ኢስላም ለሠው ዘር ምን ያበረክታል?

1
7939

ሠዎች አዕምሮ፣ ነፍስና አካል አለን። በቤተሰባችንና በማኅበረሰባችን ውስጥ እነደ ግለሠብ እንኖራለን። ሕይወት እንዳለን ሁሉ ሞትም አለብን። ስለዚህ፤ ፍላጎታችንን የሚያሟላ፣ ጥያቄያችንን ሁሉ የሚመልስ ኃይማኖት እንፈልጋለን።

ኢስላም አዕምሮና ነፍሳችንን ያረካል፤ አካላችንንም ይንከባከባል። ኢስላም በግለሠባዊ ፍላጎቶቻችን እና በማኅበረሰባዊና የጋራ ጉዳዮቻችን መካከል ሚዛንን አበጅቷል። ኢስላም በቅርቢቱ ዓለምም ሆነ በዘላለማዊ ሕይወት ደስታና ሥኬትን ያስጨብጣል። ኢስላም በእውነተኛው የሠው ልጅ ተፈጥሮ (ፊጥራ) ላይ የተመሠረተ ነው። ኢስላም አላህ ለሁሉም ነብያትና መልክተኞች የሠጠውን መልዕክት እውነተኛነቱ በተረጋገጠ ሁኔታ ያቀርባል።

فَأَقِمْ وَجْهَكَ لِلدِّينِ حَنِيفًا فِطْرَتَ اللَّهِ الَّتِي فَطَرَ النَّاسَ عَلَيْهَا لَا تَبْدِيلَ لِخَلْقِ اللَّهِ ذَٰلِكَ الدِّينُ الْقَيِّمُ وَلَٰكِنَّ أَكْثَرَ النَّاسِ لَا يَعْلَمُونَ
 

“ወደ እውነት ተዘንባይ ኾነህም ፊትህን ለሃይማኖት ቀጥ አድርግ። የአላህን ፍጥረት ያችን አላህ ሰዎችን በእርስዋ ላይ የፈጠረባትን (ሃይማኖት ያዟት)። የአላህን ፍጥረት መለወጥ የለም። ይህ ቀጥተኛ ሃይማኖት ነው። ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም።” (አር-ሩም 30፤30)

شَرَعَ لَكُم مِّنَ الدِّينِ مَا وَصَّىٰ بِهِ نُوحًا وَالَّذِي أَوْحَيْنَا إِلَيْكَ وَمَا وَصَّيْنَا بِهِ إِبْرَاهِيمَ وَمُوسَىٰ وَعِيسَىٰ أَنْ أَقِيمُوا الدِّينَ وَلَا تَتَفَرَّقُوا فِيهِ كَبُرَ عَلَى الْمُشْرِكِينَ مَا تَدْعُوهُمْ إِلَيْهِ اللَّهُ يَجْتَبِي إِلَيْهِ مَن يَشَاءُ وَيَهْدِي إِلَيْهِ مَن يُنِيبُ

“ለእናንተ ከሃይማኖት ያንን በእርሱ ኑሕን ያዘዘበትን ደነገገላችሁ። ያንንም ወዳንተ ያወረድነውን ያንንም በእርሱ ኢብራሂምን ሙሳንና ዒሳንም ያዘዝንበትን ሃይማኖትን በትክክል አቋቁሙ በእርሱም አትለያዩ ማለትን (ደነገግን)። በአጋሪዎቹ ላይ ያ ወደርሱ የምትጠራቸው ነገር ከበዳቸው። አላህ የሚሻውን ሰው ወደእርሱ (እምነት) ይመርጣል። የሚመለስንም ሰው ወደርሱ ይመራል።” (አሽ-ሹራ 42፤13)

ኢስላም ለሠው ዘር፡-

 1. ግልጽ፣ ቀላል እና ምርጥ የሆነ የእምነት ሥርዓትን በንጹህ መጽሐፍና በቅዱስ፣ እንከን አልባ ሠው አማካኝነት ያቀርባል
 2. ለሁሉም ሥፍራና ጊዜ ተስማሚ የሆነ በሥርዓት የተዋቀረ እና ግልጽ መርሆዎች ያሉት ሚዛናዊ የአፈጻጸም መመሪያ (balanced action plan) ይሰጣል
 3. ዓለማቀፋዊ የእምነትና የወንድማማችነት ማኅበረሰብ ያለው ዓለማቀፍዊ ግንዛቤ (universal outlook) ያቀርባል
 4. ለምድራዊው ዓለም ሥኬትና ደስታ ግለጽ እና ሊተገበሩ የሚችሉ ራዕዮችና ለመጪው ዘላለማዊ ዓለም ሥኬትና ደኅንነት እውነተኛ ቃልኪዳን ይሰጣል።

እያንዳንዱን ነጥብ በዝርዝር እንቃኝ፡-

1. ግልጽ፣ ቀላል፣ ምርጥ እና ጥልቅ የእምነት ሥርዓት

እ.ኤ.አ በ1734 በጆርጅ ሴል ለተተረጎመው የእንግሊዝኛ ቁርኣን ትርጉም ሰር ኤድዋርድ ዴኒሰን ሮዝ በጻፈው መቅድም ላይ የሚከተለውን አስፍሮ ነበር፡-

“ሙሐመድ በሱ ዘመን ለነበሩት ኮከብ አምላኪ አረቦች፣ ኦርሙዝና አህሪማን ለሚገዙት ፐርሺያኖዎች፣ ጣዖታትን ለሚለማመኑት ሕንዶችም ሆነ ይህ የሚባል አምላክ ላልነበራቸው ቱርኮች ያቀረበው ማዕከላዊ ቀኖና የፈጣሪ አንድነትን ነበር። ለእስልምና መስፋፋት የእምነቱ ገርነት የአዝማቾቹ የላቀ አስተዋፅዖ አበርክቷል። ካስገራሚዎች ክስተቶች አንዱ ቱርኮች ለራሳቸው የትኛውም ጦር የማይፈታቸው ኃይለኞች ሆነው ሳለ እስልምና ግን ረታቸውና ኢስላማዊ ሥርወ-መንግስት አስመሰረታቸው። በ13ኛው ክፍለ ዘመን ሞንጎሎች ባግዳድን ሲቆጣጠሩ የእስልምና ርዝራዥ የሆነን ነገር ሁሉ ጠርገው ኺላፋው ተባሮ ግብጽ ቢገባም አዲስ የተመሠረቱት ኢምፓየሮች ግን ኢስላማዊ መንግስታትን ለመመሥረት ግዜ አልወሰደባቸውም።” (ገጽ. Vii)

 • የአላህ አንድነት (ተውሂድ)፡- ይህ በጣም አመክኒዮአዊ፣ ምክንያታዊና መንፈሳዊ እምነት ነው። ቀላል ግን የመጨረሻው የሠው ልጆች ትልቁ እውነት እና ተስፋ ነው። ኢስላም አምላክ አንድ መሆኑን፣ የሁሉ ጌታ እና እጅግ ያማሩ ስሞችና ባህሪያት ባለቤት የሆነ ፈጣሪ መሆኑን ያስተምራል።
 • የኢስላም መልዕክት በመጽሃፍ (በቁርኣን) ቀርቧል፡- መጽሃፉ ንጹህና ውብ ነው። እዚህ መጽሃፍ ውስጥ ምንም ሐሰት የለም። መልዕክቱ ግልፅ፣ ሁሌም አዲስና ዘመን የማይሽረው ነው።
 • ከመልዕክቱና ከመጽሃፉ ጋር አፈ-ታሪክ ያልሆኑ በታሪክ የሚታወቁ አንድ ግለሠብ አሉ። እኚህ ግለሠብ መልዕክቱን በተግባር እየኖሩ ለሠዎች ባማረ መልኩ ያሳዩ ሠው ነበሩ- የመጨረሻው ነብይ ሙሃመድ (ሰ.ዐ.ወ)።

2. ሚዛናዊ የአፈጻጸም መመሪያ (Balanced Action Plan)

ይህ የአፈጻጻም መመሪያ ግለሠቡን፣ ቤተሠቡን እና ሕብረተሠቡን ይጠብቃል (ይንከባከባል)። መመሪያውም ምሉዕ፣ ሊተገበር የሚችልና ሚዛናዊ ነው። መመሪያው የሚያዘው

 • በአምልኮ ረገድ፡- ከአላህ ጋር ጥልቅና በፍቅር የተሞላ ግንኙነት መፍጠር።
 • በሞራልና በሥነ-ምግባር ረገድ፡- ሥነ-ሥርዓት፣ ሚዛናዊነት፣ ቅንነትና መልካምነትን ያስተምረናል።
 • ደንብና መመሪያ፡- ኢስላም መመሪያዎቹ ሊተገበሩ የሚችሉ (ተምኔታዊ ያልሆኑ)፣ ግዜን የሚያገናዝቡ እና ተራማጅ ናቸው። እነዚህ መመሪያዎች ሊተገበሩ የሚችሉ ከመሆናቸውም ጋር ዓላማቸው ሠውን ማስጨመቅ ሳይሆን ደስታን መፍጠር ነው።

3. ዓለማቀፋዊ እይታ (Universal Outlook)

ኢስላም ዘረኛ ወይም ጎሳን መሠረት ያደረገ አይደለም። ኃይማኖቱ የሠው ዘር ሁሉ እኩል እንደሆነ ይሠብካል። የብሔረተኝነት፣ የቀለም፣ የማህበራዊ ደረጃና የቋንቋ ድንበሮችን ያፈርሳል። ኢስላም የትኛውንም አይነት አድልዖ እና ጥላቻ ይቃወማል። ለሁሉም ሠዎች ፍትህ መኖር እንዳለበት ያስገነዝባል፤ ሠላም እና መቻቻል፣ ሓሳብን የመግለጽ ነጻነት እንዲኖርም ይሰብካል። ኢስላም ዓለማቀፍ የእምነትና የወንድማማችነት ማኅበረሰብን ይገነባል።

4. በምድረ-ዓለም (በዱንያ) እና በመጪው ዓለም (በአኼራ) ስኬት

ኢስላም ተከታዮቹ በዚህ ዓለም ደስተኛና ስኬታማ እንዲሆኑ ይሻል። ይህ ኃይማኖት ጨለምተኛ፣ የታመመ አልያም ይህችን ምድር የናቀ አይደለም። አላህ እንዲህ ይላል።

قُلْ إِنَّمَا حَرَّمَ رَبِّيَ الْفَوَاحِشَ مَا ظَهَرَ مِنْهَا وَمَا بَطَنَ وَالْإِثْمَ وَالْبَغْيَ بِغَيْرِ الْحَقِّ وَأَن تُشْرِكُوا بِاللَّهِ مَا لَمْ يُنَزِّلْ بِهِ سُلْطَانًا وَأَن تَقُولُوا عَلَى اللَّهِ مَا لَا تَعْلَمُونَ وَلِكُلِّ أُمَّةٍ أَجَلٌ فَإِذَا جَاءَ أَجَلُهُمْ لَا يَسْتَأْخِرُونَ سَاعَةً وَلَا يَسْتَقْدِمُونَ

“ጌታዬ እርም ያደረገው መጥፎ ሥራዎችን፣ ከርሷ የተገለጸውንና የተደበቀውን ኃጢኣትንም፣ ያላግባብ መበደልንም፣ በርሱም ማስረጃ ያላወረደበትን (ጣዖት) በአላህ ማጋራታችሁን፣ በአላህም ላይ የማታውቁትን መናገራችሁን ብቻ ነው በላቸው። ለሕዝብም ሁሉ የተወሰነ ጊዜ አላቸው። ጊዜያቸውም በመጣ ወቅት አንዲትን ሰዓት አይቆዩም። (ከጊዜያቱ) አይቀደሙምም።” (አል-አዕራፍ 7፤33-34)

በሌላ ሥፍራም አላህ ስለ አኼራ ደኅንነት ሲናገር፡-

قُلْ يَا عِبَادِيَ الَّذِينَ أَسْرَفُوا عَلَىٰ أَنفُسِهِمْ لَا تَقْنَطُوا مِن رَّحْمَةِ اللَّهِ إِنَّ اللَّهَ يَغْفِرُ الذُّنُوبَ جَمِيعًا إِنَّهُ هُوَ الْغَفُورُ الرَّحِيمُ

“በላቸው እናንተ በነፍሶቻችሁ ላይ ድንበር ያለፋችሁ ባሮቼ ሆይ! ከአላህ እዝነት ተስፋ አትቁረጡ። አላህ ኃጢኣቶችን በመላ ይምራልና። እነሆ እርሱ መሓሪው አዛኙ ነውና።” (አዝ-ዙመር 39፤53) ይላል።

1 COMMENT

 1. አንተ እንዳልከ ለመኖር ሃይማኖት ሳይሆን የሚያስፈልገን አእምሮ ነው።ሃይማኖት አእምሮን ይገድባል ወይም ይወስናል።ኢስላም ከሌሎች የተሻለ ሁኖ የሚታየው የሰው ልጆች ያስተሳሰብ ደረጃቸው እየተሻሻለ በመጣበት ዘመን ላይ ነው።ችግሩ ግን መሰረት እንዲኖረው ባደርገው ጥረት ቀደምቶቹን እና አፈታሪኮችን ተቀብሎ እንዲጓዝ ተገዷል።እስኪ ገምት ፈጣርክ አሁን ነብይ ቢልክ ምን አይነት ነብይ የሚልክ ይመስለሃ? ጥያቄዎቹ ጥንት የተለዩ እንደሚሆኑ አትጠራጠርም።
  ሙሃመድ ከምንም አልተነሳም..የአምላክ አንድነት የወረቃ ብኑ ነውፈል…እምነት ነበር።ወረቃ ብቻውን አይደለም የሱ አይነት እምነት ተከታዩች በሌላም ቦታ እንደነበሩ ግልፅ ነው።
  እምነቶች ስትሰብካቸው እና ስታስተምር እንደ መተግበሩና በተጨባጭ የሚታዩ አይደሉም።የሃይማኖት ታሪክ ግልፅ ነው በጦርነት የታጀበ እና አምባገነነትን ያሳለፍ ነው።ከዚህም በላይ ለምርምር እና ለፍልስፍና ትልቅ ጠላት ነው።ሲሰበክ እና ሲወራ ግን ውስጡን ለቄስ….!!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here