ኡማ /ኢስላማዊ ማህበረሰብ/

0
3622

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

إِنَّ هَٰذِهِ أُمَّتُكُمْ أُمَّةً وَاحِدَةً وَأَنَا رَبُّكُمْ فَاعْبُدُونِ

“ይህች (ሕግጋት) አንዲት መንገድ ስትሆን በእርግጥ ሃይማኖታችሁ ናት። እኔም ጌታችሁ ነኝና ተገዙኝ።” (አል-አንቢያእ 21፤92)

وَإِنَّ هَٰذِهِ أُمَّتُكُمْ أُمَّةً وَاحِدَةً وَأَنَا رَبُّكُمْ فَاتَّقُونِ 

“ይህችም (በአንድ አምላክ የማመን ሕግጋት) አንድ መንገድ ስትኾን ሃይማኖታችሁ ናት። እኔም ጌታችሁ ነኝና ፍሩኝ።” (አል-ሙእሚኑን 23፤52)

ይህች እኛ የምንጠራባት ሙስሊም ኡማ (ህዝብ/ማህበረሰብ) ከአደም (ዐ.ሰ.) ጀምሮ እስከ ነቢያችን ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ.) የሚገኙ የአላህ መልእክተኞች ሁሉ ማህበረሰብ ናት። መልእክተኞችና ተከታዮቻቸው በሰው ልጅ የታሪክ ሂደት ውስጥ አንድ ኡማ/ህዝብ በመባል የሚታወቁ ሲሆን ይሀውም የእስልምና ህዝብ ነው። ማንኛውም ሙስሊም የሆነ ሰው ሁሉ ተጠሪነቱ ለዚህች ኡማ ነው። በመሆኑም አንድ ሙስሊም በወንድማማችነትም ሆነ በወዳጅነት መልኩ ከዚህች ህዝብ ውጭ በሌላ መጠራቱ አይበቃለትም።

ይህች በእስልምና ሃይማኖት ሥር እምነቷን በአላህ ላይ ያደረገችው ህዝብ በታሪክ በሁለት ደረጃዎች ውስጥ አልፋለች፡-

  • የመጀመሪያው ደረጃ – ከሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) መላክ በፊት የነበረው ሲሆን
  • ሁለተኛው ደረጃ ደግሞ – በሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) መላክ ይጀምራለ።

ከሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) በፊት የእስልምና መልእክት ይገለፅ የነበረው ለአንድ ለተወሰነ የህዝብ ክፍል አሊያም አካበቢ ነበር። ይህም ማለት የአላህ መልእክተኞች ይላኩ የነበረው ወደተወሰኑ ህዝቦች አሊያም ክፍሎች ነው። መልእክተኛው መልእክቱን የሚያደርሰውና ወደ አላህ የሚጣራው ህዝቦቹ በሚኖሩበት አካባቢ ለሚገኙ ወገኖቹ ብቻ ነበር። ከኑህ እስከ ሁድ ከሹዐይብ እስከ ሷሊህ (በሁሉም ላይ የአላህ እዝነትና ሰላም ይውረድ) ያሉ ሁሉም ነቢያት በዚሁ ሁኔታ ውስጥ ማለፋቸውን አላህ (ሱ.ወ.) በቁርኣኑ ውስጥ ተርኮልናል። ያኔም የሁሉም የጥሪ መልእክት “ህዝቦቼ ሆይ! ህዝቦቼ!” የሚል ነበር። ነቢዩ ዒሣም ዐለይህ ሠላም “እኔ የተላክሁት ከእስራኤል ቤት ለጠፉ ህዝቦች በጎች ነው” ማለታቸው በወንጌል ውስጥ ተጠቅሷል። የአላህ መልእክተኛም ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ)

وكان النبي يبعث إلى قومه خاصة

“ነቢይ ይላክ የነበረው ወደህዝቦቹ ብቻ ነበር” ብለዋል (ቡኻሪና ሙስሊም)።

በነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ) መላክ ግን ማእከሉን የተወሠነ ህዝብ፣ ጎሣ አሊያም ውስን የሆነ ክፍልና አካባቢ ብቻ አድርጎ የነበረው የእስልምና ጥሪ የሰውን ልጅ ሁሉ በሚያካትት መልኩ እንዲሆን ተደረገ። “ህዝቦቼ ሆይ!” የሚለውም ጥሪም “ሰዎች ሆይ!” “ሰው ሆይ!” በሚል ተተካ።የሰው ልጅ በሙሉ አንድ የአላህ መልእክተኛ ይከተል ዘንድ ግዴታ ተጣለበት። ይህም መልእክተኛ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ናቸው። ከርሣቸው በኋላም ሌላ መልእክተኛ አይኖርም። ከሱ በፊት የነበረን መልእክተኛ መከተልም ተቀባይነት የለውም። አላህ (ሱ.ወ) ስለ ነቢዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሲናገር እንዲህ አለ

وَلَٰكِن رَّسُولَ اللَّهِ وَخَاتَمَ النَّبِيِّينَ

“ነገር ግን የአላህ መልእክተኛና የነቢያትም መደምደሚያ ነው።” (አል-አንቢእ 33፤40)

እርሣቸውም ቢሆኑ

لا نبي بعدي

“ከኔ በኋላ ነቢይ የለም።” በማለት ተናግረዋል (ቡኻሪና ሙስሊም)።

እንዲያውም

لو كان مسى حيا ما وسعه إلا أن يتبعني

“(ነቢዩ) ሙሳ በህይወት ቢኖር ኖሮ እኔን ከመከተል ውጭ አማራጭ የለውም” ብለዋል (አቡ ዳዉድ)።

አላህ እንዲህ አለ

وَإِذْ أَخَذَ اللَّهُ مِيثَاقَ النَّبِيِّينَ لَمَا آتَيْتُكُم مِّن كِتَابٍ وَحِكْمَةٍ ثُمَّ جَاءَكُمْ رَسُولٌ مُّصَدِّقٌ لِّمَا مَعَكُمْ لَتُؤْمِنُنَّ بِهِ وَلَتَنصُرُنَّهُ قَالَ أَأَقْرَرْتُمْ وَأَخَذْتُمْ عَلَىٰ ذَٰلِكُمْ إِصْرِي قَالُوا أَقْرَرْنَا قَالَ فَاشْهَدُوا وَأَنَا مَعَكُم مِّنَ الشَّاهِدِينَ
 

“አላህ የነቢያትን ቃል ኪዳን ከመጽሐፍና ከጥበብ ሰጥቻችሁ ከዚያም ‘ከእናንተ ጋር ላለው (መጽሐፍ) የሚያረጋግጥ መልክተኛ ቢመጣላችሁ በርሱ በእርግጥ እንደምታምኑበት በእርግጥም እንድትረዱት ሲል በያዘ ጊዜ (አስታውስ)። አረጋገጣችሁን? በዚህም ላይ ኪዳኔን ያዛችሁምን?’ አላቸው። ‘አረጋገጥን’ አሉ። ‘እንግዲያስ መስክሩ፤ እኔም ከእናንተ ጋር ከመስካሪዎቹ ነኝ’ አላቸው።” (ኣሊ ዒምራን 3፤81)

በዚህ መልኩ የተለያየ ማህበረሰብ ስብጥር የሆኑት የሰው ልጆች ሁሉ ነጭና ጥቁሩ፣ ቢጫና ቀዩ፣ በኢሲያ የሚኖረውም ሆነ በአውሮፓ፣ በአሜሪካም ሆነ በአፍሪካ የሚገኙት ሁሉ፤ መልካቸው፣ ዘራቸውና ቋንቋቸው ከመለያየቱ ጋር የአንድ መልእክተኛ ህዝብ ሊሆኑ ቻሉ። እርሣቸውን መከተልና በሣቸው መመራትም ግድ ይላቸዋል። በህግጋቱና በሃይማኖቱም በመኖር ለአላህ እጅ መስጠት ይኖርባቸዋል። እነኚህ ህዝቦች ሁሉ ለእስልምና ጥሪ ምላሽ የሠጡ እንደሆነ አንድ ህዝብ ሆነዋል ማለት ነው። ሁሉም ለጥሪው ምላሽ የማይሠጡ ከሆነ ግን ከነሱ ውስጥ ለጥሪው ምላሽ የሠጡት ብቻ ናቸው የእስልምናን ህዝብ (ኡማ) ሊፈጥሩ የሚችሉትና የሙስሊሙ ማህበረሰብ አባልም የሚሆኑት። ሙስሊሙ ኡማ አንድ ህዝብ ሲሆን እያንዳንዱ ሙስሊምም የዚህ ህዝብ አባል ነው።

የሙስሊሙ ማህበረሰብ የአንድነት መገለጫዎች ብዙ የተያያዙና አምሣያም የማይገኝላቸው ሲሆኑ ሙስሊሞችም በነኚህ ነገሮች ጥልቀት ባለው ሁኔታ ይያያዛሉ። የዚህ አንድነት መገለጫ ከሆኑ ነገሮች መካከል፡-

1. የዐቂዳ /የእምነት/ አንድነት

“ላ ኢላሀ ኢለሏህ ሙሀመዱ ረሱሉሏህ” (ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም ሙሀመድ የአላህ መልእክተኛ ናቸው) የምትለው ቃል ለሙስሊሞች አንድነት መስረታዊ የሆነች ቃል ናት። አንድ ሰው በዚህች ቃል ከመሠከረ እሷን ሊያፈርሱ የሚችሉ ነገሮች እስካልፈፀመ ድረስ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ኡማ አካል ነው። ከዚህች ቃል ክልል ውጭ የወጣ እንደሆነ ግን የሙስሊሙ ኡማ አካል አይደለም። አንድ ሰው በአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) መንገድ መሰረት ፊቱን ወደ አላህ (ሱ.ወ) ያዞረ እንደሆነ ለአላህ እራሱን አስገዛ፤ ከሱ ውጭ ለሆነ ለሌላ አካል ባሪያ ከመሆን ነጻ ወጣ ማለት ነው። አላህን ብቻ አምላካቸው አድርጎ ያያዙ እንደሆነ ደግሞ እምነታቸውን የሚጋሩ ሙስሊሞች ከየትኛውም ዘር ይሁኑ ሀገር አንድነታቸው ይረጋገጣል።

2. የዒባዳ /አምልኮ/ አንድነት

እኛ ሙስሊሞች የምናምንበት አላህ እርሱን እንድናመልከው ዘንድ የፈጠረን መሆኑን እናውቃለን። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ:-

وَمَا خَلَقْتُ الْجِنَّ وَالْإِنسَ إِلَّا لِيَعْبُدُونِ
 

“አጋንንትንም ሆነ የሰውን ልጅ እንዲገዙኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም” (አዝ-ዛሪያት 51፤56)

በውስጣዊ ዝንባሌም ሆነ በተግባር በአላህ ማመን በዒባዳ /የአምልኮ ተግባራት/ እንጂ ሊረጋገጥ አይችልም። ሰውም ሰው የሚሆነው የአምልኮ ተግባራትን በትክክል የፈፀመ እንደሆነ ነው።

በሁሉም ሙስሊሞች ላይ ግዴታ የተደረጉ የአምልኮ ሥራዎች በሙሉ ተመሣሣይ ናቸው። እያንዳንዱ ሰው ወንድም ይሁን ሴት ይህንን ግዴታ መወጣት ይኖርበታል። ይህም መመሣሠል የሙስሊሙን አንድነት ለማጉላት ከፍተኛ ትርጉም አለው። ከዚህም በላይ ኢስላማዊ የአምልኮ ተግባራት የሙስሊሙን ማህበረሰብ አንድነትና ጥንካሬ ከመጨመር አንፃር በርካታ ትርጉሞች አሏቸው።

ሙስሊሞች ሁሉ ወደ አንድ የሰላት ማእከል (ቂብላ) ተቀጣጭተው መስገዳቸውና በቀን አምስቴ በቀልባቸው የሚገናኙበት ሁኔታ ሲታይ ትልቅ ትርጉም ያዘለ ነው። ይህም አንድ ሙስሊም ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ በውስጡ የሚፈጥረው ስሜት ቀላል አይደለም።

በተለያየ የህይወት ክፍል ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ሙስሊም የሚሣተፍበትና ከዓለም ላይ በተመሣሣይ ጊዜ በአመት ለአንድ ወር ያህል የሚፆመው የረመዷን ወር ፆምም ተመሣሣይ መንፈሣዊ ባህሪ ከመፍጠርና ኢስላማዊ ወንድማማችነትን ከማጠናከር አንፃር ጉልህ አስተዋፅኦ አለው።

በሀጅ ደግሞ በየአመቱ በዓለም ላይ የሚገኙ ሙስሊሞች ይገናኛሉ። ሀጅ በያንዳንዱ ቻይ በሆነ ሙስሊም ላይ ግዴታ ከመሆኑ አንፃር ከዓለም ሀገራት ቢያንስ አንድ ሰው በዚያ ታላቅ ጉባኤ ይገኛል ማለት ይቻላል። በዚህም ሙስሊሞች ቋንቋቸው፣ ልብሣቸው፣ ሥራቸውና ንግግራቸው አንድ ሆኖ በአካል ይገናኛሉ። በሀጅ ሙስሊሞች ለአላህ እንጅ ለአንድም አካል የበላይነት በሌለበት ሁኔታ ይሠባሰባሉ።የአምልኮ ተግባራቱ መመሣሠል የሙስሊሙን ኡማ አንድነት ለማጠናከር ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ በሙስሊሙ ኡማ ጥላ ሥር ሆኖ አንዱ ሙስሊም ለሌላኛው አጋዠ ሊሆን በሚያስችል መልኩ ነው የተደነገጉት።

3. የባህሪ የባህልና የስነምግባር አንድነት

ለያንዳንዱ ሙስሊም መልካም አርዓያ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ናቸው። በሁሉም ሥነሥርኣቶች ውስጥ በባህሪ አንድ መሆን የዚህ አባባላችን አንደኛው ትርጉሙ ነው። ሙስሊሞች በአጠቃላይ በተመሣሣይ ሁኔታ ይበላሉ፣ በተመሣሣይ መልኩም ይተኛሉ፣ ከእንቅልፋቸው ሲነሱም በተመሣሣይ አኳሃን ይነሣሉ፣ ሌላው ቀርቶ በሚፀዳዱበት ወቅት እንኳ ተመሣሣይ የሆነ ሥርኣት አላቸው።የሠላምታ ሥርኣታቸው ተመሣሣይ ነው። በጤና ጊዜም ሆነ በህመም ወቅት ተመሣሣይ የሆነ ባህሪ ያንፀባርቃሉ። አንድ የህንድ ሙስሊም ቢያስነጥሠው ከአረብ ሙስሊም ጋር በሚያደርገው መልኩ ያደርጋል። ሁሉንም ተመሣሣይና አንድ አይነት በሆነ ሥርኣት ያስተናግዳል።ሙስሊሞች ቢሄዱ ተመሣሣይ የአካሄድ ሥርኣታቸው አንድ ሆኖ እናገኛለን። ከትእግስት፣ ከእውነት፣ ከልግስና፣ ቃልን ከመጠበቅ፣ በእምነት ላይ ከመፅናትና ከሌሎች ባህሪዎች አንፃርም ተመሣሣይ የሆነ አቋምና እይታ አላቸው። አላህ የሰው ልጆችን በአፈጣጠርና በብልህነት ደረጃ እንዲበላለጥ አድርጎ ባይፈጥር ኖሮ ሙስሊሞች ሁሉ ተመሣሣይ ቅጂ በሆኑ ነበር። ከሙስሊም ማህበረሰብ በቀር በባህሪ፣ በባህልም ይሁን በሥነምግባር አንድ እና ተመሣሣይ የሆነ ህዝብ በየትኛውም የዓለም ሀገራት ላይ አይገኝም።

4. የታሪክ አንድነት

የአንድ ሙስሊም ታሪክ በሀገር አፈር አሊያም በመልክና በቋንቋ አይነት የሚያያዝ አይደለም። ሙስሊሙ ታሪኬ ነው ብሎ የሚኮራበትና የታሪኩም አካል ነኝ ብሎ የሚያስበው ታሪክ የኢስላም ታሪክ ነው። ወደዚህ ታሪክ የጠሩትም የአላህ መልእክተኞች ናቸው (በሁሉም ላይ የአላህ እዝነትን ሠላም ይውረድ)።

እኔ ሙስሊም ነኝ። ታሪኬም ከአደም፣ ከኑህ፣ ከኢሣ፣ ከሙሣ ከሙሀመድና በነሱ ካመኑት፣ ከነሱ ጋር ካመኑትና እነሱንም ከተከተሉት ሁሉ ጋር ይያያዛል። ከነዚህ ጋር ብቻ ነው ታሪኬን የማያይዘውና ከነሱም በመሆኔ የምኮራው። ከሌላ ታሪክ ጋር ምንም የሚያገናኘኝ ነገር የለም።አንድን ዐረብ ከቀደምት መሃይማን (ጃሂሊያ) ዐረቦች ጋር የሚያያይዘው የመወዳጀትና በነሱ የመኩራራት ታሪክ የለም። ባይሆን ኩራቱ በእስልምና ነው ከሱ ውጭ ያለ ሁሉ ኩራቱ አይደለም። ይህ የያንዳንዱ ሙስሊም አቋም ነው። ከጃሂሊያም ሆነ ሙስሊም ካልሆኑት ጋር የሚያያዘው ሃይማኖታዊም ሆነ የወንድማማችነት ታሪክ የለም።

የኢስላም ታሪክ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ታሪክ ነው። እሱም የአላህ መልእክተኞች ታሪክ ነው። ይህም ታሪክ ከመጥፎ ተግባር ጋር ባለመተሣሣሩና ባለመገናኘቱ የሙስሊሙን ልቦና በኩራትና በክብር ይሞላዋል።

አንድ ሙስሊም አላህን የሚገናኝበት አመለካከቱ ይህ ነው። አላህ አንዲህ አለ

قُولُوا آمَنَّا بِاللَّهِ وَمَا أُنزِلَ إِلَيْنَا وَمَا أُنزِلَ إِلَىٰ إِبْرَاهِيمَ وَإِسْمَاعِيلَ وَإِسْحَاقَ وَيَعْقُوبَ وَالْأَسْبَاطِ وَمَا أُوتِيَ مُوسَىٰ وَعِيسَىٰ وَمَا أُوتِيَ النَّبِيُّونَ مِن رَّبِّهِمْ لَا نُفَرِّقُ بَيْنَ أَحَدٍ مِّنْهُمْ وَنَحْنُ لَهُ مُسْلِمُونَ

“በአላህና ወደኛ በተወረደው (ቁርኣን) ወደ ኢብራሂምም ወደ ኢስማዒልና ወደ ኢስሐቅም ወደ ያዕቁብና ወደ ነገዶቹም በተወረደው በዚያም ሙሳና ዒሳ በተሰጡት በዚያም ነቢያት ሁሉ ከጌታቸው በተሰጡት ከነርሱ በአንድም መካከል የማንለይ ስንኾን አመንን፤ እኛም ለርሱ (ለአላህ) ታዛዦች ነን በሉ።” (አል-በቀራህ 2፤136)

የአላህ መልእክተኛም ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም እንዲህ ብለዋል

إن الله قد أذهب عنكم عبية الجاهلية وتعاظمها بآبائها

“አላህ የጃሂሊያን ሸክምና በአባቶች መመፃደቅን አስወግዶላችኋል።” (ቲርሚዚ)

በሌላም ሀዲሣቸው

لينتهين قوم يفتخرون بآبائهم أو ليكونن أهون على الله من الجعلان

“ሰዎች በአባቶቻቸው መኩራራትን ያቆማሉ ያለበለዚያ በአላህ ዘንድ ከአርን ክብል የበለጠ የተዋረዱ ያደርጋቸዋል።” (አቡ ዳዉድና ቲርሚዚ)

አንድ ሙስሊም የእስልምና ባልሆኑ እሴቶች ቢኩራራ ይህ ድርጊቱ ከኢስላማዊ መንፈስ ያስወጣዋል። እራሱንም በተዘበራረቀና በወዳደቀ ሁኔታ ውስጥ ያገኛል። ከሰላማዊና ትክክለኛ ሁኔታም ወደ አስቀያሚና ዝቃጭ ሁኔታ ይሸጋገራል።

5. የቋንቋ አንድነት

እስልምና ማለት አመለካከት፣ አምልኮና ስነምግባር ነው። ቋንቋም የነዚህ ነገሮች ገላጭ ነው። እሱም ማድረሻ እንጅ ግብ አይደለም። ለዚም ነው እያንዳንዱ ነቢይ በህዝቦቹ ቋንቋ ሊላክ የቻለው። አላህ እንዲህ አለ

وَمَا أَرْسَلْنَا مِن رَّسُولٍ إِلَّا بِلِسَانِ قَوْمِهِ لِيُبَيِّنَ لَهُمْ
 

“ከመልክተኛ ማንኛውንም ለእነርሱ ያብራራላቸው ዘንድ በወገኖቹ ቋንቋ እንጂ በሌላ አልላክንም።” (ኢብራሂም 14፤4)

አላህ (ሱ.ወ) በቁርኣኑ ውስጥ የቋንቋንና መልክ መለያያት ከተዓምራቶቹ እንደሆኑ ተናግሯል፡-

وَمِنْ آيَاتِهِ خَلْقُ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَاخْتِلَافُ أَلْسِنَتِكُمْ وَأَلْوَانِكُمْ إِنَّ فِي ذَٰلِكَ لَآيَاتٍ لِّلْعَالِمِينَ

“ሰማያትንና ምድርንም መፍጠሩ፣ የቋንቋዎቻችሁና የመልኮቻችሁም መለያየት፣ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው። በዚህ ውስጥ ለዐዋቂዎች ተዓምራቶች አልሉበት።” (አር-ሩም 30፤22)

ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) የተላኩበት የእስልምና ምንጭ የሆኑት ቁርኣንና ሀዲስ መልእክቶች የወረዱት በዐረቦች ቋንቋ ነው። ሁሉም ዓለም ደግሞ ይህንን መልእክት መከተል ግዴታው ሲሆን ይህንንም መልእክት መረዳት የሚቻለው የዐረብኛ ቋንቋን በመማር ነው። በዚህም የተነሣ ዐረብኛ የሰው ልጅ ሁሉ ኦፊሴላዊ ቋንቋ ነው ማለት ይቻላል። በዋናነት ደግሞ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ። ለምን ቢባል ለኢስላም ጥሪ ምላሽ የሠጠው ብቸኛው ማህበረሰብ ሙስሊሙ ነውና። ኢማሙ ሻፊዒይ እንዲህ ይላሉ “የተከበረው አላህ በሁሉም ሀዝቦች ላይ ዐረብኛ ቋንቋ መማርን ግዴታ አድርጓል ቁርኣንን እንዲያናግሩበትና ለአምልኮው እንዲጠቀሙበት።”

የሀነፊ መዝሀብ ዑለማኦች ደግሞ እንዲህ ይላሉ “ዐረብኛ በዓለም ላይ ከሚገኙ ሁሉ በላጭ ቋንቋ ነው። የጀነት ሰዎችም ቋንቋ ነው። እሱን የተማረ አሊያም ለሌላ ያስተማረ ሰው ምንዳ ያገኛል።”

አንድ ሰው የዐረብኛ ቋንቋ እውቀቱ በሠፋ ቁጥር እስልምናን የማወቅ ብቃቱ ይጨምራል። ለዚህም ነው ኢማሙ ሻፊዒ እንደሚሉት ህዝቦች በዚህ ቋንቋ ንግግር የተደረገላቸው።

በሌላ በኩል የዐረብኛ ቋንቋ የእስልምና ኦፊሴላዊ ቋንቋ መሆኑ ሌላውን ቋንቋ ሁሉ ዋጋ ያሣጣል ማለት አይደለም። ለሙስሊሙ ማህበረሰብ የሚግባቡበትና አንዱ ሌላኛውን የሚረዳበት ቋንቋ ያስፈልገዋል። ይህም ቋንቋ ዐረብኛ ቢይሆን ሊገርመን አይገባም። ዐረብኛ ሙስሊሞች የአምልኮ ሥርኣት የሚፈፅሙበት ቋንቋቸው ነው። በአጋጣሚውም ሁለተኛ ቋንቋም ሆናቸው ማለት ነው። ይህ ሁሉ ምልከታና ጥቆማ ከወገናዊነት የራቀ ነው። ዐረብኛን መማር መታደል ነው። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል

“እናንተ ሰዎች ሆይ! ጌታ አንድ ጌታ ብቻ ነው፤ አባትም አንድ አባት ብቻ ነው፤ ሃይማኖትም አንድ ሃይማኖት ብቻ ነው። ዐረብኛ የአንዳችሁ አባት አሊያም እናት ቋንቋ አይደለም። ባይሆን በዐረብኛ የተናገረ ሁሉ እሱ ዐረብ ነው።” (ኢብኑ ዐሣኪር ዘግበውታል)

6. የስሜት የአስተሣሠብና የእይታ አንድነት

በምድራዊ ህይወት ውስጥ የሙስሊሞች መንገድ ግልፅና ለየት ያለ ነው። ይሀውም የነቢያት፣ የእውነተኞች (ሲዲቂን)፣ የሰማእታትና (ሹሃዳእ) የመልካም ሰዎች መንገድ ነው። አላህ ሱ.ወ. እንዲህ አለ

اهْدِنَا الصِّرَاطَ الْمُسْتَقِيمَ صِرَاطَ الَّذِينَ أَنْعَمْتَ عَلَيْهِمْ غَيْرِ الْمَغْضُوبِ عَلَيْهِمْ وَلَا الضَّالِّينَ

“ቀጥተኛውን መንገድ ምራን። የእነዚያን በነርሱ ላይ በጎ የዋልክላቸውን በነሱ ላይ ያልተቆጣህባቸውንና ያልተሳሳቱትንም ሰዎች መንገድ (ምራን፤ በሉ)።” (አልፋቲሃ 1፤6-7)

የአላህ መልእክተኛም (ሰ.ዐ.ወ)

تركتكم على الجادة ليلها كنهارها لا يزيغ عنها إلا هالك

“ለሊቷ ቀንን በሚመስል መንገድ ላይ ትቼያችኋለሁ፤ አይዋትም ቢጠፋ እንጂ።” ብለዋል (አህመድና ኢብኑ ማጃህ)

ዑመር (ረ.ዐ) የነቢዩን አባባል ለማብራራት ሲሞክሩ እንዲህ ብለዋል “ግልፅ በሆነና ለሊቱ ቀንን በሚመስል መንገድ ላይ ተትታችኋል” ዐሊም (ረ.ዐ) ደግሞ “ግልፅ ባለና የመፅሃፎች ሁሉ እናት በሆነው መንገድ ላይ ተትታችኋል” ማለት ነው ብለዋል። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በሌላ ሀዲሣቸው

من فارق الجماعة قيد شبر فقد خلع ربقة الإسلام من عنقه وإن صلى وصام وزعم أنه مسلم

“የስንዝር ያህል ከጀመዓ የወጣ ቢሰግድ፣ ቢፆምም ሙስሊም ነኝ ቢልም የኢስላምን ማተብ ከአንገቱ አውልቋል።” ብለዋል (አቡ ዳዉድ፣ አህመድን ቲርሚዚ)።

የሙስሊሙ ማሕበረሰብ ለየት ያለ መንገድ እንዳለው ሁሉ አመለካከቱም የተለየ ነው። አመለካከቱም ሆነ ግንዛቤው ከአላህ ኪታብ /ቁርኣን/ ጋር የተያያዘ ነው። አላህ እንዲህ አለ

قَدْ جَاءَكُم بَصَائِرُ مِن رَّبِّكُمْ فَمَنْ أَبْصَرَ فَلِنَفْسِهِ وَمَنْ عَمِيَ فَعَلَيْهَا وَمَا أَنَا عَلَيْكُم بِحَفِيظٍ

“ከጌታችሁ ዘንድ ብርሃኖች በእርግጥ መጡላችሁ። የተመለከተም ሰው (ጥቅሙ) ለነፍሱ ብቻ ነው። የታወረም ሰው (ጉዳቱ) በራሱ ላይ ብቻ ነው። እኔም በእናንተ ላይ ጠባቂ አይደለሁም (በላቸው)።” (አል-አንዓም 6፤ 104)

هَٰذَا بَصَائِرُ لِلنَّاسِ وَهُدًى وَرَحْمَةٌ لِّقَوْمٍ يُوقِنُونَ

“ይሀ (ቁርኣን) ለሰዎች የልብ ብርሃኖች ነው። ለሚያረጋግጡም ሕዝቦች መሪና እዝነት ነው።” (አል-ጃሲያህ 45፤20)

የሙስሊሞች አመለካከትና አስተሣሰብ ሁሉ የሚመነጨው ቁርኣን ሁሉንም ነገር የሚያዩበት እውቀት መሆኑ ነው።

7. የህገ መንግስትና የህግ መመሪያ አንድነት

የሙስሊሙ ማህበረሰብ ህገመንግስትና ህግጋት የሚመነጩት ከቁርኣንና ከሀዲሰ ነው። ለሙስሊሞችም መተዳደሪያ የአላህን ህግ የሚቃረን ህግ ሊኖር አይገባም። በመሆኑም በሙስሊሙ ዓለም ተመሣሣይ የሆነ የወንጀል መቅጫ ህግ፣ የንግድ ህግ፣ የግለሰባዊ ሁኔታ ህግ እና ተመሣሣይ የሆነ የመንግስት ህግ ሊኖር ይገባል። በመሠረቱ በሙስሊሞች መካከል የቁርኣንና ሀዲስ መልእክቶች ትርጉም በመረዳቱ ረገድ ለኢጅቲሃድ ክፍት በሆን ጉዳዮች ላይ ልዩነት ሊኖር ይችላል። ነገርግን በእስልምና ህግጋት መሠረታዊ መመሪያዎች ላይ እንደሚታወቀው የዚህ ዓይነቱ ችግር ባጋጠመ ጊዜ የሙስሊሞች ኸሊፋ ከምክር ቤት አባላት ጋር በመሆን የተሻለውን ግንዛቤ በመውሰድ አንድን ህግ ማፅደቅ ይችላሉ። አንድ ህገመንግስትና የህግ መመሪያም ይኖረዋል ማለት ነው። የዚህ ዓይነቱ ህግ በዚያ ሀገር ውስጥ የሚገኝ እያንዳንዱ የሙስሊም ግዛት የራሱ የሆነ ልዩ ህግጋት እንዳይኖረው አያግድም። በመዝሀብ ይሁን በፍቅሂ እውቀቶች ዙሪያ፤ አንዳንድ ነገሮችን መፍቀድን በተመለከተ አሊያም አንዳንድ ስምምነቶችን በመፈፀም ረገድ የራሱ የሆነ ህግ ሊኖረው ይችላል። እንደ አጠቃላይ ሲታይ ግን ማንኛውም ህግ ከቁርአንና ከሀዲስ ጋር መጋጨት አይኖርበትም።

8. የመሪ አንድነት

በመሰረቱ የሙስሊሙ ኡማ መሪ አንድ ነው። ይህም መሪ የአላህ መልእክተኛ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ናቸው። ሙስሊሞች ሁሉ እርሣቸውን ሊታዘዙ ግዴታ አለባቸው። ነቢዩ ይህችን ዓለም ተለይተው ወደ ላይኛው ዓለም በሄዱ ጊዜ ሸሪዓን የሚያስተገብር፣ የሙስሊሞችን የመስፋፋት ሂደት የሚመራ፣ ሙስሊሙን ኡማ የፖለቲካ አቅጣጫ የሚወስን ለርሣቸው ተተኪ የሚሆን ኸሊፋ መምረጥ አለባቸው። እናም ይህ መሪ ከሸሪዓ መንገድ እስካልወጣ ድረስ እሱን መከተሉ ግዴታ ነው። ሙስሊሞች በየትኛውም ሁኔታ ለይ ያለ መሪና ኢማም መኖር የለባቸውም። ትክክለኛ መሪ የአንድነታቸው ምልክት ነውና። አንድነታቸው የጥንካሬያቸው ምልክት ሲሆን ጥንካሬያቸው ደግሞ እራሣቸውን ለመከላከልም ሆነ የአላህን ሥልጣን በምድር ላይ ለማስፈን በተቻለ መጠን ሁሉ የተበላሸውን ለማስተካል መንገድ ነውና።

ማጠቃለያ

በዚህ ሁሉ ማለትም በዐቂዳ፣ በአምልኮ ሥርኣት፣ በሥነምግባር፣ በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በህግ ምንጭ፣ በአመራር አንድ መሆናቸው የሙስሊሙ ጥንካሬ የበለጠ ይጨምራል። የበለጠ ይፋፋል። የበለጠ ትልቅና ሀያል ይሆናል።

ሙስሊሙ ህዝብ አንድ ማህበረሰብ ነው። የማህበረሰቡ ልጆችም ወንድማማቾች ናቸው። አላህ እንዲህ አለ

إِنَّمَا الْمُؤْمِنُونَ إِخْوَةٌ فَأَصْلِحُوا بَيْنَ أَخَوَيْكُمْ وَاتَّقُوا اللَّهَ لَعَلَّكُمْ تُرْحَمُونَ

“ምእመናኖች ወንድማመቾች ናቸው። በሁለት ወንድሞቻችሁም መካከል አስታርቁ። ይታዘንላችሁም ዘንድ አላህን ፍሩ።” (አል-ሁጁራት 49፤10)

ወዳጅነታቸውና መረዳዳታቸው አንደኛቸው ለሌላኛው ነው።

وَالْمُؤْمِنُونَ وَالْمُؤْمِنَاتُ بَعْضُهُمْ أَوْلِيَاءُ بَعْضٍ يَأْمُرُونَ بِالْمَعْرُوفِ وَيَنْهَوْنَ عَنِ الْمُنكَرِ وَيُقِيمُونَ الصَّلَاةَ وَيُؤْتُونَ الزَّكَاةَ وَيُطِيعُونَ اللَّهَ وَرَسُولَهُ أُولَٰئِكَ سَيَرْحَمُهُمُ اللَّهُ إِنَّ اللَّهَ عَزِيزٌ حَكِيمٌ

“ምእምንና ምእምናትም ከፊሎቻቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው። በደግ ነገር ያዛሉ፤ ከክፉም ይከለክላሉ። ሶላትንም ይሰግዳሉ። ዘካንም ይሰጣሉ። አላህንና መልክተኛውንም ይታዘዛሉ። እነዚያን አላህ በእርግጥ ያዝንላቸዋል። አላህ አሸናፊ ጥበበኛ ነውና።” (አት-ተውባ 9፤71)

እንደ አንድ አካልና አንድ መንፈስም ናቸው። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል

مثل المؤمنين في توادهم وتراحمهم وتعاطفهم كمثل الجسد إذا اشتكى منه عضو تداعى له سائر الجسد بالحمى والسهر

“ሙስሊሞች እርስ በርስ መዋደዳቸው፣ በእዝነታቸውና በርህራሄያቸው እንደ አንድ ሰውነት ናቸው። አንዱ የሰውነት ክፍል የታመመ እንደሆነ ሌላው የሰውነት ክፍል በትኩሣት እና ያለ እንቅልፍ በማደር ይታመማል።” (ቦኻሪና ሙስሊም)

ሙስሊሙ ለኢስላምና ለሙሰሊም ጠላት ለአንድም አካል የልብ ወዳጅነትና የወንድማማችነት ፍቅር ሊሠጥ አይገባም። አላህ እንዲህ አለ

لَّا تَجِدُ قَوْمًا يُؤْمِنُونَ بِاللَّهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ يُوَادُّونَ مَنْ حَادَّ اللَّهَ وَرَسُولَهُ وَلَوْ كَانُوا آبَاءَهُمْ أَوْ أَبْنَاءَهُمْ أَوْ إِخْوَانَهُمْ أَوْ عَشِيرَتَهُمْ أُولَٰئِكَ كَتَبَ فِي قُلُوبِهِمُ الْإِيمَانَ وَأَيَّدَهُم بِرُوحٍ مِّنْهُ وَيُدْخِلُهُمْ جَنَّاتٍ تَجْرِي مِن تَحْتِهَا الْأَنْهَارُ خَالِدِينَ فِيهَا رَضِيَ اللَّهُ عَنْهُمْ وَرَضُوا عَنْهُ أُولَٰئِكَ حِزْبُ اللَّهِ أَلَا إِنَّ حِزْبَ اللَّهِ هُمُ الْمُفْلِحُونَ

“በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑትን ሕዝቦች አላህንና መልክተኛውን የሚከራከሩትን ሰዎች፤ አባቶቻቸው፣ ወይም ልጆቻቸው፣ ወይም ወንድሞቻቸው፣ ወይም ዘመዶቻቸው ቢኾኑም እንኳ የሚወዳጁ ኾነው አታገኛቸውም። እነዚያ በልቦቻቸው ውስጥ እምነትን ጽፏል። ከእርሱም በኾነ መንፈስ ደግፏቸዋል። ከሥሮቻቸውም ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ ያገባቸዋል። አላህ ከእነርሱ ወዷል። ከእርሱም ወደዋል። እነዚያ የአላህ ሕዝቦች ናቸው። ንቁ! የአላህ ሕዝቦቸ እነርሱ ምኞታቸውን የሚያገኙ ናቸው።” (አል-ሙጃደላህ 58፤22)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here