ሹራ /መመካከር/ በኢስላም

0
7002

መግቢያ

ኢማሙ ሙስሊም ከሰልማን እንደዘገቡት ነቢያችሁ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም እንዴት እንደምትፀዳዱ ሣይቀር ሁሉን ነገር አስተምረዋችኋል?” ተብለው ተጠየቁ። እርሣቸውም “አዎን በሽንትም ሆነ በስገራ ጊዜ ወደ ቂብላ ተቀጣጭተን አሊያም ጀርባ ሰጥተን እንዳንፀዳዳ፤ በቀኝ እጃችን ኢስቲንጃእ እንዳናደርግ /ሽንታችንን እንዳናደራርቅ/፤ ከሦስት በታች በሆነ ድንጋይ እንዳንጠቀምና በኩስ እና በአጥንት እስቲንጃእ እንዳናደርግ ከልክለውናል።” በማለት መለሡ። ይህ ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም እውቀት ከሚባል ነገር አንድም ሣያሥቀሩ ለህዝቦቻቸው አስተምረው እንዳለፉ አመላካች ነው።

የኢስላም ሁለንተናዊነት

ኢስላም የተደነገገው ለሰው ልጅ በሙሉ ሲሆን መልዕክቱም ዓለማቀፋዊ ነው። በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብም ሆነ በአጠቃላይ በኡማው (ህዝብ) ደረጃ የሰው ልጆችን የኑሮ ጣጣ ፈጣሪያቸውና ሲሣይ ለጋሻቸው የሆነው አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ በሚወደው መልኩ ይመሩ ዘንድ ያመቻችላቸዋል። ለያንዳንዱ የህይወታቸው ጫፍም ደስታና ስኬትን የሚያስገኝላቸውን እጅግ ቀጥተኛ የሆነውንም መንገድ ደንግጎላቸዋል። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

إِنَّ هَٰذَا الْقُرْآنَ يَهْدِي لِلَّتِي هِيَ أَقْوَمُ
 

“ይህ ቁርኣን ወደዚያች ቀጥተኛ ወደሆነችው መንገድ ይመራል” (አልኢስራእ፤ 9)

የአላህ መልእክተኛም ሰለላሁ ዐለይ ወሠለም እንዲህ ብለዋል

تَركْتُ فيكُمْ أَمْرَيْنِ لنْ تَضِلُّوا ما تَمسَّكْتُمْ بهما: كتابَ الله، وسنّة رسولِهِ (موطأ مالك والحاكم وصححه الألباني).

“ብትይዟቸው የማትጠሙባቸው የሆኑ ሁለት ነገሮችን በናንተ መካከል ትቼያለሁ – የአላህ ኪታብ /ቁርኣን/ ና የአላህን መልእክተኛ ሱና /ሀዲስ/” (ማሊክ እና ሃኪም ሲዘግቡት አልባኒ የሀዲሱን ትክክለኛነት አረጋግጠዋል)።

ከነዚህ የሰዎችን ጉዳይ መስመር ለማስያዝ ከሚጠቅሙ ቀጥ ካሉ መንገዶችና ለስኬት ከሚያበቁ መስመሮች መካከል ሹራ /መመካከር/ አንዱ ነው። የሹራ ትርጉሙ ምንድነው? በኢስላም ውስጥ ያለው ቦታስ? በኢስላም ታሪክ ውስጥ ያሉ ምሣሌዎችስ? ፍሬዎቹስ?.እነኚህን ጥያቄዎች በማንሣት መልስ ለመስጠት እንሞክራለን።

ትርጉሙ

የሹራ ትርጉም የተለያዩ ሀሣቦችንና አመለካከቶችን በማንሸራሸር በላጭና የተሻለ በሆነው ላይ መስማማትና ከውሣኔ ላይ መድረስ ነው።

በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ የሹራ ቦታ

ሹራ በእስልምና ውስጥ ግዴታ ከሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ ነው ብንል ጥቂት ያህል እንኳ አልተሣሣትንም። በዚህም ዙሪያ ከቁርኣን፣ ከነቢዩ ሀዲስና፣ ከርሣቸው ሞት በኋላ በተተኩ ቅን የሙስሊሙ ህዝብ መሪዎች ሊጠቀሱ የሚችሉ ማሰረጃዎች በርካቶች ናቸው።

የአላህን ኪታብ /ቁርኣንን/ የሚያነብ ሰው በመካ የወረደችውን “ሹራ” የምትል አንዲት ምእራፍ ያጋጥመዋል። በውስጧም አምላካዊው መንገድ ለሷ ግምቱ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ የሚያሣይ እጅግ የሚደንቅ ገለፃ አለ። ከአስገራሚው የአላህ ቁርኣን አንድ ምእራፍ በሷ (በሹራ) በሚለው መሰየሙ እራሱ ለጉዳዩ ምን ያህል ክብደት እንደተሠጠ አመላካች ነው። አንቀጿን በጥልቀትና በማስተንተን ስናነብ በአድናቆት መደመማችን አይቀርም። እስቲ ቀጥሎ ያለውን አንቀፅ በጥሞና እናንብብ

فَمَا أُوتِيتُم مِّن شَيْءٍ فَمَتَاعُ الْحَيَاةِ الدُّنْيَا وَمَا عِندَ اللَّهِ خَيْرٌ وَأَبْقَىٰ لِلَّذِينَ آمَنُوا وَعَلَىٰ رَبِّهِمْ يَتَوَكَّلُونَ وَالَّذِينَ يَجْتَنِبُونَ كَبَائِرَ الْإِثْمِ وَالْفَوَاحِشَ وَإِذَا مَا غَضِبُوا هُمْ يَغْفِرُونَ وَالَّذِينَ اسْتَجَابُوا لِرَبِّهِمْ وَأَقَامُوا الصَّلَاةَ وَأَمْرُهُمْ شُورَىٰ بَيْنَهُمْ وَمِمَّا رَزَقْنَاهُمْ يُنفِقُونَ

“ከምንም ነገር የተሠጣችሁ የቅርቢቱ ህይወት መጠቀሚያ ነው። አላህ ዘንድ ያለውም ምንዳ ለነዚያ ላመኑትና በጌታቸው ላይ ለሚጠጉት በላጭና ሁልጊዜ ነዋሪ ነው። ለነዚያም የሀጢኣትን ትላልቆችና መጥፎዎችን የሚርቁ በተቆጡም ጊዜ የሚምሩ ለሆኑት። ለነዚያም የጌታቸውን ጥሪ ለተቀበሉት፤ ሰላትንም ላዘወተሩት፤ ነገራቸውም በመካከላቸው መመካከር ለሆነው፤ ከሠጠናቸውም ሲሣይ ለሚለግሱ።” (ሹራ፤ 36-38 )

የሹራ ምእራፍ በመካ የወረደች መሆኗን ስናስተውል ከመባቻው ጀምሮ ኢስላማዊው ጥሪ ለዚህ ጉዳይ ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶ እንደነበር እንገነዘባለን። ኢስላም ይህን ያደረገው ገና ከወዲሁ የሹራ ትክክለኛ ትርጉሙ በሰዎች ውስጥ እንዲሰርፅና ሁኔታዎችም በሚያመቹ መልኩ ሂደቱን እንዲለማመዱ ነው። ሙስሊሞች በቁጥር ትንሽም ይሁኑ ብዙ፤ ጥንካሬም ይኑራቸው ደካሞች የተሸለ ውሣኔ ማስተላለፍ ይችሉ ዘንድ ሁሌም ሹራ አስፈላጊያቸው ነው።

وَأَمْرُهُمْ شُورَى بَيْنَهُمْ

ነገራቸውም በመካከላቸው መመካከር ነው”

የሚለውን የአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ቃል

وَأَقَامُوا الصَّلاةَ

ሰላትን ላዘወተሩት” በሚለውና

 

وَمِمَّا رَزَقْنَاهُمْ يُنْفِقُونَ

ከሠጠናቸው ሲሣይ ለሚለግሱት” በሚሉት ቃላት መካከል ሆኖ ነው የምናገኘው። ይህም የሹራ ትርጉም ግልፅ እንዲሆንና ከፍተኛ የሆነ አስፈላጊነቱንም ለማጠናከር ይመስላል። ሹራ ሁለተኛ የእስልምና ማእዘን ከሆነው ሰላት ቀጥሎና ሦስተኛ ማእዘን ከሆነው ዘካ ቀድሞ መጠቀሱ የሹራ አስፈላጊነት በዲናችን ውስጥ ምን ያህል ታላቅ ቦታ እንደተሠጠው የምናስተውልበት አንቀፅ ነው ።

በአንቀጿ ውስጥ የንግግሩ መልእክት ለአስተዳዳሪዎችና ሀላፊነት ላይ ላሉ ሰዎች ብቻ ሣይሆን ለአጠቃላይ ሙስሊም ስለሆነ ከእያንዳንዱ አማኝ ሹራን ማዘውተርና ልምዱ ማድረጉ ይፈለጋል ።

ተግባራዊ ምሣሌ

አንዳንዴ ፅንሰ ሀሣብና ተግባር የተለያዩ ሲሆኑ ፅንሰ ሀሣቡ ምስል ብቻ ይሆንና ናሙናዊ ምስልን በመፍጠር ተግባሩም ከዚህ ባነሠ መልኩ ሆኖ ይመጣል። ነገር ግን ሙስሊሙ ማህበረሰብ ሹራን ከመተግበር አንፃር የቁርኣንን ምልከታ የወሰደ እንደሆነ የቁርኣንን አስተምህሮ ከማየት አልፎ በእጁ መዳሰስና ፍሬውንም መቋደስ ይችላል። ለዚህም የተወሰኑ ምሣሌዎችን መጥቀስ እንችላለን።

በኡሁድ ዘመቻ ወቅት የሙሽሪኮችን /አጋሪዎችን/ ጦር በሚገጥሙበት ሁኔታ ላይ ሰሃቦች /የነቢዩ ባልደረቦች/ በሀሣብ ተለያዩ። ከፊሉ “ወጥተን መጋፈጥ አለብን” ሲል ሌላው ክፍል ደግሞ “መዲና መሽገን እንከላከል” አለ። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም አመለካከትም የነበረው ከመዲና ሣይወጡ እዚያው ሆነው እንዲከላከሉ ነበር። ነገር ግን የበድር ጦርነት ያመለጣቸው አንዳንድ ታላላቅ ሰሃቦችና ሌሎችም ወጥተን ካልተዋጋን በማለት ነቢዩ ላይ ችክ አሉ። እንዲህም እስከማለት ደረሱ “ የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ይህን ቀን ስንናፍቀውና አላህንም ስንለምነው ነበር። አላህም ወደኛ አመጣልን ጊዜውንም አቀረበልን። ስለዚህ ወደ ጠላቶቻችን ይዘውን ይውጡ የፈራን እንዳይመስላቸው።” አሉ።

ለመውጣት እጅግ ጓጉተው ከነበሩ ሰዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው በበድር ጦርነት ቀን ትልቅ ተጋድሎ አድርጎ የነበረው የነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም አጎት ሀምዛ ኢብኑ ዐብዱልሙጠሊብ አንዱ ሲሆን እርሱም ለነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም እንዲህ አላቸው “መፅሃፉን ባንተ ላይ ባወረደው ጌታ እምላለሁ፤ እነኚህን ሰዎች ከመዲና ውጭ ወጥቼ እስክቀጣቸው ድረስ ምግብ አልቀምስም።”

ነቢዩም ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የአብዛኛውን ሰሃባ ሀሣብ በመቀበል ከመዲና ውጭ ተንቀሣቀሱ። አማኞች በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት ደረሠባቸው። “የአላህ አንበሣ”› በመባል የሚታወቁትን ሀምዛን ጨምሮ ሰባ ያህል ታላላቅ ሰሃቦች መስዋእት ሆኑ።

የኡሁድን ዘመቻ ክስተት ተከትሎ ከሌሎች ነገሮች በበለጠ አፅንኦት ሊሠጠው በሚገባው መሠረታዊ ጉዳይን አስመልክቶ የቁርኣን አንቀፅ ወረደ። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ነቢዩን በሚያናግርበት መልኩ እንዲህ አለ

فَبِمَا رَحْمَةٍ مِّنَ اللَّهِ لِنتَ لَهُمْ وَلَوْ كُنتَ فَظًّا غَلِيظَ الْقَلْبِ لَانفَضُّوا مِنْ حَوْلِكَ فَاعْفُ عَنْهُمْ وَاسْتَغْفِرْ لَهُمْ وَشَاوِرْهُمْ فِي الْأَمْرِ فَإِذَا عَزَمْتَ فَتَوَكَّلْ عَلَى اللَّهِ إِنَّ اللَّهَ يُحِبُّ الْمُتَوَكِّلِينَ
 

“ከአላህም በኾነች ችሮታ ለዘብክላቸው፡፡ ዐመለ መጥፎ ልበ ደረቅም በኾንክ ኖሮ ከዙሪያህ በተበተኑ ነበር፡፡ ከእነርሱም ይቅር በል፡፡ ለእነርሱም ምሕረትን ለምንላቸው፡፡ በነገሩም ሁሉ አማክራቸው፡፡ ቁርጥ ሐሳብም ባደረግህ ጊዜ በአላህ ላይ ተመካ፡፡ አላህ በርሱ ላይ ተመኪዎችን ይወዳልና፡፡” (ኣሊ ዒምራን፤ 159)

ይህ አንቀፅ የሹራን ፈለግ በማስቀጠልና ቋሚ መንገድ በማድረጉ ረገድ እንዲሁም በሁሉም ነገር በማካተቱ ውስጥ ቀጥተኛና ግልፅ የሆነ ትእዛዝ ነው።

በዚህ በኩል ተጨባጭ ሁኔታዎችን ማሣየት ካስፈለገ ባልደረቦቻቸው ለነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የሠጡት ምስክርነት ተጠቃሽ ነው። አቡሁረይራ አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና እንዲህ ብለዋል

ما رأيت أحدًا أكثر مشاورة لأصحابه من رسول الله (السنن الكبرى للبيهقي(

“ሰሃቦችን በማማከር በኩል ከአላህ መልእክተኛ የበለጠ አላየሁም።” (በይሀቂ ዘግበውታል።)

ኢማም ሀሠን አልበስሪ የሹራን አስፈላጊነት ያመላከቱትን ነቢይ አስመልክተው ሲናገሩ “ነቢዩ ከምክክር የተብቃቁ ከመሆናቸው ጋር መንገዱን ከኋላቸው ለሚመጡ መሪዎች ለማሣየት ብለው ነው ይህን ያደረጉት” ብለዋል ።

ከሣቸው በኋላ የተተኩት የሙስሊሙ ኸሊፋዎችም የሣቸውን መንገድና ፈለግ ተከትለዋል። መይሙን ኢብኑ መህራን እንዲህ ይላል “አቡበክር ከሣሽና ተካሣሽ እርሣቸው ዘንድ መጥተው አቤቱታቸውን በሚያቀርቡበት ጊዜ በጉዳዩ ዙሪያ ቁርኣን የሚለውን ያያሉ። የሚፈርዱበትን አስተያያት በቁርኣን ውስጥ ያገኙ እንደሆነ ቁርኣን በሚለው ይፈርዳሉ። በቁርኣን ውስጥ ያላገኙ እንደሆነ ደግሞ ከአላህ መልእክተኛ አስተምህሮ ይፈልጋሉ። ያላገኙ እንደሆነ ደግሞ ጉዳዩን ለሙስሊሞች በማቅረብ ‘እኔ የዚህ ኣይነት ጉዳይ መጥቶብኛልና በዚህ ዙሪያ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የፈረዱበትን የምታውቁ ከሆነ ንገሩኝ’ ይሉ ነበር። በጉዳዩ ላይ ነቢዩ የፈረዱበትን ፍርድ የሚያውቁ ሰዎችን ካገኙ እሣቸውም እርሣቸው በፈረዱት ፍርድ ይፈርዳሉ። አቡበክርም የዚህ ዓይነቱን ሰው ሲያኙ እንዲህ ይሉ ነበር ‘ከኛ ውስጥ ነቢያችንን የሚጠብቅልን ያደረገልን አላህ የተመሠገነ ይሁን’ በጉዳዩ ዙሪያ ከነቢዩ ፈለግ አንድም ያጡ እንደሆነ ግን ትላልቅ ሰዎችንና ምርጦቻቸው የሚባሉትን በመሰብሰብ ያማክራሉ። በአንድ ዓይነት ሀሣብ ላይ የተስማሙ እንደሆነ በሀሣባቸው ይፈርዳሉ” (ዳርሚይ ዘግበውታል)።

ከሙሰይብ ኢብኑ ራፍዕ እንደተዘገበው እንዲህ አለ “(ሰሃቦች) ከአላህ መልእክተኛ ምልከታ ያልተላለፈበት አንድ ነገር ያጋጠማቸው እንደሆነ ተሰብስበው ከአንድ አቋም ይደርሣሉ። በመሠላቸው ትክክለኛ ሀሣብም ይወስናሉ” (ዳርሚይ)

በዚሁ መንገድ ላይ ታቢዒዮችም ተጉዘዋል። ከዑመር ኢብኑ ዐብዱልዐዚዝ እንደተዘገበው መዲና ላይ በተሾሙበት ወቅት በዘመኑ ምርጥ ናቸው ከሚባሉ ሙስሊም ምሁራኖቻቸው መካከል አሥር የሚሆኑትን መርጠው ሰበሰቡ። እንዲህም አሏቸው “እኔ ምንዳ ወደምታገኙበት ነገር ነው የጠራኋችሁ። ይህን በማድረጋችሁም ሀቅ ላይ አጋዠ ትሆናላችሁ። አንድን ነገር አልወስንም ሁላችሁንም አሊያም አንዳችሁን ያማከርኩ ቢሆን እንጂ።” (ሲየሩ አዕላም ኑበላእ።)

የሹራ ፍሬዎች

አንድ ሙስሊም የአላህን ትእዘዝ ሲፈፅምና በመንገዱም ሲፀና ከአላህ መልካም ነገርን በረከቱንና የተሟላ ምንዳውን ይጠብቃል ። በዚህም መሠረት ሹራን ልምድ ማድረግና በሱ መዘውተር መልካም ነገራትና ፍሬዎች ይኖሩታል ። ከነዚህም መካከል ፡-

  1. ሹራ ማድረግ ከእውነተኛ ምእመናን ባህሪዎች መካከል አንዱን ማሟላት ነው። አላህ  ነገራቸውም በመካከላቸው መመካከር ነው” ብሏልና።
  2. ኡማው /ህዝቡ/ የራሱን ጉዳይ ትክክለኛ በሆነ መንገድ እንዲመራ ማዘጋጃ መንገድ ነው።
  3. በማህበረሰቡ ላይ እጅግ አስፈላጊ ውሣኔን በሚጠይቁ ነገሮች ላይ ብቸኝነትንና አምባገነንትን ለመራቅ ይጠቅማል።
  4. በአመራሮችና በህዝቡ መካከል መተማመንን ለማጠንከርና ለሀገር ልማትም ጉልህ የሆነ ፋይዳ አለው።
  5. ውሣኔን ለማስተላለፍ፤ የተረጋጋ ሰላምን ለማግኘትና ከስሜትና ከግለሰብ ጥቅም ባለፈ መልኩ ሰዎችም ስራቸውን በጥሩ ሁኔታና በኢክላስ /ለአላህ ብቻ ጥርት አድርገው/ እንዲሠሩ ይጋብዛል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here