ኢስላማዊው የዓለም ግንዛቤ (WORLD VIEW)

0
2938

እያንዳንዱ ስርዓት፣ ኃይማኖታዊ ይሁን ዓለማዊ (ሴኩላር)፣ የራሱ የሆነ የዓለም ግንዛቤ (እይታ)-Worldview አለው። “Worldview” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ታዋቂው የጀርመን ፈላስፋ ኢማኑኤል ካንት Weltanschauung (ወልታንሹዋንግ) ካለው የጀርመን ቃል የተወሠደ ነው።

የዓለም ግንዛቤ ማለት “ስለ ፍጥረተ-ዓለሙ አመጣጥና ስለ ሠው ዘር ያለን ጠቅላላና ዝርዝር እምነትና ግንዛቤ ነው።”

እነዚህ እምነቶችና ግንዛቤዎች የሠዎችን ባሕሪና ሕይወት ይወስናሉ። በቅርቡ ምድር በፈጣሪ ኃያል ችሎታ ተገኝታለች በሚል እና በዝግመተ-ለውጥ (evolution) ፍጥረተ-ዓለሙ ተገኘ በሚሉ አስተሳሰቦች መካከል ክርክር ተካሂዶ ነበር።

አንዳንድ ሰዎች የዝግመተ-ለውጥ (evolution) ንድፈ-ሃሳብ ፍጥረተ-ዓለሙን ለመረዳት ብቸኛው ሳይንሳዊ መንገድ እንደሆነና ከዚህ ውጭ የሆነ የትኛውም አስተሳሰብ ተምኔታዊና ኢ-ሳይንሳዊ እንደሆነ ያምናሉ። በዚህ ዙርያ ጥናት የሚያደርጉ ሠዎች ግን የዘመናችን በዝግመተ-ለውጥ (evolution) ንድፈ-ሃሳብ (theory) ራሱ ከሌላ የዓለም ግንዛቤ የሚነሳ ነው። ይህ ግንዛቤ ደግሞ ማቴሪያሊዝም (ቁሳዊነት) ይባላል። የማቴሪያሊዝም ፍልስፍና የሚያምነው “የፍጥረተ-ዓለሙ መነሻ እና መድረሻ፤ ማጠንጠኛ እና መቆምያ፤ ማገር እና ምሰሶ ቁስ አካል ብቻ ነው” በማለት ነው። ይህ አስተሳሰብ የፈጣሪን ህልውና ይክዳል ወይም እምብዛም ለፈጣሪ ትኩረት አይሠጥም። ለነሱ ፍጥረተ-ዓለሙ (the universe) ራሱን በራሱ ያስገኘ ነው። በነሱ ግምት በፍጥረተ-ዓለሙ ያለ ነገር ሁሉ ህይወት ያለው ይሁን ግዑዝ የተገኘው ያለ ምክንያት ነው። መነሻውም የፊዚካልና ኬሚካል አካላት መስተጋብር ብቻ ነው። የማቴሪያሊዝም ሌላኛው መታወቂያ ሠው “ሩሕ” የለውም ብሎ ማመኑ ነው። በዚህ አስተሳሰብ መሠረት እኛ (ሕይወት ያለን ነገሮች ሁሉ) እጅግ የተራቀቁና በከፍተኛ ሁኔታ የተዋቀሩ ሞሎኪውሎች (molecules) ውጤት ብቻ ነን። ሐሳቦቻችንና ስሜቶቻችን ደግሞ በአዕምሯችን ውስጥ የሚገኙ ኬሚካሎች ውህደት ውጤት ነው። ስለዚህ፤ የማቴሪያሊዝም (የቁሳዊነት) ዋነኛ አጀንዳ ልክ የኢቮሉሽን ንድፈ-ሃሳብ እንደሚለው የጋራ ቅድመ-አያታችን አንድ ነው የሚል አይደለም። ይልቅስ፤ አጀንዳው ፈጣሪ አለ ወይስ የለም የሚል ነው።

ሠዎች የሚይዙት የዓለም ግንዛቤ አስተሳሰብና ድርጊታቸውን ይወስናል። ኢስላም ደግሞ እንደሌሎች ሁሉ ለራሱ የዓለም እይታ አለው። ቁርኣንም በተደጋጋሚ ይህንን ዩኒቨርስ የፈጠረው አሸናፊውና አዋቂው አምላክ (ዐዚዙን ዐሊም) መሆኑን ያስታውሰናል።

وَلَئِن سَأَلْتَهُم مَّنْ خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ لَيَقُولُنَّ خَلَقَهُنَّ الْعَزِيزُ الْعَلِيمُ

“ሰማያትንና ምድርንም ማን ፈጠራቸው ብለህ ብትጠይቃቸው ‘አሸናፊው ዐዋቂው (አላህ) በእርግጥ ፈጠራቸው’ ይላሉ።” (አዝ-ዙህሩፍ 43፤9)

አላህም በቁርኣን ይህንን ፍጥረተ-ዓለም እጅግ ብዙ ጊዜ “አያህ” (ተዓምር) ሲል ይጠራዋል። በአላህ መጽሃፍ “አያዎች” እንዳሉ ሁሉ በአላህ የተፈጥሮ መጽሃፍም ውስጥ “አያዎች” አሉ። በቁርኣን ያሉ አያዎች “ወህይ መትሉ” ሲባሉ በፍጥረተ-ዓለሙ ያሉ አያዎች ደግሞ “ወህይ መሽሁድ” ይባላሉ። በአላህ ቁርኣን ውስጥ ያሉት “ምልክቶችና” በፍጥረተ-ዓለሙ ያሉትን ተዓምራት በፅሞና ካጠናን ወደአንድ ድምዳሜ ይመራናል።

የአላህን ተዓምራት በተከበረው መጽሃፍ ላይ በጥሞና ካጠናንና ከመረመርን ፍጥረተ-ዓለሙን ስናጠና ከምናገኘው ጋር ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን። በዚህ በኩል ኢስላም ቁርኣንና ሳይንስ በመሠረቱ ልዩነት እንደሌላቸው ያምናል። ንጹህ ኃይማኖታዊ አስተምህሮና ትክክለኛ ሳይንሳዊ ምርምር ሳይጋጩ በጋራ ይሄዳሉ። ችግሩ የሚፈጠረው ኃይማኖት ከአፈ-ታሪክ ጋር ሲቀላቀል ወይም ሳይንስ ድንበርና ወሰኑን ሲያልፍ ነው።

ሱረቱ አር-ሩም ምዕራፍ 30 አንቀጽ 17-27 የአላህን ፍጥረት ውበት በተሟላ ኹኔታ ያሳየናል።

فَسُبْحَانَ اللَّهِ حِينَ تُمْسُونَ وَحِينَ تُصْبِحُونَ ﴿١٧﴾ وَلَهُ الْحَمْدُ فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَعَشِيًّا وَحِينَ تُظْهِرُونَ ﴿١٨﴾ يُخْرِجُ الْحَيَّ مِنَ الْمَيِّتِ وَيُخْرِجُ الْمَيِّتَ مِنَ الْحَيِّ وَيُحْيِي الْأَرْضَ بَعْدَ مَوْتِهَا  وَكَذَٰلِكَ تُخْرَجُونَ ﴿١٩﴾ وَمِنْ آيَاتِهِ أَنْ خَلَقَكُم مِّن تُرَابٍ ثُمَّ إِذَا أَنتُم بَشَرٌ تَنتَشِرُونَ ﴿٢٠﴾ وَمِنْ آيَاتِهِ أَنْ خَلَقَ لَكُم مِّنْ أَنفُسِكُمْ أَزْوَاجًا لِّتَسْكُنُوا إِلَيْهَا وَجَعَلَ بَيْنَكُم مَّوَدَّةً وَرَحْمَةً  إِنَّ فِي ذَٰلِكَ لَآيَاتٍ لِّقَوْمٍ يَتَفَكَّرُونَ ﴿٢١﴾ وَمِنْ آيَاتِهِ خَلْقُ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَاخْتِلَافُ أَلْسِنَتِكُمْ وَأَلْوَانِكُمْ  إِنَّ فِي ذَٰلِكَ لَآيَاتٍ لِّلْعَالِمِينَ ﴿٢٢﴾ وَمِنْ آيَاتِهِ مَنَامُكُم بِاللَّيْلِ وَالنَّهَارِ وَابْتِغَاؤُكُم مِّن فَضْلِهِ  إِنَّ فِي ذَٰلِكَ لَآيَاتٍ لِّقَوْمٍ يَسْمَعُونَ ﴿٢٣﴾ وَمِنْ آيَاتِهِ يُرِيكُمُ الْبَرْقَ خَوْفًا وَطَمَعًا وَيُنَزِّلُ مِنَ السَّمَاءِ مَاءً فَيُحْيِي بِهِ الْأَرْضَ بَعْدَ مَوْتِهَا  إِنَّ فِي ذَٰلِكَ لَآيَاتٍ لِّقَوْمٍ يَعْقِلُونَ ﴿٢٤﴾ وَمِنْ آيَاتِهِ أَن تَقُومَ السَّمَاءُ وَالْأَرْضُ بِأَمْرِهِ  ثُمَّ إِذَا دَعَاكُمْ دَعْوَةً مِّنَ الْأَرْضِ إِذَا أَنتُمْ تَخْرُجُونَ ﴿٢٥﴾ وَلَهُ مَن فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ  كُلٌّ لَّهُ قَانِتُونَ ﴿٢٦﴾ وَهُوَ الَّذِي يَبْدَأُ الْخَلْقَ ثُمَّ يُعِيدُهُ وَهُوَ أَهْوَنُ عَلَيْهِ  وَلَهُ الْمَثَلُ الْأَعْلَىٰ فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ  وَهُوَ الْعَزِيزُ الْحَكِيمُ
 

“አላህንም በምታመሹ ጊዜ በምታነጉም ጊዜ አጥሩት፤ (ስገዱለት)። ምስጋናም በሰማያትና በምድር ውስጥ ለርሱ ብቻ (የተገባው) ነው። በሰርክም፤ በቀትር ውስጥ በምትገቡም ጊዜ፤ (አጥሩት)። ሕያውን ከሙት ያወጣል። ሙታንም ከሕያው ያወጣል። ምድርንም ከሞተች በኋላ ህያው ያደርጋታል። እንደዚሁም (ከመቃብር) ትወጣላችሁ። እናንተንም ከዐፈር መፍጠሩ ከዚያም እናንተ ወዲያውኑ የምትበታተኑ ሰዎች መኾናችሁ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው። ለእናንተም ከነፍሶቻችሁ (ከጎሶቻችሁ) ሚስቶችን ወደእነርሱ ትረኩ ዘንድ መፍጠሩ፣ በመካከላችሁም ፍቅርንና እዝነትን ማድረጉ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው። በዚህ ውስጥ ለሚያስተውሉ ሕዝቦች ተዓምራቶች አልሉ። ሰማያትንና ምድርንም መፍጠሩ፣ የቋንቋዎቻችሁና የመልኮቻችሁም መለያየት፣ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው። በዚህ ውስጥ ለዐዋቂዎች ተዓምራቶች አልሉበት። በሌሊትና በቀንም መተኛታችሁ፣ ከችሮታውም መፈለጋችሁ ከምልክቶቹ ነው። በዚህ ውስጥ ለሚሰሙ ሕዝቦች ተዓምራቶች አልሉበት። ብልጭታንም ፈሪዎችና ከጃዮች ስትሆኑ ለእናንተ ማሳየቱ፣ ከሰማይም ውሃን ማውረዱ፣ በእርሱም ምድርን ከሞተች በኋላ ሕያው ማድረጉ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው። በዚህ ውስጥ ለሚያስቡ ሕዝቦች ተዓምራቶች አልሉበት። ሰማይና ምድርም (ያለምሰሶ) በትዕዛዙ መቆማቸው፣ ከዚያም (መልአኩ ለትንሣኤ) ከምድር ጥሪን በጠራችሁ ጊዜ እናንተ ወዲያውኑ የምትወጡ መሆናችሁ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው። በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የእርሱ ብቻ ነው። ሁሉም ለእርሱ ታዛዦች ናቸው። እርሱም ያ መፍጠርን የሚጀምር ከዚያም የሚመልሰው ነው። እርሱም (መመለሱ) በእርሱ ላይ በጣም ገር ነው። ለእርሱም በሰማያትም በምድርም ከፍተኛ ባሕርይ (አንድነትና ለእርሱ ብጤ የሌለው መኾን) አልለው። እርሱም አሸናፊ ጥበበኛ ነው” (አር-ሩም 30፤ 17-27)

እነዚህ አንቀጾች ዓለማዊ እይታችንን (worldview) ይሠጡናል። አላህ እየጠራን ያለው፡-

 1. እርሱን እንድናመሰግነውና ከሁሉም ጎዶሎ ባህርያት እንድናጠራው (ተስቢህና ተህሚድ)
 2. በፍጥረቱም ላይ እንድናስተነትን (ተፈኩር)
 3. ከእይታችንና ከምርምራችን ላይ እንድንማር (ዒልም)
 4. ቃላቶቹንም እንድናደምጥ (ሰምዕ)
 5. አዕምሯችንንም እንድንጠቀም (ዐቅል)

ይህ የቁርኣን አንቀጽ ሰባት ጠቃሚ ነጥቦችን ያስታውሰናል፡-

 1. አላህ ፈጣሪ ነው፡- ከምንም ነገር ያስገኛል። ሕይወት ይሠጣል፤ ይነሳልም። በሠማይም ሆነ በምድር ምሥጋና የሚገባው ለአላህ ብቻ ነው። በጠዋትም፣ በቀትርም በምሽትም ሁሉ ምሥጋና የሚገባው ለሱ ነው።
 2. አላህ ሠውን ሁሉ ከአፈር ፈጠረው፡- ውብ ቅርጽ ሰጣቸውና በምድር ሁሉ በተናቸው። አላህ እኛን በልዩ ሁኔታ ፈጠረን። ይሄ ለኛ ክብር ነው። ሆኖም፤ ከአፈር የተፈጠርን ነንና መኩራት አይገባንም። አፈር መሆን ማለት ደግሞ እንደ እንስሳቱና እጽዋቱ አይነት የሰውነት ተዋጽዖ እንዳለን ያሳየናል። የሠውነታችን መዋቅር የሌሎች ፍጡራንን ይመስላል። ሆኖም፤ የኛ የተለየ ነው።
 3. አላህ ወንዶችንና ሴቶችን በተገቢው አቋምና ቅንብር ፈጥሯል፡- አንዳቸውንም ለአንዳቸው ይመቹ ዘንድ አድርጓቸዋል። ጥንዶችም አደረጋቸው በመካከላቸውም ፍቅርና ርኅራኄን አኖረ። አካላዊ መሳሳብንና መንፈሳዊ ትስስርንም ሠጣቸው። በዚህም ምክንያት በጋራ ይሠራሉ፤ ልጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በጋራ ይንከባከባሉ። ለዚህ ነው ቤተሠብም የአላህ ፍጥረት ነው የምንለው።
 4. የሠው ዘር ብዙና የተለያየ ዐይነት ነው፡- ተመሳሳይ አፍ፣ ተመሳሳይ ምላስ እና ተመሳሳይ አገጭ ግን የተለያዩ ቋንቋዎችና የቋንቋ ዘየዎች። የቆዳችን ቀለም መለያየትም እጅግ አስገራሚ ነው። ሁለት ሠዎች አንድ ቤተሰብ ውስጥ እንኳ ሆነው ቀለማቸው ይለያያል። ይህን መሠረታዊ የተፈጥሮ ሕግ የተረዱ ሠዎች ከሌሎች ጋር በሕብርና በሠላም ይኖራሉ። በየአጋጣሚው ግጭትና ረብሻ የሚፈጥረው ይህን ብዙህነት አለማወቅ ነው።
 5. አላህ ቀንና ሌሊትን ለሥራና ለዕረፍት ይሆን ዘንድ ሠጠን፡- ሥራ በመሥራት ራሳችንንና ቤተሠቦቻችንን መደጎማችን ብቻ ዕረፍት ማግኘታችን ከአላህ ተዓምራት የሚቆጠር ነው። የአላህን ቃል የሚሠሙ ሠዎች ትክክለኛው ሥራና ተገቢውን ዕረፍት ይረዳሉ።
 6. አላህ በተጠቀሠው አንቀጽ መብረቅና ብልጭታ ከርሱ ኃይልና ችሎታ ማሳያዎች እንደሆኑ ያሳስበናል፡- ያስፈራሉ ግን ይጠቅማሉ። አላህ የሠጠንን የተፈጥሮ ችሎታ በመጠቀምም እነዚህን ተፈጥሯዊ ክስተቶች ለራሳችን ጥቅም ማዋል እንችላለን።
 7. የተጠቀሰው የቁርኣን አንቀጽ በመጨረሻ ላይ ዘላለም በምድረ-ዓለም (በዱንያ) ኗሪዎች እንዳልሆንን ይገልጽልናል፡- እንሞታለን፤ አላህም በዕለተ-ትንሳዔ ይቀሰቅሰናል። ስለሆነም፤ በሕይወታችን ሁሉ ትዕዛዛቱን እየተገበርን የከለከለንንም እየተጠነቀቅን በመቆየት ዘላለማዊ ሽልማትን እንጠብቅ።

ይህ እንግዲህ አስተሳሰባችንና ድርጊታችንን የሚወስነው ኢስላማዊ የዓለም ግንዛቤ (worldview) ነው። ይህ አይነቱ የዓለም ግንዛቤ ምክንያታዊ፣ አመንዮአዊ (logical) እና ሳይንሳዊ ነው። በዚህ ዓለማዊ ግንዛቤ አፈ-ታሪክ የለም። ቀላልና ግልጽ ነውም። ይህ ዓለማዊ ግንዛቤ ምሉዕ (comprehensive) እና ፍጥረተ-ዓለሙን ሁሉ ያካለለ ነው። የሠው ልጅን መሠረታዊ የሕይወት (ግለሠባዊ፣ ቤተሰባዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ) ገጽታዎች ያካለለ ነው። ይህ አስተሳሰብ ሕይወት ከየት መጣ፣ ለምን መጣ፣ ወደየት ይሄዳል፣ ወዘተ የሚሉትን ጥያቄዎች ይመልሳል። ይህ ኢስላማዊ ዕይታ ሠዎችን ዝቅ ያሉም (የማይንቀባረሩም) የተከበሩም ያደርጋቸዋል። ልብና አዕምሮንም ያረጋጋል። ሠዎችን በሥነ-ምግባር የታነጹ ያደርጋቸዋል። ሠዎች በየትኛውም የምድር ክፍል ቢኖሩ ለሌሎች የሚጨነቁበት አድማሳቸው ይሠፋል። ስለ ሌሎች ይበልጥ ያስባሉ። ኢስላማዊው የዓለም ግንዛቤ ፍቅር፣ አብሮ መኖርና ሠላምን ያሠፍናል፤ ራስ-ወዳድነትን፣ ዘረኝነትና ጸበኝነትንም ያስወግዳል።

አላህ በዚህ ዓለማዊ ግንዛቤ እንዲረዳን እና በሐሳባችንና በድርጊታንም እንድንተገብረው ይረዳን ዘንድ እለምነዋለሁ። አሚን!!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here