ኢስላም – የህይወት መንገድ (ክፍል 1)

3
5674

ኢስላም የመልእክተኞችና የነቢያቶች ሁሉ ሃይማኖት

ከአደም ዐለይህ ሰላም ጀምሮ የአላህ መልእክተኞች መቋጫ እስከሆኑት እስከ ነቢያችን ሙሀመድ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ድረስ ኢስላም የመልእክተኞችና የነቢያቶች ሁሉ ሃይማኖት ነው።

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላም ይህንኑ አረጋግጦታል። የሚከተሉት የቁርኣን አንቀፆች ይህንኑ ያመለክታሉ ፡፡

 • በቁርኣን ውስጥ ኑህ እንዲህ ይላል

وَأُمِرْتُ أَنْ أَكُونَ مِنَ الْمُسْلِمِينَ

“ሙስሊም እንድሆን ታዝዣለሁ፡፡” (ዩኑስ 10፤ 72)

 • ነቢዩ ኢብራሂም እና ኢስማዒል ደግሞ

رَبَّنَا وَاجْعَلْنَا مُسْلِمَيْنِ لَكَ وَمِن ذُرِّيَّتِنَا أُمَّةً مُّسْلِمَةً لَّكَ

“ጌታችን ሆይ! ላንተ ሙስሊሞች (ታዛዦች) አድርገን፡፡ ይላሉ፡፡ ከዘሮቻችንም ላንተ ታዛዦች (ሙስሊም) ሕዝቦችን (አድርግ)፡፡” (አል-በቀራህ 2፤ 128)

 • ነቢዩ የዕቁብም በኑዛዜያቸው ውስጥ ለልጆቻቸው ሲመክሩ

وَوَصَّىٰ بِهَا إِبْرَاهِيمُ بَنِيهِ وَيَعْقُوبُ يَا بَنِيَّ إِنَّ اللَّهَ اصْطَفَىٰ لَكُمُ الدِّينَ فَلَا تَمُوتُنَّ إِلَّا وَأَنتُم مُّسْلِمُونَ

“በርሷም (በሕግጋቲቱ) ኢብራሂም ልጆቹን አዘዘ፡፡ ያዕቁብም (እንደዚሁ ልጆቹን አዘዘ)፡፡ ‘ልጆቼ ሆይ! አላህ ለናንተ ሃይማኖትን መረጠ፤ ስለዚህ እናንተ ሙስሊሞች ኾናችሁ እንጂ አትሙቱ’ (አላቸው)፡፡” (አል-በቀራህ 2፤ 132) ብለዋል፡፡

 • ነቢዩ ሙሣም ለህዝቦቻቸው እንዲህ ይላሉ

وَقَالَ مُوسَىٰ يَا قَوْمِ إِن كُنتُمْ آمَنتُم بِاللَّهِ فَعَلَيْهِ تَوَكَّلُوا إِن كُنتُم مُّسْلِمِينَ

“ሙሳም አለ፡- ሕዝቦቼ ሆይ! በአላህ አምናችሁ እንደ ሆነ በርሱ ላይ ተጠጉ፡፡ ሙስሊሞች የሆናችሁ እንደሆነ በሱ ተመኩ::” (ዩኑስ 10፤ 84)

 • አላህ ለሙሣ ስለተሠጠው ተውራት (ኦሪት) መፅሃፍ ሲገልፅ

يَحْكُمُ بِهَا النَّبِيُّونَ الَّذِينَ أَسْلَمُوا 

“እነዚያ የሠለሙ (ትእዛዛትን የተቀበሉ) ነቢያት በሷ ይፈርዳሉ” (አል-ማኢዳህ 5፤ 44)

 • ነቢዩ ዩሱፍም በዱዓአቸው

تَوَفَّنِي مُسْلِمًا وَأَلْحِقْنِي بِالصَّالِحِينَ

“ሙስሊም አድርገህ ግደለኝ ከደጋጎችም አስጠጋኝ” (ዩሱፍ 12፤101)

 • የፈርኦውን ደጋሚዎች (መተተኞች)ም ነቢዩ ሙሣ ከአላህ ባመጣው መልእክት ባመኑ ጊዜ እንዲህ ብለው ነበር

رَبَّنَا أَفْرِغْ عَلَيْنَا صَبْرًا وَتَوَفَّنَا مُسْلِمِينَ 

“ጌታችን ሆይ! ትእግስትን አፍስብን ሙስሊሞች አድርገህም ግደለን” (አል-አዕራፍ 7፤ 126)

 • የነቢዩ ዒሣ ሀዋሪያትም እንዲህ ብለዋል

آمَنَّا بِاللَّهِ وَاشْهَدْ بِأَنَّا مُسْلِمُونَ

“በአላህ አምነናል ሙስሊሞች መሆናችንን መስክር” (ኣሊ-ዒምራን 3፤ 52)

 • የሣባዋ ንግስትም በአላህ ባመነች ጊዜ

وَأَسْلَمْتُ مَعَ سُلَيْمَانَ لِلَّهِ رَبِّ الْعَالَمِينَ

“ከሱለይማን ጋር ለዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ ሠልሜያለሁ (እጅ ሠጥቻለሁ)” (አን-ነምል 27፤44) ብላ ነበር፡፡

 • አንድ ሷሊህ የሆነ ሰው ዱዓእ ያደረገበትን ሁኔታ አላህ ሲገልፅልን

وَأَصْلِحْ لِي فِي ذُرِّيَّتِي إِنِّي تُبْتُ إِلَيْكَ وَإِنِّي مِنَ الْمُسْلِمِينَ

“ዘሮቼን መልካም አድርግልኝ፡፡ እኔ ወዳንተ ተመልሻለሁ እኔ ከሙስሊሞቹ ነኝ” (አል-አህቃፍ ፤15) ብሏል፡፡

 • በሀዲስም ከአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም እንዲህ የሚል ተዘግቧል፡-

“ነቢያት ወንድማማቾች ናቸው፡፡ የአንድ አባት ልጆች ሲሆኑ እናቶቻቸው የተለያዩ ናቸው፡፡ ሃይማኖታቸው ግን አንድ ነው።”(ቡኻሪ፣ ሙስሊምና አቡ ዳዉድ) ይህንንም በማስመልከት አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

شَرَعَ لَكُم مِّنَ الدِّينِ مَا وَصَّىٰ بِهِ نُوحًا وَالَّذِي أَوْحَيْنَا إِلَيْكَ وَمَا وَصَّيْنَا بِهِ إِبْرَاهِيمَ وَمُوسَىٰ وَعِيسَىٰ أَنْ أَقِيمُوا الدِّينَ وَلَا تَتَفَرَّقُوا فِيهِ

“ለናንተ ከሃይማኖት ያንን በርሱ ኑህን ያዘዘበትን ደነገገላችሁ፡፡ ያንንም ወዳንተ ያወረድነውን ያንንም በርሱ ኢብራሂምን ሙሣንና ዒሣን ያዘዝንበትን ሃይማኖትን አቋቁሙ፡፡ በርሱም አትለያዩ።” (ሹራ 42፤ 12)

የኢስላም ትርጉም

ኢስላም ማለት ትርጉሙ የአላህ ትእዛዛትን በመተግበር፣ ከክልከላው በመከልከል፣ በወህይ /መለኮታዊ ራእይ/ በወረደው መልእክቱ በማመን ሙሉ ለሙሉ ለአላህ እጅ መስጠት ነው፡፡ ፊቱን፣ ቀልቡን፣ መላ አካላቱንና በአጠቃላይ በሁሉ ነገር ውስጥ እራሱን ለአላህ የሠጠ ሰው እሱ ነው ሙስሊም (ለአላህ ታዛዠ) ማለት። ነቢያትና የአላህ መልእክተኞች ለአላህ በመስለሙ (እጅ በመስጠቱና በመታዘዙ) ረገድ የበለጡ ሆነው በመገኘታቸው የመጀመሪያዎቹ ሙስሊሞች ለመሆን ችለዋል። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ –

قُلْ إِنَّ صَلَاتِي وَنُسُكِي وَمَحْيَايَ وَمَمَاتِي لِلَّهِ رَبِّ الْعَالَمِينَ لَا شَرِيكَ لَهُ وَبِذَٰلِكَ أُمِرْتُ وَأَنَا أَوَّلُ الْمُسْلِمِينَ

“በል- ስግደቴ፣ መስዋእቴ፣ ህይወቴ፣ ሞቴ ለዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ ነው፤ አጋር የለውም በዚህም ታዝዣለሁ፤ እኔ የመጀመሪያ ሙስሊም ነኝ” (አል-አንዓም 6፤ 162-163)

በሌላ የቁርኣን አንቀፅም አላህ ስለ ነቢዩ ሙሣ ሲናገር

قَالَ سُبْحَانَكَ تُبْتُ إِلَيْكَ وَأَنَا أَوَّلُ الْمُؤْمِنِينَ

“(ከጉድለት ሁሉ) የጠራህ ነህ፡፡ ወዳንተ ተመልሽያለሁ እኔ የመጀመሪያ አማኝ ነኝ፡፡ አለ” (አል-አዕራፍ ፤143) ይለናል፡፡

ለአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እጅ መስጠት ሲባል ዳኝነቱንና ፍርዱንም ያለአንዳች ቅሬታ መቀበልን ጭምር ያጠቃልላል፡፡ ይህ ካልሆነ በስተቀር እስልምና የለም፡፡ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ እንዲህ አለ

فَلَا وَرَبِّكَ لَا يُؤْمِنُونَ حَتَّىٰ يُحَكِّمُوكَ فِيمَا شَجَرَ بَيْنَهُمْ ثُمَّ لَا يَجِدُوا فِي أَنفُسِهِمْ حَرَجًا مِّمَّا قَضَيْتَ وَيُسَلِّمُوا تَسْلِيمًا

“በጌታህ እምላለሁ፡፡ በመካከላቸው በተከራከሩበት ፍርድ እስከሚያስፈርዱህ ከዚያም ከፈረድከው ነገር በነፍሦቻቸው ውስጥ ቅሬታን እስከማያገኙና ፍፁም መታዘዝንም እስከሚታዘዙ ድረስ አያምኑም፡፡” (አን-ኒሣእ 4፤65)

የአላህ ህግጋቶች የሚታወቁት በትክክለኛው መለኮታዊ ራእይ መልእክት ነው። ይህንንም ታማኙና እውነተኛው የአላህ መልእክተኛ አድርሰውናል። ስለሆነም የሰው ልጅ የአላህ ፍጡር እስከሆነ ድረስ ለአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ መመሪያዎች እጅ መስጠቱ የግድ ነው፡፡ አላህ ሁሉንም ነገር በተገቢው መልኩ ያደላደለ ጥበበኛና እውቀቱም ሁሉን ነገር የሚያካብብ የሆነ ጌታ ነው፡፡ የሰው ልጅ የሚፈፅመው የአምልኮ ተግባራት ዋናው ፅንሠ ሀሣብ ለአላህ እጅ መስጠት ነው፡፡ የህይወት መርህም ትርጉሟ የሰው ልጅ ለአላህ መታዘዙ ነው፡፡ አላህ ስለዚህች ህይወትም ሆነ ስለ ሰው ልጅ ጠንቅቆ አዋቂ ነውና።

ለሁሉም ህዝብ ነብይ ተልኳል

የሰው ልጅ መስተካከልና ስኬትን የሚያገኘው ለአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የታዘዘ እንደሆነ ነው፡፡ በመሆኑም አላህ መልእክተኛውን ሣይልክበት የተወው አንድም ህዝብ /ማህበረሰብ/ የለም። ይህንንም በቁርኣኑ ውስጥ በተለያዩ አንቀፆች ላይ ተናግሮታል

وَإِن مِّنْ أُمَّةٍ إِلَّا خَلَا فِيهَا نَذِيرٌ

“በርግጥ ማንኛይቱም ህዝብ አስጠንቃቂ ያላለፈባት የለችም” (ፋጢር 24፤ 35)

በሌላ የቁርኣን አንቀፅ

وَلَقَدْ بَعَثْنَا فِي كُلِّ أُمَّةٍ رَّسُولًا أَنِ اعْبُدُوا اللَّهَ وَاجْتَنِبُوا الطَّاغُوتَ

“በያንዳንዱ ህዝብ ውስጥ አላህን ተገዙ ጣኦታትንም እራቁ በማለት መልእክተኛ ልከናል፡፡” (አን-ነህል 16፤ 36) ብሏል፡፡

በሌላም የቁርኣን አንቀፅ

وَمَا أَرْسَلْنَا مِن رَّسُولٍ إِلَّا بِلِسَانِ قَوْمِهِ لِيُبَيِّنَ لَهُمْ

“ከመልእክተኛ አንድንም አልላክንም ይገልፅላቸው ዘንድ በህዝቦቹ ቋንቋ ቢሆን እንጂ፡፡” (ኢብራሂም 14፤ 4) ብሏል፡፡

እነኚህ ሁሉ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የሰው ልጆች ይስተካከሉ ዘንድ ወደያንዳንዱ ህዝብ መልእክተኛ የላከ መሆኑን የገለፀበት አንቀፆች ሲሆኑ በሀዲስም የአላህ መልእክተኛም ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም

“እናንተ ከህዝቦች ሰባኞቹ ስትሆኑ በአላህ ዘንድም በላጮችና የተከበራችሁ ናችሁ፡፡” (ቲርሚዚ) ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ ከላይ የተገለፀው ሁሉ “የአላህ መልእክተኞች ወደተወሠኑ ህዝቦችና ቦታዎች ብቻ ነው የተላኩት” የሚለው አስተሣሣብ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ነው። እውነታው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ መልእክተኛ ከአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ተልኳል ማለት የምንችለው ትክክለኛ የወህይ መልእክት ሲደርሰው እንደሆነ ብቻ መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል።

ለምሣሌ ፋርሦች (ኢራኖች) ዘራድሽ የሚባል ነቢይ እንደነበራቸው ይናገራሉ፡፡ እኛ ከቁርኣን አንቀፆች ባገኘናቸው መረጃዎች በመነሣት ወደ ፋርሦች የአላህ መልእክተኛ ስለመላኩ እናምናለን፡፡ ከኢብኑ ዐባስ ረዲየሏሁ ዐንሁ ደግሞ እንዲህ የሚል ዘገባ ተላልፏል፡፡ “ፋርሦች ነቢያቸው በሞተ ጊዜ እሣት አምላኪዎች ሆኑ፡፡” ነገር ግን ይህ የሞተው ነቢይ ዘራድሽ ነው ብለን ቁርጥ ባለ መልኩ መወሰኑ ያስቸግራል። በተመሣሣይ መልኩ አንዳንድ ህዝቦች ቁርኣን ያልገለፀልንን ስለ ነቢያቸው የሚሉት አላቸው። ይህን ሁሉ ማረጋገጥም ሆነ ማስተባበል የምንችለው ትክክለኛ መረጃ ሲኖረን ብቻ ነው፡፡

3 COMMENTS

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here