የኢስላም ልዩ ባህሪያት (ክፍል 3) – ሁለንተናዊነት (አሽ-ሽሙል)

0
2044

የኢስላም ሁለንተናዊነት (comprehensiveness) በተለያዩ ነገሮች ሊገለጽ ይችላል፤ ከነዚህም ውስጥ፡-

1. እሰከ አለም ፍጻሜ ያሉ የሰው ዘርን ሁሉ የሚያጠቃልል መሆኑ

ይህ ማለት ነቢያችን (ሶ.ዐ.ወ) የተላኩትና ኢስላምን ያስተማሩት እስከ ዱንያ አለም ማብቂያ (ቂያማ ) ድረስ ላሉት ሰዎች ሁሉ ነው ማለት ነው። ኢስላም ለአለም ህዝብ በጠቅላላው የመጣ መልክት ነው፤ ለአረብ ወይም ለተወሰነ ህዝብ ብቻ የተላከ አይደለም። አይሁዳዎች ራሳቸውን ምርጥ ህዝብ ነን ብለው እነደሚሞግቱት በኢስላም ዘሩ ወይም ከለሩ ምንም ይሁን በአላህ ዘንድ የተመረጠ ልዩ ህዝብ የሚባል ነገር የለም። ይህን እውነት አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ በማለት ያረጋግጠዋል፡-

قُلْ يَا أَيُّهَا النَّاسُ إِنِّي رَسُولُ اللَّهِ إِلَيْكُمْ جَمِيعًا الَّذِي لَهُ مُلْكُ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ لَا إِلَٰهَ إِلَّا هُوَ يُحْيِي وَيُمِيتُ فَآمِنُوا بِاللَّهِ وَرَسُولِهِ النَّبِيِّ الْأُمِّيِّ الَّذِي يُؤْمِنُ بِاللَّهِ وَكَلِمَاتِهِ وَاتَّبِعُوهُ لَعَلَّكُمْ تَهْتَدُونَ

“(ሙሐመድ ሆይ!) በላቸው፡- ‘እናንተ ሰዎች ሆይ! እኔ ወደናንተ ወደሁላችሁም የአላህ መልክተኛ ነኝ። (እርሱም) ያ የሰማያትና የምድር ንግሥና ለእርሱ ብቻ የኾነ ነው። እርሱ እንጂ ሌላ አምላክ የለም። ሕያው ያደርጋል። ይገድላልም። በአላህ በዚያም በአላህና በቃላቶቹ በሚያምነው የማይጽፍ የማያነብ ነቢይ በኾነው መልክተኛው እመኑ። ቅንንም መንገድ ትመሩ ዘንድ ተከተሉት’።” (አል-አዕራፍ 7፤158)

በሌላም አንቀጽ እንዲህ ይላል፡-

وَمَا أَرْسَلْنَاكَ إِلَّا كَافَّةً لِّلنَّاسِ بَشِيرًا وَنَذِيرًا وَلَٰكِنَّ أَكْثَرَ النَّاسِ لَا يَعْلَمُونَ

“አንተንም ለሰዎች ሁሉ በመላ አብሳሪና አስፈራሪ አድርገን ቢሆን እንጂ አላክንህም። ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም።” (ሰበእ34 ፤28)

تَبَارَكَ الَّذِي نَزَّلَ الْفُرْقَانَ عَلَىٰ عَبْدِهِ لِيَكُونَ لِلْعَالَمِينَ نَذِيرًا

“ያ ፉርቃንን በባሪያው ላይ ለዓለማት አስፈራሪ ይኾን ዘንድ ያወረደው (አምላክ) ክብርና ጥራት ተገባው።” (አል-ፉርቃን 25፤1)

2. ኢስላም ሁሉንም የህይወት እርከኖች መዳሰሱ

ኢስላም የሰው ልጅ በእናቱ ሆድ ፅንስ እያለ ጀምሮ የሚያልፍባቸውን ሁሉንም የህይወት ደረጃዎቸ ያካተተና የሚመራ ሥርዓት አስቀምጧል። የሰው ልጅ በህጻንነት እያለ የናቱን ጡት የመጥባት፣ አሳዳጊና ተንካባካቢ የማግኘት መብቱን አስጠብቋል። በመቀጠልም የሰው ልጅ ለአካለ መጠን ደርሶ ትዳር ሲይዝ፤ አባት ወይም እናት ሲሆንና እንዲሁም በእርጅና እድሜ ላይ ሲደርስ በሁሉም ከልደት በፊትና ከልደት በኋላ አስከ ሞትና ከዚያም በኋላ ያለውን ሁሉንም የህይዎቱ ጉዞዎች የሚዳስሰ መመሪያ አስቀምጧል።

3. ኢስላማዊ ህግ ሁሉንም የህይዎት ዘርፎች ያጠቃልላል

ኢስላም ለሁሉም የህይዎት ዘርፎች መመሪያና ሥርዓት አድርጓል። የሰው ልጅ ከራሱ ጀምሮ ከሌሎች ጋር የሚኖረውን ግንኙነት፣ በቤቱ ውስጥ ከቤተሰቦቹ ጋር ሲሆን፣ በስራ ቦታ ላይ ሲሆንና በጠቅላላው በማንኛውም እንቅስቃሴና ሁኔታ ላይ ሲሆን የሚያስፈልገውን የህይዎት መመሪያ ኢስላም አስቀምጧል።

ኢስላም በግል፣ በቤተሰብና በማህበረሰብ ህይወታችን፤ በኢኮኖሚና በፓለቲካ፤ በባህልና በሳይንስ ወ.ዘ.ተ ባጠቃላይ በመንፈሳዊና በቁሳዊ ህይወት ልንከተለው የሚገባ የህይወት መንገድ ዘርግቷል።

ከዚህም አልፎ ይህን የህይዎት መመሪያና ህግ ለአላህ ብሎ በጥሩ ኒያ (ውስጣዊ መነሳሳት) ለሚፈጽም ሰው አምልኮ እንደፈጸመ ተቆጥሮለት በአላህ ዘንድ ምንዳ እንደሚያስገኝ ኢስላም ያስተምራል።

ኢስላም የተሟላና ሊከፋፈል የማይችል አንድ ሐይማኖት (ሥርዓት) ሲሆን ከፊሉን ወስዶ ከፊሉን መተው ፈጽም የማይቻል ጉዳይ ነው። አላህ (ሱ.ወ) እነድህ ይላል፡-

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا ادْخُلُوا فِي السِّلْمِ كَافَّةً وَلَا تَتَّبِعُوا خُطُوَاتِ الشَّيْطَانِ إِنَّهُ لَكُمْ عَدُوٌّ مُّبِينٌ

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ሁላችሁም በመታዘዝ (ኢስላም) ውስጥ (ሙሉ በሙሉ) ግቡ። የሰይጣንንም እርምጃዎች አትከተሉ፤ እርሱ ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነውና።” (አል-በቀራ 2፤208)

አይሁዶች የተወሰኑ ነብያትን ተቀብለው ሌሎችን ባለመቀበላቸውና በመካዳቸው አላህ (ሱ.ወ) እንድህ ሲል አውግዟቸዋል፡-

إِنَّ الَّذِينَ يَكْفُرُونَ بِاللَّهِ وَرُسُلِهِ وَيُرِيدُونَ أَن يُفَرِّقُوا بَيْنَ اللَّهِ وَرُسُلِهِ وَيَقُولُونَ نُؤْمِنُ بِبَعْضٍ وَنَكْفُرُ بِبَعْضٍ وَيُرِيدُونَ أَن يَتَّخِذُوا بَيْنَ ذَٰلِكَ سَبِيلًا أُولَٰئِكَ هُمُ الْكَافِرُونَ حَقًّا وَأَعْتَدْنَا لِلْكَافِرِينَ عَذَابًا مُّهِينًا

“እነዚያ በአላህና በመልክተኞቹ የሚክዱ፣ በአላህና በመልክተኞቹም መካከል መለየትን የሚፈልጉ፣ ‘በከፊሉም እናምናለን በከፊሉም እንክዳለን’ የሚሉ፣ በዚህም መካከል መንገድን ሊይዙ የሚፈልጉ፤ እነዚያ በውነት ከሓዲዎቹ እነርሱ ናቸው። ለከሓዲዎችም አዋራጅን ቅጣት አዘጋጅተናል።” (አን-ኒሳእ ፤150–151)።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here