ድቅድቅ ባለና በማእበል በታጀበ ሌሊት፣ ፍጹም ጨለማ በሆነው የአእምሮ ዋሻ ውስጥ ሸይጧን ችቦ ለኩሶ መሳጭ ታሪክ -አፈታሪክ ሊነግረን ቋምጧል፡፡ አፈታሪኩ እንዲህ ነው።
‹‹ከእለታት አንድ ቀን ቅዱስ ለሆኑት ነቢይ ኢስላም ተላከ፡፡ ይህንንም ራእይ በዙሪያው ለነበሩት ተፈጥሯዊ ዝንባሌና ስነህይወታዊ ግድፈት ለማይታይባቸው ልዩ ሰዎች (ጓደኞቹ) አካፈላቸው፡፡ እነሱም ይህን አስተምህሮ በፍጹም ትጋት፣ ያለስህተትና ግድፈት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አደረጉት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለተከታታይ ትውልዶች ሲቀባበል እኛ ጋር ደረሰ፡፡ ይህ ኢስላምን ተግባራዊ የማድረግ ሂደት ከስህተት ነጻ መሆንን፣ ከሀጢአት ሙሉ በሙሉ መራቅንና ቅዱስነትን የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡›› ሸይጧን ትረካውን በዚህ መልኩ ይቋጫል፡፡
በርግጥ ሸይጧን ሚሊዮን አመት ያስቆጠረ፣የተረገመ ፣ ተንኮለኛና ብልጣብልጥ ፍጡር ነው፡፡ አላማውም የማታ ማታ የቻለውን ያህል ብዙ ሰዎችን ከርሱ ጋር ወደ ጀሀነም መጎተት ነው፡፡ ይህንን ከሚያሳካባቸው ስልቶች ውስጥ አንዱ እንዲህ ያለውን አፈታሪክ እውነት አስመስሎ ማቅረብ ነው፡፡ ፍጹም ምሉእ የሆኑ ሰዎች አፈታሪክ!!!፡፡
ሀሳቡ በጣም ቀላል ነው-!
ሙስሊም ከሆንክ እንከን አልባ ከሀጢአት የጸዳ ሙስሊም ሁን ካልሆነ ተወው፣ ራስህን አታታል፡፡
በርግጥ እንደአንተ ያለው በወንጀል አረንቋ ውስጥ የተዘፈቀ ሰው ጀነት የመግባት እድል የለውም!
በቁጭትና በተስፋ መቁረጥ ራስህን ጥላ ሞትን ተመኝ ፣
ሸይጣን በተፈጥሯቸው ኢስላምን በሙሉ ለመተግበር የታደሉ ሰዎች እንዳሉና አንተ ከእነርሱ ጎራ እንደማትመደብ ሊያሳምንህ ይሞክራል፡፡
የርሱ ወስዋስ በጣም የሚያታልልና አሳማኝ የሚመስል ነው፡፡ ስለሆነም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሙስሊሞች ወንጀል ላይ ደጋግመው በመውደቃቸው ፣ ራሳቸውን በተደጋጋሚ በሀጢአት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀው በማግኘታቸው ምክንያት የተሻለና መልካም የመሆን ፍላጎታቸው ተሟጦ ፣ በራሳቸው ተስፋ ቆርጠው ይኖራሉ፡፡ ትክክለኛና እና ቅዱስ ሙስሊም ባለመሆናቸው ራሳቸውን ጠልተው ፣መልካም የመሆን ሞራላቸው ከስሞና ቅስማቸው ተሰብሮ በአሳዛኝ ስሜት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
በኢስላም የመኖር ትግላቸው ውስጥ የስሜት መጎዳትና ባዶነት ይሰማቸዋል፡፡ ራሳቸውን እያታለሉ እንደሆነ ይሰማቸዋል፡፡ ኒፋቅ (አስመስሎ የመኖር ስሜት) ከልባቸው ነግሷል፡፡ እናም ከእንዲህ አይነቱ የማስመሰል ህይወት ይልቅ ተስፋ ቆርጦ ፣(ትክክለኛ) ሙስሊም የመሆን ህልማቸው ተጨናግፎ ፣ ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጎ መተውን በመመኘት መካከል በሚፈጠር የስሜት መሰበር ውስጥ (ይዋልላሉ) ራሳቸውን ያገኛሉ፡፡
ሸይጣን በተፈጥሯቸው ኢስላምን በሙሉ ለመተግበር የታደሉ ሰዎች እንዳሉና አንተ ከእነርሱ ጎራ እንደማትመደብ ሊያሳምንህ ይሞክራል፡፡ ራስህን በተደጋጋሚ ስህተት ውስጥ በማግኘትህ የሚሰማህ ‹‹አንዳች መጥፎ›› ስሜት በመንፈሳዊ ምጥቀት ጉዞ በሚደረግ ተከታታይ ትግል ውስጥ የሚፈጠር ጤናማ ስሜት ሳይሆን አንተ መልካም ሙስሊም የመሆን እድሉ ስለሌለህ እና ልትሆን የማትችል እንደሆነ ይሞግትሀል፡፡
ከተቃራኒ ጾታ ጋር ያላትን ግንኙነት በኢስላም መርህ መሰረት ባለመሆኑ ሂጃቧን አሽቀንጥራ የጣለች፣ በመጥፎ ሱስ በመለከፉ ምክንያት ሰላት መስገዱን ያቆመ ወጣት፣ የዚህ የተሳካለት የሸይጧን አፈታሪክ ወጤት ናቸው፡፡ እነዚህ በመንፈሳዊ ምጥቀት የሚደረግ ትግል ውስጥ ያሉ ስሜቶች የለውጥና እድገት ሳይሆን የመሸነፍ ምልክት መሆኑንን ያመኑ የሸይጧን አፈታሪክ ሰለባ የሆኑ አሳዛኝ ሙስሊሞች ናቸው፡፡
ከተቃራኒ ጾታ ጋር ያላትን ግንኙነት በኢስላም መርህ መሰረት ባለመሆኑ ሂጃቧን አሽቀንጥራ የጣለች፣ በመጥፎ ሱስ በመለከፉ ምክንያት ሰላት መስገዱን ያቆመ ወጣት፣ የዚህ የተሳካለት የሸይጧን አፈታሪክ ወጤት ናቸው፡፡
ኢማም ሱፍያን አስ-ሰውሪ ይህን የሸይጧን ርካሽ ማታለያ በመንቃታቸው(በመገንዘባቸው) ለተከታታይ ሀያ አመታት የሌሊት ሶላትን ለዛውን ማጣጣም ሳይታደሉ መስገድ ችለዋል፡፡ እንዲህ ይላሉ
‹‹ለተከታታይ ሀያ አመታት በራሴ ላይ ጂሀድ አወጅኩ፡፡ ራሴን- ሌሊት ተነስቼ እንድሰግድ -ታገልኩ፡፡ ለነዚህ ሀያ አመታት የሌሊት ሶለትን ጥፍጥና ለማጣጣም አልታደልኩም ነበር፡፡ ከሀያ አመት የማያቋርጥ ትግል በኋላ ነው የሌሊት ሶላትን ለዛ ማጣጣም የቻልኩት›› ፡፡
እኚህ ታላቅ ሰው ከከእለታት አንድ ቀን ቆም ብለው ይሄን ሁሉ ዘመን የሌሊት ሶላትን ጥፍጥና ማግኘት አልቻልኩም፡፡ የሆነ ችግር ቢኖርብኝ ነው- እኔ ጥሩ ሰው አይደለሁም መልካም ሙስሊም ለመሆን አልታደልኩም ብለው ቢያቆሙ ኖሮ ሊፈጠር የሚችለውን ነገር ገምት፡፡
ሸይጧን አንተ ምሉእ ሙስሊም መሆን ባለመቻልህ ስለተሸነፍክ ጥሩ ሙስሊም ለመሆን የምታደርገውን ጥረት እርግፍ አድርገህ እንደትተው፣ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተሸብሽበህ እጅህን አጣጥፈህ እንድትቀመጥ ሊያሳምንህ ይጥራል፡፡
እውነታው ማንኛውም ሰው ሀጢአት መፈጸሙና ጂሀደ ነፍስ (ነፍስ ላይ የሚደረገው ትግል) የእያንዳንዱን ሰው የማያቋርጥ ትግል (ጥረት) የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑ ነው፡፡ ምርጦቹ ሰዎች ወንጀል የማይፈጽሙት ሳይሆኑ የፈጸሙት ወንጀል ለተሀድሶ የሚያነሳሳቸው ናቸው፡፡ ወደ አላህ በፍጥነት በመመለስ የበለጠ ጠንካራ ትግል የሚያደርጉና ይህም ተግባራቸው ወደ አላህ የበለጠ የሚያቃርባቸው ሰዎች ናቸው፡፡
ለአንዳንዶች በኢስላም ታላላቅ የሚባሉትን ወንጀሎችን መፈጸም ቁመው እንዲቀሩና ከጉዟቸው የሚያሰናክላቸው (እንቅፋት) ክስተት ሲሆን ለሌሎች ደግሞ ግን የህይወት ኡደታቸውን የሚቀይር ቸልተኝነታቸውንና ዝንጋታቸውን ገፍፎ የአላህን ውዴታ ማግኘት የሚያስችል ጅማሬ መንስኤ (መነሻ) የሚሆን የህይወት ዘመን ክስተት ይሆናል፡፡
ኢስላምን ከመተግበር (በኢስላም ከመኖር) አንጻር እያንዳንዱ ሙስሊም የስኬትና የውድቀት ስብስብ ነው። እናም ማንኛውም ወንጀል እንደፈጸመ፣ (ሀጢአት ላይ እንደወደቀ) ሰው ሁሉንም ሙስሊም ያቀፈ ስብስብ አባል (ውስጥ) መሆንህን አትዘንጋ፡፡ ማንኛውም ሰው በየእለቱ የተለያዩ ወንጀሎችን ይሰራል፡፡ስለሆነም ሁሉም ሰው እንደ አንተ የሸይጧንና ምክር ሰምቶ ተግባራዊ ቢያደርግ ሊከሰት የሚችለውን ነገር አስብ፡፡
በሀዲስ አል ቁድሲ እንደተቀመጠው አላህ እንዲህ ብሏል:-
‹‹ባሪያዎቼ ሆይ! በየእለቱ በቀንና በሌሊት ወንጀል ትፈጽማላችሁ እኔ ሁሉንም ወንጀል እምራለሁ። እናም ወንጀላችንን ማረን በሉኝ እምራችኋለሁ።››
ሸይጧን ፈተናው የሚታለፈው ከመቶው መቶ በማምጣት ብቻ እንደሆነ ሹክ ይልሀል፡፡ ከመቶው መቶ ማምጣት ካልቻልክ ወይም ከመቶ በታች ካመጣህ መውደቅህን እንድታስብ ያደርገሀል፡፡ በርግጥ ሸይጧንን ካመንከው አላህን እድትጠላው እንድትሰድበው ያግባባህ መሆኑ ነው፡፡ እንዴት – አላህ እጅግ በጣም ሩህሩህ፣ አዛኝ ፣እጅግ መሀሪ፣ እጅግ አፍቃሪ፣እጅግ በጣም ቸር። እርሱ ብቻ ነው ምሉእ ከጉድለት የጸዳ ና በሁሉም ነገር አዋቂ! ፡፡ እኛ እንዴት እንደተሰራንና ተፈጥሯችን ምን እንደሆነ ጠንቅቆ የሚያውቅ አምላክ ነው፡፡ እናም በምን ምክንያት ነው እኛ ልንደርስበት የማንችለውን የብጹእነት ደረጃ ባለመንካታችን፣ ይህም ሊሆን እንደማይችል እያወቀ በጭካኔ ያለርህራሄ ሊቀጣን የሚችለው፡፡
ሸይጧን እዚህ ላይ ብቻ አያቆምም። ‹‹አዎ! እርግጥ አላህ መልካም ነው። ግን አንተ ራስህን እስቲ ተመልከት እንዲህ አይነቱን በወንጀል ያደፈ ቀልብ ይዘህ ነው ውድ የሆነችውን ጀነት ለመግባት የምትመኘው፤ ይህ ቀቢጸ ተስፋነት ነው›› ሲል ለማሳመን ይሞክራል፡፡ በእውነቱ ይህ እጅግ ከባድ ስሜት ሚጎዳ አሳዛኝ ሀሳብ ነው፡፡
በወንጀል በመዘፈቅህ ምክንያት የአላህ ምህረትን ማግኘት እንደማይገባህ ከተሰማህ የአላህን ያለገደብ የመማር ችሎታ በድፍረት እያስተባበልክና ዝቅ እያደረግክ (እያሳነስክ) ነው፡፡ ያንተ ደካማ የሆነውን ወንጀል የመፈጸም አቅም ከአላህ ወንጀልን የመማር አቅም በላይ ነው እያልክ ነው፡፡ እባክህን አላህን አትሳደብ (አታነውር)! በአላህ ያስተባበሉ ከሀዲያን አላህን አል-ገፋር እያሉ ለመጥራት ይቸገሩ ነበር። አል-ገፋር ያለ ምንም ምላሽ መጠበቅ (ያለገደብ) ሁልጊዜ ያለማቋረጥ የሚምር አምላክ ለማለት ይሳናቸው ነበር፡፡
አነስ እንዳወሩት ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም አላህ እንዲህ ብሏል አሉ
‹‹የአደም ልጅ ሆይ! እኔን እስከጠራሀኝ ና እኔን እስከለመንከኝ ጊዜ ድረስ የሰራሀውን ሁሉ ይቅር እልሀለሁ (እምርልሀለሁ) ግድ የለኝም፡፡ የአደም ልጅ ሆይ! ወንጅልህ በዝቶ የሰማይ ላይ ደመና ያክል ቢደርስ እና ምሀረት ከጠየቅከኝ እምርሀለሁ፡፡ የአደም ልጅ ሆይ! ምድርን የሚሞላ ወንጀል ተሸክመህ ከኔ ጋር ብትገናኝ (ወደኔ ብትመጣ)ና በኔ ላይ ምንም ካላጋራህ ምድር በሚሞላ ምህረት እቀበለሀላሁ(እምርሀለሁ)›› ቲርሚዚ ዘግበውታል።
ይህን ሀዲስ ባነበብኩ ቁጥር የሆነ ስእል ወደ አእምሮየ ይመጣል (ይከሰትልኛል)፡፡ ይህም ተራራ ለሚያክል ወንጀል መመለስ መቻል ተስተካካይ ያንኑ ተራራ ሚያክል በረካና እዝነት (ምንዳ) ይዞ እንደሚመጣ ይታሰበኛል፡፡ እናም የፈጸምከው ወንጀል ትልቅ በሆነ ቁጥር በተመሳሳይ አላህን ይቅርታ በመጠየቅህ የምታገኘው ምንዳ (በረካና ረህመት) የዚያኑ ያህል ትልቅ ይሆናል፡፡ ይህን መረዳቱ አላህ ምን ያህል ባሪያዎቹን እንደሚወድ፣ እንደሚያዝንላቸውና እንደሚምራቸው እንድናውቅ ያደርገናል፡፡ በመሆኑም ከፈጸምነው ወንጀል ተጸጽትን (ተውበት አድርገን ስንመለስ) ወንጀላችን ይታበሳል ብቻ ሳይሆን ተውባ ያደረግንበት ወንጀል ግዝፈት ያህል ከአላህ ምንዳ (በረካና እዝነት) እናገኛለን ማለት ነው፡፡
ሸይጧን አላህ ወንጀልን ከመማር ችሎታ አንጻር የታላቆች ታላቅ መሆኑን እንድትዘነጋ ያደርግሀል፡፡ እሱ ሁለት አማራጭ ብቻ እንዳለህ እንድታስብ ይፈልጋል፡፡ ይህም ከወንጀል ሙሉ በሙሉ የጸዳ ምሉእ (ቅዱስ) ሰው መሆን ወይም ሽንፈት (ውድቀት)፡፡ ለሰው ልጅ ሰው ከመሆኑ አንጻር ምሉእነት (ቅዱስነት) የማይቻል በመሆኑ ሸይጧን ለየትኛው አማራጭ እንደተወህ አስተዋልክ! ራስህን ከንቱ አድረገህ እንድትስል፣ ራስህን እንድትጠላና ተስፋቆርጠህ ለርሱ እጅ እንድትሰጥ እያመቻቸህ ነው፡፡
ነገር ግን ሸይጧን እድታስታውሰው የማይፈልገው ሶስተኛ አማራጭ አለ፡፡ በምሉእነት፣ ፍጹምነት (እንከን አልባነትና) እና በሽንፈት መካከል አንድ እውነተኛ ምርጫ አለ፤ እርሱም ትግል (ፍልሚያ) ነው፡፡
የሸይጧንን የሽንፈት ዝማሬን መፋለም፣ የነፍስያን ወንጀል የመስራት ዝንባሌ (ጉጉት) መፋለም። የቱንም ያህል በተደጋጋሚ ወድቆ መነሳት ቢጠይቅም፣ የቱንም ያህል በ(ሸይጧን) ጠንካራ ክንድ በተደጋጋሚ ብትደቆስም፣ የቱንም ያህል ለረዥም ጊዜ መሬት ላይ ተዘርረህ ብትቆይም፣ ተነስተህ አሁንም ቁመህ ተፋለም (ታገል) ፡፡ ሸይጧንን የሚፋለምህ ያህለ ተፋለመው፣ እርሱ እስከተፋለመህ ጊዜ ድረስ አንተም መፋለምህን አታቁም፡፡ ወድቆ መነሳት ፣ ወንጀል ሰርቶ አላህን ምህረት መጠየቅ ለአንድ ሙስሊም ጤናማ ተግባር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሁላችንንም በተስፋ ብርሀን የሚሞላ ንግግር ተናግረዋል።
‹‹ነፍሴ በእጁ በሆነችው አምላክ እምላለሁ ወንጀል የማትፈጽሙ ቢሆን ኖሮ አላህ እናንተን አስወግዶ ወንጀል እየፈጸሙ ይቅርታ የሚይጠይቁትን እና ይቅር የሚላቸውን ህዝቦችን ያመጣ ነበር›› በማለት ተናግረዋል። (ሙስሊም ዘግበውታል)