ሐጅ (ክፍል 1)

0
8161

ሐጅ አምስተኛው የኢስላም መሠረት ነው። በአካልም በቀልብም በገንዘብም የሚሰራ ኢባዳ ነው። ይህ ከሌሎች ኢባዳዎች ሁሉ ለየት ያደርገዋል። የገንዘብ አቅም ያላቸው ሙስሊሞች በሐጅ ወቅት ወደመካ በመሄድ ይፈጽሙታል። ይህ ኢባዳ በንጹህ ንያ፣ የተለመደ አለባበስንና አኗኗርን ትቶ የኢህራም ልብስ በመልበስ ይጀመራል። የአላህን ቤት በመጎብኘትና የተወሰነለትን ሥርዓቶች በመፈጸም ይጠናቀቃል።

በውስጡ በርካታ የኢባዳ ስርዓቶችና ተግባራት አሉት። በፊቅህ መጽሐፍ ውስጥ ዝርዝራቸው ይገኛል።

ሐጅ- ከኢስላም በፊት

አንድን የተቀደሰ ቦታ ሄዶ መጎብኘትና ከዚያ ቦታ ላይ አምልኮ መፈጸም ከኢስላም በፊትም የተለያዩ ሕዝቦች ሲፈጽሙት ኖረዋል። የጥንት ግብጻዊያን፣ ግሪኮች፣ ጃፓናውያንና ሌሎችም ሕዝቦች እንዲህ ዓይነት የአምልኮ ስርዓት ያከናውኑ እንደነበር ይነገራል። (አል-ኢስላም አቂደቱን ወሸሪዓ ገጽ 113)

ዓረቦችም ከነቢዩ ሙሐመድ መላክ በፊት በተከበረው የካእባ መስጊድ የሐጅ ስርዓት ይፈጽሙ እንደነበር ታሪክ ያወሳል። ይህ በእንዲህ እንዳለ አላህ ለኢብራሂም የርሱ ስም የሚወሳበትና በብቸኝነት በሚመለክበት ቤት ያንጹ ዘንድ አዘዛቸው፡-

وَإِذْ بَوَّأْنَا لِإِبْرَاهِيمَ مَكَانَ الْبَيْتِ أَن لَّا تُشْرِكْ بِي شَيْئًا وَطَهِّرْ بَيْتِيَ لِلطَّائِفِينَ وَالْقَائِمِينَ وَالرُّكَّعِ السُّجُودِ ﴿٢٦﴾ وَأَذِّن فِي النَّاسِ بِالْحَجِّ يَأْتُوكَ رِجَالًا وَعَلَىٰ كُلِّ ضَامِرٍ يَأْتِينَ مِن كُلِّ فَجٍّ عَمِيقٍ ﴿٢٧﴾ لِّيَشْهَدُوا مَنَافِعَ لَهُمْ وَيَذْكُرُوا اسْمَ اللَّهِ فِي أَيَّامٍ مَّعْلُومَاتٍ عَلَىٰ مَا رَزَقَهُم مِّن بَهِيمَةِ الْأَنْعَامِ فَكُلُوا مِنْهَا وَأَطْعِمُوا الْبَائِسَ الْفَقِيرَ
 

“ለኢብራሒምም የቤቱን (የካእባን) ስፍራ መመለሻ ባደረግንለት ጊዜ በኔ ምንንም አታጋራ ቤቴንም ለሚዞሩትና ለሚቆሙበት ለሚያጎነብሱትና በግንባራቸውም ለሚደፉት ንጹሕ አድርግላቸው (ባልነው ጊዜ አስታውስ)። (አልነውም) በሰዎችም ውስጥ በሐጅ ትእዛዝ ጥራ። እግረኞች ከየሩቅ መንገድ በሚመጡ ከሲታ ግመሎችም ሁሉ ላይ ኾነው ይመጡሃልና። ለነሱ የኾኑ ጥቅሞችን ይጣዱ ዘንድ፤ በታወቁ ቀኖችም ውስጥ ከለማዳ እንስሳዎች በሰጣቸው ሲሳይ ላይ የአላህን ስም ያወሱ ዘንድ፣ (ይመጡሃል)፣ ከርሷም ብሉ፣ ችግረኛ ድኻንም አብሉ።” (አል-ሃጅ 22፤ 26- 28)

በሐጅ ወቅት ሙስሊሞች ከሁሉም ማእዘናት ወደ መካ ይጎርፋሉ። በአንድ መስክ ይሰባሰባሉ። ከምስራቅ፣ ከምእራብ፣ ከሰሜንና ከደቡብ ተጠራርተው ይገናኛሉ። ከሺዎች አመታት በፊት ነቢዩ ኢብራሂም ላደረጉት ጥሪ ምላሽ ይሰጣሉ። እርሳቸው ለጻእዳን የገነቡትን ቤት ለመጎብኘት ይሄዳሉ። “ለበይክ” ይላሉ ሁሉም በአንድ ድምጽ። “አቤቱ ብለናል ጌታችን። የባሪያህን የኢብራሂምን ጥሪ ሰምተን መጥተናል።”

የኢብራሂም ጥሪ እጅግ ይገርማል። ተአምረኛ ጥሪ። ዘመናትን ሰንጥቆ የሚያስተጋባ፣ እሰከ እለተ ቂያማ ማስገምገሙን የሚቀጥል ጥሪ። ትውልድ ሁሉ ይሰማዋል። እርሱ ወደ ፈለቀበት አቅጣጫም ይጎርፋል። የተባረከ ጥሪ።

ከላይ የሰፈሩት አናቅጽ ወደዚህ ጥሪ ታሪክ ይመልሱናል። የሐጅን መነሻ ያስታውሱናል። የሐጅን ታሪካዊ አመጣጥ ቁሳዊና መንፈሳዊ ፋይዳ ይነግሩናል።

ካእባ የተገነባበት ዓላማ

ያ ቤት የተገነባው በታላቁ ኢብራሂም እጆች፣ የታነጸው ለታላቅ ዓላማ ነበር። የሰው ልጆችም ሆኑ አጋንንት ለተፈጠሩለት ቁም ነገር። ለተውሂድ። ይህን እውነታ ከአንቀጾቹ ላይ በጉልህ ተመልክተዋል። “በኔ ምንንም አታጋራ።” የሚለው ቃል የካእባን ዓላማ ያሳያል። ቤቱ የቆመለት ዓላማ፣ የታነጸበት መሠረት ይህ ነበር።

አላህ ለኢብራሂም ቦታውን አመላከታቸው። በተውሂድ መሠረት ላይ እንዲያቆሙት አዘዛቸው። የርሱ ብቻ ቤት መሆኑን ገለጸ። ሌላ የማይመለክበት፣ ሌላ የማይጠራበት፣ ሌላ የማይወሳበት።

እንዲያጸዱትም ነገራቸው፣ ለኢብራሂም። ለነማን? እርሱን ብቻ ለሚያመልኩ፣ ለሌላ ሃይል ለማያጎበድዱ ሰዎች። ለተውሂድ ባለቤቶች።

“ቤቴንም ለጎብኝዎች፣ ለሚቆሙባት ሩኩእና ሱጁድ ለሚያደርጉት ባሮቼ አጽዳ።”

ተአምረኛ ጥሪ

ኢብራሂም ቤቱን በታዘዙት መልክ አንጸው ሲያጠናቅቁ ያን ታሪካዊ ጥሪ እንዲያሰሙ፣ ዝንተ ዓለም የሚሰማ ድምጻቸውን እንዲያስተጋቡ፣ ለሰው ልጆች የሃጅን አዋጅ እንዲያስተላልፉ ታዘዙ። “ኑ፣ የአላህን ቤት ጎብኙ። ከተከበረ ጓዳው አወድሱት። በአንድ ሆናችሁ ቀድሱት።” እንዲሉ።

ጥሪያቸውም ሰሚ እንደሚያገኝ፣ የሰው ልጆች ከሁ ም አቅጣጫ ወደዚያ ቤት እንደሚጎርፍ ቃል ተገባላቸው።

“በሰዎችም ውስጥ በሐጅ ትእዛዝ ጥራ፣ እግረኞችም ከየሩቅ መንገድ በሚመጡ ከሲታ ግመሎችም ላይ ሆነው ይመጡሃልና።”

ኢብራሂም ጥሪ አደረጉ። ጥሪያቸው ከአጥናፍ አጥናፍ ተሰማ..።

አላህ ለኢብራም የገባው ቃል ትናንት ተፈጽሟል። ዛሬም በመፈጸም ላይ ነው። ነገም ተፈጻሚነቱ ይቀጥላል። በአለፉት ሺዎች ዓመታት ቢሊዮኖች ለዚህ ጥሪ ምላሽ ሰጥተዋል። ኢብራሂም ወደ አነጹት ቤት ጎርፈዋል። “ለበይክ” እያሉ ተመዋል። “ለበይክ አላሁመ ለበይክ፣ የባሪያህን ድምጽ ስምተን መጥተናል።”

ዛሬም የሚሊዮኖች ቀልብ ያን ቤት እጅግ ያፈቅራል። ሊያየው፣ ሊጎበኘው፣ አላህን ሊያመልክበት፣ ስለ ሃጢያቱ ሊያለቅስበት ይመኛል። ዛሬም ብዙ ሚሊዮኖች ይወዱታል። ከራሳቸው ቀዬና ምድር በላይ ይሳሱለታል። የቻሉት ሃብታቸውን አፍሰው ያዩታል። ያልቻሉት በሩቅ ይናፍቁታል። በፍቅር ያለቅሱለታል..።

የኢብራሂም ጥሪ አስተጋባ። ከልብ የወጣ ጥሪ ። በቢልዮኖች ጆሮ ተሰማ። ከሁሉም በጎ ምላሽ አገኘ። የአላህ ቃልኪዳን ተረጋገጠ። ተአምሩ ተፈጸመ። የቤቱ ክብር ገነነ። የታነጸለት አላማ ተውሂድ ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬ የብዙዎቹ ሕይወት አንኳር ቁም ነገር ሆነ። ከፍጡራን ባርነት ጸድቶ ለአንድ አምላክ ብቻ ማደር፤ ከዚህች ዓለም ጠባብ ሕይወት ወደ መጪው ዓለም ስፋት፣ ከሌሎች እምነቶችና ሥርዓቶች ጭቆና ወደ ኢስላም ፍትሕ መሸጋገር።

ቁሳዊ ፋይዳ

አንቀጾቹ የሃጅን መነሻ እንዲህ ካወሱልን በኋላ ፋይዳዎች እንዳሉት ይጠቁሙናል።

“ለነርሱ የሆኑ ጥቅሞችን ይጣዱ ዘንድ”

ሐጃጆች ከሐጅ የሚያገኙዋቸው ጥቅሞች እጅግ በርካታ ናቸው። መንፈሳዊም ዓለማዊም ፋይዳዎች። የንግድ ሰዎች በገፍ ገበያ ያገኙበታል። አንድ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢትና ባዛር በያመቱ ሐረም ላይ ይዘጋጃል። ሚሊዮኖች ይህን ትርኢት ይጎበኙታል።

መንፈሳዊ ፋይዳ

በሐጅ የላቀ መንፈሳዊ ፋይዳም ይገኛል። ነፍስ ትጸዳለች። በተከበረው ቤት ውስጥ ወደ አላህ ይበልጥ የመቃረብ ስሜት ይሰማታል። ሕሊና በርካታ የሩቅም የቅርብም ዘመን ትዝታዎች ያስተናግዳል።

ኢብራሂምን ያስታውሳል። የሚወዷትን ባለቤታቸውንና የአብራካቸውን ክፋይ ልጃቸውን ከባዶ በረሃ ላይ ለአላህ አደራ ሰጥተው ሲሄዱ፣ እንዲህ እያሉ ሲለምኑት፡- “ጌታችን ሆይ ዘሮቼን አንድም አዝርእት በሌለበት ሸለቆ ውስጥ ከተከበረው ቤትህ አጠገብ ትቻቸዋለሁ። ጌታችን ሆይ .. ቀልቦች ሁሉ ወደ እነርሱ እንዲዘነበሉ አድርግ። ያመሰግኑህም ዘንድ ከፍራፍሬዎች ለግሳቸው።”

ሃጀርን ያስታውሳል። በዚያ በረሃ ውስጥ ለሷና ለልጂዋ ውሃ ፍለጋ ከሶፋና መርዋ ኮረብታዎች መሃል ስትባዝን። ጥም አቃጥሏት። ከ 7 ጊዜ ምልልስ በሁዋላ ውሃ ከምድር ፈልቆ ስታገኝና በደስታ ስትዋጥ። ያ የተከበረው ውሃ ዘምዘም ነው። በደረቅ በረሃ ውስጥ የፈነዳ የአላህ በረከት መገለጫ።

ኢብራሂምም ትዝ ይሉታል። ልጅ አልባ መሆናቸው ታስቧቸው አላህን ልጅ ሲለምኑት፤ እርሱም በጎ ምላሽ ሲሰጣቸው፤ እድሜያቸው ከገፋ በኋላ ኢስማኢልን ሲወልዱ፤ እርሱ እድሜው በጨመረ ቁጥር የርሳቸው ደስታና ተስፋም አብሮ ሲጨምር፤ በድንገት ግን ልጃቸውን፣ ተስፋቸውን፣ ኢስማኢልን እንዲያርዱ ሲታዘዙ ጭንቀታቸው ይታወሰዋል። “ልጄ ሆይ፣ በሕልሜ እንዳርድህ ታዘዝኩ። ምን ታስባለህ?” ሲሉት። ኢስማኢልም ቅንጣት ሳያመነታ የአላህን ትእዛዝ ሲቀበል፡- “አባዬ ሆይ፣ የታዘዝከውን ፈጽም። በአላህ ፈቃድ ታዛዥ ሆኘ ታገኘኛለህ።” ሲላቸው በሕሊናው ይታሰበዋል። አባት ልጃቸውን፣ ልጅ ሕይወቱን ለአላህ ክብር ሲለግሱ፤ አላህ መስዋዕት በመላክ ሁለቱንም ከጭንቀት ሲታደጋቸው ያስታውሳል።

አባትና ልጅ የአላህን ቤት ለማቆም ደፋ ቀና ሲሉም ይታወሰዋል። እንዲህ እያሉ ሲማጸኑት፤

“ጌታችን ሆይ ስራችንን ተቀበለን። አንተ ሰሚም አዋቂም ነህና። ጌታችን ሆይ ሙስሊሞች አድርገን። ከዝርያችንም ሙስሊም ሕዝብ አድርግልን።..”

ምዕተ አመታትን ተሻግሮ ነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) ያስታውሳል። እኒህ ታላቅ ስብእና የወጡበትን መስክ በአድናቆት ይመለከታል። መላ ሕይወታቸው ባይነሕሊና በረድፍ ይታየዋል። የሕፃንነት ጊዜያቸው፣ ሕይወታቸው፣ ለሰው ልጆች ደህንነት ሲሉ የከፈሉት ግዙፍ መስዋእትነት፣ አቻ የለሽ ትግላቸው፣ ያ ሁሉ ልፋትና ድካም፣ ስደቱ፣ መዲና ውስጥ የመጀመሪያ ትውልዱ አባት ሆነው ሲያሰግዱ፣ መምህር ሆነው ሲያስተምሩ፣ መንበር ላይ ሆነው ኹጥባ ሲያሰሙ፣ ሃገር ሲመሩ..።

ያ ትውልድም ይመጣበታል። ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ኮትኩተው ያሳደጉት ድንቅ ማሕበረሰብ። አቡበከርና ኡመር፣ ኡስማንና አሊ፣ ጦልሃና ዙበይር፣ እነ አኢሻ፣ እነ ኢብኑአባስ፣ እነ ኢብኑ መስኡድ.. ሁሉም በአይነ ሕሊናው በረድፍ ያልፋሉ።

ይህ ሁሉ ትዝታ መንፈስን ያበለጽጋል። እምነትን ያጎለብታል። ስሜትን ያድሳል።

ዓለማቀፋዊ ጉባኤ

ሐጅ ከዚህም በቀር አለማቀፍ ጉባኤ ነው። ሙስሊሞች በአንድ እምነት ሥር ለአንድ ዓላማ በየአመቱ በእኩልነት የሚያካሂዱት ታላቅ ስብሰባ ነው። ዘር፣ የቆዳ ቀለም፣ ሃገር ሳይለያያቸው የአንድነታቸው መገለጫ የሆነውን ተመሳሳይ ልብስ ለብሰው ይህን ጉባኤ ያካሂዳሉ።

አላህ (ሱ.ወ) ወዳጆቹ፣ ሕዝቦቹ የሚገናኙበት፣ የሚተዋወቁበት በረከቱን የሚያወድሱበት የሚወያዩበት መድረክ አመቻችቶላቸዋል። ሙስሊሙ ሕዝብ በአንድ እንዲሰባሰበብ፣ እንዲዋደድ፣ እንዲፋቀር፣ ፍጹም አንድ እንዲሆን፤ አንድ ሕዝብ፣ አንድ መርህ፣ አንድ እምነት፣ አንድ አላማ፣ የዚህ ውሕደት እና አንድነት አንዱ መገለጫ መንገድ ሐጅ ነው። የቦታ ርቀት ሳይበግራቸው፣ ቋንቋና የዘር መጋረጃ ሳይጋርዳቸው፣ ለአንድ ዓላማ፣ በአንድ ልብ፣ ከምእራብ፣ ከምስራቅ፣ ከሰሜን፣ ከደቡብ ተጠራርተው፣ አንድ አይነት ለብሰው፣ በአንድ ቦታ ቆመው፣ ፊታቸውን ወደ አንድ አቅጣጫ አዙረው፣ አንድ ጌታን እያወሱ፣ ለሱ እያለቀሱ ሊዋደዱ፣ ችግሮቻቸውን በጋራ ሊያስወግዱ፣ ሊማማሩ፣ ሊመካከሩ፣ ሲገናኙ ከዚህ የበለጠ ውሕደት፣ ከዚህ የበለጠ አንድነት ይኖር ይሆን? የባሕል፣ የንግድ፣ የተሞክሮ፣ ልውውጥ ያደርጋ ። በአላህ ቤት ውስጥ። በአላህ ጥላ ሥር።

ሁሉም ትውልድ እንደ አቅሙና እንደየሚገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ ከሃጅ ይጠቀማል። አላህ ሃጅን በሙስሊሞች ላይ ሲደነግግ፣ ኢብራሂምን ጥሪ እንዲያስተጋቡ ሲያዝ፣ ለሙስሊሞች ካቀደላቸው ጥቅሞች ጥቂቶቹ እነኚህ ናቸው። “ጥቅሞቻቸውን ሊጣዱ..”

ለኢስማኢል ፊዳ ሆኖ ከሰማየ ሰማያት የወረደውን በግ ለማስታወስ ሐጃጆቹ መስዋእት ያቀርባሉ። መስዋእቱ ከዚህም በላይ ኢባዳ ነው። ድሆችም ከእርዱ ይመገባሉ።

ባጠቃላይ ከልብ በመነጨ ኒያ ወደ ሐጅ የተጓዘ ሙስሊም እነኝህንና ሌሎችንም ብዙ፣ በጣም ብዙ ቁም ነገሮችን ያገኛል። ውሃ ከማይፈልቅበት፣ እርጥበት ከማይታይበት፣ ለአይን እንኳ ለምለም ዛፍ ከጠፋበት፣ ጭው ያለ ደረቅ በረሃ ውስጥ ኢስላም ለአለም አለኝታን ለተጨቆኑት መከታ ለመሆን ከዘላን ሕዝቦች መሃል መፍለቁን ለ 1400 ዓመታት ያህል ወደ ኋላ ተመልሶ በአጽንኦት ማስታወሱ ብቻ በቂ ነው።

ያ ጀግና ትዉልድ፣ ያ ተአምረኛ ትውልድ ዓለምን ሊመራ፣ የአዳምን ዘር ከብዙ አማልክት ባርነት ወደ አንድ አምላክ አምልኮ ነፃነት፣ ከጠባብ ቁሳዊ ሕይወት ወደ ሰፊው ብሩህ እምነት፣ ከሰው ሰራሽ ስርዓቶችና እምነቶች ጭቆና ወደ ኢስላም ፍትሕ ሊያሸጋግር ከዚያ አሸዋማ መሬት የፈለቀ መሆኑን ማስታወስ ብቻ ወደር የለሽ ደስታን ይለግሳል።

የታዛዥነት ተምሳሌት

የሐጅ ክንውኖች ለአላህና ለመልእክተኛው የመታዘዝ ተምሳሌቶች ናቸው። ክንውኖቹ ትርጉም ባይገባቸውም አድርጉ ስለተባሉ ብቻ ይፈጽሙታል። ጠዋፍ፣ ዓረፋ ላይ መቆሙ፣ ጸጉርን መላጨቱ ወይም ማሳጠሩ፣ ጠጠር መወርወሩ እና ሌሎችም የሐጅ ክንውኖች የዚህ ታዛዥነት መገለጫዎች ናቸው።

ሙስሊም በሁ ም ሕይወቱ እንዲያ ሊሆን ይገባል። አላህና መልእክተኛው ያዘዙትን ይፈጽማል። የታዘዘበት ነገር ሚስጥር ባይገባውም።

የመልካም ስነ ምግባራት መማሪያ

በሐጅ ሙስሊም መልካም ስነ ምግባራትን ይማራል።

  • ትእግስትንና ትጋትን ይማራል። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

أفضل الجهاد حج مبرور

“በላጬ ጅሃድ ተቀባይነትን ያገኘ ሐጅ ነው።” (ቡኻሪ)

  • በዘውትራዊ ዒባዳ ውስጥ መሆንን ይማራል። ለብዙ ቀናት ከኢባዳ ወደ ኢባዳ ሲዘዋወር ይኖራልና።
  • ሩህሩህና አዛኝ መሆንን ይማራል።
  • ስሜቱን መቆጣጠር፣ ቁጣውን መግታትን ይማራል።
  • በምላሹ ምንም ነገር ሳይጠብቅ- ገንዘቡን በአላህ መንገድ ማውጣትን ይማራል።
  • አላህ ያላቀውን ማላቅን፣ አላህ ያሳነሰውን ማሳነስን፣ አላህ የወደደውን መውደድን፣ እርሱ የጠላውን መጥላትን ይማራል።
  • በሐጅ ከአላህ ጋር ያለውን ግንኙነት ያጠናክራል። በአላህ ቤት ውስጥ እንግዳ ነውና። አላህ እንግዳውን ይረዳል፤ ይንከባከባል።
  • ሐጅ የስልጠና ማዕከል ነው። ሙስሊሞች ከየዓለማት ማእዘናቱ ተሰባስበው ስልጠናውን ይወስዳሉ። አላህን የማምለክ ስልጠና፣እርስ በርስ የመፋቀር፣ ስህተትን የማለፍ፣ የመታገስ፣ ከራስ ይልቅ ለወንድም የማሰብ ስልጠና… ወዘተ በየቤታቸው የሚያገኟቸውን ምቾቶች ሁሉ ጥለው ይህን ስልጠና ይወስዳሉ።
  • ሐጅ በጥቅሉ በርካታ ስነ ምግባሮች የምንማርበት ማእከል ነው።

አላህ እንዲህ ብሏል፡-

الْحَجُّ أَشْهُرٌ مَّعْلُومَاتٌ فَمَن فَرَضَ فِيهِنَّ الْحَجَّ فَلَا رَفَثَ وَلَا فُسُوقَ وَلَا جِدَالَ فِي الْحَجِّ

“የሐጅ (ጊዜ) የታወቁ ወራት ናቸው። በነኝህ (ወራት) ውስጥ ሐጅን በራሱ ላይ ግዳጅ ያደረገ ሐጅ ውስጥ ከሴት ጋር መገናኘት፣ (በአላህ ላይ) ማመጽም፣ (ከባልደረቦች) ጋር መከራከርም የለበትም።” (አል-በቀራህ 2፤ 197)

መጭውን ዓለም ማስታወስ

ሐጅ አድራጊ የኢህራም ልብስ ለቀናት ለብሶ ይቆያል። የተለመደ ልብሱን አውልቆ። ይህ የሐጅ አለባበስ ለሞት መገነዝን ያስታውሳል። የእያንዳንዱ ሰው ፍጻሜ ይህው ነው። ለኢህራም በሚለብሳት አይነት ብጣሽ ጨርቅ ተጠቅልሎ ነው ቀብር የሚገባው።

كُلُّ نَفْسٍ ذَائِقَةُ الْمَوْتِ ثُمَّ إِلَيْنَا تُرْجَعُونَ

“እያንዳንዷ ነፍስ ሞትን ቀማሽ ናት። ከዚያም ወደኛ ትመለሳላችሁ።” (አል-አንከቡት 29፤ 57)

የዓረፋ ቀን መቆሙ፣ ሁሉም ራቁት ሊባል በሚችል ቁራጭ ጨርቅ ሆኖ ልዩ ልዩ ኢባዳዎችን ለማከናወን የሚታየው ትርምስ መጭውን ዓለም ያስታውሳል። የሰው ልጅ ያኔም እንዲህ ይተራመሳል። ያኔም እንዲህ ይጋፋል። አረፋ ላይ እንደሚቆመው የአላህን ፍርድ ፍለጋም ይቆማል። አላህ እንዲህ ብሏል፡-

يَا أَيُّهَا النَّاسُ اتَّقُوا رَبَّكُمْ إِنَّ زَلْزَلَةَ السَّاعَةِ شَيْءٌ عَظِيمٌ ﴿١﴾ يَوْمَ تَرَوْنَهَا تَذْهَلُ كُلُّ مُرْضِعَةٍ عَمَّا أَرْضَعَتْ وَتَضَعُ كُلُّ ذَاتِ حَمْلٍ حَمْلَهَا وَتَرَى النَّاسَ سُكَارَىٰ وَمَا هُم بِسُكَارَىٰ وَلَٰكِنَّ عَذَابَ اللَّهِ شَدِيدٌ

“እናንተ ሰዎች ሆይ! ጌታችሁን ፍሩ። የሰዓቷ (የትንሳኤ) ነውጥ እጅግ አስፈሪ ነውና። በምታይዋት ቀን አጥቢ እናቶች የሚያጠቧቸውን ልጆቻቸውን ይረሳሉ። እርጉዞች ይጨነግፋሉ። ሰዎች የሰከሩ ሆነው ታያቸዋለህ። ግና (ጠጥተው) የሰከሩ አይደሉም። የአላህ ቅጣት እጅግ ብርቱ (እና አስፈሪ) ከመሆኑ የተነሳ እንጅ።” (አል-ሐጅ 22፤ 1-2)

_________

ምንጭ፡- “ኢስላም ድንቅ እምነት ድንቅ ሕይወት” በሐሰን ታጁ፣ አልበያን ሊሚትድ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here