ለአላህ ብሎ መዋደድ (ክፍል 5)

0
2488

4. በወንድማማችነት ሀቅ ዙሪያ ከታሪክ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት

እዝነት እና መረዳዳት

 • ሙሀመድ ኢብኑ ኢስሃቅ እንዲህ ይላል፦ በመዲና ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ነገር ግን ማን እንደሚያኖራቸውና እንደሚቀልባቸው የማይታወቁ ሰዎች ነበሩ። ዘይን አል ዓቢዲን ኢብኑ አል ሁሴን አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላችሁ በሞተ ጊዜ ግን ይሠጣቸው የነበረ ነገር ተቋረጠ። በዚህን ጊዜ በየለሊቱ አንዳንድ ነገሮችን ያመጣላቸው የነበረው እርሱ መሆኑን አወቁ።

በሞተ ጊዜ አስከሬኑ ሲታይ ባላቸው የሞተባቸውንና ድሆችን ለመመገብ እህል ይሸከምበት የነበረው ጀርባውና ትከሻው ላይ ምልክት አዩ።

 • ለይስ ኢብኑ ሰዕድ ከሰባ ሺህ ዲናር የሚበልጥ አመታዊ ገቢ ነበረው። ነገርግን ሁሉንም አንድም ሣያስቀር ይመፀውታል። በዚህም የተነሳ ዘካ ግዴታ አይሆንበትም እስከመባል ተደርሷል። በአንድ ወቅት የሆነ ቤት ገዛ። ወኪሉ ቤቱን ለመረከብ ሲሄድ በውስጡ ወላጅ አጥ የሆኑ ትናንሽ ልጆችን አገኘ። ውስጡ የሚኖሩ ሰዎች ቤቱን እንዲተውላቸው በአላህ ጠየቁት። ይሀው ጉዳይ ለለይስ ኢብኑ ሰዕድ በደረሠ ጊዜ “ቤቱ ለናንተ ይሁን። ከዚህም በተጨማሪ በየቀኑ ለናንተ ወጭ የሚሆንም ክፍያ ይደረጋል።” አላቸው።
 • ዐብዱላህ ኢብኑ አልሙባረክ ምፅዋት የሚያበዛ ሰው ነበር። አመታዊ ምፅዋቱም እስከ መቶ ሺህ ዲናር ያህል ነው። በአንድ ወቅት ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ሀጅ ለማድረግ ወጣ። የተወሰኑ ሀገሮችን ካለፈ በኋላ አንድ የሞተ አሞራ አጋጠመው። አሞራው በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ እንዲጣል አዘዘ። ጓደኞቹ ቀድመውት ሄዱ። እሱ ግን ወደ ኋላ በቀረበት ወቅት በቆሻሻ መጣያው አካባቢ በሚያልፍበት ጊዜ አንዲት ሴት ከአካባቢው ከሚገኝ ቤት ወጥታ ያን የሞተ አሞራ ስትወስድ አየ። አልሙባረክ ለምን ይህን እንደምታደርግ ጠየቃት። እሷም እሷና ወንድሟ ድሆች እንደሆኑና ምንም እንደሌላቸው ይህንንም ማንም እንደማያውቅ ነገረችው። ኢብኑ አልሙባረክ አጀቡ ሁሉ እንዲመለስ አዘዘ። ለወኪሉም “ምን ያህል ገንዘብ ይዘሃል” በማለት ጠየቀው። ወኪሉም “አንድ ሺህ ዲናር።” አለው። አልሙባረክም “ወደ መርው ለመድረስ የሚበቃንን ያህል ድርሃም ያዝና ሌላውን ስጣት። ለዘንድሮው ሀጃችን ይሀው ይሻለናል።” በማለት ሀጅ ሳያደርግ ተመለሠ።
 • ኢማም አል ገዛሊ ኢህያእ በተሰኘው ኪታባቸው ውስጥ እንደተረኩት “ከነቢዩ ሰሃቦች መካከል የሆነ አንድ ሰው የፍየል እራስ በስጦታ መልክ ተላከለት። እሱም “ከኔ በላይ እገሌ ተቸግሯል።” በማለት ወደ ሌላ ሰው ላከ። የደረሰውም ሰው “ከኔ በላይ የተቸገረ ሰው አለ።” በማለት ወደ ሌላኛው ላከ። ሰባት ሰዎች በዚህ መልኩ ከተቀባበሉ በኋላ የፍየሏ እራስ ወደ የመጀመሪያው ሰው ዘንድ ተመልሳ መጣች።
 • ሃኪም በአል ሙስተድረክ ውስጥ እንደዘገቡት ሙዓዊያ ኢብኑ አቢ ሱፍያን ሰማኒያ ሺህ ድርሃም ለዓኢሻ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላችሁ ላከላት። እሷ ፆመኛ ነበረች። የቀደመ ፆም ነበረባት። ምንም ሣታስቀር የደረሣትን ገንዘብ ወዲያውኑ ለድሆች እና ችግረኞች አከፋፈለች። አገልጋይዋ “የምእመናን እናት ሆይ በሁለቱ ድርሃም ምናለ ሥጋ ገዝተሸ ብታፈጥሪበት።” አለቻቸት። ዓኢሻም “ልጄ ሆይ አስታውሠሽኝ በሆን ኖሮ እንዲያ ባደረግኩ ነበር አለቻቸት።” ዓኢሻ ሌሎችን በማስበለጧ እራሷን ረሣች።
 • አልቁርጡቢ አል ዐደዊን በመጥቀስ ይህን አስገራሚ ታሪክ ዘግበዋል “በየርሙክ ጦርነት ወቅት በሞት አፋፍ ላይ ያገኘሁት እንደሆን ላጠጣው በማሰብ የተወሠነ ውሃ ይዤ የወንድሜን ልጅ ፍለጋ ተንቀሳቀስኩ። በርግጥም ሲያጣጥር አገኘሁትና “ልስጥህ” አልኩት። እሺ ካለኝ በኋላ ወዲያውኑ “አህአህ” የሚል ሰው ድምፅ ሰማ።“በል ሂድና ለሱ ስጠው።” አለኝ። ሰውየው ሂሻም ኢብኑ አልዓስ ነበር። “ላጠጣህ” ስለው እሽ አለኝ። ነገርግን እሱም ወዲያው ሌላ “አህ አህ” የሚል ሰው ድምፅ ሰማ። እሱም “በል ሂድና እሱን አጠጣ።” አለኝ። ስደርስ ሰውየው ሞቶ አገኘሁት። ተመልሼ ወደ ሂሻም ስመጣ እሱም ህይወቱ አልፋለች። ወደ አጎቴ ልጅ ተመለስኩ። እሱንም ሞቶ አገኘሁት።” አንደኛው ሌላኛውን ከራሱ በማስበለጡ አንዳቸውም ሳይጠጡ ሦስቱም በዚህ መልኩ ሞቱ።

ትእግስትና ይቅርባይነት

 • የአቡበክር የቅርብ ዘመድ የሆነ ሚስጠህ የሚባል ሰው ነበር። ይህ ሰው አቡቡከር በሚያደርግለት እገዛና ድጎማ ነበር የሚተዳደረው። ነገርግን ለውለታው ግድ ሣይኖረው ሙናፊቆች በውሸት የእናታችንን ዓኢሻን አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላችሁ ስም ባጠፉ ጊዜ የውሸትና የቅጥፈት ተባባሪ በመሆን ወሬውን አብሮአቸው በተነ። በዚህ የተነሣ ሚስጠህ የእስልምናን፣ የዝምድናን እና የመልካም ውለታን ሀቅ ረሣ። አቡበክር በሁኔታው በመናደድ ይህንን ዘመዳቸውን ለማራቅና ለማገለል ማሉ። ዝምድናውንም ለመቁረጥ ወሠኑ። በዚህን ጊዜ አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ እንዲህ የሚለውን የቁርዓን አንቀፅ አወረደ”

 ከእናንተም የችሮታና የክብረት ባለቤቶች የኾኑት ለቅርብ ዘመዶችና ለድኾች በአላህም መንገድ ለተሰደዱ ሰዎች ላይሰጡ አይማሉ ይቅርታም ያድርጉ። (ጥፋተኞቹንይለፉም አላህ ለእናንተ ሊምር አትወዱምንአላህም መሓሪ አዛኝ ነው (አን ኑር፤ 22)

وَلَا يَأْتَلِ أُولُو الْفَضْلِ مِنكُمْ وَالسَّعَةِ أَن يُؤْتُوا أُولِي الْقُرْبَىٰ وَالْمَسَاكِينَ وَالْمُهَاجِرِينَ فِي سَبِيلِ اللَّهِ ۖ وَلْيَعْفُوا وَلْيَصْفَحُوا ۗ أَلَا تُحِبُّونَ أَن يَغْفِرَ اللَّهُ لَكُمْ ۗ وَاللَّهُ غَفُورٌ رَّحِيمٌ

የቁርዓንን ትእዛዛት ያለ አንዳች ቅሬታ የሚቀበሉት ታላቁ ሰው አቡበክርም አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላችሁ ሚስጠህን ይቅር በማለትና በማለፍ በፊት ይሠጡት የነበረውን ነገር መስጠት ጀመሩ። በጊዜውም ከቁርዓን አንቀፁ መልአክት በመነሣት እንዲህ ይሉ ነበር “ እኔ አላህ እንዲምረኝ እፈልጋለሁ።

 • ቡኻሪ ከኢብኑ ዐባስ እንደዘገቡት ዑየይናህ ኢብኑ ሂስን ወደ መዲና በመጣ ጊዜ ወንድሙ አልሁር ኢብኑ ቀይስ ዘንድ አረፈ። ቁርዓንን በደንብ ከሚያነቡ ሰሃቦች መካከል ነበርና ከምእመናን መሪ ጋር ለሹራ ከሚቀመጡና ዑመር ከሚያቀርባቸው ትላልቅ ሰዎችና ወጣቶች መካከል አንዱ ነበር። ዑየይናህ ወደ ምእመናን መሪ መግባት ፈለገና አስፈቅዶት ገባ። ወደርሱ በገባ ጊዜም “የአልኸጧብ ልጅ ሆይ የሚገባንን አትሠጠንም በመካከላችንም በፍትህ አትፈርድም።” አለው። ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላችሁ ለመማታት እስኪያስቡ ድረስ በንግግሩ እጅግ ተቆጡ። ይህን ያስተዋለው አል ሁር ብኑ ቀይስ “የምእመናን መሪ ሆይ አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ ለነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላል “ይቅር በል በመልካም እዘዝ። ከመሃይማንም ዘወር በል።” ይህ ሰው ከመሃይማን ነው” አላቸው። ዑመርም አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላችሁ ይህን የቁርዓን አንቀፅ በሰሙ ጊዜ ከዚያ አልፈው አልተራመዱም። የአላህን ቁርዓን ህግጋት የማያልፉ ሰው ነበሩ።
 • በአንድ ወቅት ዘይን አልዓቢዲን ኢብኑ ዐሊ ወደ መስጅድ ለመሄድ ወጣ። የሆነ ሰውም ተከትሎ ሰደባቸው። አገልጋዮቹ ሰውየውን ለመደብደብና ልክ ለማስገባት አሰቡ። ዘይን አልኣቢዲን ግን ከለከሏቸው። እረፉ አሏቸውና ወደ ሰውየው ዘወር በማለት “አንተ ሰው ሆይ እኔ አንተም ከምትለውም በላይ ክፉ ሰው ነኝ። ስለኔ ከምታውቀውም የማታውቀው የበዛ ነው። መናገሩ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ ልነግርህ እችላለሁ።” በዚህን ጊዜ ሰውዬው አፈረና አንገቱን ደፋ። ዘይንል ዓቢዲን ቀሚሣቸውን በማውለቅ አንድ ሺህ ድርሃም እንዲሠጠው አዘዙ። ሰውየውም ነገሩን በማስተዋል “ይህ ወጣት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ልጅ መሆኑን እመሠክራለሁ።” በማለት ተመልሦ ሄደ። ሰውየው ግምቱ ትክክል ነበር። ዘይን አልዓቢዲን በልጃቸው ፋጢማ በኩል የነቢዩ ሰዐወ የልጅ ልጅ ነበሩ።
 • በሌላ ከርሱ በተላለፈ ዘገባ ደግሞ አንድ አገልጋዩ ከጭቃ በተሠራ ኢብሪቅ ውሃ እየጨመረለት ሣለ ኢብሪቁ ወደቀና በዘይን አልዓቢዲን እግር ላይ ተከሠከሠ። በዚህን ጊዜ እግራቸው ተጎዳ። ወዲያውም አገልጋዩ “ጌታዬ ሆይ አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል አለው።

 “ቁጣቸውን የሚውጡ የሆኑ”

ዘይን አልዓቢዲንም ቁጣዬን ውጫለሁ አለው።

እንዲሁም  “ለሰዎች ይቅር የሚሉ”ይላል አለው።

“ዐፍው ብየሃለሁ” አለው።

“አላህ መልካም ሠሪዎችን ይወዳል።” በማለት ጨመረለት።

ዘይንልዓቢዲንም “አንተ ለአላህ ሲባል ነፃ ነህ።” በማለት አሠናበተው።

መዋደድና ፍቅርን መግለፅ

 • ኢማም ማሊክ አል ሙወጠዕ በተባለ ኪታባቸው ውስጥ ከአቢ ኢድሪስ አልኸውላኒ እንዳስተላለፉት እንዲህ አሉ “ወደ ደማስቆ መስጅድ በገባሁ ጊዜ ፈገግታው እጅግ የሚያበራ ሰው አየሁ። ሰዎች በአንድ ነገር ያልተስማሙ እንደሆነ ጉዳዩን ወደርሱ ያደርሣሉ። የሱንም ሀሳብና አስተያየት ይጠብቃሉ። ማን እንደሆን ስጠይቅ ሙዓዝ ኢብኑ ጀበል እንደሆነ ተነገረኝ። በማግስቱ በጠዋቱ ወደ መስጊድ ሄድኩኝ። ቀድሞኝ ሄዶ ኖሮ ሲሰግድ አገኘሁት። ሰላቱን እስኪጨርስ ጠበቅኩና በፊት ለፊቱ በኩል በመምጣት ሠላምታ ከሠጠሁት በኋላ “ወላሂ እኔ እወድሃለሁ።” አልኩት። “ወላሂ በል።” አለኝ። “ወላሒ” አልኩት። በነጠላዬ ጫፍ በመያዝ ወደራሱ አስጠጋኝና “አብሽር እኔ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም “ውዴታዬ በኔ መንገድ ለተዋደዱ፣ በኔ መንገድ ለተቀማመጡና በኔ መንገድ መከራ ላዩት ግዴታ ሆነች።” ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ። አለኝ።
 • ኢማም ማሊክ በአል ሙወጠእ ኪታባቸው ከጡፈይል ኢብኑ ኡበይ ኢብኑ ከዕብ እንደዘገቡት ኡበይ ወደ ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር በመሄድ ከርሱ ጋር በማለዳ ወደ ገበያ ይወጣ ነበር። “ወደ ገበያ በምንወጣበት ወቅት ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር ተራ ነገሮችን የሚሸጠውን፣ ውዱንም ነገር የሚሸጠውንም ሆነ ድሃውንም ጭምር ሰላም ሣይል አያልፍም ነበር።” ይላል ኡበይ። ጡፈይል ደግሞ እንዲህ ይላል “ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመርን አገኘሁትና ወደ ገበያ ሲሄድ እንድከተለው ጠየቀኝ። እኔም “ከገበያ ምን ትሠራለህ አንተ የምትገዛውም ሆነ የምትጠይቀው ነገር የለህም። በገበያ መሃልም መቀመጥ አይኖርብህም።” አልኩት። እሱም “የጡፈይል አባት ሆይ እኛ ወደ ገበያ ማልደን የምንወጣው እኮ ለሠላምታ ነው። ያገኘነውን ሁሉ ሠላም እንላለን።” አለኝ።
 • ኢማም አቢ ሀኒፋ ረሂመሁላህ ኩፋ ሣሉ አንድ ጎረቤት ነበራቸው። ጎረቤታቸው ሁሌም ከሥራ ወደ ቤቱ በሚመለስበት ወቅት ድምፁን ከፍ አድርጎ የችግር ብሦት ያዜማል። ድምፁ በርግጥም የሚረብሽ ነበር)።አቢ ሀኒፋ በየለሊቱ ይህ ሰውዬ የሚያንጎራጉረውን ዜማ ይሠማሉ። በአንድ ወቅት ጥበቃዎች ይህን ጎረቤታቸውን ወስደው አሠሩት። አቡ ሀኒፋም የለመዱትን ድምፅ በማጣታቸው በነጋታው ሰዎችን ሲጠይቁ ሰውየው እንደታሠረ ተነገራቸው። ወዲያውም በጊዜው ወደነበሩት አሚር ዒሣ ኢብኑ ሙሣ ዘንድ በመሄድ ጎረቤታቸውን እንዲፈቱላቸው ጠየቁ። ጎረቤቱም ከእስር በተፈታ ጊዜ አቢ ሀኒፋ በሚስጢር ጠርተውት “እስር ቤቱ ውስጥ ዘነጋንህ ቆየንብህ እንዴ አንተ ወጣት።” አሉት። ሰውየውም “አይደለም መልካም ሰርተሃል በጎ አድርገሃል። አላህ ምንዳህን ይክፈልህ።” በማለት እርሣቸው ትልቅ እርሱ ትንሽ፤ እርሣቸው ጥሩ ጎረቤት መሆናቸውን እርሱ ግን መጥፎ መሆኑን የሚገልፅ ዜማ  እያዜመ ተሠናበታቸው።

መስጠትና ለጋስነት

 • ጦበራኒ አልከቢር በተባለ ኪታባቸው ውስጥ እንደዘገቡት ዑመር ኢብኑ አልኻጧብ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላችሁ አራት መቶ ድርሃም በስልቻ ውስጥ ካኖሩ በኋላ ለአገልጋያቸው “ሂድና ይህን ለአቡ ዑበይዳ ስጥ።“የምእመናን መሪ ይህንን ገንዘብ ለአንዳንድ ጉዳዮችህ ማስፈፀሚያ እንድታውል ነው።” ይሉሃል በለው።  በዚያውም እዚያው የሆነ ነገር እየሠራህ ቆይና ገንዘቡን ምን እንደሚደርግበት ተመልከት።” አሉት። አቡ ዑበይዳ መልእክቱ በደረሣቸው ጊዜ “አላህ ዑመርን ይቀበለው ይዘንለትም።” በማለት ሴት አገልጋያቸውን በመጥራት “እነኚህን ሰባቱን ለእገሌ፣ አምስቱን ለእገሌ፣ እነኚህን አምስቱን ደግሞ ለእገሌ ስጭ እስክትጨርሽ ድረስ።” አሏት።

ይህን የታዘበው የዑመር አገልጋይ ተመለሠና ያየውን ሁሉ ነገራቸው። ዑመር ለአቡ ዑበይዳ የላኩትን ተመሣሣይ ለሙዓዝ ኢብኑ ጀበልም አዘጋጅተው ነበርና እንዲወስድለት እና “ለአንዳንድ ጉዳዮችህ አውል ብለውሃል” በማለት ላኩት። ሙዓዝም እንደ አቡ ዑበይዳ ሁሉ “ዑመርን አላህ ይቀበለው ይዘንለትም።” ካሉ በኋላ “ነይ አንች ልጅ ይህን የእገሌ ቤት ውሰጅ ይህን ያህል ደግሞ ለእገሌ ቤት ስጭ …” አሏት። ለአገልጋያቸው። የሙዓዝ ባለቤት ሙዓዝ የሚደርጉትን ካየች በኋላ “ወላሂ እኛ ድሆች ነን። ለኛ ስጥ ይገባናል አለቸው። በቋጠሮው ውስጥ ሁለት ዲናር ብቻ ነበር የቀረውና እሱኑ ወረወረላት።፡ አገልጋዩ ሙዓዝ ዘንድ ያየውንም ነገር ተመልሦ ለዑመር ነገራቸው። ዑመርም በሁኔታው በመደሠት “ እነሱ ወንድማማቾች ናቸው።” አሉ።

 • በዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላችሁ ዘመን ሰዎች ከፍተኛ በሆነ ድርቅ ተመቱ። በዚህ ቀውጢ ሰዓት አንድ ሺሕ ግመሎችን ያቀፈና የተለያዩ የምግብ እና የልብስ ዓይነቶችን የያዘ የኡስማን የንግድ ቅፍለት ከሻም ተነስቶ መካ ደረሠ። ነጋዴዎች ተረባርበው ለመግዛት ወደ ቦታው ሮጡ። ዑስማንም “በምን ያህል ትርፍ ትገዙኛላችሁ” አላቸው። እነርሱም “በአሥር አምስት እናትርፍልህ” አሉት። እሱም “እኔ ከዚህ በላይ ዋጋ አግኝቻለሁ።” አላቸው። እነሱም “እኛ በንግድ ዓለም ውስጥ ከዚህ በላይ የሚሠጥ ማንንም አናውቅም።” አሉት። ዑስማንም “እኔ ግን በአንድ ድርሃም ሰባት መቶና ከዚያም በላይ በሆነ እጥፍ የሚከፍለኝ አግኝቻለሁ በማለት

مَّثَلُ الَّذِينَ يُنفِقُونَ أَمْوَالَهُمْ فِي سَبِيلِ اللَّهِ كَمَثَلِ حَبَّةٍ أَنبَتَتْ سَبْعَ سَنَابِلَ فِي كُلِّ سُنبُلَةٍ مِّائَةُ حَبَّةٍ ۗ وَاللَّهُ يُضَاعِفُ لِمَن يَشَاءُ ۗ وَاللَّهُ وَاسِعٌ عَلِيمٌ

የእነዚያ ገንዘቦቻቸውን በአላህ መንገድ የሚለግሱ ሰዎች (ልግስናምሳሌ በየዘለላው ሁሉ መቶ ቅንጣት ያለባቸውን ሰባት ዘለላዎች እንደአበቀለች አንዲት ቅንጣት ብጤ ነው። አላህም ለሚሻው ሰው (ከዚህ በላይያነባብራል። አላህም ችሮታው ሰፊ ዐዋቂ ነው። (አል በቀራ፤ 261)

የሚለውን የቁርዓን አንቀፅ አነበቡላቸው።

ቀጥለውም “እናንተን ምስክር አደርጋለሁ። በአላህ እምላለሁ። እናንተ ነጋዴዎች ሆይ! የንግድ ቅፍለቷ ከነጫነችው ስንዴ፣ ዱቄት፣ ዘይት፣ ቅቤ እና ልብስ ለመዲና ድሆችና ችግረኞች ሠጥቻለሁ። በሙስሊሞች ሰደቃ አድርጌለሁ። አላቸው።

ቡኻሪ እና ሙስሊም ከአቢ ሙሣ አል አሽዐሪ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላችሁ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ “የአሽዐሪ ሰዎች ለጦርነት በወጡ ጊዜ ስንቃቸው ካለቀች አሊያም በመዲና ያሉ ቤተሰቦቻቸው የምግብ ችግር የገጠማቸው እንደሆነ እያንዳንዱ ሰው ዘንድ ያለውን ሁሉ በአንድ ልብስ ይሰበስቡና በአንድ መስፈሪያ በመካከላቸው እኩል ይከፋፈላሉ። እነርሱ ከኔ ናቸው እኔም ከነርሱ ነኝ።”

ይህ በታሪክ ስለነዚያ ምርጥ ሰሃቦችና ቀደምት ሠለፎች ከተላለፈልን ጥቂቱ ነው። ሥራቸውና ምግባራቸው በርግጥ እጅግ መልካምና የሚወደስ ለአብነትም የሚጠቀስ ነው። በነዚያ ቀደምት ሰሃቦችና እነሱንም በበጎ መንገድ በተከተሉ ማህበረሰቦች ውስጥ ምርጥ ሥነምግባር ለመትከል በነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም  የተደረገው ሩጫ በእጅጉ የተሣካ ነበር። እነርሱ በርግጥም ነቢዩም ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንደተናገሩት በላጩ ዘመን እርሳቸውና ሰሃቦቻቸው የኖሩበት ዘመን ስለመሆኑ በተግባር አስመስክረዋል። እኛም የዚያን ምርጥ ትውልድ መንገድ መከተል በእጅጉ ያስፈልገናል።

ታላቁ ሰሃባ ዐብዱላህ ኢብኑ መስዑድ የነዚያን ሰሃቦች ፋና መከተል ያለውን ትልቅ ደረጃ ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ

“እከተላለሁ ያለ የአላህን መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሰሃቦች ይከተል። እነሱ የዚህ ኡማ እጅግ ምርጥ ሰዎች፣ እጅግ አዋቂዎች፣ እጅግ ገሮች፣ እጅግ ቅኖችና እጅግ መልካሞች ናቸው። አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ የሱ ነቢይ ባልደረቦች ይሆኑ፤ ሃይማኖቱንም ያስፋፉ ዘንድ መረጣቸው።  የነርሱን ደረጃ እወቁ ፋናቸውን ተከተሉ። እነርሱ ቀጥ ባለው መንገድ ላይ ናቸውና።”

የታቢኢዮች /ሰሃቦችን ዘመን ተከትለው የመጡ ህዝቦች/  ዘመን ምርጥ ስለመሆኑም አያጠራጥርም። በመልካምነቱ፣ በበረከቱ እና በበጎነቱ ከሰሃቦች ዘመን ቀጥሎ ያለው ዘመን በደረጃ ብልጫ ይከተላል።

ከዚህ ምርጥ ስብእናቸውና ታሪካቸው ብዙ ሙስሊም ትውልድ ሲጠቀም ኖሯል። በብርሃናቸው ተመርቷል። ሥልጣኔንና ብልፅግናን በመገንባቱ ረገድም በነርሱ መንገድ ነበር የተጓዘው። ኋላ ላይ ግን አመታት እየራቁ ሲሄዱ ኢስላማዊው ሥርዓት እየተዳከመ መጣ። የኺላፋ ዘመንም አበቃ። እስልምና በመንግስት ደረጃ መተግበር ቀርቶ በግለሰብና በተወሰኑ ቡድኖችና ማህበራት ላይ ብቻ ተወሠነ።

ይህንኑ አጋጣሚ በመጠቀም የኢስላም ጠላቶች ዓለማቸውን ወደ ማሣካቱ ጎዳና ገቡ። ያለሙትን የረጅም ጊዜ ህልማቸውን ተገበሩ… በቅኝ ግዛትና በሌላም የእስልምናውን ዓለም በጣጠሱት፣ በታተኑት.. የሚጠላሉ የሆኑ ትንንሽ  መንግስታትም አደረጓቸው። በዚህም የተነሣ አብዛኞቹ ስሜት የሚመራቸው፣ የየራሣቸው ፍላጎት እና ጥቅም ብቻ የተጠናወታቸው፣ ለኡማው የማይጨነቁ፣ ዓላማቸውን የማያውቁና በምድር ላይም ያለ አንዳች ግብና ስኬት የሚኖሩ ለሙስሊሙ አንድነት ግድ የሌላቸው መንግስታት ተፈጠሩ። ሲያዩዋቸው አንድ ይመስላሉ ልቦናቸው ግን የተለያየ ነው። ሲመለከቷቸው ብዙ ናቸው ነገርግን ሀይላቸውና ጥንካሬያቸው እንደ ውሃ ላይ ዐረፋ ነው።

ሆኖም ግን ይህ ሁኔታ ብዙ ጊዜ ይቀጥላል ተብሎ አይታሰብም። ኢንሻአላህ ሙስሊሞች ከረጅሙ እንቅልፋቸው የሚነቁበት ከቆዩበት ድክመት የሚባንኑበት ቀን ይመጣል። ያኔ ምድር ላይ የእስልምና መርሆ ይወርዳል፤ የቁርዓን መመሪያም ይተገበራል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here