በአላህ መንገድ ወንድማማች የመሆን መስፈርቶች
በአላህ መንገድ ላይ ያለ ወንድማማችነት መስፈርቶች አሉት። እነኚህ መስፈርቶችና መሠረቶቹ ካልተሟሉ ወንድማማችነትም ሙሉ አይሆንም። በአላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ ዘንድም ተቀባይነት አይኖረውም። በመሆኑም ሙስሊሞች እነኚህን መስፈርቶች በጥንቃቄ ማወቅና መከተል ይገባናል። መስፈርቶቹን በተከታይ እንመልከት
1. ወንድማማችነት ለአላህ እና ለአላህ ብቻ መሆን አለበት
ወንድማማቾች ሲቀራረቡ ግንኙነታቸው ከዓለማዊ ጥቅምና ግላዊ ፋይዳ የፀዳ መሆን ይኖርበታል። እንዲያ ሲሆን ወንድማማችነት ውጤት ይኖረዋል። ፍሬውም ሆነ ትሩፋቱ ከራስ አልፎ ለማህበረሰቡ ይዳረሣል።
በክፍል አንድ ባየነውና ከነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ከተላለፈልን ሀዲስም የምንረዳው ይኸው ነው። መልዓኩ ወንድሙን ሊጠይቅ የሚሄደውን ሰውዬ “የት ነው የምትሄደው?” በማለት በጠየቀው ጊዜ ሰውየውም “በዚህች መንደር የሚገኝ አንድ ወንድሜን ልዘይር ነው።” በማለት መለሠለት።“ውለታ ውሎልህ ውለታውን ለመመለስ ነው ወይ?” ብሎ በጠየቀውም ጊዜ “አይደለም ለአላህ ብዬ ብቻ ስለምወደው ነው” አለው። በዚህን ጊዜ መልዓኩ “እኔ ከአላህ ወዳንተ የተላክሁ መልእክተኛ ነኝ ለሱ ብለህ እንደወደድከው አላህም ወዶሃል።” እንዳለው አይተናል። ይህ የሚያሣየን ካለ አንዳች ዓለማዊ ጥቅም መዛመድ፣ ጉድኝነት መፍጠር እና ወንድማማች መሆን ምንዳው ላቅ ያለ መሆኑን ነው። አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ እውቅና የሚሠጠውም የሱ ፊት ብቻ ተፈልጎበት የተመሠረተን ወንድማማችነት ነው።
2. ወንድማማችነት ከኢማን እና ከአላህ ፍራቻ ጋር በተያያዘ መልኩ መሆን ይኖርበታል
አንድ ሙስሊም አማኝ ጓደኛ ሲመርጥ የመጀመሪያ መስፈርቱ አማኞች ሊሆኑ ይገባል። ከአማኞችም መካከልም ምርጥና አላህን ፈሪዎች የሆኑትን መምረጥ ይኖርበታል። ጓደኞች አላህን ፈሪዎችና አማኞች መሆን እንዳለባቸው በቁርዓን ውስጥ ተጠቅሷል። አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ
“ምእመናን ወንድማማቾች ናቸው።” (አልሁጁራት፤ 10)
አላህን ፈሪ ያልሆኑ ሰዎችን ጓደኛ አድርጎ መያዝ ነገ መወቃቀስና መካካድን ያመጣል። አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ እንዲህይላል፦
“ወዳጆች በዚያ ቀን ከፊላቸው ለከፊሉ ጠላት ነው። አላህን ፈሪዎች ብቻ ሲቀሩ።” (አዝ ዙኽሩፍ፣ 67)
አቡ ዳውድ እና ቲርሚዚ አቢ ሰዒድ አልኹድሪን በመጥቀስ እንደዘገቡት ደግሞ የአላህ ነቢይ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም
“አማኝ እንጂ ጓደኛ አትያዝ። አላህን ፈሪ እንጂ ምግብህን አይብላ።” ብለዋል።
አቢ ሁረይራን በመጥቀስ አቡ ዳውድ እና ቲርሚዚ በዘገቡት ሌላ ሀዲስ ደግሞ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም “አንድ ሰው በወዳጁ ሃይማኖት ላይ ነው። ከማን ጋር እንደተወዳጃችሁ አስተውሉ።” ብለዋል።
እምነትና ኢማንን መሠረት አድርጎ የተመሠረተ ወንድማማችነት እጅግ አስተማማኝ ነው። ከተራራ በላይ ፅናት አለው። ከግዙፍ ህንፃ በላይም ጥልቀት አለው። የትኛውም ውሽንፍርና ውዥንብር አይበግረውም። የጊዜ ብዛትም አያላላውም።
3. ወንድማማችነት የእስልምናን መንገድ የተከተለ መሆን ይኖርበታል
ወንድማማቾች በአላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ ህግጋት ለመዳኘትና በሁሉም ጉዳያቸው ውስጥ ነቢያዊ መመሪያን ለመከተል ቃል መገባባት ይኖርባቸዋል።፤ በክፍል አንድ ባሣለፍነው ሀዲስም ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም “ሁለት ሰዎች ለአላህ ብለው የተዋደዱ፣ ለሱ ብለው የተሰባሰቡና፣ በሱም ላይ የተለያዩ ..” ማለታቸው ወንድሞች ሲሰባሰቡና ሲገናኙ የአላህን ህግጋት አጥብቀው ለመያዝና ለመፈፀም፤ በሸሪዓውም ለመመራት ቃል የተገባቡና ሲለያዩም በሸሪዓው ለመሥራት ቃል ተሠጣጥተው የተለያዩ ሲሆኑ ማለት ነው።
የዚህን ነቢያዊ ምልከታ ምንዳ ለመቋደስ ጉጉ የነበሩት ቀደምት ሰሃቦች በተገናኙ ቁጥር አንድ ልምድ ነበራቸው። ሁለት ሰሃቦች የተገናኙ እንደሆነ አንደኛው በሌላኛው ላይ ትልቅ መልእክት ያዘለችውን ሱረቱ “አል ዐስርን” ያነባል። አስከትለውም ሠላም ይባባላሉ።
የሱረቱ አልዐስር መልእክት መተዋወስና መመካከር ላይ ያነጣጥራል። ለዚህም ነው እነሱም በኢማን፣ እውነትን በመያዝ፣ በትእግስትና በመልካም ሥራ ላይ አደራ የሚባባሉት። በዚህ መልኩ በተገናኙ ቁጥር በዲኑ መንገድ ላይ ቀጥ ብለው ለመጓዝ ከወሰኑት ጋር ለመሆን ቃል ይገባባሉ።
እጅግ ከፍተኛ የዲን ግንዛቤና ጥልቅ ማስተንተን የነበራቸው ታላቁ ዓሊም ኢማሙ አሽ-ሻፊዒይ በዚህች ምዕራፍ ዙሪያ ሲናገሩ “ከሱረቱ አል ዐስር ውጭ ከቁርዓን ሌላ ባይወርድ ኖሮ በበቃች ነበር።” ይላሉ።
እኛም ወንድማማችነትን ሰሃቦች በተረዱት መልኩ ተረድተን ቢሆን ኖሮ እያንዳንዱ ሙስሊም በባህሪው፣ ሥነ-ምግባሩና ከሌሎች ጋር ባለው የኑሮ ግንኙነቱ በምድር ላይ የሚንቀሳቀስ ቁርዓን በሆነ ነበር።. ለምን ቢባል የቁርዓንን መንገድና የኢስላምን መርሆ ተከትሏልና ነው። እስልምናም ትርጉሙ በውስጥ ማሰብ፣ በምላስ መመስከርና በሰውነት ክፍል ደግሞ መሥራትን ያጠቃልላል።
4. ወንድማማችነት ለአላህ ብሎ መመካከርን መሠረት ማድረግ አለበት
ሙስሊም ለሙስሊም ወንድሙ መስታወት ነው። መልካም ነገር ያየበት እንደሆነ ያበረታታዋል፤ እንዲገፋበትም ይመክረዋል። መጥፎ ነገር አሊያም የሆነ እንከንና ጉድለት ያየበት እንደሆነ ደግሞ በሚስጢርና በተለሣለሰ አንደበት ያስታውሰዋል። ወደ ትክክለኛው ጎዳና እንዲመለስና የእውነትን መንገድ እንዲይዝም ይመክረዋል። ይህ አካሄድ እያንዳንዱ ሙስሊም በበላጭና መልካም ነገሮች ለመዋብና ከተራና ርካሽ ነገሮች ለመራቅ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ትልቅ መተጋገዝ ነው። የወንድማማችነት መሠረቱ እስልምናን እና አስተምህሮውን መሠረት ያደረገ በሆነ መልኩ መሆኑንም ማሣያ ነው።
ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ከሰሃቦቻቸው ጋር ቃኪዳን የተጋቡትም በዚሁ ምርጥ በሆነ የመተዋወስና የመመካከር ሥርዓት ላይ ነበር። ይህንን ያደረጉትም ሰሃቦቻቸው በደረሱበትና በተጓዙበት ቦታ ሁሉ በማህበረሰባቸው ውስጥ ወደ እውነት ተጣሪና የቅን መንገድ አመላካቾች ሆነው እንዲወጡ ነው።
ቡኻሪና ሙስሊም ከጀሪር ኢብኑ ዐብዱላህ እንደዘገቡት እንዲህ አለ፦
“ሰላትን በትክክልና አዘውትሬ በመስገድ፣ ዘካን ለመስጠት እና ለያንዳንዱ ሙስሊም መልካም መካሪ ለመሆን ከአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ጋር ቃል ተጋብቻለሁ።”
ከዚህም ባለፈ መልኩ ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እያንዳንዱ ሙስሊም አማኝ ለአላህ፣ ለቁርዓኑ፣ ለመልእክተኛው፣ ለሙስሊም መሪዎችና ለሁሉም ማህበረሰብ መካሪና አስተዋሽ ይሆን ዘንድ መመሪያ አስተላልፈዋል።
ሙስሊም እንደዘገቡት የአላህ መልክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም “ዲን ምክር ነው።” አሉ። ሰሃቦችም “ለማን?” በማለት ጠየቋቸው። እርሣቸውም “ለአላህ፣ ለቁርዓኑ፣ ለመልእክተኛው፣ ለሙስሊም መሪዎች እና ለሁሉም።” በማለት መለሱላቸው።
አንድ ወንድም የሙስሊም ወንድሙን ምክር የማይሠማ ከሆነስ?
አንድ ወንድም በሚሰጠው ምክርም ሆነ ማስታወስ አልሻሻል ብሎ በመጥፎ ሥራውና ወንጀሉ የገፋበት እንደሆነ ያ ወንድም ወደ ትክክለኛው መስመር እስኪመለስ ድረስ ማኩረፍና መራቅ ይበቃል። ሆኖም ግን ሆነ ብሎ እውነትን ባለመቀበሉ ሂደት ከቀጠለበት ግን እስከመጨረሻው ድረስ መራቅና ግንኙነቱን ማቋረጥ ይቻላል። ለአላህ ብሎ አንድን ሰው መራቅና ማኩረፍ ጠንካራ የሆነ የኢማን ገመድ ነው።
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የወረዱ ሀዲሦችን እንመልከት
ጦበራኒ ኢብኑ ዐባሰን በመጥቀስ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም “የኢማን አስተማማኙና ጠንካራው ገመድ ለአላህ ብሎ መወዳጀት፣ ለአላህ ብሎ ጠላት መሆን፣ ለአላህ ብሎ መዋደድ እና ለአላህ ብሎ ጥላቻን ማሣየት ነው።” ብለዋል።
ኢማም ቡኻሪም “አልታዘዝ ያለን ሰው ማኩረፍ” በሚለው የኪታባቸው ምዕራፍ ሥር እንዳወሱት ከዕብ ኢብኑ ማሊክአላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ከተቡክ ዘመቻ በቀረ ጊዜ እንዲህ ማለቱን ዘግበዋል “ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሰዎች ሁሉ ለሃምሣ ቀናት ያህል እኛን እንዳያናግሩ ከልክለዋል።” በዚህም የተነሣ የተኮረፉት ሦስት ሰዎች ምድር ከነስፋቷ ጠበበቻቸው። ነፍሣቸውም ጭንቅ አላት። አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ ተውበታቸው ተቀባይነት ማግኘቱን የቁርዓን አንቀፅ አውርዶ ማእቀቡ እስከተነሣላቸው ጊዜ ድረስ ለሰላምታም ሆነ ለሌላ ወሬ አንድም ሰው አያናግራቸውም ነበር።
ከዚህም ሌላ ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሚስቶቻቸው የአላህን መመሪያ በመጣሣቸው ምክኒያት ለማስፈራራትና ሥርዓት ለማስያዝ ለአንድ ወር ያህል አኩርፈዋቸው እንደነበር ተረጋግጧል።
ኢብኑ ሙገፈል ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ጠጠር ማስፈንጠር የከለከሉ መሆኑን ለአንድ ዘመዳቸው ቢነግሩትም ሰውየው ደጋግሞ በማስፈንጠሩ “የማትሠማኝ ከሆነ እስከመጨረሻው አላናግርህም” እንዳሉት ቡኻሪና ሙስሊም አቡሁረይራን በመጥቀስ ዘግበዋል።
ለአላህ ብሎ ማኩረፍ ዋና ዓላማው ማኩረፍን እንደ ጊዜያዊ ማዕቀብ በመጠቀም መልካም ውጤት ለማግኘት ነው። በዚህም ምክኒያት ነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሚስቶቻቸውን ወር ሙሉ አኩርፈዋል። ሰሃቦችም በነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ትእዛዝ ከተቡክ ዘመቻ የቀሩትን እነ ከዕብ ኢብኑ ማሊክን ለሃምሣ ቀናት አኩርፈዋል።
ይህ ሁሉ የሚሆነው የሚኮረፉ ሰዎች በሸሪዓ ያመኑ ሙስሊሞች ሆነው ነገር ግን ከአላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ ትእዛዝ ያፈነገጡ እንደሆነ ነው። የአላህን መኖር የካደንና ክህደቱንም ግልፅ ያደረገውን አሊያም ከእምነቱ የተመለሰን ሰው ግን በማኩረፍ ብቻ ሣይወሰኑ ከሱ መላቀቅ እና መራቅ የተሻለ ነው የሚሆነው። እሱን ማኩረፍና አለማናገር የኢማን ትንሹ ክፍል ነው። አላህን የካደ ሰው አሊያም ከእስልምና የተመለሰው እጀግ በጣም የቅርብ ሰው ልጅ፣ አባት አሊያም ሌላ ቢሆንም እንኳ ማኩረፍና ማግለል ግድ ነው።
አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ ይላል፦
“በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑትን ሕዝቦች አላህንና መልክተኛውን የሚከራከሩትን ሰዎች፤ አባቶቻቸው፣ ወይምልጆቻቸው፣ ወይም ወንድሞቻቸው፣ ወይም ዘመዶቻቸው ቢኾኑም እንኳ የሚወዳጁ ኾነው አታገኛቸውም። እነዚያ በልቦቻቸው ውስጥ እምነትን ጽፏል። ከእርሱም በኾነ መንፈስ ደግፏቸዋል። ከሥሮቻቸውም ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ ያገባቸዋል። አላህ ከእነርሱ ወዷል። ከእርሱም ወደዋል። እነዚያ የአላህ ሕዝቦች ናቸው። ንቁ! የአላህ ሕዝቦቸ እነርሱ ምኞታቸውን የሚያገኙ ናቸው።” (ሙጃደላህ፤22)
በሌላ የቁርዓን አንቀፅም
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አባቶቻችሁና ወንድሞቻችሁ ክህደትን ከእምነት አብልጠው ቢወዱ ወዳጆች አድርጋችሁ አትያዙዋቸው። ከእናንተም ውስጥ ወዳጅ የሚያደርጋቸው እነዚያ እነሱ በዳዮች ናቸው፤” (ተውባህ፤23)
በዚሁ ምእራፍ ላይም እንዲህ ብሏል።
“የኢብራሂምም ለአባቱ ምሕረትን መለመን ለእርሱ ገብቶለት ለነበረችው ቃል (ለመሙላት) እንጂ ለሌላ አልነበረም። እርሱም የአላህ ጠላት መኾኑ ለእርሱ በተገለጸለት ጊዜ ከርሱ ራቀ፤ (ተወው)። ኢብራሂም በእርግጥ በጣም ሩኅሩኅ ታጋሽ ነውና።” (ተውባህ፤ 114)
ከነኚህ አንቀፆች የምንረዳው የቅርብ የሥጋ ዘመዶቻችን በክህደት ላይ የሙጥኝ የሚሉ ከሆነ እነሱን ማኩረፍና ማግለል ግድ መሆኑን ነው። ይህንንም እስልምና አስተምሮታል፤ አዞበታልም። እስልምና የኢስላማዊ ወንድማማችነትን ትስስር ከየትኛውም ትስስር በላይ የበላይ አድርጎ ነው የሚመለከተው። በአላህ እምነት መያያዝ ከየትኛውም መያያዝ በላይ ነው።
ምንጊዜም የማይቀየረው ዘመንና ሁኔታ የማይሽረው የኢስላም መርሆ
“ምእመናን ወንድማማቾች ናቸው።” የሚለው ነው።
መቼም የማይለወጠው መፈክሩ “አላህ ዘንድ በላጫችሁ አላህን ፈሪያችሁ ነው።” የሚለው ነው። (አል ሁጁራት፤ 13)
5. ወንድማማቾች በደስታም ይሁን በመከራ ጊዜ መረዳዳት አለባቸው
ይህም የሚሆነው አንድ ወንድም በወንድሙ መደሠት የተደሰተ፤ ሲያዝን ደግሞ አብሮት ያዘነ እንደሆነ ነው። እስልምና በደስታም ይሁን በመከራ ጊዜ በሙስሊሞች መካከል መረዳዳትን ግዴታ ያደረገ ሲሆን ከወንድማማቾች አንፃር ሲሆን ደግሞ ነገሩ ከዚህ ከፍ ይላል። ለምን ቢባል በአላህ መንገድ ወንድማማቾች የሆኑ ሰዎች በንግግርም ይሁን በተግባር የእስልምናን መንገድ ሊይዙ ህግጋቱንም ተግባር ላይ ሊያውሉ ቃል የተገባቡ ናቸውና ነው። ስለሆነም አንዳቸውም ሃይማኖታቸው ከነርሱ ከሚፈልገው ውጭ የስንዝር ያህል መንሸራተት የለባቸውም። በድርጊታቸውም ሆነ በባህሪያቸው ከአላህ መንገድ ቅንጣት ታህል ማፈንገጥ አይኖርባቸውም።
በቁርዓንና ሀዲስ የመጡ ትእዛዞችም ይህንኑ ያመለክታሉ። አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ
“በመልካም ነገርና በአላህ ፍራቻ ላይ ተረዳዱ።” (አል ማኢዳህ፤ 2)
ታላቁ ነቢይም ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በሚከተሉት ሀዲሦቸው እንዲህ በማለት ያስተምራሉ፣-
“አንዳችሁም አላመናችሁም ለራሣችሁ የምትወዱትን ነገር ለወንድማችሁ እስካልወደዳችሁ ድረስ።”
“ትርፍ መጓጓዣ እንሠሳ ያለው ሰው ለሌለው ያካፍል። ትርፍ ስንቅ ያለው ሰው የሌለውን ያስታውስ።”
“ሙስሊም የሙስሊም ወንድም ነው፤ አሣልፎ አይሠጠውም፤ የወንድሙን ሃጃ የፈፀመለትን አላህ ሃጃውን ይፈፅምለታል፤ አንድን ሙስሊም ከጭንቀት የገላገለን አላህ በዚያ ምክኒያት ከትንሣኤ ቀን ጭንቀቶች ከአንዷ ይገላግለዋል፤ የሙስሊምን ገመና የሸፈነን ሰው አላህ ትንሣኤ ቀን ገመናውን ይሸፍንለታል።”
“ከውዴታ፣ ከአዘኔታ እና ከመረዳዳት አንፃር የሙስሊሞች ምሳሌ እንደ አንድ ሰውነት ነው። አንድ የሰውነት ክፍል የታመመ እንደሆነ የተቀረውም የሰውነት ክፍል እንቅልፍ በማጣት እና በትኩሣት ይከተለዋል።”
በዚህ የነቢዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ንግግር ውስጥ በመጀመሪ ደረጃ ላይ ሊገቡ የሚችሉት በአላህ መንገድ ወንድማማቾች የሆኑት ናቸው። ኢስላማዊውን ህግጋት ወደ ተግባር በመለወጥና የእስልምናን መመሪያዎችን አጥብቆ በመያዝ ረገድ ከሌሎች የተሻሉ ናቸውና። በአጭሩ ኢስላማዊ ወንድማማችነት ማለት ይህ ነው።
6. ያለ ዓለማዊ አንዳች ጥቅም ለአላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ ብቻ ታስቦ መሆን አለበት።
ከኢማን እና ከአላህ ፍራቻ ጋር የተቆራኘ ነው።
በአላህ መንገድ ላይ መፅናትን ግድ ይላል።
ለአላህ ብሎ መመካከርና መተዋወስ ነው።
በመከራም ይሁን በደስታ ጊዜ መረዳዳት ነው።
ኡኹዋህ/ወንድማማችነት/ ይህን ባህሪ የተላበሠ እንደሆነ፤ መስፈርቱም በተገቢው መልኩ ከተፈፀመ የትኛውም የሌት ይሁን የቀን ክስተት ጥንካሬውን አይሸረሽረውም። እንደ ፍጥረተ ዓለሙ ሁሉ ዘወትር ይኖራል። እንደ ተራራ የፀና ይሆናል። እንደ ፀሃይ ይበራል። እንደ ቀንና ለሊትም እየታደሠ ይኖራል።