አጥፊዎቹ (አል – ሙፍሲዱን)

0
4053

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፦

ظَهَرَ الْفَسَادُ فِي الْبَرِّ وَالْبَحْرِ بِمَا كَسَبَتْ أَيْدِي النَّاسِ لِيُذِيقَهُم بَعْضَ الَّذِي عَمِلُوا لَعَلَّهُمْ يَرْجِعُونَ

“የሰዎች እጆች በሠሩት ሀጢኣት ምክኒያት የዚያን የሠሩትን ከፊሉን ያቀምሣቸው ዘንድ መከራው በየብስና በባህር ተገለጠ (ተሠራጨ)። እነርሱ ሊመለሱ ይከጀላልና።” (አልሩም 30፤ 41)

ይህች የቁርኣን አንቀፅ ለአንድ አፍታ አቆመችኝ። እንዲህም አልኩኝ – ይህ በዓለማችን ላይ በስፋት የተሠራጨውና እየተሠራጨ ያለው የጥፋት መኣት እጃችን ባመጣው መዘዝ ነው ወይንስ በሌላ!? በጥፋቱስ የእኛ ድርሻ ይኖርበት ይሆን! ማታለል፣ መክዳት፣ ዝሙት፣ የህዝብ ሀብት መስረቅ፣ በስልጣን መባለግ፣ ለበጎ ዓላማ የቆሙ ደጋግና መልካም የሚባሉ ሰዎችን ማሰቃየት፣ ጥሩ ሠሪዎችን ማሠር፣ ደካሞችን መበደል … የነኚህ ሁሉ ነገሮች ውጤት ይሆን ዛሬ በፕላኔታችን ላይ የሚታየው ጥፋትና ክፋት! ወደ ኋላ ተመልሰን ይህንን ነገር ለማስተካከልስ ተስፋ ይኖረን ይሆን? አላህ አጥፊዎችን አይወድም። ዛሬ በምድራችን ላይ ጥፋትን ዓላማቸው አድርገው የሚንቀሣቀሱ ሰዎች ነገ በመጨረሻይቱ ዓለም ቦታ አይኖራቸውም። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

تِلْكَ الدَّارُ الْآخِرَةُ نَجْعَلُهَا لِلَّذِينَ لَا يُرِيدُونَ عُلُوًّا فِي الْأَرْضِ وَلَا فَسَادًا وَالْعَاقِبَةُ لِلْمُتَّقِينَ

“ይህች የመጨረሻይቱ አገር ለነዚያ በምድር ውስጥ ኩራትንና ማመፅን ለማይፈልጉት እናደርጋታለን። ያማረ መጨረሻም ለጥንቁቆቹ (አላህን ለሚፈሩት) ነው።” (አል ቀሰስ 28፤ 83)

ጀነት የአላህን ፈሪዎች እንጂ በጥፋት የሚሄዱ ሰዎች ማረፊያና መቀመጫ አይደለችም። በመሆኑም የነገን የአኺራ ህይወት ጀነትንና ጸጋዎቿን ለማግኘት የምንሻ ከሆነ ወደሷ ለመድረስ ከሚያግዱን ነገሮች መሸሽና መጠንቀቅ ይኖርብናል። ከዚህ ቀደም ለበርካታ ለውርደት ለዳረጉንና የዚህችን ዓለም ህይወታችንን ላበላሹብንና የአላህንም ፀጋ ላሣጡን ድርጊቶች እጅ ሠጥተናል። ይሀው መሸነፋችን ግን ቀጣይ መሆን የለበትም። በነሱ ይብቃ ማለት ይገባናል።

ከአጥፊዎች ባህሪ በከፊል

1. ቀጣፊ ምላሰኛ

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፦

وَمِنَ النَّاسِ مَن يُعْجِبُكَ قَوْلُهُ فِي الْحَيَاةِ الدُّنْيَا وَيُشْهِدُ اللَّهَ عَلَىٰ مَا فِي قَلْبِهِ وَهُوَ أَلَدُّ الْخِصَامِ وَإِذَا تَوَلَّىٰ سَعَىٰ فِي الْأَرْضِ لِيُفْسِدَ فِيهَا وَيُهْلِكَ الْحَرْثَ وَالنَّسْلَ وَاللَّهُ لَا يُحِبُّ الْفَسَادَ

“ከሰዎችም ውስጥ እርሱ ክርክረ ብርቱ ሲሆን በቅርቢቱ ህይወት ንግግሩ የሚደንቅህና በልቡ ውስጥ አላህን ባለው ነገር የሚያስመሰክር ሰው አለ። በዞረም ጊዜ በምድር ላይ በውስጧ ሊያበላሽና ይሮጣል አዝመራን እንሰሳዎችን ሊያጠፋ ይሮጣል።  አላህም ማበላሽትን አይወድም።” (አል-በቀራ 2፤204- 205)

በጥፋት የሚሮጥ ሰው ምላሱ ጣፋጭ አንደበቱ ማራኪ መሆኑ ግልፅ ነው። በነኚህም ሥር ተደብቆ የውስጥ ቅናቱንና ምቀኝነቱን ይዞ ይኖራል። አጥፊ ሰው በምላሱ ሥር የተደበቀ ሙናፊቅ ነው። ንግግሩና ምግባሩ አይገናኙም። ከዚህም አልፎ የአጥፊ ሰው ጥፋቱ በሰዎች ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም። አላህም በቁርኣኑ እንደገለፀው ትውልድን፣ አዝመራን ሆነ እንሠሣትን፣ ንብረትን ለማጥፋት ይሮጣል። በአጠቃላይ የነገሮች ማማርና ጥሩ መሆን ለሱ ምቾት አይሠጡትም።

2. ኩራትና ጥመት

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፦

وَإِذَا قِيلَ لَهُمْ لَا تُفْسِدُوا فِي الْأَرْضِ قَالُوا إِنَّمَا نَحْنُ مُصْلِحُونَ

“ለነርሱም በምድር ላይ አታበላሹ በተባሉ ጊዜ እኛ አሣማሪዎች ብቻ ነን ይላሉ።” (አል-በቀራህ 2፤11)

አዎን … አሣማሪዎች ነን ይላሉ። አጥፊ ሰዎች መቼም ቢሆን “አጥፊዎች ነን” ብለው በራሣቸው ላይ የመሠከሩበት ጊዜ አልታየም። በራሣቸው ጥፋትና በሌሎችም መጥፋት ላይ ስለመሠማራታቸው አያምኑም። እንዲያውም በሚያስገርም መልኩ እራሣቸውን አሣማሪና ጥሩ ሠሪ አድርገው ያቀርባሉ። እራስን “አሣማሪ፣ የጥሩ ሠሪ ሰዎች መሪ ነን” ብሎ ማቅረብ ደረጃው ከደጋግ (በጎ) ሰዎችም የበለጠ ነው። ሳሊህ /በጎ ሰው/ ማለት እራሱን፣ ሥነምግባሩንና አምልኮውን ለጌታው የሚያጠራ ሰው ነው። ሙስሊህ /አሣማሪ/ ማለት ደግሞ ለራሱም ሳሊህ ሆኖ ሌሎችንም የሚያስተካክል ከፍ ያለ ደረጃ ያለው ነው።

3. አጥፊ ሰው እላይ ላዩን ቢክድም ጥፋተኛ ስለመሆኑ ግን በውስጡ (በልቡ) ያውቃል

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፦

وَجَحَدُوا بِهَا وَاسْتَيْقَنَتْهَا أَنفُسُهُمْ ظُلْمًا وَعُلُوًّا فَانظُرْ كَيْفَ كَانَ عَاقِبَةُ الْمُفْسِدِينَ

“ነፍሦቻቸውም ያረጋገጧት ሲሆኑ በበደልና በኩራት በርሷ ካዱ። የአጥፊዎችም ፍፃሜ እንዴት እንደነበረ ተመልከት።” (አንነምል 28፤14)

  1. 4.ድግምትም ሌላው የአጥፊ ሰዎች መገለጫ ነው

አላህም እንዳለው

فَلَمَّا أَلْقَوْا قَالَ مُوسَىٰ مَا جِئْتُم بِهِ السِّحْرُ إِنَّ اللَّهَ سَيُبْطِلُهُ إِنَّ اللَّهَ لَا يُصْلِحُ عَمَلَ الْمُفْسِدِينَ

“(ገመዶቻቸውን) በጣሉም ጊዜ ሙሣ አለ- በርሱ የመጣችሁበት ነገር ድግምት ነው አላህም በርግጥ ያፈርሠዋል። አላህ የአጥፊዎችን ሥራ ፈፅሞ አያበጅምና።” (ዩኑስ 10፤81)

ሲህር (ድግምት) ሲባል ዓይነቱ ብዙ ነው። አፍዝ፣ አደንዝዝና አሣሣች የሆነ ነገር ሁሉ ሲህር ሊሆን ይችላል። ነቢዩም ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም “ከአገላለፅም ድግምት አለ” ብለዋል። በተለያዩ ሚዲያዎች ውሸትን እውነት፣ ጥቁሩን ነጭ በማስመሠል የሰዎችን አስተሣሠብና ህሊና በመያዝ አመለካከታቸውን ለማበላሸት የሚደረገው ጥረትም ከዚህ የሚተናነስ አይደለም። አላህ እነሱን በአጥፊነታቸው የገለጻቸው ሲሆን እኛን ደግሞ የአጥፊዎች እድሜ ረጅም ባለመሆኑ እንድንፅናና እንድንረጋጋ መክሮናል። አጥፊዎች የሰዎችን ዐይን፣ ህሊናና፣ አስተሣሰባቸውን ለመያዝ የቱን ያህል ቢሮጡም አላህ በመጨረሻ እውነትን ማንገሱና ለሷም ድልን መስጠቱ አይቀሬ ነው። ያኔም ውሸት ታፍራለች፤ መግቢያ በማጣትም ካናካቴው ትጠፋለች።

5. ማታለል

ሱረቱ ሁድ ላይ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፦

وَيَا قَوْمِ أَوْفُوا الْمِكْيَالَ وَالْمِيزَانَ بِالْقِسْطِ وَلَا تَبْخَسُوا النَّاسَ أَشْيَاءَهُمْ وَلَا تَعْثَوْا فِي الْأَرْضِ مُفْسِدِينَ بَقِيَّتُ اللَّهِ خَيْرٌ لَّكُمْ إِن كُنتُم مُّؤْمِنِينَ وَمَا أَنَا عَلَيْكُم بِحَفِيظٍ

“ህዝቦቼ ሆይ! ስፍርንና ሚዛንን ሙሉ። ሰዎችንም ነገሮቻቸውን አታጉድሉባቸው። በምድርም ውስጥ አጥፊዎች ሆናችሁ አታበላሹ። አላህ ያስቀረላችሁ ለናንተ የተሻለ ነው፤ ምእመናን እንደሆናችሁ። እኔም በናንተ ላይ ተጠባባቂ ኤይደለሁም።” (ሁድ 11፤85–86)

የሰዎችን ነገር ማጉደል ማለት ሀቃቸውን አለመሙላት፣ አደራን መዘንጋት፣ የሀቅ ባለቤት ያልሆነውን ሰው ትክክለኛ የሀቅ ባለቤት ከሆነው ማስቀደም እና ሆነ ብሎ እውነታን ማድበስበስ ነው።

6. ፀጋን ማስተባበል

ይህም ሌላኛው የጥፋት ዓይነት ሲሆን ለዚህም ትልቅ ምሣሌ ሊሆነን የሚችለው ቃሩን ነው። እሱም አላህ ሀብትን ሰጥቷቸው፣ ከብዙ ሰዎችም በችሮታው አስበልጧቸው እንደሱ ለሚያስቡና “የተሠጠሁት ባለኝ እውቀት እንጂ በሌላ አይደለም” ለሚሉ የአላህን ፀጋ አስተባባዮች ሁሉ ምልክት ነው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እሱንና እንደሱ የአላህን ፀጋ ሆነ ብለው ሊሚክዱ ሁሉ እንዲህ በማለት ይመክራል

وَابْتَغِ فِيمَا آتَاكَ اللَّهُ الدَّارَ الْآخِرَةَ وَلَا تَنسَ نَصِيبَكَ مِنَ الدُّنْيَا وَأَحْسِن كَمَا أَحْسَنَ اللَّهُ إِلَيْكَ وَلَا تَبْغِ الْفَسَادَ فِي الْأَرْضِ إِنَّ اللَّهَ لَا يُحِبُّ الْمُفْسِدِينَ

“አላህም በሠጠህ ሀብት የመጨረሻይቱን አገር ፈልግ፤ ከቅርቢቱም ዓለም ፈንታህን አትርሣ። አላህም ላንተ መልካምን እንዳደረገልህ ሁሉ መልካምን አድርግ። በምድርም ውስጥ ማጥፋትን አትፈልግ። አላህ አጥፊዎችን አይወድምና።” (አል-ቀሶስ 28፤ 77)

7. አምባገነኑ ፈርኦን የጥፋት ምልክትና የአጥፊዎችም ሁሉ መሪ ነበር

ፈርኦውን በቁርኣን ውስጥ የአጥፊ ገዠዎች ሁሉ ምልክት ተደርጎ ነው የተገለፀው። በዚህም ድርጊቱ እራሱንም ሆነ መላውን ህዝቡን በድሏል። ቁምነገሩ ሥሙን ማወቁ ላይ አይደለም። ባይሆን የጥፋት ባህሪዎቹን ማወቁ ነው። በየዘመናቱ የሚደጋገሙ ናቸውና እነኚህን ስለሱ የሚናገሩትን አንቀፆች እንመልከት

إِنَّ فِرْعَوْنَ عَلَا فِي الْأَرْضِ وَجَعَلَ أَهْلَهَا شِيَعًا يَسْتَضْعِفُ طَائِفَةً مِّنْهُمْ يُذَبِّحُ أَبْنَاءَهُمْ وَيَسْتَحْيِي نِسَاءَهُمْ إِنَّهُ كَانَ مِنَ الْمُفْسِدِينَ

“ፈርኦን በምድር ላይ ተንጠባረረ። ነዋሪዎቿንም የተከፋፈሉ ጓዶች አደረጋቸው። ከነሱ ጭፍሮች ከፊሎቹን ያዳክማል። ወንዶች ልጆቻቸውን በብዛት ያርዳል። ሴቶቻቸውንም ይተዋል። እርሱ ከሚያበላሹት ሰዎች ነበር።” (አል-ቀሶስ 28፤4)

وَقَالَ فِرْعَوْنُ ذَرُونِي أَقْتُلْ مُوسَىٰ وَلْيَدْعُ رَبَّهُ إِنِّي أَخَافُ أَن يُبَدِّلَ دِينَكُمْ أَوْ أَن يُظْهِرَ فِي الْأَرْضِ الْفَسَادَ

“ፈርኦን ‘ተውኝ ሙሣን ልግደል ጌታውንም ይጥራ (ያድነው እንደሆነ)። እኔ ሃይማኖታችሁን ሊለውጥ ወይም በምድር ውስጥ ጥፋትን ሊያሠራጭ እፈራለሁና።’ አለ።”  (ጋፊር 40፤26)

ይህ በምድር ላይ ጥፋትን የሚያስፋፉ አምባገነኖች ከትክክለኛ መሪና ዳዒ አንፃር የሚናገሩት ቃል ነው። በቆንጆ ሀቅ ፊት የምትነገር መጥፎ ቃል። ትክክለኛውን የኢማን መንገድ ለመጋፈጥ ሲሉ የሚሏት አስቀያሚ የክህደት ቃል ናት። ያለነሱ አሣማሪና የትክክለኛ ጎዳና ባለቤት ያለ አይመስላቸውም። በርግጥም ይህች ቃል ክህደትና እምነት ፊት ለፊት በተገናኙ ጊዜ ዘወትር የምትባል ናት። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ፈርኦንና ጭፍሮቹ እንዴት በምድር ላይ በጥፋት ሲሄዱ እንደነበር በቁርኣኑ ያወሣልናል። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፦

وَفِرْعَوْنَ ذِي الْأَوْتَادِ الَّذِينَ طَغَوْا فِي الْبِلَادِ فَأَكْثَرُوا فِيهَا الْفَسَادَ

“በፈርኦውንም ባለ ችካሎች በሆነው። በነዚያ በአገሮች ላይ ግፍ የሠሩ። በርሷም ውስጥ ጥፋትን ያበዙ በሆኑት።” (አል-ፈጅር፣ 10-12)

ከዚህ አንቀፅ እንደምንረዳው አምባገነኖች መጀመሪያ ላይ ጥፋታቸውን የሚጀምሩት በሌሎች ላይ ድንበር በማለፍመሆኑን ነው።በዚህም ድርጊታቸው የሚጋፈጣቸውና የሚናገራቸው ከሌለ ወደ ሌላ ደረጃ ይሸጋገራሉ። ቀስ እያለም አምባገነንነቱ ይሠፋና በምድር ላይ ጥፋቱ ይቀጥላል። በደሉም ይበዛል። ለዚህም ትልቅ ምሣሌ ሊሆንልን የሚችለው በቁርኣን ስለ ፈርኦን የተገለፀው ነው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፦

فَاسْتَخَفَّ قَوْمَهُ فَأَطَاعُوهُ إِنَّهُمْ كَانُوا قَوْمًا فَاسِقِينَ

“ህዝቡንም አቄላቸው ታዘዙትም እነርሱ አመፀኞች ህዝቦች ነበሩና።” (ዙኽሩፍ 43፤54)

ከላይ በተገለፀው አንቀፅ መሠረት ህዝቦቹ የዚህን አምባገነን ጥፋት እያዩ በዝምታ መታዘዛቸው ትክክል እንዳልነበር እንረዳለን። ይህንንም በማድረጋቸው አላህ እነሱንም ከአመፀኞች መደባቸው። ሌላም የቁርኣን አንቀፅ እንመልከት፡-

وَقَالَ الْمَلَأُ مِن قَوْمِ فِرْعَوْنَ أَتَذَرُ مُوسَىٰ وَقَوْمَهُ لِيُفْسِدُوا فِي الْأَرْضِ وَيَذَرَكَ وَآلِهَتَكَ قَالَ سَنُقَتِّلُ أَبْنَاءَهُمْ وَنَسْتَحْيِي نِسَاءَهُمْ وَإِنَّا فَوْقَهُمْ قَاهِرُونَ

“ከፈርዖንም ሰዎች ታላላቆቹ (ለፈርዖውን) ሙሣንና ሰዎቹን በምድር ላይ በጥፋት እንዲሄዱና አንተንና አማልክቶችህን እንዲተው ትተዋቸዋለህን? አሉ። እሱም ‘ወንዶች ልጆቻቸውን እንገድላለን፤ ሴቶቻቸውንም እናስቀራለን። እኛም ከበላያቸው ነን አሸናፊዎች።’ አለ።” (አል አዕራፍ 7፤127)

8. አይሁዶች

አይሁዶች ማን እንደሆኑ እናውቅ ይሆን?

كُلَّمَا أَوْقَدُوا نَارًا لِّلْحَرْبِ أَطْفَأَهَا اللَّهُ وَيَسْعَوْنَ فِي الْأَرْضِ فَسَادًا وَاللَّهُ لَا يُحِبُّ الْمُفْسِدِينَ

“ለጦርነት እሣትን በለኮሱ ቁጥር አላህ ያጠፋታል። በምድርም ውስጥ በጥፋት ይሮጣሉ። አላህም አጥፊዎችን አይወድም።” (አል-ማኢዳህ 5፤64) የተባሉት እነሱ ናቸው ።

አይሁዶች ሁሌም ፈተናዎችን በመቀስቀስ እንደቆሙ ናቸው። አንድ ማህበረሰብ የሆነውን ህዝብ በመከፋፈልና በሰዎች መካከልም ጦርነት እንዲጫር የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። መሪያቸውም ፈርኦን ነው። ያ ሰዎችን ከፋፍሎና ደካሞችንም ረግጦ ሲገዛ የኖረው። ያ ሥልጣኑን እንዳይቀናቀኑት በመፍራት ወንዶች ልጆችን በማረድ ሴቶችንም ያስቀር የነበረው። በቁርኣን ውስጥ አንድ አስከፊ ነገር የተወሣ እንደሆነ አይሁዶች ከዚያ ነገር ድርሻ አላቸው። አላህም ሱብሃነሁ ወተዓላ ትልቅ እርግማን አውርዶባቸዋል።

9. ሰዎችን ከአላህ መንገድ መመለስ፣ ወደ ሀቅ እንዳይመጡ ማገድና ግርዶ መሆን

ከጥፋት ከሚመደቡ ነገሮች መካከል አንዱ በሰዎችና በሀቅ መካከል መቆም ነው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፦

الَّذِينَ كَفَرُوا وَصَدُّوا عَن سَبِيلِ اللَّهِ زِدْنَاهُمْ عَذَابًا فَوْقَ الْعَذَابِ بِمَا كَانُوا يُفْسِدُونَ

“እነዚያ የካዱ ከአላህም መንገድ የከለከሉ ያጠፉ በነበሩት ምክኒያት ቅጣትን በቅጣት ላይ ጨመርንባቸው።” (አን ነህል 16፤ 88) በዚህ ሁኔታ በየመንገዱ አየተቀመመጡ ሰዎችን ወደ ጥመት የሚነዱ አሉ። መንገድ በማሣበር ሰዎች ሀቅን እንዳይቀበሉ ለእውነትም ጆሮ እንዳይሠጡ ያስፈራራሉ። ይህም የሆነው ለአንድም ሰው መልካምን ነገር ስለማይወዱ ነው። ለነሱ ተደራራቢ ቅጣት አለላቸው። ምክኒያቱም የጥፋታቸው ፋና ተደራራቢ ነውና።

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፦

وَلَا تَقْعُدُوا بِكُلِّ صِرَاطٍ تُوعِدُونَ وَتَصُدُّونَ عَن سَبِيلِ اللَّهِ مَنْ آمَنَ بِهِ وَتَبْغُونَهَا عِوَجًا وَاذْكُرُوا إِذْ كُنتُمْ قَلِيلًا فَكَثَّرَكُمْ وَانظُرُوا كَيْفَ كَانَ عَاقِبَةُ الْمُفْسِدِينَ

“(ሰዎችን) የምታስፈራሩና ከአላህም መንገድ በእርሱ ያመኑትን የምታግዱ መጥመሟንም የምትፈልጉዋት ኾናችሁ በየመንገዱ አትቀመጡ፡፡ ጥቂቶችም በነበራችሁና ባበዛችሁ ጊዜ አስታውሱ፡፡ የአጥፊዎችም መጨረሻ እንዴት እንደነበረ ተመልከቱ፡፡”  (አል-አዕራፍ 7፤ 86)

ቅጣታቸው

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፦

إِنَّمَا جَزَاءُ الَّذِينَ يُحَارِبُونَ اللَّهَ وَرَسُولَهُ وَيَسْعَوْنَ فِي الْأَرْضِ فَسَادًا أَن يُقَتَّلُوا أَوْ يُصَلَّبُوا أَوْ تُقَطَّعَ أَيْدِيهِمْ وَأَرْجُلُهُم مِّنْ خِلَافٍ أَوْ يُنفَوْا مِنَ الْأَرْضِ ذَٰلِكَ لَهُمْ خِزْيٌ فِي الدُّنْيَا وَلَهُمْ فِي الْآخِرَةِ عَذَابٌ عَظِيمٌ

“የነዚያ አላህንና መልእክተኛውን የሚዋጉ በምድርም ላይ ለማጥፋት የሚተጉ ሰዎች ቅጣት መገደል ወይም መሠቀል ወይም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን በማፈራረቅ መቆረጥ ወይም ከአገር መባረር ነው። ይህም ለነሱ በቅርቢቱ ዓለም ላይ ውርደት ሲሆን በመጭው ዓለምም ለነሱ ከባድ ቅጣት አለ።” (አል-ማኢዳህ 5፤ 33)

ይህ ነው የነሱ ምንዳ!! ይህም ከኢስላም ህግጋቶች አንዱ ነው። ብንፈልግም ባንፈልግም፤ ብንቀበልም ባንቀበልም። በአላህና በመልእክተኛው ህግጋት ላይ ጦርነት መክፈት ደግሞ በአላህ እና በመልእክተኛው ላይ ጦርነት እንደ መክፈት ነው። በአላህ መንገድ ከመቆምና የአላህ ህግጋት እንዳይሠራበት ከመከልከል የከፋ ወንጀል የለም።

መጨረሻቸው

አላህ ሱብሃሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፦

وَجَاوَزْنَا بِبَنِي إِسْرَائِيلَ الْبَحْرَ فَأَتْبَعَهُمْ فِرْعَوْنُ وَجُنُودُهُ بَغْيًا وَعَدْوًا حَتَّىٰ إِذَا أَدْرَكَهُ الْغَرَقُ قَالَ آمَنتُ أَنَّهُ لَا إِلَٰهَ إِلَّا الَّذِي آمَنَتْ بِهِ بَنُو إِسْرَائِيلَ وَأَنَا مِنَ الْمُسْلِمِينَ آلْآنَ وَقَدْ عَصَيْتَ قَبْلُ وَكُنتَ مِنَ الْمُفْسِدِينَ

“የኢስራኢልን ልጆች ባህር አሣለፍናቸው። ፈርኦውንና ሠራዊቱም ወሠን ለማለፍና ለመበደል ተከተሏቸው። መስጠምም ባገኘው ጊዜ- አመንኩ እነሆ ከዚያ ከኢስራኢል ልጆች እነሱ ከአመኑበት በስተቀር ሌላ አምላክ የለም። እኔ ከታዛዦቹ ነኝ። አለ። ከአሁን በፊት በርግጥ ያመፅክ የነበርክ ስትሆን አሁን (አመንኩ ትላለህ?!)” (ዩኑስ 10፤ 91-92 )

ፈርዖን አጥፊና የለየለት እንቢተኛ ነበር። ይህም የኖረለት ዓላማውና የሥራ ድርሻው ነበር። መጨረሻው ግን በሰው ዐይን ፊት በውሃ መበላት ሆነ። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የደካማ የኢማን ባለቤቶች ከሱ ትምህርት ይወስዱና የጥፋተኞች መጨረሻ እንዴት እንደሆነ ያውቁና ያስተነትኑ ዘንድ ይህን አደረገ። ይህ ሰው ልኩን ሣያውቅ “እኔ ታላቁ ጌታችሁ ነኝ” እስከማለት ደርሦ ነበር። መጨረሻ ላይ በአላህ እጅ በገባበት ሰዓት ግን የተውሂድን ቃል መናገሩና በአላህ አንድነት መመስከሩ አልፈየደውም። ለበርካታ አመታት በምድር ላይ በጥፋት ሲሄድ ሰዎችንም ባሮቹ አድርጎ ሲኖር ነበርና። አውቆ ሲያጠፋ ኖሯልና ጣእረሞት ላይ ሆኖ በአላህ አምላክነት መመስከሩ አንዳችም አልጠቀመውም። አላህ ይጠብቀን።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here