ታላላቅ የሐዲስ ዘጋቢ ሶሐቦች

0
7342

ከሰሀቦች መካከል ሀዲስን በመዘገብ የታወቁ ነበሩ። እነዚህ ሶሐቦች ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ሀዲሱን የሰሙና በተግባርም ድርጊቶችን በአይናቸው የተመለክቱ ነበሩ። ከነዚህ ሶሐቦች መካከል ሰባቱን ታዋቂ ዘጋቢዎች እንጠቅሳለን። እነዚህ ዘጋቢዎች በምሁራን ዘንድ አያሌ ሃዲሶችን ዘጋቢዎች (ሙካሲሩን) በመባል ይታወቃሉ።እያንዳንቸው ከአንድ ሺ በላይ ሐዲሶችን ዘግበዋል። ቀጥሎ እያንዳቸውን በተናጠል እንመለከታለን

1. አቡሁረይራ

አቡሁረይራ (ረ.ዐ) ከሐዲስ ዘጋቢዎች ሁሉ የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዝ ሶሐባ ሲሆን ይህም የሆነው እጅግ በርካታ ሃዲሶችን ለመዘገብ በመቻሉ ነው። በረሱል (ሰ.ዐ.ወ )ዘንድም ከሙስሊሞች መካከል የሀዲስ መረጃን ለማግኘት በጣም ጉጉ ከሚባሉት አንዱ እንደሆነ ተነግሮለታል። አቡሁረይራ (ረ.ዐ) የዳውስ ጎሳ- የትልቁ ጎሳ አዝድ ተወላጅ ሲሆን ወደ መዲና የመጣውም በሰባተኛው አመተ ሂጅራ ነበር። በጊዜው ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ኸይበር ላይ መሆናቸው ስለተነገረው ወደዚያው በመሄድ እስልምናን ተቀበለ። አቡሑረይራ ከሰለመበት እለት ጀምሮ እስከ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እለተ ሞት ድረስ ዘወትር ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ ) ጎን ሳይለይ መረጃዎችን በመቀበል እና በቃሉም በማጥናት የቀኑን ክፍለ ጊዜ ያሳልፍ ነበር። ይህን ሁሉ ሲያደርግ ግን ዓለማዊ ኑሮውን እና ደስታውን ለዚሁ አላማ ሲል በመተው ነበር።

ከታሪክ መረጃዎች እንደተገኘው አቡሁረየራ የምሽት ጊዜውን ለሶስት ይከፍለው ነበር። የመጀመሪያውን ለእንቅልፍ፣ ሁለተኛውን ለሶላት እና የመጨረሻውን ክፍል ደግሞ ለጥናት ነበር። ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ሞት በኋላ በዑመር ኢብኑል ኸጣብ የአስተዳደር ዘመን የባህሬን አስተዳዳሪ ሆኖ የተሾመ ሲሆን በሙዓዊያም በኡመያድ ዘመንም የመዲና አስተዳዳሪ ሆኖም ቆይቷል። ከሀዲስ ዘጋቢዎች መካከል ታዋቂ የነበረው አቡ ሁረይራ በሂጅራ አቆጣጠር በ 59 (678 እ.አ.አ) ከዚህ አለም በሞት ተለየ።

ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ከሞቱ በኋላ ስለ ኢስላም፣ ፍትህ እና ተያያዠነት ያላቸው ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የሚሰጥ አካል ያስፈልግ ነበር።በጊዜው ከ 800 በላይ የሐዲስ ተማሪዎች የነበሩት አቡሁረይራ (ረ.ዐ) ከዚህ ቀደም በጥንቃቄ የሰበሰባቸውንና እና ያጠናቸውን ሐዲሶች ለሰዎች ማስተማር ጀመረ።

ከዚህም በላይ አንዳንዴ ሌሎች ሶሐቦች የማያውቋቸውን ሐዲሶች እንዲያብራራ ይጠየቅ ነበር። አቡሁረይራም ሐዲሶቹን እና እውቀቱን ያገኘውና የተማረው የመዲና ሰዎች በመሬትና በንብረት ጉዳይ ሙሃጅሮች ደግሞ በንግድ ጉዳይ ላይ ተጠምደው በነበረበት ጊዜ እንደሆነ ይገልጽ ነበር።

ከእለታት አንድ ቀን አንድን ሐዲስ እንዲያመሳክር በአብደላህ ኢብኑ ዑመር አማካኝነት የተላከው አቡሁረይራ የሰራውን ስራ ትክክለኛነት ለማስመስከር አብደላህ ኢብኑ ዑመርን ወደ አዒሻ (ረ.ዐ) ዘንድ በመውሰድ እውነተኛነቱን አስመስክሯል። የአቡ ሁረይራ ሐዲስን የማስታወስ ችሎታ በወቅቱ የመዲና ገዢ በነበረው ኢብኑል-ሐኪምም ተፈትኖ ያውቃል። መርዋን በአቡሁረይራ የተዘገቡ የተወሰኑ ሓዲሶችን ከወሰደ በኋላ እነኚህኑ ሐዲሶች ከአመት በኋላ ይጠይቀዋል። በሚገርም ሁኔታ ኢብኑል-ሐኪም የሰማውና ከአመት በፊት የመዘገባቸው ሐዲሶች ፍጹም ተመሳሳይ ሆነው አግኝቷቸዋል።

አቡሁረይራ ሐዲስን ለመማር ካለው ጥልቅ ቁርጠኝነት፣ ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ጋር በነበረው ጥብቅ ግንኙነት እንዲሁም በጓደኞቹና በሌሎችም ሰዎች የማስታወስ ችሎታውን ለመፈተን ከቀረቡበት የተለያዩ ሙከራዎች አንጻር ማንኛውም ሰው ሐዲሶቹን ፈልስፎ እንዳልዘገባቸው ይረዳል።

2. አብደሏህ ኢበኑ ዑመር

አብደሏህ ኢብን ዑመር (ረ.ዐ) የኸሊፋው ዑመር ኢብኑል-ኸጣብ ልጅ ሲሆን አያሌ ሐዲሶችን በመዘገብ የሁለተኛነቱን ደረጃ ይይዛል። ሁለቱም (አባትና ልጅ) በአንድ ጊዜ እስልምናን ከመቀበላቸው በተጨማሪ አብረውም ወደ መዲና በስደት ተጉዘዋል። አብደሏህ ኢበኑ ዑመር በረሱል (ሰ.ዐ.ወ) የህይወት ዘመን በበርካታ ጦርነቶች ላይ የተሳተፈ ሲሆን ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ሞት በኋላም በሜሶፖታሚያ (ኢራቅ)፣ በፐርሺያና በግብጽ በተደረጉት ጦርነቶች ላይ ተሳትፏል። የሶስተኛውን ኸሊፋ -ኡስማን ኢብኑ አፋን መገደል ተከትሎ በሙሰሊሞች መካከል ግጭት በተፈጠረበት ወቅት አብደላህ ኢበኑ ዑመር ገለልተኘነትን መርጧል። በመላው ሙሰሊም ዘንድ አክብሮትና ውዴታ የነበረው ሲሆን በተደጋጋሚ የቀረበለትን የኸሊፋነት ሹመት ባለመቀበል አንዲሁም ራሱን ከተራ የቡድን ግጭቶች እና ልዩነቶች አርቆ ኖሯል።

በእነዚህ አመታትም ልክ አባቱ ሞዴል መሪ እንደነበረው ሁሉ እሱም ከራስ ወዳድነት የራቀና ለሀይማኖቱ ታማኝ የሆነ ጥሩ ሙሰሊም በመሆን አሳልፏል። በመጨረሻም በ87 አመቱ በሂጅራ አቆጣጠር 74 (692 እ.ኤ.አ) መካ ላይ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል። አብደላህ ኢበኑ ዑመር ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ጋር በነበረው የቆየ ግንኙነት፣ ከነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) ባለቤት ሐፍሳ እና ከሌሎችም ሶሐቦች ጋር የነበረው ጥብቅ ትስስር ሐዲስን ከሌሎች በላቀ ሁኔታ እንዲማር ረድቶታል። ያሳለፈው ረጅምና ሰላማዊ ህይወት ከዚህ ቀደም ከሌሎች የቀሰማቸውን የረሱልን (ሰ.ዐ.ወ) ሐዲሶች እንዲያስተምርና ኢስላማዊ አሰተምህሮትንም ለማሰራጨት በቂ ጊዜ ለማግኘት አስችሎታል። ከሚዘግባቸው ሐዲሶች ጋር በተገናኘ በነበረው ከፍተኛ ጥንቃቄ በሰዎች ዘንድ ይታወቅ ነበር።ስለሆነም ታዋቂው የሀዲስ ዘጋቢ ሻዕቢ እንደዘገበው ከአብደላህ ኢብኑ ዑመር ጋር ለአንድ አመት ያህል ሲቆይ አንድም ሀዲሰ ሳይሰማ ቆየቷል። አብደላሀ ሐዲስ በሚዘግብበት ወቅትም አይኖቹ በእንባ ይሞሉ ነበር። እስልምናን ለማገልገል የሚፈፅማቸው ተግባራት፣ ቀለል አድርጎ ህይወቱን መምራቱ፣ እውነተኛ እና ታማኝ ባህሪው፣ ለሀዲሰ አያያዝ ያለው ጥንቃቄ እና ሌሎችም በጎ ባህሪያቱ ተደማምረው ከሱ ለምናገኛቸውና ለምንቀስማቸው እውቀቶች ታላቅ ግምተ እንድንሰጥ ያደርገናል።

3. አነስ ኢብኑ ማሊክ

ከስደት በኋላ አነስ (ረ.ዐ) በእናቱ ኡሙሱለይም አማካኝነት በ 10 ዓመቱ ለረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ተሰጠ። ከዚያ ጊዜ አንስቶ አስከ ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) እለተ ሞት ድረስ ረሱልን (ሰ.ዐ.ወ.) በቅርበት ሲያገለግለ ቆይቷል። ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ሞት በኋላም በአቡበክር ሲዲቅ ዘመን የግብር ሰብሳቢ ሆኖ ወደ ባህሬን ተልኳል። አነስ በ 93 አመተ ሂጀራ (711 እ.ኤ.አ) ህይወቱ እስካለፈችበት ጊዜ ድረስ በስራ (ኢራቅ) ውስጥ ኖሯል። አነስ ከ 100 አመት በላይ እንደኖረም ይነገራል።

ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ጋር በቆየባችው 10 አመታት እጅግ በርካታ ሃዲሶችን ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ለማዳመጥና በእዕምሮ ለማስቀመጥ ችሏል። ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) በኋላም ከአቡበክር ሲዲቅ፣ ከዑመርና ከሌሎች ሶሐቦች የረሱልን (ሰ.ዐ.ወ) ሐዲሶች ለመማር ቸሏል።አነስ በነበረው ጥልቅና ሰፊ የሐዲስ እውቀት የተነሳ የሱ መሞት የአጠቃላይ ሃዲስ ግማሽ እንደሞተ ተደርጎ ይቆጠር ነበረ። በዚህም የተነሳ የሀዲስ ሊቃውንት አነስን ከፍተኛ ሃዲስ ካስተላለፉት ሶሐቦች አንዱ አድርግው መድበውታል።

4. የሙእሚኖች እናት ዓኢሻ

ዓኢሻ (ረ.ዓ) ብዙ ሃዲሶችን ከዘገቡት ሶሃቦች መካከል በአራትኛነት ትቀመጣልች። ዓኢሻ ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ጎን በመሆን ስምንት አመት ከግማሽ ያሳለፈች ሲሆን የሞተችውም በሂጅራ አቆጣጠር በ 57 (676 እ.ኤ.አ) በ 65 አመቷ ነበር። በተፈጥሮዋ ከፍተኛ የሆነ የማሰታወስ ተሰጥኦ የነበራተ ዓኢሻ በጣም በርካታ የሆኑ የጥንታዊ አረቦችን ግጥሞች በማሰታወስ ችሎታና በዚህም ዘርፍ እንደ መረጃ ምንጭነት የምትጠቀስ እንስት ነበረች። ዓኢሻ በሕይወት ዘመኗ በህክምና እና በኢሰላማዊ ህጎችም እንዲሁ ከፍተኛ ሊቅ ነበረች።

ዓኢሻ (ረ.ዓ) በጣም ብዙ ሃዲሶችን ከባለቤቷ ማዳመጥና መሰብሰብ መቻል ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ሶሃቦች በሃዲስ አረዳድ ላይ የሚፈጥሩትን ስህተት ታርም ነበር። ለምሳሌ፡- ኢቡኑ ኡመር፤ “ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ‘ሟች ቀብር ላይ በዘመዶቹ ለቅሶ ምክንያት ይቀጣል’ ብለዋል” ብለው የዘገቡትን ሃዲስ ዓኢሻ ደግሞ ረሱል ያሉት ኢብኑ ዑመር እንዳለው ሳይሆን “ሟች ቀብር ላይ በራሱ ወንጀል እየተቀጣ ዘመዶቹ ያለቅሱለታል ነው” ያሉት ብላለች። ዓኢሻ በሐዲስ ትምህርትና በኢስላም ህግ ሰፊ የሆነ እውቀት ስለነበራት በጣም ከፍተኛ ቦታ ያላችው ሶሀቦች እንኳን ሳይቀሩ በህግ ነክ ጉዳዮች ላይ አስተያት (ምክር) ይጠይቋት ነበር። ከሷ ሀዲስን የዘገቡ ስም ዝርዝር የሚያሳይ ረዥም የመረጃ ዝርዝር የተጠቀሰበት በ ኢብን ሃጀር የተዘጋጀ “ተሕዚብ አት-ተሕዚብ” የተሰኘ መፅሐፍ ይገኛል።

5. ዐብደላህ ኢብኑ አባስ

ዐብደላህ ኢብኑ አባስ (ረ.ዐ) ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) በስደት ወደ መዲና ከመሄዳቸው 3 ዓመት ቀደም ብሎ የተወለደ ሲሆን ረሱል በሞቱበት ጊዜ ደግሞ የ13 ዓመት ታዳጊ ነበር። ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ለሱ የሚጠቅሙትን እና እሱን የሚመለከቱትን ሐዲሶች ይቀስም የነበረው ታዳጊው አብደላህ በረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ ተወዳጅ ነበር። በሂ.አ በ68 (689 እ.ኤ.አ) በ71 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

በለጋነት እድሜው ጥቂት ሓዲሶችን ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ተምሯል። ኢብን ሐጀር ያህያ ኢብኑ አል-ቀህጧንን ጠቅሰው እንደዘገቡት ኢብኑ ዓባስ ከ4-10 የሚደርሱ ሐዲሶችን በቀጥታ ከረሱል ሰምተው እንደዘገቡ ጠቅሰው ነገር ግን ኢብን ሐጀር ይህ ቁጥር ትክክል አለመሆኑን በማስረጃ ይገልጸሉ። ምክንያቱም በትክክለኛው የሐዲስ ጥራዝ-ቡኻሪና ሙሰሊም-ብቻ ከ10 በላይ በኢብኑ ዓባስ በቀጥታ ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ሰምተው የተዘገቡ ሐዲሶች ሰፍረዋል።

በእርግጥ ኢበኑ ዓባስ ከሌሎቹ ሶሐቦች የዘገባቸው ሰዲሶች በቀጥታ ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ከዘገባቸው ጋር ስናነጻጽረው በጣም ጥቂት መሆናቸው የታወቀ ጉዳይ ነው። ብዙዎቹን ሐዲሶችም የተማረው ለአመታት ባደረገው ከፍተኛ ትግል አማካኝነት ነው። እሱም ይህን ጥረቱን ሲናገር እንዲህ ይላል፦“አንድን ሐዲስ ከሶሐቦች ለመማር ስፈልግ መረጃውን ይሰጠኛል ብይ ከገመትኩት ሰው በር ላይ እሄድና፤ ባለቤቱ ከቤት እስኪወጣና ‘አንተ የረሱል (ሰ.ዐ.ወ) የአጎት ልጅ ሆይ! ወደዚህ ቦታ ምን አመጣህ? እኔ ወደ አንተ እንድመጣ መልዕከት አትልክልኝም ነበር?’ እስኪለኝ እጠብቅ ነበር። እኔም ‘እኔ ወደ አንተ መምጣት ስለነበረብኝ ነው የመጣሁት’ ብዬ እመልሳለሁ። ከዚያም ሐዲስን ከሰውዬው እማራለሁ።”

ኢበኑ ዓባስ በእውቀቱ ስፋትና በማስታወስ ብቃቱ በሁሉም ዘንድ ታዋቂነትን ያገኘ ነበር። ቁርአንንና ሱናን ለማጥናት ሙሉ ጊዜውን መስጠቱ እና ሌሎችም መሰል ተግባራቱ በአራቱም ኸሊፋዎች እና በወዳጆቹ ዘንድ እንዲከበርና እንዲወደድ አስችሎታል። ብዙ መጽሐፍት እንዲጽፍባቸው ያስቻሉትን በርካታ ሐዲሶች ለመሰብሰብ ችሏል። በመጽሐፉም ለተማሪዎቹ ትምህርት ይሰጥ እንደነበርና ሙጃሒድ በተባለ ተማሪው አማካኝነት ወደታችኛው ትውልድ የተላለፈው የተፍሲር መጽሐፉ ደግሞ እጅግ የሚታወቅበትና የኋለኞቹ ትውልዶችም እንደማጣቀሻነት ይገለገሉበት የነበረ ነው።

6. ጃቢር ኢብኑ ዐብደሏህ

ጃቢር (ረ.ዐ) ከመዲና ውስጥ ቀደም ብለው ወደ ኢስላም ከገቡት ሶሐቦች አንዱ ነው። ለሁለተኛ ጊዜ የመጀመሪያዎቹ የመዲና ሙሰሊሞች ቡድን ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ መካ ውስጥ ተሳትፏል። ከረሱል ጋር በመሆን 19 ጦርነቶችን የተዋጋው ጃቢር በ94 አመቱ በሂ.አ በ74 (693 እ.ኤ.አ) ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ጃቢር ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ብቻ ሳይሆን ከረሱል ዋና ዋና ሶሐቦች ከሚባሉት ከአቡበከር፣ ዑመር እና ሌሎችም ሶሐቦች ዘንድ ሐዲስን ተምሯል። በተጨማሪም የአቡበክር ልጅ የሆነችውን ኡሙ ኩልሱምን ጨምሮ ከሌሎች ታቢዒዮች (ከነቢዩ ቀጥሎ የነረው ትውልድ) ዘንድም ሐዲስን ለመማር በቅቷል። መደበኛ በሆነ መልኩም መዲና መስጊድ ውስጥ ሐዲስን ያስተምር ነበር።

7. አቡ ሰዒድ አል-ኹድሪ

ስሙ ሰዕድ ኢብኑ ማሊክ ሲሆን ሌላው ከመዲና ቀዳሚ ሙሰሊሞች ውስጥ አንዱ ነው። አባቱ በእሁድ ዘመቻ ላይ ተገድሏል። ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) በህይወት በነበሩበት ወቅት በ12 ጦርነቶች ላይ ተሳትፏል። በሂ.አ በ64 (683 እ.ኤ.አ) ከዚህ አለም በሞት ተለየ። ልክ እንደ አቡሑረይራ፤ አቡ ሰዒድ አል-ኹድሪ (ረ.ዐ) “የአህሉስ-ሱፋህ” (በትምህርትና በዒባዳ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረጉ ሶሐቦች) አባል ነው። አቡ ሰዒድ ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ ሐዲሶች ከመማሩ በተጨማሪ ከአቡበክር፤ ዑመርና ከዘይድ ኢብኑ ሳቢት ዘንድ ተምሯል። አቡ ሰዒድ ከወጣት ሶሐቦች መካከል ምርጡ “የህግ አዋቂ” ነበር።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here