ኢስላምን ማስተዋወቅ

0
5048

ኢስላም ማለት ምን ማለት ነው?

ኢስላም ማለት የአላህ (ሱ.ወ) አንድነትን በማወቅና በማመን ለርሱ እጅ መስጠት፣ ለፍላጎቱና ትዕዛዛቱ ማደር፣ ተግባራዊ ለማድረግም በታዛዥነት መንፈስ መንቀሳቀስ፣ ከሽርክ (በአምልኮ ሌላን አካል ከርሱ ጋር ማጋራት) መጽዳት ነው። ይህም አላህ (ሱ.ወ) ያዘዛቸውን ነገሮች በመፈጸምና የከለከላቸውን ደግሞ በመራቅ ይረጋገጣል።ኢስላም ከላይ በተሰጠው ትርጓሜ መሰረት በአላህ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ብቸኛና እውነተኛ ሐይማኖት ነው፤

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል

إِنَّ الدِّينَ عِندَ اللَّهِ الْإِسْلَامُ
 

“አላህ ዘንድ (የተወደደ) ሃይማኖት ኢስላም ብቻ ነው።” (አሊ-ዒምራን 3፤91)

አላህ (ሱ.ወ) ለመልክተኞቹና ነብያቶቹ በየዘመኑ ያወረዳቸው ህግጋቶች የተለያዩ ቢሆኑም ለሁለም ነብያትና ህዝቦች የወረዱት ህግጋቶች የአላህን አንድነት በማስተማር፣ ለሰው ልጆች ጠቃሚ ነገሮችን በማረጋገጥና ወደ መልካም ሥነ-ምግባር ጥሪ በማድረግ ያለቸው አስተምህሮት ተመሳሳይ ነው። እንደየ ዘመኑ ሁኔታና ለሰዎች ኑሮ አስፈላጊነት አኳያ አንዳንድ ህጎች ላይ ልዩነቶች ያሉ ሲሆን ከዚሁ ጋር ተያይዞ በየዘመኑ የወረዱት የአላህ (ሱ.ወ) ህግጋቶች ያላቸውም ስፋትና ጥበት የተለያየ ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል

لِكُلٍّ جَعَلْنَا مِنكُمْ شِرْعَةً وَمِنْهَاجًا
 

“ከእናንተ ለሁሉም ሕግንና መንገድን አደረግን።” (አል-ማኢዳ 5፤48)

ከሰማይ የወረዱት መለኮታዊ ህግጋቶች በብዙ ጉዳዮ ላይ ተመሳሳይነት ይንጸባረቅባቸዋል፤ ከነዚህም ውስጥ፡

1. መነሻ (ምንጭ)

የመለኮታዊ ህግጋቶች ምንጭ ከብቸኛውና አንዱ አምላክ አላህ.(ሱ.ወ) ስለሆነ ደረጃው ከፍ ያለ ነው፤ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል

إِنَّا أَوْحَيْنَا إِلَيْكَ كَمَا أَوْحَيْنَا إِلَىٰ نُوحٍ وَالنَّبِيِّينَ مِن بَعْدِهِ
 

“እኛ ወደ ኑሕና ከርሱ በኋላ ወደ ነበሩት ነቢያት እንዳወረድን ወደ አንተም አወረድን።” (አን-ኒሳእ 4፤163)

2. አላማ

መለኮታዊ ህጎች ከአላማዎች መካከል፡-

  • ሰዎችን ለጌታቸው ተገዥዎች እንዲሆኑ ማድረግ። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል

وَمَا أَرْسَلْنَا مِن قَبْلِكَ مِن رَّسُولٍ إِلَّا نُوحِي إِلَيْهِ أَنَّهُ لَا إِلَٰهَ إِلَّا أَنَا فَاعْبُدُونِ

“ከአንተ በፊትም እነሆ ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ በማለት ወደርሱ የምናወርድለት ቢኾን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም።” (አል-አንቢያእ 21፤25)

በሌላ የቁርኣን አንቀጽም አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

وَلَقَدْ بَعَثْنَا فِي كُلِّ أُمَّةٍ رَّسُولًا أَنِ اعْبُدُوا اللَّهَ وَاجْتَنِبُوا الطَّاغُوتَ فَمِنْهُم مَّنْ هَدَى اللَّهُ وَمِنْهُم مَّنْ حَقَّتْ عَلَيْهِ الضَّلَالَةُ فَسِيرُوا فِي الْأَرْضِ فَانظُرُوا كَيْفَ كَانَ عَاقِبَةُ الْمُكَذِّبِينَ

“በየሕዝቡም ሁሉ ውስጥ ‘አላህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ’ በማለት መልክተኛን በእርግጥ ልከናል። ከእነሱም ውስጥ አላህ ያቀናው ሰው አልለ። ከእነሱም ውስጥ በእርሱ ላይ ጥመት የተረጋገጠበት ሰው አልለ። በምድርም ላይ ኺዱ፤ የአስተባባዮችም መጨረሻ እንዴት እንደ ነበረ ተመልከቱ።” (አን-ነህል 16፤36)

  • ሰዎች ጌታቸውን እሱ በደነገገው ህግጋትና ባዘዘው መሰረት በፍቅርና በፍቃደኝነት መገዛት። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

إِنَّمَا كَانَ قَوْلَ الْمُؤْمِنِينَ إِذَا دُعُوا إِلَى اللَّهِ وَرَسُولِهِ لِيَحْكُمَ بَيْنَهُمْ أَن يَقُولُوا سَمِعْنَا وَأَطَعْنَا وَأُولَٰئِكَ هُمُ الْمُفْلِحُونَ

“የምእምናን ቃል የነበረው ወደ አላህና ወደ መልክተኛው በመካከላቸው ሊፈርድ በተጠሩ ጊዜ ሰማን፤ ታዘዝንም ማለት ብቻ ነው። እነዚህም እነሱ የፈለጉትን የሚያገኙ ናቸው።” (አን-ኑር 24፤51)

3. አጠቃላይ ጽንሰ ሐሳቦች

መለኮታዊ ህጎች ጠቅላላ በሆኑ ጽንሰ ሐሳቦች ዙሪያ ተመሳሳይ አቋም አላቸው፤ ለምሳሌ ሁለም ሰው የስራውን እንደሚያገኝ፤ ጥሩ የሰራ ጥሩ ምንዳ እንደሚከፈለውና መጥፎ የሰራ ደግሞ ቅጣት እንደሚገባው፤ አንድ ሰው በሌላ ሰው ወንጀል እነደማይጠየቅና ከራሱ ሥራ ውጭም እንደማያገኝ ሁሉም መለኮታዊ ህጎች ይስማማሉ። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

أَمْ لَمْ يُنَبَّأْ بِمَا فِي صُحُفِ مُوسَىٰ ﴿٣٦﴾ وَإِبْرَاهِيمَ الَّذِي وَفَّىٰ ﴿٣٧﴾ أَلَّا تَزِرُ وَازِرَةٌ وِزْرَ أُخْرَىٰ ﴿٣٨﴾ وَأَن لَّيْسَ لِلْإِنسَانِ إِلَّا مَا سَعَىٰ ﴿٣٩﴾ وَأَنَّ سَعْيَهُ سَوْفَ يُرَىٰ ﴿٤٠﴾ ثُمَّ يُجْزَاهُ الْجَزَاءَ الْأَوْفَىٰ

“ይልቁንም በዚያ በሙሳ ጽሑፎች ውስጥ ባለው ነገር አልተነገረምን? በዚያም (የታዘዘውን) በፈጸመው በኢብራሂም (ጽሑፎች ውስጥ ባለው አልተነገረምን?) (እርሱም ኃጢያት) ተሸካሚ ነፍስ የሌላይቱን ነፍስ ኃጢኣት አትሸከምም። ለሰውም ሁሉ የሠራው እንጅ ሌላ የለውም። ሥራውም ሁሉ ወደ ፊት ይታያል። ከዚያም ሙሉውን ምንዳ ይመነዳዋል።” (አን-ነጅም 53፤36-41)

ያለፉት መለኮታዊ ህጎችና መመሪያዎች ሁሉ ለአላህ. (ሱ.ወ) መታዘዝንና ከሰው ልጅ በመረጣቸው መልክተኞቹ አንደበት በደነገገው ህግ መሰረትም እርሱን ብቻ ማምለክን ያስተምራሉ።

የመጀመሪያው መልክተኛ ነቢ ኑህ (ዐ.ሰ) እንዲህ ይላሉ፡-

وَأُمِرْتُ أَنْ أَكُونَ مِنَ الْمُسْلِمِينَ

“ከሙስሊሞች እንድሆንም ታዝዣለሁ።” (አን-ነምል 10፤91)

የነብያቶች አባት በመባል የሚታወቁት ነብዩላህ ኢብራሂምና ልጃቸው ኢስማዒልም እንድህ ይላሉ፡-

رَبَّنَا وَاجْعَلْنَا مُسْلِمَيْنِ لَكَ وَمِن ذُرِّيَّتِنَا أُمَّةً مُّسْلِمَةً لَّكَ وَأَرِنَا مَنَاسِكَنَا وَتُبْ عَلَيْنَا إِنَّكَ أَنتَ التَّوَّابُ الرَّحِيمُ

“ጌታችን ሆይ! ላነተ ታዛዦችም አድርገን። ከዘሮቻችንም ላንተ ታዛዦች ሕዝቦችን (አድርግ)። ሕግጋታችንንም አሳየን፤ (አሳውቀን)። በኛም ላይ ተመለስን፤ አንተ ጸጸትን ተቀባዩ ሩኅሩኅ አንተ ብቻ ነህና።” (አል-በቀራ 2፤128)

ነቢዩላህ ኢብራሂምና ነቢዩላህ የዕቁብም (ዐማ.ሰ) ዝርዮቻቸው ትክክለኛውን የአላህ ዲን ኢስላምን ብቻ ይዘው እንዲኖሩና እንዲሞቱ አደራ ሲሰጡ እንድህ ብለዋል

وَوَصَّىٰ بِهَا إِبْرَاهِيمُ بَنِيهِ وَيَعْقُوبُ يَا بَنِيَّ إِنَّ اللَّهَ اصْطَفَىٰ لَكُمُ الدِّينَ فَلَا تَمُوتُنَّ إِلَّا وَأَنتُم مُّسْلِمُونَ

“በርሷም (በሕግጋቲቱ) ኢብራሂም ልጆቹን አዘዘ። ያዕቁብም (እንደዚሁ ልጆቹን አዘዘ)። ‘ልጆቼ ሆይ! አላህ ለናንተ ሃይማኖትን መረጠ፤ ስለዚህ እናንተ ሙስሊሞች ኾናችሁ እንጂ አትሙቱ’ (አላቸው)።” (አል-በቀራ 2፤132)

ነቢዩላህ ዩሱፍ (ዐ.ሰ) ይህንኑ ከአላህ ሲለምኑ እንዲህ ይላሉ፡-

رَبِّ قَدْ آتَيْتَنِي مِنَ الْمُلْكِ وَعَلَّمْتَنِي مِن تَأْوِيلِ الْأَحَادِيثِ فَاطِرَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ أَنتَ وَلِيِّي فِي الدُّنْيَا وَالْآخِرَةِ تَوَفَّنِي مُسْلِمًا وَأَلْحِقْنِي بِالصَّالِحِينَ 

“ጌታዬ ሆይ! ከንግሥና በእርግጥ ሰጠኸኝ። ከሕልሞችም ፍች አስተማርከኝ። የሰማያትና የምድር ፈጣሪ ሆይ! አንተ በቅርቢቱና በመጨረሻይቱ ዓለም ረዳቴ ነህ። ሙስሊም ሆኘ ግደለኝ። በመልካሞቹም አስጠጋኝ (አለ)።” (ዩሱፍ 12፤101)

ነቢ ሙሳ (ዐ.ሰ) ትክክለኛ አማኝ ማለት ለአላህ (ሱ.ወ) ያደረ ሙስሊም መሆኑን ለህዝባቸው ሲያስተምሩ እንዲህ ይላሉ

وَقَالَ مُوسَىٰ يَا قَوْمِ إِن كُنتُمْ آمَنتُم بِاللَّهِ فَعَلَيْهِ تَوَكَّلُوا إِن كُنتُم مُّسْلِمِينَ

“ሙሳም አለ፡- ‘ሕዝቦቼ ሆይ! በአላህ አምናችሁ እንደ ሆነ በርሱ ላይ ተጠጉ። ታዛዦች እንደ ሆናችሁ (በአላህ ላይ ትመካላችሁ)’።” (ዩኑስ 10፤84)

ይህን ጉዳይ የሚያስረዱ ሌሎች የቁርኣን አንቀጾች በብዛት ይገኛሉ።

የኢስላም ልዩ ትርጓሜ

እንደሚታወቀው ለሰው ልጆች አስፈላጊና ጠቃሚ ነገሮች ከግዜና ሁኔታዎች መለያየት ጋር ተያይዞ ሊለያዩ ይችላሉ፤ ስለዚህም ጥበበኛ የሆነው ጌታ አላሁ (ሱ.ወ) ቀድሞ በእውቀቱ እንዳሳለፈው ለሰው ልጆች በየጊዜው ጠቃሚና አስፈላጊ የሚሆነውን ነገር ይደነግጋል፤ ስለዚህም ነው ሻሪ ከተሻሪ በአብዛኛው በላጭና የተሻለ ሆኖ የምናገኘው። ምክኒያቱም ከጥሩ ነገር ወደ በላጭ ነገር መሸጋገር አላህ (ሱ.ወ) በፍጡራኑ ላይ ያደረገው ተፈጥሯዊ ህግ ነው፤ አላህ (ሱ.ወ) ባሮቹን ምንግዜም ቀስ በቀስ ከትንሽ ወደ ትልቅ፣ ከጥሩ ነገር ወደ በላጭና ሙሉ ወደ ሆነ ነገር ይወስዳቸዋል።

ኢስላማዊ ሸሪዓ (ህግ) አላህ (ሱ.ወ) ለሰው ልጆች መመሪያ ያወረደው የመጨረሻና የማይሻር መለኮታዊ ህግ ነው፣ ስለዚህ ሁሉንም የህይዎት ዘርፎች የሚዳስስና ሰፊ ይዘት ያለው ሆኖ እናገኘዋለን። የሸሪዓ ህግ ውስጥ የተለያየ ደረጃ ያላቸው ድንጋጌዎች ናቸው ያሉት፤ አቅመ ደካማዎች እንደ ችሎታቸው የሚሰሩበት የተግራራ ሥርዐት ያለ ሲሆን ጠንካሮችና ብረቱዎችም ባለቸው አቅም ተጠቅመው ሐላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያስችሉ ጠንከር ያሉ ትዕዛዛት ይገኛሉ። ይህም አላህ (ሱ.ወ) ለባሮቹ ያለውን ሰፊ እዝነት ያሳያል። አላህ (ሱ. ወ) እንዲህ ይላል

ثُمَّ جَعَلْنَاكَ عَلَىٰ شَرِيعَةٍ مِّنَ الْأَمْرِ فَاتَّبِعْهَا وَلَا تَتَّبِعْ أَهْوَاءَ الَّذِينَ لَا يَعْلَمُونَ
 

“ከዚያም ከነገሩ (ከሃይማኖት) በትክክለኛይቱ ሕግ ላይ አደረግንህ። ስለዚህ ተከተላት። የእነዚያንም የማያውቁትን ሕዝቦች ዝንባሌዎች አትከተል።” (አል-ጃሲያ ፤18)

አላህ (ሰ.ወ) ነብያችን ሙሃመድን (ሶ.ዐ.ወ) በመላክ መሰረታዊ ጽንሰ ሐሳቦቹንና ድንጋጌዎቹን ያብራራበትና ለሰው ልጆች ሁሉም እንዲያደርሱት ወደ እሱም ያዘዛቸው ዲነል-ኢስላም አላህ ዘንድ ተቀባይነት ያለውና ለባለቤቱም የሚጠቅም ብኛው ሐይማኖት እሱ መሆኑን አወጀ። ስለዚህ ኢስላም ከሱ በፊት የነበሩትን ሐይማኖቶች ሁሉ ሽሯል፤ በመሆኑም ኢስላምን የተከተለ ለፈጣሪው ያደረ (ሙሰሊም) ማለት እርሱ ነው፤ ከኢስላም ያፈነገጠ ደግሞ ለፈጣሪው አላደረም ወይም ሙስሊም አይደለም ማለት ነው።

ወደዚህ የአላህ ዲን ኢስላም መግቢያ በሩ “ላኢላሀ ኢለሏህ ሙሃመድ ረሱሉሏህ” በማለት የአላህን ብቸኛ አምላክነትና የነብዩ ሙሃመድ የአላህ መልክተኝነት መመስከር፤ የዚህ የሰጠኸውን የምስክረነት ቃል ድንጋጌዎችና ቅድመ ግደታዎች ተግባራዊ ማድረግና እንደዚሁም ይህን የምስክረነት ቃልህን የሚጻረርን ነገርን ሁሉ መራቅ ናቸው።

ታለቁ ጌታ አላህ (ሱ. ወ) እንድህ ይላል

وَمَن يَبْتَغِ غَيْرَ الْإِسْلَامِ دِينًا فَلَن يُقْبَلَ مِنْهُ وَهُوَ فِي الْآخِرَةِ مِنَ الْخَاسِرِينَ

“ከኢስላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰው ፈጽሞ ከርሱ ተቀባይ የለውም። እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎቹ ነው።” (አሊ-ዒምራን 3፤85)

ነብያችን ሙሃመድ (ሶ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ

والذي نفس محمد بيده لايسمع بي أحد من هذه الأمة، يهودي ولا نصراني ثم يموت ولم يؤمن بالذي أرسلت به إلا كان من أصحاب النار. رواه مسلم

“በዚያ የሙሃመድ ነፍስ በእጁ በሆነችው ጌታ እምላለሁ፤ ከዚች ኡማ ውስጥ ማንኛውም ሰው የሁዳም ይሁን ነሳራ (ክርስቲያን) የኔን መልክት ሰምቶ በዚያ እኔ በተላኩበት ነገር (ኢስላም) ሳያምን ከሞተ (እርሱ) ከሳት ባልደረባዎች ነው።” (ሙስሊም ዘግበውታል)

በዚህም መሰረት ከነብያችን ሙሃመድ (ሶ.ዐ.ወ) መላክ በኋላ ያሉ አይሁድም ይሁን ክርስቲያን ወደ ኢስላም ካልገቡ በቀደምት ነብያቶቻው ማመናቸው አይጠቅማቸውም ማለት ነው፤ ምክኒያቱም ነብያችን ሙሃመድ (ሶ.ዐ.ወ) ይዘውት የመጡት ዲነል-ኢስላም ከሱ በፊት የነበሩትን ሐይማኖቶች የሚሽር ስለሆነ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here