የሐዲስና የፊቅህ ጥምረት

0
3710

ሀዲስን ማጥናት የፈለገ ሰዉ የሀዲስና የፊቅህ ዕዉቀት ሊኖረዉ ይገባል። የሁለቱም መስክ ዕዉቀት በጥምረት ያለዉ ሰው ከመረጃዎቹ የተለያዩ አስምህሮቶችንና ህጎችን ማመንጨት ይችላል። ስለሆነም ብዙ ሙስሊም ምሁራን ለሁለቱም የትምህርት ዘርፎት ትኩረት የሚሰጡት።

በሂጅራ አቆጣጠር በ110 የሞቱት አል-ሐሰን አል-በሰሪ እንዲህ ይላሉ “አንድ ሰው ምንም እንኳ ብዙ ሀዲሶችን ቢያዉቅም ጥልቅ የሆነ የፊቅህ ግንዛቤ ከሌለዉ ዕዉቀቱ ጥቅም የለዉም።”

በሂጅራ አቆጣጠር 181 የሞቱት ዐብዱሏህ ኢብኑ አል-ሙባሪክ “አንድ ሰው መቼ ነው ፈትዋ መስጠት የሚችለው?” ተብለው ሲጠየቁ “የሀዲስን ዕውቀት በቅጡ የሚገነዘብና ምክንያታዊነትን በደንብ ማመንጨት (ፊቅህ) የሚችል ሰው ሲሆን” ብለዋል።

ለሐዲስ ሊቃውንት የፊቅህ ዕውቀት አስፈላጊነት

የሐዲስን ዕውቀት (ትምህርት) ለመገንዘብ፣ አስፈላጊነቱን ለመረዳት፣ አላማዉን ለማወቅና በተገቢዉ ሁኔታ በተግባር ላይ ለማዋል ጥልቅ ዕዉቀት ያለዉ ምሁር ያስፈልጋል። ችሎታ ያላቸው ምሁራን ሻሪ (ናሲኽ) መረጃ ከተሻሪ (መንሱኽ)፤ ሁለንተናዊ (ዓም) የሆነው ከተገደበው (ኻስ)፤ ውሱን (ሙቀየድ) የሆነን ክስተት የሚመለከተውን አጠቃላይ (ሙጥለቅ) ሁኔታ ከሚመለከተውና አጠቃላይ ገዥ ከሆነው ህግ ውሱን ጉዳይን ከሚመለከተው ህግ መካከል ያለውን በአግባቡ መለየት ይችላሉ።

ሐዲስ በጥሬ ትርጉሙ የሚወሰድ ከሆነ ብዙ ጥፋት ሊፈፀም ይቻላል። ስለሆነም የሐዲስ ሊቅ የትኛው ሐዲስ ለሚፈልገው ጉዳይ እንደሚውልና እንደሚተዉ የፊቅህ ዕዉቀት መማር አለበት።

አብዱረሕማን ኢብን መህዲ (198 ሂጅራ ላይ የሞቱ) ደግሞ “ልብ በሉ! አንድ ሰው ጥሩ ተብሎ የሚያዘውንና የማያዘውን መረጃ በቅጡ መለየት እስካልቻለ ድረስ ኢማም ሊባል አይችልም።” ለዚህም ነው አብደላህ ኢብን ወሐብ (197 ሂጅራ የሞቱ) ከኢማሙ ማሊክ ኢብኑ አነስ (179 ሂጅራ የሞቱ) ዘንድ እና ኢማሙ አል-ለይስ ኢብኑ ሰዐድ ሐዲስን ያጠኑና ይመረምሩ የነበረዉ።

ይህን የሚያደርጉት በሐዲስ ትምህርት ውስጥ የትኛው መርህ ተግባራዊ እንደሚሆንና እንደማይሆን ለይቶ ለማወቅ ነው። በተጨማሪም እንዲህ ብለዋል “ማሊክ እና አል-ለይስ ባይኖሩ ኖሮ እኔ ለጥፋት በተዳረግኩ ነበር። እኔ ሁሉም ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) የተባለ ሀዲስ ሁሉ በጥሬው ተግባራዊ የሚሆን ይመስለኝ ነበር”።

በተጨማሪም ዐብደላህ ኢብኑ ወህብ “አኔ 360 ምሁራንን አግኝቻለሁ። ነገር ግን እንደ ማሊክና እንደ አል-ለይስ የሚሆን አላየሁም። እኔም እነሱን ባላገኝ ኖሮ ከዕውቀት እርቅ ነበር” ይላሉ። እንዲህም ተጠየቁ “ሁኔታው እንዴት ነበር?” ሲመልሱ “እኔ ብዙ ሐዲሶችን ተምሪያለሁ ቢሆንም ግን ግራ ተጋብቸ ነበር። ስለሆነም ሐዲሶቹን ለማሊክና ለአል-ለይስ አሳየኋቸው። እነሱም መያዝና መተው ያለብኝን ነገሩን” ብለዋል።

የቡኻሪ ሸይኽ የሆኑት አቡ ኑዐም አል ፈድል ኢብኑ ዱኸይን (የሞቱት በ218 ሂጅራ ላይ ነው) እንዲህ አሉ “ዙፋር ኢብኑ ሁዘይል (የሐነፊ መዝሀብ አዋቂ ሲሆኑ የሞቱት በ158 ሂጅራ ላይ ነው) እጎበኝ ነበር።” እሱም ለእኔ እንዲህ ይለኛል “የሰማኸዉን እኔ አጣራልሃለሁ” በተጨማሪም “እኔ ለዙፋር ሀዲሶችን አሳየው ነበር” እሱም “ይህ ሐዲስ ሻሪ ሲሆን ይሄኛው ደግሞ ተሸሪ ነው” ይለኛል። እንዲሁም “ይህ ሀዲስ ተቀባይነት ያለው ሲሆን ይሄኛው ደግሞ ተቀባይነተ የሌለው ውድቅ ሀዲስ ነው” በማለት ይረዳኛል።

የሐዲስ ዐዋቂዎች (ሙሃዲሲን) ፊቅህ ለሐዲስ ያለውን ጠቀሜታ ስለተገነዘቡ የፊቅህ አዋቂዎችን (ፉቀሃ) ስለሐዲሱ የተለያዩ ትርጓሜዎች ማብራሪያ ይጠይቁ ነበር። የሁለቱ ዕውቀት መስኮች ጥምረት አስፈላጊነት ከቀጣዩ ምሳሌ መረዳት ይቻላል። አቡሐኒፋ (የሞቱት በ150 ሂጅራ) እንዲህ ይላሉ “ፊቅህን ችላ ብሎ ሀዲስን የሚያጠና ሰው ልክ በሽታን ሳያውቅ መድሀኒት እንደሚሰበስብ ፋርማሲስት ነው፤ በሽተኞች የሚድኑት የህክምና ባለሞያ ትክክለኛውን መድሀኒት ሲያዝ እንደሆነ ሁሉ ልክ እንደዚሁ የሀዲስ ተማሪም የሀዲሱን መልዕክት ሊያውቅ የሚችለዉ የፊቅህ ምሁራን በመልዕክቱ ላይ ውሳኔ ሲሰጡበት እንደሆነ ነው።”

በዚህ ምክንያት ብዙ ሊቃውንት (ኢማሞች) የሀዲስ ተማሪዎች የሀዲስ ጥናታቸው ፊቅህን መሰረት ያደረገ እንዲሆን ይመክራሉ። የሀዲስ ተማሪዎች ሐዲሶች በስንት መንገድ እንደተላለፉ ወይም ሐዲሶቹ ከህፀፅ የፀዱ መሆናቸው ላይ ብቻ ማትኮር የለባቸውም።

ማሊክ ኢቡኑ አነስ፤ አጎት ለሚሆንላቸው አቡበከርና ኢስማዒል (የኡወይስ ልጅ) እንዲህ ብለዋል “እናንተ ሐዲስን በአዕምሮችሁ መያዝን ትወዱ የለምን?” እነሱም አዎ አሉ። እሱም “እናንተ በምትማሩት ተጠቃሚ መሆን ከፈለጋችሁ፤ ከመሸምደድ በተጨማሪ ሐዲሱን ይዘት ለመገንዘብ ትኩረት መስጠት ይኖርባችኃል” የሚል ምክር ለግሷቸዋል።

አቡ ያዕቆብ ኢስሀቅ ኢቡኑ አል-ሑሰይን አል-ሐርቢ ደግሞ “ለአቡ ዐብደላህ አህመድ ኢብኑ ሐንበል (241 ዓ ሂጅራ የሞቱ) አንድ ሰው ተገቢ የሆነ የሀዲስ አመዘጋገብ እንዴት ሊጎናፀፍ ይችላል? ብዩ ጠየኩት እሱም ኢስሀቅ ሆይ! ሐዲስን ጥቅም ላይ ማዋል ሐዲሱን በአዕምሮ ከመሸምደዱ በጣም ከባድ ነው” እኔም እንዴት ነው መጠቀም የምችለው? ብየ ስጠይቃቸዉ “በሀዲሱ ላይ ጥልቅ የሆነ ጥናት ማድረግ አለብህ” አሉኝ ብሎ አስተላልፏል።

የፊቅህ ዕውቀት ላላቸው የሐዲስ ዘጋቢዎች ቅድሚያ መስጠት

በተለያዩ የሀዲስ መረጃዎች መካከል ግጭት በሚከሰትበት ወቅት ለፊቅህ ዕውቀት ባለቤት (ፉቀሃ) ዘጋቢዎች ቅድሚያ መሰጠቱ በአዋቂዎች መካከል የታወቀ ነገር ነው። አል-ኸጢብ አልባግዳዲ (በ463 ሂጅራ የሞቱ) እንዲህ ብለዋል፡-

“የሐዲስ መረጃን ለመቀበል ከማንኛውም ሰው ይልቅ የፊቅህ ዕውቀት ያላቸው ዘጋቢዎች ቅድሚያ መስጠት ተገቢ ነው። ምክንያቱም እነሱ ሸሪዓዊ ህጎችን ከሌሎቹ የበለጡ አዋቂዎች ስለሆኑ ነው።”

ሱፍያን ኢብኑ ሰዕድ አል-ሠወሪ (በ161 ሂጅራ የሞቱ) ደግሞ “ሐላል የሆነውንና ያልሆነውን የሚጠቅስ የሐዲስ ዘገባ የፊቅህ ዕውቀት ካላቸው አዋቂዎች ዘነድ ውሰድ። ነገር ግን ሌላውን ከሌሎች ምሁራን ውሰድ” ይህ ማለት ግን የፊቅህ ዕውቀት የሌላቸው ምሁራን ዘገባ ውድቅ ይደረጋል ማለት አይደለም። ቅድሚያ የሚሰጠዉ ሁለት የሚቃረኑ ዘገባዎች ሲገኙ በተወሰኑ መስፈርቶች አማካኝነት ለፊቅህ ዓዋቂ ቅድሚያ ይሰጣል ማለት ነው። ከመስፈርቶቹ አንዱ የሚሆነዉ ከዘጋቢዎቹ መካከል የትኛው የፊቅህ ዕውቀት እንዳለው የሚመለከት ሲሆን በተለይ የሐዲሱ መረጃ የተላለፈው ከቃላት ሳይሆን ከትርጉም አንፃር ከሆነ ይህ መስፈርት ቅድሚያ ይሰጠዋል። የፊቅህ ምሁራን ከሌሎች በተሸለ ሁኔታ የሐዲስን ትርጓሜና የሀሳቡን በትክክል ከመጠቆም አንፃር የተሻለ ብቃት አላቸው።

ሙሃዲስ በፊቅህ የትምህርት ዘርፍ ባይሳተፍና የሸሪዓውን መሰረታዊ ሳይንሳዊ ህጎች ባያውቅ ሀይማኖታዊ ብያኔዎችን ለማመንጨት (ኢስቲንባጥ አል-አህካም) ይቸገራል።

የሀዲስ ትምህርት ለፊቅህ ዕውቀት ያለው አስፈላጊነት

የሐዲስ አዋቂ (ሙሀዲስ) የፊቅህንና የሸሪዓውን መሰረታዊ መርሆች ማውቅ እንዳለበት ሁሉ የፊቅህ አዋቂም (ፈቂህ) ሐዲስንና ከሀዲስ ዕውቀት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመረጃ የመቀበል፣ የመጣል፣ የመተቸት (ጀርህ ወታእዲል) ወዘተ ሐዲሳዊ መርሆችን ማወቅ ይጠበቅበታል። በፊቅህ ምክንያታዊ (reasonable) ለመሆን በሚሞከርበት ጊዜ ያልተረጋገጡ የሀዲስ መረጃዎችን መሰረት ማድረግ የለበትም እንዲሁም ብዪኑ (ፈተዋዉ) ቢድዓ (ዒባዳዊ ፈጠራ) ውስጥ መዘፈቅ የለበትም።

ስለዚህ ሀዲስ ለፊቅህ ምሁር ሲቀርብና ምሁሩ የቃላቱን ቅድም ተከተልና ትክክለኛነት እርግጠኛ ካለሆነ በጉዳዩ ላይ የሐዲስ አዋቂ መጠየቅ ይኖርበታል። ስለሆነም በጉዳዩ ላይ አሰላስለዉ የራሳቸዉን ውሳኔ ለመስጠት ያስችላቸዋል።

በሂጅራ አቆጣጠር በ204 የሞቱት ኢማሙ ሻፊዒ፤ ለኢማሙ አህመድ ኢብኑ ሀንበል እንዲህ ይሏቸዋል “ይህ ሐዲስ ጠንከራ የሆነ የመረጃ ሰንሰለት (ሰነድ) አሉትን? ሀዲሱ በአንተ ወይስ በሌሎች ነዉ የተዘገበው?” የዚህ ጥያቄ ምላሽ አወንታዊ ከሆነ እሱ ሐዲሱን የፊቅህ ህግጋት ምንጭ አድርጎ መጠቀም እንዲችል ያደርገዋል። አብዛሃኛዉን ጊዜ ኢማሙ ሻፊዒ ፊቅህ አቋማቸዉን ጥያቄ ዉስጥ የሚያስገቡት ሀዲሱ ደካማ ወይም ግልፅ ሳይሆን ሲቀር ነዉ።

የፊቅህ ተማሪዎች ብዙ ውጤታማ ለመሆን ትኩረት የሚያደረጉት ፊቅሀዊ ህጎችን በአዕምሮቸው በመያዝና ህጎቹን ካወጧቸው ኢማሞቻቸው መረጃ መውሰድ ላይ ነው። ስለሆነም የፊቅህ ተማሪዎች የያዙት መረጃ ተቀባይነት ይኑረው አይኑረው አስፈላጊ የሆኑ የሀዲስ ጥራዞችን ከመዳደስ ችላ ይላሉ ወይም ትኩረት አይሰጡም። እንዲህ አይነቱ ሰው ዕውቀቱ ውሱን የሆነ ነው። በተጨማሪም ይህ ግለሰባዊ አላዋቂነትን በፊቅህ ምሁራን በቀላሉ ሊጋለጥ የሚችል ነገር ነው።

ሱናን የሚያጠና ሰው የሐዲስና የፊቅህን ሙሉ መሰረታዊና ዝርዝር መርሆች ማወቅ ግድ ይለዋል። እነዚህን መርሆች በተገቢው መንገድ የማስኬድና ፈትዋ የመስጠት ብቃት ይኖረዋል። ይህም ተማሪዎች ኢስላማዊ ህጎች ላይ ጥሩ ስሜት እንዲፈጠርባቸው ያግዛል። ስለሆነም ሰዎች መረጃዎችን ያለአግባብ የመተንተን ተግባር እንዳይፈፅሙ ያግዳል። በአጠቃላይ ፈቅህ የሐዲስ ቅርንጫፍ ሲሆን ሐዲስ ደግሞ ፊቅህ የተመሰረተበት መሰረት ነው። ስለሆነም አንዱ ለሌላዉ መኖር ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትና ተደጋጋፊ የዕዉቀት መስኮች መሆናቸዉን ያሳያል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here