ለአላህ ብሎ መዋደድ (ክፍል 1)

0
7199

ሙስሊሞች እንደ ማህበረሰብ ብሎም እንደ ኡማ ጥንካሬያቸውንና የተሟላ ማንነታቸውን አስጠብቀው ዘውታሪ ወደሆነ ስኬትና ሀሴት መዝለቅ እንዲችሉ ሊከተሏቸው የሚገቡ መርሆዎች አሉ። ከነዚህ ወሳኝ መርሆዎች መካከል መልካም የሆነ የእርስ በርስ ትስስር እና መለኮታዊ መስፈርት ላይ የተገነባ ግንኙነት መሆኑ ግልጽ ነው። በተለይም የሙስሊሞች ህይወት ምንጭ ኢስላም እንደመሆኑ የህይወታቸው መልካም ዋስትና ለአላህ ብለው መዋደዳቸው እና መረዳዳታቸው ነው።

 ይህን አስመልክቶ በማይበጠሰው የአላህ የአንድነት እና የውዴታ ገመድ የተሳሰሩ ሰዎች ደራጃ፣ መገለጫዎች፣ ምንዳ እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች በተከታታይ ክፍሎች በአላህ ፍቃድ ለማየት እንሞክራለን።

“ለአላህ ብሎ መዋደድ” ምንድነው?

በአላህ መንገድ ወንድማማችነት እጅግ የተቀደሠ የአላህ ሱብሃሁ ወተዓላ ስጦታ፣  አንፀባራቂ የሆነ የጌታ ሽልማት እና ታላቅ አምላካዊ ፀጋም ነው። ይህን ፀጋ ማንም ተራ ሰው አያገኘውም። የትኛውም ሰው በቀላሉ አይታደለውም። አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ ከባሮቹ መካከል እሱን አጥርተው ለሚገዙ የሚሠጠው ነው። ከወዳጆቹም መካከል ለመረጣቸው የሚያወርሰው እንጂ ሌላ አይደለም። ከፍጥረታቱም ውስጥ እጅግ ፅዱ ልቦና ባላቸው ሰዎች ቀልብ ውስጥ ይህን ችሮታ ያኖረዋል።

አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ በሱረቱል ዓሊ ዒምራን ላይ እንዲህ ይለናል

وَاعْتَصِمُوا بِحَبْلِ اللَّهِ جَمِيعًا وَلَا تَفَرَّقُوا ۚ وَاذْكُرُوا نِعْمَتَ اللَّهِ عَلَيْكُمْ إِذْ كُنتُمْ أَعْدَاءً فَأَلَّفَ بَيْنَ قُلُوبِكُمْ فَأَصْبَحْتُم بِنِعْمَتِهِ إِخْوَانًا وَكُنتُمْ عَلَىٰ شَفَا حُفْرَةٍ مِّنَ النَّارِ فَأَنقَذَكُم مِّنْهَا ۗ كَذَٰلِكَ يُبَيِّنُ اللَّهُ لَكُمْ آيَاتِهِ لَعَلَّكُمْ تَهْتَدُونَ

የአላህንም (የማመን) ገመድ ሁላችሁም ያዙ። አትለያዩም። ጠበኞችም በነበራችሁ ጊዜ በእናንተ ላይ (የዋለውን) የአላህን ጸጋ አስታውሱ።በልቦቻችሁም መካከል አስማማ። በጸጋውም ወንድማማቾች ኾናችሁ። በእሳት ጉድጓድ አፋፍም ላይ ነበራችሁ። ከእርስዋም አዳናችሁ። እንደዚሁ ትመሩ ዘንድ አላህ ለእናንተ አንቀጾቹን ያብራራል።  (አል ኢምራን፤ 103)

ኡኹዋህ /ወንድማማችነት/ ኢስላማዊው የእምነት አመላከከት /ዐቂዳ/፣ የኢማን እና የአላህ ፍራቻ ውጤት ከሚያስተሣስር ማንኛውም ሙስሊም ጋር በጥብቅ የሚያቆራኝ ከውስጥ የሆነ ጥልቅ የመተዛዘን፣ የመዋደድ፣ የመካባበርና የመተማመን ስሜትን የሚያወርስ ኢማናዊ ጥንካሬ ነው። ይህ ወንድማዊ ስሜት እየጎለበተ ሲሄድ በአንድ አማኝ ልብ ውስጥ በጎ የሆነ ጥልቅ ስሜትን ይፈጥራል። መረዳዳትና ሌላውን ከራስ አስበልጦ መውደድ፣ ለሌላው መቆርቆር፣ መተዛዘን፣ ይቅር መባባል፣ በችግር ጊዜ መደራረስ፣ በድካም ጊዜ መተጋገዝና የመሣሰሉት.. ከበጎ ውጤቶቹ መካከል ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው። እውነተኛ የወንድማማችነት ስሜት በሰው ልጆች ነፍስ፣ ንብረትም ሆነ ክብር ላይ ከሚደርሰው ማንኛውም ጉዳት አንፃር የተቃዋሚነት አቋምም ለመያዝ ያስችላል።

በአላህ መንገድ ወንድማማችነት ከኢማን ጋር እጅግ የተቆራኘ ባህሪ ነው። ከአላህ ፍራቻ ጋርም በእጅጉ የተዛመደ ነው። ያለ ኢማን ወንድማማችነት እንደማይኖር ሁሉ ያለ ወንድማማችነትም ኢማን የለም። ያለ አላህ ፍራቻ የልብ ጓደኝነት እንደማይኖር ሁሉ ያለ የልብ ጓደኝነትም የአላህ ፍራቻ የለም። በሌላ አነጋገር “በአላህ መንገድ ወንድማማችነት ኢማንን መሠረት ያደረገ ነው። ሰዎች ለወንድማማችነታቸው ትኩረት የማይሠጡ ከሆነ ኢማናቸው ያጠራጥራል።” እንደማለት ነው። እንዲሁም “ሰዎች አላህን ፍራቻ መሠረት አድርገው የልብ ጓደኛ መያዝ አለባቸው። የልብ ጓደኝነት ከሌለም የአላህ ፍራቻ የለም” ማለት ነው።

ከላይ የጠቃቀስናቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ በቁርዓን ውስጥ የተጠቀሠ ነገር አለ።“ያለ ኢማን/እምነት/ ወንድማማችነት የለም።” ላልነው አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ በሱረቱ አልሁጁራት ላይ ያለውን በመጥቀስ ነው። “ምእመናን ወንድማማቾች ናቸው።”

“ያለ አላህ ፍራቻ እውነተኛ ጓደኝነት አይኖርም።” ላልነው ደግሞ ማስረጃችን አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ እንዲህ ማለቱን በመጥቀስ ነው።

الْأَخِلَّاءُ يَوْمَئِذٍ بَعْضُهُمْ لِبَعْضٍ عَدُوٌّ إِلَّا الْمُتَّقِينَ

ወዳጆች በዚያ ቀን ከፊላቸው ለከፊሉ ጠላት ነው። አላህን ፈሪዎች ብቻ ሲቀሩ። (ዙኽሩፍ፤ 67)

ኢማንን መስፈርቱ ያላደረገ ወንድማማችነት የራስ ጥቅም ማሳደጃና ግለሰባዊ ፋይዳን ማሟያ መድረክ ነው የሚሆነው። ወዳጅነትም በአላህ ፍራቻ አንፃር ካልመሠረተ የሰው ልጅ በየፊናው በዚህች ዓለም ጥቅም ተታሎ የራሱን ጥቅም ለማስከበር ትግል ማድረጉ አይቀርም። በዚህም የተነሣ ሽኩቻ፣ ጥላቻና ጠላትነትን ትርፉ ይሆናል።

አንድ ሙስሊም ኢማን እና አላህ ፍራቻ ምልክት እየታየበት እውነተኛ የወንድማማችነት ስሜትና የልብ የሆነ ወዳጅነት የማይንፀባረቅበት ከሆነ ያ ኢማኑ በርግጥም የተሟላ ነው ማለት አይቻልም። የአላህ ፍራቻውም ቢሆን የይስሙላ ነው ማለት ይቻላል።

የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ “አንዳችሁ አላመናችሁም ለራሣችሁ የምትወዱትን ነገር ለወንድማችሁ እስካልወደዳችሁ ድረስ።”

“ፍራቻውም የይስሙላ ነው።” ስንል አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ በቁርዓኑ ውስጥ የተናገረውን በማስረጃነት በመጥቀስ ነው።

وَتَعَاوَنُوا عَلَى الْبِرِّ وَالتَّقْوَىٰ ۖ وَلَا تَعَاوَنُوا عَلَى الْإِثْمِ وَالْعُدْوَانِ ۚ وَاتَّقُوا اللَّهَ ۖ إِنَّ اللَّهَ شَدِيدُ الْعِقَابِ

በበጎ ነገርና አላህን በመፍራትም ተረዳዱ። ግን በኃጢአትና ወሰንን በማለፍ አትረዳዱ። አላህንም ፍሩ። አላህ ቅጣተ ብርቱ ነውና።” (አል ማኢዳህ፤2)

መሰረቷን ኢማን ላይ አድርጋ የቆመችና በአላህ ፍራቻም የታነፀች ነፍስ በአላህ ፍራቻና በኢማን ከሚመሣሰሏት ጋር በምትገናኝበት ወቅት ውዴታዋን ለማሣየት የምትሰስተው የላትም። ይሉኝታም አይዛትም። በመጀመሪያ ግንኙነቷና እይታዋ ብቻ የወዳጅነት ስሜት ይንፀባረቅባታል። በመጀመሪያው የትውውቅ ቅፅበት ንፁህ የሆነ ስሜት ይፈጠርባታል። ሁለቱ ነፍሦች በአንድ ጊዜ እንደ አንድ ነፍስ ይሆናሉ። እንደ አንድ ልብም ይወዳጁና አንደኛው ሌላኛውን ይስባል። ወዲያውኑ የመዋደድ ስሜት በደምሥራቸው ውስጥ ይፈሣል፤ ወንድማማችነት በደማቸው ውስጥ ይሠራጫል፤ ደስታ በፊታቸው ላይ ይንቦገቦጋል። አንደኛው የሌላኛውን እጅ በእዝነት፣ በፍቅር እና በርህራሄ ስሜት በመያዝ ፅዱና ጥርት ባለው ዓለም ውስጥ ይንሳፈፋሉ። ጎን ለጎን በመሆንም የቃልኪዳን ጉዞ ይጀምራሉ። በጉዞአቸውም ወቅት የተንጣለለ በሆነው የመዋደድ ጥላ ሥር ያርፋሉ።

እያንዳንዳቸው ወደ ሰዎች ጆሮ ተጠግተው እንዲህ የሚል ዜማ የሚያንቆረቁሩ ይመስላሉ።

አንተም እኔ ነህ እኔም ሆንኩ አንተን 

ሁለት ነፍስ ይዘን አንድ ሰው ሆነን

መሠረቷ መጥፎ ሆኖ በመጥፎ ነገሮች ላይም ያደገች ነፍስ ግን እጅግ የተረጋጋች ከሆነችው የአማኝ ነፍስ ጋር በምትገናኝበት ወቅት ፈፅሞ አትጣጣምም። ቀድሞውኑ አይተዋወቁምና። በጉዞ መስመርም በመንፈስም እጅግ የተራራቁ ናቸው። የሚመርጡትም ሆነ የሚፈልጉት አይመሣሰልምና።

ከነቢያችን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም የመጡልን ሀዲሦችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ። ቡኻሪና ሙስሊም እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል –

“ሰዎች እንደ ወርቅና ብር ማዕድናት ሁሉ ይበላለጣሉ። በጃሂሊያ /ከኢስላም በፊት በነበረው ዘመን/ ምርጥ የነበሩት የጠለቀ እውቀት ያገኙ አንደሆን በኢስላም ውስጥም ምርጥ ናቸው። ነፍሦች የተጠናዱ ወታደሮች ናቸው። የተዋወቁት ይሣሣባሉ። የማይተዋወቁት ግን ይራራቃሉ።”

ይህ እንግዲህ በአላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ መንገድ ወንድማማችነት ምንነት ነው።

ወንድማማችነት አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ እሱን ብቻ አጥርተው በሚያመልኩ አማኞች ቀልብ ውስጥ የሚጥለው ምርጥ ችሮታ ነው።

ወንድማማችነት በኢማን የተዋቡና በአላህ ፍራቻ የሚታወቁ ነፍሦችን የሚያስተሣስር  ከውስጥ የሆነ ኢማናዊ ጥንካሬ ነው።

አንድ አማኝ የመውደድ፣ ሌላን የማስቀደም፣ የእዝነት፣ የመደጋገፍና የመሣሰሉትን ሌሎች በጎ አቋሞች እንዲይዝም የሚያደርግ ነው።

ወንድማማችነት ከኢማን ጋር በእጅጉ የተዛመደና ከአላህ ፍራቻ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው።

ወንድማማችነት ንፁህ ከሆኑና ከሚመሣሏት ነፍሦች ጋር የጠበቀ ጓደኝነት አላት። መጥፎና ተንኮለኞች ተቃራኒዎቿ ከሆኑት ጋር ደግሞ አትተዋቅም።

ስለሆነም በመጠኑም ቢሆን የወንድማማችነት ትርጉሙ እንዲህ መሆኑን ካወቅን ከአሁኑ ጀምሮ ወደ ወንድማማችነት መስመር በመምጣት በልባችን ልናረጋግጥ፣ በነፍሦቻችንም ውስጥ ልናሰርፅ ይገባል። ያኔ በመካከላችን እዝነት ይኖራል፤ በጠላቶቻችን ላይ ጥንካሬና ብርታት እናገኛለን።

በአላህ መንገድ ወንድማማችነት ያለው ደረጃ

በአላህ መንገድ ወንድማማችነት አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ ዘንድ ትልቅ ቦታ ያለው በመሆኑ ትልቅ ምንዳም ተዘጋጅቶለታል። ይህም ማንኛውም ሙስሊም ከዚህ ማዕድ እንዲቋደስ፣ ለትግበራው እንዲነሣሣና መስመሩንም አጥብቆ እንዲይዝ ያደርገዋል። ከፅዱ አማኞችና ከደጋግ አላህን ፈሪዎች እስኪሆን ድረስ።

ቀጥሎ በአላህ መንገድ ወንድማማችነት ያለውን ደረጃና ምንዳ እንመልከት

1. ፊታቸው ብርሃን ነው

አቡዳውድ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም  እንዲህ አሉ

“ከአላህ ባሮች መካከል ነቢያትም ሰማእታትም ያልሆኑ ሰዎች አሉ። በትንሣኤ ቀን ከአላህ ዘንድ ባላቸው ቦታ የተነሣ ነቢያትና ሰማእታት ይቀኑባቸዋል። ሰሃቦች “የአላህ መልእክተኛ ሆይ! እነማናቸው እነርሱ ይንገሩን?” አሏቸው። እርሣቸውም “ እነሱ ምንም ዝምድና ሣይኖራቸውና ያለምንም የገንዘብ ጥቅም በአላህ መንፈስ የተሣሰሩ ናቸው። ወላሂ ፊታቸው ኑር/ብርሃን/ ነው። እነርሱም በብርሃን ላይ ናቸው። ሰዎች በሚፈሩበት ጊዜ አይፈሩም። ሰዎች በሚያዝኑበት ጊዜም አያዝኑም።” አሉ።

2. ወንጀላቸው ይማርላቸዋል

ጦበራኒ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ

“አንድ ሙስሊም ሙስሊም ወንድሙን አግኝቶ በእጁ የያዘው እንደሆነ ነፋሻማ በሆነ ቀን ውስጥ ደረቅ ቅጠል ከዛፍ ላይ እንደሚረግፈው ሁሉ ወንጀላቸው ይረግፍላቸዋል። ወንጀላቸው የባህር ዐረፋ ያህል የበዛ ቢሆንም እንኳ ይማርላቸዋል።”

3. የትንሣኤ ቀን በአላህ ዐርሽ ጥላ ሥር ነው የሚሆኑት

ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል

“የተከበረውና ልቅናው ከፍ ያለ ጌታ አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ የትንሣኤ ቀን እንዲህ ይላል “ ለክብሬ የተዋደዱ የታሉ! ዛሬ የማንም ጥላ በሌለበት ቀን በጥላዬ ሥር አስጠልላቸዋለሁ።”

ቡኻሪና ሙስሊም እንደዘገቡት በሀዲሱ ላይ ከተጠቀሱት ሰባት ሰዎች መካከል “ለአላህ ብለው የተዋደዱ፣ በውዴታውም ላይ የተሰባሰቡና በዚያው ላይ የተለያዩ ሁለት ሰዎች ይገኙበታል።” ብለዋል።

4.በአላህ የውዴታ ር ናቸው

የአላህ ውዴታን ማግኘት ለሰው ልጅ የስኬቶች ሁሉ ጫፍ፤ ፍጥረታት ሁሉ የሚሮጡለት ዓላማ ነው። ኢማም ማሊክ ረሂመሁሏህ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል

“የተከበረውና ልቅናው ከፍ ያለው ጌታ አላህ እንዲህ አለ “ውዴታዬ በኔ መንገድ ለተዋደዱ፣ በኔ መንገድ ለተጠያየቁትና መከራ ላዩት ሁሉ ግድ ሆነ።” ብለዋል።

በሌላ ዘገባ ደግሞ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል

“አንድ ሰው በአንዲት መንደር የሚገኝ ወንድሙን ለመጠየቅ ወጣ። ወደዚያች መንደር በሚወስደው መንገድ ላይ አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ መልዓክ አስቀመጠና መልዓኩ

“ወዴት ነው የምትሄደው?” በማለት ጠየቀው።

ሰውየውም “በዚህች መንደር የሚኖር አንድ ወንድሜን ለመዘየር ነው።” አለው።

መልዓኩም “የዋለልህ ውለታ ኖሮ ልትመልስለት ነው ወይ?” በማለት ጠየቀው ።

ሰውየውም “አይደለም። ነገርግን እኔ ለአላህ ብዬ ስለምወደው ብቻ ነው።” አለ። መልዓኩም “እኔ ወዳንተ የተላክሁ የአላህ መልእክተኛ ነኝ። ለሱ ብለህ ስለወደድከው አላህ ወዶሃል።” በማለት አበሰረው።

5. በአላህ ጀነትና እንክብካቤ ውስጥ ናቸው

ቱርሚዚ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል –

“በሽተኛን የጠየቀ  አሊያም በአላህ መንገድ ወንድሙ የሆነን ሰው የዘየረን ተጣሪ ይጠራውና “ምንኛ አምረሃል! አካሄድህም አምሯል! ከጀነትም ቦታ ተዘጋጅቶልሃል።” ይለዋል።”

6. የኢማንን ጥፍጥና ያጣጥማሉ

ቡኻሪና ሙስሊም እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል

“ሦስት ነገሮች በውስጡ ያሉት ሰው የኢማንን ጥፍጥና አገኘ። አላህ እና መልእክተኛው ከሌሎች ነገሮች ሁሉ በበለጠ መልኩ በርሱ ዘንድ የተወደዱ መሆን፣ አንድን ሰው ለአላህ ብቻ ብሎ የወደደ እንደሆነ፣ ወደ እሳት መጣልን እንደሚጠላ ሁሉ አላህ ከክህደት ነፃ ካወጣው በኋላ ወደ ክህደት መመለስን መጥላት።” ብለዋል።

እንግዲህ ይህ ነው ኢስላማዊ ወንድማማችነት.. በዚህች ዓለምም ሆነ በመጭው ዓለም ትልቅ ደረጃ ያለው ነገር ነውና ሙስሊሞች ሁሉ ትክክለኛ የአላህ ባሮችና ወንድማማቾች ለመሆን ሊሮጡለት ይገባል።

በአላህ መንገድ ወንድማማቾች የሆኑ ሰዎች የሚኖራቸው ምንዳ እጅግ የሚያጓጓ ነው። ፊታቸው ብርሃን ነው፤ ወንጀላቸው እንደ ቅጠል ይረግፍላቸዋል፣ የማንም ጥላ በሌለበት ቀን አላህ ያስጠልላቸዋል፣ በመዋደዳቸው አላህ ይወዳቸዋል፣ ከጀነቱም ያስገባቸዋል፣ የኢማንን ጥፍጥናና የኢስላምን ጣእም ለማጣጣምም የታደሉ ናቸው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here