ኢስላም – የህይወት መንገድ (ክፍል 2)

0
3688

ኢስላም- በመጨረሻው መለኮታዊ መልእክት

ኢስላም ሲባል ትርጉሙ በሁለት ነገሮች ላይ ሊያተኩር ይችላል

  • አንደኛው – አላህ ሃይማኖቱን ለመግለፅ በአንቀፆቹ ባወረደው የወህይ (መለኮታዊ ራእይ) መልእክት ላይ ሲሆን
  • ሁለተኛው – የሰው ልጅ በነኚህ አንቀፆች በማመኑና በነሱ በመመራቱ በሚሠራው ሥራ ላይ ነው።

እዚህ ጋ ልብ ማለት ያለብን ነገር ምንም እንኳ በዋናና መሠረታዊ ነገር ተመሣሣይ ቢሆንም ኢስላም በመጀመሪያው ትርጉሙ በስፋቱና ከሚያጠቃልለው መልእክት አንፃር ከአንድ መልእክተኛ ወደ ሌላው መልእክተኛ የሚለያይ መሆኑን ነው። ለምሣሌ በነቢዩ ሙሣ (ዐ.ሰ) ላይ የወረደው የእስልምና ሥርዓት በነቢዩ ኑህ (ዐ.ሰ) ላይ ከወረደው ሰፋ ይላል። አላህ ተውራትን (ኦሪት) እንዲህ በማለት ገልፆታልና፡-

وَكَتَبْنَا لَهُ فِي الْأَلْوَاحِ مِن كُلِّ شَيْءٍ مَّوْعِظَةً وَتَفْصِيلًا لِّكُلِّ شَيْءٍ

“ለርሱም በሠሌዳዎች ላይ ለነገሩ ሁሉ ግሣፄንና ለነገሩም ሁሉ ማብራሪያን ፃፍንለት።” (አል-አዕራፍ 7፤ 145)

ነቢያችን ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ይዘውት የመጡት የእስልምና አስተምህሮ ደግሞ ከቀደሟቸው መልእክተኞች ሁሉ ሰፋ ይላል። ቀደምት የአላህ መልእክተኞች ሁሉ የተላኩት ለየህዝቦቻቸው ሲሆን ነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ግን የተላኩት ለሰው ልጆች በሙሉ ነው። ለዚህም ነው እስልምናቸው ከቀደሟቸው መልእክቶች ሁሉ የሰፋ ነው ለማለት የቻልነው። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

وَنَزَّلْنَا عَلَيْكَ الْكِتَابَ تِبْيَانًا لِّكُلِّ شَيْءٍ وَهُدًى وَرَحْمَةً وَبُشْرَىٰ لِلْمُسْلِمِينَ 

“መፅሃፉንም ለሁሉ ነገር አብራሪ፣ መሪም፣ እዝነትም ለሙስሊሞችም አብሣሪ ሆኖ ባንተ ላይ አወረድነው።” ( አን-ነህል 16፤ 89)

በነቢያችን መላክ ነቢያትንና የመልእክተኞች ወደ ሰው ልጆች የመላኩ ሂደት መቋጫ አግኝቷል።

አላህም ሱብሃነሁ ወተዓላም የቀደሙንን ነቢያትና መልእክተኞች መንገድ ይዘን እንጓዝ ዘንድም አላህ አዞናል።

أُولَٰئِكَ الَّذِينَ هَدَى اللَّهُ فَبِهُدَاهُمُ اقْتَدِهْ

“እነዚያ እነሱ አላህ የመራቸው ናቸው። በመንገዳቸው ተከተል” (አል-አንዓም 6፤ 90) በማለት።

በሃይማኖት በኩል መሟላት የሚገባውንም ሁሉ አሟላልን። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

الْيَوْمَ أَكْمَلْتُ لَكُمْ دِينَكُمْ وَأَتْمَمْتُ عَلَيْكُمْ نِعْمَتِي وَرَضِيتُ لَكُمُ الْإِسْلَامَ دِينًا

“ዛሬ ሃይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ፡ ፀጋዬንም በናንተ ላይ ፈፀምኩ፤ እስልምናንም በሃይማኖት በኩል ለናንተ ወደድኩ።” (አል-ማኢዳህ 5፤ 3)

የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም እራሣቸውንና የቀደሟቸውን ነቢያት ምሣሌ እንዲህ በማለት ይገልፁልናል።

“የኔና ከኔ በፊት የነበሩ ነቢያት ምሣሌ እንደ አንድ ቤት የሠራና ቤቱንም ያሣመረና ያስዋበ ከምኩራቡ በኩል ትንሽ ክፍት ቦታ ብቻ የተወ ሰው ነው። ሰዎችም ቤቱን እየዞሩና እየተገረሙ ‘ምናለ ይህችን ክፍት ቦታ ብትዘጋ ኖሮ’ ይሉታል። እኔ የዚያች ክፍት ቦታ መዝጊያ ነኝ። እኔ የነቢያቶች ሁሉ መቋጫ ነኝ።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

እስልምና እንዲህ የተሟላና ክፍተት የሌለው በመሆኑ የሁሉም የሰው ልጆች ልብ ወደሱ ማዘንበሉ አይቀርም። ይህ እንከን የለሽ ባህሪው ደግሞ የቀደሙትን ሃይማኖታዊ ህግጋት ሁሉ እንዲሽር አስችሎታል። ከሱ በኋላም እሱን የሚሽር ሌላ የእምነት ህግ አይመጣም፤ በሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም መላክ የአላህ መልእክት ተቋጭቷልና። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ –

مَّا كَانَ مُحَمَّدٌ أَبَا أَحَدٍ مِّن رِّجَالِكُمْ وَلَٰكِن رَّسُولَ اللَّهِ وَخَاتَمَ النَّبِيِّينَ وَكَانَ اللَّهُ بِكُلِّ شَيْءٍ عَلِيمًا 

“ሙሀመድ ከወንዶቻችሁ የማንም አባት አይደለም። ግን የአላህ መልአክተኛና የነቢያት መደምደሚያ ነው። አላህም በነገሩ ሁሉ አዋቂ ነው።” (አል-አህዛብ 33፤ 40)

قُلْ يَا أَيُّهَا النَّاسُ إِنِّي رَسُولُ اللَّهِ إِلَيْكُمْ جَمِيعًا

“በላቸው – እናንተ ሰዎች ሆይ! እኔ ወደናንተ ወደ ሁላችሁም የአላህ መልእክተኛ ነኝ።” (አል-አዕራፍ 7፤ 158)

وَمَا أَرْسَلْنَاكَ إِلَّا كَافَّةً لِّلنَّاسِ بَشِيرًا وَنَذِيرًا

“አንተን ለሰዎች ሁሉ በመላ አብሳሪና አስጠንቃቂ አድርገን ቢሆን እንጂ አልላክንህም” (ሰበእ 34፤ 28)

وَمَا أَرْسَلْنَاكَ إِلَّا رَحْمَةً لِّلْعَالَمِينَ 

“ለዓለማት እዝነት እንጂ አልላክንህም” (አል-አንበያእ 21፤ 107)

وَمَن يَبْتَغِ غَيْرَ الْإِسْلَامِ دِينًا فَلَن يُقْبَلَ مِنْهُ وَهُوَ فِي الْآخِرَةِ مِنَ الْخَاسِرِينَ

“ከኢስላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰው ፈጽሞ ከርሱ ተቀባይ የለውም። እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎቹ ነው። (ኣሊ-ዒምራን 3፤ 85)

إِنَّ الدِّينَ عِندَ اللَّهِ الْإِسْلَامُ 

“(ትክክለኛ) ሃይማኖት አላህ ዘንድ እስልምና ነው” (ኣሊ-ዒምራን 3፤ 19)

ነቢዩ ሙሀመድን ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የማይከተል ሰው እሱ በርግጥ መንገድ የሣተና የጠመመ ነው። በሰሂህ (ትክክለኛ) ሀዲስም ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም እንዲህ ብለዋል

“ነፍሴ በእጁ በሆነችው ጌታ እምላለሁ። ከዚህች ህዝብ አይሁድም ይሁን ክርስቲያን አንድም ሰው ስለኔ መላክ ሰምቶ እኔ በተላክሁበት ነገር ያላመነ እንደሆነ እርሱ የእሣት ሰው ነው።” (ሙስሊም)

አላህም እንዲህ አለ

وَمَن يُشَاقِقِ الرَّسُولَ مِن بَعْدِ مَا تَبَيَّنَ لَهُ الْهُدَىٰ وَيَتَّبِعْ غَيْرَ سَبِيلِ الْمُؤْمِنِينَ نُوَلِّهِ مَا تَوَلَّىٰ وَنُصْلِهِ جَهَنَّمَ وَسَاءَتْ مَصِيرًا 

“ቅኑ መንገድ ለርሱ ከተገለጠለት በኋላ መልእክተኛውን የሚጨቃጨቅና ከምእመኖቹ መንገድ ሌላ የሆነን የሚከተል ሰው በተሾመበት ላይ እንሾመዋለን፤ ጀሀነምንም እናስገባዋለን። መመለሻይቱም ከፋች።” ( አን-ኒሣእ 4፤ 115)

በሌላ የቁርኣን አንቀፅም

إِنَّ الَّذِينَ يَكْفُرُونَ بِاللَّهِ وَرُسُلِهِ وَيُرِيدُونَ أَن يُفَرِّقُوا بَيْنَ اللَّهِ وَرُسُلِهِ وَيَقُولُونَ نُؤْمِنُ بِبَعْضٍ وَنَكْفُرُ بِبَعْضٍ وَيُرِيدُونَ أَن يَتَّخِذُوا بَيْنَ ذَٰلِكَ سَبِيلًا أُولَٰئِكَ هُمُ الْكَافِرُونَ حَقًّا وَأَعْتَدْنَا لِلْكَافِرِينَ عَذَابًا مُّهِينًا 

“እነዚያ በአላህና በመልእክተኛው የሚክዱ፤ በአላህና በመልእክተኞቹም መካከል መለያየትን የሚፈልጉ፤ በከፊሉም እናምናለን በከፊሉም እንክዳለን የሚሉና በዚህም መካከል መንገድን ሊያዙ የሚፈልጉ እነዚያ በውነት ከሓዲዎቹ እነርሱ ናቸው። ለከሓዲዎችም አዋራጅን ቅጣት አዘጋጅተናል።” (አን-ኒሣእ 4፤ 150-151)

በመሠረቱ ዛሬ ላይ ሆነን ሁኔታዎችን ስንመለከት ያለፉት መልእክተኞች የተላኩበት ኢስላም ተረስቷል ወይ ትርጉሙ ተጣሟል፤ አሊያም ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል፤ የያዘው እውነትም እንዲጠፋ ተደርጓል። በእምነት በአምልኮ ይሁን በሥነምግባር በኩል የውሸት አስተምህሮ ቦታ አግኝቷል። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ከቁርኣንና ከአላህ መልእክተኛ ትክክለኛ ሀዲስ ውጭ ያልተበረዘና ያልተደለዘ ሃይማኖታዊ መፅሃፍ የሌለ መሆኑ የታወቀ ነው። በመሆኑም የሰው ልጅ ወደ ጌታው መንገድ መመራት የፈለገ እንደሆነ ሙሀመድን ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ከመከተል ውጭ አማራጭ ሊኖረው አይገባም። አላህ ከእስልምና ውጭ ሌላን መንገድ አይቀበልምና። አላህ እንዲህ አለ

يَا أَهْلَ الْكِتَابِ قَدْ جَاءَكُمْ رَسُولُنَا يُبَيِّنُ لَكُمْ عَلَىٰ فَتْرَةٍ مِّنَ الرُّسُلِ أَن تَقُولُوا مَا جَاءَنَا مِن بَشِيرٍ وَلَا نَذِيرٍ فَقَدْ جَاءَكُم بَشِيرٌ وَنَذِيرٌ وَاللَّهُ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ 

“እናንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! ‘አብሳሪና አስፈራሪ አልመጣልንም’ እንዳትሉ ከመልክተኞች በመቋረጥ ጊዜ ላይ ሲኾን (ሕጋችንን) የሚያብራራ ኾኖ መልክተኛችን በእርግጥ መጣላችሁ። አብሳሪና አስፈራሪም በእርግጥ መጣላችሁ። አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው።”(አል-ማኢዳህ 5፤ 19)

የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም የሰው ልጆችን የጠሩበት ኢስላም ለመላው የሰው ልጅ ትክክለኛና የተሟላ መመሪያ ሲሆን የሚታወቀውም የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ባስተማሩት መንገድ በቁርኣንና በሀዲስ ነው።

የተላቀውና የተከበረው ጌታችን አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እስልምናን የተሟላና ሁሉን ጠቅላይ አድርጎታል። እስልምና አንድ ነገር የተፈቀደ (ሙባህ) አሊያም ክልክል (ሀራም)፣ ተወዳጅ (ሙሰተሃብ) አሊያም የተጠላ (መክሩህ)፣ ሱና (ቢሠራ መልካምና ምንዳ የሚያስገኝ) ይሁን ግዴታ (ፈርድ/ዋጂብ) ስለመሆኑ የገለፀ ቢሆን እንጂ አላለፈም። የእምነት፣ የአምልኮ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ ኑሮ፣ የኢኮኖሚ፣ የጦርነት አሊያም የሠላም፣ የህግጋት ጉዳይ ሊሆን ይችላል በአጠቃላይ በዓለማችን ላይ ከሚገኙና በሰው ልጅ አእምሮ ውስጥ ከሚመላለሱ ነገሮች ውስጥ አንድም ሣያነሣው ያስቀረው ጉዳይ የለም። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ መፅሃፉን ሲገልፅ እንዲህ ይላል

وَنَزَّلْنَا عَلَيْكَ الْكِتَابَ تِبْيَانًا لِّكُلِّ شَيْءٍ وَهُدًى وَرَحْمَةً وَبُشْرَىٰ لِلْمُسْلِمِينَ

“መፅሃፉንም ለሁሉ ነገር አብራሪ፣ መሪም፣ እዝነትም ለሙስሊሞችም አብሣሪ ሆኖ ባንተ ላይ አወረድነው” (አን-ነህል 16፤ 89)

በሌላ የቁርኣን አንቀፅም

وَتَفْصِيلَ كُلِّ شَيْءٍ

“ለነገርም ሁሉ ገላጭ” (ዩሱፍ 12፤ 111) በማለት ገልፆታል።

በቁርኣን እና በሀዲስ በግልፅና በቀጥታ ያልተቀመጡ ነገሮችንም ቢሆን ተመሣሣይ ህግጋት በተዘዋዋሪ መልኩ መረዳት ይቻላል። ይህም በህዝበ ሙስሊም ውስጥ የሚገኙ የሃይማኖት ሊቃውንቶችና ተመራማሪዎች (ሙጅተሂዶች) በጥረታቸው (በኢጅቲሃድ) የሚያገኙትና የሚስማሙበት ጉዳይ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here