የሐዲስን መረጃ ማስተላለፍ

0
2223

የሐዲስን መረጃ ስርጭትና የማሰባሰብ ስራ በተከናወነባቸው የመጀመሪያዎቹ ሶስት ክ/ዘመናት የተለያዩ ሐዲሶችን የማስተማሪያና የማጥሪያ ዘዴዎች ተግባር ላይ ውለዋል።

እነዚህ ዘዴዎች የኋላ ኋላ በየመልካቸው ሊከፋፈሉና ቴክኒካዊ ብያኔም ሊበጅላቸው ችሏል። ቀጣዮቹ 8 ዘዴዎች ግንባር ቀደሞቹ ሲሆኑ ከእነዚህም የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ በጣም የሚታወቁና ትክክለኛነታቸውም በጣም የላቁ መመዘኛዎች ናቸው።

1. ሰምዕ (ከአስተማሪ ማዳመጥ)

ይህ ዘዴ አራት ንዑስ ሐዲስን የማስተላለፊያ ገጽታዎች (መልኮች) አሉት፡-

  1. መምህሩ በአዕምሮ የሸመደደውን (የሀፈዘውን) ለተማሪዎቹ ማስደመጥ፡- ይህ ዘዴ እስከ ሁለተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በሰፊው ተግባራዊ ሲሆን ቆይቷል። ከዚህ ጊዜ በኋላ ይህ ዘዴ እየቀነሰ መጥቷል። በዚህ ዘዴ መሰረት ተማሪዎች ብቃታቸው እስኪረጋገጥ ድረስ አስተማሪዎቻቸው ዘንድ ለረጅም ጊዜ ይቆዩ ነብር።
  2. መፅሐፍት ማንበብ፡- በዚህ ዘዴ መሰረት መምህሩ የራሱን መፅሐፍት (ተመራጩ መንገድ) ወይም የተማሪውን መፅሐፍ ሊያነብ ይችላል። የተማሪው መረጃ (መፅሐፍ) ከአስተማሪው ኮፒ የሆነ ወይም ተመርጦ የተወሰደ ነው።
  3. ጥያቄና መልስ፡- ተማሪዎች የተወሰነውን የሐዲስ ክፍል በቃላቸው እንዲይዙና ከዚያም (በአዕምሮዋቸው) እንዲሉት ይደረግና ቀሪውን ደግሞ መምህሩ እንዲጨርስ ይደረጋል።
  4. መረጃ መፃፍ፡- ይህ ዘዴ አስተማሪው ድምፁን ከፍ አድርጎ በማንበብ ተማሪዎቹ እንዲፅፉ የማድረጊያ ዘዴ ነው። በታሪክ ይህን ዘዴ ተግባራዊ ለማድረግ ክፍሎችን ለይቶ ሐዲሶችን ለማስተማር የተጠቀመው ወሲላ ኢብን አል-አሽቃ (የሦስተኛው ዓ.ሂ 83) ነው። ይህ ዘዴ መጀመሪያ አካባቢ ተማሪዎች ሐዲስን የሚያገኙበት አጋጣሚ የተወሰነ ስለነበር ብዙም ሳቢ አልነበረም። ቢሆንም ግን አዝ-ዙሁርይ (ሂ.አ 142 የሞተ) ቀድሞ የነበረውን የሐዲስ መረጃ ማስተላለፊያ መንገድ ትቶ ይህን ዘዴ ብቻውን ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ። ተማሪዎቹ ሐዲሱን ካልፃፉ ምሁራን ይህን ዘዴ ተግባራዊ አያደርጉም አበር።

ይህ ዘዴ ተግባራዊ የሚሆነው በአዕምሮ ያለውን መልሶ በመናገር ወይም ከመፅሐፍ እየተመለከቱ ሊሆን ይችላል። አንዳንዴ ፈጣን ፀሐፊ ከተማሪዎቹ ተመርጦ ሐዲሶችን እንዲመዘግብ ሲደረግ ቀሪዎቹ ደግሞ ፀሐፊው ሲዘግብ እንዳይሳሳት በትኩረት ይከታተሉታል። ከዚህም በኋላ እነዚህ ሰዎች የሐዲስ መፅሐፍትን በመፃፍ የራሳቸው መፅሐፍን ያዘጋጃሉ። ይህ ኮፒ ሆኖ የተዘጋጀው መፅሐፍ በተማሪዎቹ ወይም በመምህሩ ክለሳ ይደረግበታል።

2. ዐርድ (ከተማሪ ማዳመጥ)

በዚህ ዘዴ ተማሪዎች የመምህራቸውን መፅሐፍ በማንበብ ሌሎቹ ተማሪዎች የያዙትን መረጃ እንዲያመሳክሩ ማድረግ ወይም ትኩረት በተሞላበት መንገድ ሐዲሶቹን በፅሞና ማዳመጥን የሚመለከት ነው።

በመጀመሪያና በሁለተኛው ክፍለ ዘመን ላይ ይህ ዘዴ በጣም ታዋቂ እና ተቀባይነት ያለው ዘዴ ነበር። ብዙ ጊዜ መምህሩ የራሱን ኮፒ የሚያዘጋጀው እንደሌሎቹ በራሱ ፅሕፈት ነው። ተማሪዎች ቀድመው ኮፒ በማድረግ በያንዳንዱ ሀዲስ መጨለሻ ላይ በማክበብ ምልክት ያደርጋሉ ቀትሎም ከመምሀራቸው ጋር ያመሳክራሉ፡፡

ምንም እንኳ አንድ ተማሪ ሐዲሶችን ከመፅሐፍት ላይ ቢያውቃቸውም ለሌሎች ከማስተላለፉ ወይም በራሱ መድብል ውስጥ ከማካተቱ በፊት ወደ መምህሩ በመመለስ ያመሳክርና እንዲፀድቅለት ይደረጋል። ከዚህ ውጪ የሆነ ዘዴ ከተከተለ (ከሰራ) ግን “ሳሪቅ አል-ሀዲስ” (የሐዲስ ሌባ) ይባላል። ዛሬ በዘመናዊ መልኩ መረጃ የመውሰድ መንገድ “የኮፒ መብት” እንደሚባለው መሆኑ ነው። ሰዎች ብዙ የመፅሐፍት ኮፒዎችን መግዛት ቢችሉም የሰውን ስራ ግን አንድ ኮፒ እንኳ መልሰው ማሳተም አይችሉም።

3. ኢጃዛ (የማስተላለፍ ፍቃድ)

በሐዲስ መረጃን የመሰብሰብና የማስተላለፍ ትምህርት መሰረት “ኢጃዛ” መምህሩ ለተማሪው ሐዲሶቹን ለሌላ ሰው እንዲያስተላልፍ ፍቃድ መስጠት ነው። በዚህ ስራ ተማሪው የአስተማሪውን መፅሐፍ ይጠቀማል መልሶም ከመምህሩ ጋር የመናበብ ኃላፊነት የለበትም። ይህ ዘዴ ተግባራዊ መሆን የጀመረው ከሦስተኛው ክ/ዘመን ጀምሮ ነው። ዘዴው የሐዲስ ድርሳናትን ከመበረዝ አደጋ ይጠብቃል። ቢሆንም ግን የሰነዶቹን ፅኑነት ማረጋገጫ የሚሰጡት የተወሰኑ ምሁራን ናቸው።

4. ሙናወላ (መፅሐፍትን ማዋስ)

በዚህ ዘዴ ደግሞ መምህሩ የራሱን መፅሐፍ ለተማሪዎቹ በመስጠት ወይም ያረጋገጠውን የራሱን ኮፒ በእሱ ፍቃድ አማካኝነት ሐዲሶቹን ማስተላለፍ ነው። ለምሳሌ አዝ-ዙህሪ የራሱን የመረጃ ሰነዶች (ማኑስክሪፕት) ለብዙ ምሁራን ሰጥቷቸዋል ከነዚህም መካከል አስ-ሰወሪ፣ አል-ዐውዛዒ እና ዑብይዱሏህ ኢብኑ ዐማር ይገኙበታል። ይህ ዘዴ በመጀመሪያው ክ/ዘመን አካባቢ እምብዛም አልነበረም።

5. ኪታባ (ማስተላለፍ)

ይህ ዘዴ መምህሩ ሐዲሶችን ይፅፍና ለተማሪዎቹ ሐዲሶቹን ለሌላ ወገን እንዲያስተላልፍ መላክ ነው። በዚህም ነው ኪታባ (መፃፍ፤ ማስተላለፍ) የተሰኘው። ይህ ዘዴ በዛሬው ጊዜ ያለውን የርቀት ትምህርት አሰጣጥን (distance learning/ learning by correspondence) የሚመስል ተግባር ነው። ዘዴው በመጀመሪያው ክ/ዘመን አናሳ ነበር፡፡ የኸሊፋዎቹ ደብዳቤዎች አያሌ ሐዲሶችን የያዙና ኋላም በምሁራን የተላለፉ ናቸው። ብዙ ሊቃውንት ሐዲሶችን በመፃፍ ለተማሪዎቻቸው ልከዋል። ከነዚህም መካከል አብደሏህ ኢብኑ ዐባስ ተጠቃሽ ነው። እሱ ሐዲሶቹን በመፃፍ ለኢብኑ አቡሙላይካ እና ለነጅዳ ልኳል።

6. ኢዕላም (ይፋ ማድረግ)

ይህ ቃል አስተማሪ ወይም ተማሪ የእሱን መፅሐፍ ማስተላለፍ እንደሚችሉ ለሌሎች ፍቃድ መስጠትና ይህንንም ማሳወቂያ መንገድ ነው። ቢሆንም ግን ከማንኛውም ተማሪ በፊት ፍቃድ ሰጪው የሚተላለፈውን መፅሐፍ የያዘውን ሐዲስ መስማት ይኖርበታል። በዚህም ሐዲሱ የመጀመሪያው ቅጂ ሆኖ ካገኘው የእሱነቱን ፊርማ ያስቀምጥበታል።

7. ወሲያ (ባደራ መጠቀም)

ይህ ኃላፊነትን አሳልፎ የመስጠት (ሐዲሱን) ዘዴ ተግባራዊ የሚሆነው በሞት እለት ነው። ተማሪው ይህን ሐዲስ የማስተላፍ ፍቃድ የሚያገኘው የመፅሐፉ ባለቤት ወደ ሞት ሲቀርብ ነው። ለምሳሌ፡- አቡቂላብ አብደሏህ ኢብኑዘይድ አል-በስሪ (በሂ.አ 104 ላይ የሞተ) ታቢኢይ ነበር። ታዲያ እሱ ሞት ሲመጣበት የእሱ መፅሐፍ ለአዩብ አስ-ሳክቲያኒ እንዲሰጥለት ተናዟል።

8. ዊጃዳ (መጽሐፍ ማሰስ)

አንድ ተማሪ ወይም መምህር የማስተላለፍ ፍቃድ ሳያገኝ የአንድን ዓሊም የሐዲስ ጥራዝ አግኝቶ ቢያስተላልፍ በሐዲስ የመማር ስርዓት እውቅና የሚሰጠው ተግባር አይደለም። አንድ ሰው የሌላን መረጃ ወስዶ ማስተላለፍ ከፈለገ የግዴታ ከማን መፅሐፍ መረጃውን እንደወሰደ መጥቀስ ይኖርበታል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here