ተውሒድና ዓይነቶቹ (ክፍል 3)

0
3531

ሦስተኛ- ተውሒድ አል-አስማ ወስ-ሲፋት

ተውሒድ አል-አስማ ወስ-ሲፋት ትርጉምና ይዘት፡- አላህ በምሉእ ባህሪያት የሚገለጽ፣ ከጎደሎ ባህሪያት ሁሉ የጠራ፣ በመልካም ስሞች የሚጠራና በዚህ ረገድ ከፍጡራን ሁሉ የተለየ መሆኑን በእርግጠኝነት ማመን፤

አላህ ወይም መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ያጸደቋቸውን በቁርአንና በሱንና የተገለጹ የአላህ ስሞችና ባህሪያት የቃላት አወቃቀራቸው ወይም ትርጉማቸውን ሳይለውጡ (ተሕሪፍ)፣ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ውድቅ ሳያደርጉ (ተዕጢል)፣ በምናብ ቅርጽ ሳያስይዙ (ተክዪፍ) ወይም ከፍጡራን ባህሪያት ጋር ሳያመሳስሉ (ተሽቢህ) እንደወረዱ መቀበል ግዴታ ነው።

ይህ ማብራሪያ ሦስት መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳቦችን የያዘ ሲሆን፣ አንዱን ያጓደለ ይህን የተውሒድ ዘርፍ አላሟላም።

  • አንደኛ፡- አላህን ከፍጡራን ጋር ከማመሳሰል (ተሽቢህ) ወይም ከጎደሎ ባህሪያት ማጽዳት፣
  • ሁለተኛ፡- በቁርአንና በሱንና የተገለጹ የአላህ ባህሪያትንና ስሞች ሳይቀንሱና ሳይጨምሩ ወይም ውድቅ ሳያደርጉ (ተዕጢል) እንደወረዱ መቀበል፣
  • ሦስተኛ፡- እነዚህን ባህሪያትና ስሞች ምናባዊ ቅርጽ (ተሽቢህ) ለማስያዝ ከመሞከር መታቀብ።

ግዴታዎች፡- የአላህን ባህሪያትና ስሞች ከርሱ ምሉእነት ጋር በሚጣጣሙ ትርጉሞቻቸው መረዳት፤ ይህውም ከፍጡራን ማመሳሰል (ተሽቢህ)፣ ይዘታቸውን ማራቆት (ተዕጢል)፣ ወይም በምናብ ቅርጽ ለማስያዝ መሞከር (ተክዪፍ) ያልታከለበትን ትክክለኛ ትርጉማቸውን መቀበል፤ ኢማም አሽ-ሻፊዒ የተናገሩትን ተከታዩን ጽንሰ ሐሳብ ማጽደቅ ነው፡-

آمنت بالله وبما جاء عن الله على مراد الله

“በአላህ፣ ከአላህ በመጣው መልእክት፣ እርሱ በፈቀደው ትርጉሙና ይዘቱ አምኛለሁ።”

የአላህ ስሞች፡- አላህ በቁርአኑ እንዲሁም መልእክተኛው በሱንናቸው የአላህን መልካም ሰሞች አስተዋውቀውናል። እነርሱም የአላህን ባህሪያት ለማስተዋወቅ የሚረዱ ስሞች ሁሉ ናቸው። የአላህን ስሞችና ባህሪያት መልእክት አጠቃልሎ የያዘው ቃል “አላህ” የሚለው ሲሆን፣ አምላካችንን የምንጠራው፣ የምናስታውሰው፣ የምናመልከው፣ የምንለምነው እነዚህን ስሞቹን ተጠቅመን ነው። አላህ እንዲህ ብሏል፡-

وَلِلَّهِ الْأَسْمَاءُ الْحُسْنَىٰ فَادْعُوهُ بِهَا
 

“ለአላህም መልካም ስሞች አሉት፡፡ (ስትጸልዩ) በእርሷም ጥሩት።” (አል-አዕራፍ 7፤ 180)

አቡ ሁረይራ (ረ.ዐ) እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

إن لله تسعة وتسعين اسمًا مائة إلا واحدًا – من أحصاها دخل الجنة

“አላህ ዘጠና ዘጠኝ ስሞች አሉት- ከመቶ አንድ ሲቀር- እነርሱን በአእምሮው የያዘ ጀነት ገባ።” (ቡኻሪ፣ ሙስሊም፣ ነሣኢ፣ ኢቢን ማጃህ)

የአላህ መልካም ስሞች ትርጉም

ስም

ትርጉም

አላህ

የሁለንተናዊ አምላካዊ ባህሪያት ባለቤት የሆነን አካል የሚያመለክት ስም ነው።

አል-ረሕማን

ሙእሚንም ካሐዲም ለሆኑ ፍጡራን እዝነቱ ሰፊና ትልቅ

አር-ረሒም

ከስራ እጥፍ ድርብ የላቀ ምንዳ የሚሰጥ (ለሙእሚኖች በተለየ ሁኔታ በጎ ዋይ እና አዛኝ)

አል-መሊክ

በግዛቱ ያሻውን የሚፈጽም ንጉስ

አል-ቁዱስ

በስሜት ሕዋሳት ሊደረስበት ወይም በምናብ ሊታሰብ ከሚችል ባህሪ ሁሉ የጸዳ

አስ-ሰላም

ከነውር እና ከጉድለት የጸዳ፤ ሰላሙን በፍጡራኑ ላይ የሚያሰፍን

አል-ሙእሚን

ራሱ፣ መጽሐፍቱና መልእክተኞቹ ስለርሱ የተናገሩትን የሚያጸድቅ

አል-ሙሀይሚን

በምሉእ ችሎታው ሁሉንም ነገር የሚቆጣጠር

አል-ዓዚዝ

አቻ የለሽ ሐያልና አሸናፊ

አል-ጀባር

ፈቃዱን በሐይል የሚፈጽም፣ ጠጋኝ እና ፈዋሽ

አል-ሙተከቢር

የልዕልና ባህሪያቱ ብቸኛ ባለቤት፣ ከጉድለትና አንዳች ነገር ከመከጀል የጸዳ

አል-ኻሊቅ

ፍጡራንን በፈቃዱ ያስገኘ

አል-ባሪእ

ለፍጡሮቹ የተለያዩ ገጽታዎችን በማላበስ አንዱ ከሌላው እንዲለይ ያደረገ ጠቢብ

አል-ሙሶዊር

ለእያንዳንዱ ፍጡር የተለየ ቅርጽ የሰጠ

አል-ገፋር

መጥፎ ድረጊትን በዱንያ (በምድራዊ ሕይወት) የሚሸፍን፣ በመጭው ዓለም ደግሞ ይቅር የሚል

አል-ቀህሃር

አምባነገኖችን ሁሉ የሚያሸንፍ

አል-ወህሃብ

በችሮታው የሚያንበሸብሽ

አል-ረዛቅ

ሲሳዮችን የፈጠረና ወደ ፍጡራኑ የሚያደርስ

አል-ፈትታሕ

ለባሮቹ የችሮታውን ካዝናዎች የሚከፍት

አል-ዓሊም

በእውቀቱ ሁሉንም ነገር ያካበበ

አል-ቃቢድ

ከፍጡራኑ ለሚሻው፣ የፈለገውን ነገር የሚነሳ

አል-ባሲጥ

ምስጢራቱን ለሚሻው አካል የሚያካፍል

አል-ኻፊድ

ካሐድያንና ወንጀለኞችን ዝቅ የሚያደርግ

አር-ራፊዕ

ወዳጆቹን ከፍ የሚያደርግ

አል-ሙዒዝ

እርሱን ለሚታዘዙ አማኞች ክብር የሚለግስ

አል-ሙዚል

ከሀዲያንን የሚያዋርድ

አስ-ሰሚዕ

ድምጾች የማያመልጡት

አል-በሲር

ፍጡራንን ሁሉ የሚመለከት

አል-ሐኪም

የነገሮችና የፍርዶች ሁሉ መመለሻ

አል-ዓድል

በግዛቱ ውስጥ ነውር ወይም ጉድለት የሌለበት

አል-ለጢፍ

ለባሮቹ የሚያዝን

አል-ኸቢር

ግልጽም ስውርም የሆኑ ነገሮችን ሁሉ የሚያውቅ

አል-ሐሊም

ለቅጣት የማይቸኩል

አል-ዐዚም

ከአእምሮ ግንዛቤና ችሎታ በላይ የሆነ

አል-ገፉር

ጠላቱን የሚምርና ተውበትን የሚቀበል

አሽ-ሸኩር

ባሮቹን የሚመነዳ

አል-ዐሊይ

ከሁሉ በላይ የኾነው

አል-ከቢር

ከአልባሌ ነገሮች የጠራ

አል-ሐፊዝ

ፍጡራንን ከመናጋት የሚጠብቅ

አል-ሙቂት

ለፍጡራን ቀለባቸውን የሚፈጥር እና የሚያከፋፍል

አል-ሐሲብ

የፍጡራንን ጉዳይ ያለ ተጋሪ የሚያከናውን፣ ለጉዳያቸው በቂ

አል-ጀሊል

ልእልናውና ምሉእነቱ የላቀ

አል-ከሪም

ስጦታው የማይነጥፍ

አር-ረቂብ

ፍጡራንን የሚያውቅና የሚከተታተል

አል-ሙጂብ

ዱዓን ተቀባይ

አል-ዋሲዕ

ዙፋኑ ከሰማያትና ከምድር የሰፋ

አል-ሐኪም

ከምሉእነቱና ከልቅናው ጋር የሚቃረኑ ተግባራትን ከመፈጸም የጠራ

አል-ወዱድ

በፍጡራኑ ዘንድ የሚወደድ

አል-መጂድ

በማንነቱም ሆነ በስራው የላቀ፣ ችሮታውም ብዙ።

አል-ባኢሥ

ሙታንን ለምርመራ የሚቀሰቅስ

አሽ-ሸሂድ

ግልጽም ስውርም የሆኑ ጉዳዮችን ሁሉ የሚመለከት

አል-ሐቅ

ሁሉንም ነገር በጥበብ የፈጠረ

አል-ወኪል

የሁሉንም ጉዳዮች ሐላፊና ከዋኝ።

አል-ቀዊይ

ምንም ነገር የማይሳነው

አል-መቲን

ምንም ነገር የማያሸንፈው

አል-ወሊይ

በወዳጆቹ ተወዳጅ፣ የነርሱ ረዳትና አለኝታ

አል-ሐሚድ

ለምስጋናና ለውዳሴ ተገቢ

አል-ሙሕሲ

ጥቃቅን ጉዳዮች የማያመልጡትና ታላላቆች የማይሳኑት

አል-ሙብዲእ

ፍጡራንን መጀመሪያ ካልነበሩበት ያስገኘ ፈጣሪ

አል-ሙዒድ

ፍጡራንን ወደ ሞት የሚመልስ (መላሽ)

አል-ሙሕይ

የበሰበሱ አጥንቶችን ዳግመኛ ሕያው የሚያደርግ

አል-ሙሚት

ነፍስን ከአካል በመነጠል የሚገድል

አል-ሐይ

ዘልዓለማዊ ሕይወት ያለው (ሕያው)

አል-ቀዩም

ሁሉንም ነገር ያለ ረዳት የሚያከናውን (ራሱን ቻይ)

አል-ዋጅድ

የሚፈልገውንና ያሻውን ሁሉ ማግኘት የሚችል (አግኝ)

አል-ማጅድ

የተላቀ ችሮታና በጎ ምግባር ባለቤት

አል-ዋሒድ

በማንነቱም፣ በባህሪውም፣ በስራውም መሰል የለሽ (ብቸኛ)

አስ-ሰመድ

ጉዳዮች የሚከጀሉበት (መጠጊያ)

አል-ቃዲር

ፍጡራኑን በመፍጠር ብቸኛ የሆነ

አል- ሙቅተዲር

የሻውን ነገር የሚወስን

አል-ሙቀዲም

ነብያትን፣ ወዳጆቹንና ከፍጡራን የሚሻውን የሚያስቀድም

አል-ሙአኽኺር

ጠላቶቹን (ከእዝነቱ) በማራቅ የሚያዘገይ

አል-አወል

ሁሉንም ነገር የቀደመ

አል-አኺር

ፍጡራን ከጠፋ በኋላ ወደኋላ የሚቀር

አዝ-ዛሂር

በምልክቶቹ፣ በተአምራቱና በአድራጎቱ ሕልውናው ግልጽ የሆነ

አል-ባጢን

ከእይታ የተሰወረ፣ ሚስጥራትን ሁሉ አዋቂ

አል-ዋሊ

የነገሮች ባለቤት፣ በችሮታው ውለታ የሚውል፣ መከራን የሚከላከል።

አል-ሙተዓል

ደረጃው ከፍ ያለ፣ የዐርሽ ባለቤት፣ በክብሩና በሕልውናው የላቀ

አል-በር

ለለመኑት ቸር

አት-ተዋብ

ከባሮቹ ተውበትን ንስሃን የሚቀበልና ሐጢአትን ይቅር የሚል

አል-ሙንተቂም

ብቀላው የሚፈራ፣ እዝነቱ በፍርሃትና በተስፋ የሚከጀል

አል-ዓፍዉ

ወንጀልን የሚያብስ፣ ጥፋትንና ወንጀልን የሚያልፍ

አር-ረኡፉ

ለባሮቹ በጣም አዛኝ

ማሊከል ሙልክ

ፍላጎቱን ያለገደብ ፈጻሚ፣ በንግስናው የፈለገውን በፈለገው ቦታና በፈለገው ጊዜ የሚያደርግ፣ ውሳኔው የማይሻር በፈረደው የማይቀጣ

ዙልጀላሊ ወልኢክራም

የልእልናዎችና የልቅናዎች ሁሉ ባለቤት፣ ከፍጡራኑም የላቀ።

አል-ሙቅሲጥ

ፍትሕ አስፋኝ (ፍትሐዊ)

አል-ጃሚዕ

በማንነቱ፣ በባህሪውና በስራው ምሉእ ባህሪያትን ሁሉ የሰበሰበ (ሰብሳቢ)

አል-ገንይ

በማንነቱ፣ በሕልውናውም ሆነ በስራው አንዳች ነገር የማይከጅል (ሐብታም)

አል-ሙግኒ

ከባሮቹ ለሚሻው ሰው የሚሰጥ

አል-ማኒዕ

ባሮቹን ለመጠበቅ መከራን የሚያስቀርና ለፈተና ችሮታውን የሚያቅብ

አድ-ዷር

ከባሮቹ የሚሻውን የሚጎዳ፣ የጉዳት ባለቤት

አን-ናፊዕ

የመጥቀም ባለቤት፣ በሁሉም ነገር ላይ ቻይ

አን-ኑር

በተውሒዱ የእውነተኞችን ልቦናዎች የሚያበራ

አል-ሃዲ

ሁሉንም ነገር የፈጠረና የመራ

አል-በዲዕ

ጥበበ-ረቂቅ ፈጣሪ

አል-ባቂ

ዝንተ ዓለም የሚኖር

አል-ዋሪስ

በሰማያትና በምድር ያሉ ፍጡራን ሁሉ ባለቤት፣ የሁሉም ነገር ጌታ፣ ሲሳይ ለጋሽና አዛኝ

አር-ረሺድ

እርሱን ለሚታዘዙና ለሚገዙ ሰዎች ቅኑን ጎዳና አመላካች

አስ-ሰቡር

ጊዜ የሚሰጥ፣ የሚታገስ፣ የማይቸኩል።

                                                       *     *     *

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here