የሐዲስ አስፈላጊነት በእስልምና

0
2975

ሐዲስና ቁርአን የማይነጣጠሉ አንድ አካል ናቸው። የሐዲስ መረጃዎችን ሳናጣቅስ ቁርዓንን መረዳት ፈፅሞ አዳጋች ነው። ቁርዓን በጅብሪል (ዐ.ሰ) አማካኝነት ከአላህ (ሱ.ወ) የመጣ መልዕክት ሲሆን ሐዲስ (የነብዩ /ሰ.ዐ.ወ/ ንግግሮች፣ ተግባራትና አጠቃላይ ህይወት) ደግሞ የዚህ መልዕክት ማብራሪያ ነው። ይህንን ሀሳብ የሚከተሉት አራት ነጥቦች ያጠናክሩልናል።

1. ቁርዓን በበርካታ አንቀፆች ላይ በግልፅ እደሚያሰወቀምጠው የመልዕክተኛው ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ተግባር መልዕክቱን (ቁርዓንን) ማድረስ ብቻ እንዳልሆነ እንረዳለን። ይልቁንም መልዕክቱን የማብራራትና ግልፅ የማድረግ ሀላፊነት ተሰጥቷቸው ነው የተላኩት።

ይህ ሀሳብ በበርካታ የቁርዓን አንቀፆች ውስጥ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ለምሳሌ፡- አል-ነህል 16፤44 እንዲሁም አል-ነህል 16፤64 መጥቀስ ይቻላል።

وَأَنزَلْنَا إِلَيْكَ الذِّكْرَ لِتُبَيِّنَ لِلنَّاسِ مَا نُزِّلَ إِلَيْهِمْ وَلَعَلَّهُمْ يَتَفَكَّرُونَ
 

“ወደ አንተም ለሰዎች ወደእነሱ የተወረደውን (ፍች) ልትገልጽላቸውና ያስተነትኑም ዘንድ ቁርኣንን አወረድን፡፡” (አል-ነህል 16፤44)

وَمَا أَنزَلْنَا عَلَيْكَ الْكِتَابَ إِلَّا لِتُبَيِّنَ لَهُمُ الَّذِي اخْتَلَفُوا فِيهِ وَهُدًى وَرَحْمَةً لِّقَوْمٍ يُؤْمِنُونَ
 

“ባንተም ላይ መጽሐፉን አላወረድንም፤ ያንን በርሱ የተለያዩበትን ለነርሱ ልታብራራላቸውና ለሚያምኑትም ሕዝቦች መሪና እዝነት ሊኾን እንጂ፡፡” (አል-ነህል 16፤64)

ስለዚህ ከላይ ከተጠቀሱት የቁርዓን አንቀፆች የምንረዳው ነገር፣ ሐዲስ ቁርዓንን ግልፅ ከማድረግ እና ከማብራራት በዘለለ በቁርዓን ላይ ያሉ ብዥታዎችን የማጥራት ሚና ይጫወታል። ስለሆነም ሐዲስን ወደጎን በመተው የቁርዓንን አጠቃላይ መልዕክት ለመረዳት መሞከር ፍፁም የማይቻል ነገር ይሆናል።

2. ያለሐዲስ ተጨማሪ ማብራሪያ አብዛኛዎቹ የእስልምና አስተምህሮዎች ከወረቀት ፅሁፍነት የዘለለ ሚና አይኖራቸውም። ምክንያቱም ያለሐዲስ እንዴት መስገድ፣ መፆም፣ ዘካ ማውጣት እንዲሁም ሀጅ ማድረግ እንዳለብን አናውቅም። እነዚህን የአምልኮ ግዴታዎች በደፈናው ተቀመጡ እንጂ በቁርዓን ውስጥ እንዴት ለሚለው ጥያቄ ሰፋ ያለ ምላሽ አናገኝም።

3. አላህ (ሱ.ወ) በቁርዓኑ እንደሚነግረን ከሆነ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ለተከታዮቻቸው ያስተማሩት ቁርዓኑን ብቻ ሳይሆን ጥበቡንም (ሒክማ) ጭምር ነው። ይህን በተመለከተ በቁርዓን ውስጥ 2:231፣ 33፡34፣ 4፡113 እና ሌሎችንም መመልከት ይቻላል።

وَاذْكُرُوا نِعْمَتَ اللَّهِ عَلَيْكُمْ وَمَا أَنزَلَ عَلَيْكُم مِّنَ الْكِتَابِ وَالْحِكْمَةِ يَعِظُكُم بِهِ وَاتَّقُوا اللَّهَ وَاعْلَمُوا أَنَّ اللَّهَ بِكُلِّ شَيْءٍ عَلِيمٌ 

“የአላህንም ጸጋ በናንተ ላይ ያደረገውን ከመጽሐፍና ከጥበብም በርሱ የሚገስጻችሁ ሲኾን በናንተ ላይ ያወረደውን አስታውሱ፡፡ አላህንም ፍሩ፤ አላህም ነገሩን ሁሉ ዐዋቂ መኾኑን ዕወቁ፡፡” (አል-በቀራ 2፤231)

وَاذْكُرْنَ مَا يُتْلَىٰ فِي بُيُوتِكُنَّ مِنْ آيَاتِ اللَّهِ وَالْحِكْمَةِ إِنَّ اللَّهَ كَانَ لَطِيفًا خَبِيرًا
 

“ከአላህ አንቀጾችና ከጥበቡም በቤቶቻችሁ የሚነበበውን አስታውሱ፡፡ አላህ እዝነቱ ረቂቅ ውስጠ ዐዋቂ ነውና፡፡” (አል-አህዛብ 33፤ 34)

وَأَنزَلَ اللَّهُ عَلَيْكَ الْكِتَابَ وَالْحِكْمَةَ وَعَلَّمَكَ مَا لَمْ تَكُن تَعْلَمُ وَكَانَ فَضْلُ اللَّهِ عَلَيْكَ عَظِيمًا
 

“አላህም በአንተ ላይ መጽሐፍንና ጥበብን አወረደ፡፡ የማታውቀውንም ሁሉ አስተማረህ፡፡ የአላህም ችሮታ በአንተ ላይ ታላቅ ነው፡፡” (አን-ኒሳእ 4፤ 113)

እንደ ኢማሙ ሻፊዒ አባባል ከሆነ “ጥበብ” ሲል አላህ (ሱ.ወ) የገለፀው የረሱልን (ሰ.ዐ.ወ) ፈለግ ወይም ሱናን ነው። እናም ሐዲስን መተው (ችላ ማለት) ቁርዓንን እንደመተው (ችላ እንደ ማለት) ሊቆጠር ይችላል።

4. ቁርዓን ሁሌም መልዕክተኛውን (ሰ.ዑ.ወ) እንድንታዘዝና መመሪያቸውን እንድናከብር በተለያዩ አንቀፆች ገልፆልናል። ተከታዮቹ አንቀጾች ለዚህ ምሳሌ ይሆኑናል፡-

فَلَا وَرَبِّكَ لَا يُؤْمِنُونَ حَتَّىٰ يُحَكِّمُوكَ فِيمَا شَجَرَ بَيْنَهُمْ ثُمَّ لَا يَجِدُوا فِي أَنفُسِهِمْ حَرَجًا مِّمَّا قَضَيْتَ وَيُسَلِّمُوا تَسْلِيمًا
 

“በጌታህም እምላለሁ በመካከላቸው በተከራከሩበት ፍርድ እስከሚያስፈርዱህ ከዚያም ከፈረድከው ነገር በነፍሶቻቸው ውስጥ ጭንቀትን እስከማያገኙና ፍጹም መታዘዝንም እስከሚታዘዙ ድረስ አያምኑም፤ (ምእመን አይኾኑም)፡፡” (አን-ኒሳዕ 4፤65)

وَأَنِ احْكُم بَيْنَهُم بِمَا أَنزَلَ اللَّهُ وَلَا تَتَّبِعْ أَهْوَاءَهُمْ وَاحْذَرْهُمْ أَن يَفْتِنُوكَ عَن بَعْضِ مَا أَنزَلَ اللَّهُ إِلَيْكَ فَإِن تَوَلَّوْا فَاعْلَمْ أَنَّمَا يُرِيدُ اللَّهُ أَن يُصِيبَهُم بِبَعْضِ ذُنُوبِهِمْ وَإِنَّ كَثِيرًا مِّنَ النَّاسِ لَفَاسِقُونَ
 

“በመካከላቸውም አላህ ባወረደው ሕግ ፍረድ፡፡ ፍላጎቶቻቸውንም አትከተል፡፡ አላህም ወደ አንተ ካወረደው ከከፊሉ እንዳያሳስቱህ ተጠንቀቃቸው (ማለትን አወረድን)፡፡ ቢዞሩም አላህ የሚሻው በከፊሉ ኃጢአታቸው ሊቀጣቸው መኾኑን ዕወቅ፡፡ ከሰዎቹም ብዙዎቹ አመጸኞች ናቸው፡፡” (አል-ማዒዳህ 5፤49)

ታዲያ ይህን መሰል ትዕዛዛት (ውሳኔዎችን) ከሐዲስ ውስጥ ካልሆነ የት ልናገኛቸው እንችላላን?

ቁርዓን ሙእሚኖችን መልክተኛውን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው አርአያ አድርገው እንዲይዙና ይህም የአላህን ውዴታ ለማግኘት ብቸኛው መንገድ እንደሆነ ይገልፃል። ስለዚህ በዘወትር እንቅስቃሴያችን የመልዕተኛውን ባህሪያትና ተግባራት ማንፀባረቅ በእጅጉ አስፈላጊ ይሆናል። ይህንን ልናደርግ የምንችለው ደግሞ ሐዲን በአግባቡ ማጥናት ስንችል ነው።

ዓኢሻ (ረ.ዐ.) ስለረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ባህሪ በተጠየቀች ግዜ የሰጠችው መልስ ይህን ጉዳይ በደንብ ያብራራልናል። ስለረሱል (ሰ.ዐ.ወ) የተናገረችው እንዲህ ብላ ነበር “ባህሪያቸው ቁርዓን ነበር” ይህ ማለት ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) የቁርዓን ፅንስ ሃሳቦችንና እሴቶችን በተግባር አንፀባርቀዋል እንደማለት ነው። ታዲያ እንዴት አድርገን ነው ቁርዓናዊ ሀሳቦች ግልፅ የተደረጉበትን እና ወደ ነብዩ ህይወት ሊመሩን የሚችሉትን የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሐዲሶች ገሸሽ የምናደርገው? ይህን ስንል ግን አንድ ልንረዳው የሚገባ ነጥብ አለ ይኸውም ሁሉም የሐዲስ ስብስቦች እውነተኛ እና ቅን ናቸው ማለታችን አይደለም። ሐዲሶች ሁሌም ቢሆን ታላላቅ የኢስላም ምሁራን ባስቀመጧቸው መመዘኛዎች መገምገም አለባቸው። ከመመዘኛዎቹ ውስጥ ከመሠረታዊ የቁርዓን መርህ ጋር ወይም ግልፅ ከሆነ ዕውነታ ጋር የሚጋጭ ከሆነ ምንጩ ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ስለማይሆን እንደ ሀዲስ አይወሰድ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here