ከእውነተኛው . . . ጋር በፍቅር መውደቅ

0
11130

ከልብ የወደዱትን ነገር እንደመተው የሚከብድ ነገር ይኖር ይሆን? አይመስለኝም። ግን አንዳንዴ ብቸኛው አመራጫችን እሱ ይሆናል። አንድ አንድ ጊዜ ልናገኘው የማንችለውን ነገር እንመኛለን፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሚጎዳንን ነገር ልንወድ እነችላለን ከሁሉም በላይ ግን ፈጣሪያችን የማይወደውን ነገር ልናፈቅር እንችላለን። እነኚህን ነገሮች መተው ሲኖርብን ግን ማድረጉ  በጣም ይከብደናል። ልብ የወደደውን ነገር ለመተው ከሚያደርገው ፍልሚያ በላይ የሚገጥመው ከባድ ጦርነት አይኖርም።

ግን ይህ ሁሉ ጦርነት፣ ፍልሚያ እና ግርግር ሳይስፈልግ አንዴ ወደነው የነበረውን ነገር መተው የምንችልበት ቀላል መንገድ ቢኖርስ? ከተጣበቅንበት ነገር በቀላሉ መላቀቅ እንደምንችል የሚጠቁመን ነገር ቢመጣስ? አዎ በእርግጥ እንዲህ ያለ ተዓምር መስራት የሚቻለው ነገር አለ። እርሱም ከቀድሞው የበለጠ የምንወደውን ሌላ ነገር ማግኘት ነው።

የተሻለ ካላገኘህ የቀድሞውን አትተውም የሚባል አባባል አለ።

እኛ እንደሰው ልጅ ባዶነትን መቛቛም አንችልም። ሁሌም ባዶ ቦታ መሞላት አለበት ያውም በፍጥነት። የባዶነት እና የብቸኝነት ህመም ጠንካራ ስለሆነ ያንን ክፍተት መሙላት ተቀዳሚ ስራችን ይሆናል። የብቸኛነት ሰሜት እንዲሰማን ያደረገችን ትንሿ ደቂቃ ትልቅ ጉዳትን ትጎዳናለች። ስለዚህ ነው ሁሌም ከአንድ ግንኙነት ወደ ሌላ ግኙነት፤ ከስብራት ወደ ሌላ ስብራት በፍጥነት የምንሄደው።

ግን አንዴ ትክክል ያልሆነ ትስስር ከዳበረ ወዲህ እንዴት ይሁን እራሳችንን ነፃ ማውጣት የሚቻለን? ይህ በጣም ከባድ ነው። እነዚህ ነገሮች እየጎዱን፣ ህይወታችንን እያበላሹ እና ከፈጣሪያችን ጋር የሚኖረንን ግንኙነት እያጠለሹ  እንደሆነ እያወቅን ቢሆን እንኳ አንዴ በሱሳቸው ከወደቅን ወዲህ እነሱን ከህይወታችን ማስወጣትን አንወድም። ብንወድ እንዃ አንችልም። እነሱ ውስጣችን ያለውን ክፍተት በምንፈልገው መልኩ እንደሞሉልን ስለምናምን እነርሱ ላይ ክፉኛ ጥገኛ እንሆናለን።ከእነርሱ ውጭ መኖር ህልም ስለሚሆንብን ከእነርሱ ለመነጠል የምናደርገውን ፍልሚያ ጥግ ሳናደርስ ዳግም እንተዋለን።

ግን ለምን እንዲህ ይሆናል? እራሳችንን መውደዳችን እንዲሀ ድንበር አልፎ ፈጣሪ ለሚወደው ነገር ስንል እኛ የወደድነውን ነገር መስዋት ማድረግ እስኪያቅተን ድረስ ለምን ይህን ያህል ይከብደናል? በእርግጥ በእጃችን ካለው ነገር የተሻለን ነገር ማግኘት ስላልቻልን ነው?

አንድ ህፃን ልጅ የመኪና ቅርፅን ከያዘች መጫወቻ ጋር በፍቅር የወደቀ እለት ታሪኩ ሁሉ ይቀየራል። የዚህ ህፃን ልጅ የህይወት ህልምና ግብ ይህቺን መጫወቻ እጁ ማስገባት እና ማስገባት ብቻ ይሆናል። ይህ ህፃን ይህችን ነገር የግሉ ማድረግ የተሳነው እንደሆነስ? ያኔማ ሁሌም የምትሸጥበት ሱቅ መስኮት ጋር ሁኖ በጥሞና ይመለከታታል። ልቡ ገብተህ ውሰዳት አንሳት ቢለውም ፍርሀት ከውጭ መስታወቱ ጋር አስቁሞታል። ግን ድንገት የሆነ ቀን ሌላ አዲሰ ነገር ቢከሰትስ? እውነተኛዋን ፌራሪ እውነተኛዋን መኪና ከመስኮቱ ዝቅ ብላ ቢመለከታትስ? አሁንም ያቺ መጫወቻ ላይ አፍጦ የሚውል ይመስላችኋል ወይስ ወደ እውነተኛዋ መኪና እየበረረ ይሄዳል?

እኛ ፍቅር ፣ ገንዘብ፣ ማዕረግ እና ህይወትን እንፈልጋለን። ልክ እንደዛኛው ህፃን እኛም በእነዚህ ነገሮች ፍቅር ተውጠናል። እናማልክ መስኮቱ ጋር እንደ ቆመው ህፃን እኛም እነዚህን ነገሮች ማግኘት ሳይቻለን ስንቀር የማግኘት እና ያለማግኘት ግብ ግብ ውስጥ እንወድቃለን። እኛ የምንወደውን ለማግኘት ስንል ሀራም ላለመስራት ትግል ውሰጥ እንገኛለን። ሀራም የሆኑ አለባበሶችን፣ግንኙነቶችን እና ቢዝነሶችን ለመተው ግብ ግብ ውስጥ ነን። እኛ ማለት ከአሻንጉሊቶቻ ጋር በፍቅር ወድቀን መልሰን ከእነርሱ ፍቅር ለመውጣት የምንታገል ምስኪን ፍጡሮች ነን።

ይሀች ምድር እና በእርሷ ውስጥ ያሉት ነገሮች በሙሉ እንደዛች አሻንጉሊቶች ናቸው። ሆኖም እነሱን ለመተው የምንቸገረው ከእነርሱ የተሻለን ነገር ማግኘት ስላልቻልን ነው። እኛ ትክክለኛውን ሞዴል እና ደረጃ ማየት ተስኖናል። አላህም በቁርአን ውሰጥ ይህንን  ነግር ሲወቅስ “ቢያውቁ ኖሮ” እያለ ብዙ ቦታ ይናገራል። አዎ እኛ ትክክለኛውን ነገር ማወቅ እና ማየት ብንችል ኖሮ ለዚህች ዝቅተኛ እና አርቴፊሻል ህይወት ያለን ፍቅር እንዲህ ባላየለ ነበር። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ በ(ሱረቱል አዓላ፡ 16-17) እንዲህ ይላል፦

بَلْ تُؤْثِرُونَ الْحَيَاةَ الدُّنْيَا ﴿١٦﴾ وَالْآخِرَةُ خَيْرٌ وَأَبْقَىٰ 

“ይልቁንም ቅርቢቱን ሕይወት ትመርጣላችሁ፡፡ መጨረሻይቱ (ሕይወት) በላጭ ሁል ጊዜ ዘውታሪም ስትኾን።”

እውነተኛዋ ሞዴል (አኼራ) በጥራትም ቢሆን የተሻለች ስትሆን፤ በመጠን የበለጠች ናት። በዚህች ምድር ውስጥ የወደድነው ነገር ምንም እንኳ ቆንጆ እና ኃያል ቢሆንም የእነዚህ ሁለት ነገሮች ተጠቂ ከመሆን አያመልጥም። በመጠንም ቢሆን ትንሽ እና አላቂ ሲሆን በጥራትም መጉደሉ የማይቀር ነው።

ይህ ማለት ግን እዚህች ዓለም ውስጥ ያሉ ነገሮችን በሙሉ መውደድ እና የግላችን ማረግ የለብንም ማለት አይደለም። እኛ እነደ አማኝ የዚህችንም ዓለም ሆነ የዛኛውን ዓለም መልካም ነገር መመኘት ግዴታችን ነው። ይሁንና የእነዚህ ሁለት ነገሮች ልዩነት ልክ እንደ እነደ እውነተኛው እኛ እንደመጫመቻው መኪና መሆኑን መዘንጋት አያኖርብንም። ስለዚህ በመጫወቻው እየተዝናናን ልዩነቱን ማስተዋል ብልህነት ነው። ያኔ ከዐረበኛ ስርወ ቃሉ “ዳንያ” ማለትም ዝቅተኛ ከሚለው ቃል ከተመዘዘው ከዱንያ እና ከምንም በላይ ኃያል ከሆነው ከአኼራ መሃል ያለው ልዩነት ግልፅ ይሆንልናል።

የእነዚህን ነገሮች ልዩነት መገንዘብ ሀላል ነገርን ለማሳደድ እና ሀራም ከሆኑ ነገሮች በቀላሉ ለመሸሽ ይረዳል። ዘላቂ የሆኑ ነገሮችን ለይቶ የማየት ችሎታ ጊዜያዊ የሆኑን ነገሮች አስፈላጊ በሆነ ሰዓት በቀላሉ ለመተው ይጠቅመናል። ጊዜያዊ የሆነችውን ዱንያን ለአኼራ ጥቅም ስንል መተው ያኔ ቀላል ይሆንልናል። ልክ እንደ ብልሁ ህፃን እውነተኛውን መኪና ለማግኘት ሲባል መጫወቻውን ስንጠየቅ ለመስጠት አንንቀጠቀጥም።

ለምሳሌ የነቢያችንን ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ባልደረቦች  የህይወት ጉዞ መለስ ብለን ብንቃኝ አብዛኃኞቹ ሰሀቦች ባለፀጎች እንደነበሩ እናስተውላለን። ሆኖም ያቺ ሰዓት ስትመጣ እና አስፈላጊ ሁኖ ሲገኝ ግማሹን አልያም መሉውን ንብረታቸውን ለአላህ ሲሉ ሲሰጡ ታይተዋል።

ከአንድ ንጉስ የምንፈልገው ትልቅ ነገር ሲኖር እና ንጉሱን በአካል ማግኘት ሳንችል ስንቀር መጀመሪያ የምንወስደው እርምጃ የእርሱን የቅርብ አገልጋይ መተዋወቅ እና በእርሱ ለመወደድ እና ለመታመን መልፋት ይሆናል። ይሁንና ንጉሱን ማግኘት እንደምንችል ካወቅን እና በርሱ እርግጠኛ ከሆንን ያንን ሁሉ ጊዜ አገልጋዩ ላይ አናጠፋም። ከፊት ለፊታችን የኛን ትኩረት የሚሻ ንጉስ እያለ ትኩረታችንን በአገልጋዩ ላይ አናባክንም። ምክኒያቱም የዚህ አገልጋይ የስልጣን ምኝጭ ይሄው ንጉስ ነውና ዳግም ይሄው ስልጣን በእርሱ መነጠቅ ይችላል።

እውነተኛውን ነገር የማይት ችሎታችን የውዴታችንን እና የጉጉታችንን ደረጃ ይወስነዋል። ኢብን ተይሚያህ ይህንን ነገር በተመለከት እንዲህ ሲሉ ተናግረው ነበር።

“ልብህ ጌትነት ለማይገባው አካል ባርያ የሆነ እንደሆን ከፈጣሪ ፊትህን ማዞርህን እና ከእርሱ መንደር ብዙ መራቅህን ያመለክታል።ልብ አንድ ጊዜ አላህን መገዛት ያወቀች እና ያጣጣመች ጊዜ ከዚህ ሲሜት ውጭ ለእርሷ ውድ እና አስደሳች ነገር አይኖርም። ማንም ሰው ፈርቶ አልያም ሌላ የተሻለ የሚወደውን ነገር አጊኝቶ ቢሆን እንጂ ቀድሞ ያዘውን ነገር አይተውም። ልብም እንደዛው ሃራምን የፈራች ጊዜ ወይንም የተሻለውን እና እውነተኛውን ፍቅር ያጣጣመች ጊዜ ከውሸተኛ ትስስር ትላቀቃለች።”

የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንደነገሩን እኛ እንደ ኡማ ትልቁ ችግራችን ዱንያን ከልክ በላይ መውደዳችን እና ሞትን ደግሞ መፍራታችን ነውእኛ ከዱንያ ጋር በፍቅር ወድቀናል። እውነተኛውን እና ዘላቂውን ፍቅር ማየት እስኪሳነን ድረስ በማይጠቅም ፍቅር መንገላታታችን ይቀጥላል። ነገር ግን ነገ ከመልዕክተኛው እና ከፈጣሪያችን ጋር የምንኖርበት ቤት ጀነት ውስጥ እንደተዘጋጀልን እና እንደሚጠብቀን ማወቅ የቻልን እንደሆን ያኔ የዱንያን ፍቅር ከውስጣችን ንቅል አድርገን የማውጣት አቅም እናገኛለን። እናም ያኔ ስግደቴም፤ መስዋቴም፤ ህይወቴም ሆነ ሞቴ ለዓለማት ፈጣሪ ለሆነው ለአላህ ብቻ ነው የማለት ጉልበት እነገኛለን። ስለዚህ የወደዱትን ስለመተው እያወራን ከሆነ መልሱ ያለጥርጥር መልሶ ማፍቀር የሚለው ሆኖ እናገኘዋለን። ከእውነተኛው ነገር ጋር በፍቅር መውደቅ መቻል። እውነተኛውን ቪላ ቤት ያየን ጊዜ ከዕቃቃዋ ቤት ጋር ያለን ትስስር ይበጠሳል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here