ለአላህ ብሎ የመዋደድ መርህ (ክፍል 1)

0
3796

የተለያዩ የህይወት ተግዳሮቶች በበዙበት ዘመን ውስጥ እየኖርን እንገኛለን፡፡ ከነዚህም መካከል የሰዎች ግንኙነት በቁሳዊ ጥቅም የበላይነት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነዉ፡፡ ስለዚህ “ለአላህ ሲባል የተመሰረተ ወንድማማችነት መርህ” ተሀድሶ የሚየስፈልገዉ ነገር መሆኑን  በአግባቡ ልናዉቀው፣ ደረጃውን በሚመጥንና ሙሉ በሆነ መልኩ ልንሰራበት፣ ለኢስላም ሊሰራ ለሚነሳ ሁሉ የሀይል ምንጭ መሆኑንና በዛሬዉ ጊዜ ከተጋረጠብን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ፊት ፀንተን ለመቆም የመንፈስ ብርታት መሰረት እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

“ለአላህ ሲባል የተመሰረተ ወንድማማችነት መርህ” ማለት በአላህ ዉዴታ ጥላ ስር ሆኖ አንዱ ከሌላዉ ጋር እንዴት መኗኗር፣ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር፣ ይቅርታ መደራረግ፣ መዋደድ እና የሀሳብ ልዩነትን ማስተናገድ እንደሚችል የሚያብራራ ፅንሰ-ሀሳብ ነዉ፡፡

ለኢስላም መስራት ሲባል ይህ መርህ አስፈላጊነቱ የጎላ የሚሆነው በእስልምና መንገድ ላይ ያሉ ሁሉ በመካከላቸዉ ያለው ግንኙነት ተጠናክሮና አንድነታቸው ሲጠበቅ ሁላችንም ሀይላችንን ያለአግባብ እንዳናባክን ስለሚረዳ ነዉ፡፡

‹‹ኢስላማዊ ወንድማማችነት›› ከፍ የሚደረግ አርማና የሚደጋገም ቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚገለፅ ስራ፣ የህይወት ዘይቤ፣ መተጋገዝ የሚተገበርበት፣ አንዱ የሌላዉን ክፍተት የሚሸፍንበት፣ መረዳዳት የሚስተዋልበት፣ በግልፅ እያንዳንዱ ራሱን የሚያይበት መስታወት፣ ግልፅነት የተሞላበት፣ ሌላዉን የሚያፀዳ እጅ፣ መዋደድ የሚንፀባረቅበት፣ መፈቃቀር የሚታይበት፣ መተዛዘን የሰፈነበት፣ ልክ እንደ አንድ አካል አሊያም በጥንቃቄ እንደተሰራ ጠንካራ ግንብ የሚመሰል እሴት ነው፡፡

ከላይ የተገለፀውን ደረጃ ከደረስን የምንጠብቀውንና የምንጓጓለትን የአላህን እርዳታ ለማግኘት አንድ እርምጃ ወደፊት ማለታችንን የሚሳይ ነዉ፡፡ ለእኛ የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም አርያነት በቂያችን ነው፡፡ የአማኞችን እምነት በልባቸዉ ላይ እንዲፀና እና ለነገሮች ያላቸዉን አተያይ በኢስላማዊ መነፀር እንዲሆን ካደረጉ በኋላ የመጀመሪያ ዋና ተግባራቸዉ ከመካ ወደ መዲና የተሰደዱትን ሙሀጅሮች እና የመዲና ነዋሪ ሆነው ከመካ የተሰደዱትን በመልካም የተባበሩት አንሷሮችን አንድ ለአንድ በሆነ ወንድማማችነት ማስተሳሳር ነበር፡፡

ይህንን አላማ እዉን ማድረግ ይቻል ዘንድ የወንድማማችነትን አስፈላጊነት፣ ደረጃዉን፣ እንዴት ማጠናከርና ጠብቆ ማቆየት እንደሚቻል እንዲሁም በግለሰብና በማህበረሰብ ደረጃ የሚያሳድረዉን አዎንታዊ ተፅእኖ እንመለከታለን፡፡

የወንድማማችነት አስፈላጊነት

ኢስላማዊ ወንድማማችነት አላህ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ለአማኝ ባሮቹ የሚለግሰው ፀጋ ሲሆን ዛሬ በምንኖርበት ዘመን እንደ እርሱ በሰዎች መካከል ጠንካራ ትስስር የሚፈጥር ነገር አናገኝም፡፡  ይህ መሰል ወንድማማችነት ምንም አይነት የጎንዮሽ ቁሳዊ ጥቅም የማይሻበት ለአላህ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ብቻ ተብሎ የተመሰረተና ወንድማዊ ትስስሩ ልባዊና በጠንካራ የውስጥ መንፈስ ላይ የፀና ስለሆነ ፈፅሞ ለማፍረስ አይቻልም፡፡

አላህ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል:-

وَأَلَّفَ بَيْنَ قُلُوبِهِمْ ۚلَوْ أَنفَقْتَ مَا فِي الْأَرْضِ جَمِيعًا مَّا أَلَّفْتَ بَيْنَ قُلُوبِهِمْ وَلَٰكِنَّ اللَّهَ أَلَّفَ بَيْنَهُمْ ۚإِنَّهُ عَزِيزٌ حَكِيمٌ

“በልቦቻቸውም መካከል ያስማማ ነው፡፡ በምድር ያለውን ሁሉ (ሀብት) በለገስክ ኖሮ በልቦቻቸው መካከል ባላስማማህ ነበር፡፡ ግን አላህ በመካከላቸው አስማማ፡፡ እርሱ አሸናፊ ጥበበኛ ነውና፡፡” (አንፋል 63) 

አላህ ይዘንለትና ኡስታዝ ሰይድ ቁጥብ እንዲህ ብሏል “በእርግጥ ይህ ታዓምራዊ ክስተት በሀያሉ አላህ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንጂ በሌላ አካል እውን ሊሆን አይችልም፡፡ የኢስላማዊ አቂዳ (እምነት) ፍሬ እንጂ የሌላ ሊሆን ይችላል ተብሎ ፈፅሞ አይታሰብም፡፡ ፍፁም የሀሳብ አንድነት የሌላቸውና በልባዊ መናቆር ደረጃ ውስጥ ያሉ ሰዎች በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ እና የጀነት ተምሳሌት በሆነ መልኩ ወደ ጥልቅ ትስስርና ወንድማማችነት አንዱ ለሌላው የሚተናነስለት፣ እርስበርስ መዋደድ፣ እርስበርስ መተሳሰር ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡” አላህ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የጀነትን ምሳሌ እንደገለፀው፡-

وَنَزَعْنَا مَا فِي صُدُورِهِم مِّنْ غِلٍّ إِخْوَانًا عَلَىٰ سُرُرٍ مُّتَقَابِلِينَ

“ባልጋዎችም ላይ ፊት ለፊት የሚቅጣጩ ወንድማማቾች ኾነው በደረቶቻቸው ውስጥ ከቂም ያለውን ሁሉ እናስወግዳለን፡፡” (ሒጅር 47)

ከዚህ አቂዳ (ኢማን) ተግባረዊ አስገራሚ ገፅታዎች መካከል በጥቂቱ ብናወሳ ቀልብን በተዋሃደ ጊዜ የለዝባል፣ ድርቅናን ያረጥባል፣ በቀልቦች መካከል ጥብቅና ጥልቅ ትስስር ይፈጥራል፣ በአይናቸው ሲያማትሩ በምልክት ሲጠቋቆሙና በቀልባቸዉ ውል ሲልባቸው ልክ ከዚህ በፊት እንደሚተዋወቁና እንደሚዋደዱ፣ የወገናዊ ስሜትና መተጋገዛቸው፣ ቸርነታቸውንና አዛኝነታቸውን ሚስጥር ስንመለከት ይኸው ወንድማማችነት ነው፡፡ የሚያጣጥሙት ለዛና ጥፍጥናም ራሳቸውልቦቹ እንጂ ሌላ አያውቀውም፡፡

አላህ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ለባሮቹ ከዋለላቸው ታላቅ ችሮታው መካከል ወደ አንድነትና ልዩነትን ወደ መተው መጥራቱ መሆኑን በሚከተለዉ የቁርዓን አንቀፅ ያብራራል፡፡

وَاعْتَصِمُوا بِحَبْلِ اللَّهِ جَمِيعًا وَلَا تَفَرَّقُوا ۚ وَاذْكُرُوا نِعْمَتَ اللَّهِ عَلَيْكُمْ إِذْ كُنتُمْ أَعْدَاءً فَأَلَّفَ بَيْنَ قُلُوبِكُمْ فَأَصْبَحْتُم بِنِعْمَتِهِ إِخْوَانًا وَكُنتُمْ عَلَىٰ شَفَا حُفْرَةٍ مِّنَ النَّارِ فَأَنقَذَكُم مِّنْهَا ۗ كَذَٰلِكَ يُبَيِّنُ اللَّهُ لَكُمْ آيَاتِهِ لَعَلَّكُمْ تَهْتَدُونَ

“የአላህንም (የማመን) ገመድ ሁላችሁም ያዙ።አትለያዩም። ጠበኞችም በነበራችሁ ጊዜ በእናንተ ላይ (የዋለውን) የአላህን ጸጋ አስታውሱ። በልቦቻችሁም መካከል አስማማ። በጸጋውም ወንድማማቾች ኾናችሁ። በእሳት ጉድጓድ አፋፍም ላይ ነበራችሁ። ከእርስዋም አዳናችሁ። እንደዚሁ ትመሩ ዘንድ አላህ ለእናንተ አንቀጾቹን ያብራራል።” (ኢምራን 103)

በእምነት መንገድ ላይ በተገኘ ትስስር የተፈጠረውን የወንድማማችነት ፀጋ አላህ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ በመጀመሪያዎቹ ሙስሊሞች ላይ እንዳደረገው ሁሉ ሁልጊዜም ቢሆን ለሚወዳቸው ባሪያዎቹ ይለግሳል፡፡

እስልምና ብቻ ነው ስር የሰደደ መናቆር፣ ታሪካዊ ጠላትነት፣ የጎሳ በቀል ስሜት፣ ራስ ወዳድነትና ስግብግብነት የተንሰራፋበትና በዘረኝነት የተበታተኑ ህዝቦችን በአንድ ታላቅ የእምነት ባንዲራ ስር ሁሉንም ሰብስቦ በመከባበርና መፈቃቀር ላይ የተመሰረተ ወንድማማችነት የሰፈነበት ህብረተሰብ የገነባዉ፡፡

የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለምመዲና ከገቡ በኋላ የመጀመሪያ ስራቸው የነበረዉ በአንሷሮችና ሙሃጅሮች መካከል ወንድማማችነትን መመስረት ነበር፡፡ የዚህ ጉዳይ አሳሳቢነት እና አስፈላጊነት የጎላ የሚሆነዉ የመጀመሪያዋን የኢስላም ሀገር መመስረት የሚችለወን ያ ምርጥ ትዉልድ የላቀ፣ አላማ የሰነቀ እና አንድነቱን በእምነት(ተዉሂድ) ገመድ የጠበቀ መሆን ስለነበረበት ነዉ፡፡ በእርግጥ በዚህ መልኩ የተመሰረተው ወንድማማችነት ገና ወደ ስራ ከመግባቱ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ተጋርጠውበታል፡፡

አላህ ይዘንለትና ኢማም ሸሂድ ሀሰን አል-በና እንዲህ ብሏል፡ “እኔ የምፈልገዉ ወንድማማችነት በእምነት የፀና የልብና የመንፈስ ትስስር ሲሆን ነዉ፡፡ እንደ እምነት ጠንካራ ትስስርን የሚፈጥር ነገር የለም፤ ወንድማማችነት የዕምነት መገለጫ ሲሆን መበታተን የክህደት አጋር ነዉ፡፡ አንድነት ኃይል ሲሆን ያለዉዴታ አይገኝም፡፡ የዝቅተኛዉ ውደታ መገለጫ አንዱ ስለሌላዉ በልቡ መልካም ማሰብ ሲሆን ከፍተኛዉ ከራስ ማስበለጥ ነዉ፡፡

وَمَن يُوقَ شُحَّ نَفْسِهِ فَأُولَٰئِكَ هُمُ الْمُفْلِحُونَ

“የነፍሱንም ንፍገት የሚጠበቅ ሰው እነዚያ እነሱ ምኞታቸውን አግኚዎች ናቸው፡፡” (ሀሽር፤ 9)

እውነተኛ ወንድም ወንድሞቹን ከራሱ አስበልጦ ያያል ምክንያቱም እነርሱ የርሱ የማንነቱ መገለጫዎች ናቸውና፤ እነሱ ከእርሱ ጋር መሆን ባይችሉ ከሌሎች ጋር ይሆናሉ፡፡ ተኩላ የምትበላዉ ብቻዉን የተገነጠለውን በግ ነዉ፡፡

“المؤمن للمؤمن كالبنيان يشد بعضه بعضًا”

“አማኝ ለአማኝ ልክ እንዴ ግንብ ነዉ ከፊሉ ሌላዉን ያጠነክራል።”

አላህ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ብሏል፡-

وَالْمُؤْمِنُونَ وَالْمُؤْمِنَاتُ بَعْضُهُمْ أَوْلِيَاءُ بَعْضٍ
 

“ምእምንና ምእምናትም ከፊሎቻቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው፡፡” (ተዉባ 71)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here