የምዕራቡ ስልጣኔ መነሻና ምንጭ ቅርብ አይደለም። ስሩ ሺ ዓመታት ወዳስቆጠሩት የግሪክና የሮማ ስልጣኔዎች ይመለሳል። አስራ ዘጠነኛው ክፍለዘመን ደርሶ አዲስ ቅብ እስኪኖረው ድረስ የምዕራቡ ዓለም የሮማንና የግሪክን መንፈስ ፍልስፍና ሃሳቦች ሲያዳብርና ሲያሳድግ ኖሯል። ይህ ስልጣኔ በደረበው ግሩም ካባ ለመሸወድ ቢችልም እውነታው ግን የአዲሱ ካባ ድርና ማግ የተሰራው ከግሪክና ሮማ ቁሶች መሆኑ ነው።
ነደዊ The Rise of The West & Its Consequence በተባለው ምእራፍ የምአራቡ ዐለም ስልጣኔ ከግሪክና ሮማ ስልጣኔዎች ጋር ያለው ቁርኝት በሚደንቅ ሁኔታ ዳሰውታል። ከዚህ በታች የሚቀርቡት ሃሰቦች ከዚሁ ምዕራፍ ላይ ተቀንጭበው የተወሰዱ ናቸው [ነደዊ 1983፣ ገጽ 113-157]
የጥንት ስልጣኔዎች በጥልቀት ሲመረመሩ የግሪክ ስልጣኔ የመጀመሪያው የምዕራቡ አስተሳሰብ ነጸብራቅ መሆኑን ያሳያል። ይህ ስልጣኔ በምዕራቡ አስተሳሰብ ስነምግባር እሴቶችና ህልሞች ላይ በተለየ ሁኔታ የተገነባ የመጀመሪያው ስልጣኔ ነው።
የግሪክ ስልጣኔ አስተሳሰብ መሰረቶች አራት ሲሆኑ እነዚህም
- ከሰው ልጅ ዕውቀትና ልምድ በላይ የላቁ እውነታዎችን (transcendental truths) ማስተባበል
- የሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ስሜት እጦት
- ቁሳዊ ምቾትን ድሎትን ማምለክ
- የተጋነነ ጀብደኝነት (patriotism) ናቸው
የግሪክ ስልጣኔ ሁሉም ነገሩ ቁሳዊ ነው። ግሪኮች አምላክን ሳይቀር የሰውነት አካላዊ ቅርጽና ለባህሪያቶቹም ምስል በመስራትና ቤተ መቅደስ ዉስጥ በመትከል ለሚጸልዩት አካል የሚታይ ምስል እንዲኖራቸው ያደርጋሉ። የቁጣ፣ የርህራሄ፣ የሲሳይ አምላኮች አሏቸው። ሁሉም አካላዊ ህልውና ያለው ባህሪ ሁሉ ለአምላኮች የተሰጠ ሲሆን እንደ ዉበት ፍቅር ያሉ ረቂቅ ጽንሰሃሳቦች የተለያዩ ጣኦት ሆነው ተመልክተዋል።
ብዙ የምእራቡ አለም ጸሃፍት በግሪኮች ዘንድ የነበረው ሃይማኖተኝነትና የአምልኮ ስርዐት ከመንፈሳዊ ህይወት ቀውስና ሞራል ድቀት ማውጣት ያልቻለ እንደነበረ አበክረው ይከትባሉ። ለምሳሌ ያህል ሌክ History of European Morals በተባለው መጸሃፉ ዉስጥ የሚከተለውን ጽፋል [ሌኪ (Lecky) 1869 ገጽ 344-345]
The Greek spirit was essentially rationalistic and eclectic; the Egyptian spirit was essentially mystical and devotional… The Egyptian deities, it was observed by Apuleius, `were chiefly honored by lamentations and the Greek divinities by dances’… The truth of that last part of this very significant remark appears in every page of Greek history. No nation has a richer collection of games and festivals growing out of its religious system; in none did a light, sportive and often licentious fancy play more fearlessly around the popular creed, in none was religious terrorism more rare. The Divinity was seldom looked upon as holier than man, and a due observance of certain rites and ceremonies was deemed and ample tribute to pay to him.
“….የግሪኮች መንፈሳዊ እይታ በምክንያታዊነትና የተሻለውን በመምረጥ /መመዘን/ ላይ የተመሰረተ ሲሆን የግብጾች ደግሞ በጥብቅ በማመን /በመታመን/ ላይ ያተኩራል…. እንደ አፑሊየስ ምልከታ ‘የግብጾች ጣኦት የሚመለኩት /የሚከበሩት/ በሃዘንና በለቅሶ ሲሆን የግሪኮች ደግሞ በዳንስና ጭፈራ ነው’… ይህም እውነታ በሁሉም የግሪኮች ታሪክ ገጽ ላይ ይነበባል። ከሃይማኖት ስርአት የመነጩና የዳበሩ ፌሰቲቫሎች በብርሃን ያሸበረቁ ሰፖርታዊ ዝግጅቶች እንግዳ የሆኑ ወሲብ ጠቀስ አስጸያፊ ድርጊቶች የሚፈጸምበት ነው….ብዙውን ጊዜ መለኮት ከሰው ልጅ በበለጠ ቅዱስ ተደርጎ የማይታይ ሲሆን አንዳንድ የሀይማኖት የበዐል ስርአቶችን ማክበርና መፈጸም እንደ በቂ የታዛዥነት ምልክት ተደርገው ይቆጠራሉ።”
ከምዕራቡ አለም ጠቅላላ የህይወት ፍልስፍና ባለፈ የግሪኮችን የስነመለኮት ፍልስፍና ለመንፈሳዊ ምጥቀትና መለኮታዊ ክብር መስጠት ረገድ የሰጠው ቦታ ኢምንት ነው። የአምላክን ባህሪያት በተለይም የዩኒቨረሱ ተቆጣጣሪና አስተናባሪ መሆኑን ማስተባበልና በምትኩም ለንቁው አዕምሮ ከፍተኛ ቦታ መስጠት ለመንፈሳዊው ርክሰትና ዝቅጠት ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። በአምላክ ፍጹም ተንከባካቢነት ሰጪነት ያላመነ ሰው ለምን ሲባል ሊወደውና ጸሎቱን ወደሱ ሊያቀርብ ይችላል?
ግሪኮች የአምላክ መኖርን በግልጽ ባያሰተባብሉም በተጨባጭ ህይወታቸው ውስጥ አንዳች ቦታ የለውም። እንደነሱ አስተሳሰብ አምላክ ንቁውን አዕምሮ ካስገኘ ቡሃላ ከአለሙ ጉዳይ ገለልተኛና ሚና አልባ ሆኗል። መለኮትን ከሰው የበለጠ ቅዱስ ነው ብለው አያምኑም። በታሪክ ብዙ የፈጠራ ሰዎችን እናውቃለን። ነገር ግን የአምላክ መኖርን ለርሱ የፍቅርና ክብር ስሜት እንዲሰማን አነሳስተውናል?
የጣዖት አምልኮ፣ ለቁሳዊ ድሎት የተጋነነ ትኩረት መስጠት፣ በስዕል ሙዚቃና በመሳሰሉት ጥበባት መመሰጥ፣ የተጋነነ የግለሰብ ነጻነት ጽንሰ ሃሳብ፣ መረን በለቀቀ ጨዋታና ፌሰቲቫል መጠመድ፣ በግሪኮች አስተሳሰብ ሞራልና ስብዕና ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። አስጸያፊ በሆነ እንስሳዊ ፍላጎት መዋኘት፣ በየትኛውም አይነት ባለስልጣን ላይ የማያባራ አመጽ ቀስበቀስ የየዕለቱ የተለመደ ተግባር ሆነ። ስድነት ተቀባይነት አግኝቶ ስግብግብነት ነገሰ።
በመቀጠልም የሮማ ስልጣኔ ተከሰተ። ግሪኮች በአስደናቂ ስነጽሁፎችና ፍልስፍና ተጠምደው ሳለ ሮማዎች ግን በጦርነት ገድል ተማርከው ነበር። በዚህ ሁኔታ ዉስጥ ሮማዎች ግሪክን መውረራቸው በግሪኮች አስተሳሰብና እሴቶች እንዲመሰጡ ምክንያት ሆኗል። በዚህ ርዕሠ ጉዳይ ላይ ሌኪ እንደጻፈው [ሌኪ 1869 ገጽ 243]
“ሮማዎች ምንም በሌላቸውና ቋንቋቸውም ለስነጽሁፍ ዓላማ ያልዳበረና ያልተገራ በሆነበት ጊዜ ግሪኮች ለዘመናት ያዳበሩት ድንቅ ስነ ጽሁፍ መኖሩ የወታደራዊ ሃይል የበላይነት ብቻ የነበራቸውን ሮማውያን በግሪክ አስተሳሰቦች እንዲማረኩ አድርጓል። ፋቢየስ ፒክቶርና ሲንሲየስ አሊምነተስ የተባሉት ቀደምት ምሁራን እንደጻፉት ‘…ከግሪክ በሮማውያን መያዝ ቡሃላ የፖለቲካ የበላይነት ለሮማውያን ምሁራዊ የበላይነት ደግሞ ለግሪካውያን መሆኑ ይፋ ነበር።’…..የግሪኮች ስሜትና አስተሳሰብ በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ዉስጥ ሰርጎ ለመግባትና በሁሉም የሮማውያን ህይወት ላይ ተጽእኖ ማሳደር ችሏል።”
የሮማውያን ሃይማኖት ለሞራላዊ መነቃቃት /መነሳሳት/ ምንጭ ሆኖ አያውቅም። ፍጹም ጣኦታዊ መሆኑም እያደገ የመጣውን ተጠራጣሪነትና አምላክ የለሽነት መቋቋም እንዳይችል አድርጎታል። ስለሆነም ሮማውያኖች የባህል እድገት ባሳዩ ቁጥር ለሃይማኖታቸው በግልጽ ንቀት ማሳየት ጀመሩ- አምላኮቻቸው በአለማዊና ተጨባጭ ህይወታቸው ላይ ዉሳኔ ማሳረፍ አይችሉም ብለው አስኪደመድሙ ድረስ። ሲሰሮ (Cicero) እንደዘገበው በትያትር ቤቶች አምላክ በሰዎች ነገር ላይ ቦታ የለውም የሚለውን ሃሳብ የሚያውጁ መስመሮች በተነበቡ ቁጥር ታዳሚው በደመቀ ጭብጨባ ድጋፉንና የአድናቆት ስሜቱን ይገልጽ ነበር። ቅዱስ ኦግስቲንና ሌሎች አባቶች የሚያመልኩት ጌታ ጣዖታውያን ይሳለቁባቸው ነበር።
ሮማ ውስጥ ሃይማኖት ከማህበራዊ ባህልነት የዘለለ ዋጋ አጣ። ሌኪ እንደጻፈው [ሌኪ 1869 ገጽ 177]
…. The Roman Religion was purely selfish. It was simply a method of obtaining prosperity, averting calamity, and reading the future. Ancient Rome produced many heroes, but no saints. Its self-sacrifice was patriotic, not religious. Its religion was neither an independent teacher nor a source of inspiration….
“…. የሮማውያን ሃይማኖተኝነት ፍጹም ራሰ ወዳድነት ነበር። ሀይማኖት ብልጽግና ለማግኘት፣ ከመቅሰፍት ለመዳንና የወደፊቱን ለመተንበይ የሚያግዝ ነገር ብቻ ሆነ። ቀደምት ሮማውያን ብዙ ጀግኖችን እንጂ ጻድቃንን ማፍራት አልቻሉም። መስዋዕትነቱም ቢሆን የጀብደኝነት እንጂ በሃይማኖተኝነት የሚፈጸም አይደለም። ሀይማኖቱ የለውጥ ወይም የመነሳሳት ምክንያት ሆኖ አያውቅም።”
በራስ ወዳድት ተነሳስቶ ቅኝ መግዛት ደካማ ህዝቦችን መጨቆን የሮማውያን ሌጣ ቁሳዊነት መገለጫ ሆነ። በዘመናዊው የምዕራባዊያን ስልጣኔ የተወረሰው ይሄው ርካሽ ተግባር ነው። ሙሃመድ አሳድ እንዳለው [አሳድ 1955 ገጽ 38-39]
… the underlying idea of the Roman Empire was the conquest of power and the exploitation of other nations for the benefit of the mother country alone. To promote better living for a privileged group, no violence was for the Romans too bad, no justice was too base. The famous `Roman Justice’ was justice for the Romans alone. It is clear that such an attitude was possible only on the basis of an entirely materialistic conception of life and civilization- a materialism certainly refined by an intellectual taste, but none the less foreign to all spiritual values. The Romans never in reality knew religion. Their traditional gods were a pale imitation of the Greek mythology, colorless ghosts silently accepted for the benefit of social convention. In no way were the gods allowed to interfere with real life. They had to give oracle through the medium of their priests if they were asked; but they were never supposed to confer moral laws upon men.
“….የሮማ ኢምፓየር መነሻ አስተሳሰብ ለእናት ሃገር ጥቅም ሲባል በሃይል የበላይ በመሆን ደካማ ህዝቦችንን መበዝበዝ የሚለው ነው። ለሹማምንት የተሻለ ኑሮ መፍጠር እስከተቻለ ድረስ የትኛውም አይነት ሁከትና ኢፍትሃዊነት ጉዳያቸው አይደለም። ታዋቂው ‘የሮማ ፍትህ’ ፍትህ ለሮማውያን ብቻ የሚል ሃሳብ ያነገበ ነበር። በግልጽ እንደሚታየው እንዲህ አይነቱ አመለካከት ሊመነጭ የሚችለው መሰረቱ ሙሉ በሙሉ ቁሳዊ ከሆነ የሕይወትና ስልጣኔ እይታ ነው- ለመንፈሳዊ እሴቶች እንግዳ ከሆነ አስተሳሰብ /አዕምሮ/ የተወለደ ቁሳዊነት። ሮማውያን በእውነቱ ከሆነ ሃይማኖትን አያውቁም ነበር። ባህላዊ አምላኮቻቸው ለማህበራዊ ስምምነት ሲባል በዝምታ ተቀባይነት ያገኙ የግሪክ ጥንታዊ እምነት ኩረጃዎች ናቸው። አማልክት የማህበረሰቡ የእለተ ተእለት ኑሮ /እንቅስቃሴ/ ዉስጥ ጣልቃ እንዲገቡ በምንም መልኩ አይፈቀድላቸውም። በቄሶቻቸው አማካኝነት አማልክቱ ስለወደፊቱ ዕጣፈንታ ከመተንበይ ባለፈ በሰዎች ላይ የሞራል ድንጋጌዎች አይጭኑም ነበር።”
ወደ መጨረሻው አመታት የሮማ ኢምፓየር ወደ ክፋትና ብክለት ባህርነት ተቀይሮ ነበር። የመጀመሪያዎቹ ወታደራዊ ዲሲፒሊኖቻቸውና የስነምግባር ደንቦቻቸው በሃብትና ቅንጦት ማእበል ተናዱ። ድራፐር History of The Conflict between Religion & Science ላይ እንደጻፈው [ድራፐር (Draper) 1927 ገጽ 31-32]
“ኢምፓየሩ ከወታደራዊና ፖለቲካዊ እይታ አኳያ ጣራ ሲደርስ ከሃይማኖታዊና ማህበራዊ እሴቶች አኳያ የኢሞራላዊነት ጥግ ነክቷል። ሮማውያን በቅንጦት ባህር ተዘፍቀው ነበር ህይወት ሁሌም በዓል ናት። መልካምነትና ራስን መቆጣጠር አስፈላጊነቱ ደስታን ለማፈራረቅና እንዲቆይ ለማድረግ ብቻ ነው። የምግብ አዳራሽ በወርቕ አሸብርቆ በከበሩ ማእድናት ተውቦ በባሪያዎችና ሴቶች ታጅበው በሚያስደንቁ ትያትር ቤቶች በግላድያተርስ-ሰው ከሰው /ከአውሬ/ ጋር በሚያደርገው ትግል በመዝናናት- ጊዜያቸውን ያሳልፉ ነበር። አለምን የተቆጣጠሩት ወራሪዎች በመጨረሻ የደረሱበት ነገር ቢኖር ብቸኛው መመለክ ያለበት ነገር ሃይል መሆኑን ነው። በሃይል ሃያልነት /ትልቅነት/ ይረጋገጣል። በድካምና በልፋት የሚገኘው ንግድ በቀላሉ በገፍ ይገኛል። የቁሶችና የመሬት ውርስና ግብር የተሳካለት ጦረኛ ሽልማቶች ሲሆኑ ንጉሰ ነገስቱ ደግሞ የሃይሉ አርማ ተደርጎ ይቆጠራል።…”
በ 305 የቆስጠንጢኖስ የቄሳርን መንበረ ስልጣን መቆናጠጥ ክርስትናን የሮማ ኢምፓየር መንግስታዊ ሃይማኖት ለማድረግ ያስቻለ ታሪካዊ ክስተት ነበር። በዚህም ምክንያት ክርስትና በሌላ አጋጣሚ አልማ የማታውቀውን ኢምፓየር ባለቤት እንድትሆን አስችሏታል።
የቆስጠንጢኖስ ድል በክርስቲያን ደጋፊዎች ገድልና መስዋእትነት የተገኘ ከመሆኑ አንጻር በኢምፓየሩ ዉስጥ ሰፊ ቦታ ችሮታ እንዲለግሳቸው ምክንያት ሆኖ ነበር። ነገር ግን ይህ ክስተት ለክርስትና የወደፊት ዕጣ ፈንታ ትልቅ ኪሳራ ነበር። ክርስትና ኢምፓየር አግኝታ ነፍስ አጥታለች። በጦር አውድማ አሸንፋ በእምነትና ስነምግባር ዓለም ድል ተነስታለች። ጣዖታውያን ከዚያም በላይ ክርስቲያኖች ራሳቸው የክርስትናን ርዕዮት አምክነውታል።
ድረፐር History of the Conflict between Religion & Science ላይ እንደጻፈው [ድራፐር 1927 ገጽ 34-41]
Place, power, profit- these were in view of whoever now joined the conquering sect. Crowds of worldly persons, who cared nothing about its religious ideas, became its warmest supporters. Pagans at heart, their influence was soon manifested in the paganization of Christianity that forthwith ensued. The Emperor, no better than they, did nothing to check their proceedings. But he did not personally conform to the ceremonial requirements of the Church until the close of his evil life, ….
“ማዕረግ ስልጣንና ትርፍ የገዢውን አንጃ የተቀላቀሉ ሰዎቸ ህልሞች ነበሩ። ሀይማኖታዊ አጀንዳዎች የማያሰጨንቃቸው ዓለማዊ ሰዎች የንጉሱ ጠንካራ ደጋፊዎች ሆኑ። በዋነኝነት በጣዖታውያን ተጽእኖ ክርስትናን ጣዖታዊ የማድረጉ እንቅስቃሴ ይስተዋል ጀመረ። ንጉሰ ነገስቱም ይህን ጉዞ ለመግታት አንዳችም ነገር መፈጸም አልፈቀደም። ህይወቱ እስካለፈች ቅጽበት ድረስ በግሉ ለቤተክርስተያን ስነስርዓቶች ተገዢ አልነበረም።…”
… Though the Christian party had proved itself sufficiently strong to give a master to the Empire, it was never sufficiently strong to destroy its antagonist, paganism. The issue of struggle between them was an amalgamation of the principles of both. In this, Christianity differed from Mohammedanism which absolutely annihilated its antagonist and spread its own doctrines without adulteration…
“….የክርስቲያኑ ቡድን የኢምፓየሩን ባለስልጣናት ማንነት በመወሰን ረገድ ተጽዕኖ ማሳደር ቢሳካለትም ተቀናቃኙን ጣዖታዊነትን ግን ለማስወገድ አልቻለም። የፍልሚያውም አብይ መንስኤ የሁለቱ መርሆዎች ውህደት ነው። ከዚህ አንጻር ተቀናቃኙን በማጥፋትና ሙሉ በሙሉ በመደምሰስ ያለ አንዳች ብረዛና ክለሳ ቀኖናውን ማስፋፋት ከቻለው እስልምና ጋር በሰፊው ተለያይቷል።…”
“…ኢ-አማኝ ለሆነ ንጉስ የርዕዮት ውህደቱን ማበረታታት ለራሱ ለኢምፓየሩና ለተቀናቃኝ (ለክርስቲያኖችና ጣዖታዊያን) ወገኖች መልካም መሆኑ አያጠራጥርም። ይህንንም ታማኝ ክርስቲያኖች ሳይቀር እንኳ አልተቃወሙትም- ምናልባትም የማታ ማታ እውነት ገና ትወጣለች በሚል እምነት።”
የክርስትና መንፈስና ዉበት እንዲያጣ ያደረገው የክርስትናና ጣዖታዊያን ውህደት ለሮማኖች የስነምግባር ርክሰት መፍትሄ ሊሆን አልቻለም። ምናልባትም ከአለማዊነት /ቁሳዊነት/ በላይ በዓለም የስነምግባር ታሪክ ዉስጥ የማይሽር ከባድ ጠባሳ ጥሎ ላለፈው ለባህታዊነት ስሜት መገንፈል ምክንያት ሆኗል። ይህ ዘግናኝና አስቀያሚ የሆነ ራስን የመቅጣት ልማድ በአውሮፓ ዉስጥ ቁሳዊነትና ኢ-ሀይማኖተኝነት በሰፊው እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ራስን መቅጣት በምንኩስናው ዐለም የመጨረሻው የሞራልና መንፈስ ምጥቀት ማረጋገጫ ተደርጎ ይቆጠራል። የአሌክስንደሪያው ቅዱስ ማካሪየስ ራሱን ለመርዘኛና ተናዳፊ ፍጥረታት በማጋለጥ ለስድስት ወር ተኝቷል። 80 ፓውንድ የሚመዝን ብረት መሸከምም ያዘወትር ነበር። የሱ ተማሪ የነበረው ኢዮሴቢስ 150 ፓውንድ ብረት ይሸከም ነበር። ለ3 ዓመትም ያህል በደረቅ ጉድጓድ ዉስጥ ኖሯል። ሌላኛው ጆን የተባለው ጻድቅ በቁም ጸሎት ለ 3 ዓመት ሲያሳልፍ የደከሙ ባቶቹን ለማሳረፍ በአለት ላይ አልፎ አልፎ ጋደም ይል ነበር።
አንዳንድ ባህታዊያን ልብሶቻቸውን ጥለው ራቁታቸውን በቆሻሻ ጉንጉን ጸጉራቸው ብቻ በመሸፈን እንደ እንሰሳ በአራት እግር ይሄዱ ነበር። አንዳንዶች በአውሬ በተሞላ ጫካ ዉስጥ ሲኖሩ ሌሎች መቃብሮችን ይመርጡ ነበር። የሰውነት ጻዕድነት እንደ መንፈስ ብክለት ይቆጠር ነበር። በእድፍ የተሞሉ አስጠሊታ ቅዱሳን የህዝብ ከፍተኛ አድናቆት ይቸራቸዋል። በጊዜው ቅዱሳን እግራቸውን ዉሃ ማስነካታቸው እንደ መንፈሳዊ ርክሰት ተቆጥሮ ይወቀሱ ነበር። ለ50 ዓመት ያህልም እጅና እግራቸው ዉሀ ሳያስነኩ የኖሩ ነበሩ። የቅርቦቹም ቢሆኑ ያለፈውን በማስታወስ፣ “የኛ አባቶች ፊታቸውን እንኳ ታጥበው አያውቁም ነበር እኛ ግን አዘውትረን ገላችንን እንታጠባለን” በማለት ራሳቸውን ይተቻሉ።
ባህታዊያን እንደ ሃይማኖት መምህር ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ህጻናትን ለትእዛዞቻቸው ተገዢ ያደረጉ ነበር። የወላጅና ልጅ ግንኙነት ተሰበረ።ቤተሰቦቻቸውን ትተው መነኩሴ የሆኑ ህጻናት ከፍተኛ የህዝብ ክብር አገኙ። ከወላጅ አባት ይልቅ ባህታዊያን ክብርና ሞገስ ተቸራቸው።ምንኩስና የማህበራዊ ገመድ እንዲበጠስ፣ ቤተሰባዊ መዋቅር እንዲናድ፣ የቤት ዉስጥ እሴቶች እንዲተኑ ምክንያት ሆነ። ባህታዊያን የእናቶቻቸውን ልብ ሰበሩ፣ ሚስትና ልጆቻቸውን ዘነጉ። ጉዳያቸው የራሳቸውን ነፍስ ማዳን ብቻ በመሆኑ ቤተሰቦቻቸውን ትኩረት ነፈጉ።ከሴትነት ጋር በተያያዘ ነገሩ የከፋ ነበር- ከእናት፣ ከሚስት፣ ከእህት ጋር ማውራት እንደ ከባድ ሃጢአት ተቆጠረ። በጎዳና ላይ አንዲት ሴት ካጋጠመቻቸው ወይም ጥላዋ ካረፈ ለዘመናት የገቡት ንስሀ ገደል እንደገባ ይታሰባል።
የቤተሰብ ፍቅርና ክብር መክሰም በአጠቃላይ የማህበረሰቡ እሴት ላይ ከፍተኛ ቀውስ አስከትሏል። ድፍረት፣ ጀግንነት፣ ቸርነት፣ ግልጽነት ወንድማማችነትን የመሳሰሉት እሴቶች ወደሙ።
ድንበር ያለፈ ባህታዊነት የሮማውያንን ቁሳዊነት በመመከት ረገድ በየትኛውም መመዘኛ ተሳክቶለታል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። የሞራልና የሃይማኖት ታሪክ የሚያረጋግጠውም ይሄንኑ ነው- ባህታዊነት ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር የሚቃረን በመሆኑ። የህይወት ተሞክሮ እንደሚያሳየው አለማዊነትን /ቁሳዊነትን/ በተሳካ ሁኔታ መከላከል የሚቻለው ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር ስምሙ የሆነ መንፈሳዊ ስርዓት በመዘርጋት ነው። እናም መፍትሄ የሚሆነው የሰው ልጅ አስፈልጎቶች መደምሰስ ሳይሆን ከስሜቱ በላይ ከፍ በማድረግና ሰውኛ በሆነ መንገድ በማስተናገድ ወደ ጤናማ ማህበራዊ ሀይል መቀየር መቻል ነው።
የሮማ ክርስትና የሰው ልጅ ተፈጥሮ መቀየርና ከሰው ልጅ ሰብዓዊ ችሎታ በላይ በሆነ ስርዐት ዉስጥ መኖርን የሚጠይቅ ፍጹም የማይቻል ተልዕኮ ዉስጥ ራሷን ከታለች። ምንኩስናን መጀመሪያ ላይ ሰዎች በቁሳዊነት ክፉኛ ተዘፍቆ ከነበረው ቅድመ ክርስትና ሮማ ማምለጫ /መሸሸጊያ/ ጎዳና አድረገው ቢመለከቱትም ብዙም ሳይቆይ ግን ተቀባይነት አጣ። እናም የክርስትናው ዓለም ሁለት ትይዩ ነገር ግን ፍጹም ተቃራኒ በሆኑ እንቅስቃሴዎች መናጥ ጀመረች- በቁሳዊ እንስሳዊነት እና በባህታዊነት።
ቀስ በቀስ ብክለቱ በጣም ቅዱስ በሚባሉ ተቋማትና መደቦች ላይ መታየት ጀመረ። መንግስት በ 7 ኛው ክፍለዘመን በሃይል እስኪያፍነው ድረስ ለክርስትና አንድነት ምልክት የሚቆጠሩት የፍቅር በዓላት በመጠጥና በዓመጽ ተግባራት ተሞሉ። የሰማእታት መታሰቢያ /ተዝካር/ የከንቱ ሰዎች ቅሌት ማስታወሻ ሆነ። ታላላቅ ካህናት በአሳፋሪ የስነምግባር ግድፈቶች ተከሰሱ። ካህንነት /ቅስና/ በሙስና በአድሎ በድርድር መገኘት ጀመረ። ማዕረግ እንደ ሸቀጥ ተቸበቸበ።
በ 11 ኛው ክፍለዘመን በቤተክርስትያንና መንግስት መካከል መሪር ትግል ተካሄደ። በመጀመሪያው ዙር ፓፓሱ ከንጉሱ የተሻለ ስልጣን የነበረው ሲሆን የቤተክርስቲያን ስልጣን እየጨመረ ሄዶ በ 1077 ፓፓስ ሄልደርባንድ ንጉስ ሄንሪን አራተኛን እጅ እንዲሰጥ /እንዲታዘዘው/ ትእዛዝ እስከማስተላለፍ ደርሶ ነበር። ከዚያ በኃላ እድል በቤተክርስቲያንና መንግስት መካከል እየተመላለሰች አንዴ ንጉሱ ሌላ ጊዜ ፓፓሱ የበላይ እየሆኑ ቆይቶ ከመቶ ዓመት ብጥብጥና ደም መፋሰስ በኃላ ቤተክርስቲያን መሸነፏን አምና እጅ ሰጠች።
ቤተክርስቲያን በመካከለኛው ዘመን ከሮማው ንጉስ የበለጠ ስልጣን ከመያዟ አንጻር ፍላጎቱ ቢኖር ኖሮ ለአውሮፓ ስልጣኔ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባበረከተች ነበር። በሚያሳዝን ሁኔታ የቤተክርስቲያን ሰዎች /አባቶች/ ይህን ማድረግ አልቻሉም። ስልጣናቸውንና መልካም አጋጣሚዎች ያለአግባብ በመጠቀም ነገሮችን የባሰ አበላሹ።
የአንድ ሀገር የኑሮ ሁኔታና መልካምነት በጠቅላላው በህዝቡ ቁጥር ልዩነት ይታወቃል። ከዚህ አንጸር በአምስት መቶ አመት ዉስጥ የእንግሊዝ ህዝብ እጥፍ ለመድረስ የቻለው በግድ ሲሆን አውሮፓ ባጠቃላይ አንድ ሺህ አመት ዉስጥ እንኳ የህዝብ ቁጥሩ እጥፍ መሆን አልቻለም። ይህ ሊሆን የቻለው በከፊል ከወሲብ በመታቀብ ልማድ ሲሆን በዋነኝነት ግን ከምግብ እጥረት ልብስና መጠለያ አለመኖር፣ ንጽህና /ጽዳት/ ችግር፣ የሃኪሞች እጥረት፣ የፀበል ህክምና መግነን ናቸው። ሳይንሳዊ ህክምናና ጥበብ የቤተ መቅደስን ትርፍና ገቢ የሚቀንሱ በመሆናቸው በቤተ ክርስቲያነን ክፉኛ ይወገዛሉ። ህዝቡም የቤተ መቅደስ ህክምና እንዲጠቀም ይበረታታል። እናም ተላላፊ በሸታዎች በአህጉሩ በቀላሉ እንዲዛመቱና ብዙ ሰው እንዲያልቅ ሆነ።
ካህናት በጊዜው ተቀባይነት ያገኙ የጂአግራፊና ፊዚክስ ሃሳቦችን በቅዱሳን መጽሃፍት ዉስጥ እንዲካተት ማድረጋቸው ከሁሉም የከፋው አደገኛ ስህተት ነበር። ምንም እንኳ ካህናቱ ሰዎች ለቅዱሳን መጻኅፍት ያላቸው ክብር ከፍ እንዲል በማሰብ የፈጸሙት ቢሆንም ውጤቱ ግን አሰቃቂ ነበር። እናም መጀመሪያውኑ በቀኖናው ላይ ብክለትና ብረዛ የደረሰበት ክርስትና ከሳይንስ ጋር የከረረ ግጭት ዉስጥ ገባ።በመጨረሻም ክርስትና ተሸንፋ የካህናቱም ክብር ለዘላለሙ ተዋረደ። ከሁሉም በላይ የከፋው ግን አውሮፓ ፊቷን ወደ አምላክ የለሽነት ማዞሯ ነበር።
ክርስትና ራሷን እንደብቸኛ የዕውቀት ፋኖ በመቁጠር ከአስተምህሮቷ ጋር የሚቃረኑ ግለሰቦች ለማስገደድ ሀይል ትጠቀም ነበር። አንዳች መለኮታዊ ድጋፍ ባይኖረውም በቤተክርስቲያን የሚሰበከውን “ክርስቲያናዊ ጂኦግራፊ” ያልተቀበሉ ሰዎችን በአደባባይ ታወግዝና ትገዝት ነበር።
ከጊዜ በኋላ በጎረቤት የሚገኙ ስልጣኔዎች ሙቀት የተነሳ በምድረ አውሮፓ የዕውቀት እሳተ ገሞራ ፈነዳ። አሳቢዎች /ፈላስፋዎች/ እና ሳይንቲስቶች የአዕምሮ ባርነትን ሰንሰለት በጣጥሰው መጣል ቻሉ። አሳማኝ ማስረጃ በማቅረብ የካህናትን አስተምህሮቶች በይፋና በድፍረት መቃወም ጀመሩ። እናም የቤተክርስቲያን ባለስልጣናት በጭካኔ የአፀፋ መልስ ሰጡ። ኢንኪውዜሽን (Inquisition) የሚባል ተቋምና አሰራር ተመሰረተ። የቤተክርስቲያንን አቋም የሚቃወም ሁሉ ከነ መጽሃፉ ያለ ርህራሄ ተቃጠለ፣ ተገደለ፣ ተሳደደ፣ ኢሰብኢዊና አዋራጅ ቅጣቶች ተፈጸሙ- እውነት ክርስቲያን ሆኖ መኖርና በአልጋ ላይ ሆኖ መሞት አይቻልም እስኪባል ድረስ።
ከ 1481 እስከ 1801 ድረስ ብቻ በኢንኪውዜሽን ሶስት መቶ አርባ ሺህ ሰዎች የተቀጡ ሲሆን ሰላሳ ሁለት ሺው ሰዎች ታዋቂውን ሳይንቲስት ብሩኖን ጨምሮ ከነህይወታቸው እንዲቃጠሉ ተደርጓል። የብሩኖ ብቸኛ ጥፋት /ወንጀል/ የአለማችንን ብዙሃንነት ማስተማሩ ነበር። ብሩኖ እዝነት በተሞላበትና ያለ አንዳች ደም መፍሰስ እንዲቀጣ ተልኮ ዘግናኝ በሆነ መልኩ ከነህይወቱ ተቃጥሎ እንዲሞት ተደርጓል። ሌላው ታዋቂ ሳይንቲስት ጋሊሊዮ ከቅዱሳን መጽሃፍት በተቃራኒ መሬት በጸሃይ ዙሪያ ትሽከረከራለች በማለቱ ያለርህራሄ እስኪሞት ድረስ በእስር ቤት ተሰቃይቷል። በመጨረሻም የአውሮፓ ምሁራን ትእግስት ተሟጦ በይፋ በክርስትናና በተወካዮቿ ባህል ላይ አመጹ። በካህናት የአዕምሮ ዝግመትና በኢንኪውዜሽን ዘግናኝ ጭካኔ የተሞላበት ድረጊት የተነሳሱት የአውሮፓ ልሂቃን ከቤተክርስቲያንና ከሃይማኖት ጋር ለተያያዘ እውቀት ስነምግባርና እውነታ መሪር ጥላቻ አዳበሩ። ስለሃይማኖታዊ አጀንዳዎች ባሰቡ ቁጥር ከነዚያ አስፈሪና አሰጨናቂ የቤተክርስቲያን ግፍና ከአለማዊ ልሂቃን እንግልትና ሰቆቃ ትውስታ ውጭ ሆነው ማየት አልቻሉም። ጨፍጋጋ የኢ-አማኝነት ጉም በአህጉሩ ላይ አንዣበበ። ከቀድሞው የክርስትና ጭቆና ግፍ ቀንበር በቅርቡ ከመላቀቁ አንጻር የአውሮፓ ማህበረሰብ ማንኛውንም አይነት መንፈሳዊነት /ሃይማኖተኝነት/ ለመታገስ ያለመቻሉን በግልጽ ማሳየት ጀመረ።
ስለሆነም በክርስትናና በሳይንስ መካከል የተጀመረው ሀያል ትግል በሃይማኖትና ሳይንስ መካከል ወደሚደረግ የፉክክር ነበልባልነት አደገ። የአውሮፓ ምሁራን ሃይማኖትና ሳይንስ የማይስማሙ ባላንጣ መሆናቸውን በማርዳት በምክንያት ያልተደገፈ ችኩል ድምዳሜ ላይ ደረሱ። እናም ለሳይንስ ዕድገት የሃይማኖት መወገድ አስፈላጊ መሆኑ ታወጀ። በርግጥ ግጭቱ ከክርስትና ጋር ብቻ ነው መባል ሲገባው ከሀይማኖት ጋር በጠቅላላው ነው ተብሎ መደምደሙ ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ነበር። ምሁራኖቹ በእውነተኛ ሃይማኖትና ራሳቸውን በሾሙ መሪዎች መካከል ያለውን ልዩነት ለማስተዋል ትዕግስቱን አጥተዋል። ስለሆነም በጥንቃቄ፣ ያለ አድልዎ በሰከነ መንፈስ ለተፈጠረው አሳዛኝ ክስተት ተጠያቂው የሀይማኖቱ አስተምህሮ ወይስ የካህናቱ መሀይምነትና ግትርነት የሚለውን ለማየት አልቻሉም። የካህናቱ ጥፋት ከሆነስ በነሱ ስህተት ሀይማኖትን በጠቅላላው ማውገዝ ምን ያህል ምክንያታዊ ነው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስም አልደፈሩም።
አውሮፓ በመንፈሳዊ ባዶነት ጎዳና አሳዛኝ ጉዞ ጀመረች። ወደቁሳዊነት ባህር በጥልቀት ሰመጠች። ማህበራዊ ልሂቃንና ሳይንቲስቶች በዓለምና የህይወት ባህሪ ላይ በጥልቀት ተመራመርን አሉ። ምንም አይነት ፍጹም ሃያል ፈጣሪና አስተናባሪ- ለሌላ ህግ የማይገዛ- አምላክ እንደሌለ በመቁጠር- ለቁሳዊ ዩኒቨርስ መገለጫዎቹን መካኒካዊና ሳይንሳዊ ትርጉም ብቻ በመስጠት- ከአምላክ መኖር መነሻነት የቀረቡ ሃሳቦችን ለአጉል ባህል ባሪያ እንደመሆን በመቁጠር-፣ በዚህ ስሜት ውስጥ ተውጠው በንቀት ውድቅ አደረጉ። ከቁስና ከሀይል ውጭ ያለውን ነገር ሁሉ አንድ ባንድ አስተባበሉ። ማንኛውም በተሞክሮ መገንዘብ ያልተቻለ ነገር ሁሉ ሊለካና እውቅና ሊሰጠው የማይችል ነው በማለት ፍጹም የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ደረሱ። በስሜት ህዋሳት ሊደረስባቸው ወይም በቤተ ሙከራ ሊረጋገጡ ከሚችሉ ቁሳዊ ነገሮች ህልውና ዉጭ ከዚያ ባሻገር ያሉ ነገሮችን በሙሉ አስተባበሉ።
ማጣቀሻ፡-
Asad, M., Islam at the Crossroad, Lahore, Pakistan, 1955.
Draper, J.W., History of the Conflict between Religion and Science, London, 1927.
Lecky, W.E.H., History of European Morals, London, 1869.
Nadwi, A.A., Islam and the World, International Islamic Federation of Student Organizations, Kuwait, 1983.