ዒድ – ስርዓቶችና ደንቦች

0
3919

የዒድ አስፈላጊነት

ዒድ ማለት “ዓውድ” ከሚለው የዓረብኛ ቃል የተያዘ ሲሆን መመላለስ ማለት ነው። ዒድም በየአመቱ ስለሚመላለስ ይህን ስያሜ አግኝቷል። የዓረብኛ ቋንቋ ማንኛውንም የደስታ ቀን ዒድ (በዓል) ብሎ ይጠራል። በስድ ጥቅም ላይ ሲውል ግን ኢስላማዊ ትርጓሜው ሁለቱን የኢስላም በዓላት ብቻ ይጠቁማል።

የሙስሊሞች በዓላት ሁለቱ ዒዶች -ዒድ አልፊጥር እና ዒድ አልአድሃ- ናቸው። ከአነስ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው

قَدِمَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ الْمَدِينَةَ وَلَهُمْ يَوْمَانِ يَلْعَبُونَ فِيهِمَا فَقَالَ مَا هَذَانِ الْيَوْمَانِ قَالُوا كُنَّا نَلْعَبُ فِيهِمَا فِي الْجَاهِلِيَّةِ فَقَالَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ إِنَّ اللَّهَ قَدْ أَبْدَلَكُمْ بِهِمَا خَيْرًا مِنْهُمَا يَوْمَ الْأَضْحَى وَيَوْمَ الْفِطْر

“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) መዲና ሲገቡ የመዲና ሠዎች የሚደሰቱባቸው ሁለት በዓላት እንዳሏቸው አወቁ። እርሳቸውም እነዚህ ሁለቱ ቀናት ምንድናቸው በማለት ጠየቁ። ሰዎችም ከእስልምና በፊት በጃሂሊያ ጊዜ እንጫወትባቸው የነበሩ በዓላት ናቸው አሏቸው። የአላህ መልእክተኛም (ሰ.ዐ.ወ) ‘አላህ ከነርሱ የተሻሉ ሁለት ዒዶችን ሠጥቷችኋል። ዒዱልፊጥር እና ዒድ አልአድሃን።’ አሏቸው።” (አቡ ዳውድ ዘግበውታል)

ዒዱል-ፊጥር የሸዋል ወር የመጀመሪያው ቀን ላይ የሚከበር የሙስሊሞች የመጀመሪያው በዓል ነው። ከዚያም ወርሀ ዙልሒጅጃ ላይ ሁለተኛው ዒድ -ዒዱል-አድሓ- አለ። ዒዱል-ፊጥር ሙስሊሞች ከረመዳን ፆም በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያፈጥሩበት ወይም ፆማቸውን የሚገድፉበት ቀን ላይ የሚውል በዓል ነው። ለዚህ ነው ዒዱል-ፊጥር የሚባለው።

ዒድ ሰዎች ከህይወት ጭንቅና ሀሳብ እረፍት እንዲያደርጉ፣ በሙስሊሞች መሀል እዝነትንና ፍቅርን ለማስፈን፣ የአላህን ፀጋዎች ለማመስገን… የታለመ በዓል ነው።

የኢስላም ዒድ ከሌሎች የኃይማኖት በዓላት ይለያል። ኢስላም ውስጥ ዒድ ግዴታ ከሆኑ አምልኮዎች ጋር ተሳስሯል። የዒድ ደስታ ያን ቀን ከሚፈፀሙ አምልኮዎች ጋር ይተሳሰራል። ግዴታ የሆነባቸውን ፆም የፆሙ ሰዎች ፆማቸው ሲጠናቀቅ ሊደሰቱ ይገባል። ምክንያቱም ግዴታ የሆነባቸውን የአምልኮ ስርዓት ለማጠናቀቅ አላህ ገጥሟቸዋል። ሐጅ ያደረጉ ሠዎች ሐጃቸውን ሲያጠናቅቁ ሊደሰቱ ይገባል። ምክንያቱም ግዴታ የሆነባቸውን ሐጅ ፈፅመዋል። ስለዚህ ኢስላም ውስጥ -ዒድ- እንደ የዒባዳ (የአምለኮ) ምልክት ይታያል። ስለዚህ ከሌሎች በዓላት ይለያል።

ቁርአን በኩራትና በአናኒያ የተወጠረ ደስታን ከልክሏል። የአላህ ፍጡሮች ላይ የበላይነትን ለማሳየት የሚደረግ ደስታ መግለጫን አውግዟል። ስለቃሩን በተናገረ ጊዜ አላህ እንዲህ ብሏል፡-

إِذْ قَالَ لَهُ قَوْمُهُ لَا تَفْرَحْ إِنَّ اللَّهَ لَا يُحِبُّ الْفَرِحِينَ

“ወገኖቹ ለእርሱ አትኩራ፤ አላህ ኩራተኞችን አይወድምና ባሉት ጊዜ (አስታውስ)።” (አል-ቀሰስ 28፤ 76)

እንዲህ አይነቱን ደስታ አላህ አይወደውም። ምክንያቱም በሰውየውና በማህበረሰቡ መሀል ፍቅር እንዳይኖር ያደርጋል። ጥላቻን ያሰፍናል። በሌላ ቦታ ላይ ደግሞ አላህ በእዝነቱና በችሮታው እንድንደሰት አዞናል። ከአላህ እዝነት መገለጫዎችና ከችሮታዎቹ ማሳያዎች መሀል ለታላላቅ የአምልኮ ሥርዓት መገጠማችን እና እንድንታዘዘው መፍቀዱ ነው።

ዒድ ኢስላም ውስጥ ለደስታ ብቻ አልተደነገገም። የበጎ ስራ ፍላጎቶችን ለማጎልበትም ጭምር ተወጥኗል እንጂ። በጎ ስራ ከዒድ ውጭ የግል ልማድ ሊሆን ይችላል። በዒድ ጊዜ ግን የማህበረሰብ ጉዳይ ይሆናል።

أغنوهم عن السؤال في هذا اليوم

ነብዩ- (ሰ.ዐ.ወ) ስለ ዘካቱልፊጥር ሲናገሩ “በዚህ ቀን ከልመና ገላግሏቸው።” ማለታቸው በተለይ ይህን ፋይዳ ያስረዳል።

ኢስላም የኡድሒያን እርድ ሲደነግግ ድሆችንና ሚስኪኖችን ለመመገብ እንጂ የማረድ አቅም ያላቸውን ሀብታሞች ለማጥገብ አይደለም። ምክንያቱም ድሆች ለብዙ ጊዜያት ሥጋ ላያገኙ ይችላሉ። በዚህ ረገድ ዒዱ ለሀብታሞቹ ይዞት የሚመጣው አዲስ ነገር ግን አይኖርም።

ተከታይዋ አንቀፅ ይህን ነጥብ ይበልጥ ታብራራለች። ዒባዳ ጠቃሚ ስነምግባርና በጎ ተግባር ካፈራ ታላቅነቱን ትጠቁማለች። ሶላት፣ ፆም…እና ሌሎችም የአምልኮ ሥርዐቶች የሠዎች ባህሪና ተግባር ላይ ምንም አይነት ለውጥ ካልፈጠሩ ባዶ ቀፎ እንደሚሆኑ ታስተምራለች። አላህ እንዲህ ይላል፡-

لَّيْسَ الْبِرَّ أَن تُوَلُّوا وُجُوهَكُمْ قِبَلَ الْمَشْرِقِ وَالْمَغْرِبِ وَلَٰكِنَّ الْبِرَّ مَنْ آمَنَ بِاللَّهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ وَالْمَلَائِكَةِ وَالْكِتَابِ وَالنَّبِيِّينَ وَآتَى الْمَالَ عَلَىٰ حُبِّهِ ذَوِي الْقُرْبَىٰ وَالْيَتَامَىٰ وَالْمَسَاكِينَ وَابْنَ السَّبِيلِ وَالسَّائِلِينَ وَفِي الرِّقَابِ وَأَقَامَ الصَّلَاةَ وَآتَى الزَّكَاةَ وَالْمُوفُونَ بِعَهْدِهِمْ إِذَا عَاهَدُوا وَالصَّابِرِينَ فِي الْبَأْسَاءِ وَالضَّرَّاءِ وَحِينَ الْبَأْسِ أُولَٰئِكَ الَّذِينَ صَدَقُوا وَأُولَٰئِكَ هُمُ الْمُتَّقُونَ

“መልካም ሥራ ፊቶቻችሁን ወደ ምሥራቅና ምዕራብ አቅጣጫ ማዞር አይደለም። ግን መልካም ሥራ በአላህና በመጨረሻው ቀን፣ በመላእክትም፣ በመጻሕፍትም፣ በነቢያትም፣ ያመነ ሰው ገንዘብንም ከመውደዱ ጋር ለዝምድና ባለቤቶችና ለየቲሞች ለምስኪኖችም፣ ለመንገደኞችም፣ ለለማኞችም፣ ለጫንቃዎችም (ማስለቀቅ) የሰጠ ሰውና ሶላትንም ደንቡን ጠብቆ የሰገደ፣ ዘካንም የሰጠ፣ ቃል ኪዳንም በገቡ ጊዜ በኪዳናቸው የሞሉ (ሰዎች ሥራ) ነው። በችግር በበሽታና በጦር ጊዜም ታጋሾችን (እናወድሳለን)። እነዚህ እነዚያ እውነትን የያዙ ናቸው። እነዚያም ተጠንቃቂዎቹ እነርሱ ናቸው። (አል-በቀራ 2፤ 177)

ይህን በርጋታ እናጢነው። ዒድ ችግርተኞችን በሙሉ ያካተተ እዝነትን ለማሳየት ይጠቅማል። ማህበረሰብ በዚህ መተሳሰብና መተዛዘን እንጂ ህልውናው አይጠበቅም። ይህ ነው ጠቅላላው የኢስላም አስተምህሮ። ዒድ ላይም የታለመው ዋናው ግብ ይኸው ነው።

ኢስላም ውስጥ ዒዶች ታላቅ ጥበብና ዓላማ አላቸው። ዒድ ደስታን ለመግለፅ፣ የማህበረሰብ ትስስርን ለማጠናከር፣ በእዝነት ለመተሳሰብ እና እውነትን በመያዝ ላይ አደራ ለመባባልና ለመመካከር ምርጥ አጋጣሚ ነው። አሳሳቢና ጠቃሚ ቀን በመሆኑም ለዚህ የሚረዱ ዝርዝር ኢስላማዊ አዳቦችና አስተምህሮዎችን ከመለኮታዊ ምንጮች በብዛት እናገኛለን። ከነዚህ መሀል እጃችን ላይ ያሉትን ወደናንተ እንወርውር።

የዒድ ሥርዓቶችና ሱናዎች

1.ትጥበት

ለዒድ ሰላት ከመውጣታችን በፊት ገላን መታጠብ ሱና ነው። ሙወጣእ በተሠኘው መፅሀፍ ላይ እንደተዘገበው ታላቁ ሰሃባ ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር (ረ.ዐ) የዒድ አልፊጥር ቀን ወደ ሰላት ከመውጣታቸው በፊት ይታጠቡ ነበር።

ታላቁ ታቢዒይ ሰዒድ ኢብኑ ጁበይር እንዲህ ብለዋል፡-

سنة العيد ثلاث المشي والاغتسال والأكل قبل الخروج

“የዒድ ሱናዎች ሦስት ናቸው። እነሱም በእግር መሄድ፣ ትጥበት እና ለሰላት ከመውጣት በፊት መብላት ናቸው።” ሰዒድ ኢብኑ ጁበይር ይህን ንግግራቸውን ከአንዳንድ ሰሃቦች ወስደውት ይሆናል የሚል ግምት ዑለሞች ጠቁመዋል።

“በዒድ ቀን ትጥበት የተወደደ ስለመሆኑ ዑለማኦች ተስማምተውበታል።” ይሉናል ኢማም ነወዊ። ከዚህ ሌላም ሙስሊሞች ለሚሠበሰቡበት ማንኛውም ስብሰባ ገላን መታጠብ ተወዳጅ እንደሆነ ፉቀሀዎች ያምናሉ።

2.ወደ ሶላት ከመሄዳችን በፊት መመገብ

በዒድ አልፊጥር ቀን ወደ ሶላት ከመሄድ በፊት መመገብ ሱና ነው። ከአነስ ኢብኑ ማሊክ (ረ.ዐ.) እንደተዘገበው

كَانَ رَسُولُ اللَّهِ- صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ- لا يَغْدُو يَوْمَ الْفِطْرِ حَتَّى يَأْكُلَ تَمَرَاتٍ. وَيَأْكُلُهُنَّ وِتْرًا

“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የተወሠኑ ተምሮችን ሳይበሉ የዒድ አልፊጥር ቀን ወደ ሰላት መስገጃ ቦታ አይወጡም። ተምሩን ዊትር (ነጠላ) አድርገው ይበሉ ነበር።” ብለዋል። (ቡኻሪ ዘግበውታል)

ወደ ሰላት ከመውጣት በፊት መመገቡ ሱና የሆነው በዚያ ቀን ውስጥ መፆሙ በእጅጉ የተከለከለ መሆኑን ለማሣወቅ እንዲሁም ፆም የተጠናቀቀ መሆኑንና መብላት የተፈቀደ መሆኑን ለመግለፅ ነው ተብሎ ይታመናል።

“ይህ ፆምን ጨምረው በሚፆሙ ሰዎች ላይ መንገድ ለመዝጋትና ወደ አላህ ትእዛዛት ለመፍጠን ያለንን ፍላጎት ማሳያ ነው።” ይሉናል ኢማም ኢብኑ ሐጀር (ፈትሁል ባሪ፣ ቅጽ 2፣ ገጽ 446)

በእለቱ ተምር ያላገኘ ሰው በማንኛውም ሀላል ምግብ ማፍጠር ይችላል። በዒድ አልድሃ ግን ተቃራኒው ነው የሚደረገው። ከኡድሂያ እርድና ከሰላት በኋላ እንጂ ምግብ አይበላም።

3.የዒድ ቀን ተክቢራ

በዒድ ቀን ከሚደረጉ ትላልቅ ሱናዎች መካከል ተክቢራ አንዱ ነው። አላህ በእነዚህ ቀናት ተክቢራ እንድናበዛ ይመክረናል። እንዲህ ይላል፡-

وَلِتُكْمِلُوا الْعِدَّةَ وَلِتُكَبِّرُوا اللَّهَ عَلَىٰ مَا هَدَاكُمْ وَلَعَلَّكُمْ تَشْكُرُونَ
 

“ቁጥሮችንም ልትሞሉ አላህንም ቅኑን መንገድ ስለመራችሁ ታከብሩትና ታመሰግኑት ዘንድ (ይህን ደነገግንላችሁ)።” (አል-በቀራ 2፤ 185)

ከወሊድ ኢብኑ ሙስሊም እንደተዘገበው ኢማም አል-አውዛዒንና ማሊክ ኢብኑ አነስን በሁለቱ የዒድ ቀናት ድምፅን ከፍ አድርጎ ተክቢራ ስለማድረግ ጠየኳቸው። እነርሱም “አዎን ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር ኢማሙ ለሠላት እስኪወጣ ድረስ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ተክቢራ ያደርጉ ነበር።” አሉኝ።

ከአቢ ዐብዱረህማን አስ-ሱለሚ እንደተዘገበው “(ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር) በዒድ አልፊጥር ቀን ከዒድ አል-አድሃ ይበልጥ (በተክቢራው ላይ) ያጠብቁ ነበር።” ዳረልቁጥኒ እና ሌሎችም እንደዘገቡት “ኢብኑ ዑመር የዒድ አልፊጥር እና የዒድ አል-አድሃ ቀን ጠዋት ወደ መስገጃ ቦታቸው ደርሠው ኢማሙ ለሶላት እስኪወጣ ድረስ ተክቢራ ይሉ ነበር።”

ኢብኑ አቢ ሸይባህ ዙህሪይን ዋቢ በማድረግ እንደዘገቡት

كان الناس يكبرون في العيد حين يخرجون من منازلهم حتى يأتوا المصلى وحتى يخرج الإمام فإذا خرج الإمام سكتوا فإذا كبَّر كبروا

“በዒድ ቀን ሰዎች ከቤቶቻቸው ሲወጡ መስገጃ ቦታቸው ላይ እስኪደርሱና ኢማሙ እስኪወጣ ድረስ ተክቢራ ይሉ ነበር። ኢማሙ ለሶላት ብቅ ሲል ግን ዝም ይላሉ። እሱ ለሶላት ‘አላሁ አክበር!’ ሲል እነርሱም ‘አሏሁ አክበር!’ ይላሉ።”

ከቤት ጀምሮ ኢማሙ እስኪወጣበት ጊዜ ድረስ ተክቢራ ማድረጉ በሠለፎች ዘንድ እጅግ የታወቀ ተግባር ነው። ስለዚህ አጥብቀን ልንይዘው የሚገባ ተወዳጅ ነገር ነው።

የተክቢራ አደራረግ

ኢብኑ አቢ ሸይባህ እንደዘገቡት ዐብዱላህ ኢብኑ መስዑድ (ረ.ዐ.) እንደሚከተለው ተክቢራ ያደርጉ ነበር።

“አሏሁ አክበር! አሏሁ አክበር! አሏሁ አክበር! አሏሁ አክበር ወሊላሂል ሀምዱ!”

በሌላ ዘገባ ደግሞ

“አላሁ አክበር ከቢራ አላሁ እክበር ከቢራ አሏሁ አክበር ወአጀሉ አሏሁ አክበር ወሊላሂል ልሀምዱ” የሚል ተገኝቷል።

የእንኳን አደረሳችሁ መልእክቶች

ሰዎች የሚለዋወጧቸው የደስታ መልእክቶች ዒድ ላይ ተወዳጅ ከሆኑ ነገሮች መሀል ነው። ደስታን በማንኛውም ቋንቋ መግለፅ ይወደዳል። የቃላት ስብጥር ልዩነትም ችግር የለውም። ሶሐቦቹ ይጠቀሟቸው የነበሩትን የደስታ ቃላት ብንጠቀም ግን መልካም ነው።

ከጁበይር ኢብኑ ኑፈይር (ረ.ዐ) እንደተዘገበው የነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሰሃቦች የዒድ ቀን ሲገናኙ “ከኛም ከናንተም አላህ ይቀበል” ይባባሉ ነበር። እነዚህ የደስታ መልእክቶች ሰሃቦች ዘንድ የታወቁ ነበሩ። ኢማም አህመድን የመሳሰሉ የዒልም ባለቤቶችም የደስታ መግለጫ መልእክቶችን መለዋወጥ ይፈቀዳል ሲሉ ብይን ሰጥተዋል።

የደስታ መልእክቶች የመልካም ባህሪ መገለጫዎች ናቸው። በሙስሊሞች መካከልም ማህበረሰባዊ ግንኙነቶቻቸውን ለማጠናከርም ዓይነተኛ ሚና አላቸው። በዒድ ዕለት በደስታ መልእክት መቅደም ባንችል እንኳን መልእክቱን ያደረሰንን ሰው “እንኳን ደስ ያለህ!” በማለት አፀፋ መመለስ ይገባል። ኢማም አህመድ እንዲህ ይላሉ “እኔ ቀድሜ እንኳን አደረሰህ ካላልኩኝ የቀደመኝን ሠው የደስታ መግለጫ እመልሳለሁ።”

ለዒድ ቀን ማማርና መዋብ

ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር እንደዘገቡት ዑመር (ረ.ዐ) ገበያ ላይ ይሸጥ የነበረ ከኢስተብረቅ /ስስ ሀር/ የተሠራ ካባ ወደ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ወሰደና

عن عبد الله بن عُمَرَ- رضي الله عنه- قَالَ أَخَذَ عُمَرُ جُبَّةً مِنْ إِسْتَبْرَقٍ تُبَاعُ فِي السُّوقِ فَأَخَذَهَا فَأَتَى بِهَا رَسُولَ اللَّهِ- صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ- فَقَالَ: يَا رَسُولَ اللَّهِ، ابْتَعْ هَذِهِ تَجَمَّلْ بِهَا لِلْعِيدِ وَالْوُفُودِ فَقَالَ لَهُ رَسُولُ اللَّهِ- صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ- “إِنَّمَا هَذِهِ لِبَاسُ مَنْ لا خَلاقَ لَهُ

“የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ይህን ካባ ይግዙና ለዒድ ቀን ይዋቡበት፤ እንግዶችንም ይቀበሉበት አላቸው። የአላህ መልእክተኛም (ሰ.ዐ.ወ) ‘ይህ ልብስ (በአኼራ ላይ) እድል የሌለው ሰው ልብስ ነው!’ አሉት።” (ቡኻሪ ሀግበውታል)

ከዚህ ሀዲስ የምንረዳው ነገር ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ለዒድ ቀን እና ለእንግዳ መዋብ መልካም መሆኑን ተቀብለውታል። ልብሱ ግን ሐር በመሆኑ ሊገዙት አልፈቀዱም።

ከጃቢር (ረ.ዐ) እንደተዘገበው ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ)

كان للنبي- صلى الله عليه وسلم- جبة يلبسها للعيدين ويوم الجمعة

“ለዒድ እና ለጁሙዓ ቀን የሚለብሱት ካባ ነበራቸው።” (ኢብኑ ኹዘይማህ ዘግበውታል)

በይሃቂም እንደዘገቡት “ኢብኑ ዑመር (ረ.ዐ) በዒድ ቀን እጅግ ምርጥና ቆንጆ የተባለ ልብስ ይለብሱ ነበር።”

ስለሆነም አንድ ሰው በዒድ ቀን ምርጥና ቆንጆ ያለውን ልብሱን ሊለብስ ይገባል። ወደ ዒድ ሶላት የሚሄዱ ሴቶች ግን ሽቶ መቀባት አይፈቀድላቸውም።

የዒድን ኹጥባ ማዳመጥ

ኢብኑ ቁዳማ እንዲህ ይላሉ፡- “…ኢማሙ ባሠላመተ ጊዜ የጁሙዓን ኹጥባ የሚመስሉ ሁለት ኹጥባዎች ያደርጋል። ይህን የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሠርተውታል። ኹጥባው በአራት ነገሮች ከጁሙዓ ኹጥባ ይለያል…” በማለት ሦስቱን ከቆጠሩ በኋላ “አራተኛው እነኚህ ኹጥባዎች ሱና ናቸው። ስለዚህ ማዳመጥ አሊያም ኹጥባው ሲደረግ ዝም ማለት ግዴታ አይደለም።” ብለዋል።

ከዐብዱላህ ኢብኑ ሳኢብ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው

شهدت مع رسول الله- صلى الله عليه وسلم- العيد، فلما قضى الصلاة قال: إنا نخطب من أراد أن يجلس للخطبة فليجلس، ومن أحب أن يذهب فليذهب

“ከአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር የዒድ ቀን ላይ ተገናኝቻለሁ። ሰላት ሲጨርሱ ‘ኹጥባ እናደርጋለን መቀመጥ የሚፈልግ ይቀመጥ መሄድ የፈገለም ይሂድ’ አሉ።” (ነሳኢ፣ አቡ ዳዉድና ኢብኑ ማጃህ ዘግበውታል)

ኢማም ነወዊ (ረሂመሁሏህ) መጅሙዕ ሸርህ አል-ሙሀዘብ በሚባለው ኪታባቸው ላይ እንዲህ ይላሉ

ويستحب للناس استماع الخطبة، وليست الخطبة ولا استماعها شرطًا لصحة صلاة العيد، لكن قال الشافعي: لو ترك استماع خطبة العيد أو الكسوف أو الاستسقاء أو خطب الحج أو تكلم فيها أو انصرف وتركها كرهته ولا إعادة عليه

“ኹጥባ ማዳመጥ የተወደደ ነው። ግዴታ ወይም ለዒድ ሰላት እንደመስፈርት (ሸርጥ) የሚታይ ግን አይደለም። ኢማሙ ሻፊዒይ ደግሞ እንዲህ ይላሉ፡- ‘አንድ ሰው የዒድ፣ የኩሱፍ /በፀሃይ ወይም የጨረቃ ግርዶሽ ጊዜ የሚሰገድ ሰላት/፣ የኢስቲስቃእ /ዝናብ ሲጠፋ የሚሰገድ ሰላት/ አሊያም የሀጅ ጊዜ ኹጥባ ባያዳምጥ አሊያም በመኾጠብ ላይ እያለ ቢናገር ወይንም ሳያዳምጥ ትቶ ቢሄድ ይጠላል። ሶላቱን እንዲመልስም አይገደድም።” ይህ ሲባል ግን ኹጥባ ለማዳመጥ የሚቀመጡ ሠዎችን መረበሽ ግን ሀራም ነው።

እንደ ከፊል ዓሊሞች ደግሞ ለኹጥባው ከተቀመጠ ኹጥባውን ማዳመጥ ግዴታ መሆኑን ያመላክታሉ።

የጁምዓ ሰላትን አስመልክቶ እንደ አብዘሃ አሊሞች (ጁምሁረል ዑለማ) እይታ ኹጥባውን በፅጥታ ማዳመጥ፤ ኹጥባው ባይሰማ እንኳ ዝም ማለት ግዴታ (ዋጂብ) መሆኑንና በኹጥባው ጊዝ መናገር የተከለከለ (ሀራም) መሆኑን መዘንጋት የለብንም።

ሲሄዱ በአንድ መንገድ ሲመለሱ ደግሞ በሌላ መንገድ መመለስ

ከጃቢር ኢብኑ ዐብዲላህ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው “ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) በዒድ ቀን በሄዱበት መንገድ አይመለሱም ነበር።” ብለዋል (ቡኻሪ ዘግበውታል)። በሌላ ዘገባ በእግራቸው ወደ መስገጃ ቦታ እንደሚሄዱና ያለ አዛን እና ኢቃማ እንደሚሰግዱ ሲጨርሱም ባልመጡበት መንገድ እንደሚመለሱ ተነግሯል።

ይህን የሚያደርጉት ሁለቱም መንገዶች የቂያማ ቀን በአላህ ዘንድ እንዲመሰክሩላቸው በማሰብ ነበር። በሁለቱም መንገዶች የእስልምናን ምልክቶች (ሸዓኢር) ለማሳየት እንዲሁም የአላህን ሥም በየቦታው ከፍ ለማድረግ፣ መናፍቃንንና ከሀዲያንን ተስፋ ለማስቆረጥና የሙስሊሙን ህዝብ ብዛት ለማሳየትም የታለመ ሊሆን ይችላል። የሰዎችን ጉዳዮች ለመስማት፣ ለማስተማርና ሰዎችም እርሣቸውን በማየት የአላህን ዲን እንዲቀበሉ፣ በአንደኛው መንገድ ያልነበረውን ችግረኛ በሌላኛው መንገድ ላይ አግኝቶ ለመርዳት ወይም ዘመድ ለመጠየቅ ሊሆንም ይችላል ተብሏል።

የዒድ ቀን መፆም

በሁለቱ ዒዶች ቀን መፆም የተከለከለ ነው። ከአቢ ሰዒድ አልኹድሪይ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው

أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ- صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ-نَهَى عَنْ صِيَامِ يَوْمَيْنِ يَوْمِ الْفِطْرِ وَيَوْمِ النَّحْرِ

“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሁለት ቀናትን- ዒዱልፊጥርና ዒዱልአድሓን- መፆም ከልክለዋል።” (ሙስሊም ዘግበውታል)

የዒድ ሰላት

ከፊል ዑለማኦች የሁለቱ ዒዶች ሰላት ግዴታ ነው ብለዋል። ይህ የሀነፊዮች አቋም ነው። ኢብኑ ተየሚያህ ይህን አቋም ደግፈዋል። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አዘውትረው የሰገዱት መሆኑ ግዴታ ነው የሚሉ ሠዎች ከሚያቀርቧቸው መረጃዎች መሀል ነው።

فَصَلِّ لِرَبِّكَ وَانْحَر

“ለጌታህ ስገድ እረድም።” የሚለው የቁርዓን አንቀፅ ደግሞ በተጨማሪ ማስረጃነት ያቀርቡታል። ይህ ትእዛዝ ለኢድ አልአድሃ ሰላትና ከሱ በኋላ ላለው የእርድ ሥነሥርዓት የወረደ ነው ብለው ያምናሉ። ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ) ሴቶች እንኳን ወደ ዒድ መስገጃ ቦታ እንዲወጡና የምትለብሰው ጅልባብ የሌላትም ከእህቷ ተውሳ እንድትወጣ ማዘዛቸው ግዴታነቱን ያጠናክረዋል ይላሉ።

ሐንበሊዎች ደግሞ ፈርዱል-ኪፋያ (ከፊሉ ሠው የሠገደ እንደሆነ በቀረው ላይ ግዴታ የማይሆን ግዴታ) ነው ብለዋል።

ሶስተኛው አመለካከት በማሊኪዎችና በሻፊዒዮች የተንጸባረቀው የጠበቀ ሱና (ሱና ሙአከዳህ) መሆኑን ነው። ለዚህ እንማስረጃ የሚያቀርቡት አላህ በሙስሊሞች ላይ አምስት ሰላቶችን ብቻ እንጂ ሌላ ግዴታ ያላደረገ መሆኑን ነው።

ይህ እንዳለ ሆኖ ማንኛውም ሙስሊም በሰላቶቹ ላይ ከመገኘት መሣነፍ የለበትም። ወደ ግዴታነት ደረጃ የሚያስጠጉት ዐሊሞች ብዙዎች ናቸው። በዒድ ሰላት ላይ መገኘት ከፍተኛ በረከትን ትልቅ ምንዳን ያስገኛል። የነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) ፈለግ መከተል ያለው ደረጃና ክብርም የላቀ ነው።

ነዋሪ መሆንና ጀመዓ መሆን የዒድ ሶላት መስፈርት ነው የሚል እምነት ያላቸው የሐንበሊያ እና የሐነፊያ መዝሀብ ዑለሞች አሉ። በዚህ መሠረት የዒድ ሶላት ጁሙዐ ሶላት ላይ እንደ መስፈርት የተቀመጡ ነገሮች ሲሟሉ የሚሠገድ ሶላት ነው። ከላይ እንደጠቀስነውም በኹጥባዋ ላይ መገኘት ግን እንደ ጀሙዓው ኹጥባ ግዴታ አለመሆኑ ያስማማል።

እንደ አብዛኞቹ ዑለማኦች ከሆነ የዒድ ሰላቶች ወቅት የሚጀምረው ፀሃይ የስንዝር ያህል ከፍ ካለችበት ጊዜ ሲሆን ፀሃይ ከመሃል ሰማይ ዘንበል እስከምትልበት ድረስም ጊዜው ይቆያል።

የዒድ ሰላት አሰጋገድ

ዑመር (ረ.ዐ) እንዳሉት “የዒድ አልፊጥር እና የዒድ አልአድሃ ሰላት ሁለት ሁለት ረከዐ ናቸው።” ከአቢሰዒድ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው

كان رسول الله- صلى الله عليه وسلم- يخرج يوم الفطر والأضحى إلى المصلى، فأول شيء يبدأ به الصلاة، والتكبير سبعًا في الركعة الأولى وخمسًا في الآخرة والقراءة بعدهما كلتيهما

“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ለዒድ አልፊጥር እና ለዒድ አልአድሃ ሰላት ወደ ሜዳ ይወጡ ነበር። መጀመሪያ የሚጀምሩትም በሰላት ነው። በመጀመሪያው ረከዓ ላይ ሰባት ጊዜ በሁለተኛው ረከዓ ደግሞ አምስት ጊዜ ተክቢራ የሚያደርጉ ሲሆን ተክቢራዎቹን ከጨረሱ በኋላ ቁርዓንን ያነቡ ነበር።”

ከዓኢሻ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው

“በዒድ አልፊጥር እና ዒድ አልአድሃ ሶላት ላይ በመጀመሪያው ረከዓ ላይ -ከመክፈቻው ተክቢራ ውጪ- ሰባት ጊዜ በሁለተኛው ረከዓ ላይ ደግሞ -ከሩኩዑ ተክቢራ ውጪ- አምስት ጊዜ ተክቢራ ያደርጉ ነበር።” (አቡ ዳዉድ ዘግበውታል)

አንድ ሰጋጅ ኢማሙ ተክቢራ በማድረግ ላይ እያሉ ከመሃል ላይ ቢደርስ ከኢማሙ ጋር ይከተላል። ያለፉትን ተክቢራዎች ቀዷ መክፈል አይገባውም። ምክንያቱም ተክቢራዎቹ ሱና እንጂ ዋጂብ አይደሉምና።

በዒድ ሰላት ላይ የሚነበቡ ሱራዎች

በዒድ ሰላት ወቅት ኢማሙ የ “ቃፍ” ሱራ እና የ “ኢቅተረበት” ምራፍን እንዲያነብ ይወደዳል። ሙስሊም እንደዘገቡት ዑመር ኢብኑ-ልኸጧብ (ረ.ዐ) አቢዋፊድ አል-ለይሲን የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በዒድ አልአድሃ እና አልፊጥር ወቅት የትኛውን ሱራ እንደሚያነቡ ጠየቃቸው። እሱም የ “ቃፍ” እና የ “ኢቅተረበት” ሱራዎችን ያነባሉ። አለ።

በሙስሊምና በሌሎች ዘገባዎች ደግሞ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በነዚህ የዒድ ሶላቶች ሱረቱል-አዕላ (ሰቢህ) እና የ “አል-ጋሺያህ” ምእራፎችን እንደሚያነቡ ይጠቁማሉ። እነዚሁን ሱራዎች በጁሙዐ ሶላት ላይም ያነቧቸው እንደነበር በሰፊው ተዘግቧል።

ከኹጥባው ሶላቱ ይቀድማል

በሙስነድ ኢማም አህመድ እንደተዘገበው ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ

أَشْهَدُ أن رَسُولِ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ صَلَّى قَبْلَ الْخُطْبَةِ فِي الْعِيدِ ثُمَّ خَطَبَ

“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ከኹጥባ በፊት እንደሰገዱና ኋላም ኹጥባ እንዳደረጉ እመሠክራለሁ።” ብሏዋል።

በአቢ ሰዒድ ሀዲስ ላይም “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ለዒድ አልፍጥር እና ዒድ አልአድሃ ሰላት ወደ መስገጃ ሜዳ ይወጣሉ። መጀመሪያ የሚጀምሩት በሰላት ነበር። ከዚም ሰዎች ተቀምጠው ባሉበት ሁኔታ ወደነርሱ ይዞሩና ይመክሯቸዋል፤ ያዟቸዋል። ወደ ሌሎች አካባቢዎች ልዑክ ለመላክ የፈለጉ እንደሆነም ይልካሉ። የሚያዙት ነገር ካለም ያዛሉ።” ብለዋል (ቡኻሪ ዘግበውታል)።

አቢ ሰዒድ በማስከተል ከሰላት በፊት ኹጥባን ማስቀደም የጀመረው መርዋን የመዲና አሚር በነበረበት ወቅት መሆኑንና መርዋንም ምክኒያቱን ሲገልጽ ሰጋጆች ከሰላት በኋላ ኹጥባውን ሊያዳምጡለት ብዙ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን በማመን እንደሆነ ተርከዋል። (ቡኻሪ)

የዒድ ሰላቶችን ማዘግየት

የዒድ ሰላቶችን በተጋነነ መልኩ ማዘግየት አይደገፍም። የነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሰሃባ የነበረው ዐብዱላህ ኢብኑ ቡሸር ለዒድ ሰላት ከሰዎች ጋር ወጣ። የኢማሙንም መዘግየት ባየ ጊዜ ትችት አቀረበ። እንዲህም አለ “እኛ ያኔ በዚህ ወቅት ሰግደን እንጨርስ ነበር።” (ቡኻሪ)

ከዒድ ሰላት በፊት ሱና መስገድ

ከዒድ ሰላት በፊትም ሆነ በኋላ የተለየ ሱና ሰላት የለም። ይህም የዒድ ሰላት ሜዳ ላይ የሚሠገድ ከሆነ ነው። መስጊድ ውስጥ ከሆነ ግን ተሒየቱል-መስጂድ ይሰገዳል።

የዒድ ቀን መሆኑን ያላወቁ

ከዑመይር ኢብኑ አነስ እንደተዘገበው ከአንሷር ከሆነችው አክስቱ እንዳስተላለፈው ሰዎች እንዲህ አሉ “የሸዋል ጨረቃ ዳመነብንና ፆመኞች ሆነን ነጋ። በቀኑ መጨረሻ ላይ ግን ሠዎች መጡና ትናንት ጨረቃ እንዳዩ መሠከሩ። ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ) ሰሐቦቹ ዛሬውኑ እንዲያፈጥሩ እና ነገ ደግሞ ለዒድ ሶላት እንዲወጡ አዘዟቸው።” (አምስቱ የሀዲስ ዘጋቢዎች)

ስለዚህ የዒድ ሶላት ያለፈው ሰው ቀዷ ሊያወጣ ይችላል።

ሴቶች በዒድ ሶላት ስለመሳተፍ

ከሐፍሷ እንደተዘገበው እንዲህ ብለዋል፡-

“ልጃገረዶች ለዒድ ሶላቶች እንዳይወጡ እንከለክል ነበር። ከዚያም አንዲት ሴት መጣችና በበኒኸለፎች ህንፃ ውስጥ አረፈች። ስለእህቷም አጫወተችን። የእህቷ ባል ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር አስራ ሁለት ዘመቻዎችን ዘምቷል። ከነዚህ መሀል ስድስቱ ላይ እህቷ አብራው ነበረች። ‘የቆሰሉትን እናክምና የታመሙን እንንከባከብ ነበር። ከዚያም እህቴ ወደ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ሄደችና ‘ጂልባብ የሌላት ሴት ባትወጣ ችግር አለው?’ ብላ ጠየቀች። ነብዩም ‘ጓደኛዋ ጂልባቧን ታልብሳትና መልካም ስብሰባ ላይና የሙስሊሞች ዱዓ ላይ ትገኝ።’ አሏት።’ አለች። እኔም ኡሙዐጢያ ስትመጣ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲሉ ሰምተሻል? ብዬ ጠየኳት። ‘በአባቴ እምላለሁ! አዎን! ሰምቻለሁ።’ አለች። ረስታ ነው እንጂ በአባቴ እምላለሁ አትልም ነበር። ‘ልጃገረዶች፣ የጎጆ ባለቤቶች (የደረሱ ሴቶች ለብቻቸው ጎጆ ይሠራላቸው ነበር እነሱን ለመጥቀስ ነው) እና የወር አበባቸው ላይ ያሉ ሴቶች ወደ (መስገጃ ቦታ) ይውጡ። መልካም ነገሮች እና የሙእሚኖች ዱዓ ላይ ይገኙ። የወር አበባቸው ላይ ያሉ ሴቶች ግን ከመስገጃው (ትንሽ) ይራቁ።’ ሲሉ ሰምቻለሁ። አለችኝ” (ቡኻሪ ዘግበውታል)

በመጨረሻም “ተቀበለላሁ ሚና ወሚንኩም! ዒድ ሙባረክ!” እያልን አላህ ሁላችንንም ለመልካም ነገሮች እንዲመርጠን፣ ከሚቀበላቸው ሠዎች እንዲመድበን እየለመነው እንሰናበታችኋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here