ለአላህ ብሎ መዋደድ (ክፍል 4)

0
3723

ለአላህ ብሎ የመዋደድ ሀቆች / አንድ ሙስሊም ወንድም በሌላኛው ሙስሊም ላይ የሚኖሩት መብቶች/

አጠቃላይ ሀቆች (ለሁሉም መሠጠት ያለባቸው) እና ልዩ የሆኑ ሀቆች (ለተወሰኑ ሰዎች የሚሠጡ) ብለን በሁለት ልንከፍላቸው እንችላለን።

ለሁሉም ሙስሊም መድረስ ያለባቸው /አጠቃላይ ሀቆች/መብቶች የምንላቸው የታወቁ ሲሆኑ

 1. ሠላምታን ማብዛት/ አሠላሙ ዐለይኩም ማለት
 2. ሠላምታን መመለስ
 3. የታመመን መጠየቅ
 4. የሞተን መከተል /መሸኘት
 5. ለጥሪ ምላሽ መስጠት
 6. ያስነጠሰን ማስደሠት ( የርሀመከላህ ማለት)
 7. የማለን መሀላውን ማፅናት (ያደርግልኛል ብሎ በኛ ተማምኖ የማለን)
 8. የተበደለን ማገዝ
 9. ምክር ለሚያስፈልገው ሰው ማሰብና መጨነቅ
 10. የተጨነቀን ከጭንቀቱ መገላገል
 11. የቸገረውን ከችግሩ ማውጣት
 12. ያጠፋን ነውሩን መሸፈን/ ገመናውን በአደባባይ አለማጋለጥ
 13. ከምቀኝነት፣ ጥላቻ፣ በደል፣ ንቀትና ከመሣሰሉት መጥፎ ባህሪዎች መራቅ እና ሌሎችም ወሣኝ የሆኑ ወንድማዊ ሀቆች እና መሠረታዊ የሆኑ ማህበራዊ ግዴታዎች ሊጠቀሱ ይችላሉ።

በጠቀስናቸው ሀቆች/መብቶች/ ዙሪያ ብዙዎቻችን የምናውቃቸው በርካታ ሀዲሦች ከነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ተላልፈውልናል። ከነኚህም መካከል፦

 • ሙስሊም አቢ ሁረይራን አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና በመጥቀስ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ “የሙስሊም በሙስሊም ላይ ያለው ሀቆች /መብቶች ስድስት ናቸው፡- ስታገኘው ሠላም በለው፣ ሲጠራህ ለጥሪው ምላሽ ስጥ፣ ከማከረህ አማክረው፣ አስነጥሦ አልሀምዱሊላህ ያለ እንደሆነ አስደስተው (የርሀምከላህ) በለው፣ ከታመመ ጠይቀው፣ ከሞተ ሸኘው፡”
 • ቡኻሪ እና ሙስሊም ከአል በራእ ኢብኑ ዓዚብ በዘገቡት ሀዲስ ደግሞ እንዲህ አለ “የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በሰባት ነገሮች አዘውናል፤ ከሰባት ነገሮች ደግሞ ከልክለውናል። በሽተኛን እንድንጠይቅ፣ ጀናዛን እንድንከተል (ወደ መቃብር እንድንሸኝ)፣ ያስነጠሠን እንድናስደስት፣ የማለን መሃላውን እንድናፀናለት ( ወላሂ እንዲህ ያደርግልናል ብሎ ተማምኖ ከማለብን እንድናደርግለት)፣ ተበዳይን እንድናግዝና፣ ሰላምታን እንድናበዛ አዘውናል።
 • ኢማም ሙስሊም አቡ ሁረይራን በመጥቀስ እንደዘገቡት ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል “ከዱኒያ ጭንቀቶች መካከል ከአንዱ ጭንቅ አማኝን የገላገለ ሰው ከትንሣኤ ቀን ጭንቀቶች ከአንዱ አላህ ይገላግለዋል። አንድ ነገር የከበደውን ሰው ያግራራለት ሰው አላህ በዱኒያም ሆነ በአኺራ ያግራራለታል። የሙስሊምን ነውር የሸፈነን ሰው አላህ ነውሩን ይሸፍንለታል። አንድ ወንድም ወንድሙን በመርዳት ላይ እስከዘወተረ ድረስ አላህ ይረዳዋል።፡”
 • ኢማም ቡኻሪ አቢ ሁረይራን በመጥቀስ በዘገቡት ሌላ ሀዲስ ደግሞ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ “አደራችሁን መጥፎ ጥርጣሬን ተጠንቀቁ እሱ የውሸቶች ሁሉ ትልቁ ነውና። አትሠላለሉ፣ አጉል ፉክክር አትፎካከሩ፣ አትመቀኛኑ፣ አትጠላሉ፣ የአላህ ባሮች ወንድማማቾች ሁኑ። ሙስሊም የሙስሊም ወንድም ነው። አይበድለውም፣ አያዋርደውም፣ አይንቀውም፣ ፍራቻ እዚህ ጋ ነው (ወደ ልባቸው እያመለከቱ)። አንድ ሰው ሙስሊም ወንድሙን መናቁ ከክፋት ይበቃዋል። እያንዳንዱ ሙስሊም በሌላኛው ሙስሊም ላይ እርም ነው። ደሙ ክብሩና ገንዘቡ።”

ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚሠጡ ልዩ ሀቆች የምንላቸው

እነኚህ ከፍ ያሉ፣ እጅግ ግዙፍና በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሀቆች ናቸው። እነኚህ ሀቆች አንድ ሙስሊም በምድር ላይ ሲኖር በችግር ጊዜ አጋዡ፣ በመከራ ጊዜ ደራሹ፣ በፈተና ጊዜ አፅናኙ፣ በደስታ ጊዜ ተጋሪው.. ለሚሆኑ፤ እጅግ ለሚቀርቡትና እራሱ ለራሱ ብሎ ለመረጣቸው ሚስጢረኞቹ፣ አማካሪዎቹና መካሪዎቹ ምርጥ ወንድሞቹ የሚሠጣቸው ሀቆች ናቸው። ስለሆነም አንድ ሰው እነኚህን ትላልቅ መብቶች እጅግ በተሟላ መልኩ መፈፀም ይችል ዘንድ የሀቆቹን ዋና ዋና ነጥቦችና መፈፀሚያ መንገዶቹን ጠንቅቆ ሊያውቅ ይገባዋል።

 1. ከላይ አጠቃላይ መብቶች ብለን የጠቀስናቸው ሁሉ እዚህ ሥር የሚካተቱ ሲሆን
 2. እሱን ሣያስፈቅዱና ሳያሣውቁ ከልብ ጓደኛ ቤት መብላት የሚቻል ስለመሆኑ

لَّيْسَ عَلَى الْأَعْمَىٰ حَرَجٌ وَلَا عَلَى الْأَعْرَجِ حَرَجٌ وَلَا عَلَى الْمَرِيضِ حَرَجٌ وَلَا عَلَىٰ أَنفُسِكُمْ أَن تَأْكُلُوا مِن بُيُوتِكُمْ أَوْ بُيُوتِ آبَائِكُمْ أَوْ بُيُوتِ أُمَّهَاتِكُمْ أَوْ بُيُوتِ إِخْوَانِكُمْ أَوْ بُيُوتِ أَخَوَاتِكُمْ أَوْ بُيُوتِ أَعْمَامِكُمْ أَوْ بُيُوتِ عَمَّاتِكُمْ أَوْ بُيُوتِ أَخْوَالِكُمْ أَوْ بُيُوتِ خَالَاتِكُمْ أَوْ مَا مَلَكْتُم مَّفَاتِحَهُ أَوْ صَدِيقِكُمْ ۚ لَيْسَ عَلَيْكُمْ جُنَاحٌ أَن تَأْكُلُوا جَمِيعًا أَوْ أَشْتَاتًا ۚ فَإِذَا دَخَلْتُم بُيُوتًا فَسَلِّمُوا عَلَىٰ أَنفُسِكُمْ تَحِيَّةً مِّنْ عِندِ اللَّهِ مُبَارَكَةً طَيِّبَةً ۚ كَذَٰلِكَ يُبَيِّنُ اللَّهُ لَكُمُ الْآيَاتِ لَعَلَّكُمْ تَعْقِلُونَ

“(ከሰዎች ጋር በመብላት) በዕውር ላይ ኀጢአት የለበትም። በአንካሳም ላይ ኀጢአት የለበትም። በበሽተኛም ላይ ኀጢአት የለበትም። በነፍሶቻችሁም ላይ ከቤቶቻችሁ ወይም ከአባቶቻችሁ ቤቶች ወይም ከእናቶቻችሁ ቤቶች ወይም ከወንድሞቻችሁ ቤቶች ወይም ከእኅቶቻችሁ ቤቶች ወይም ከአጎቶቻችሁ ቤቶች ወይም ከአክስቶቻችሁ ቤቶች ወይም ከየሹሞቻችሁ ቤቶች ወይም ከየሹሜዎቻችሁ ቤቶች ወይም መክፈቻዎቹን ከያዛችሁት ቤት ወይም ከወዳጃችሁ ቤት (ብትበሉ) ኀጢአት የለባችሁም። ተሰብስባችሁ ወይም ተለያይታችሁ ብትበሉ በእናንተ ላይ ኀጢአት የለባችሁም። ቤቶችንም በገባችሁ ጊዜ፤ ከአላህ ዘንድ የኾነችን የተባረከች መልካም ሰላምታ በነፍሶቻችሁ ላይ ሰላም በሉ። እንደዚሁ አላህ አንቀጾችን ለእናንተ ያብራራል። ልታውቁ ይከጀላልና።” (ኑር፤ 61)

ከላይ የተጠቀሰውን የቁርአን አንቀፅ ዑለማኦች ሲያብራሩ

“እዚህ ጋር የተጠቀሰው ማስፈቀድ አንድ ሰው ከገዛ ቤቱ ለመብላት እንዲያሰፈቅድ ሳይሆን ሰዎች ያለፈቃድ ከቅርብ ዘመዶቹ ወዳጆቹ ቤት ቢበላ ከራሱ ቤት እንደሚበሉ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው። ማንኛውም ሰው ከራሱ ቤት ለመብላት ፈቃድ እንደማያስፈልገው ይታወቃልና።” ይላሉ።

ከዚህ ግንዛቤ በመነሣት አንድ ሰው ከራሱ ቤት ቢበላ እንደሚበቃለት ሁሉ ከጓደኛው አሊያም ከቅርብ ዘመዱ ቤት ቢበላ ይበቃለታል። ማለት ይቻላል።

ኢማም ቁርጡቢ ረሂሙሏህ አንዳንድ ምሣሌዎችንና ተጨባጭ ነገሮችን በማንሣት ይህንኑ ጉዳይ በማስረገጥ ተናግረዋል።

ሙሀመድ ኢብኑ ሰውር ሙዐመር እንዲህ ማለቱን ዘግቧል። “የቀታዳህ ቤት ገባሁ። የሆነ ተምርም አገኘሁና በላሁ።” “ምንድነው እሱ?” አለኝ። “ቤትህ ውስጥ እሸት ተምር አገኘሁና በላሁ።” አልኩት። እሱም “ጥሩ አደረግክ።” በማለት(አሊያም ከጓደኞቻችሁ ቤት)  የሚለውን የቁርዓን አንቀፅ አነበበልኝ።

ሙዐመር አንዲህ ይላል “ለቀታዳህ ከዚህ የውሃ መያዣ ልጠጣ ወይ?” ብዬ ጠየቅኩት። እሱም “አንተ የልብ ጓደኛዬ ነህ ማስፈቀድ ለምን አስፈለገ?” በማለት መለሠልኝ።

ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በይሩሃእ ወደሚባለው የአቢ ጦልሃ መናፈሻ በመግባት ሣያስፈቅዱ ገብተው ያርፉ ጣፋጭ ውሃዋንም ይጠጡ ነበር።

1. በግላዊ ጉዳይ ከሦስት ቀን በላይ መኮራረፍ ክልክል ስለመሆኑ

ቡኻሪና ሙስሊም ከአቡ አዩብ አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ “ለአንድ ሙስሊም ከሦስት ቀን በላይ ወንድሙን መዝጋት አይበቃለትም። ይገናኛሉ ይሄም ዞር ይላል ያም ዞር ይላል። በላጫቸው በሠላምታ የጀመረው ነው።”

ማኩረፍና መዝጋቱ ለዲን ጉዳይ ከሆነ ግን ከሦስት ቀን በላይም ቢሆን ይበቃል። አቡ ደርዳእ ግን “ወንድምህ ከነበረበት መጥፎ ሁኔታ የሚቀየርና አንዴ የሚስተካከል ሌላ ጊዜ የሚበላሽ ዓይነት ከሆነ በኩርፊያ አታርቀው አናግረው።” የሚል አመለካከት አላቸው።

ታላቁ ታቢዒ ኢብራሂም አንነኸዒም የአቡ ደርዳእን አቋም በመደገፍ እንዲህ ይላሉ፡-

“ወንድምህን አትቁረጠው። አርቀህም ለተኩላ አሳልፈህ አትስጠው። እሱ ዛሬ ያጠፋውን ነገ ሊታረምበት ይችላልና።”

ኢማም ገዛሊም ይህንኑ የአቡ ደርዳእን እና የኢብራሂም አን ነኸዒን መንገድ በመከተል“ከአንድ ወንድማችን ጋር ያለንን ግንኙነት የበጠስን እንደሆነ ወደ ቀጥተኛው መንገድ የሚመለስበትን አንድ እድል አጣን ማለት ነው።  እሱ ምናልባትም ጥፋት አጥፍቶ ጥፋቱን ለምናስወግድለት ክፉ ቀን እኛን አስቀምጦ ይሆናልና”

ኢማሙ አክለውም “አንድ ወንድም በደሀየ ጊዜ ወንድሙ ሊረዳው ግድ እንደሆነ ይታወቃል። የዲን ድህነት ደግሞ ከገንዘብ ድህነት የበለጠ ነውና በዲን የደሀየን ሰው ይበልጡኑ መርዳት ያስፈልጋል።” ይላሉ።

ይህ ታላቁ ሰሃባ አቡ ደርዳእ፣ ታላቁ ታቢዒ ኢብራሂም አን ነኸዒና ታላቁ ዓሊም ኢማም አልገዛሊ የያዙት መንገድ “አንድ ሙስሊም ወንጀል ላይ የወደቀ እንደሆነ ቆርጠን ካልጣልነው ወደ ኸይር ይመለሣል ተብሎ ይታሠባል።” በሚል ነው። ያጠፋን አሊያም የሣተን ወንድም ወደራሣችን ካስጠጋነውና ከመከርነው መጥፎ ነገሮችን ይተዋል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል። በወንጀሉ ላይ ገፍቶ የሄደ እንደሆነና  በሀጢዓት ውስጥ ከሠጠመ ግን ምክርም ሆነ ማስታወስ ምንም አይጠቅመውም። በዚህ ጊዜ ደግሞ እሱን መዝጋትና ማኩረፉ የጠንካራ ኢማን ምልክት ነው።

2. በየትኛውም ሁኔታና ነገሮች ላይ ከወንድሞች ጋር መሥራትና መኗኗር

የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም “ከመዋደድና ከመተዛዘን አንፃር የአማኞች ምሳሌ እንደ አንድ የሰውነት ክፍል ነው። አንደኛው የታመመ እንደሆነ ሌላኛው በትኩሣትና እንቅልፍ በማጣት ይጠራራል።”

በሌላም ሀዲሣቸው “አንዳችሁም አላመናችሁም ለራሱ የሚወደውን ነገር ለወንድሙ እስካልወደደ ድረስ።” ብለዋል።

ይህ መኗኗር በማንኛውም ሁኔታ በገንዘብ፣ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይም ሆነ በችግር ጊዜ ለወንድም ጉዳይ ቅድሚያ መስጠትን ያጠቃልላል።

ወንድምን በማስበለጡ ዙሪያ አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

وَالَّذِينَ تَبَوَّءُوا الدَّارَ وَالْإِيمَانَ مِن قَبْلِهِمْ يُحِبُّونَ مَنْ هَاجَرَ إِلَيْهِمْ وَلَا يَجِدُونَ فِي صُدُورِهِمْ حَاجَةً مِّمَّا أُوتُوا وَيُؤْثِرُونَ عَلَىٰ أَنفُسِهِمْ وَلَوْ كَانَ بِهِمْ خَصَاصَةٌ ۚ وَمَن يُوقَ شُحَّ نَفْسِهِ فَأُولَٰئِكَ هُمُ الْمُفْلِحُونَ

“እነዚያም ከበፊታቸው አገሪቱን መኖሪያ ያደረጉት እምነትንም የለመዱት ወደእነርሱ የተሰደዱትን ሰዎች ይወዳሉ። (ስደተኞቹ) ከተሰጡትም ነገር በልቦቻቸው ውስጥ ቅሬታን አያገኙም። በእነርሱ ላይ ችግር ቢኖርባቸውም በነፍሶቻቸው ላይ ሌላውን ይመርጣሉ። የነፍሱንም ንፍገት የሚጠበቅ ሰው እነዚያ እነሱ ምኞታቸውን አግኚዎች ናቸው።” (ሀሽር፤ 9)

የወንድምን ጉዳይ መፈፀምን አስመልክቶ ደግሞ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ

“አንድ (የአላህ) ባሪያ ወንድሙን በመርዳት እስከዘወተረ ድረስ አላህ ይረዳዋል።

ለወንድም መቆርቆርንና መታመመን በተመለከተ ደግሞ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል “አንድን አማኝ ከዱኒያ ጭንቀቶች መካከል ከአንዱ ያላቀቀን አላህ ከትንሣኤ ቀን ጭንቀቶች ከአንዱ ያላቅቃዋል።”

ማስተማሪያና ማነቃቂያ ይሆኑን ዘንድ ወንድምን በማስበለጥ፣ በመርዳትና፣ ጉዳዩን በመፈፀም ዙሪያ አንዳንድ ምሳሌዎችንና ታሪኮችን እንመልከት

 • ፈትህ አልሙሰሊ ወደ አንድ ሙስሊም ወንድሙ ቤት ሄደ። ወንድሙ ቤት ውስጥ አልነበረም። ባለቤቱን ጠየቃትና ገንዘብ ከሚቀመጥበት ሳጥን ውስጥ ለጉዳዩ የሚያስፈልገውን ያህል ወስዶ ሄደ። ወደ ቤት ሲመለስ ሠራተኛው የሆነውን ሁሉ ነገረችው። ጓደኛውም አልሙስሊ በሠራው ነገር በመደሠት “የነገርሽኝ ነገር በርግጥም እውነት ከሆነ አንችን ለአላህ ብዬ ነፃ አርጌሻለሁ።” አላት።
 • ዐሊ ኢብኑ አልሁሴን አንድን ሰውዬ “አንዳችሁ በወንድማችሁ ኪስ ውስጥ እጃችሁን አስገብታችሁ ያለርሱ ፈቃድ የምትፈልጉትን ነገር ትወስዳላችሁን” በማለት ጠየቀው። ሰውዬውም “አይ የለም” አላቸው። ዐሊም“እንግዲያውስ እናንተ ወንድሞቼ አይደላችሁም” አለው።
 • ሌላው ደግሞ እንዲህ ይላል “ከአንድ ወንድማችሁ ገንዘብ ፈልጋችሁ “ምን ልታረግበት ነው” ብሎ የጠየቃችሁ እንደሆነ የወንድማማችነት ሀቅ ቦታ አጥቷል ማለት ነው።
 • መስሩቅ የኑፈይል እዳ ነበረበት። በወንድሙ ኸይሠማ ላይም እንዲሁ እዳ ነበር። መስሩቅ ሄደና ኸይሰማ ሳያውቅ ዕዳውን ከፍሎለት ተመለሠ። ኸይሠማም በበኩሉ መስሩቅ በማያውቅበት ሁኔታ ሄዶ ዕዳውን ከፈለለት። እነኚህ ሰዎች በርግጥም ከራሣቸው ይልቅ የወንድማቸው ነገር የሚያሣስባቸው መሆኑን እናያለን።
 • ኢብኑ ሺብራህ ለተወሰኑ ወንድሞቹ ከባድ ጉዳይ ፈፀመላቸው። እነርሱም ለበጎ ሥራው ስጦታ ይዘውለት መጡ። ኢብኑ ሺብረህም “ምንድነው ይሄ” አላቸው። እነርሱም “ላደረግክልን መልካም ነገር ውለታ ለመመለስ ነው” አሉት። ኢብኑ ሺብራህም “አላህ ይጠብቅህ ገንዘብህን ውሰድ።” አለውና እንዲህ በማለትም አስታወሰው  “አንድ ወንድምህን የሆነ ጉዳይ እንዲፈፅምልህ ጠይቀኸው ሊፈፅምልህ ካልቻለ ለሰላት ውዱእ አድርግ። አራት ተክቢራም አላሁ አክበር በልና ለሙታን የሚሰገደውን ሰላት ስገድበት።”
 • በአንድ ወቅት የሆነ ኸሊፋ ደጋግ የሆኑ ሦስት ሰዎች እንዲገደሉ አዘዘ። አቡል ሁሴን አን ኑሪ አንደኛቸው ነበር። ፍርዱ ሊፈፀም ሲቀርብ በአንደኝነት አንገቱን ለመቀላት ብሎ ወደፊት ወጣ። ኸሊፋው በሁኔታው በመገረም ለምን ይህን እንዳደረገ ጠየቀው። አቡ አልሁሴንም እንዲህ በማለት መለሠ“በዚህች አጋጣሚ ወንድሞቼ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን በህይወት እንዲቆዩልኝ ከራሴ ይልቅ እነርሱን መርጬ ነው።” አለ። በዚህም የተነሳ ሦስቱ ለግድያ ቀርበው የነበሩ ሰዎች ነፃ እንዲሆኑ ተደረገ።

ከነኚህ ምሣሌዎች የምንማረው ነገር ወንድማማችነት ላቅ ያለ የትብብር መንፈስ የተሞላበት መሆኑን ነው። ለየት ያለ ግንኙነትና እጅግ እውነተኛ የሆነ ቅርርቦሽም ነው። ጥርት ያለ ውዴታ የተሞላበት፤ ወንድምን ለመጥቀም እራስን መጉዳት የሚታይበት፣ ወዳጅን ለማስደሠት ለራስ ፀጋ ማጣትን የሚያካትት ነው.. እውነተኛ ወንድማማችነት።

3. የወንድምን ነውር መሸፈን/ ገመናውን በአደባባይ አለማውጣት

ሙስሊም ወንድምን ሆነብሎ ማጋለጥ የሙስሊም ባህሪ አይደለም። የሰው ልጅ ሁሌም ተሣሣች ነውና አንድ ወንድም የተሣሣተ እንደሆነ ጥፋቱን መደበቅ ያስፈልጋል። ይህም ከአላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ ዘንድ ታላቅ ምንዳን ያስገኛል። ሙስሊም አቢ ሁረይራን በመጥቀስ እንደዘገቡት ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ

“አንድ ባሪያ የአንድን ባሪያ ነውር አይሸፍንለትም አላህ የትንሣኤ ቀን ነውሩን የሸፈነለት ቢሆን እንጂ።”

በሌላ ዘገባ ደግሞ“ሙስሊምን የሠተረ/ነውሩንና ገመናውን የሸፈነ/ አላህ በዱኒያና በአኺራ ነውሩን ይሸፍንለታል።” ብለዋል።

ሙስሊም አቢ ሁረይራን በመጥቀስ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም “ሀሜት ምን እንደሆነ ታውቃላችሁን?” አሉ።“አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ እና መልእክተኛው ናቸው የሚያውቁት።” አሏቸው። ነቢዩም ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም “ወንድምህን በሚጠላው ነገር ማንሣት ነው።” “ወንድሜ እኔ የምለው ነገር ያለበት ቢሆንስ?” አሏቸው። እርሳቸውም “የምትለው ነገር ካለበት አምተሀዋል በሌለው ነገር የምታነሣው ከሆነ ደግሞ ዋሽተህበታል።” አሉ።

ከሀዲሱ የምንረዳው አንድ ወንድም የሌላኛውን ወንድሙን ሚስጢር መበተን እንደሌለበትና በሚጠላውም ነገር እሱን ማንሣት እንደሌለበት ነው። ነውሩን ማንሣትና በአደባባይም በመጥፎ ባህሪ እሱን መግለፅ የለበትም። አንድ ሰው በአንድ ወንድሙ ላይ መጥፎ ነገር ያየ እንደሆነ ሰዎች ፊት ማጋለጥ የለበትም። ለብቻው በመገለልና በመጥራት ይምከረው። በሰው ፊት ሰውን መምከር ሣይሆን ማዋረድ ነው።

ምክርም ሲደረግ ለአላህ ብቻ ታስቦ መሆን አለበት። የሚመከረውም ሰው ምክሩን መቀበልና ተግባር ላይ ለማዋል መንቀሣቀስ ይኖርበታል። አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

وَالْعَصْرِ ﴿١﴾ إِنَّ الْإِنسَانَ لَفِي خُسْرٍ ﴿٢﴾ إِلَّا الَّذِينَ آمَنُوا وَعَمِلُوا الصَّالِحَاتِ وَتَوَاصَوْا بِالْحَقِّ وَتَوَاصَوْا بِالصَّبْرِ

በጊዜያቱ እምላለሁ። ሰው ሁሉ በእርግጥ በኪሳራ ውስጥ ነው። እነዚያ ያመኑትና መልካሞችን የሠሩት፣ በእውነትም አደራ የተባባሉት፣ በመታገስም አደራ የተባባሉት ብቻ ሲቀሩ። (ዐስር፤1-4)

አንድ ሰው ወንድሙን በሚመክርበት ወቅትም ተመካሪውን ሰው ማጨናነቅና ማጣበብ መልኩ መሆን የለበትም። ዲን ሁሌም ምክር ነውና። ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና እንዲህ ይላሉ፦

“ነውሬን በስጦታ መልክ ያበረከተልኝን ሰው አላህ ይዘንለት።”

አንድ አማኝ የተሠጠውን ምክር በሰፊ ደረት፣ በተረጋጋ መንፈስና ውዴታ እንዲሁም በበጎ ጎኑ በመተርጎም መቀበል ይኖርበታል። ወንድሙ ሲመክረው እሱን መማዋረድ ሣይሆን መጥቀም ፈልጎ ነው። ይህን የሚያደርገው ወንድሙ ከሀጢዓት ወንጀል እንዲርቅ ወንድማዊ አደራውን ለመወጣት አስቦ ነው።

የሰው ልጅ የቱን ያህል አላህን ፈሪና መልካም ቢሆንም ሰው ነውና የሰው ልጅ የተፈጠረበት የስህተትና ወንጀል ባህሪ ላይ መውደቁ አይቀርም። የሰው ልጅ ሁሌም በጥንካሬ አይዘልቅም። ይወድቃል ይነሳል፤ ይሣሳታል ይመለሣል። ነገርግን እውነተኛ አማኝ የሆነ እንደሆነ በተሣሣተ ጊዜ አስታውሦ ይመለሳል። ተፀፅቶ ዳግም ወደ አላህ መንገድ ይገባል። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል

“የአደም ልጅ ሁሉ ተሣሣች ነው። ከተሣሣቾች ሁሉ በላጮቹ በተውባ ወደ አላህ የሚመለሱት ናቸው።”

ይቅርታ ከትላልቅ የኢስላም ሥነ-ምግባራት መካከል የሚመደብ ነው። እዝነት ደግሞ የአማኞች ባህሪ ነው። አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ አንዲህ ይላል፦

وَجَزَاءُ سَيِّئَةٍ سَيِّئَةٌ مِّثْلُهَا ۖ فَمَنْ عَفَا وَأَصْلَحَ فَأَجْرُهُ عَلَى اللَّهِ ۚ إِنَّهُ لَا يُحِبُّ الظَّالِمِينَ

የመጥፎም ነገር ዋጋ ብጤዋ መጥፎ ናት። ይቅርም ያለና ያሳመረ ሰው ምንዳው በአላህ ላይ ነው። እርሱ በደለኞችን አይወድም። (አሽ ሹራ፤ 40)

مُّحَمَّدٌ رَّسُولُ اللَّهِ ۚ وَالَّذِينَ مَعَهُ أَشِدَّاءُ عَلَى الْكُفَّارِ رُحَمَاءُ بَيْنَهُمْ ۖ تَرَاهُمْ رُكَّعًا سُجَّدًا يَبْتَغُونَ فَضْلًا مِّنَ اللَّهِ وَرِضْوَانًا ۖ سِيمَاهُمْ فِي وُجُوهِهِم مِّنْ أَثَرِ السُّجُودِ ۚ ذَٰلِكَ مَثَلُهُمْ فِي التَّوْرَاةِ ۚ وَمَثَلُهُمْ فِي الْإِنجِيلِ كَزَرْعٍ أَخْرَجَ شَطْأَهُ فَآزَرَهُ فَاسْتَغْلَظَ فَاسْتَوَىٰ عَلَىٰ سُوقِهِ يُعْجِبُ الزُّرَّاعَ لِيَغِيظَ بِهِمُ الْكُفَّارَ ۗ وَعَدَ اللَّهُ الَّذِينَ آمَنُوا وَعَمِلُوا الصَّالِحَاتِ مِنْهُم مَّغْفِرَةً وَأَجْرًا عَظِيمًا

የአላህ መልክተኛ ሙሐመድ እነዚያም ከእርሱ ጋር ያሉት (ወዳጆቹበከሓዲዎቹ ላይ ብርቱዎች በመካከላቸው አዛኞች ናቸው። አጎንባሾች፣ ሰጋጆች ኾነው ታያቸዋለህ። ከአላህ ችሮታንና ውዴታን ይፈልጋሉ። ምልክታቸው ከስግደታቸው ፈለግ ስትኾን በፊቶቻቸው ላይ ናት። ይህ በተውራት (የተነገረውጠባያቸው ነው። በኢንጂልም ውስጥ ምሳሌያቸው ቀንዘሉን እንደ አወጣ አዝመራና፣ (ቀንዘሉእንዳበረታው፣ እንደወፈረምና፣ ገበሬዎቹን የሚያስደንቅ ኾኖ በአገዳዎቹ ላይ ተስተካክሎ እንደቆመ (አዝመራነው። (ያበረታቸውና ያበዛቸውከሓዲዎችን በእነርሱ ሊያስቆጭ ነው። አላህም እነዚያን ያመኑትንና ከእነርሱ በጎዎችን የሠሩትን ምሕረትንና ታላቅ ምንዳን ተስፋ አድርጎላቸዋል። (አል ፈትህ፤ 29)

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا مَن يَرْتَدَّ مِنكُمْ عَن دِينِهِ فَسَوْفَ يَأْتِي اللَّهُ بِقَوْمٍ يُحِبُّهُمْ وَيُحِبُّونَهُ أَذِلَّةٍ عَلَى الْمُؤْمِنِينَ أَعِزَّةٍ عَلَى الْكَافِرِينَ يُجَاهِدُونَ فِي سَبِيلِ اللَّهِ وَلَا يَخَافُونَ لَوْمَةَ لَائِمٍ ۚ ذَٰلِكَ فَضْلُ اللَّهِ يُؤْتِيهِ مَن يَشَاءُ ۚ وَاللَّهُ وَاسِعٌ عَلِيمٌ

እናንተ ያመናችሁ ሆይከእናንተ ውስጥ ከሃይማኖቱ የሚመለስ ሰው አላህ (በእነርሱ ስፍራየሚወዳቸውንና የሚወዱትን፣ በምእመናን ላይ ትሑቶች፣ በከሓዲዎች ላይ ኀያላን የኾኑን በአላህ መንገድ የሚታገሉን የወቃሽን ወቀሳ የማይፈሩን ሕዝቦች በእርግጥ ያመጣል። ይኸ የአላህ ችሮታ ነው፤ ለሚሻው ሰው ይሰጠዋል፤ አላህም ችሮታው ሰፊ ዐዋቂ ነው። (አል ማኢዳህ፤ 54)

አንድ ወንድም ለወንድሙ ይቅር እስካላለ ድረስ ምርጥ ወንድም መሆን አይችልም። የወንድሙን ስህተት ያላለፈ እንደሆነም አዛኝ አይባልም። ለአማኝ ወንድሙ ስህተትና ጥፋት እስካልታገሠ ድረስ ራራለት አይባልም። የሰው ልጅ ጥፋቱ እጅግ ብዙ ነው። ምርጥ ሰው ማለት የሚቆጠሩ ሀጢኣቶች ያሉት ሰው ነው።

በሌላ በኩል የወንድምን ነውር መሸፈን ስንል በጥፋቱ ይገፋ ዘንድ አይቶ እንዳላዩ መሆን እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል። ባይሆን ያዩትን መጥፎ ነገር ለማንም ሳይናገሩ ለአጥፊው ብቻ መንገርና መምከር ነው። እያጠፋ ዝም ማለት በመልካም አለማዘዝና ከመጥፎ አለመከልከል የሙስሊም ባህሪ አይደለም። ሙስሊሞች በሀቅ ጉዳዮች ላይ ካልተመካከሩ መልካምነት አይኖራቸውም። በአላህ መንገድ ላይ እስካልተረዳዱም ትርጉም የላቸውም። በመልካም ነገር እስካልተመካከሩና ከመጥፎ እስካልተከላከሉ ድረስ በሸሪዓ ሚዛን እርባና ቢስ ናቸው።

እስልምና በአላህ መንገድ ላይ መመካከርን ከእስልምና መሰረቶች አንዱ አድርጎ ነው የሚቆጥረው። በሀቅ ላይ መመካከር ኢማን ግድ የሚለው ነገር ነው። በጥሩ ማዘዝና ከመጥፎ መከልከል የኢስላም መርሆ ነው።

አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ በመልካም የማያዙና ከመጥፎ የማይከለክሉ የነበሩትን የኢስራኢል ልጆች በነቢዩ ዳውድ እና በነቢዩ ዒሳ ዓለይሂ ሰላም እንደበት መረገማቸውን አውስቷል።፡ እንዲህ በማለት

لُعِنَ الَّذِينَ كَفَرُوا مِن بَنِي إِسْرَائِيلَ عَلَىٰ لِسَانِ دَاوُودَ وَعِيسَى ابْنِ مَرْيَمَ ۚ ذَٰلِكَ بِمَا عَصَوا وَّكَانُوا يَعْتَدُونَكَانُوا لَا يَتَنَاهَوْنَ عَن مُّنكَرٍ فَعَلُوهُ ۚ لَبِئْسَ مَا كَانُوا يَفْعَلُونَ

ከእስራኤል ልጆች እነዚያ የካዱት በዳውድና በመርየም ልጅ በዒሳ ምላስ ተረገሙ። ይህ ትእዛዝን በመጣሳቸውና ወሰንን የሚያልፉ በመኾናቸው ነው። ከሠሩት መጥፎ ነገር አይከላከሉም ነበር። ይሠሩትየነበሩት ነገር በእርግጥ ከፋ!” (አል ማኢዳህ፤ 78-79)

እንግዲህ ከላይ የተመለከትናቸው በአላህ መንገድ ወንድማማቾች የሆኑ ወገኖች አንዱ በሌላኛው ላይ ያላቸው ሀቆችና አንድ ሙስሊም ከሌላኛው አንፃር ያለበት ግዴታ ነው። ከላይ እንዳየነው ከነኚህ ሀቆች መካከል በአላህ ጌትነት ያመኑ፣ እስልምናን በሃይማኖትነት የተቀበሉ፣ ቁርዓንን በመመሪያነት የያዙና የሙሀመድን ነቢይነት እና መልእክተኝትን የተቀበሉ ሙስሊሞችን ሁሉ የሚያካትቱ የሆኑ አጠቃላይ ሀቆች አሉ። እነኚህ ሀቆች አብሮ ለሚኖር ሰውም ሆነ፣ ለጎረቤት፣ ለሥራ ጓደኛ፣ ለሥጋ ዘመድም ሆነ ለሌሎች ሙስሊም ወንድሞች ሁሉ መሰጠት አለባቸው።

ሌሎች ደግሞ እራሣችን ለራሳችን ብለን ከመረጥናቸው ልዩ ጓደኞች አንጻር የሚጠበቁብን ሀቆች አሉ። ለነኚህም ወንድሞች አጠቃላይም ሆነ ልዩ የሆኑ ሀቆቻቸውን ልንሰጣቸው ይገባል።

ዋና ዋና ነጥቦችን በአጭሩ ለማስታወስ ያህል

 • የልብ ጓደኛ በማይኖርበት ሰዓት ያለርሱ እውቅና እና ፈቃድ ከሱ ቤት መብላት የሚቻል መሆኑን። ይህም የወንድም ቅርርቦሽ ምን ያህል ጥልቀት ያለው እንደሆነ የሚያሣይ መሆኑን
 • ከሦስት ቀን በላይ መኮራረፍ የተከለከለ መሆኑን
 • ከወንድሞች ጋር በየትኛወም ነገርና ሁኔታ ላይ መኗኗር እንደሚገባ
 • ነውርን መሸፈን፣ አለመተማማት፣ ስህተትን ማለፍ ከዋና ዋናዎቹ የወንድማማችነት ሀቆች በተጨማሪ ልዩ በሆነ ጓደኝነት ውስጥ የሚጠቀሱ መሆናቸውን አይተናል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here