የሐዲስ ዓይነቶች

0
4048

የሐዲስ የጥናት መስክ “ሙሰጦለህ አል-ሐዲስ” ሀዲሶችን (ደረጃቸዉን መሰረት አድርጎ) የተለያዩ የሀዲስ አይነቶች እንዳሉ ያስተምራል። ከዚህ በታች የእያንዳንዱን ክፍል አሳጥረን እንመለከታለን።

  1. ሐዲሱ ከተወሰደበት ምንጭ አንጻር፡- ሀዲሱ የተወሰደዉ ቀጥታ ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ)፣ ከሰሐባ ወይም ከታብዒይ ሊሆን ይችላል። ከዚህ አንጻር ሐዲሱን በቀጥታ ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) የመጣ ከሆነ (መርፉዕ) ሲባል ከሰሀባ የተወሰደ ከሆነ የቆመ (መውቁፍ) ተብሎ ሲጠራ ከታቢዒይ ከተወሰደ የተቆረጠ (መቅጡዕ) ይባላል።
  2. ከመረጃዎ ሰንሰለት አንፃር (ኢስናድ)፡- ይህ ማለት ደግሞ የመረጃ ሰንሰለት የተቋረጠ ወይም የተቀጠለ መሆኑን የሚያመለክት ነው። ከዚህ አንጻር የመረጃው ሰንሰለት (ኢስናድ) ሰንሰለቱ የተደገፈ (ሙስነድ)፣ ቀጣይነት ያለውን (ሙተሲል)፣ የተቆረጠ (ሙንቀጢዕ)፣ የተንጠለጠለ (ሙዓለቅ)፣ የተምታታ (ሙዓደል) እና የመረጃው ሰንሰለ የተዘለለ ከሆነ- ከታቢዒይ ተነስቶ ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ የደረስውን (ሙርሰል) ይባላል።
  3. በእያንዳንዱ የመረጃ ሰንሰለት ሐዲሱን ከሚያስተላልፉት ሠዎች ቁጥር አንፃር፡- ሐዲሱ በብዙ አቅጣጫ ከተዘገበ ተከታታይ (ሙተዋቲር) ሲባል ከአንድ አቅጣጫ የተዘገበ ከሆነ ደግሞ ነጠላ (አሀድ) ይባላል። ነጠላ (አሀድ) በሶስት ይከፈላል። እነሱም እንግዳ (ገሪብ) መጠነኛ፤ ጠንካራ (ዐዚዝ) ታዋቂ (መሽሁር) ይባላል።
  4. ከሐዲሱ አዘጋገብ ሁኔታ አንፃር፡- ሐዲሱ “ከእገሌ” (ዓን) ተረከልን (ሐደሰና) ሐዲሱን ዘጋቢው ለተቀባዮቹ ሲተረክላቸው ደግሞ ነገረን (አኽበረና) ሐዲሱን ዘጋቢዉ ከሰማ (ሰሚዕቱ) ይላል። በተጨማሪም በዚህ የሐዲስ ሰንሰለት አዘጋገብ ስር ስለተደበቀ (ሙደለስ) እና ወጥ (ሙሰልሰል) የሀዲስ አይነቶችን ማየት ይቻላል።
  5. ከሐዲሱ ጥሬ መልዕክት (መትን) እና ከመረጃው ሰንሰለት (ኢሰናድ) አኳያ፡- በሐዲሱ ላይ የታማኝ ዘጋቢ ጭማሪ (ዚያደቱል ሲቃ) ይባላል። ታአማኒነቱ ዝቅ ያለው ዘጋቢ ታማኝ የሆነዉን ዘጋቢ ሲቃወም ኢ-መደበኛ (ሻዝ) ይባላል። በአንዳንድ ሁኔታም ግልፅ እና ምንክያታዊ ያልሆነ መልዕክት የያዘ ሀዲስ በሐዲስ አዋቂዎች ዘንድ “ሰነዱን” ግምት ውስጥ ሳያስገቡ ሀዲሱን ውድቅ ያደርጉታል። የዚህ አይነቱ ሐዲስ ተቀባይነት የሌለው (ሙንከር) ይባላል። ከዋናው የሐዲስ ገለፃ ላይ በዘጋቢዉ የሚጨመር ተጨማሪ ሀሳብ ደግሞ የተበረዘ (ሙድረጅ) ይባላል።
  6. በሐዲሱ ሰነድ ወይም መትን ረቂቅ እንከን ከመኖር አኳያ፡- ከላይ በተዘረዘሩት የሐዲስ አይነቶች ውስት ሊካተት ቢችልም ነጥሎ ማየቱ አይከፋም። ረቂቅ እንከን ያለበት በሽተኛ (ሙዐለል) ይባላል። ሐዲሱ ላይ የሚከሰተዉ እንከን የተለያየ ሊሆን ቢችልም በሽተኛ (ሙዐለል) ሀዲስ ሁለት አይነት መልክ አለዉ፤ እነሱም የተገለበጠ (መቅሉብ) እና የሚያጠራጥር (ሙጦሪብ)ናቸዉ።
  7. ከዘጋቢው ታማኝነትና አስተዋሽነት አንፃር፡- የሐዲሱ የመጨረሻ ውሳኔ ከዘጋቢው ታማኝነትና አስተዋሽነት አንፃር የተያያዘ ነው። ይህ ውሳኔም ሐዲስ እጅግ በጣም ትክክለኛ (ሶሒሕ)፣ መለስተኛ ትክክለኛ (ሐሰን)፣ ደካማ (ዶዒፍ) እና መሰረተ-ቢስ (መውዱዕ) ተብሎ እንዲከፈል ያደርጋል። ብዙ ጊዜ እነዚህ የሐዲስ አይነቶች መሰረት የሚያደረጉት ኢስናድ ላይ ያለውን የዘጋቢውን ሚና ከግምት ዉስጥ በማስገባት ነው።

 

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here