የኢማን ትርጉምና አስፈላጊነት

0
5601

የኢማን ትርጉም

አላህ እንዲህ ብሏል፡-

آمَنَ الرَّسُولُ بِمَا أُنزِلَ إِلَيْهِ مِن رَّبِّهِ وَالْمُؤْمِنُونَ كُلٌّ آمَنَ بِاللَّهِ وَمَلَائِكَتِهِ وَكُتُبِهِ وَرُسُلِهِ لَا نُفَرِّقُ بَيْنَ أَحَدٍ مِّن رُّسُلِهِ وَقَالُوا سَمِعْنَا وَأَطَعْنَا غُفْرَانَكَ رَبَّنَا وَإِلَيْكَ الْمَصِيرُ
 

“መልክተኛው ከጌታው ወደ ርሱ በተወረደው አመነ። ምእምኖቹም (እንደዚሁ)። ሁሉም በአላህ፣ በመላዕክቱም፣ በመጻሕፍቱም፣ በመልክተኞቹም ከመልክተኞቹ ‘በአንድም መካከል አንለይም’ (የሚሉ ሲኾኑ) አመኑ። ‘ሰማን፤ ታዘዝንም። ጌታችን ሆይ! ምሕረትህን (እንሻለን)። መመለሻም ወዳንተ ብቻ ነው’ አሉም፡:” (አል-በቀራህ 2፤ 285)

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا آمِنُوا بِاللَّهِ وَرَسُولِهِ وَالْكِتَابِ الَّذِي نَزَّلَ عَلَىٰ رَسُولِهِ وَالْكِتَابِ الَّذِي أَنزَلَ مِن قَبْلُ وَمَن يَكْفُرْ بِاللَّهِ وَمَلَائِكَتِهِ وَكُتُبِهِ وَرُسُلِهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ فَقَدْ ضَلَّ ضَلَالًا بَعِيدًا 

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህና በመልክተኛው በዚያም በመልክተኛው ላይ ባወረደው መጽሐፍ በዚያም ከበፊቱ ባወረደው መጽሐፍ እመኑ። በአላህና በመላእክቱም፣ በመጽሐፎቹም፣ በመልክተኞቹም፣ በመጨረሻውም ቀን፣ የካደ ሰው (ከእውነት) የራቀን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ።” (አል-ኒሳእ 4፤ 136)

እውቅ በሆነው የጅብሪል (ዐ.ሰ) ሐዲስ ውስጥ ጅብሪል በደዊን ተመስሎ ወደነቢዩ በመምጣት ስለ ኢስላም፣ ኢማንና ኢሕሳን በጠየቃቸው ጊዜ ኢማንን እንዲህ አብራርተውለታል፡-

أن تؤمن بالله وملائكته وكتبه ورسله واليوم الآخر وتؤمن بالقدر خيره وشره 

“በአላህ፣ በመላኢኮች፣ በመጽሐፎች፣ በመልእክተኞች፣ በመጨረሻው ቀንና በቀዷ ቀደር- በጎም ሆነ ክፉ- ማመንህ ነው።” (ሙስሊም)

ከላይ ከተወሱት የቁርአን አናቅጽና የሐዲስ ዘገባ እንደምንረዳው ኢማን ስድስት ጽንሰ ሐሳቦችን አካትቷል። እነርሱም

 1. አንደኛ፡- አላህን፣ የላቁ ስሞቹንና ባህሪያቱን፣ የሕልውናውን መርሆዎች፣ የልዕልናውን መገለጫዎች ማወቅ፤
 2. ሁለተኛ፡- ከእይታ ባሻገር ያለውን ድብቅ ዓለም፣ በውስጡ ያዘላቸውን በመላኢኮች የሚወከል የበጎ ሐይል፣ በኢብሊስና በአጋሮቹ ሰይጣናት የሚወከል የክፉ ሐይል፣ እንዲሁም የዚሁ ድብቅ ዓለም አካል የሆኑትን አጋንንትና መናፍሳት ማወቅ፤
 3. ሦስተኛ፡- የእውነትንና የሐሰትን፣ የበጎና የክፋትን፣ የሐላልና የሐራምን፣ የጥሩና የመጥፎን ወሰኖች ለማበጀት አላህ ያወረዳቸውን መጽሐፍት ማወቅ፤
 4. አራተኛ፡- የመቀናት ተምሳሌት ይሆኑ ዘንድና የሰው ልጆችን ወደ ቅን ጎዳና እንዲመሩ አላህ የመረጣቸውን ነብያትና መልእክተኞች ማወቅ፤
 5. አምስተኛ፡- መጭው ዓለም፣ ከሞት መቀስቀስ፣ ምንዳ ወይም ቅጣት፣ ጀነት ወይም እሳት የመኖሩን እውነታ ማወቅ፤
 6. ስድስተኛ፡- ዩኒቨርሱ የሚመራበት የቀዷ ቀደር ስርዓት መኖሩን ማወቅ። (ሸይኽ ሰይድ ሳቢቅ፣ አልዓቃኢዱ-ል-ኢስላሚያህ)

ኢማን ማለት እውቀት ወይም የልቦና እምነት ብቻ ሳይሆን የአንደበት ምስክርነትንና ተግባርን ያካትታል። ይህን ሁለንተናዊ የኢማን ይዘት የሚያብራሩ የቁርአን አናቅጽና የሐዲስ ዘገባዎች በርካታ ናቸው። አላህ እንዲህ ብሏል፡-

إِنَّمَا الْمُؤْمِنُونَ الَّذِينَ آمَنُوا بِاللَّهِ وَرَسُولِهِ ثُمَّ لَمْ يَرْتَابُوا وَجَاهَدُوا بِأَمْوَالِهِمْ وَأَنفُسِهِمْ فِي سَبِيلِ اللَّهِ أُولَٰئِكَ هُمُ الصَّادِقُونَ 

“(እውነተኛዎቹ) ምእምናን እነዚያ በአላህና በመልእከተኛው ያመኑት ከዚያም ያልተጠራጠሩት በገንዘቦቻቸውና በነፍሶ ቻቸውም በአላህ መንገድ የታገሉት ብቻ ናቸው። እነዚያ እነሱ እውነተኞቹ ናቸው።” (አል-ሁጁራት 49፤ 15)

إِنَّمَا الْمُؤْمِنُونَ الَّذِينَ إِذَا ذُكِرَ اللَّهُ وَجِلَتْ قُلُوبُهُمْ وَإِذَا تُلِيَتْ عَلَيْهِمْ آيَاتُهُ زَادَتْهُمْ إِيمَانًا وَعَلَىٰ رَبِّهِمْ يَتَوَكَّلُونَ

“ፍጹም ምእምናን እነዚያ አላህ በተወሳ ጊዜ ልቦቻቸው የሚፈሩት፣ በነሱም ላይ አንቀጾቻችን በተነበቡ ጊዜ እምነትን የሚጨምሩላቸው፣ በጌታቸውም ላይ ብቻ የሚመኩት ናቸው።” (አል-አንፋል 8፤ 2)

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ!” ተብሎ ሙእሚን የተጠራባቸው እና “ሙእሚን ማለት” በሚል ቃል ተወጥነው የኢማንን መስፈርት የሚያብራሩ የቁርአን መልእክቶች ብዙዎች ሲሆኑ እነርሱን ማስተንተንና ማስተዋል ተገቢ ነው። ይህን የኢማን ይዘት ከሚያብራሩ ሐዲሶች መካከል ኢብን ዑመር (ረ.ዐ) ያስተላለፉት ይገኝበታል፣ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

من سرته حسناته وساءته سيئاته فهو مؤمن 

“ደግ ስራው ያስደሰተውና መጥፎ ስራው ያስከፋው ሰው ሙእሚን ነው።” (አህመድ ዘግበውታል)

ኡባደት ኢቢን ሷሚት (ረ.ዐ) እንዳስተላለፉት ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

إن أفضل الإيمان أن تعلم ان الله معك حيثما كنت

“በላጩ ኢማን የትም ቦታ ብትሆን አላህ ካንተ ጋር እንዳለ ማወቅህ ነው።” (ጦበራኒ ዘግበውታል)

ዐብደላህ ኢቢን ዑመር (ረ.ዐ) እንዳስተላለፉት ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

الحياء شعبة من الإيمان

“ሐያእ (ይሉኝታ) የኢማን ዘርፍ ነው።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

አነስ (ረ.ዐ) እንዳስተላለፉት ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

لا يؤمن أحدكم حتى يحب لأخيه ما يحب لنفسه

“ከናንተ አንዳችሁ ለራሱ የሚወደውን ለወንድሙ እስካልወደደ ድረስ አላመነም።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

አቡ ሹረይሕ አል ካዕቢ (ረ.ዐ) እንዳስተላለፉት ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡-

والله لا يؤمن والله لا يؤمن والله لا يؤمن . قالوا : من ذلك يا رسول الله صلى الله عليه وسلم؟ قال : من لا يأمن جاره بوائقـه 

“በአላህ እምላለሁ አለመነም።” በማለት ሦስት ጊዜ ተናገሩ። “ይህ ሰው ማን ነው?” ተብለው ሲጠየቁ፡- “ጎረቤቱ ተንኮሉን የማያምነው ሰው” በማለት መለሱ። (ቡኻሪ ዘግበውታል)

ቁርኣንና ሐዲስ ያስተማሩት ኢማን፣ መንገድ የሳቱ ሐይማኖቶች፤ “እውር ሆነህ እመን”፣ “አእምሮህን ዝጋና ተከተለኝ” እንደሚሉት ዓይነት አእምሯችንን ቆልፈን የምንቀበለው እውር እምነት አይደለም። ይልቁንም ግዙፉን ዩኒቨርስ እና በውስጡ ያካተታቸውን ወደ እምነት የሚጠሩ ጥበቦች በጥልቀት ከማጤንና ከማስተንተን የሚመነጭ ነው።

የኢማን አስፈላጊነት

 • አላህን ማወቅ፡- በርካታ በጎ ስሜቶችን ያሰርጻል። ሕሊናን ለደግ ስራ ያነቃቃል። ራስን የመቆጣጠርን ክህሎት ያጎናጽፋል። ለላቁ ዓላማዎች ያነሳሳል። ከአጓጉል ድርጊቶችም ያርቃል።
 • መላኢኮችን ማወቅ፡- ከነርሱ ጋር ለመመሳሰል መጣርን፣ ለሐቅና ለሰናይ መተባበርን ይጋብዛል። ጥንቁቅና ንቁም ያደርጋል። መላኢኮች ካጠገቡ እንዳሉ የታሰበው ሰው መልካም ነገር እንጅ ከርሱ አይመነጭም። ለላቀ ዓላማ እንጅ አይንቀሳቀስም።
 • መለኮታዊ መጽሐፍትን ማወቅ፡- የሰው ልጅ ውጫዊና ውስጣዊ ምሉእነትን ይጎናጽፍ ዘንድ እንዲጓዝበት አላህ ያሰመረለትን ቅን ጎዳና ማወቅ ነው።
 • መልእክተኞችን ማወቅ፡- ፈለጋቸውን መከተል፣ ባህሪያቸውን መውረስ፣ እነርሱን አርአያ (Role Model/ ቁድዋ) ማድረግ ማለት ነው። ምክንያቱም እነርሱ የመልካም እሴትና አላህ ለሰው ልጅ ያለመለት ጻእድ ሕይወት ተምሳሌቶች ናቸውና።
 • የመጭውን ዓለም ሕልውና ማወቅ፡- በጎ ነገር ለመስራት እና ከክፋት ለመታቀብ ግፊት በማሳደር ወደር አይገኘለትም።
 • በቀዷ ቀደር ማመን፡- ችግሮችንና እንቅፋቶችን ለማለፍ የሚያስችል ወሰን አልባ ጉልበት ይለግሳል። ይህ እምነት በልቦና ውስጥ ካለና ከሰረጸ ግዙፍ ክስተቶች ሁሉ ኢምንት ሆነው ይታያሉ።

ከላይ የሰፈረው ገለጻ በጉልህ እንደሚያመለክተው ኢማን ዓላማው ስብእናን ማስተካከል፣ ነፍስን ማጽዳትና ፊትን ወደ ላቀ አርአያ ማዞር ነው። ይህ ዓይነቱ ኢማን ለግለሰቦች ሕይወት ነው። እርሱ ካለ መልካም ሕይወት ይኖራሉ። እርሱ ከሌለ ደግሞ መንፈሳቸው ይሞታል። ኢማን መንገድ አመላካች ብርሃን ሲሆን፣ ያለርሱ የሰው ልጅ እውር ነው። መንገድ ስቶ በሕይወት ጥሻዎች ውስጥ ይወሸቃል፣ በጥመት ሸለቆዋች ውስጥ ይጠፋል፣

أَوَمَن كَانَ مَيْتًا فَأَحْيَيْنَاهُ وَجَعَلْنَا لَهُ نُورًا يَمْشِي بِهِ فِي النَّاسِ كَمَن مَّثَلُهُ فِي الظُّلُمَاتِ لَيْسَ بِخَارِجٍ مِّنْهَا كَذَٰلِكَ زُيِّنَ لِلْكَافِرِينَ مَا كَانُوا يَعْمَلُونَ 

“ሙት የነበረና ሕያው ያደረግነው ለእርሱም በሰዎች መካከል በእርሱ የሚኼድበትን ብርሃን ያደረግንለት ሰው በጨለማዎች ውስጥ ከርሷ የማይወጣ ኾኖ እንዳልለ ሰው ብጤ ነውን? እንደዚሁ ለከሓዲዎች ይሠሩት የነበሩት ነገር ተጌጠላቸው።” (አል-አንዓም 6፤ 122)

ይህም ብቻ አይደለም። ኢማን ማለት ከመላ የዩኒቨርሱ አካላት፣ ከአላህና እንዲሁም ዩኒቨርሱን ከሚገዛው ሕግና ስርዓት ጋር መገናኘት ማለት ነው። ከአላህ ጋር የተሳሰረ፣ በርሱ ያመነ፣ ትእዛዙን የተከተለ፣ ከዩኒቨርሱ ጋር በመገናኛ፣ በጎ ተጽእኖውን በማስተናገድና ተጽእኖ በማሳደር በዚህችም በቀጣዩም ዓለማት በደስታ ይኖራል።

فَمَنِ اتَّبَعَ هُدَايَ فَلَا يَضِلُّ وَلَا يَشْقَىٰ 

“መሪየን የተከተለ አይሳሳትም አይቸገርምም።” (ጧሃ 20፤ 123)

ሰውየው ከአላህ ጋር ካልተሳሰረ ከዩኒቨርሱ ጋር ያለው ግንኙነትም ይቋረጣል። ነፍሱም ለርሱ እና ከርሱ ለሚመነጩት ነሮች ሁሉ ባይተዋር ትሆናለች። ይህም ሲሆን በዚህችም በመጭውም ዓለም ደስታ ቢስ ይሆናል።

وَمَنْ أَعْرَضَ عَن ذِكْرِي فَإِنَّ لَهُ مَعِيشَةً ضَنكًا وَنَحْشُرُهُ يَوْمَ الْقِيَامَةِ أَعْمَىٰ 

“ከግሣጼዬም የዞረ ሰው ለእርሱ ጠባብ ኑሮ አለው። በትንሣኤም ቀን ዕውር ኾኖ እንቀሰቅሰዋለን።” (ጧሃ 20፤ 124)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here