እስልምናን ለመገንዘብ በዲን ዕውቀት ከተሻሉ ሰዎች መታገዝ

0
6266

አላህ ሁሉንም መልእክተኞች ሲልክ በቀላሉ እንዲግባቡ በህዝቦቻቸው ቋንቋ መላኩ የተለመደ ክስተት ነው::

وَمَا أَرْسَلْنَا مِن رَّسُولٍ إِلَّا بِلِسَانِ قَوْمِهِ لِيُبَيِّنَ لَهُمْ

“ከመልክተኛ ማንኛውንም ለነርሱ ያብራራላቸው ዘንድ በወገኖቹ ቋንቋ እንጅ በሌላ አልላክንም” (አብራሒም :4)

كَمَا أَرْسَلْنَا فِيكُمْ رَسُولًا مِّنكُمْ يَتْلُو عَلَيْكُمْ آيَاتِنَا وَيُزَكِّيكُمْ وَيُعَلِّمُكُمُ الْكِتَابَ وَالْحِكْمَةَ وَيُعَلِّمُكُم مَّا لَمْ تَكُونُوا تَعْلَمُونَ

“በውስጣችሁ ከናንተው የኾነን አንቀጾቻችንን የሚያነብላችሁና የሚያጠራችሁ መጽሐፍንና ጥበብንም የሚያስተምራችሁ ታውቁት ያልነበራችሁትን ነገር የሚያሳውቃችሁ የኾነን መልክተኛ እንደላክን (ጸጋን ሞላንላችሁ)” (አል-በቀራህ: 151)

አላህ (ﷻ) በፍጡራኑ ላይ ያለውን ፍላጎት ለማብራራት የመጀመሪያው አስተማሪ መልክተኛው(ﷺ) ነበሩ። የማያውቁትን ያስተምሯቸው፣ ያልገባቸውን ሲጠይቁ ያስረዷቸውና፣ ሲሳሳቱም ያስተካክሏቸው ነበር።

خذوا عنى مناسككم

“(የአምልኮ) ተግባራችሁን ከእኔ ያዙ”

አማር (አላህ ሥራውን ይውደድለትና) እንዳወራው “አንድ ቀን ጀናባ ሆኘ ውሃ አጣሁ። ሜዳ ላይ ተንከባለልኩና ሰገድኩ። ይህም ተግባሬ ለነብዩ(ﷺ) ተነገራቸው። እንዲህ ብታደርጉም አኮ ይበቃ ነበር አሉና እጃቸውን መሬት ላይ አሳረፉ፣ ከዚያም አቧራውን በትንፋሻቸው አራገፉና ፊታቸውን ከዚያም መዳፎቻቸውን አበሱ” (ቡኻሪና ሙስሊም)

ቡኻሪና ሙስሊም በዘገቡት ሌላ ሀዲስ ደግሞ አዲይ ብኑ ሃቲም እንዲህ አሉ

﴿حَتَّىٰ يَتَبَيَّنَ لَكُمُ الْخَيْطُ الْأَبْيَضُ مِنَ الْخَيْطِ الْأَسْوَدِ مِنَ الْفَجْرِ﴾

ከጎህ የኾነው ነጩ ክርም ከጥቁሩ ክር ለናንተም እስከሚገለጽላችሁ ድረስ” የሚለው የቁርአን አንቀጽ በወረደ ጊዜ አንድ ጥቁር ቋጠሮና አንድ ነጭ ቋጠሮ አዘጋጅቼ ትራሴ ሥር አስቀመጥኩኝ፣ ከዚያም በሌሊት መመልከት ጀመርኩ ነገር ግን ሊለይልኝ አልቻለም። በማለዳም ወደ ረሱል(ﷺ) ዘንድ ሄድኩና ነገርኳቸው። እንዲህም አሉኝ ማለት እኮ የሌሊቱን ጨለማነትና የቀኑን ብርሃንነትለማመልከት ነው።

ከዚህም በላይ ነብዩ(ﷺ) አንድ ሰው ወደ እርሳቸው ካልሆነም ወደ አንድ ሌላ ዑለማእ ዘንድ በመሄድ ዕውቀት ሳይቀስም በራሱ ስሜት ፈትዋ ሲሰጥ ካዩ ይቆጡ ነበር፣ ድርጊቱንም ይጠሉ ነበር። ጃቢር አላህ ሥራቸውን ይውደድላቸውና ባወሩት ሀዲስ ለጉዞ በወጣንበት ከመካከላችን አንዱ በድንጋይ ተመትቶ እራሱ ቆስሏል። በዚህ ሁኔታ እያለ ኢህቲላም ሆነ (በህልሙ የዘር ፈሳሽ አፈሰሰ)። ከዚያም ጓደኞቹን ተየሙም በማድረግ (የሰውነትን ሙሉ ትጥበት በመተው) ልታግራሩልኝ ይቻላልን? በማለት ጠየቃቸው። እነርሱም አንተ መታጠብ ስለምትችል ምንም አይነት ማግራራት ልናገኝልህ አንችልም አሉት። እርሱም ታጠበና በዚያው ምክንያት ሞተ። ወደ ረሱል(ﷺ) በተመለስን ጊዜ ይህ ጉዳይ ተነገራቸው። እርሳቸውም “ገደሉት! አላህ ይግደላቸው ካላወቁ አይጠይቁም ነበርን? ላለማወቅ መድሃኒቱ መጠየቅ ነው፣ ተየሙም ማድረግ ይበቃው ነበር ወይንም ደግሞ ቁስሉን በቁራጭ ጨርቅ በማሰር በውሃ ካበሰ በኋላ የቀረውን ሰውነቱን መታጠብ ይችል ነበር።” አቡ ዳዉድ፣ ኢብን ማጃህና ዳረ ቁጥኒይ ዘግበውታል፣ ኢብኑ ሰከን ሶሂህ ነው ብለዋል

ረሱል(ﷺ) እንዲህ ብለዋል፡ “ከእናንተ መካከል ፈትዋ ለመስጠት የሚቀድም እሳት ለመግባትም ቀዳሚ ነው”

ዕውቀትን የፈለገ ከዲኑ ታላላቅ መሪዎች (አኢማዎች) አንዱን ሊከተልና ከእርሱም ቃል በቃል ትምህርት ሊወስድ ይገባል። ይህ መንገድ ነው ነብዩ(ﷺ) ከርሳቸው በኋላ ለነበሩት ሰለፎች(ምትኮች) ያወረሱት፣ እነርሱም እንዲሁ ለተከታዮቻቸው፣ ተከታዮቻቸውም ለተከታዮቻቸው አስተላልፈዋል … ሂደቱም አስከ ዕለተ ትንሳኤ ድረስ የሚቀጥል ይሆናል። ይህም የማይቀየሩ ከሆኑት ከአላህ ሱናዎች(የተፈጥሮ ህግጋት) መካከል አንዱ ሲሆን ለዚህም በዋነኛነት የሚከተሉት ምክኒያቶች ይጠቀሳሉ::

የዑለማኦች ደረጃና ብልጫ

  • ዑለማኦች የነቢያቶች ወራሽ ናቸው

ዑለማኦች ከረሱል(ﷺ) በኋላ ወደ እስልምና በቀጣይነት የመጣራትን (ዳዕዋ ማድረግ)፣ ግልፅ የማድረግን፣ የማብራራትና እንዲሁም የማስተማርን ኃላፊነት የወረሱ ናቸው። ረሱል(ﷺ) እንዲህ ብለዋል። “አላህ መልካም ያሻለትን ሰው በዲን ጥልቅ ግንዛቤን ይቸረዋል”ዕውቀት ደግሞ በመማር ነው፣ ነቢያት (የአላህ ሰለዋት በእነርሱ ላይ ይውረድና) ዲናርንም ይሁን ዲርሃምን አላወርሱም፣ እነርሱ በእርግጥ ያወረሱት ዕውቀትን ነው፣ ዕውቀትን የያዘ ትልቅ እድልንና ሙሉ የሆነ ነገርን ይዟል።”

በማንኛውም ጉዳይ የአላህን (ﷻ) ድንጋጌዎች ከቁርአንና ሀዲስ ለመረዳት መዳረሻችን ዑለማኦች ሊሆኑ ይገባል። አላህ (ﷻ) እንዳዘዘውም

فَاسْأَلُوا أَهْلَ الذِّكْرِ إِن كُنتُمْ لَا تَعْلَمُونَ

“የማታውቁም ብትኾኑ የዕውቀትን ባለቤቶች ጠይቁ” (አናህል 43)

የሚለውን በተግባር ልናውለው ግድ ይለናል። ሰሃባዎችም በአጠቃላይ ይህንን ጉዳይ ተግባራዊ በማድረግ በወቅቱ የነበረው ህብረተሰብ ያልገባውን ነገር ይጠይቃቸውና እነርሱም መልስ ይሰጡ ነበር። ጥያቄ በመጠየቁ ምክንያት አንድንም ሰው አይነቅፉም ነበር። ተራው ሰው አላህን ከሚፈሩ ሰዎች በስተቀር በዘፈቀደ ማንኛውንም ተራ ሰው ስለ ዲን ጉዳይ መጠየቅ (ፈትዋ መውሰድ) አይፈቀድለትም። በሀገሩ ውስጥ በዲን ጉዳይ ተመራማሪዎች (ሙጅተሂዶች)ካሉ ከነርሱ መካከል የፈለገውን ሰው መጠየቅ ይችላል። የትኛው ሰው የተሻለ ነው ብሎ እነርሱን ማበላለጥ አይጠበቅበትም።

  • ዑለማኦች የዲኑ ጠባቂዎች ናቸው

ዑለማኦች በየዘመናቱ የሸሪዓ ተሸካሚዎችና ከፅንፈኞች ፅንፍ፣ ከአፈንገጮች ማፈንገጥ፣ ከአጥፊዎች ጥፋት፣ ከአመጸኞችና ከከሃድያን ትግል የዲኑ ተከላካዮች ናቸው።

ከኢብኑ ዑመር (አላህ ሥራቸውን ይውደድላቸውና) እንደተወራው ረሱል (ﷺ) እንዲህ ብለዋል፡

“አላህ ዕውቀትን ለሰዎች ከሰጣቸው በኋላ የሚያነሳው ከነርሱ መንጭቆ በመውሰድ አይደለም፤ነገር ግን ዕውቀትን የሚያነሳው ዑለማኦችን በማንሳት(በሞት) ነው። አንድ ዐሊም በጠፋ ቁጥር ከርሱ ጋር ያለው ዕውቀትም አብሮ ይጠፋል፣በዚህ ሂደት መጨረሻ ላይ [ዐሊሞቹ ሁሉ ጠፍተው] የአላዋቂዎች(ጃሂሎች) ቁንጮ የሆኑት ብቻ ይቀሩና ፈትዋ ሲጠየቁ ያለዕውቀት መልስ ይሰጣሉ፣እራሳቸው ጠመው ሌላውንም ያጠማሉ” (ቡኻሪና ሙስሊም ተስማምተውበታል፣ ቡኻሪ ዒልሙል ሀዲስ በሚለው ክፍል ቁጥር 98)

ዑለማኦች ለሁሉም የዕውቀት አይነት መሠረት የጣሉና ይህም መሠረት እንዳይናጋ ጠባቂዎች ናቸው። ከነርሱ መካከል እንደ ኢማም አቡ ሐኒፋ፣ ኢማሙ ሻፊዕይ፣ ኢማሙ ማሊክና ኢማሙ አህመድ ኢብኑ ሀንበል ያሉት የፊቅህ ሊቃውንት በዋነኝነት የሚጠቀሱ ሲሆን እነዚህ ታላላቅ ዑለማኦች ስለዒባዳ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ግንዛቤ መሠረት የጣሉ ናቸው። እንደ ኢማም አል-ጋዛሊ ያሉት ዑለማኦች በጊዜው መስመር የለቀቀውን የፍልስፍናና የዙህድን አስተሳሰብ ሰርአት በማስያዝ ኢስላማዊው እውቀት መልሶ እንዲያብብ ብዙ ለፍተዋል:: እንደ ኢብኑ ተይሚያና ኢብኑል ቀይም ያሉት ዑለማኦች ደግሞ በዘመኑ ከድንበር ያፈነገጡና ጽንፈኝነትን የሚያራምዱ የተሰዉፍ ፍልስፍናና የባጢኒያ ቡድኖችን በሰፊው መክተዋል። በዘመናችን ከነበሩት ዑለማኦች መካከል እንደ ኢማም ሀሰን አል-በና፣ ሸይኽ አል-ጋዛሊ፣ ሸይኽ ሸዕራዊ እና ሸይኽ አል-ቀርዳዊ ያሉት ደግሞ ሰዎች እስልምናን እነዴት መረዳት እንዳለባቸው በሰፊው ያብራሩና በዘመናችን የሰዎችን አስተሳሰብ ችግር ውስጥ እያስገባና አዕምሮን እየሸረሸረ ያለውን የቁሳዊነት (ማቴሪያሊዝም) አይዲሎጅ አቀንቃኞች በከፍተኛ ሁኔታ የተጋፈጡ ናቸው።

  • ዑለማኦችን ማክበር ወደ አላህ ያቃርባል

ዑለማኦችን ማክበር ወደ አላህ ከማቃረቡም ባሻገር ከሸሪዓ አንጻር በራሱ ግደታ ነው። ኢማሙ ጠሃዊ እንደሚሉት “ቀደምት የሰለፍ ዑለማኦችንም ሆነ ከነርሱ በኋላ ያሉ መልካምና ደጋግ የፊቅህ አዋቂዎች በጥሩ እንጅ በመጥፎ ሊነሱ አይገባም። እነርሱን በመጥፎ የሚያነሳ በአማኞች መንገድ ላይ አይደለም።”

ይህን ኪታብ ማብራሪያ የጻፉለት ሼይኸ እንዲህ ይላሉ “በማንኛውም ሙስሊም ላይ አላህንና መልእክተኛውን እንደሚወድ ሁሉ በቀጣይነትም አማኞችን ሊወድ ይገባል። በቁርአን ውስጥ በተለየ ሁኔታ እንደተብራራው እነዚያ የነቢያት ወራሽ የሆኑትንና ህብረተሰቡን በየብስም ሆነ በባህር ውስጥ ከጨለማ ወደ ብርሀን በመምራት ረገድ አላህ(ﷻ) የኮከብነትን ደረጃ የሰጣቸውን ዑለማኦች ማክበር ግደታ ነው።

ነብዩ ሙሐመድ(ﷺ) ከመምጣታቸው በፊት ለነበሩት ህዝቦች ዑለማኦቻቸው ከነርሱ ውስጥ በጣም ተንኮለኞቹ የነበሩ ሲሆን ሙስሊሞች ግን ዑለማኦቻቸው ከነርሱ መካከል በጣም ምርጦቹ ናቸው። የሙስሊሙ ኡማ መሪዎች የረሱል (ﷺ) ምትኮች ሲሆኑ ረሱል (ﷺ) ከሞቱ በኋላም ፈለጋቸውን ህያው ያደርጋሉ… እነርሱ መልዕክተኛው የተላከበትን መልእክት ቀድሞ በማድረስና ግልፅ ያልሆነውን በማብራራት በኩል ፈጣን ከመሆናቸው አኳያ ትልቅ ደረጃና ክብር እንድንሰጥ በእኛ ላይ ግደታ ይሆንብናል። አላህ ሥራቸውን ይውደድላቸው፣ እነርሱንም ይውደዳቸው የተባለላቸው ናቸው።” (ኡሱሉል አቂዳ ሊኢብኒ አሊ-አል-ዒዚ ገጽ ከ197-198 የተወሰደ)

ሸሂድ ሀሰን አል-በና አንዲህ ብሏል “ደጋጎችን መውደድና ማክበር፣ ለታወቁ መልካም ተግባራቶቻቸው እነርሱን ማሞገስ ወደ አላህ (ﷻ) ከሚያቃርቡ መንገዶች ነው።”

አህነፍ (አላህ ሥራቸውን ይውደድለቸውና) እንደሚሉት “በዕውቀት ላይ ያልተገነባ ክብር ወደ ውርደት ማዘንበሉ አይቀርም”። አሊይ (አላህ ሥራቸውን ይውደድለቸውና) እንዳሉት ደግሞ “ዐሊም ከጿሚ፣ ከሌሊት ሰጋጅና ከታጋይ ይበልጣል። አንድ ዐሊም በሞተ ጊዜ ከኢስላም በእርሱ ተሸፍኖ የነበረው ቀዳዳ ክፍት ይሆናል። የርሱን ክፍተት ሊሞላ የሚችለው የእርሱ ተተኪ ካለ ብቻ ነው”

  • ዕውቀት ከባለቤቶቹ ይወሰዳል

የዲን ዑለማኦች በዲኑ ዘርፍ የቆሙ ዘቦች ናቸው። ከመካከላችን በዱንያው ዘርፍ የህክምና፣ የምህንድስና፣የሂሳብ ሥራ ወይንም የፋብሪካ፣ የግብርና፣ የዕደ ጥበብ ጉዳዮች ቢገጥሙን በሙያው ልዩ ዕውቀት ወዳላቸው ባለሞያዎች እንሄዳለን። ታዲያ የዲን ዕውቀትን መማር ስንፈልግ በሸሪዓ ዘርፍ ዕውቀት ወዳላቸው ባለሞያዎች የማንሄደው ለምንድን ነው? እራሳችንን ለእነርሱ አስገዝተን ዕውቀትንንና ግንዛቤን ለምን አንፈልግም? አላህ (ﷻ) እንዲህ ብሏል ፡-

﴿فَاسْأَلُوا أَهْلَ الذِّكْرِ إِن كُنتُمْ لَا تَعْلَمُونَ﴾

“የማታውቁ ከሆናችሁ የዕውቀት ባለቤቶችን ጠይቁ” (አናሀል 43)

﴿فَاسْأَلْ بِهِ خَبِيرًا﴾

“ከእርሱም ዐዋቂን ጠይቅ” (አል ፉርቃን 59)

﴿وَلَا يُنَبِّئُكَ مِثْلُ خَبِيرٍ﴾

“እንደ ውስጠ ዐዋቂው ማንም አይነግርህም” (ፋጢር 14)

ዑለማኦች ሀላልም ግልጽ ነው፣ ሀራምም ግልጽ ነው፣ በሁለቱ መካከል ግን አሻሚ ጉዳዮች አሉ ከሰዎች ብዙዎቹ አያውቋቸውም…”በሚለው የነብዩ(ﷺ) ንግግር ውስጥ የተንጸባረቁ ናቸው። ኢብኑ ረጀብ አል-ሀንበሊ እንደሚሉት “የዚህ ሀዲስ ትርጉም ሀላል ግልጽ የሆነ ጉዳይ ነው። በውስጡ አሻሚነት የለበትም። ሀራምም እንደዚሁ ግልጽ ነው። ነገር ግን በነዚህ ሁለት ጉዳዮች መካከል ለብዙ ሰው ሀላል ነው ወይንስ ሀራም? በሚል አሻሚ የሆኑ ነገሮች አሉ። በዕውቀቱ ጥልቅ ግንዛቤ ያላቸው ዑለማኦች እነዚህ ጉዳዮች አሻሚ አይሆኑባቸውም። ከየትኛው ክፍል እንደሆኑ በቀላሉ ይለይዩዋቸዋል።”

ኢማም አንነወዉይ አንደሚሉት “አሻሚ የሆነ ጉዳይ ማለት ሀላል ይሁን ሀራም ግልጽ ያልሆነ ማለት ሲሆን ይህ ደግም ብዙ ሰው የማያውቀዉና ምን እንደሚያስወስንም የማይረዱት የሆነ ነው። ዑለማኦች ግን እራሱን በቀጥታ በመረዳት(ነስ) ወይንም ጉዳዩን ከቁርአንና ከሌላ ሀዲስ ጋር በማዛመድ (ቂያስ) ካልሆነም የጉዳዩን ከዚህ በፊት መከሰትና በቀጣይም የመኖሩን ሁኔታ በማጤን (ኢሰቲስሀብ) ወይንም በሌላ መልኩ የነገሩነን ሁክም ያውቁታል።”

አቡ ሀሚድ አል-ጋዛሊ እንዲህ ይላሉ፡-“አላህ ሱብሀነሁ ወተዐላ በዐሊም ቀልብ ላይ የእርሱ መለዮ የሆነችን ዕውቀት ከፍቶለታል። እርሱ እንደ ግምጃ ቤት ነው፣ በነፍሱ ውስጥ እርሷን ጠባቂ ነው። ይህችን ዕውቀት ፈልጎ ለሚመጣ ከዚያች ቆንጥሮ እንዲሰጥ ተፈቅዶለታል።ለመሆኑ በአላህና በፍጡራኑ መካከል አገናኝ ወደ እርሱ አቃራቢና ዘላለማዊ ወደ ሆነችው ገነት መሪ ከመሆን በላይ ለአንድ ባሪያ ምን የላቀ ደረጃ ይኖረዋል? ”

የዕውቀትና የመማር አስፈላጊነት

  • ጠቢባን ስለ ዕውቀትና ስለ መማር አስፈላጊነት ብዙ ንግግሮች አሏቸው። ከፊሎቹን እንጠቅሳለን፡

ጥበበኛው ሉቅማን ለልጃቸው እንዲህ ሲሉ መክረዋል፡-“ልጀ ሆይ ዑለማኦችን ተጠጋ በጉልበትህ ተንበርክከህ ቅረባቸው። አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ ልብን በጥበብ ብርሃን ህያዉ ያደርጋታል፤ ልክ ምድርን ከሰማይ በሚወርድ ዝናብ ህያው እነደሚያደርግ ሁሉ”

ከዐሊሞች መካከል አንዱ እንዲህ ብሏል፡- “የዕውቀት መሠረቶች አምስት ናቸው፤ አስተማሪው፣ ተማሪው፣ ዕውቀቱ በራሱ፣ ስልቶቹና መርጃ መሳሪያዎቹ ናቸው። እነዚህን መሠረቶች የያዘ በእርግጥ (ዕውቀትን) ሰብስቧል።” አላህ (ﷻ) እንዲህ ብሏል፡-

﴿اقْرَأْ وَرَبُّكَ الْأَكْرَمُ﴿٣﴾الَّذِي عَلَّمَ بِالْقَلَمِ﴿٤﴾عَلَّمَ الْإِنسَانَ مَا لَمْ يَعْلَمْ

“አንብብ፤ ጌታህ በጣም ቸር ሲሆን፤ያ በብዕር ያስተማረ፤ ሰውን ያላወቀውን ሁሉ ያሳወቀ ሲሆን” (አል-ዐለቅ: 3-5)

እነዚህ አንቀፆች የዕውቀት መሰረቶችን ሰብስበዋል። አስተማሪው አላህ፣ ተማሪው የሰው ልጅ ሲሆን ትምህርቱ ደግሞ የሰው ልጅ ሊያውቀው የሚፈልገው ነገር ሁሉ ነው፤ መርፌ መሥራት እንኳን ቢሆን። የዕውቀቱ ማግኛ መንገድ ደግሞ ማንበብና ማዳመጥ ሲሆን የትምህርት መሣሪያዎቹ ደግሞ ብዕርና መጻህፍቱ ናቸው።

አንድ ሌላ ዓሊም እንደተናገሩት “አስተማሪው መጽሀፉ ብቻ የሆነ ሰው ከሚሰራው መልካም ሥራ ይልቅ ስህተቱ ይበዛል”።

ኢማም አል-በና እንዲህ ብለዋል “ማንኛውም በዲን ጉዳይ በራሱ ተገንዝቦ የመወሰን ደረጃ ላይ ያልደረሰ ሙስሊም ቅርንጫፋዊ በሆኑ ድንጋጌዎች ላይ ከኡማው ታላላቅ ዑለማኦች አንዱን ሊከተል ይገባል። ከዚሁ ጎን ለጎን ማስረጃዎቹን በራሱ መገንዘብ እንዲችል ጥረት ሊያደርግ ይገባል። በግልጽ መረጃ ተደግፎ የቀረበለትን ምክር የመካሪው ብቃት አስተማማኝነቱን እስካረጋገጠ ድረስ ሊቀበል ይገባዋል:: አሊም ከሆነ በራሱ ተገንዝቦ መወሰን እሰከሚችልበት ደረጃ (ደረጀተ-ነዘር) ድረስ እስከሚደርስ በዕውቀቱ ዙሪያ ያለበትን ጉድለት ሊያሟላ ግድ ይለዋል።”

አቡ ዑስማን ነይሳቡሪይ እንዲህ ብለዋል፡- “አላህን መጎዳኘት በመልካም ስነ-ምግባርና እርሱን ዘወትር በመፍራትና እርሱ እንደሚከታተለን በማወቅ ነው። ከረሱል (ﷺ) ጋር ያለ ጉድኝት ሱናቸውን በመከተልና ግልጽ በሆነው ግንዛቤ ላይ በመዘውተር ነው። ከዑለማኦች ጋር የሚኖረን ጉድኝት ደግሞ ለእነርሱ ተገቢውን ክብር በመስጠትና በማገልገል ነው።”

  • መወገድ ያለበት ክፍተት

በአሁኑ ጊዜ ከዑለማኦች ጋር መቀማመጥ አስፈላጊ አይደለም የሚሉ አንዳንድ ሰዎች ብቅ ብለዋል። አንዳንድ ጊዜ ዑለማኦቹም ሰው ናቸው እኛም ሰው ነን የሚል ተራ ምክንያት ያቀርባሉ። በአንድ ወቅት አንዱ ሸይኽ አብዱረዛቅ የሚባሉ አሊም ሲያስተምሩ ‘’ከአብዱረዛቅ ሄደህ አትሰማምን?’’ ሲባል ‘’ከፈጣሪ(ረዛቅ) መስማት የሚችል ሰው ከአብዱረዛቅ መስማት ምን ያስፈልገዋል?’’ በማለት መለሰ። ይህ ሰው በንግግሩ የፈለገው ዕውቀቱን በቀጥታ ከቁርአን አገኘዋለሁ ለማለት ነው።ይህና መሰል ንግግሮች አላዋቂነትና የሰይጣን ንግግሮች ናቸው። እንደ አብዱረዛቅና መሰል የሀዲስ ዑለማኦች ባይኖሩ ኖሮ ይህንና ሌሎች የእስልምና ተግባራት በፍጹም ባልደረሱ ነበር። (ተዝሂብ መዳሪጅ ሳሊኪን-መንዚለቱል ዒልም)

ዑለማኦች በህዝብ ላይ መስካሪዎች ናቸው። አላህ (ﷻ) በርሱ ብቸኝነት (ተውሂድ) ጉዳይ የዕውቀት ባለቤቶችን ምስክር አድርጓቸዋል። ምስክርነታቸውንም ከእርሱ መስካሪነትና ቀጥሎም ከመላእክት መስካሪነት ጋር አቆራኝቶታል፡- “አላህ ከእርሱ በስተቀር ሊገዙት የሚገባ ሌላ አምላክ እንደሌለ መስክሯል፣ መላእክቶቹም ከዚያም የዕውቀት ባለቤቶችም መስክረዋል፤ በትክክለኛ ውሳኔ ላይ የቆመ፡ ከርሱ በስተቀር ሊገዙት የሚገባ አምላክ የለም፣ እርሱ አሸናፊና ጥበበኛ ነው” (አል-ዒምራን 18)

  • ጠቃሚ ምክር

የዑለማኦችና የዲን ታጋዮችን ታሪክ እንዲሁም በዲኑ የጥልቅ ዕውቀት ባለቤትና የፈጣሪን ቅን አገልጋዮች ፈለግ ደጋግሞ የሚቃኝ ሰው እነርሱን ሞዴል አድርጎ እንዲይዝ ነፍሱ ትጎተጉተዋለች፣ በተግባራቸው ለመመሳሰል ደፋ ቀና እንዲል ውስጡ ያስገደድዋል፣ አላህ ፈቅዶለት የእነርሱን ደረጃ ለመድረስ ይጣጣራል። ኢማሙ ጁነይድ “ሂካያ (ትረካ) ከአላህ ሠራዊቶች አንዱ ነው፤ ልቦችን በኃይል ያጎለብታል” ሲሉ ለዚህ ማስረጃ አለህን? ብለው ጠየቋቸው። እርሳቸውም “አዎ አላህ በቁርአኑ እንዲህ ብሏል”

﴿نَّقُصُّ عَلَيْكَ مِنْ أَنبَاءِ الرُّسُلِ مَا نُثَبِّتُ بِهِ فُؤَادَكَ﴾

“ከመልክተኞቹም ዜናዎች (ተፈላጊውን)። ሁሉንም ልብህን በርሱ የምናረካበትን እንተርክልሃለን…”

ስለሆነም ውድ ወንድሜ ሆይ የዑለማኦችን፣ የፉቀሓዎችን፣ የሙጅተሂዶችን ታሪክ ለማንበብ ተጣደፍ፤ በታጋሽነታቸው፣ በፅናታቸውና በጥብቅነታቸው እነርሱን ሞዴል አድርገህ ለመኖር ጥረት አድርግ!!

እንደነርሱም ባትሆኑ እስኪ እነርሱን ምሰሉ

እጅጉን ይሻላልና በጀግኖች መመሰሉ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here