ለምን ሱናን እንከተላለን?

0
10304

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

“ለእናንተ አጥብቃችሁ እስከያዛችኋቸው ድረስ በፍፁም የማትጠሙበትን ነገሮች ትቼላችኋለሁ እነሱም፡- የአላህን መፅሐፍ (ቁርዓን) እና የኔን ፈለግ (ሱና)”

አላህ (ሱ.ወ) በቁርዓን ውስጥ እንደነገረን

الْيَوْمَ أَكْمَلْتُ لَكُمْ دِينَكُمْ وَأَتْمَمْتُ عَلَيْكُمْ نِعْمَتِي وَرَضِيتُ لَكُمُ الْإِسْلَامَ دِينًا
 

“ዛሬ ሃይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ፤ ፀጋዬንም በናንተ ላይ ፈፀምኩ፤ እስልምናንም ለእናንተ እንደሃይማኖት ወደድኩላችሁ” (አል-ማዒዳህ 5፤3)

ኢስላም የመጨረሻ ሰማያዊ እምነት ነው። ነብዩ መሐመድ ደግሞ “የአላህ መልዕክተኛና የነብዮች መደምደሚያ ናቸው” (አል-አህዛብ 33፤40) ሙስሊሞች የአላህን እዝነት፤ ተቀባይነት እንዲሁም ጀነትን ለማግኘት ምን ዓይነት ባህሪ መላበስ እንዳለባቸው ሊያውቁ ይገባል። ከምን መቆጠብ ምን ዓይነት ተግባራት መፈፀም እንዳለባቸው፤ ሀላልና ሀራም ነገሮችን፤ በአጠቃላይ በህይወታቸው አላህን የሚያስደስቱ ነገሮችን ጠንቅቀው ማወቅ ይኖርባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምንጫቸው ቁርዓን ነው። አላህ ለባሪያዎቹ አዛኝ በመሆኑ አርአያ ሊሆነን የሚችል መልዕክተኛ ላከልን፤ እሱን በመከተልም የአላህን ውዴታ እንደምናገኝ ነገረን፤ የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የስነ ምግባር እሴቶች ሁሌም እራሳችንን የምንገመግምባቸው መመዘኛዎች ናቸው።

لَّقَدْ كَانَ لَكُمْ فِي رَسُولِ اللَّهِ أُسْوَةٌ حَسَنَةٌ لِّمَن كَانَ يَرْجُو اللَّهَ وَالْيَوْمَ الْآخِرَ وَذَكَرَ اللَّهَ كَثِيرًا
 

“ለእናንተ አላህንና የመጨረሻውን ቀን የሚከጅል ለሆነ ሰው፣ አላህንም በብዙ ለሚያወሳ በአላህ መልዕክተኛ መልካም መከተል አልላችሁ።” (አል-አህዛብ 33፤ 21)

ነብዩ ሙሐመድ ከነበራቸው የእምነት፣ የመለኮታዊነት፤ በዕውቀት የመጠቁ የስነምግባር እሴቶች አንፃር ለሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዓርአያ ሊያደርጋቸው የሚገባ ስብዕና ነበሩ። ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) የነበራቸው ትዕግስት፤ ዕምነት፤ ጀግንነት፤ ተሰጥኦ፤ ወደ አላህ መቅረብ፤ ፍትህ፤ ርህራሄ፤ ፍቅር፤ ለሙዕሚኖች የነበራቸው ጥልቅ ስሜት እና የሌሎች የስነ-ምግባር እሴቶች ባለቤት መሆን ለርሳቸው ቅርብ በነበሩት ባልደረቦቻቸው ተመስክሮላቸዋል።

ሁሉም ሙስሊም እነዚህን በቁርዓን ውስጥ የተጠቀሱ ድንቅ ባህሪያትን መላበስና በዚህም የረሱልን (ሰ.ዐ.ወ) ምክሮች፣ ንግግሮች፣ ተግባራት በአጠቃላይ የሳቸውን የህይወት ፈለግ (ሱና) መከተል ይጠበቅበታል።

የእርሳቸውን መንገድ መከተል እንዳለብን ከሚገልፁ ቁርዓን አንቀፆች መሀከል አል-ኒሳእ 4፤80 እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

مَّن يُطِعِ الرَّسُولَ فَقَدْ أَطَاعَ اللَّهَ وَمَن تَوَلَّىٰ فَمَا أَرْسَلْنَاكَ عَلَيْهِمْ حَفِيظًا
 

“መልክተኛውን የሚታዘዝ ሰው በእርግጥ አላህን ታዘዘ። ከትእዛዝም የሸሸ ሰው (አያሳስብህ)። በእነሱ ላይ ጠባቂ አድርገን አልላክንህምና።” (አል-ኒሳእ 4፤80)

አንድ አማኝ ለአላህ ያለው ታማኝነትና ታዛዥነት ለረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ባለው ታዛዥነትና ፅናት ይለካል። በመሰረቱ አላህ መልዕክተኞችን የላከው ሰዎችን ወደትክክለኛው መንገድ እንዲመሩ ነው። ሰዎች እንደ አላህ ፍቃድ ኑሮአቸውን መምራት እንዲሁም የርሱን ውዴታ ማግኘት ከፈለጉ መልዕክተኛውን መታዘዝና በእርሱ መንገድ ላይ ቀጥ ማለት አለባቸው ይህንን እውነታ ቁርዓን እንዲህ ሲል ገልፆታል።

كَمَا أَرْسَلْنَا فِيكُمْ رَسُولًا مِّنكُمْ يَتْلُو عَلَيْكُمْ آيَاتِنَا وَيُزَكِّيكُمْ وَيُعَلِّمُكُمُ الْكِتَابَ وَالْحِكْمَةَ وَيُعَلِّمُكُم مَّا لَمْ تَكُونُوا تَعْلَمُونَ 

“በውስጣችሁ ከናንተው የኾነን በናንተ ላይ አንቀጾቻችንን የሚያነብላችሁና የሚያጠራችሁ፣ መጽሐፍንና ጥበብንም የሚያስተምራችሁ፣ ታውቁት ያልነበራችሁትንም ነገር የሚያሳውቃችሁ የኾነን መልክተኛ እንደላክን (ጸጋን ሞላንላችሁ)።” (አል-በቀራህ 2፤151)

የተፍሲር ምሁራን በዚህ አንቀፅ ውስጥ “ጥበብ” ሲል አላህ የገለፀው የነብዩን ፈለግ (ሱና) መሆኑን ይስማማሉ።

ሙዕሚኖች በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በመካከላቸው አለመስማማት ቢከሰት ይህንን ችግር በቁርዓንና በሱና መፍታት እንዳለባቸው አላህ ይነግረናል።

فَلَا وَرَبِّكَ لَا يُؤْمِنُونَ حَتَّىٰ يُحَكِّمُوكَ فِيمَا شَجَرَ بَيْنَهُمْ ثُمَّ لَا يَجِدُوا فِي أَنفُسِهِمْ حَرَجًا مِّمَّا قَضَيْتَ وَيُسَلِّمُوا تَسْلِيمًا
 

“በጌታህም እምላለሁ በመካከላቸው በተከራከሩበት ፍርድ እስከሚያስፈርዱህ ከዚያም ከፈረድከው ነገር በነፍሶቻቸው ውስጥ ጭንቀትን እስከማያገኙና ፍጹም መታዘዝንም እስከሚታዘዙ ድረስ አያምኑም፤ (ምእመን አይኾኑም)።” (አል-ኒሳእ 4፤65)

ሱና ቁርዓንን እንዴት መረዳት (መገንዘብ) እንዳለብን ይነግረናል። ስለሆነም የትኛውም ሙስሊም (ወንድም ሆነ ሴት) ሱናን ተግባራዊ በማድረግ ረሱልን (ሰ.ዐ.ወ) መከተል ይኖርበታል።

በዚህ ረገድ አል-አህዛብ 33፡36፣ አል-ሀሽር 59፡7፣ አል-ኑር 24፡51 ከላይ የተገለፀውን ሀሳብ ሚያጠናክሩ የቁርዓን ምሳሌዎች ናቸው።

وَمَا كَانَ لِمُؤْمِنٍ وَلَا مُؤْمِنَةٍ إِذَا قَضَى اللَّهُ وَرَسُولُهُ أَمْرًا أَن يَكُونَ لَهُمُ الْخِيَرَةُ مِنْ أَمْرِهِمْ وَمَن يَعْصِ اللَّهَ وَرَسُولَهُ فَقَدْ ضَلَّ ضَلَالًا مُّبِينًا 

“አላህና መልክተኛውም ነገርን በፈረዱ ጊዜ ለምእምናንና ለምእምናት ከነገራቸው ለእነርሱ ምርጫ ሊኖራቸው አይገባም! የአላህንና የመልክተኛውንም ትእዛዝ የጣሰ ሰው ግልጽ የሆነን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ።” (አል-አህዛብ 33፤36)

وَمَا آتَاكُمُ الرَّسُولُ فَخُذُوهُ وَمَا نَهَاكُمْ عَنْهُ فَانتَهُوا وَاتَّقُوا اللَّهَ إِنَّ اللَّهَ شَدِيدُ الْعِقَابِ
 

“መልክተኛውም የሰጣችሁን (ማንኛውንም) ነገር ያዙት። ከእርሱም የከለከላችሁን ነገር ተከልከሉ። አላህንም ፍሩ። አላህ ቅጣተ ብርቱ ነውና።” (አል-ሀሽር 59፤7)

إِنَّمَا كَانَ قَوْلَ الْمُؤْمِنِينَ إِذَا دُعُوا إِلَى اللَّهِ وَرَسُولِهِ لِيَحْكُمَ بَيْنَهُمْ أَن يَقُولُوا سَمِعْنَا وَأَطَعْنَا وَأُولَٰئِكَ هُمُ الْمُفْلِحُونَ
 

“የምእምናን ቃል የነበረው ወደ አላህና ወደ መልክተኛው በመካከላቸው ሊፈርድ በተጠሩ ጊዜ ሰማን፤ ታዘዝንም ማለት ብቻ ነው። እነዚህም እነሱ የፈለጉትን የሚያገኙ ናቸው።” (አል-ኑር 24፤51)

እራስን ለመልዕክተኛው መስጠት፣ እንዲሁም በትዕዛዙ ስር ሙሉ በሙሉ ማደር የአንድን ሙስሊም የእምነት ፅናት ያመለክታሉ። ለመልዕክተኛው እጅ መስጠት ማለት ለአላህ እጅ መስጠት ነው የሚለውን ፅንስ ሀሳብ በህይወታቸው ላይ የሚተገብሩ ሙስሊሞች ይህ አመለካከታቸው ስለ እስልምና ያላቸውን የጠራ ግንዛቤ ያሳያል።

وَمَا يَنطِقُ عَنِ الْهَوَىٰ إِنْ هُوَ إِلَّا وَحْيٌ يُوحَىٰ 

“ከልብ ወለድም አይናገርም። እርሱ (ንግግሩ) የሚወርረድ ራእይ እንጅ ሌላ አይደለም።” (አል-ነጅም 53፤3-4)

ረሱልም (ሰ.ዐ.ወ) በበኩላቸው የሳቸውን መንገድ መከተል እንዳለብን ሳያስተምሩ አላለፉም። በተለይ ከእርሳቸው በኋላ የሚመጡት ትውልዶች መንገዳቸውን እንዲከተሉ በሚከተለው ሐዲሳቸው አጥብቀው አስጠንቅቀዋል

“ከእኔ በኋላ የመኖር እድል ያላችሁ ሰዎች ብዙ አለመስማማቶችን ታያላችሁ ታዲያ ያን ጊዜ የእኔና የአራቱን ምትኮች (ኸሊፋዎች) መንገድ መከተል አለባችሁ (ማለትም አቡበከር፣ ኡመር፣ ኡስማንና አሊይ)። መንገዴን ያዙ፤ እጅግ የሙጥኝ ብላችሁም ያዙት፤ አዳዲስ ነገሮችን (በዲኑ ጉዳይ ላይ) ተጠንቀቁ፤ ምክንያቱም አዳዲስ ነገሮች ፈጠራዎች ናቸውና። ፈጠራ ደግሞ ወደ ጥመት ያመራል። ከንግግሮች ሁሉ በላጩ ቁርዓን ነው። ከጎዳናዎች ሁሉ ቅኑ ጎዳና የነብዩ ሙሐመድ ነው” (ኢብን ማጃህ)

በተጨማሪም ሱና ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ህዝቦቻቸውን የጠሩበት ጎዳና ለሙዕሚኖች ዳግሞ ህይወትን እንደሚለግሳቸው ልንዘነጋ አይገባም። አላህም በቁርዓኑ እንዲህ ይለናል

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا اسْتَجِيبُوا لِلَّهِ وَلِلرَّسُولِ إِذَا دَعَاكُمْ لِمَا يُحْيِيكُمْ وَاعْلَمُوا أَنَّ اللَّهَ يَحُولُ بَيْنَ الْمَرْءِ وَقَلْبِهِ وَأَنَّهُ إِلَيْهِ تُحْشَرُونَ 

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! (መልክተኛው) ሕያው ወደሚያደርጋችሁ እምነት በጠራችሁ ጊዜ ለአላህና ለመልክተኛው ታዘዙ። አላህም በሰውየውና በልቡ መካከል የሚጋርድ መኾኑን ወደርሱም የምትሰበሰቡ መኾናችሁን እወቁ።” (አል-አንፋል 8፤24)

ፅኑ ሙስሊሞች የመልዕክተኛውን መንገድ አጥብቀው መያዝና የእርሱን ፈለግ መንገዳቸው አድርገው መያዝ ይጠበቅባቸዋል። ምክንያቱም የረሱልን ጎዳና መከተል ህያው እንደሚያደርጋቸው ጠንቅቀው ያውቃሉና።

አላህን የሚፈራ እና የርሱን ውዴታ ለማግኘት የሚጥር ሰው የመልዕክተኛው ታማኝ ተከታይና እርሱን በዕምነትና በስነ-ምግባር የሚመስል መሆን አለበት። ይህ ደግሞ የሚሳካው ቁርዓንን አጥብቀን ስንይዝና የነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) ሱና መተግበር ስንችል ብቻ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here