ወንድማማችነትን የበለጠ የሚያጠናክሩ አስራ ሁለት ዘዴዎች

0
6762

1ኛ ፍቅርህን ግለፅለት

በአላህ መንገድ ላይ የተገናኙ ወንድማማቾች በመሃከላቸው የቱንም ያህል ጥብቅ ትስስር ቢኖራቸው፤ ይህንን እውነተኛ የፍቅር ስሜት በአንደበት መግለፅ ይጠበቅባቸዋል። በዚህም ይህ ረቂቅና አዎንታዊ የሆነ ስሜት በወንድማማቾቹ ልብ ውስጥ ላፍታ እንኳ ሊደበዝዝ የማይችል ውዴታን ፈጥሮ ያልፋል። ከዚህም ባሻገር ፍቅራቸው ተጠብቆ እንዲቆይ መልካም ዕድልን ይፈጥራል።

አቡ ዳውድና ትርሚዚይ በዘገቡት ሀዲስ የአላህ መልዕክተኛ ሰላላሁ ዓለይሂ ወሰለም “አንዳችሁ ለሚወደው ወንድሙ እወድሃለሁ በማለት ፍቅሩን ይግለፅለት”። ሲሉ ያስተምራሉ። ለምንወዳቸው ወንድሞቻችን ሁሉ “ለአላህ ብዬ እወድሃለሁ” በማለት ለርሱ ያለንን ጥልቅ ፍቅር በአንደበት መግለፅ የእርስ በርስ ግንኙነታችንን የበለጠ ከሚያጠናክሩ ስልቶች ቀዳሚው ነው።                    

2ኛ በዱዓህ አትርሳው

አሁንም በአላህ መንገድ ላይ የተገናኙ ወንድማማቾች በተለያዩ ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች አብረው የማይቆዩባቸው ከስተቶች ከተፈጠሩ በመሀከላቸው ተመስርቶ የነበረው ወንድማማችነትና ውዴታ ሊደበዝዝ ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ፍቅራቸው ተጠብቆ እንዲቆይና የመንፈስ ትስስራቸው የበለጠ እንዲፋፋ በአካል ለተራራቁ ወንድማማቾች የአላህ መልዕክተኛ ሰላላሁ ዓለይሂ ወሰለም በተግባር ያስተማሩበት አጋጣሚ አለ… በአንድ ወቅት ሁለተኛው ኸሊፋ ዑመር አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና መልዕክተኛው ዘንድ በመምጣት ዑምራ እሄድ ዘንድ ፍቀዱልኝ በማለት መልዕክተኛውንሰላላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሲያስፈቅዷቸው የረሱል ሰላላሁ ዓለይሂ ወሰለም ምላሽ የነበረው “ዑመር ሆይ በዱዓ አትርሳን” የሚል ነበር። ከዚህ ሃዲስ እንደምንገነዘበው በወንድማማቾች መሃል የተፈጠረውን ውዴታ ለማዝለቅ በአካል በተራራቁ ወቅት በዱዓ መተዋወስን ሌላኛው ዘዴ ሆኖ እናገኘዋለን።

3ኛ በፈገግታ ተቀበለው

አቡዘር ባስተላለፉትና ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ የአላህ መልዕክተኛ ሰላላሁ ዓለይሂ ወሰለም ወንድምን በብሩህ ገፅታ መቀበልን ከመልካም ስራዎች ጋር አውስተውታል። ይህን መሰሉ አቀባበል በሁለት ሰዎች መሀከል የተመሰረተውን ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ከማሻገሩ በላይ ፍቅራቸው ተጠብቆ እንዲቆይም ያግዛል። አስታውስ ወንድምህን በፈገግታ ለመቀበል የምታወጣው ወጪም ሆነ ሌላ ትርፍ ነገር የለም። ይህን በማድረግህ ግን ምንዳ ከማግኘትህ ባሻገር ከወንድምህ ጋር የመሰረትከው ወንድማማችነትም በቀላሉ የማይላላ ትስስር ይኖረዋል።

4ኛ ስትጨብጠው ፈጥነህ አትልቀቀው 

ወንድምህን ስታገኘውና ሰላምታ ስትለዋወጡ ወዳጅነታችሁ ጥብቅና ግንኙነታችሁ የጠነከረ መሆኑን ከምትገልፅባቸው መንገዶች አንዱ ጠንከር ባለ ስሜት ተሞልተህ መጨበጥህ ነው። የአላህ መልዕክተኛ ሰላላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሁለት ሙስሊሞች ተጨባብጠው በሚቆዩባቸው ቅፅበቶች ውስጥ መዳፎቻቸው እስኪለያዩ ድረስ የሰሩት ኃጢያት እንደሚታበስ በሃዲሳቸው ያወሱ ሲሆን ከዚሁ ጎን ለጎን የወንድምህን መዳፍ ጠንከር አድርገህ መያዝህ ፍቅራችሁ በቀላሉ የማይላላና ወዳጅነታችሁም እንደጠነከረ የሚዘልቅ መሆኑን ያመላክታል። የአላህ መልክተኛ ሰላላሁ ዓለይሂ ወሰለም ከአንድ ሰው ጋር ከተጨባበጡ የሰውዬው መዳፍ እስኪለቃቸው ድረስ ቀድመው አይለቁም ነበር።

5ኛ በሚወደው ስያሜ ጥራው

ከወንድምህ ጋር ያላችሁ የጠነከረ ወዳጅነት እንዳበበ ከሚዘልቅባቸው ዘዴዎች ሌላኛው እርሱን የምትጠራበት መንገድ ነው። በሚወደው ስም ስትጠራው የሚሰማውን ጥልቅ የፍቅር ስሜት ለመለካት በቀላሉ አንድ ሰው በማይወደው ቅፅል ስም ሲጠራ የሚሰማውን አሉታዊ ስሜት መረዳት በቂ ነው። በመሆኑም ወንድምህን ስትጠራው በቅፅል ስሙ አሊያም በማቆላመጥ ይሁን። በርግጥ የቁልምጫ ስም አሰጣጦች በየአካባቢው የተለያዩ መሆናቸውን ማስታወስ ይጠቅማል።ለምሳሌ አረቦች ከልጆቻቸው ስም ጋር ተቆራኝተው ሲጠሩ ደስ ይሰኛሉ “አዩብ የሚሰኝ ልጅ ያለውን አባት አቡ አዩብ ብሎ እንደመጥራት…”በርግጥ ይህን ባህል ብዙዎቹ ሙስሊሞች ሲፈፅሙት ይስተዋላል።

6ኛ በተደጋጋሚ ጎብኘው

የወንድምህ ጉዳዮች ሁሉ ያንተ ጉዳዮች እንዲሆኑ ከሚረዱ ስልቶች አንዱ ስለ እርሱ በቅርበት ማወቅህ ነው። ይህን ለማሳካት ደግሞ ተደጋጋሚ የጉብኝት ፕሮግራም ሊኖርህ ይገባል። ማሊክ ባወሩት ሃዲስ የአላህ መልዕክተኛ ሰላላሁ ዓለይሂ ወሰለምአላህ “ውዴታዬ ስለኔ በተዋደዱ፤ በተቀማመጡና፤ በተጠያየቁ ባሮቼ ሁሉ ግዴታ ሆኗል” ብሏል ማለታቸው የተዘገበ ሲሆን ከታላላቆቹ ሶሃቦች አንዱ አብደላህ ኢብኑ መስዑድ እሳቸውን ጥየቃ ለመጡ ወዳጆቻቸው “…ለመሆኑ እርስ በርስ ትቀማመጣላችሁን?” ሲሉ ጠየቋቸው፤ እንግዶቹም “ከዚህ ነገር ተቋርጠን አናውቅም” ሲሉ መለሱላቸው፤ ኢብኑ መስዑድ አስከትለው “በአግባቡስ ትገናኛላችሁን?” ሲሉ ጠየቋቸው። እንግዶቹም “አዎ አቡ አብድረህማን አንዳችን ወንድሙን ሲያጣው እሱን ፍለጋ እስከ ኩፋ ጠረፍ ድረስ በእግሩ ሄዶ የሚፈልገውና የሚያገኘው ቢሆን እንጂ..”ሲሉ መለሱ። በእንግዶቹ ድርጊት የተደሰቱት ኢብኑ መስዑድ “ይህን ከተገበራችሁስ በርግጥም በመልካም ሁኔታ ላይ ነው ያላችሁት” ሲሉ መለሱላቸው። ተደጋጋሚ ጉብኝቶች ወዳጅነትን ለማጠንከርና ፍቅርን ለማዝለቅ የማይተካ ሚና እንዳላቸው ይታወቃል።

7ኛ የመልካም ምኞት መግለጫዎችህን አብዛ

ብዙ ጊዜ ደስታችንን ለሚካፈሉ ሰዎች ልባችን ውስጥ የተለየ ቦታ እንሰጣቸዋለን። ጋብቻ ስንመሰርት፤ ከትምህርት ቤት ስንመረቅ፤እንዲሁም ልጅ ስናገኝና በሌሎች ደስታችንን በሚያበዙልን ሁኔታዎች ስንከበብ የነዚህ ወዳጆቻችን የደስታ መግለጫ መልዕክቶች በተለየ ሁኔታ ይደርሰናል። ወንድምህን ያስደሰተው ጉዳይ አንተንም እንዳስደሰተህ መግለፅ በመልዕክተኛው ሰላላሁ ዓለይሂ ወሰለም አንደበት እንዲህ ተገልጿል፤ “ወንድሙ በተደሰተበት ጉዳይ መደሰቱን ለማሳወቅ ወንድሙን ያገኘ ሰው በቂያማ ዕለት አላህ እሱንም ያስደስተዋል” ከሃዲሱ መገንዘብ እንደሚቻለው ወንድማችንን ደስ ያሰኘው ጉዳይ የኛም የደስታ ምንጭ መሆኑን በመግለፃችን ብቻ የሁለት ዓለም ትሩፋት እናገኛለን።

8ኛ የሀዘኑ ተካፋይ ሁን  

ሙስሊም ወንድሙን በደስታው ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሃዘኑ በበረታም ሰዓት ከጎኑ አያጣውም። በደረሰበት መሪር ሀዘን ልቡ እንዳይሰበር ጊዜ ሰጥቶ ያፅናናዋል። የብርታቱ ምንጭም ለመሆን በተቻለው አቅም ሁሉ ጥረቱ አይቋረጥም። ለርሱ ያለው ፍቅር በተድላ ወቅት ፈክቶ በመከራው ቀናት የሚከስም እንዳልሆነ ከጎኑ ሳይርቅ ያሳየዋል። በዚህም የወንድማማችነት ፍቅር መሰረት የበለጠ ይፀናል።

9ኛ ጉዳዩን ለማስፈፀም ትጋ

ጦበራኒ በዘገቡት ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ ሰላላሁ ዓለይሂ ወሰለም አላህ አንድ ባሪያውን ከማገዝ [ከመርዳት] አይዘነበልም፤ ያ የአላህ ባሪያ ወንድሙን እስከረዳና እስካገዘ ድረስ።” ሲሉ ይናገራሉ። ይህ ሀዲስ ሙስሊሞች ልብ ለልብ ከመተሳሰር ባለፈ በጉዳዮቻቸው ሁሉ እንዲተጋገዙ የማነሳሳት ኃይል አለው። በማናቸውም ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኝ ሙስሊም ሊወጣው የማይችል ጉዳይ ሲገጥመው ሸክሙን የሚያቀሉለት ወንድሞች በዙሪያው እንዳሉ ስለሚያምን “ከንግዲህ አበቃልኝ” ብሎ ተስፋ አይቆርጥም። ይልቁንም በፍጥነት አጠገቡ የሚደርሰውንና ጉዳዩን ዳር የሚያደርስለትን  ወንድሙን ይጠብቃል።

10ኛ ስጦታ ስጠው

የወንድምህን ጉዳዮች ሁሉ መከታተል ከቻልክ በህይወቱ ውስጥ የተፈጠሩና ለየት ያሉ አጋጣሚዎችን የማወቅ ዕድሉ ይኖርሃል። በመሆኑም ይህን መሰሉን ግሩም አጋጣሚ እንዲሁ አታሳልፈው። በተፈጠረው ሁኔታ የተሰማህን ጥልቅ ስሜት በስጦታ አጅበህ ግለፅለት። የአላህ መልእክተኛ ሰላላሁ ዓለይሂ ወሰለምስጦታ በሁለት ወንድማማቾች መሀከል ፍቅርን የሚያጠናክር ድልድይ መሆኑን ሲገልፁ “ስጦታን ተለዋወጡ ትዋደዳላችሁ።” ማለታቸው ተወስቷል። ከዚህ በተጨማሪ ስጦታ በአንተ ልብ ውስጥ ለወንድምህ የሰጠኸውን ልዩ ቦታ የምታሳይበትም  ግሩም አጋጣሚ ነው።

11ኛ ተነስተህ ተቀበለው

ወንድምህ አንተን ለመጎብኘት ሲመጣ አቀባበልህ እንዴት ያለ ነው? እርሱ ወደ አንተ ከመምጣቱ በፊት ከነበርክበት ሁኔታ አንዳች ለውጥ ሳታሳይ ከሆነ የምትቀበለው “ለምን መጣህ”? የሚል መልዕክት እያስተላለፍክለት እንደሆነ አትዘንጋ። በመሆኑም ፈፅሞ ልትሰስታቸው ከማይገቡ ነገሮች አንዱ በቻልከው መጠን ሁሉ የተሻለ ምቾት የሚያገኝበትን ስፍራ መርጠህ አረፍ እንዲል መጋበዝ ነው። አቀባበልህ ፍጹም የተለየ ይሁን። ወዳንተ እየገፋ ያመጣውን ወንድማዊ ፍቅር እንዳታደበዝዘው ጥንቃቄ አድርግ።

12ኛ በሌለበት ዱዓ አድርግለት 

አቡ ደርዳዕ ባስተላለፉት ሃዲስ የአላህ መልዕክተኛሰላላሁ ዓለይሂ ወሰለም አንድ ሙስሊም ከጎኑ ለራቀው ወንድሙ የሚያደርገው ዱዓ ተቀባይነት አለው፤ዱዓውንም ባሰማ ቁጥር አላህ የወከለው መላኢካ “አሚን” በማለት “ላንተም እንዲሁ ይሁን” ይለዋል ማለታቸዉን ሙስሊም ዘግበዉታል። የሃዲሱ አስተላላፊ ታላቁ ሶሃባ አቡ ደርዳዕ “እኔ ሱጁድ ላይ ሆኜ የሰባ ወንድሞቼን ስም እያነሳሁ ዱዓ አደርግ ነበር።” በማለት ተሞክሯቸውን ይገልፃሉ፤ አንተስ ወንድምህን በሌለበት በዱዓ አስታውሰኸው ታውቃለህን..? በአንድ ጠጠር ሁለት ወፍ እንዲሉ…ከጎንህ ለሌለው ወንድምህ ዱዓ ስታደርግ ያንተም ጉዳዮች እንደሚሳኩልህ አትርሳ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here