ሀዲስና በኢስላም ያለው ጠቀሜታ

0
4003

በአረብኛ ቋንቋ ‘ሀዲስ’ የሚለው ቃል ዜና፣ ንግግር፣ ትረካ ወይም ዘገባ ማለት ሲሆን እነዚህ ነገሮች ታሪካዊ ወይም አፈ-ታሪካዊ አልያም ቀድሞ ካለ ነገር ጋር የተያያዙ ሊሆን ይችላል። ልክ እንደሌሎቹ የአረበኛ ቃላቶች (ሰላት፣ ዘካ…) ሀዲስ የሚለዉ ቃል በእስልምና ዉስጥ የራሱ የሆነ ትርጉም ይኖረዋል።

ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) በነብይነት ከተላኩበት ጊዜ ጀምሮ ትረካቸዉና የመግባቢያ ስልታቸዉ በሌሎች የመግባቢያ መንገዶች ላይ ጫና ሲፈጥር ተስተዉሏል። “ሀዲስ” የሚለው ቃል በልዩ ሁኔታ የረሱልን (ሰ.ዐ.ወ) ድርጊትና ንግግር ብቻ ለመግለጽ ሆኗል። “ሀዲስ” በእስልምና ዉስጥ ያለዉ ደረጃ ቀንጨብ ቀንጨብ አድርገን እናቀርባለን።

1. ወሕይ /ራእይ/ ነው

የረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ንግግርና ድርጊት ምንጩ ከአላህ (በወህይ መልክ) ነው። በመሆኑም ሀዲስ ከቁርአን ቀጥሎ የኢስላም መሰረታዊ የህግ ምንጭ ነው። አላህ (ሱ.ወ) ነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፡-

وَمَا يَنطِقُ عَنِ الْهَوَىٰ إِنْ هُوَ إِلَّا وَحْيٌ يُوحَىٰ 

“ከልብ ወለድም አይናገርም። እርሱ (ንግግሩ) የሚወርረድ ራእይ እንጅ ሌላ አይደለም።” (አል-ነጅም 53፤3-4)

ስለሆነም ሀዲስ ለረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ከአላህ የተሰጠ መለኮታዊ መመሪያ ነዉ። ይህ ባህሪው ከቁርዓን ጋር ያመሳስለዋል። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ይህንን ሀሳብ በማጠናከር እንዲህ ብለዋል፡-

“እኔ በእርግጥም ቁርአንና ከሱ ተመሳሳይ የሆነ ነገር ተሰጥቻለሁ” (አቡዳውድ)

2. የቁርአን ማብራሪያ ነው

ቁርዓንን የመጠበቁ ተግባር ቃላቶቹ እንዳይለወጡ ብቻ ላይ አልተገደበም። ቃላቶቹ ሳይቀየሩ ሰዎች ቁርዓንን እንደፈለጉ ሊተረጉሙ በቻሉ ነበር። ነገር ግን አላህ (ሱ.ወ) ቃላቶቹ እንዳይለወጡ እንደሚጠብቀዉ ሁላ መሰረታዊ ትርጉሙ እንዳይለወጥና እንዳይበረዝ የማብራራቱን ሃላፊነት ለነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ብቻ ሰጥቷል። ከዚህ አኳያ አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَأَنزَلْنَا إِلَيْكَ الذِّكْرَ لِتُبَيِّنَ لِلنَّاسِ مَا نُزِّلَ إِلَيْهِمْ وَلَعَلَّهُمْ يَتَفَكَّرُونَ 

“ወደ አንተም ለሰዎች ወደእነሱ የተወረደውን (ፍች) ልትገልጽላቸውና ያስተነትኑም ዘንድ ቁርኣንን አወረድን።” (አል-ነሐል 16፤44)

ስለሆነም አንድ ሰው የቁርአንን መልዕክት ለመረዳት ከፈለገ ረሉል (ሰ.ዐ.ወ) በጉዳዩ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት ግምት ውስጥ ማስገባት አለበት። ለምሳሌ አላህ በቁርዓን (በአል-በቀራ 2፤43) አማኞች ሶላት እንዲሰግሱና ዘካ እንዲያወጡ አዟል ነገር ግን ይህንን ትዕዛዝ በተገቢው መንገድ ለመፈፀም በጉዳዩ ላይ የረሱልን የአፈፃፀም ስልት ማጥናት የግድ ይላል።

የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ስለ ሰላትና ዘካ አፈፃፀም ከሰጧቸዉ በርካታ ማብራሪያዎች መካከል ሰላትን በተመለከተ እንዲህ ብለዋል“እኔ ስሰግድ እንዳያችሁት አድርጋችሁ ስገዱ” (ቡኻሪ) በተጨማሪም ሌሎች ብዙ ሶሂህ በሆኑ ነቢያዊ ሐዲሶች ስለዘካና የአፈፃፀሙ ሁኔታ ብዙ ተብሏል፤ ለምሳሌ ቀጣዩን ዐልይ ኢብኑ አቢጧሊብ የዘገቡትን ሀዲስ ማየት እንችላለን። ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) “ሁለት መቶ ድርሀም ኖሮህ አመት ካለፈዉ አምስቱን ድርሀም ለዘካ ታወጣዋለህ፤ በዓመት 20 ዲናር ከሌለህ ዘካ የማውጣት ግዴታ የለብህም፤ 20 ዲናር ካለህ ግማሽ ዲናር ዘካ አለብህ ቁጥሩም በጨመረ ልክ በሂሳብ ይወጣለታል። አንድ ሰው ዘካ የሚያወጣው ለዘካ የደረሰ ንብረቱ አንድ አመት ሲያልፈዉ ነው” (አቡዳውድ)።

3. ህግ ነው

ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ተቀዳሚ ተግባር ዉስጥ አንዱ በሁለት ሰዎች መካከል የሚከሰተውን አለመግባባት መፍታት ነበር። ከላይ እንዳየነዉ የእርሳቸዉ ማንኛዉም ንግግራቸዉም ይሁን ተግባራቸዉ መሰረቱ ወህይ ነዉ። ስለሆነም በኢስላማዊ መንግስት የእርሳቸዉ ፍርድ ዉሳኔ እንደመጀመሪያ የህግ ምንጭ ተደርጎ መወሰድ አለበት። አላህ (ሱ.ወ) ይህንን ሃላፊነታቸዉን በቁርአን እንዲህ ብሎ አስቀምጦታል፡-

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا أَطِيعُوا اللَّهَ وَأَطِيعُوا الرَّسُولَ وَأُولِي الْأَمْرِ مِنكُمْ فَإِن تَنَازَعْتُمْ فِي شَيْءٍ فَرُدُّوهُ إِلَى اللَّهِ وَالرَّسُولِ إِن كُنتُمْ تُؤْمِنُونَ بِاللَّهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ ذَٰلِكَ خَيْرٌ وَأَحْسَنُ تَأْوِيلًا
 

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ተገዙ። መልክተኛውንና ከእናንተም የስልጣን ባለቤቶችን ታዘዙ። በማንኛውም ነገር ብትከራከሩ በአላህና በመጨረሻው ቀን የምታምኑ ብትኾኑ (የተከራከራችሁበትን ነገር) ወደ አላህና ወደ መልክተኛው መልሱት። ይህ የተሻለ መጨረሻውም ያማረ ነው።” (አል-ኒሳእ 4፤59)

ስለዚህ በኢስላማዊ መንግስት ለተቃናና ለተቀላጠፈ የህግ አሰራርና የፍርድ አሰጣጥ ስርዓት ሀዲስ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

4. የህይወት ሞዴልነትን ማሳያ ነው

ረሱል(ሰ.ዐ.ወ) በመለኮታዊ ትዕዛዝ የሚመሩ ስለሆኑ በግላዊ ህይወታቸው፣ ባህሪቸው ማህበራዊ ግንኙነታቸው ወዘተ ለሙስሊም እስከ መጨረሻው ዕለት ድረስ (ቂያማ) ምሳሌ ናቸው። ቀጣዩ የቁርአን አንቀፅም ይህንኑ የሚገልፅ ነው፡-

لَّقَدْ كَانَ لَكُمْ فِي رَسُولِ اللَّهِ أُسْوَةٌ حَسَنَةٌ لِّمَن كَانَ يَرْجُو اللَّهَ وَالْيَوْمَ الْآخِرَ وَذَكَرَ اللَّهَ كَثِيرًا
 

“ለእናንተ አላህንና የመጨረሻውን ቀን የሚከጅል ለሆነ ሰው፣ አላህንም በብዙ ለሚያወሳ በአላህ መልዕክተኛ መልካም መከተል አልላችሁ።” (አል-አህዛብ 33፤21)

የረሱል (ሰ.ዐ.ወ) የህይወት ውሎ በሐዲስ ስለተመዘገበ የመልካም ስነምግባር መመሪያ ሆኖ ያገለግላል። ዓኢሻ እንደተናገሩት የረሱልን (ሰ.ዐ.ወ) ምግባራቸወን ተጠይቀው ሲናገሩ፡-

“ረሱል ምግባራቸው ሁሉ ቁርአን ነው” ብልዋል (አልባኒ ሰሒሕ ነው ብለዋል)።

5. ኢስላማዊ የመረጃ እውናዊነት /የዲነል ኢስላም መከታ ነዉ/

መረጃን የመሰብሰብ፣ የማስተላለፍ እና ሀዲስን የመተቸት ሳይንስ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከመምጣታቸዉ በፊት የሚታወቅ አልነበረም። ይህንን የመሰለ አስተማማኝ መረጃን መሰብሰቢያና ማቆያ ዘዴ ባለመኖሩ የቀደምት ነብያት አስተምህሮት ከነሱ በኋላ ለተተካዉ ትዉልድ ሳይተላላፍ ተረስቶ ከቀረበትና የተላለፈውም ከተበረዘበት ምክንያት ዉስጥ አንዱ ነዉ። ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መረጃን የመቀበል፣ የመያዝና የማስተላለፍ ስልት ባይኖር ኖሮ የረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ሐዲስ ዛሬ ላይ አይደርስም ነበር። ቢደርስም የተበከለና የተበላሸ መረጃ ይሆን እንደነበር መገመት አያስቸግርም። በዚህ ተገቢ በሆነ ሳይንሳዊ አካሄድ የኢስላማዊ የህግ ምንጭ ተጠብቆ እንዲቆይ ሆኗል። ቁርአን እንዲህ ይላል፡-

إِنَّا نَحْنُ نَزَّلْنَا الذِّكْرَ وَإِنَّا لَهُ لَحَافِظُونَ
 

“እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው። እኛም ለእርሱ ጠባቂዎቹ ነን።” (አል-ሂጀር 15፤9)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here