ተውሒድና ዓይነቶቹ (ክፍል 2)

0
3863

ሁለተኛ- ተውሒድ አል-ኡሉሂያ

የተውሒደል አል-ኡሉሂያህ ትርጉምና ይዘት፡- እውነተኛው አምላክ አላህ ብቻ መሆኑንና ከርሱ ሌላ አምላክ እንደሌለ በእርግጠኝነት ማመን፣ አምልኮዎችንም ለርሱ ብቻ ማዋል ነው።

የአምልኮን (ዒባዳን) ትርጉም ኢማም ኢብን ተይሚያህ ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል፡-

كمال الحب مع كمال الخضوع

“ዒባዳ ማለት ከፍጹማዊ ፍቅር የሚመነጭ ፍጹማዊ ታዛዥነት ነው።”

እንዲህ ሲሉም አክለዋል፡-

وهذا التوحيد هو الفارق بين الموحدين والمشركين ، وعليه يقع الجزاء والثواب في الأولى والآخرة ، فمن لم يأت به كان من المشركين

“ሙወሒዶችን ከጣኦታውያን የሚለየው የተውሒድ ዓይነት ይህ ሲሆን፣ በመጭው ዓለምም ለምንዳ ወይም ለቅጣት የሚያበቃው ይህ የተውሒድ ክፍል ነው። ይህን የተውሒድ ክፍል ያልፈጸሙ ከጣኦታውያን ይፈረጃሉ።” (ሪሳቱል ሐሰናህ ወሰይኢህ፣ ቢን ተይሚያህ።)

ይህ የተውሒድ ክፍል የአላህ መልእክተኞች ዳዕዋ መሠረት ነው። እርሱን ለማብራራት መጸሐፍት ወርደዋል። ይህን የተውሒድ ዘርፍ ለየወገኖቹ ያላስተማረ አንድም የአላህ መልእክተኛ የለም። አላህ እንዲህ ብሏል፡-

وَمَا أَرْسَلْنَا مِن قَبْلِكَ مِن رَّسُولٍ إِلَّا نُوحِي إِلَيْهِ أَنَّهُ لَا إِلَٰهَ إِلَّا أَنَا فَاعْبُدُونِ
 

“ከአንተ በፊትም እነሆ ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ በማለት ወደርሱ የምናወርድለት ቢኾን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም፡፡” (አል-አንቢያእ 21፤ 25)

ግድ የሚያደርጋቸው ሐላፊነቶች፡- ዒባዳን ሁሉ ለአላህ ብቻ ማዋል፣ ቀልቦቻችንን ከአላህ ውጭ ካለ አካልና አቅጣጫ ማጽዳት ሲሆን፣ ይህ ጽንሰ ሐሳብ በርካታ ቁም ነገሮችን ያካተተ ነው። ከብዙው በጥቂቱ፡-

1. ለአላህ ፍጹማዊ ፍቅርን መለገስ፣ ማለትም ሰውየው ልክ እንደ አላህ የሚወደው ወይም በፍቅር ከአላህ የሚያስቀድመውን ሌላ አካል መያዝ የለበትም። ይህን ያደረገ ከጣኦታውያን ይፈረጃል፡-

وَمِنَ النَّاسِ مَن يَتَّخِذُ مِن دُونِ اللَّهِ أَندَادًا يُحِبُّونَهُمْ كَحُبِّ اللَّهِ وَالَّذِينَ آمَنُوا أَشَدُّ حُبًّا لِّلَّهِ 

“ከሰዎችም ከአላህ ሌላ ባለንጣዎችን (ጣዖታትን) አላህን እንደሚወዱ የሚወዷቸው ኾነው የሚይዙ አልሉ። እነዚያ ያመኑትም አላህን በመውደድ (ከነርሱ) ይበልጥ የበረቱ ናቸው።” (አል-በቀራህ 2፤ 165)

በሙእሚን ዘንድ በዚህች ዓለም የየትኛውም ነገር ፍቅር ከአላህ ፍቅር ቀጥሎ የሚመጣ ነው። የአላህ ፍቅር ከሁሉም ፍቅሮች በላይ ነው። ይህም በመሆኑ የትኛውም ነገር ከአላህ ፍቅር ጋር ተቃርኖ ከተገኘ ሙእሚን ራሱን ከመሰዋት አያመነታም። ምድራዊ እሴቶችን ከአላህና ከመልእክተኛው ፍቅር የሚያስቀድሙ ወገኖችን አላህ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል፡-

قُلْ إِن كَانَ آبَاؤُكُمْ وَأَبْنَاؤُكُمْ وَإِخْوَانُكُمْ وَأَزْوَاجُكُمْ وَعَشِيرَتُكُمْ وَأَمْوَالٌ اقْتَرَفْتُمُوهَا وَتِجَارَةٌ تَخْشَوْنَ كَسَادَهَا وَمَسَاكِنُ تَرْضَوْنَهَا أَحَبَّ إِلَيْكُم مِّنَ اللَّهِ وَرَسُولِهِ وَجِهَادٍ فِي سَبِيلِهِ فَتَرَبَّصُوا حَتَّىٰ يَأْتِيَ اللَّهُ بِأَمْرِهِ وَاللَّهُ لَا يَهْدِي الْقَوْمَ الْفَاسِقِينَ
 

“አባቶቻችሁና ወንዶች ልጆቻችሁ፣ ወንድሞቻችሁም፣ ሚስቶቻችሁም፣ ዘመዶቻችሁም፣ የሰበሰባችኋቸው ሀብቶችም፣ መክሰሩዋን የምትፈሩዋት ንግድም፣ የምትወዷቸው መኖሪያዎችም እናንተ ዘንድ ከአላህና ከመልክተኛው በርሱ መንገድም ከመታገል ይበልጥ የተወደዱ እንደኾኑ አላህ ትእዛዙን እስከሚያመጣ ድረስ ተጠባበቁ በላቸው፡፡ አላህም አመጸኞች ሕዝቦችን አይመራም፡፡” (አል-ተውባህ 9፤ 24)

2. ከአላህ ውጭ ሌላ አካል ማድረግ በማይችላቸው ነገሮች አላህን ብቻ መማጸን፣ በርሱ ብቻ መመካትና እርሱን ብቻ ተስፋ ማድረግ ግዴታ ነው። አላህ እንዲህ ብሏል፡-

وَلَا تَدْعُ مِن دُونِ اللَّهِ مَا لَا يَنفَعُكَ وَلَا يَضُرُّكَ فَإِن فَعَلْتَ فَإِنَّكَ إِذًا مِّنَ الظَّالِمِينَ
 

“ከአላህም በቀር የማይጠቅምንና የማይጎዳን አትገዛ፡፡ ብትሠራም አንተ ያንጊዜ ከበደለኞቹ ትሆናለህ (ተብያለሁ በላቸው)፡፡” (ዩኑስ 10፤ 106)

وَعَلَى اللَّهِ فَتَوَكَّلُوا إِن كُنتُم مُّؤْمِنِينَ
 

“ምእመናንም እንደኾናችሁ በአላህ ላይ ተመኩ” (አል-ማኢዳህ 5፤ 23)

إِنَّ الَّذِينَ آمَنُوا وَالَّذِينَ هَاجَرُوا وَجَاهَدُوا فِي سَبِيلِ اللَّهِ أُولَٰئِكَ يَرْجُونَ رَحْمَتَ اللَّهِ وَاللَّهُ غَفُورٌ رَّحِيمٌ

“እነዚያ ያመኑትና እነዚያም (ከአገራቸው) የተሰደዱት በአላህም መንገድ ላይ የተጋደሉት እነዚያ የአላህን እዝነት ይከጅላሉ። አላህም እጅግ መሓሪ አዛኝ ነው።” (አል-በቀራህ 2፡ 218)

3. አላህን ብቻ መፍራት፡- ከፍጡራን አንዳቸውም በነጻ ፈቃዳቸው ሊጎዱኝ ይችላሉ ብሎ የፈራ ሰው በአላህ ላይ አጋርቷል። አላህ እንዲህ ብሏል፡-

فَإِيَّايَ فَارْهَبُونِ
 

“እኔንም ብቻ ፍሩ፡፡” (አል-ነህል 16፡ 51)

وَإِن يَمْسَسْكَ اللَّهُ بِضُرٍّ فَلَا كَاشِفَ لَهُ إِلَّا هُوَ وَإِن يُرِدْكَ بِخَيْرٍ فَلَا رَادَّ لِفَضْلِهِ يُصِيبُ بِهِ مَن يَشَاءُ مِنْ عِبَادِهِ وَهُوَ الْغَفُورُ الرَّحِيمُ 

“አላህም ጉዳትን ቢያደርስብህ ከእርሱ ሌላ ለእርሱ ገላጭ የለውም፡፡ በጎንም ነገር ቢሻልህ ለችሮታው መላሽ የለም፡፡ ከባሮቹ የሚሻውን በእርሱ ይለይበታል፡፡ እርሱም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡” (ዩኑስ 10፡ 107)

4. እንደ ሰላት፣ ሩኩዕ፣ ሱጁድ፣ ጾምና ጠዋፍ ያሉ አካላዊ የአምልኮ ተግባራት፣ እንዲሁም እንደ ኢሰቲግፋርና ስለት (ነዝር) ያሉ በአንደበት የሚፈጸሙ ዒባዳዎችን ለአላህ ብቻ ማድረግ ግዴታ ነው። ከነዚህ ወይም ከሌሎች አምልኮዎች መካከል አንዳቸውንም ከአላህ ውጭ ለሌላ አካል ያዋለ በአላህ ላይ አጋርቷል፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡-

إِنَّ اللَّهَ لَا يَغْفِرُ أَن يُشْرَكَ بِهِ وَيَغْفِرُ مَا دُونَ ذَٰلِكَ لِمَن يَشَاءُ وَمَن يُشْرِكْ بِاللَّهِ فَقَدِ افْتَرَىٰ إِثْمًا عَظِيمًا

“አላህ በእርሱ ማጋራትን በፍጹም አይምርም፡፡ ከዚህ ሌላ ያለውንም (ኀጢአት) ለሚሻው ሰው ይምራል፡፡ በአላህም የሚያጋራ ሰው ታላቅን ኀጢአት በእርግጥ ቀጠፈ፡፡” (አል-ኒሳእ 4፡ 48)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here