የእስልምና ዳይናሚዝም ምንጮች

0
3059

ምንም እንኳ ዛሬ ሙስሊሞች በብዙ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ እያለፉ ቢሆንም ቅሉ ኢስላም ሁሌም ጠንካራና ሕያው መሆኑ አይታበልም። ሙስሊሞች ደካማ ቢሆኑም ቅሉ ኢስላም እንዳልደከመ ማንም የሚያውቀው ሐቅ ነው። የኢስላም ሕያውነትና ጥንካሬ ዛሬም ሺዎችን እየሳበ ወደ ኢስላም እያስገባ መሆኑን እለት ተለት እየታዘብን እንገኛለን። አላህ በቁርኣን እንደነገረን ዛሬ ድረስ ኢስላምን (የአላህን ብርሃን) በአፋቸው “እፍ” ብለው ለማጥፋት የሚታትሩ ሠዎች አሉ።

يُرِيدُونَ أَن يُطْفِئُوا نُورَ اللَّهِ بِأَفْوَاهِهِمْ وَيَأْبَى اللَّهُ إِلَّا أَن يُتِمَّ نُورَهُ وَلَوْ كَرِهَ الْكَافِرُونَ

“የአላህን ብርሃን በአፎቻቸው ለማጥፋት ይፈልጋሉ። አላህም ከሓዲዎች ቢጠሉም እንኳ ብርሃኑን መሙላትን እንጅ ሌላን አይሻም።” (አት-ተውባ 9፤ 32)

ዛሬ ኢስላም እያስተናገደ እንዳለው መገፋትና የሥም ማጥፋት ዘመቻ ያስተናገደ ወይም እያስተናገደ ያለ ኃይማኖት የለም፤ አልነበረም። ሆኖም፤ እንደዚህ ኃይማኖት የሥም ማጥፋቱን በከፍተኛ ብቃት እየተቋቋመ ያለ የለም። ኢስላም እጅግ አስገራሚ ውስጣዊ ኃይል ወይም ዳይናሚዝም አለው። ኢስላምን በዚህ ሁሉ ፈተናዎች እና ጥቃቶች መካከል እያለፈ እንኳ ጥንካሬው እንዳይፈታ ያደረጉት ውስጣዊ የዳይናሚዝም ምንጮቹ ምን ምንድን ናቸው?

እነዚህን ምንጮች በጥሞና መቃኘት ወደፊት ሊገጥሙን የሚችሉትን ማናቸውንም ያልተለመዱ ክስተቶች በብቃት ለመወጣት ይረዳናል። ታላቁ የዘመናችን ሙስሊም ፈላስፋ እና ገጣሚ ምሁር ዶ/ር ሙሐመድ ኢቅባል አንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፡-

“ከሙስሊሞች ታሪክ የተማርኩት አንዱ ነገር፣ ሙስሊሞች በከፍተኛ ጭንቅ ውስጥ በገቡበት አጋጣሚ ነፃ የሚያወጣቸው ኢስላም ነው፤ ተገላቢጦሹ አይደለም።”

ከዚህ ቀጥሎ የኢስላ ዳይናሚዝም ምንጭ የሆኑትን አምስት ምንጮች እናስፍር፡-

  1. የኢስላም ኦሪጅናልነት (ቀዳሚነት)
  2. የኢስላም ዓለማቀፋዊነት
  3. የኢስላም ንጹህነትና አለመበረዝ
  4. የኢስላም ገርነትና ቸርነት
  5. የኢስላም ሠማያዊ መሠጠት (Divine authority)

1. የኢስላም ኦሪጅናልነት (ቀዳሚነት)

ኢስላም ከምድር መፈጠር አንስቶ የተላኩት ነብያት ሁሉ ኃይማኖት ነው። በሁሉም የአላህ መልክተኞችና ነብያት እናምናለን። ኢስላም የሁሉንም ነብያትና መልክተኞች ኦርጂናል አስተምህሮ ጠብቆ አቆይቷል። በዘመናችን ቋንቋ ለመናገር ኢስላም በታሪክ የተነሱትን ሁሉንም ሠማያዊ መልክቶች አንድ ላይ አቅፏል። አላህም በተከበረው ቃሉ፡-

شَرَعَ لَكُم مِّنَ الدِّينِ مَا وَصَّىٰ بِهِ نُوحًا وَالَّذِي أَوْحَيْنَا إِلَيْكَ وَمَا وَصَّيْنَا بِهِ إِبْرَاهِيمَ وَمُوسَىٰ وَعِيسَىٰ  أَنْ أَقِيمُوا الدِّينَ وَلَا تَتَفَرَّقُوا فِيهِ  كَبُرَ عَلَى الْمُشْرِكِينَ مَا تَدْعُوهُمْ إِلَيْهِ  اللَّهُ يَجْتَبِي إِلَيْهِ مَن يَشَاءُ وَيَهْدِي إِلَيْهِ مَن يُنِيبُ
 

“ለእናንተ ከሃይማኖት ያንን በእርሱ ኑሕን ያዘዘበትን ደነገገላችሁ። ያንንም ወዳንተ ያወረድነውን ያንንም በእርሱ ኢብራሂምን ሙሳንና ዒሳንም ያዘዝንበትን ሃይማኖትን በትክክል አቋቁሙ በእርሱም አትለያዩ ማለትን (ደነገግን)። በአጋሪዎቹ ላይ ያ ወደርሱ የምትጠራቸው ነገር ከበዳቸው። አላህ የሚሻውን ሰው ወደእርሱ (እምነት) ይመርጣል። የሚመለስንም ሰው ወደርሱ ይመራል።” (አሽ-ሹራ 42፤13;) በተጨማሪ ሱረቱል በቀራ 2፤131-133; ሱረት አል-ዒምራን 3፤83-85 ይመልከቱ።

2. የኢስላም ዓለማቀፋዊነት (Universality)

የኢስላም ሌላኛው ዳይናሚክስ መልዕክቱ ለፍጥረተ-ዓለሙ ሁሉ የተሠጠ መሆኑ ነው። ኢስላም ለሁሉም ዘመንና ቦታ ያገለግላል። ኃይማኖቱ በተፈጥሮው ዓለማቀፋዊ ነው። አንዳንድ ሙስሊም ምሁራን በግሎባል (ዓለማቀፍ) እና ግሎባልስቲክ (ዓለማቀፋዊ) ልዩነቱን ያብራራሉ። ኢስላም ዓላማዊ ሳይሆን ለዓለም የቆመ ነው። ኢስላም ኢምፔሪያሊስት ሳይሆን ዓለማቀፋዊ የሆነ ነው። ነብዩ ሙሐመድም (ሰ.ዐ.ወ) ገና ከመጀመሪያው ለመላው የሠው ዘር እንደተላኩ ገልጸዋል። “ዐለሚን” (ለመላው የሠው ዘር) የሚለው ቃል መካ ላይ በወረዱት የቁርኣን ምዕራፎች በብዛት ይስተዋላል። ለአብነት ያህል፡- ሱረቱል አንቢያ ም.27፤ 107፣ ሱረቱል ፉርቃን ም. 25፤1 እና ሱረተ አር-ረዕድ ም. 38፤87-88 ይመልከቱ።

ኢስላም የሠው ልጆች ሁሉ ከአንድ ምንጭ የተቀዱ የአንድ ቤተሠብ አባላት እንደሆኑ በአጽንዖት ያስረዳል። ኢስላም የሚናገረው ስለሁሉም የሠው ዘር ክብር ነው። ኢስላም ስለ ቀለም ልዩነት፣ ስለቋንቋ ጉራማይሌነት፣ ስለዘርና ጎሳዎች ይናገራል። ሆኖም፤ ዘረኝነትን፤ ጎሰኝነትን እና የቋንቋና የቀለም ዘረኝነትን አጥብቆ ያወግዛል። ኢስላም ለሠብዐዊ መብት፤ ለኃይማት ነጻነት እና ለጾታ እኩልነት የቆመ ኃይማኖት ነው። ኢስላም ተፈጥሮ የአላህ እጅ ሥራ መሆኗን ያስተምራል። በሠማይም በምድርም ያለ ሁሉ አላህን ያወድሳል። ኢስላም የተፈጥሮ ኃብቶች የኛ ብቻ ሳይሆን የሌሎችም ፍጥረታት ኃብት እንደሆኑ ያስገነዝባል። ስለ መጪው ትውልድ ማሠብም የኛ ኃላፊነት መሆኑንም አጥብቆ ያስተምራል።

3. የኢስላም ንጹህነትና አለመበረዝ

የኢስላም ዋነኛ ምንጮች (ቁርኣን እና የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሐዲስ) ያለተበረዙና ንጽህናቸውን ጠብቀው የሚገኙ ናቸው። አንዳንድ ጥቃቅንና ዝርዝር በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሙስሊም ምሁራን የተለያየ አቋም የሚይዙበት አጋጣሚ ቢኖርም መሠረታዊ የሆነው ጉዳይ ላይ ግን ሁሉም አንድ ነው። ሁሉም ሙስሊሞች መሠረታዊ የሆኑ ሃላልና ሐራሞች ላይ መግባባት አላቸው። አላህም ቁርኣንን ራሱ እንደሚጠብቀው ቃል ገብቷል።

إِنَّا نَحْنُ نَزَّلْنَا الذِّكْرَ وَإِنَّا لَهُ لَحَافِظُونَ

“እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው። እኛም ለእርሱ ጠባቂዎቹ ነን።” (አል-ሂጅር 15፤ 9)

4. የኢስላም ገርነትና ቸርነት

ኢስላም ቀላል፣ ገርና ያልተወሳሰበ ነው። ነብያችንም (ሰ.ዐ.ወ) በብዙ ሐዲሶች ላይ ይህንኑ መስክረዋል።

قال صلى الله عليه وسلم بعثت بالحنيفية السمحة سمحة سهلة ميسرة لا إفراط فيها و لا تفريط– أخرج أحمد في مسنده والطبراني والبزار وغيرهما عن ابن عباس( قال قيل : يا رسول الله ، أي الأديان أحب إلى الله ، قال: الحنيفية السمحة  وأخرجه البزار من وجه آخر بلفظ أي الإسلام

“እኔ በንጹህና ገር ኃይማኖት ተልኬያለሁ።” እንዲሁም “የትኛው ኃይማኖት ነው አላህ ዘንድ ይበልጥ ተቀባይነት ያለው?” ተብለው ሲጠየቁ “ንጹሁና ገሩ” ሲሉ መልሰዋል። (ሙስነድ አሕመድ፣ ጠበራኒ እና በዛዝ ሌሎችም ዘግበውታል)

ኢስላም በቀላል፣ ቸርና ለቀቅ ባለ የሕይወት ዘዬ ያምናል። ይህ ዘዬ በፍቅር እና በቸርነት፣ በሠላምና በመተሳሰብ ላይ የተገነባ ነው። በርግጥ ሕግና ደንቦች አሉት። ሁሉም ሕግጋት ግን ለሕይወት ጥሩ እና ሕይወትን የማያወሳስቡ ናቸው። ኢማም ኢብኑል ቀይም እንዳሉት፡-

فان الشريعة مبناها وأساسها على الحكم ومصالح العباد، في المعاش والمعاد، وهى عدل كلها ورحمة كلها ومصالح كلها وحكمة كلها، فكل مسألة خرجت من العدل إلى الجور وعن الرحمة إلى ضدها وعن المصلحة إلى المفسدة وعن الحكمة إلى العبث فليست من الشريعة وإن أدخلت فيها بالتأويل.

“ሸሪዓ የተመሠረተው እና የተደላደለው ለሠዎች ምድራዊና ዘላለማዊ ጥቅምን በማስገኘት ላይ ነው። ሸሪዓ በጥቅሉ ፍትሕ፣ እዝነት፣ ጥቅምና ጥበብ ነው። የትኛውም ከፍትህ ይልቅ በደል፣ ከርህራሄ ይልቅ ጭካኔን፣ ከጥቅም ጉዳትን እና ከጥበብ ድንቁርናን ካመጣ ሠዎች ሸሪዓ ነው ቢሉ እንኳ ያለምንም ጥርጥር ከሸሪዓ ያፈነገጠ ነው።” (ዒእላም አል-ሙዋቂን ቅጽ 1፤ ገጽ 14-15)

5. የኢስላም ሠማያዊ መሠጠት (Divine authority)

ከሁሉ የላቀው የኢስላም ዳይናሚዝም ሠማያዊ መሠጠቱ ነው (Divine authority) ነው። የዚህ ኃይማኖት ባለቤት አላህ ነው። ትልቁን ትኩረት የሚሠጠውም ለተውሂድ ነው። አንድ አምላክ ብቻ ነው ያለው። አላህ ብቻ ነው የዓለማቱ ጌታ። ስለዚህም ብቻውን ነው መመለክ ያለበት። ማንም በርሱ ላይ ሊጋራ አይገባም። በተውሂድ ማመን ለሙእሚን ኃይልና ምግብ ነው። ይህ ኃይል ለኃያሉ አምላክ አላህ (ሱ.ወ) እጅን በመስጠት ይገኛል። ተውሂድ የኢስላም መቅኒ እና ዋነኛ ጥንካሬ ነው። የተውሂድ ሠው ታላቅ ትዕግስት፣ ቆራጥነት እንዲሁም ቆፍጣናነት አለው። ምንም ችግር ቢመጣ አይፈታም። መተማመኛው አላህ ነው። ይህ ሲባል ግን የተውሂድ ሠው ማናለብኝ ያለበት ወይም ድንፋታም ነው ማለት አይደለም። ምክንያቱም፤ ስኬቱና እድሉ ሁሉ የተገኘው በራሱ ችሎታ ሳይሆን ከአላህ እንደሆነ ያውቃልና። እንዲህ አይነቱ ሠው አላህን ሰርክ ያመሠግናል፤ በርሱም ላይ ጥገኛ እንደሆነ ሁልጊዜ ያስታውሳል። ሙእሚን በዚህ ፍጥረተ-ዓለም ያለውን ሁሉ የፈጠረው አላህ እንደሆነና የሁሉ ነገር ባለቤትም ራሱ አላህ እንደሆነ ይገነዘባል። ይህ ግንዛቤው ሠፋ አድርጎ እንዲያስብ፣ ቻይ እንዲሆን እና ሠዎችን ተንከባካቢ እንዲሆን ይገፋዋል። በተውሂድ ማመን ከአዕምሮ ውስጥ ምቀኝነትን፣ ስግብግብነትን ሲያስወግድ፣ አላግባብ የመበልጸግን ፍላጎት ያጠፋል። በተውሂድ የሚያምን ሠው ሁሉ ነገር በአላህ እጅ እንደሆነ ያምናል። ክብር፣ ኃይል፣ ሥልጣን እና ሌሎችም ነገሮች ሁሉ በአላህ ቁጥጥር ሥር ያሉ ነገሮች ናቸው። ለፈለገው ይሰጣቸዋል። የሰው ልጅ ግዴታ መልፋት፣ መልካም መሥራት እና በአላህ ላይ ተስፋ ማድረግ ነው።

እነዚህ ከላይ የዘረዘርናቸው የኢስላም ወሳኞቹ ዳይናሚክሶች ናቸው። ዋነኞቹ ጥንካሬዎቹና መስህቦቹም ናቸው። እነዚህን መርሆች አጥብቀን ይዘን የራሳችን ዳይናሚክ አካላት ካደረግናቸው ስኬታማ እንሆናለን፤ ዓለምንም ወደ መልካምና ወደ ብርሃን እንወስዳታለን።

قُلْ إِنَّنِي هَدَانِي رَبِّي إِلَىٰ صِرَاطٍ مُّسْتَقِيمٍ دِينًا قِيَمًا مِّلَّةَ إِبْرَاهِيمَ حَنِيفًا  وَمَا كَانَ مِنَ الْمُشْرِكِينَ ﴿١٦١﴾ قُلْ إِنَّ صَلَاتِي وَنُسُكِي وَمَحْيَايَ وَمَمَاتِي لِلَّهِ رَبِّ الْعَالَمِينَ ﴿١٦٢﴾ لَا شَرِيكَ لَهُ  وَبِذَٰلِكَ أُمِرْتُ وَأَنَا أَوَّلُ الْمُسْلِمِينَ ﴿١٦٣﴾ قُلْ أَغَيْرَ اللَّهِ أَبْغِي رَبًّا وَهُوَ رَبُّ كُلِّ شَيْءٍ  وَلَا تَكْسِبُ كُلُّ نَفْسٍ إِلَّا عَلَيْهَا  وَلَا تَزِرُ وَازِرَةٌ وِزْرَ أُخْرَىٰ  ثُمَّ إِلَىٰ رَبِّكُم مَّرْجِعُكُمْ فَيُنَبِّئُكُم بِمَا كُنتُمْ فِيهِ تَخْتَلِفُونَ ﴿١٦٤﴾ وَهُوَ الَّذِي جَعَلَكُمْ خَلَائِفَ الْأَرْضِ وَرَفَعَ بَعْضَكُمْ فَوْقَ بَعْضٍ دَرَجَاتٍ لِّيَبْلُوَكُمْ فِي مَا آتَاكُمْ إِنَّ رَبَّكَ سَرِيعُ الْعِقَابِ وَإِنَّهُ لَغَفُورٌ رَّحِيمٌ

“እኔ ጌታዬ ወደ ቀጥተኛው መንገድ ትክክለኛን ሃይማኖት ወደ እውነት አዘንባይ ሲኾን የአብርሃምን መንገድ መራኝ። እርሱም ከአጋሪዎቹ አልነበረም” በል። “ስግደቴ፣ መገዛቴም፣ ሕይወቴም፣ ሞቴም ለዓለማት ጌታ ለአላህ ነው” በል። ለእርሱ ተጋሪ የለውም። በዚህም (በማጥራት) ታዘዝኩ። እኔም የሙስሊሞች መጀመሪያ ነኝ” (በል)። በላቸው እርሱ (አላህ) የሁሉ ጌታ ሲኾን ከአላህ በቀር ሌላን ጌታ እፈልጋለሁን? ነፍስም ሁሉ በራሷ ላይ እንጅ (ክፉን) አትሠራም። ተሸካሚም (ነፍስ) የሌላይቱን ሸክም (ኃጢአት) አትሸከምም። ከዚያም መመለሻችሁ ወደ ጌታችሁ ነው። ወዲያውም በእርሱ ትለያዩበት የነበራችሁትን ሁሉ ይነገራችኋል። እርሱም ያ በምድር ምትኮች ያደረጋችሁ በሰጣችሁም ጸጋ ሊፈትናችሁ ከፊላችሁን ከከፊሉ በላይ በደረጃዎች ከፍ ያደረገ ነው። ጌታህ ቅጣቱ ፈጣን ነው። እርሱም እጅግ መሓሪ ሩኅሩኅ ነው።” (አል- አንዓም 6፤161-165)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here