ሐጅ (ክፍል 2)

0
6809

የሐጅ ዋና ዋና ክንውኖች

የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡-

خذوا عنى مناسككم

“የሐጅ ክንውኖቻችሁን ከኔ ተማሩ።”

ከነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) የተገኙ አበይት የሐጅ ክንውኖች ኢህራም፣ ተልቢያ፣ ጠዋፍ፣ሰእይ፣ ዓረፋ ላይ መቆም (ውቁፍ)፣ ጠጠር ውርወራና እርድ ናቸው።

ቀጥሎ ተመልክተዋል፡-

1.ኢህራም

ሐጅ አድራጊ መጀመሪያ የሚፈጽመው ተግባር ኢህራም ነው። ይህም ማለት የአላህን ውዴታ በመሻት ሐጅ ለማድረግ መወሰኑን የሚያሳይ ነው። አላህ ለርሱ ያልሆነን ድርጊት አይቀበልም። ስራ ሁሉ በኒያ ነው። ሰውየው የሚያገኘው የኒያውን ነው። ለዓለማዊ ዓላማ ከሄደ ዓለማዊ ጥቅምን እንጅ አላህን አያገኝም።

ሐገሮች የየራሳቸው የተለየ የኢህራም ቦታ አላቸው። ኢህራም ካደረገ በኋላ በሐጅ ወቅት ክልክል የሆኑ ነገሮችን በሙሉ ይታቀባል። ከስነ ምግባር አኳያም ራሱን የመግዛት መርህን ይከተላል። አላህ እንዲህ በማለት እንዳዘዘው፡-

الْحَجُّ أَشْهُرٌ مَّعْلُومَاتٌ فَمَن فَرَضَ فِيهِنَّ الْحَجَّ فَلَا رَفَثَ وَلَا فُسُوقَ وَلَا جِدَالَ فِي الْحَجِّ
 

“የሐጅ (ጊዜ) የታወቁ ወራት ናቸው። በነኝህ (ወራት) ውስጥ ሐጅን በራሱ ላይ ግዳጅ ያደረገ ሐጅ ውስጥ ከሴት ጋር መገናኘት፣ (በአላህ ላይ) ማመጽም፣ (ከባልደረቦቹ) ጋር መከራከርም የለበትም።” (አል-በቀራህ 2፤ 197)

ኢህራም ከነፍስያ ፍላጎት ራስን ማቀብን ያመለክታል። ነፍስን ሙሉ በሙሉ ለአላህ የመስጠት መገለጫ ነው። ከላይ እንደገለጽነው የኢህራም አለባበስ ለሞት መገነዝን ያስታውሳል።

2.ተልቢያህ

ቀጣዩ የሐጅ ክንውን ተልቢያህ ነው። ይህውም፡- “ለበይክ አሏሁመ ለበይክ” ማለት ነው። ትርጉሙ፡- “አቤቱ አምላካችን ሆይ፣” ማለት ነው። ሐጅ አድራጊ “ተልቢያህ” ሲል ለአላህ ትእዛዝ ለማደር ቃል እየገባ ነው። ወደርሱ እየሄደ መሆኑን እያስታወሰ ነው።

3.የመግቢያ ጦዋፍ

መካ እንደደረሱ በካእባ ዙሪያ ሰባት ዙር ጠዋፍ በማድረግ ለአላህ “የመጥቻለሁ” ሰላምታ ያቀርባል። “የመግቢያ ጦዋፍ” በመባል ይታወቃል። ጦዋፍ ከጥቁሩ ድንጋይ ይጀመራል። ድንጋዩ የተለየ ቅዱስነት የለውም። ነቢዩ ኢብራሂም ለጠዋፍ አድራጊዎች ምልክት ይሆን ዘንድ ያስቀመጡት ነው። ሌላ የተለየ ሚስጥር የለውም። ወይም አንዳንድ የሌላ እምነት ተከታዮች እንደሚያስቡት እና እንደሚናገሩት ሙስሊሞች የሚያመልኩት ድንጋይ አይደለም። ዑመር ቢን አል ኸጣብ እንዲህ ሲል መናገራቸው ተዘግቧል፡-

إنى لأعلم أنك حجر لا تضر ولا تنفع, ولولا أنى رأيت رسول الله يقبلك لما قبلتك

“ድንጋይ እንደሆንክ አውቃለሁ። የአላህ መልእክተኛ ሲስምህ ባላይ ኖሮ አልስምህም ነበር።”

ስለዚህ ጥቁሩ ድንጋይ አይመለክም። የተለየ ቅድስናም የለውም። እንደዚያ የሚያስቡ ሙስሊሞች ካሉ ካለማወቅ በመነጨ ነው።

4.በሶፋና በመርዋ መካከል መሮጥ (ሰእይ)

ሐጅ አድራጊው የመግቢያ ጠዋፉን እንዳጠናቀቀ በሶፋና በመርዋ መካከል ሰባት ዙር ይሮጣል። ይህ ስርዓት “ሰእይ” ይባላል። ይህ ስርዓት የአላህን ምህረት እና እዝነት ፍለጋ የመማሰን ተምሳሌት ነው። ይህ ስርዓት የኢብራሂም ሚስት ሐጀር ውሃ ፍለጋ ልጇን ጥላ ያደረገችውን መመላለስም ያስታውሳል። አላህ ወዲያው ውሃ አፈለቀላት። ለዚህ ቤት መመስረትም መነሻ ክስተት ሆነ። ይህ የበረከት አገርም ተቆረቆረ።

5.ከኢህራም መፈታት

ሐጅንና ዑምራን በአንድ ለመፈጸም ያሰበ ሌሎችን የሐጅ ክንውኖች ከኢህራም ሳይፈታ መቀጠል ይኖርበታል። ሁለቱን ለየብቻ ለማከናወን ያሰበ ግን ጸጉሩን በመላጨት ወይም በማሳጠር ከኢህራም ይፈታል። እናም ያለፉት ክንዉኖች (ማለትም ኢህራም፣ጠዋፍና ሰእይ) ዑምራ ይሆኑለታል። በነርሱም ተገቢውን ምንዳ ያገኛል። እንዲህ ባደረገ ጊዜ የ “ተመቱእ” እርድ ማረድ አለበት። ይህን እርድ አላህ በሚከተለው የቁርአን አንቀጽ አውስቶታል፡-

وَأَتِمُّوا الْحَجَّ وَالْعُمْرَةَ لِلَّهِ فَإِنْ أُحْصِرْتُمْ فَمَا اسْتَيْسَرَ مِنَ الْهَدْيِ وَلَا تَحْلِقُوا رُءُوسَكُمْ حَتَّىٰ يَبْلُغَ الْهَدْيُ مَحِلَّهُ فَمَن كَانَ مِنكُم مَّرِيضًا أَوْ بِهِ أَذًى مِّن رَّأْسِهِ فَفِدْيَةٌ مِّن صِيَامٍ أَوْ صَدَقَةٍ أَوْ نُسُكٍ فَإِذَا أَمِنتُمْ فَمَن تَمَتَّعَ بِالْعُمْرَةِ إِلَى الْحَجِّ فَمَا اسْتَيْسَرَ مِنَ الْهَدْيِ فَمَن لَّمْ يَجِدْ فَصِيَامُ ثَلَاثَةِ أَيَّامٍ فِي الْحَجِّ وَسَبْعَةٍ إِذَا رَجَعْتُمْ تِلْكَ عَشَرَةٌ كَامِلَةٌ

“ሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ ከሆናችሁ (በተሟላ መልኩ ከመፈፀም የሚያግዳችሁ ነገር ከሌለ) እስከ ሐጅ ድረስ በዑምራህ የተጣቀመ ከሀድይ የቻለውን (ለመስዋእትነት ያቅርብ)። ይህን ያላገኘ በሐጅ ወራት ሦስት ቀናትን፣ (ወደ ቤተሰቦቹ) ሲመለስ ደግሞ ሰባት ቀናትን ይጹም። እነኝህ (ሀድይን የሚተኩና የተሟሉ) አሥር ቀናት ይሆናሉ።” (አል-በቀራህ 2፤ 196)

ወዲያው ኢህራሙን እንደፈታ ማረድ ይችላል። እስከ “የውመነህር” (የእርድ ቀን) ድረስ እንዲቆይ አይገደድም።

6.ዓረፋ ላይ መቆም

ኢህራምን የፈታ ሰው በዙል ሒጃ ወር በሁለተኛው ቀን ለሐጅ ኢህራም ያደርጋል። አፈጻጸሙ ልክ እንደበፊቱ ነው። በሚና አድርጎም ወደ አረፋ ይጓዛል። በዙልሂጃ ዘጠነኛው ቀን ሁሉም ሐጃጆች አረፋ ላይ ይገናኛሉ። ይህ ክንውን የሐጅ ስራዎች አስኳል በመሆኑ የአላህ መልእክተኛ እንዲህ እስከማለት ደርሰዋል፡-

الحج عرفة

“ሐጅ ማለት ዓረፋ ነው።”

ይህ መስክ ከአላህ ፊት መቆምን ያስታውሳል። የውመል ቂያማን በዓይነ ሕሊና ያመጣል። ሰዎች ከጌታቸው ፊት ፍርድ ለመቀበል የሚቆሙበትን ቀን።

በዚህ እለት ታላቅ ጸጋ ለሙስሊሙ ኡምማ ተፈጽሟል። አላህ ዲኑን ምሉእ እንዳደረገው ያወጀው በዚህ ቀን ነበር፡-

الْيَوْمَ أَكْمَلْتُ لَكُمْ دِينَكُمْ وَأَتْمَمْتُ عَلَيْكُمْ نِعْمَتِي وَرَضِيتُ لَكُمُ الْإِسْلَامَ دِينًا

“ዛሬ ሃይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ። ፀጋዬንም በናንተ ላይ ፈፀምኩ። ለናንተም ከሃይማኖት (ሁሉ) ኢስላምን መረጥኩ።” (አል-ማኢዳህ 5፤ 3)

7.ሙዝደሊፋ ላይ መቆም

ዓረፋ ላይ የመቆም ስርዓት ሲጠናቀቅ ሙዝደሊፋ ላይ መቆም ይከተላል። ሐጃጁ ከአረፋ ወደ መዝደሊፋ ይጓዛል። በአስረኛው ቀን ሚና ላይ ይገኛል። ጠጠር ይለቅማል። ያርዳል። የመመለሻ ጠዋፍ (ጠዋፈል ኢፋዳ) ያደርጋል። ቅደም ተከተላቸው ችግር የለውም።

8.ጠጠር ውርወራ

የጠጠር ውርወራ ስርዓት ይከናወናል። ጠጠር ውርወራው ሰውየው ከእኩይ ድርጊቶች መራቁን የሚገልጽበት ተምሳሌት ነው። አንዳንድ ሰዎች የጠጠር ውርወራ ስርዓቱን ሰይጣንን እንደ መደብደብ አድርገው ይቆጥሩታል። እናም በቁጣ ግለው፣ በንዴት ተቃጥለው እየጮሁና እየፎከሩ ነው ስርዓቱን የሚፈጽመት። ከጠጠር አልፎ ድንጋይ፣ ጫማ … የሚወረውሩ አሉ። ይህ ሁሉ ስህተት ነው። መሠረተቢስ አመለካከት ነው። ሸሪዓዊ መነሻ የለውም።

9.የስንብት ጠዋፍ

ሐጃጁ የሐጅ ስራውን አጠናቆ ወደ ሐገሩ ሊመለስ ሲያስብ ወደ ካእባ ሄዶ የመሰናበቻ ጠዋፍ ያደርጋል። ሲገባ አስፈቅዶ (ጠዋፍ አድርጎ) እንደገባው ሁሉ ሲመለስም አስፈቅዶ (ጠዋፍ አድርጎ) ይመለሳል። እናም ከወንጀል የጸዳና በተቅዋ የተሞላ ሆኖ ከሐገሩ ይደርሳል።

10. እርድ

እርድ ከሐጅ ተግባር ጋር የተያያዘ ስርዓት ነው። በአላህ ስም ይታረዳል። ስጋው ለድሆች ይሰጣል።

وَالْبُدْنَ جَعَلْنَاهَا لَكُم مِّن شَعَائِرِ اللَّهِ لَكُمْ فِيهَا خَيْرٌ فَاذْكُرُوا اسْمَ اللَّهِ عَلَيْهَا صَوَافَّ فَإِذَا وَجَبَتْ جُنُوبُهَا فَكُلُوا مِنْهَا وَأَطْعِمُوا الْقَانِعَ وَالْمُعْتَرَّ كَذَٰلِكَ سَخَّرْنَاهَا لَكُمْ لَعَلَّكُمْ تَشْكُرُونَ

“ግመሎችንም ከአላህ ምልክቶች አደረግናቸው። ከነርሱ (ብዙ) መልካም ነገሮችን ታገኛላችሁ። ስለዚህም (ለእርድ) በረድፍ በቆሙ ጊዜ የአላህን ስም አውሱ። (ከታረዱም በኋላ) በጐቻቸው በወደቁ ጊዜ (ከሥጋዎቻቸው) ተመገቡ። መለመን የማይከጅሉ (ችግረኞችንም)፣ ለማኝንም መግቡ። በዚህ አኳኋን እርሷን (ግመሏን) ገራንላችሁ፤ ታመሰግኑ ዘንድ።” (አል-ሐጅ 22፤ 36)

አላህ እርድን የሚቀበልበትን ስሜትና ኒያ እንዲህ ሲል ገልጿል፡-

لَن يَنَالَ اللَّهَ لُحُومُهَا وَلَا دِمَاؤُهَا وَلَٰكِن يَنَالُهُ التَّقْوَىٰ مِنكُمْ
 

“ሥጋዎችዋም ወይም ደሞቿም አላህን አያገኙም። ግና የሚያገኘው እርሱን የመፍራት ስሜታችሁ ነው።” (አል-ሐጅ 22፤ 37)

እንዲህም ብሏል፡-

قَالَ إِنَّمَا يَتَقَبَّلُ اللَّهُ مِنَ الْمُتَّقِينَ

“አላህ የሚቀበለው እርሱን የሚፈሩትን (ሰዎች ቁርባን ነው)” (አል-ማኢዳህ 5፤ 27)

የእርድ ስርዓት የሚፈጸምበት ሁኔታ ከፊቅህ መጽሐፍት ውስጥ በዝርዝር ማግኘት ይቻላል።

ስለ ሐጅ ተግባር ተጨማሪ ማብራሪያዎችም በፊቅህ መጽሐፍት ውስጥ ይገኛ ። ለበለጠ ግንዛቤ እነርሱን ማንበብ ጠቃሚ ነው።

_________

ምንጭ፡- “ኢስላም ድንቅ እምነት ድንቅ ሕይወት” በሐሰን ታጁ፣ አልበያን ሊሚትድ።

*****

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here