናጋት ሊያገኘው ይችላል። እግሩን ያዳልጠዋል። ከእውነተኛ አማኝ የማይጠበቁ ድርጊቶችን ይፈጽማል።

ግና ወዲያውኑ ያስታውሳል። ወዲያውኑ ያስተውላል። ይጸጸታል። ወደ አምላኩ ይመለሳል። ምህረቱንም ይለምናል፦

إِنَّ الَّذِينَ اتَّقَوْا إِذَا مَسَّهُمْ طَائِفٌ مِّنَ الشَّيْطَانِ تَذَكَّرُوا فَإِذَا هُم مُّبْصِرُونَ

“እነዚያ የተጠነቀቁት ከሰይጣን የኾነ ዘዋሪ በነካቸው ጊዜ (ጌታቸውን) ይገነዘባሉ። ወዲያውም እነሱ ተመልካቾች ይኾናሉ።” (አል አእራፍ፤ 201)

መዘናጋት ከሙእሚን ቀልብ ውስጥ ብዙ አትቆይም። አላህን ከዘነጋ ቀልብ ላይ ነው ጎጆዋን የምትቀልሰው። የሙእሚን ቀልብ ምንጊዜም ለጸጸት ዝግጁ ነው። ለተውባ ዝግጁ ነው። የታዛዥነት ብርሃን አይከስምበትም።

ዓላማው አምላኩን ማስደሰት ነው

እውነተኛ ሙስሊም በድርጊቶቹ የሰዎችን ይሁን የአላህን ፍቅርና ውዴታ ይሻል። በእያንዳንዱ እርምጃው፣ በእያንዳንዱ ተግባሩ ይህን ይፈልጋል፡ አንዳንድ ጊዜም አላህን ለማስደሰት ሲል ሰዎችን የሚያስቆጣበት አጋጣሚ ይፈጠራል። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦

“ሰዎችን በማስቆጣት የአላህን ፍቅር የፈለገ፣ የሰዎችን ተንኮል አላህ ይበቃዋል። አላህን በማስቆጣት የሰዎችን ፍቅር የፈለገ፣ አላህ ጉዳዩን ለሰዎች ይተውለታል።” (ቲርሚዚ)

እናም ድርጊቶቹን በአላህ ሚዛን ይመዝናቸዋል። ሚዛን ከደፉ ይፈጽማቸዋል። ከቀለሉ ደግሞ ይተዋቸዋል።

በዚህ መልኩ የሙእሚን መስፈርት ቀጥ ያለ ነው። አይወላገድም። አላህን በአንድ ጉዳይ ታዞ በሌላ ጉዳይ በመወንጀል ሕይወቱን በተቃርኖ አይሞላም። አንድን ነገር አምና ሐራም አድርጎና ታቅቦ ዘንድሮ ሐላል በማድረግ አይዳፈረውም። መንገዱ ግልጽ፣ ሚዛኑም ትክክለኛ እስከሆነ ድረስ እንዲህ ዓይነት ተቃርኖ ቦታ የለውም። እነዚያ በመስጊድ ውስጥ ለአላህ በተመስጦ ሲሰግዱ ታይተው ገበያ ውስጥ በአራጣ ወይም በሌላ እርም በሆነ መንገድ ንግዳቸውን በሚያንቀሳቅሱ፣ የሚሰርቁ፣ የሚያታልሉ ወገኖች ትክክለኛ ሙስሊሞች አይደሉም። መስጊድ ውስጥ አላህን እያመለኩ፣ በቤታቸው፣ በመንገድ ላይ ወይም በሌላ ቦታ አላህን የሚቃረኑ ሰዎች የተሟላ የዲን ግንዛቤ የላቸውም።

ኢስላም ተከታዮቹ እያንዳንዱን ነገር በአላህ ሚዛን እንዲመዝኑ ይሻል። ይህን የሚያደርጉ ወገኖች ግማሽ ሙስሊሞች ናቸው። ምን አልባትም ከእስልምና የቀራቸው ስም ብቻ ሊሆን ይችላል።

በዚህ ባለንበት ዘመን ሙስሊሞች ከደረሱባቸው ውድቀቶች ሁሉ የከፋው ይህ ዓይነቱ ተቃርኖ ነው።

የግዴታዎች እና ሱንና ዒባዳዎችን ይፈጽማል

ትክክለኛ ሙስሊም ኢስላም ግዴታ ያደረገበትን ዒባዳዎች አሳምሮና አሟልቶ ይፈጽማል። በዚህ በኩል ከርሱ ዘንድ ቀልድ የለም። አቃሎ አይመለከታቸውም። ችላም አይላቸውም።

የግዴታ ሶላቶችን ወቅታቸውን ሳያሳልፍ ይሰግዳል። ሶላት የዲን መሠረት ነውና። ሶላት የሰገደ ዲንን ጠበቀ። እርሱን ችላ ያለ ዲኑን አፈረሰ።

ሶላት ከስራዎች ሁሉ በላጩ ነው። ኢብን መስዑድ እንዳስተላለፉት የአላህን መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም፦“ከስራዎች ሁሉ በላጬ የትኛው ነው?” በማለት ተጠየቁ።  “ሶላትን ወቅቱን ጠብቆ መስገድ።” ሲሉ መለሱላቸው። “ከርሱ ቀጥሎስ?” በማለት ጠየቁ።  የወላጆችን መብት መጠበቅ” አሉ። “ከርሱ ቀጥሎስ?” ተባሉ። “በአላህ መንገድ መዋጋት” አሉ።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

ሶላት በሰውየውና በአላህ መካከል አገናኝ ገመድ ናት። ሰውየው ከዱንያዊ ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ወጥቶ ራሱን ወደ አላህ ብቻ የሚያዞርባት ናት። ከርሱ መቀናትን፣ እገዛን፣ ከቀጥተኛው ጎዳና ላይ መጽናትን የሚለምንባት መድረክ ናት። እናም ሶላት ከስራዎች ሁሉ በላጭ መሆኗ የሚያስገርም አይደለም። ሙስሊም አላህን የመፍራት ስሜትን የሚሰንቅባት፣ ወንጀልንም የሚያጥብባት ኢባዳ ናትና።

አቡ ሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም፦“ከናንተ አንዳችሁ በቤቱ አጠገብ የሚያልፍ ወንዝ ቢኖርና ከዚያ ውስጥ በቀን አምስት ጊዜ ቢታጠብ ከአካሉ ላይ ቆሻሻ ይኖራል ብላችሁ ታስባላችሁን?  በማለት ባልደረቦቻቸውን ጠየቁ። አይኖርም ሲሉ መለሱላቸው። አምስት ወቅት ሶላቶችም እንዲሁ ናቸው። አላህ በነርሱ ወንጀልን ያብሳል። አሉ። (ቡኻሪና ሙስሊም)

ጃቢር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦

“የአምስት ወቅት ሶላቶች ምሳሌ ከናንተ በአንዳችሁ በር አጠገብ እንደሚያልፍና በቀን አምስት ጊዜ እንደሚታጠብበት ወንዝ ማለት ነው።” (ሙስሊም)

ኢብን መስዑድ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዳስተላለፉት አንድ ሰው አንዲትን (ባእድ) ሴት ሳመ። ከነቢዩ ዘንድ ቀረበና ግድፈቱን ነገራቸው። አላህ ወዲያውኑ የሚከተለውን የቁርአን አንቀጽ አወረደ፦

وَأَقِمِ الصَّلَاةَ طَرَفَيِ النَّهَارِ وَزُلَفًا مِّنَ اللَّيْلِ ۚ إِنَّ الْحَسَنَاتِ يُذْهِبْنَ السَّيِّئَاتِ ۚ ذَٰلِكَ ذِكْرَىٰ لِلذَّاكِرِينَ

“ሶላትንም በቀን ጫፎች ከሌሊትም ክፍሎች ፈጽም። መልካም ሥራዎች ኀጢአቶችን ያስወገድዳሉና። ይህ ለተገሳጮች ግሳጼ ነው።”  (ሁድ፤ 114)

ይህ አንቀጽ መልእክቱ እኔን ብቻ የሚመለከት ነውን? አላቸው። ተከታዮቼን በሙሉ ይመለከታል። አሉት። (ቡኻሪና ሙስሊም)

አቡ ሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦

“አምስት ወቅት ሶላቶችና ከጁሙዓ እስከ ጁሙዓ ከመካከላቸው ያሉትን ሐጢአቶች ያሳብሳሉ። ትልልቅ ወንጀሎች እስካልታከሉበት ድረስ።” (ሙስሊም)

ኡስማን ቢን አፋን እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦

“አንድ ሙስሊም የሶላት ወቅቱ በገባ ጊዜ ውዱእ አሳምሮ አድርጎ፣ ሩኩእና ሱጁዱንም በተመስጦ ፈጽሞ ከሰገዳት ከርሷ በፊት የነበረውን ሐጢአት ታስምራለች። ትልልቅ ወንጀሎች እስካልታከሉ ድረስ። ይህ ዓመቱን ሙሉ የሚደጋገም ነው።” (ሙስሊም)

የሶላትን ጥቅም የሚገልጹ ሐዲሶችና ዘገባዎች በርካታ ናቸው። በነዚህ ጥቂት ገጾች ዘርዝሮ መጨረስ ይከብዳል።

አላህን የሚፈራ ሙስሊም መስጊድ ውስጥ የመጀመሪያውን ጀማዓ ለማግኘትም የሚችለውን ሁሉ ጥረት ያደርጋል። ምክንያቱም የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም “በጀማዓ የሚሰገድ ሶላት በግል ከሚሰገደው ሃያ ሰባት ደረጃ ይበልጣል።” ማለታቸውን ያውቃልና። (ቡኻሪና ሙስሊም)

የጀማአ ሶላትን ልቅና የሚያወሱ የሐዲስ ዘገባዎች በርካታ በመሆናቸው በጥቂት ገፆች ማጠቃለል አይቻልም። ሙስሊም ከቻለ የመስጊዱን ዋነኛ ጀማአ (የመጀመሪያ ጀመአ) ለማግኘት ይጥራል። ምክንያቱም የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦

“የጀመአ ሶላት ለብቻ ከሚሰገድ ሶላት በሃያ ሰባት ደረጃዎች ይበልጣል።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

እንዲህም ብለዋል፦

“አንድ ሙስሊም ውዱእ አሳምሮ አድርጎ ለሶላት ዓላማ ብቻ ወደ መስጊድ ከወጣ አንድ እርምጃ በተራመደ ቁጥር አላህ ደረጃውን ከፍ ያደርግለታል። ወንጀሉን ያብስለታል። በሚሰግድ ጊዜም የሚሰግድበትን ቦታ ካልለቀቀ ወይም ውዱእ ካልፈታ መላኢኮች “አላህ ሆይ፣ እዝነትህንና በረከትህን አውርድለት” እያሉ ዱዓ ያደርጉለታል። ሶላትን እስከተጠባበቀ ድረስ ሶላት ውስጥ እንዳለ ይቆጠርለታል።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

ለጀማዓ ሶላት ጠዋት ማታ የሚመላለስን ሰው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በጀነት እንዲህ ሲሉአብስረዋል፦

“ጠዋትም ማታም ወደ መስጊድ የሚመላለስ በተመላለሰ ቁጥር አላህ በጀነት ውስጥ መስተንግዶ ያዘጋጅለታል።”(ቡኻሪና ሙስሊም)

ይህም በመሆኑ ሶሐቦች ለጀማዓ ሶላት እጅግ ጉጉና ብርቱ ነበሩ። አብደላህ ቢን መስ ድ ይህን በማስመልከት ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦

“አላህን ነገ ሙስሊም ሆኖ መገናኘት የሚሻ ሰው እነዚህን ሶላቶች በጀመዓ ይስገድ። አላህ ለነብያችሁ የመቀናትን መንገድ አሳይቷል። እነዚህ ሶላቶች ደግሞ ከመቀናት መንገዶች ናቸው። ጀማዓን ትታችሁ ከቤታችሁ ከሰገዳችሁ የነብያችሁን ሱንና ተዋችሁ። የነብያችሁን ሱንና ከተዋችሁ ደግሞ ጠመማችሁ። በነቢዩ ዘመን ከጀማዓ ሶላት የሚቀሩት ሙናፊቅ መሆናቸው በግልጽ የሚታወቅ ሰዎች ብቻ ነበሩ። በሰዎች ተደግፈው ለጀማዓ ሶላት የሚመጡ ሰዎች ነበሩ።”(ሙስሊም)

የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ለጀማዓ ሶላት ከሚሰጡት ትኩረትና ክብደት የተነሳ ከጀማዓ ያለ ምክንያት ወደ ኋላ የሚቀሩ ሰዎችን ቤት ለማቃጠል እስከማሰብ ደርሰው ነበር። እንዲህ ብለዋል፦

“ነፍሴ በእጁ በሆነችው ጌታ እምላለሁ፣ እንጨት እንዲሰበሰብና ለሶላት ኢቃማ እንዲደረግ አዝዥ፣ አንድ ሰው ሰዎችን ኢማም ሆኖ እንዲያሰግዳቸው በመወከል ከጀማዓ ሶላት ወደቀሩ ሰዎች በመሄድ ቤታቸውን ላቃጥል አስቤ አውቃለሁ።”(ቡኻሪና ሙስሊም)

ሰኢድ ቢን ሙሰየብ ለሰላሣ አመታት ያህል ሶላት ውስጥ የሰው ጀርባ ሳያዩ እንዲኖሩ ያደረጋቸው ይህ መንፈስ ነበር። ሁሌም ከመጀመሪያው ሶፍ የሚሰግዱ በመሆኑ ለሶላት የቆመ ሰው ጀርባ አይተው አያውቁም። እንደ ሰኢድ ያሉ በርካታ ሰዎች በኢስላማዊው ታሪክ ተመዝግበዋል።

ሶሐቦች የቤታቸው ርቀት ወደ ጀማዓ ከመምጣት አያግዳቸውም ነበር። አዛን ሲሰሙ ለሶላት ይሰለፋሉ። ወደ መስጊድ ይሄዳሉ። ሶላት በሕይወታቸው ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ነበረውና። ከዚህም አልፈው ቤታቸው ከመስጊድ በመራቁ ይደሰቱ ነበር። እርምጃቸው በዝቶ ብዙ ምንዳ እንዲያገኙና ብዙ ወንጀል እንዲታበስላቸው በመሻት።

ኡበይ ቢን ከእብ እንዳስተላለፉት አንድ የአንሷር ሰው ነበር። ቤቱ ከየትኛውም ሰው ቤት ይርቃል። “በጨለማና በርቀት ጊዜ የምትጋልባት አህያ ለምን አትገዛም?” ተባለ። “ቤቴ ከመስጊዱ አጠገብ እንዲሆን የምመርጥ አይደለሁም። ወደ መስጊድ በማደርገው ጉዞና ከመስጊድ ስመላለስ እርምጃዬ እንዲጻፍልኝ እሻለሁ።” አለ። የአላህ መልእክተኛም ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም፦ “አላህ ይህን ሁሉ አድርጎልሐል።” አሉት።

የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ቤታቸው ከመስጊድ የራቀ ባልደረቦቻቸውን ወደ መስጊድ ቀረብ እንዳይሉ መክረዋል። ወደ መስጊድ የሚያደርጉት እርምጃ ከመልካም ስራ መዝገባቸው ውስጥ እንደሚሰፍር አብስረዋቸዋል። እርምጃዎቻቸው ከንቱ እንደማይቀሩ ነግረዋቸዋል።

ጃቢር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዲህ ሲሉ አስተላልፈዋል፦

በመስጊድ ዙሪያ የነበረው ቦታ ባዶ ነበር። የበኑ ሰለማህ ጉሣ አባላት ከርሱ ላይ ለመስፈር አሰቡ። ይህ ሐሳባቸው ለነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ተነገረ። እርሳቸውም እንዲህ አሉ፦ “ከመስጊዱ አጠገብ ለመስፈር ማሰባችሁ ደርሶኛል።” እነርሱም፦ “አዎ፣ አስበናል።” አ”። የአላህ መልእክተኛም ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም፦ “በኒ ሰለማህ ሆይ፣ በታችሁን ያዙ። ኮቴዎቻችሁ ይጻፉላችኋል። ቤታችሁን፤ ያዙ ኮቴዎቻችሁ ይጻፉላችኋል።”  ሰዎቹም፦ ከመስጊድ አጠገብ መስፈራችን የሚያስደስተን አልሆነም። አሉ። (ቡኻሪና ሙስሊም)

አቡ ሙሣ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦

“በሶላት የበዛውን ምንዳ የሚያገኘው ከሩቅ ቦታ የሚመጣው ነው። ከኢማሙ ጋር ለመስገድ የሚጠባበቅ (ብቻውን) ሰግዶ ከሚተኛው የበለጠ ነው።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

በተለይም የሱብሒንና የኢሻን ሶላቶች በጀማዓ መስገድ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን የሚያመላክቱ ሐዲሶች በብዛት ተላልፈዋል። በነኝህ ወቅቶች በጀማዓ የሚሰገድ ሶላት እጅግ የበረከተ ምንዳ እንደሚያስገኝ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም አብራርተዋል። በዚህ ረገድ ከተነገሩ ሐዲሶች መካከል ሁለቱን ብቻ በማስታወስ እንወሰናለን፦

ኡስማን ቢን አፋን እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦

“ኢሻን በጀማዓ የሰገደ የሌሊቱን ግማሽ በሶላት እንዳሳለፈ ይቆጠራል። ሱብሒንም (አክሎ) የሰገደ ሌሊቱን በሙሉ እንደሰገደ ይቆጠራል።” (ሙስሊም)

አቡ ሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦

“ለሙናፊቆች ከሱብሒና ከኢሻእ ሶላት የበለጠ የከበደ የለም። ከነርሱ ውስጥ ያለውን ምንዳ ቢያውቁ ኖሮ እየዳሁም ቢሆን ይመጧቸው ነበር።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

ሙስሊም ከዚህ በተጨማሪ ሱንና ሶላቶችንም ችላ አይልም። ለመጭው ዓለም ስኬቱ እጅግ ይጠቅሙታልና። በሌሊትም በቀንም አቅሙ በፈቀደው ልክ ሱንናን ያዘወትራል። ሱንናን ማብዛት ወደ አምላክ ያቃርባል። በአላህ መፈቀር በእርግጥ ትልቅ ደረጃ ነው። አላህ አንድን ሰው ከወደደው የሚሰማበት ጆሮው፣ የሚያይበት አይኑ፣ የሚራመድበት እግሩ፣ የሚይዝበት እጁ ይሆነዋል። ተከታዩ ሐዲስ ይህን ደረጃ ያበስራል፦

“ባሪያዬ የእኔን ፍቅር እስኪያገኝ ድረስ በሱንናዎች ወደኔ ይቃረባል። በወደድኩት ጊዜ የሚሰማበት ጆሮው፣ የሚያይበት አይኑ፣ የሚይዝበት እጁ፣ የሚራመድበት እግሩ እሆንለታለሁ። ሲጠይቀኝ እሰጠዋለሁ። ጥበቃየን ሲከጅልም እጠብቀዋለሁ።” (ቡኻሪ)

ሰውየውን አላህ ሲወደው የሰማያትም የምድርም ደጋጎች ይወዱታል። አቡ ሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ያስተለለፉት ሐዲስ ይህን ያመለክታል። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦

“አላህ አንድን ባሪያ በወደደው ጊዜ ጅብሪልን ይጠራና “እገሌን እወደዋለሁና ውደደው” ይለዋል። ጅብሪልም ይወደዋል። ከዚያም በሰማይ ውስጥ ጥሪ ያደርጋል። “አላህ እገሌን ወዶታልና ውደዱት” በማለት በሰማይ ውስጥ ጥሪ ያደርጋል። የሰማይ ነዋሪዎችም ይወዱታል። ከዚያም በምድር ላይ ሰውየው ተቀባይነት ይኖረዋል። አንድን ባሪያ ከጠላው ደግሞ ጅብሪልን ይጠራና፦ ይህንን ባሪያየን ጠልቸዋለሁና ጥላው።” ይለዋል። ጅብሪልም ይጠላዋል። ለሰማያት ነዋሪዎችም፦ “አላህ እገሌ የተባለውን ባሪያውን ጠልቶታልና ጥሉት።” ይላቸዋል። ይጠሉታል። ሰውየው በምድር ላይ ተቀባይነትን ያጣል።” (ሙስሊም)

ይህም በመሆኑ ነው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እግራቸው እስኪያብጥና እስኪሰነጠቅ ድረስ የሌሊት ሶላት የሚሰግዱት። የአማኞች እናት አኢሻም፦ “የአላህ መልእክተኛ ሆይ፣ አላህ ያለፈውንም የሚመጣውንም ወንጀል ምሮልዎታል። ለምንድን ነው ይህን ያህል የሚደክሙት?  በማለት ጠየቀቻቸው። እርሳቸውም፦ “አመስጋኝ ባሪያ ልሆን አይገባኝምን?” በማለት መለሱ።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

ሙስሊም እያንዳንዱ ሶላቱ ጥሩ እንዲሆን ይሻል። ሸርጡን አሟልቶ ይፈጽማታል። ሶላት የአእምሮና የቀልብ ተሳትፎ የሌለበት አካላዊ እንቅስቃሴ ብቻ አይደለምና። ሶላቱን እንዳጠናቀቀም ወዲያውኑ ዘወር ብሎ በሕይወት ጣጣዎች ውስጥ አይዋጥም። ይልቁንም እንዳሰላመተ ባለበት ሆኖ ኢስቲግፋር ያደርጋል። ሱንና ዚክሮችን ይፈጽማል። አላህን ይለምናል። የዚህችን እና የመጭውን ዓለም በጎ ነገሮች ይጠይቀዋል። መቀናትን ይማጸነዋል።

ይህ ሲሆን ሶላት መንፈስን የማጽዳትና የማምጠቅ ተግባሯን ታከናውናለች። ቀልብን የማለዘብና ነፍስን የመግራት ስራዋን ትሰራለች። ለዚህም ነው የአላህ መልእክተኛ፦ “ሶላት የአይኔ ማረፊያ ሆነች።” ሲሉ የተናገሩት። (አህመድና ነሣኢ)

እውነተኛ ሰጋጆች የአላህ ጥበቃ ስር ናቸው። መጥፎ ነገር ሲያገኛቸው አይታወኩም። በጎ ነገር ሲያገኙም ንፉግ አይሆኑም።

إِنَّ الْإِنسَانَ خُلِقَ هَلُوعًا  إِذَا مَسَّهُ الشَّرُّ جَزُوعًا  وَإِذَا مَسَّهُ الْخَيْرُ مَنُوعًا إِلَّا الْمُصَلِّينَ

“ሰው ቅጠ ቢስ ኾኖ ተፈጠረ። ክፉ ነገር ባገኘው ጊዜ ብስጪተኛ። መልካምም ነገር (ድሎት) ባገኘ ጊዜ ከልካይ (ኾኖ ተፈጠረ)። ሰጋጆቹ ብቻ ሲቀሩ።”  (አል መዓሪጅ። 19-21)

ሙስሊም የዘካ ግዴታውንም በአግባቡ ይወጣል። በታማኝነት ይሰጣል። በጥንቃቄ ይፈጽማል። ለሚገባቸው ወገኖችም ያደርሳል። በሺዎች ቀርቶ በሚለዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ግድ ቢሆንበትም አይሰስትም። አላህ ግድ ካደረገበት የገንዘብ ሐላፊነት ለማምለጥ አይሞክርም።

ዘካ ችላ ሊባል የማይገባው ሸሪዓዊ ግዴታ ነው። በሐይማኖቱ ይዞታ ላይ ችግርና ድክመት፣ የስነ ምግባሩ ብክለት፣ የንፍቅ ሶላት ያየለበት ካልሆነ ይህን ኃላፊነት ችላ አይልም።

ዘካን የከለከለን መንግስት እንዲዋጋው መታዘዙ ክብደቱን ያመለክታል። አቡበክር ሲዲቅ ስለ ዘመናቸው ዘካ ከልካዬች የተናገሩት ቃል የዚህን ዲን ዱንያን ከአኼራ የማቆራኘት ባህሪ በማጉላት ዝንተ ዓለም ሲነገር ይኖራል። እንዲህ ብለው ነበር፦

“በአላህ ስም እምላለሁ፣ ሶላትን ከዘካ የነጠለን እዋጋዋለሁ።”

ይህ የአቡበክር መሐላ የዚህን ምሉእ ዲን ባህሪ፣ በሶላትና በዘካ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት በጥልቀት የተረዱ መሆኑን ያመለክታል። ቁርአን ዘካን ከሶላት አቆራኝቶ ያቀረበባቸው ሱራዎች እጅግ በርካታ ናቸው። ለአብነት፦

إِنَّمَا وَلِيُّكُمُ اللَّهُ وَرَسُولُهُ وَالَّذِينَ آمَنُوا الَّذِينَ يُقِيمُونَ الصَّلَاةَ وَيُؤْتُونَ الزَّكَاةَ وَهُمْ رَاكِعُونَ

“ረዳታችሁ አላህና መልክተኛው እነዚያም ያመኑት ብቻ ናቸው። (እነርሱ) እነዚያ ሶላትን በደንቡ የሚሰግዱ እነርሱም ያጎነበሱ ኾነው ምጽዋትን የሚሰጡ ናቸው።” (አል ማኢዳህ፤ 55)

إِنَّ الَّذِينَ آمَنُوا وَعَمِلُوا الصَّالِحَاتِ وَأَقَامُوا الصَّلَاةَ وَآتَوُا الزَّكَاةَ لَهُمْ أَجْرُهُمْ عِندَ رَبِّهِمْ وَلَا خَوْفٌ عَلَيْهِمْ وَلَا هُمْ يَحْزَنُونَ

“እነዚያ ያመኑ። መልካም ሥራዎችንም የሠሩ። ሶላትንም ያስተካከሉ። ዘካንም የሰጡ ለነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው አላቸው። በእነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም እነርሱም አያዝኑም።” (አል በቀራ፤ 277)

ትክክለኛ ሙስሊም ረመዷንን ከልብ ይጾማል። በጠቃሚነቱ አምኖበትና ከአላህ ምንዳን በመሻት። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦

“ረመዷንን አምኖበትና ከአላህ ምንዳን በመሻት የጾመ ያለፈ ወንጀሉ ይማርለታል።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

የጾምን ደንብና ስርዓትም ይረዳል። ሆዱ ብቻ ሳይሆን ሌላው አካሉም ይጾማል። ምላሱን ይጠብቃል። አላህን ከመወንጀል ይቆጠባል። ጾምን የሚያጎድፍ ድርጊት አይፈጽምም። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦

“ከናንተ አንዳችሁ በሚጾም ጊዜ ብልግና አይናገር። አይጬህ። አንድ ሰው ከሰደበው ወይም ከተጋደለውም “እኔ ጾመኛ ነኝ” ይበል።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

“ሐሰትን መናገርንና በርሱ መስራትን ያልተወ ምግብና መጠጥ መተው ለአላህ ምኑም አይደለም።” (ቡኻሪ)

ሙስሊም የረመዷንን ወር እንደዋዛ አያልፈውም። የጾም ወር ነው። ጾሙም የአላህ ነው። ምንዳውን የሚከፍለውም አላህ ራሱ ያለመጠን ነው። የአላህ ችሮታና ትሩፋት ወሰን እና መጠን የለውም። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ሲሉ ነግረውናል፦

“እያንዳንዱ የአደም ልጅ በጎ ስራ በአስር ይባዛለታል። እስከ ሰባት መቶ እጥፍም ሊበዛለት ይችላል። አላህ እንዲህ ብሏል፦ “ጾም ሲቀር። እርሱ የኔ ነው። እኔ (ያለ መጠን) እመነዳዋለሁ። ሰውየው ለኔ ብሎ ምግቡንና መጠጡን ይተዋልና። ጾመኛ ሁለት ደስታዎች አሉት። አንደኛው ሲያፈጥርና ሁለተኛው ጌታውን በሚገናኝ ጊዜ። የአፉ ጠረንም ከአላህ ዘንድ ከሚስክ ይበልጥ ያማረ ነው።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

እናም ሙስሊም የዚህን ወር ትሩፋት ይጠቀማል። በበጎ ስራም ይሞላዋል። ቀኑን በሶላትና በጾም፣ በቁርአንና በዚክር ያሳልፈዋል። ሌሊቱን በዱዓ፣ በተራዊህና በሌሊት ሶላቶች ያደምቀዋል። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦

“ረመዷንን አምኖበትና ከአላህ ምንዳን በመፈለግ የጾመ ያለፈ ወንጀሉ ይማርለታል።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በረመዷን ወር ከሌሎች ጊዜያት በበለጠ ለበጎ ስራ ይበረታሉ። በተለይም በመጨረሻዎቹ አስር ቀናት።

አኢሻ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በረመዷን ወር ከሌሎች ጊዜያት በበለጠ ይበረታሉ። በመጨረሻዎቹ አስር ቀናት ደግሞ ከሌሎቹ የረመዷን ቀናት ይበልጥ ይበረታሉ። (ሙስሊም)

አኢሻ እንዲህ ሲሉም አስተላልፈዋል፦

የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የረመዷን የመጨረሻናዋቹ አስር ቀናት በሚገቡ ጊዜ ሌሊቱን በሙሉ በኢባዳ ያሳልፋሉ። ቤተሰቦቻቸውንም ያነቃሉ። ይበረታሉ። ሽርጣቸውን ያስራሉ። (ቡኻሪና ሙስሊም)

ለይለቱል ቀድርን በመፈለግም ያዙ ነበር። የዚህችን ይህችን የሶላት ያሳለፈ ሌሊት በኢባዳ ማሳለፍንም እንዲህ በማለት አዘዋል፦

ለይለተል ቀድርን አምኖበት እና ምንዳን ከአላህ በመሻት የቆመ በኢባዳ ያሳለፈ ያለፈ ወንጀ  ይማርለታል።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

ይህም በመሆኑ ይህ ወር የኢባዳ ወር ሆኗል። እናም እውነተኛ ሙስሊም የረመዷንን ሌሊቶች አንዳንዶቹ እንደሚያደርጉት እንዲሁ በዋዛ ፈዛዛ አያሳልፍም። ሌሊት እንዲሁ በቀልድና በጨዋታ የሚያሳልፉ ሰዎች። ሊነጋጋ ሲል እንቅልፍ ይጥላቸዋል። ከዚያ በኋላ ለሱብሒ እንኳ አይነሱም። በዚያው እንደተኙ ያረፍዳ ።

ጠንቃቃ ሙስሊም ተራዊህ ይሰግዳል። ከርሱ እንደተመለሰ ብዙ አያመሽም። ወዲያውኑ ወደ እንቅልፍ ይሄዳል። ጥቂት አረፍ ብሎ ለሌሊት ሶላትና ለሱህር ይነሳል። ከዚያም ሱብሒን መስጊድ ውስጥ በጀማዓ ይሰግዳል።

የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሱህርን መመገብን አዘዋል። በረከት አለውም ብለዋል። እንስማቸው፦

“ሱህርን ተመገቡ። ሱህር በረከት አለውና።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

ይህም የሆነው ለሱህር መነሳት የሌሊትን ሶላት ስለሚያስታውስ ነው። ወደ መስጊድ ለመሄድ እና በጀማዓ ለመስገድም ብቁና ንቁ ያደርጋል። ለጾምም አካልን ያበረታል። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ያደርጉት የነበረው እና ለባልደረቦቸቸውም ያስተማሩት ይህን ነው።

ዘይድ ቢን ሳቢት አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዲህ ሲሉ አስተላልፈዋል፦

ከአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ጋር ሱህር ተመገብን። ከዚያም ወደ ሶላት ሄድን።

“በመካከላቸው ምን ያህል ጊዜ ነበር?  ተብለው ተጠይቀው “ሃያ አንቀጾችን ያህል ለማንበብ የሚያስችል ጊዜ ነው።” ሲሉ መለሱ።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

ሙስሊም ከረመዷን በተጨማሪ ሌሎች ሱንና ጾሞችም አያመልጡትም። ለምሳሌ የዓረፋን ቀን፣ የአሹራ ቀንና ዘጠነኛውን ቀን ይጾማል። እነዚህን ቀናት መጾም ወንጀልን የሚያስምር ትልቅ ተግባር ነው። አቡ ቀታዳ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በዓረፋ ቀን ስለመጾም ተጠይቀው እንዲህ ብለዋል፦

“ያለፈውንም የሚመጣውንም ዓመት ወንጀል ያስምራል።” (ሙስሊም)

ኢብን አባስ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የአሹራ ቀን ጾመዋል። ሌሎች ሰዎች እንዲጾሙትም አዘዋል።

አቡ ቀታዳ እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ የአሹራን ቀን ስለመጾም ተጠይቀው፦ “ያለፈውን ዓመት ወንጀል ያስምራል።” ሲሉ መልሰዋል። (ሙስሊም)

ኢብን አባስ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም፦“የሚቀጥለውን ዓመት በሕይወት ካለሁ ዘጠነኛውን ቀንም እጾማለሁ።” ብለዋል። (ሙስሊም)

ከሸዋል ስድስት ቀናትን መጾምም እንዲሁ ሱንና ነው። የዚህን ጾም ትሩፋት በማስመልከት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሲናገሩ፦

“ረመዷንን የጾመ፣ ከዚያም ከሸዋል የስድስት ቀናት ያስከተለው አመቱን በሙሉ እንደጾመ ይቆጠራል።” (ሙስሊም)

ጾም ከሚወደድባቸው ቀናት አንዱ በየወሩ ሦስት ቀናትን መጾም ነው። አቡ ሁረይራ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ይህን በማስመልከት እንዲህ ብለዋል፦

“ወዳጄ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሦስት ምክሮችን ለግሰውኛል። ከየወሩ ሦስት ቀናትን እንድጾም፣ ረፋድ ላይ ሁለት ረከአ እንድሰግድና ከመተኛቴ በፊት ዊትር ሶላት እንድሰግድ።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

አቡ ደርዳእ እንዲህ ሲሉ አስተላልፈዋል፦

“ወዳጄ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሦስት ምክሮችን ለግሰውኛል። በሕይወት እስካለሁ ድረስም እፈጽማቸዋለሁ። ከየወሩ ሦስት ቀናትን እንድጾም፣ የዱሐን ሶላት እንድሰግድና ዊትርን ከመስገዴ በፊት እንዳልተኛ።”(ሙስሊም)

አብደላህ ቢን አምር ቢን አል አስ እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦

“ከየወሩ ሦስት ቀናት መጾም አመቱን ሙሉ እንደመጾም ነው።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

እነዚህ ሦስት ቀናት ከየወሩ አስራ ሦስተኛው፣ አስራ አራተኛውና አስራ አምስተኛው ቀናት ቢሆኑ እንደሚመረጥ ዘገባዎች ያመለክታሉ። እነዚህ ቀናት አያመልቢድ በመባል ይታወቃሉ።

የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ከየወሩ ሦስት ቀናትን ይጾሙ እንደነበር የሚያመለክቱ ዘገባዎች ተላልፈዋል። ሙዓዘተል አደዊያህ እንዳስተላለፉት አኢሻን፦ “የአላህ መልእክተኛ በየወሩ ሦስት ቀናትን ይጾሙ ነበርን?” በማለት ጠየቁ። አኢሻም፦ “አዎን ሲሉ መለሱ። “የትኛቹን ቀናት?” ሲሉም ጠየቋቸው። “የትኞቹም ቢሆኑ ግድ አልነበራቸውም።” ሲሉ መለሱ። (ሙስሊም)

ትክክለኛ ሙስሊም ሐጅንም አይዘነጋም። ከቻለ የአላህን ቤት ይጎበኛል። ወደ ሐጅ ከመሄዱ በፊት የሐጅ ክንውኖችን ይማራል። እያንዳንዱን ነገር ትልቅ ትንሽ ሳይል ያጠናል። እናም የተሟላ ሐጅ አድርጎ ይመለሳል። ስርዓቱን ሳያጓድል፣ ጥቅሙን ሳያጣ። ልቦናው በኢማንና እጅግ በሚማርክ ስሜት ተሞልቶ ወደ ሐገሩ ይመለሳል።

እናቱ እንደወለደችው ቀን ከወንጀል የጸዳ ሆኖና በአላህ ታላቅ ዲን ላይ እምነት ጨምሮ ይመለሳል። ይህ እለት ከየዓለም ዳርቻ ሰዎችን በአንድ ቦታና ጊዜ ማሰባሰብ መቻሉ በእርግጥም ይደነቃል። እምነቱን ያድሳል።

ሐጅ በዚህች ዓለም ውስጥ በሌላ ቦታ የማይፈጸም ድንቅ ዓለማቀፋዊ ጉባኤ ነው። የተለያየ ዘር፣ ቀለም፣ ቋንቋ ያላቸው ሰዎች በአንድነት አላህን ያወሳሉ። ያወድሳሉ። ያመሰግናሉ። ክብሩን ይገልጻሉ። ልዑልና ኃያል ለሆነው አምላክ የታዛዥነት ቃል ያድሳሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here