ተውሒድና ዓይነቶቹ (ክፍል 1)

0
5341

የኢማን መሠረቶች

በዑመር ኢቢን አል-ኸጧብ (ረ.ዐ) የተላለፈው እውቁ የጅብሪል (ዐ.ሰ) ሐዲስ ስድስቱን የኢማን መሠረቶች (አርካን አል-ኢማን) ዘርዝሯቸዋል። ጅብሪል “ስለ ኢማን ይንገሩን” በማለት

የአላህን መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በጠየቃቸው ጊዜ እንዲህ ሲሉ መመለሳቸው ይታወሳል፡-

أن تؤمن بالله وملائكته وكتبه ورسله واليوم الآخر وتؤمن بالقدر خيره وشره 

“ኢማን ማለት በአላህ፣ በመላእከት፣ በመጽሐፍቶች፣ በመልእክተኞች፣ በመጭው ዓለምና በቀዷ ቀደር -ደግም ሆነ ክፉ- ማመንህ ነው።” (ሙስሊም ዘግበውታል)

ቀጥሎ የመጀመሪያውን የኢማን መሠረት እንመለከታለን። ዓላማውንና በጎ ተጽእኖውንም እንቃኛለን።

የመጀመሪያው መሠረት- በአላህ ማመን

በአላህ ማመን ማለት አላህ የሁሉም ነገር ባለቤትና ፈጣሪ መሆኑን ማመን (ተውሒድ አር-ሩቡቢያህ)፣ ሶላት፣ ጾም፣ ዱዓእ፣ ተስፋ ማድረግ፣ መፍራት፣ መዋረድ፣ መተናነስና ሌሎችም ዒባዳዎች ለርሱ ብቻ እንደሚገቡ ማመን (ተውሒድ አል-ኡሉኒያህ)፣ እንዲሁም ከጎደሎ ባህሪያት የጸዳና በምሉእ ባህሪያት የሚገለጽ አምላክ መሆኑን ማመን (ተውሒድ አል-አስማኢ ወስ-ሲፋት) ናቸው።

በአላህ ማመን በሦስት መስክ ብቸኝነቱን መቀበልን ይጠይቃል። በመፍጠርና በመንከባከብ ስልጣኑ (ሩቡብያ)፣ አምልኮ ለርሱ ብቻ መሆኑ (ኡሉህያ) እና የምሉእና የላቁ ስያሜዎችና ባህሪያት ባለቤት መሆኑ (አስማእ ወሲፋት)።

የተውሒድ ዓይነቶች

አንደኛ፡- ተውሒድ አር-ሩቡቢያ

  • የተውሒዱ አር-ሩቡብያህ ጥቅል ትርጉም፡- አላህ የሁሉም ነገር ፈጣሪ፣ ተንከባካቢና አስተናባሪ መሆኑን እና ከርሱ ሌላ ይህን ማድረግ የሚችል አካል እንደሌለ በእርግጠኝነት ማመን።
  • የተውሒደ አር-ሩቡብያህ ይዘት፡- የፍጡራን ፈጣሪና ባለቤት፣ ሕይወት ለጋሽ፣ ገዳይ፣ ጠቃሚ፣ ጎጅ፣ የችሎታ ባለቤት፣ የሚሰጥም የሚነሳም አላህ ብቻ መሆኑን፣ መፍጠርም ማዘዝም የርሱ ብቻ ስልጣን መሆኑን ማመን።

ይህ የተውሒድ ክፍል ለሌሎች የተውሒድ ዓይነቶች ሁሉ መሠረት ነው፤ ይህ ተውሒድ ሲረጋገጥና ሲጸና አላህን በፍጹም መተናነስና ፍርሃት የማምለክ ሁኔታ ይከሰታል። ለምስጋና፣ ለመታወስ፣ ለመለመን፣ ተስፋ ለመደረግና ለመፈራት ተገቢው አላህ ብቻ ነው። አምልኮ የመፍጠርም ሆነ የማዘዝ ስልጣን ሁሉ ባለቤት ከሆነው አካል ውጭ ለሌላ ለማንም ተገቢ አይደለም። በሌላ በኩል ፈጣሪና ባለቤት የሆነው አካል የላቁና ምሉእ ባህሪያት ይገቡታል። እንዲህ ዓይነት ባህሪያት ለዓለማት ጌታ እንጅ ለሌላ ተገቢ አይደሉም። ምክንያቱም ሕያው፣ ሰሚ፣ ተመልካች፣ ቻይ፣ ተናጋሪ፣ የፈለገውን ሰሪ፣ በንግግሩም ሆነ በስራው ጥበበኛ ያልሆነ አካል የፍጡራን ፈጣሪ፣ ባለቤትና አስተናባሪ ሊሆን አይችልምና። ይህም በመሆኑ ቁርኣን ተውሒደ አር-ሩቡቢያህን በበርካታ ቦታዎች ላይ ሲያወሳ እናነባለን።

ከምስጋና ጋር አያይዞ እንዲህ ማለቱን ሙስሊም በእያንዳንዱ የሶላት ረከዓዎች ውስጥ ያነባል፡-

الْحَمْدُ لِلَّهِ رَبِّ الْعَالَمِينَ
 

“ምስጋና ለአላህ ይገባው የዓለማት ጌታ ለኾነው፤” (አል-ፋቲሐ 1፤2-5)

እንዲህም ይላል፡-

فَلِلَّهِ الْحَمْدُ رَبِّ السَّمَاوَاتِ وَرَبِّ الْأَرْضِ رَبِّ الْعَالَمِينَ 

“ምስጋናም ለአላህ ለሰማያት ጌታ ለምድርም ጌታ ለዓለማት ጌታ የተገባው ነው።” (አል-ጃሲያህ 45፤36)

እርሱን ብቻ የበጎ ምግባር ዓላማ ከማድረግ ጋር አያይዞም እንዲህ ብሏል፡-

قُلْ إِنَّ صَلَاتِي وَنُسُكِي وَمَحْيَايَ وَمَمَاتِي لِلَّهِ رَبِّ الْعَالَمِينَ 

“ስግደቴ፣ መገዛቴም፣ ሕይወቴም፣ ሞቴም ለዓለማት ጌታ ለአላህ ነው በል፡፡” (አል-አንዓም 6፤162)

ከላቁ ሰሞቹና ባህሪያቱ ጋር በተያያዘም የሰማያትና የምድር፣ እንዲሁም በመካከላቸው ያሉ ፍጡራን ጌታ፣ ባለቤትና አስተናባሪ በመሆኑ የሚገለጸውን የአላህ ፈጣሪነት (ሩቡቢያህ) ከላቁ ስሞቹና ባህሪያቱ ጋር አያይዞ ቁርአን ሲያቀርብ እናነባለን። ተከታዩን የአላህ ቃል አስተንትን፡-

اللَّهُ لَا إِلَٰهَ إِلَّا هُوَ الْحَيُّ الْقَيُّومُ لَا تَأْخُذُهُ سِنَةٌ وَلَا نَوْمٌ لَّهُ مَا فِي السَّمَاوَاتِ وَمَا فِي الْأَرْضِ مَن ذَا الَّذِي يَشْفَعُ عِندَهُ إِلَّا بِإِذْنِهِ يَعْلَمُ مَا بَيْنَ أَيْدِيهِمْ وَمَا خَلْفَهُمْ وَلَا يُحِيطُونَ بِشَيْءٍ مِّنْ عِلْمِهِ إِلَّا بِمَا شَاءَ وَسِعَ كُرْسِيُّهُ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ وَلَا يَئُودُهُ حِفْظُهُمَا وَهُوَ الْعَلِيُّ الْعَظِيمُ 

“አላህ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም። ሕያው ራሱን ቻይ ነው። ማንገላጀትም እንቅልፍም አትይዘውም። በሰማያት ውስጥና በምድር ውስጥ ያለው ሁሉ የርሱ ብቻ ነው። ያ እርሱ ዘንድ በፈቃዱ ቢኾን እንጅ የሚያማልድ ማነው? (ከፍጡሮች) በፊታቸው ያለውንና ከኋላቸው ያለውን ሁሉ ያውቃል። በሻውም ነገር እንጂ ከዕውቀቱ በምንም ነገር አያካብቡም (አያውቁም)። መንበሩ ሰማያትንና ምድርን ሰፋ። ጥበቃቸውም አያቅተውም። እርሱም የሁሉ በላይ ታላቅ ነው።” (አል-በቀራህ 2፤255)

ተውሒድ አር-ሩቡቢያህን ለሌሎች የተውሒድ ዘርፎች መሠረት ከመሆኑ ጋር በአላህ የማመንን ጽንሰ ሐሳብ በተሟላ መልኩ ለመገንዘብ ብቻውን በቂ አይደለም። አላህ የሁሉም ነገር ፈጣሪና አስተናባሪ መሆኑን አምነው እርሱን በብቸኝነት የማያመልኩና ከርሱ ጋር ሌላን አካል የሚያጋሩ፣ እንዲሁም ለላቁ ስሞቹና ባህሪያቱ ብቸኛው ተገቢ አካል መሆኑን የማይቀበሉ ወገኖች ተውሒድ አር-ሩቡቢያህን ማጽደቃቸው አይጠቅማቸውም። ከክህደት ክልል አውጥቶም ወደ እምነት ክልል አያስገባቸውም። ጣኦታውያን የአላህን የሁሉም ነገር ፈጣሪነት የሚያጸድቁ ቢሆንም እርሱን በብቸኝነት ማምለኩን ስላልወደዱና ምሉእና የተላቁ ስሞችና ባህሪያት ብቸኛ ሊያደርጉት ስላልፈቀዱ ጣኦታዊ ሆነው መቀጠላቸውን አላህ ይናገራል፡-

وَمَا يُؤْمِنُ أَكْثَرُهُم بِاللَّهِ إِلَّا وَهُم مُّشْرِكُونَ 

“አብዛኞቻቸውም፤ እነሱ አጋሪዎች ኾነው እንጂ በአላህ አያምኑም፡፡” (ዩሱፍ 12፤106)

ሙጃሂድ ይህችን አንቀጽ አስመልክተው ሲናገሩ፡-

قال مجاهد في هذه الآية : إيمانهم بالله قولهم أن الله خلقنا ويرزقنا ويميتنا فهذا إيمان مع شرك عبادتهم غيره

“በአላህ ማመናቸው፣ አላህ ፈጥሮናል፣ ሲሳይ ለግሶናል፣ ይገድለናል፣ ማለታቸው ሲሆን፣ ይህ እምነታቸው በርሱ ከማጋራታቸውና ሌላን አካል ከማምለካቸው ጋር የተቀላቀለ ነው።”

እናም አላህ የሁሉ ነገር ፈጣሪ መሆኑን ያጸደቁ ሁሉ በአምልኮ ወይም በስሞቹና በባህሪያቱ እርሱን ብቸኛ ያደርጋሉ ማለት አይደለም። አብዛኛዎቹ ሰዎች የፈጣሪን ሕልውናና ጌትነት፣ እንዲሁም በፍጡራን ላይ ያለውን የጌትነት ስልጣን አያስተባብሉም፤ የአብዛኛዎች ክህደት መሠረት ከርሱ ውጭ ሌላን አካል ማምለካቸው ነው።

ተውሒድ አር-ሩቡቢያን ለማጽናት የሚረዱ ስልቶች፡-

  • በተለየ መልኩ ማስተንተንን የሚጋብዙ የቁርአን አናቅጽን በማስተንተን ማንበብ፣
  • የአላህን ፍጥረታት ጥበብ ለመረዳት የሚያስችል ጉዞ፣
  • የአላህን ፍጥረታት ተአምራትና የቁርአንን ሳይንሳዊ ተአምራት የሚያብራሩ የሸይኽ ዘንዳኒን፣ የዶክተር ዘግሉል አን-ነጃርንና የሃሩን ያህያ የመሳሰሉ የቪዲዮ ካሴቶች መመልከት
  • የሰውን ልጅ ድንቅ የአፈጣጠር ጥበብ ማስተንተን፡-

وَفِي أَنفُسِكُمْ أَفَلَا تُبْصِرُونَ 

“በነፍሶቻችሁም ውስጥ (ምልክቶች አልሉ)፤ ታዲያ አትመለከቱምን?” (አል-ዛሪያት 51፤21)

  • ስለ ባህር፣ ስለ መሬት ነውጥ፣ ስለ እሳተ ጎመራ እና ስለ አስትሮኖሚ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ የቪዲዮ ካሴቶችን ማየት፣
  • ይህንን የእውቀት መስክ የሚያጎለብቱ መጽሐፍትን ማንበብ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here